ልዩ ማስታወቂያ
ልዩ ማስታወቂያ
የፔንስልቬኒያው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ጥቅምት 7, 2000 ያደረገው ዓመታዊ ስብሰባ ሲጠናቀቅ የአስተዳደር አካል አባል የሆነው የስብሰባው ሊቀ መንበር ጆን ኢ ባር አንድ ልዩ ማስታወቂያ ተናገረ። ይህ ማስታወቂያ ቴዎዶር ጃራዝና ዳንኤል ሲድሊክ የዚያን ዕለት ቀደም ብለው ባቀረቡት ንግግር ላይ የተመሠረተ ነው።—የዚህን መጽሔት ገጽ 12-16 እና 28-31 ተመልከት።
ወንድም ባር እንደሚከተለው በማለት በጣም ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነጥብ ተናግሯል:- “ታማኝና ልባም ባሪያና የአስተዳደር አካሉ ከሕጋዊ ማኅበራቱ የሚበልጥ ተደራራቢ አደራ ተሰጥቶታል። እነዚህ ሕጋዊ ማኅበራት የሚያገለግሉት በቻርተራቸው ላይ ለሰፈረው ዓላማ ብቻ ነው። ሆኖም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የታማኝና ልባም ባሪያን ክፍል ‘ባለው ሁሉ’ ላይ ወይም እዚህ ምድር ባለው የመንግሥቱ ፍላጎት ሁሉ ላይ ሾሞታል።”—ማቴዎስ 24:45-47
ወንድም ባር የፔንስልቬኒያውን ማኅበር በተመለከተ የሚከተለውን አክሎ ተናገረ:- “የፔንስልቬኒያው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ከተመሠረተበት ከ1884 ጀምሮ በዘመናዊ ታሪካችን ውስጥ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። ሆኖም ‘ታማኝና ልባም ባሪያ’ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሊጠቀምበት የሚችል ሕጋዊ መሣሪያ ብቻ ነው።”
“ታማኝና ልባም ባሪያ” የጌታን ምድራዊ ንብረት በሙሉ በአደራ መረከቡ የባሪያው ክፍል አንዳንድ አስተዳደራዊ ኃላፊነቶችን ‘ከሌሎች በጎች’ መካከል ለሆኑ ብቃት ላላቸው ወንዶች ከመስጠት አያግደውም። (ዮሐንስ 10:16) ወይም ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠቀሙባቸው ሕጋዊ አካላት ዲሬክተሮች በሙሉ ወይም አንዳንዶቹ ቅቡዓን ክርስቲያኖች መሆን አለባቸው የሚል ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት የለም።
ወንድም ባር ዲሬክተሮችና ኃላፊዎች ሆነው ያገለግሉ የነበሩ የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባላት በዩናይትድ ስቴትስ ከሚገኘው “ታማኝና ልባም ባሪያ” ከሚጠቀምባቸው የዲሬክተሮች ቦርድ በጠቅላላ በቅርቡ በፈቃደኝነት መልቀቃቸውን ለአድማጮች አሳወቀ። በእነሱ ምትክ ‘ከሌሎች በጎች’ ክፍል የሆኑ ኃላፊነት የሚጣልባቸው ወንድሞች ተመርጠዋል።
ይህ ውሳኔ በእርግጥም ጠቃሚ ነው። የአስተዳደር አካል አባላት ይበልጥ ጊዜያቸውን መንፈሳዊ ምግብ ለማዘጋጀትና የዓለም አቀፉን የወንድማማች ማኅበር መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት እንዲያውሉት ይረዳል።
በመጨረሻም ሊቀ መንበሩ በጣም ለተደሰቱት አድማጮቹ እንደሚከተለው ሲል ተናገረ:- “የተለያዩ ሕግ ነክና የአስተዳደር ሥራዎች ተሞክሮ ላላቸው የበላይ ተመልካቾች ቢሰጡም . . . ሁሉም የሚያገለግሉት የአስተዳደር አካል በሚሰጣቸው መንፈሳዊ መመሪያ ሥር ሆነው ነው። . . . ለታላቅ ስሙ ክብርና ምስጋና ፈቃዱን ለመፈጸም የምናደርገውን የተባበረ ጥረት እንዲባርክ ሁላችንም ጸሎታችንን ለይሖዋ እናቀርባለን።”