በጎነትን ማዳበር የምንችልበት መንገድ
በጎነትን ማዳበር የምንችልበት መንገድ
ዘመናዊ መዝገበ ቃላት “በጎነት” የሚለውን ቃል “ጥሩ ሥነ ምግባር፣ ጥሩነት” የሚል ፍቺ ይሰጡታል። “ትክክለኛ ድርጊትና አስተሳሰብ እንዲሁም መልካም ባሕርይ” ነው። የመዝገበ ቃላት አዘጋጅ የሆኑት ማርቪን አር ቪንሰንት “በጎነት” ተብሎ የተተረጎመው ጥንታዊው የግሪክኛ ቃል “የማንኛውንም ነገር የላቀ ደረጃ” እንደሚያመለክት ገልጸዋል። እንግዲያው እንደ ማስተዋል፣ ድፍረት፣ ራስን በራስ መገሰጽ፣ አለማድላት፣ ርኅራኄ፣ ጸንቶ መቆም፣ ሐቀኝነት፣ ትሕትናና ታማኝነት የመሳሰሉት ባሕርያት በሆነ ወቅት ላይ እንደ በጎነት ተቆጥረው መወደሳቸው ምንም አያስደንቅም። በተጨማሪም በጎነት “ከትክክለኛነት መስፈርት ጋር መስማማት” ተብሎም ተተርጉሟል።
መስማማት ያለብን ማን ካወጣው የጥሩነት፣ የመልካምነትና የትክክለኛነት መመዘኛ ጋር ነው? “የሥነ ምግባር ፍልስፍና ዋነኛ ትምህርት እንደሚለው ከሆነ” ይላል ኒውስዊክ መጽሔት፣ “በ18ኛው መቶ ዘመን የነበረው የፍልስፍና ንቅናቄ የፈጠረው የጥርጣሬ መንፈስ ትክክልና ስህተት የሆነው ነገር የሚወሰነው በግል ስሜት፣ ምርጫ ወይም ፍላጎት ነው የሚል አስተሳሰብ እንዲዳብር አድርጓል።” ይሁን እንጂ የግል ስሜት ወይም ምርጫ በራሱ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር ለመለየት የሚያስችል ጥሩ መንገድ ነውን? አይደለም። በጎነትን ማዳበር እንድንችል መልካምና ክፉ የሆነውን መለየት የምንችልበት አስተማማኝ የሆነ መስፈርት ያስፈልገናል። አንድን ድርጊት፣ አመለካከት ወይም ባሕርይ ትክክል ወይም ስህተት ብለን መፈረጅ የምንችልበት መስፈርት ያስፈልገናል።
ብቸኛው እውነተኛ የሥነ ምግባር መስፈርቶች ምንጭ
እውነተኛው የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ምንጭ የሰው ልጆች ፈጣሪ የሆነው ይሖዋ አምላክ ብቻ ነው። ይሖዋ አምላክ የመጀመሪያውን ሰው አዳምን ከፈጠረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ እንዲህ ብሎ አዘዘው:- “ከገነት ዛፍ ሁሉ ትበላለህ፤ ነገር ግን መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህና።” (ዘፍጥረት 2:16, 17) ይሖዋ አምላክ መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር ለፍጥረታቱ የመወሰን ሥልጣን ያለው እሱ ብቻ መሆኑን ለማመልከት ሲል ለዛፉ ለየት ያለ ስያሜ ሰጥቶታል። በመሆኑም አምላክ መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር በተመለከተ ያወጣው መስፈርት የሰውን ድርጊት፣ አመለካከትና ባሕርይ ለመመዘንና ፍርድ ለመስጠት የሚያገለግል መሠረት ሆኗል። እነዚህ መስፈርቶች ባይኖሩ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት አንችልም ነበር።
መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀውን ዛፍ በተመለከተ የተሰጠው ትእዛዝ በአዳምና በሔዋን ፊት የመታዘዝና ያለመታዘዝ ምርጫ አስቀምጦ ነበር። ለእነሱ በጎነት ማለት ይህን ትእዛዝ ማክበር ማለት ነበር። ከጊዜ በኋላ ይሖዋ ደስ ስለሚያሰኙትና ደስ ስለማያሰኙት ነገሮች ተጨማሪ መግለጫ የሰጠ ከመሆኑም በላይ ይህም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦ እንዲቆየን አድርጓል። እንግዲያው በጎነትን ማዳበር በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከተገለጹት የይሖዋ የጽድቅ መስፈርቶች ጋር ተስማምቶ መኖር ይጠይቃል።
