በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ አገልጋዮች ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ የተሾሙ ናቸው

የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ አገልጋዮች ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ የተሾሙ ናቸው

የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ አገልጋዮች ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ የተሾሙ ናቸው

“መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት [“የበላይ ተመልካቾች፣” NW ] አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።”​—⁠ሥራ 20:​28

1, 2. ኢሳይያስ 60:​22 ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?

 ይሖዋ በፍጻሜው ዘመን አንድ ድንቅ ነገር እንደሚከናወን ከብዙ ዘመን በፊት ተንብዮአል። በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት እንደሚከተለው ብሎ ነበር:- “ታናሹ ለሺህ የሁሉም ታናሹ ለብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር በዘመኑ ይህን አፋጥነዋለሁ።”​—⁠ኢሳይያስ 60:​22

2 ይህ ትንቢት ዛሬ ፍጻሜውን እያገኘ እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ አለን? አዎን፣ በእርግጥ አለ! በ1870ዎቹ በአልጌኒ ፔንስልቬኒያ ዩ ኤስ ኤ ውስጥ አንድ የይሖዋ ሕዝቦች ጉባኤ ተቋቁሞ ነበር። ከዚህ ትንሽ ጅምር ተነሥቶ ዛሬ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ጉባኤዎች የተቋቋሙ ሲሆን ቁጥራቸው በዓለም ዙሪያ እየጨመረ ነው። ዛሬ ታላቅ ብሔር የሆኑ በሚልዮን የሚቆጠሩ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በምድር ዙሪያ በ235 አገሮች በሚገኙ ከ91, 000 የሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ ተሰባስበዋል። ይህም በጣም እየቀረበ ያለው “ታላቅ መከራ” ከመፈንዳቱ በፊት ይሖዋ እውነተኛ አምላኪዎችን የመሰብሰቡን ሥራ እያፋጠነው እንዳለ የሚያረጋግጥ የማያሻማ ማስረጃ ነው።​—⁠ማቴዎስ 24:​21፤ ራእይ 7:​9-14

3. ‘በአብ፣ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም መጠመቅ’ ማለት ምን ማለት ነው?

3 እነዚህ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ ከወሰኑ በኋላ በኢየሱስ መመሪያ መሠረት “በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም” የተጠመቁ ናቸው። (ማቴዎስ 28:​19) ‘በአብ ስም’ ተጠምቀዋል ማለት እነዚህ ራሳቸውን የወሰኑ ግለሰቦች ይሖዋ ሰማያዊ አባታቸውና ሕይወት ሰጪያቸው መሆኑን በመገንዘብ ለሉዓላዊነቱ ይገዛሉ ማለት ነው። ‘በወልድ ስም’ መጠመቃቸው ኢየሱስ ክርስቶስ የሚቤዣቸው፣ መሪያቸው እና ንጉሣቸው መሆኑን አምነው መቀበላቸውን ያመለክታል። የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል ሕይወታቸውን በመምራት ረገድ የሚጫወተውን ሚናም ይገነዘባሉ። ይህ ‘በመንፈስ ቅዱስ ስም’ መጠመቃቸውን የሚጠቁም ይሆናል።

4. ክርስቲያን አገልጋዮች የሚሾሙት እንዴት ነው?

4 አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ሲጠመቁ የይሖዋ አምላክ አገልጋዮች ሆነው ይሾማሉ። የሚሾማቸው ማን ነው? በመሠረታዊ ሥርዓት ደረጃ በ⁠2 ቆሮንቶስ 3:​5 ላይ ያሉት ቃላት ለእነርሱም ይሠራሉ:- “[አገልጋይ የመሆን] ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው።” በራሱ በይሖዋ ከመሾም የበለጠ ምን ክብር ሊመኙ ይችላሉ! ከተጠመቁ በኋላ የአምላክን መንፈስ አመራር እስከተቀበሉና ቃሉን ሥራ ላይ ማዋላቸውን እስከቀጠሉ ድረስ ‘የወንጌሉ’ አገልጋዮች በመሆን መንፈሳዊ እድገት ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ።​—⁠ማቴዎስ 24:​14፤ ሥራ 9:​31

ዲሞክራሲያዊ ሳይሆን ቲኦክራሲያዊ ሹመት

5. ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ አገልጋዮች የሚመረጡት በዲሞክራሲያዊ መንገድ ነውን? አብራራ።

5 ቁጥራቸው እያደገ የሚሄደውን የአምላክ አገልጋዮች መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት ብቃት ያላቸው የበላይ ተመልካቾች ብስለት ያለው የበላይ ