በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል ተራመዱ

ከይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል ተራመዱ

ከይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል ተራመዱ

“የሰላም አምላክ . . . ፈቃዱን ታደርጉ ዘንድ በመልካም ሥራ ሁሉ ያስታጥቃችሁ።”​—⁠ዕብራውያን 13:​20, 21 NW

1. የዓለም ሕዝብ ብዛት ምን ያህል ነው? የአንዳንድ ሃይማኖቶች አባላትስ ምን ያህል ናቸው?

 በ1999 የዓለም ሕዝብ ብዛት ስድስት ቢልዮን ሞልቷል! ዘ ወርልድ አልማናክ እንደሚጠቁመው ከዚህ ውስጥ 1, 165,​000, 000 ሙስሊሞች፤ 1, 030,​000, 000 የሮማ ካቶሊኮች፤ 762, 000,​000 ሂንዱዎች፤ 354, 000, 000 ቡዲስቶች፤ 316, 000, 000 ፕሮቴስታንቶች፤ እንዲሁም 214, 000, 000 ኦርቶዶክሶች ናቸው።

2. ዛሬ ስላለው ሃይማኖታዊ ሁኔታ ምን ማለት ይቻላል?

2 ዛሬ ካለው ሃይማኖታዊ መከፋፈልና ግራ መጋባት አንጻር ሲታይ በሚልዮን የሚቆጠሩት እነዚህ ሁሉ ሰዎች ከአምላክ ፈቃድ ጋር በሚስማማ መንገድ የሚመላለሱ ናቸው ሊባል ይችላልን? የለም፣ አይቻልም። “እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለም።” (1 ቆሮንቶስ 14:​33) በሌላ በኩል ግን ስለ ይሖዋ አገልጋዮች ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር ምን ለማለት ይቻላል? (1 ጴጥሮስ 2:​17 NW ) ጉዳዩን በጥንቃቄ ስንመረምር ‘የሰላም አምላክ ፈቃዱን ያደርጉ ዘንድ በመልካም ሥራ እንደሚያስታጥቃቸው’ እንረዳለን።​—⁠ዕብራውያን 13:​20, 21

3. በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በኢየሩሳሌም ምን ነገር ተከናውኗል? ለምንስ?

3 እርግጥ የይሖዋ ምሥክሮች መለኮታዊ ሞገስ ማግኘት አለማግኘታቸው የሚለካው ከእነርሱ ጋር በሚተባበሩት ሰዎች ብዛት አይደለም፤ ይሖዋም ቢሆን የቁጥር ብዛት አይማርከውም። እስራኤላውያንን የመረጠው ‘ከአሕዛብ ሁሉ በቁጥር ስለ በዙ’ አልነበረም። ይሁን እንጂ ከአሕዛብ ሁሉ “በቁጥር ጥቂቶች” ነበሩ። (ዘዳግም 7:​7) እንዲያውም የእስራኤል ብሔር አምላክን በመክዳቱ ምክንያት ይሖዋ በ33 እዘአ ሞገሱን ከኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ወደተውጣጣው አዲስ ጉባኤ አዞረ። እነዚህ ደቀ መዛሙርት በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ተቀብተው ስለ አምላክና ስለ ክርስቶስ የሚገልጸውን እውነት ለሰዎች በቅንዓት ማወጅ ጀመሩ።​—⁠ሥራ 2:​41, 42

ሳያቋርጡ ወደፊት መግፋት

4. የጥንቱ ክርስቲያን ጉባኤ ያለማቋረጥ ወደፊት ይገሰግስ ነበር ብለን መናገር የምንችለው ለምንድን ነው?

4 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ አዳዲስ የአገልግሎት ክልሎችን በመክፈት፣ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት በማፍራትና ስለ አምላክ ፈቃድና ዓላማ ያለውን ግንዛቤ በማስፋት ያለማቋረጥ ወደፊት ይገሰግስ ነበር። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት ከተጻፉት መልእክቶች ከሚያገኘው መንፈሳዊ ብርሃን ጋር እኩል ይራመዱ ነበር። ሐዋርያትና ሌሎችም በሚያደርጉላቸው ጉብኝት በመበረታታት አገልግሎታቸውን ይፈጽሙ ነበር። ይህ ሁሉ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሚገባ ተመዝግቦ ይገኛል።​—⁠ሥራ 10:​21, 22፤ 13:​46, 47፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:​13፤ 4:​5፤ ዕብራውያን 6:​1-3፤ 2 ጴጥሮስ 3:​17, 18

5. ዛሬ የአምላክ ድርጅት እድገት እያደረገ ያለው በምን ምክንያት ነው? እኛስ ከዚህ ድርጅት ጋር እኩል መራመድ ያለብን ለምንድን ነው?

5 የዘመናችን የይሖዋ ምሥክሮችም እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች የተነሱት በጣም አነስተኛ ከሆነ ጅምር ነው። (ዘካርያስ 4:​8-10) ከ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ የይሖዋ መንፈስ ከድርጅቱ እንዳልተለየ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች አሉ። በሰው ኃይል ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ አመራር በመታመናችን በቅዱሳን ጽሑፎች ማስተዋልና የአምላክን ፈቃድ በማድረግ እያደግን መሄዳችንን ቀጥለናል። (ዘካርያስ 4:​6) ዛሬ “በመጨረሻው ቀን” ላይ የምንገኝ በመሆናችን ወደፊት በመገስገስ ላይ ከሚገኘው ከአምላክ ድርጅት ጋር እኩል መራመዳችን የግድ አስፈላጊ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5) ይህን ማድረጋችን ተስፋችንን ሕያው አድርገን እንድንኖርና ይህ የአሁኑ ክፉ ሥርዓት ከመፈጸሙ በፊት ስለተቋቋመው የአምላክ መንግሥት በመላው ምድር ላይ በመመስከሩ ሥራ እንድንካፈል ያስችለናል።​—⁠ማቴዎስ 24:​3-14

6, 7. ቀጥሎ የምንመረምራቸው የይሖዋ ድርጅት ወደ ፊት እየገሰገሰ ያለባቸው ሦስት አቅጣጫዎች የትኞቹ ናቸው?

6 በ1920ዎቹ፣ 30ዎቹና 40ዎቹ ዓመታት ከይሖዋ ድርጅት ጋር መተባበር የጀመሩ ሰዎች በመካከላችን ይገኛሉ። በእነዚህ የመጀመሪያ ዓመታት ድርጅቱ አሁን ከደረሰበት ከዚህ አስደናቂ እድገትና ጭማሪ ላይ ይደርሳል ብሎ የገመተ ከመካከላችን ማን ነበር? በዘመናዊ ታሪካችን የተፈጸሙትን ታላላቅ ክንውኖች ለአንድ አፍታ አስብ! ይሖዋ በቲኦክራሲያዊ መንገድ በተደራጁ ሕዝቦቹ አማካኝነት ያከናወናቸውን ነገሮች መለስ ብሎ ማሰብ በመንፈሳዊ የሚክስ ይሆናል።

7 በጥንት ዘመን ይኖር የነበረው ዳዊት የይሖዋን ድንቅ ሥራዎች ባሰበ ጊዜ በጥልቅ ተነክቶ ነበር። “ባወራም ብናገርም ከቍጥር ሁሉ በዛ” ብሏል። (መዝሙር 40:​5) የእኛም አቅም ውስን በመሆኑ ይሖዋ በዘመናችን ያከናወናቸውን ብዙ ታላላቅና ድንቅ ሥራዎች መዘርዘር አንችልም። ቢሆንም ድርጅቱ እድገት ያደረገባቸውን ሦስት መስኮች እንመልከት:- (1) ደረጃ በደረጃ የተገለጠልን መንፈሳዊ የእውቀት ብርሃን፣ (2) እየተሻሻለና እያደገ የመጣው አገልግሎት እንዲሁም (3) በድርጅታዊ አሠራር ረገድ የተደረጉት ወቅታዊ ማስተካከያዎች ናቸው።

ለመንፈሳዊው የእውቀት ብርሃን አመስጋኝ መሆን

8. ከ⁠ምሳሌ 4:​18 ጋር በሚስማማ መንገድ መንፈሳዊው ብርሃን የአምላክን መንግሥት በሚመለከት ምን ነገር እንድናስተውል አስችሎናል?

8 ደረጃ በደረጃ እየተገለጠ በሚሄደው የእውቀት ብርሃን ረገድ ምሳሌ 4:​18 በትክክል ተፈጽሟል። እንዲህ ይላል:- “የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፣ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል።” ደረጃ በደረጃ እያደገ የሚሄድ መንፈሳዊ ብርሃን በማግኘታችን ምንኛ አመስጋኞች ነን! በ1919 በሴዳር ፖይንት ኦሃዮ በተደረገው ስብሰባ ላይ ለአምላክ መንግሥት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ ነበር። ይሖዋ ስሙን ለመቀደስና ልዕልናውን ለማረጋገጥ እንደ መሣሪያ አድርጎ የሚጠቀመው ይህንን መንግሥት ነው። እንዲያውም ይሖዋ በልጁ በሚተዳደረው መንግሥት አማካኝነት ስሙን ለመቀደስ ስላለው ዓላማ መጽሐፍ ቅዱስ ከመጀመሪያው የዘፍጥረት መጽሐፍ አንስቶ እስከ መጨረሻው የራእይ መጽሐፍ ድረስ የሚሰጠውን ምሥክርነት እንድናስተውል ያስቻለን መንፈሳዊው የእውቀት ብርሃን ነው። የሁሉም ጽድቅ ወዳዶች ድንቅ ተስፋ በዚህ ላይ የተመሠረተ ነው።​—⁠ማቴዎስ 12:​18, 21

9, 10. በ1920ዎቹ ስለ አምላክ መንግሥትና ስለ ሁለት ተቃራኒ ድርጅቶች ምን መገንዘብ ተችሏል? ይህስ ጠቃሚ ሆኖ የተገኘው እንዴት ነው?

9 በ1922 በሴዳር ፖይንት ኦሃዮ ተደርጎ በነበረው ስብሰባ ላይ ዋናው ተናጋሪ ጄ ኤፍ ራዘርፎርድ “ንጉሡንና መንግሥቱን አስታውቁ፣ አስታውቁ፣ አስታውቁ” ሲል የአምላክን አገልጋዮች አጥብቆ አሳስቦ ነበር። በመጋቢት 1, 1925 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣው “የብሔሩ መወለድ” የሚለው ርዕስ የአምላክ መንግሥት በ1914 መቋቋሙን ስለሚያመለክቱ ትንቢቶች በተገኘው ጥልቅ መንፈሳዊ ማስተዋል ላይ ያተኮረ ነበር። በተጨማሪም በ1920ዎቹ ዓመታት ሁለት የተለያዩና እርስ በርሳቸው የሚጻረሩ ድርጅቶች ማለትም የይሖዋና የሰይጣን ድርጅቶች መኖራቸው ተስተዋለ። በሁለቱ ድርጅቶች መካከል የሚደረገው ውጊያ ዛሬም ቀጥሏል። በአሸናፊው ወገን መሆን የምንችለው ከይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል መራመዳችንን ከቀጠልን ብቻ ይሆናል።

10 እንዲህ ያለው ተጨማሪ መንፈሳዊ ብርሃን የረዳን እንዴት ነው? የአምላክ መንግሥትም ሆነ ንጉሡ ኢየሱስ ክርስቶስ የዚህ ዓለም ክፍል ስላልሆኑ እኛም የዓለም ክፍል መሆን የለብንም። ከዓለም ተለይተን በመኖር ከእውነት ጎን መሰለፋችንን እናሳያለን። (ዮሐንስ 17:​16፤ 18:​37) ይህን ክፉ ሥርዓት ቀስፈው የያዙትን ውስብስብ ችግሮች ስንመለከት የሰይጣን ድርጅት ክፍል ባለመሆናችን ምንኛ አመስጋኞች ነን! በይሖዋ ድርጅት ውስጥ መንፈሳዊ መረጋጋትና ደህንነት አግኝተን ለመኖር በመቻላችን ምንኛ ታድለናል!

11. በ1931 የአምላክ ሕዝብ የትኛውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ስም ተቀብሏል?

11 በ1931 በኮሎምበስ ኦሃዮ ተደርጎ በነበረው ስብሰባ ላይ ኢሳይያስ 43:​10-12 ተግባራዊነቱ ይፋ ሆኗል። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን ለየት ያለ ስያሜ ተቀበሉ። ሰዎች የአምላክን ስም ጠርተው መዳን ይችሉ ዘንድ የአምላክን ስም ማሳወቅ መቻል ምንኛ ታላቅ መብት ነው!​—⁠መዝሙር 83:​18 NW፤ ሮሜ 10:​13 NW 

12. በ1935 እጅግ ብዙ ሰዎችን በተመለከተ የተገኘው መንፈሳዊ ብርሃን ምንድን ነው?

12 ከ1930ዎቹ በፊት ከአምላክ ሕዝብ መካከል ብዙዎቹ ስለወደፊቱ ሕይወት ተስፋቸው እርግጠኞች አልነበሩም። አንዳንዶች ስለ ሰማያዊ ሕይወት ያስቡ የነበረ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ምድራዊ ገነት የሚሰጠው ትምህርት ይማርካቸው ነበር። በ1935 በዋሽንግተን ዲሲ ተደርጎ በነበረው የአውራጃ ስብሰባ ላይ በራእይ ምዕራፍ 7 ላይ የተገለጸው እጅግ ብዙ ሕዝብ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች የተካተቱበት ቡድን መሆኑ ሲገለጥ ታላቅ ደስታ ሆነ። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ይህንን እጅግ ብዙ ሕዝብ የመሰብሰቡ ሥራ በከፍተኛ ፍጥነት ወደፊት በመገስገስ ላይ ይገኛል። የእጅግ ብዙ ሕዝብ ማንነት ለእኛ ምሥጢር ባለመሆኑ አመስጋኞች አይደለንምን? ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶችና ቋንቋዎች የተውጣጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሲሰበሰቡ ማየታችን ከይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል ስንራመድ ተግተን እንድንሠራ ያነሳሳናል።

13. በ1941 በሴንት ሉዊስ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ጎላ ብሎ የተገለጸው ትልቅ ርዕሰ ጉዳይ ምን ነበር?

13 ሰብዓዊውን ኅብረተሰብ ሊያሳስበው የሚገባው ትልቅ ጥያቄ በ1941 በሴንት ሉዊ፣ ሚዙሪ ተካሂዶ በነበረው ስብሰባ ላይ ጎላ ተደርጎ ተገልጿል። ይህ አጽናፈ ዓለማዊ አገዛዝን ወይም ልዕልናን የሚመለከት ጉዳይ ነው። ይህ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ምላሽ ማግኘት የሚገባው ጥያቄ ሲሆን ለጥያቄው መልስ የሚገኝበት ታላቁና አስፈሪው ቀንም በፍጥነት እየቀረበ ነው! በተጨማሪም በ1941 ከዚህ ጋር የሚዛመደው ፍጹም አቋም የመጠበቅ ጉዳይ ትኩረት የተሰጠው ሲሆን ይህን ማድረጋችን የአምላክን ልዕልና በሚመለከት ከየትኛው ወገን እንደተሰለፍን ለማሳየት የሚያስችል አጋጣሚ ይሰጠናል።

14. በ1950 በተከናወነው ዓለም አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ ላይ በ⁠ኢሳይያስ 32:​1, 2 ላይ ስለተጠቀሱት መሳፍንት ምን ነገር መረዳት ተችሏል?

14 በ1950 በኒው ዮርክ ከተማ በተደረገው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ኢሳይያስ 32:​1, 2 ላይ የተገለጹት መሳፍንት ማንነት በትክክል ታውቋል። ወንድም ፍሬድሪክ ፍራንዝ በዚሁ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ባደረገው ንግግር ወደፊት በአዲሱ ምድር መሳፍንት የሚሆኑት ሰዎች በመካከላችን እንደሚገኙ መግለጹ የሁሉንም ስሜት ነክቶ ነበር። በዚህና ከዚያ በኋላ በተደረጉት የአውራጃ ስብሰባዎች ላይ በርካታ የመንፈሳዊ ብርሃን ብልጭታዎች ተገኝተዋል። (መዝሙር 97:​11) መንገዳችን ‘ሙሉ ቀን እስኪሆን ድረስ እየተጨመረ እንደሚበራ የንጋት ብርሃን’ በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን!

በአገልግሎታችን ወደ ፊት መግፋት

15, 16. (ሀ) በ1920ዎቹና በ1930ዎቹ በአገልግሎታችን ወደፊት የገፋነው እንዴት ነው? (ለ) ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ለክርስቲያናዊው አገልግሎት ግፊት የጨመሩለት ጽሑፎች የትኞቹ ናቸው?

15 የይሖዋ ድርጅት እድገት ካደረገባቸው መንገዶች ሁለተኛው፣ ዋነኛ ሥራችን የሆነውን የመንግሥት ስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ የሚመለከት ነው። (ማቴዎስ 28:​19, 20፤ ማርቆስ 13:​10) ይህን ሥራ ለማከናወን እንድንችል ድርጅቱ አገልግሎታችንን ማስፋት ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ሲያሳስበን ቆይቷል። በ1922 ሁሉም ክርስቲያኖች በስብከቱ እንቅስቃሴ እንዲካፈሉ ማበረታቻ ተሰጥቶ ነበር። እያንዳንዱ ክርስቲያን ብርሃኑ እንዲታይ የማድረግና እውነትን የመመስከር ኃላፊነት ነበረበት። (ማቴዎስ 5:​14-16) በ1927 እሁድ ለመስክ አገልግሎት የተወሰነ ቀን እንዲሆን የሚያደርግ እርምጃ ተወሰደ። ከየካቲት ወር 1940 ጀምሮ የይሖዋ ምሥክሮችን በየጎዳናውና በንግድ አካባቢዎች መጠበቂያ ግንብ እና መጽናኛ (አሁን ንቁ! የሚባለው) የተባሉትን መጽሔቶች ሲያበረክቱ ማየት የተለመደ ሆነ።

16 በ1937 ዘ ሞዴል ስተዲ የተባለ ንዑስ መጽሐፍ ወጣ። ይህ ጽሑፍ ለሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማስተማር ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳስብ ነበር። ከዚያ ወዲህ ባሉት ዓመታት ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንቅስቃሴ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቷል። በ1946 “እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን” በ1968 ደግሞ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተባሉት መጻሕፍት መውጣታቸው ለዚህ የአገልግሎት ዘርፍ ከፍተኛ ግፊት ጨምረውለታል። በአሁኑ ጊዜ የምንጠቀመው ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ ነው። እንዲህ ያለውን ጽሑፍ ማስጠናት ደቀ መዛሙርት ለማድረጉ ሥራ ጽኑ መሠረት ይጥላል።

ከድርጅታዊ ማሻሻያዎች ጋር ወደፊት መግፋት

17. ከ⁠ኢሳይያስ 60:​17 ጋር በሚስማማ መንገድ የይሖዋ ድርጅት ወደፊት የተራመደው እንዴት ነው?

17 የይሖዋ ድርጅት ወደፊት የተራመደበት ሦስተኛው ዘርፍ በአደረጃጀት መስክ የተደረገው ማሻሻያ ነው። በኢሳይያስ 60:​17 መሠረት ይሖዋ እንደሚከተለው ሲል ተንብዮአል:- “በናስ ፋንታ ወርቅን፣ በብረትም ፋንታ ብርን፣ በእንጨትም ፋንታ ናስን፣ በድንጋይም ፋንታ ብረትን አመጣለሁ። አለቆችሽንም ሰላም፣ የበላይ ገዢዎችሽንም ጽድቅ አደርጋለሁ።” ከዚህ ትንቢት ጋር በሚስማማ መንገድ ለመንግሥቱ የስብከት ሥራ የተሻለ ክትትል ለማድረግና መንጋውን በተገቢ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚያስችሉ እርምጃዎች ተወስደዋል።

18, 19. ባለፉት ዓመታት ውስጥ ምን ድርጅታዊ ማስተካከያዎች ተደርገዋል?

18 በ1919 ማኅበሩ ለመስክ አገልግሎት መደራጀት ለፈለገ ለእያንዳንዱ ጉባኤ የአገልግሎት ዲሬክተር ይሾም ነበር። ይህ አዲስ ዝግጅት ለመስኩ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ኃይል ጨምሮለታል። ሽማግሌዎችንና ዲያቆናትን በድምፅ ብልጫ መምረጥ በ1932 አቆመ። ይህም የጉባኤ ጉዳዮች በዲሞክራሲያዊ አሠራር የሚካሄዱበት ሁኔታ እንዲያከትም አድርጓል። በ1938 በጉባኤ ውስጥ ያሉ አገልጋዮችን በሙሉ ከመጀመሪያው የክርስቲያን ጉባኤ አሠራር ጋር ይበልጥ በሚመሳሰል መንገድ መሾም ሲጀመር አዲስ የአደረጃጀት ምዕራፍ ተከፈተ። (ሥራ 14:​23፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:​14) በ1972 የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ አገልጋዮች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ወንዶች በሚሾሙበት መንገድ ይሾሙ ጀመር። አንድ ሰው ብቻውን የጉባኤው የበላይ ተመልካች ሆኖ እንዲያገለግል በማድረግ ፋንታ ፊልጵስዩስ 1:​1 እና ሌሎችም ጥቅሶች እንደሚያመለክቱት የበላይ ተመልካች ለመሆን ቅዱስ ጽሑፋዊውን ብቃት የሚያሟሉ ሁሉ የሽማግሌዎች አካል አባላት ይሆናሉ።​—⁠ሥራ 20:​28፤ ኤፈሶን 4:​11, 12

19 በ1975 የአምላክ ድርጅት ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ በይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል ኮሚቴዎች የሚመራበት ዝግጅት ተጀመረ። በተጨማሪም በየአገልግሎት ክልሎቻቸው የሚካሄደውን ሥራ በበላይነት የሚቆጣጠሩ የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴዎች ተሾሙ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ‘ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ትኩረት መስጠት’ ይቻል ዘንድ የዋናውን መሥሪያ ቤትም ሆነ የቅርንጫፍ ቢሮዎችን አሠራር ቀልጣፋና ቀላል ለማድረግ ጥረት ተደርጓል። (ፊልጵስዩስ 1:​9, 10) በክርስቶስ የበታች እረኞች ጫንቃ ላይ የተጫነው ኃላፊነት በወንጌላዊነቱ ሥራ ግንባር ቀደም መሆን፣ በጉባኤ ውስጥ ማስተማርንና የአምላክን መንጋ በተገቢው ሁኔታ መጠበቅን የሚጨምር ነው።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:​16፤ ዕብራውያን 13:​7, 17፤ 1 ጴጥሮስ 5:​2, 3

በሥራ ላይ ያለው የኢየሱስ አመራር

20. ከይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል መራመድ የኢየሱስን ቦታ በተመለከተ ምን ነገር መገንዘብን ይጠይቃል?

20 ከይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል መራመድ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአምላክ ያገኘውን ‘የጉባኤ ራስ’ የመሆን ሥልጣን አምኖ መቀበልን ይጠይቃል። (ኤፌሶን 5:​22, 23) በ⁠ኢሳይያስ 55:​4 ላይ ያሉት “እነሆ፣ [እኔ ይሖዋ] ለአሕዛብ ምስክር፣ ለወገኖችም አለቃና አዛዥ እንዲሆን ሰጥቼዋለሁ” የሚሉትም ቃላት ልብ ሊባሉ ይገባል። ኢየሱስ መንጋውን እንዴት እንደሚመራ አሳምሮ ያውቃል። በጎቹንና ሥራቸውን ሁሉ ያውቃል። እንዲያውም በትንሿ እስያ የነበሩትን ሰባት ጉባኤዎች በመረመረ ጊዜ ‘ሥራህን አውቃለሁ’ እያለ አምስት ጊዜ ተናግሯል። (ራእይ 2:​2, 19፤ 3:​1, 8, 15) በተጨማሪም ኢየሱስ ልክ እንደ አባቱ እንደ ይሖዋ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ያውቃል። ኢየሱስ የናሙና ጸሎቱን ይዘት ከመዘርዘሩ በፊት “ሳትለምኑት አባታችሁ የሚያስፈልጋችሁን ያውቃል” ብሏል።​—⁠ማቴዎስ 6:​8-13

21. የኢየሱስ አመራር በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የተገለጠው እንዴት ነው?

21 የኢየሱስ አመራር የሚገለጠው እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ “የወንዶች ስጦታ” በሆኑት የበላይ ተመልካቾች በኩል ነው። (ኤፌሶን 4:​8 NW ) ራእይ 1:​16 ቅቡዓን የበላይ ተመልካቾች በክርስቶስ ቀኝ እጅ እንዳሉ ማለትም በእርሱ ቁጥጥር ሥር እንደሆኑ ያመለክታል። የእነዚህ ወንዶች ተስፋ ሰማያዊም ይሁን ምድራዊ ዛሬ ሽማግሌዎችን ለመሾም የተደረገውን ዝግጅት የሚመራው ኢየሱስ ነው። በፊተኛው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው ከቅዱሳን ጽሑፎች ብቃት ጋር በሚስማማ መንገድ በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ ናቸው። (1 ጢሞቴዎስ 3:​1-7፤ ቲቶ 1:​5-9) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኢየሩሳሌም የነበረው የሽማግሌዎች ቡድን የአስተዳደር አካል ሆኖ ይሠራ የነበረ ሲሆን ጉባኤዎቹንና የመንግሥቱን የስብከት ሥራ በአጠቃላይ በበላይነት ይከታተል ነበር። ዛሬም የይሖዋ ድርጅት የሚከተለው ይህን ቅዱስ ጽሑፋዊ አሠራር ነው።

እኩል ተራመድ!