አምላክ ያወጣቸውን መስፈርቶች ጠንቅቀህ እወቅ
ይሖዋ አምላክ መልካምና ክፉን መለየት የሚቻልባቸውን መስፈርቶች ያወጣና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲገለጹ ያደረገ በመሆኑ እነዚህን መስፈርቶች ጠንቅቀን ማወቅ አይኖርብንም? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል።”—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
ለምሳሌ ያህል ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ኩኒሂቶ ባደገበት ባሕል እንደ ልከኝነት የሚቆጠረውን ባሕርይ ባንጸባረቀ ጊዜ ከአለቃው ጋር የተፈጠረውን የሐሳብ አለመግባባት ተመልከት። ከጊዜ በኋላ ቅዱስ ጽሑፋዊ መስፈርቶችን ጠለቅ ብሎ መመርመሩ ይበልጥ ሚዛናዊ የሆነ አቋም እንዲይዝ ረዳው። መጽሐፍ ቅዱስ የልከኝነት ባሕርይን እንድናዳብር የሚያበረታታ ሲሆን በአንጻሩ ከልክ በላይ በራስ ከመተማመን መንፈስና ከትዕቢት እንድንርቅ አጥብቆ ይመክረናል። (ምሳሌ 11:2፤ ሚክያስ 6:8 NW ) ሆኖም ሐዋርያው ጳውሎስ “የበላይ ተመልካችነት” ብቃቶችን በዘረዘረ ጊዜ ለዚህ መብት ስለ ‘መጣጣር’ ተናግሯል። (1 ጢሞቴዎስ 3:1 NW ) አንድ ሰው ለዚህ መብት ‘በሚጣጣርበት’ ጊዜ ከኩራት ወይም ከትዕቢት መንፈስ መራቅ ብቻ ሳይሆን ሳያስፈልግ ራሱን ከልክ በላይ ዝቅ ማድረግም የለበትም።
መጽሐፍ ቅዱስ በንግድ መስክ የላቀ ሥነ ምግባር ማሳየትን በተመለከተ ምን ይላል? በዛሬው ጊዜ ባለው የንግድ ዓለም ውስጥ አጠያያቂ የሆኑ መንገዶችን መጠቀም ወይም ከመንግሥት ደንቦችና የቀረጥ ሕጎች ለማምለጥ የተለያዩ ማምለጫ ቀዳዳዎችን መፈለግ የተለመደ ነገር ሆኗል። ይሁን እንጂ ሌሎች ምንም አደረጉ ምን የመጽሐፍ ቅዱስ መስፈርት ‘በሁሉም ነገር ሐቀኞች እንድንሆን’ ይጠይቅብናል። (ዕብራውያን 13:18 NW ) በመሆኑም ከአሠሪዎች፣ ከሠራተኞች፣ ከደንበኞችና ከዓለማዊ መንግሥታት ጋር በሚኖረን ግንኙነት ረገድ ሐቀኞች በመሆንና ከአድልዎ በመራቅ በጎነትን እናዳብራለን። (ዘዳግም 25:13-16፤ ሮሜ 13:1፤ ቲቶ 2:9, 10) ሐቀኝነት የመተማመን መንፈስ እንዲሰፍን የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ ጥሩ ስም ያተርፋል። በተጨማሪም ውሎችን በጽሑፍ ማስፈር ብዙውን ጊዜ “ያልታሰበ አጋጣሚ [NW ]” በሚያስከትላቸው ሁኔታዎች ሳቢያ አለመግባባቶችና ውስብስብ ችግሮች እንዳይፈጠሩ ለመከላከል ይረዳል።—መክብብ 9:11፤ ያዕቆብ 4:13, 14
በጎነትን ልናዳብርበት የሚገባው ሌላው መስክ ደግሞ አለባበስና አጋጌጥ ነው። የአለባበስ ምርጫዎች ከባሕል ወደ ባሕል የሚለያዩ ሲሆን በየጊዜው ከሚለዋወጡት አዳዲስ የአለባበስ ዓይነቶችና ፋሽኖች እኩል እንድንራመድ የሚገፋፋ ከባድ ተጽዕኖም ሊደርስብን ይችላል። ይሁን እንጂ ዘመን ያመጣውን የአለባበስ ዓይነትና ፋሽን ሁሉ የምንከተልበት ምን ምክንያት አለ? መጽሐፍ ቅዱስ “ይህን ዓለም አትምሰሉ” ሲል አጥብቆ ይመክረናል። (ሮሜ 12:2) ሐዋርያው ጳውሎስ ደንብ ከማውጣት ይልቅ በመንፈስ አነሳሽነት ተገፋፍቶ የሚከተለውን ጽፏል:- “ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፤ እግዚአብሔርን እንፈራለን ለሚሉት ሴቶች እንደሚገባ . . . እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቊ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ።” (1 ጢሞቴዎስ 2:9, 10) ይህ መሠረታዊ መስፈርት ለወንዶችም ሆነ ለሴቶች ይሠራል። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን በባሕል ወይም በግል ምርጫ ላይ የተመሠረቱ የተለያዩ አስደሳች የአለባበስ ዓይነቶችን የመከተል ነፃነት አለ።
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በቀጥታ የሚያወግዛቸውን ሥነ ምግባር የጎደላቸው ድርጊቶች ይዘረዝራል። በ1 ቆሮንቶስ 6:9, 10 ላይ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ እናነባለን:- “ወይስ ዓመፀኞች የእግዚአብሔርን መንግሥት እንዳይወርሱ አታውቁምን? አትሳቱ፤ ሴሰኞች ቢሆኑ ወይም ጣዖትን የሚያመልኩ ወይም አመንዝሮች ወይም ቀላጮች ወይም ከወንድ ጋር ዝሙት የሚሠሩ ወይም ሌቦች ወይም ገንዘብን የሚመኙ ወይም ሰካሮች ወይም ተሳዳቢዎች ወይም ነጣቂዎች የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።” ይህ ጥቅስ ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ማሪያ ፈጣሪ ካወጣው የላቀ የሥነ ምግባር መስፈርት አንጻር ሲታይ ከሁዋን ጋር የነበራት ግንኙነት ስህተት እንደሆነና የአምላክን ሞገስ ማግኘት ከፈለገች ይህን ግንኙነት ማቋረጥ እንዳለባት እንድትገነዘብ ረድቷታል። በጎነትን ለማዳበር የአምላክን መስፈርቶች ጠንቅቀን ማወቅ እንዳለብን ምንም አያጠያይቅም።
በልብ ውስጥ ሊኮተኮት የሚገባው ባሕርይ
በጎነት መጥፎ የሆነውን ነገር በማስወገድ ብቻ የሚወሰን አይደለም። ትክክለኛ የሆነውን ነገር እንድናደርግ የሚገፋፋ ኃይል አለው። በጎ ምግባር ያለው ሰው መልካም ነገርም ያደርጋል። “በጎነት” ይላሉ አንድ ፕሮፌሰር፣ “በልብና በአእምሮ ውስጥ ሊዳብር የሚገባው ባሕርይ ነው።” እንግዲያው በጎነትን ለማዳበር ከአምላክ ቃል ጋር በሚገባ መተዋወቅ ብቻውን በቂ አይደለም። ልባችን ለይሖዋ ባለን የአመስጋኝነት ስሜት እንዲሞላና ቅዱስ ጽሑፋዊ የሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ እንድንችል በቃሉ ውስጥ በሰፈረው ሐሳብ ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል።
መዝሙራዊው “ሕግህን እጅግ እወዳለሁ፤ ስለ እርሱ ቀኑን ሙሉ አስባለሁ” ሲል በጥልቅ ስሜት ተውጦ ተናግሯል። (መዝሙር 119:97 የ1980 ትርጉም ) በተጨማሪም ንጉሥ ዳዊት “የቀድሞውን ዘመን አሰብሁ፣ ሥራህንም [የአምላክን] ሁሉ አሰላሰልሁ፤ የእጅህንም ሥራ ተመለከትሁ” ሲል ጽፏል። (መዝሙር 143:5) እኛም መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በምናጠናበት ጊዜ በጸሎት የማሰላሰልን አስፈላጊነት ከፍ አድርገን ልንመለከተው ይገባል።
እርግጥ ነው፣ ማሰላሰል የታከለበት ጥልቅ ጥናት ለማድረግ የሚያስችል ጊዜ መመደቡ ፈታኝ ሊሆን ይችላል። ሆኖም በጎነትን ለማዳበር የምናደርገው ጥረት ከሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ ጊዜ እንድንዋጅ ይጠይቅብናል። (ኤፌሶን 5:15, 16) የ24 ዓመቱ ኤረን በየዕለቱ ጠዋት ጠዋት ይነሳበት ከነበረው ጊዜ 30 ደቂቃ ያህል ቀደም ብሎ በመነሳት ለእንዲህ ዓይነቱ ዓላማ የሚውል ጊዜ ይዋጃል። እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “መጀመሪያ ላይ ሠላሳውንም ደቂቃ የማሳልፈው መጽሐፍ ቅዱስ በማንበብ ነበር። ማሰላሰል ያለውን ጥቅም የተገነዘብኩት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ነው። በመሆኑም አሁን ከዚህ ጊዜ ላይ ግማሽ ያህሉን ባነበብኩት ነገር ላይ በማሰላሰል አሳልፋለሁ። ይህም በእጅጉ ጠቅሞኛል።” በሌሎች ጊዜያትም ቢሆን ማሰላሰል ይቻላል። ዳዊት ለይሖዋ ባቀረበው ጣዕመ ዜማ ላይ “ሌሊቱንም ሁሉ የአንተን ነገር አስባለሁ” ሲል ዘምሯል። (መዝሙር 63:6 የ1980 ትርጉም ) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ “ይስሐቅም በመሸ ጊዜ በልቡ እያሰላሰለ ወደ ሜዳ ወጥቶ ነበር” ሲል ይገልጻል።—ዘፍጥረት 24:63
ማሰላሰል ይሖዋ የሚሰማው ዓይነት ስሜት እንዲሰማንና እሱ ያለው ዓይነት አመለካከት እንዲኖረን ስለሚረዳን በጎነትን ለማዳበር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ቀላል አይደለም። ለምሳሌ ያህል ማሪያ አምላክ ዝሙትን እንደሚከለክል ታውቅ ነበር። ሆኖም ‘ክፉ ነገርን ለመጸየፍና ከበጎ ነገር ጋር ለመተባበር’ ቁልፍ በሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ማሰላሰል ነበረባት። (ሮሜ 12:9) ‘እንደ ዝሙት፣ ርኩሰት፣ ፍትወት፣ ክፉ ምኞትና መጎምጀት ያሉትን ብልቶቻችንን እንድንገድል’ አጥብቆ የሚያሳስበንን ቆላስይስ 3:5ን በማንበብ ለውጥ የማድረግን አስፈላጊነት እንድታስተውል እርዳታ ተደረገላት። ማሪያ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራሷን መጠየቅ አስፈልጓት ነበር:- ‘ልገድለው የሚገባኝ የጾታ ፍትወት ምን ዓይነት ነው? ርኩስ ምኞቶችን ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ምን ነገሮችን ማስወገድ አለብኝ? ከተቃራኒ ጾታ ጋር ባለኝ ግንኙነት ረገድ ላደርጋቸው የሚገቡ ለውጦች ይኖራሉ?’
ማሰላሰል አንድ ድርጊት የሚያስከትለውን ውጤትም ቆም ብሎ ማሰብን ይጨምራል። ጳውሎስ ‘ማንም እንዳይተላለፍና ወንድሙን እንዳያታልል’ ከዝሙት መራቅና ራስን መግዛት እንደሚያስፈልግ ክርስቲያኖችን አጥብቆ መክሯል። (1 ተሰሎንቄ 4:3-7) በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰሉ ጠቃሚ ነው:- ‘ይህን ድርጊት መፈጸሜ በራሴ፣ በቤተሰቤና በሌሎች ላይ የሚያስከትለው ጉዳት ምንድን ነው? በመንፈሳዊነቴ፣ በስሜቴና በአካሌ ላይ ምን ሊያስከትል ይችላል? በቀደሙት ዘመናት የአምላክን ሕግ የጣሱ ሰዎች ምን ደርሶባቸዋል?’ ማሪያ በዚህ መንገድ ማሰላሰሏ ጽኑ ልብ እንዲኖራት የረዳት ሲሆን እኛንም በተመሳሳይ ሊረዳን ይችላል።
ከምሳሌዎች ተማር