22. የአስተዳደር አካሉ ምን እገዛ ያደርጋል?

22 የአምላክ መንግሥት ንብረት በሙሉ በአደራ የተሰጠው “ለታማኝና ልባም ባሪያ” ሲሆን ይህም ባሪያ በይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል ይወከላል። (ማቴዎስ 24:​45-47) የአስተዳደር አካሉ ዋነኛ ትኩረት ለክርስቲያን ጉባኤ መንፈሳዊ ትምህርትና መመሪያ መስጠት ነው። (ሥራ 6:​1-6) ይሁን እንጂ ወንድሞች በተፈጥሮ አደጋዎች በሚጎዱበት ጊዜ የአስተዳደር አካሉ አንድ ወይም ከዚያ በላይ ሕጋዊ ሰውነት ያላቸው ማኅበራት እርዳታ የማቅረቡንና ጉዳት የደረሰባቸውን ቤቶችና የመንግሥት አዳራሾች የመጠገኑን ሥራ እንዲያከናውኑ ይጠይቃል። አንዳንድ ክርስቲያኖች በደል በሚፈጸምባቸው ወይም ስደት በሚደርስባቸው ጊዜ እነርሱን በመንፈሳዊ ለማነጽ የሚያስችሉ እርምጃዎች ይወሰዳሉ። ‘በአስቸጋሪ ወቅቶች’ የመንግሥቱ ሥራ ወደፊት እንዲገሰግስ የሚቻለው ሁሉ ጥረት ይደረጋል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 4:​1, 2 NW 

23, 24. የይሖዋ ሕዝብ ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢደርስበት ይሖዋ ምን መስጠቱን አያቋርጥም? የእኛስ ቁርጥ ውሳኔ ምን መሆን ይኖርበታል?

23 ይሖዋ ምንም ዓይነት ሁኔታ በሕዝቡ ላይ ቢደርስ መንፈሳዊ ምግብና አስፈላጊ መመሪያ መስጠቱን አያቋርጥም። በተጨማሪም ይሖዋ በቲኦክራሲያዊ ድርጅት ወደፊት ለሚመጡ እድገቶችና ማስተካከያዎች የሚያስፈልጉትን ዝግጅቶች ለማድረግ የሚያስችል ማስተዋልና ግንዛቤ በኃላፊነት ላይ ላሉት ወንድሞች ይሰጣል። (ዘዳግም 34:​9፤ ኤፌሶን 1:​16, 17) ይሖዋ ደቀ መዛሙርት የማድረግ ተልዕኮአችንን ለመወጣትና በምድር ዙሪያ አገልግሎታችንን ለመፈጸም የሚያስችለንን ነገር አንድም ሳይጎድል ያሟላልናል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 4:​5

24 ይሖዋ ታማኝ ሕዝቡን እንደማይጥል ፍጹም እርግጠኞች ነን። ከመጪው “ታላቅ መከራ” ያድናቸዋል። (ራእይ 7:​9-14፤ መዝሙር 94:​14፤ 2 ጴጥሮስ 2:​9) በመጀመሪያ የነበረንን ትምክህት እስከ መጨረሻው አጽንተን እንድንይዝ የሚያደርጉ በቂ ምክንያቶች አሉን። (ዕብራውያን 3:​14) እንግዲያው ከይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል መራመድ ቁርጥ ውሳኔያችን ይሁን።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• የይሖዋ ድርጅት ወደፊት መገስገሱን ቀጥሏል ለማለት የሚያስችለን ምንድን ነው?

• የአምላክ ሕዝብ ደረጃ በደረጃ መንፈሳዊ ብርሃን እየፈነጠቀለት እንደሄደ የሚያሳዩ ምን ማስረጃዎች አሉ?

• በክርስቲያናዊ አገልግሎት ረገድ ማሻሻያዎች የተደረጉት እንዴት ነው?

• በይሖዋ አገልጋዮች መካከል የተደረጉት ወቅታዊ የሆኑ ድርጅታዊ ማሻሻያዎች ምንድን ናቸው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልክ እንደ ዳዊት እኛም የይሖዋን ድንቅ ሥራዎች ቆጥረን አንዘልቃቸውም

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ መንጋ ወቅታዊ ከሆኑት ድርጅታዊ ማስተካከያዎች ተጠቅሟል