በጎነትን በክፍል ውስጥ መማር ይቻላል? ይህ ፈላስፎችን ለብዙ ሺህ ዓመታት ግራ ሲያጋባ የኖረ ጥያቄ ነው። ግሪካዊው ፈላስፋ ፕላቶ ይቻላል ወደሚል አስተሳሰብ አዘንብሎ ነበር። አርስቶትል ደግሞ በአንጻሩ በጎነት በልምድ የሚገኝ ነገር ነው የሚል ሐሳብ ሰጥቷል። አንድ ጋዜጠኛ በጉዳዩ ላይ የተነሳውን ክርክር እንዲህ በማለት ጠቅለል አድርገው ገልጸውታል:- “በአጭሩ የበጎነትን ሥነ ምግባር ለብቻ መማር አይቻልም። በመማሪያ መጻሕፍትም ልንማረው የምንችለው ነገር አይደለም። መልካም ምግባርን መማር የሚቻለው . . . በጎነት ከፍ ተደርጎ በሚታይባቸውና ወሮታ በሚያስገኝባቸው ማኅበረሰቦች ውስጥ በመኖር ነው።” ይሁን እንጂ በእርግጥ በጎ ምግባር ያላቸውን ግለሰቦች የት ልናገኝ እንችላለን? አብዛኞቹ ኅብረተሰቦች ቢያንስ ቢያንስ በአፈ ታሪኮቻቸው ውስጥ በበጎነታቸው የሚታወቁ አንዳንድ ምሳሌዎችን የሚጠቅሱ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ በርካታ እውነተኛ ምሳሌዎች ይዟል።
ከሁሉ የላቀው የበጎነት ምሳሌ ይሖዋ ነው። የሚያደርገው ነገር ሁሉ በጎነት የሚንጸባረቅበት ከመሆኑም በላይ ጽድቅና መልካም የሆነውን ነገር ያደርጋል። እኛም ‘አምላክን በመምሰል’ በጎነትን ማዳበር እንችላለን። (ኤፌሶን 5:1) የአምላክ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስም ‘ፍለጋውን እንድንከተል ምሳሌ ትቶልናል።’ (1 ጴጥሮስ 2:21) ከዚህም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ እንደ አብርሃም፣ ሣራ፣ ዮሴፍ፣ ሩት፣ ኢዮብ እንዲሁም ዳንኤልና ሦስቱ ዕብራውያን ጓደኞቹ ያሉ የበርካታ ታማኝ ግለሰቦችን ታሪክ ይዟል። በዛሬው ጊዜ ባሉት የይሖዋ አገልጋዮች መካከል የሚገኙት የበጎነት ምሳሌዎችም ሳይጠቀሱ አይታለፉም።
ሊሳካልን ይችላል
በአምላክ ፊት በጎ የሆነውን ነገር በማድረግ ረገድ በእርግጥ ሊሳካልን ይችላል? አለፍጽምና የወረስን በመሆናችን አልፎ አልፎ በውስጣችን በአእምሯችንና በሥጋችን መካከል ማለትም በጎ የሆነውን ነገር ለማድረግ ባለን ፍላጎትና በኃጢአት ዝንባሌዎቻችን መካከል ከባድ ውጊያ ሊኖር ይችላል። (ሮሜ 5:12፤ 7:13-23) ሆኖም በአምላክ እርዳታ ውጊያውን በድል አድራጊነት ልንወጣ እንችላለን። (ሮሜ 7:24, 25) ይሖዋ ቃሉንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን ሰጥቶናል። ቅዱሳን ጽሑፎችን በትጋት በማጥናትና በእነዚህ ጽሑፎች ላይ በጸሎት በማሰላሰል ልባችን ንጹሕ እንዲሆን ማድረግ እንችላለን። ከእንዲህ ዓይነቱ ንጹሕ ልብ በጎ ሐሳብ፣ ቃልና ድርጊት ሊወጣ ይችላል። (ሉቃስ 6:45) የይሖዋ አምላክንና የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ መሠረት በማድረግ አምላካዊ ባሕርይ ልንገነባ እንችላለን። በተጨማሪም በዛሬው ጊዜ አምላክን በታማኝነት እያገለገሉ ካሉ ግለሰቦች ብዙ መማር እንችላለን።
ሐዋርያው ጳውሎስ አንባቢዎቹ በጎነትንና ሌሎች ምስጋና የሚገባቸውን ነገሮች ‘ማሰባቸውን እንዲቀጥሉ’ አጥብቆ አሳስቧል። ይህን ማድረግ የአምላክን በረከት እንደሚያስገኝ የተረጋገጠ ነው። (ፊልጵስዩስ 4:8, 9) በጎነትን ለማዳበር የምናደርገው ጥረት በይሖዋ እርዳታ ሊሰምርልን ይችላል።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ማሰላሰል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ አንዱ አካል ይሁን
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቶስ ኢየሱስን በመምሰል አምላካዊ ባሕርይ አዳብር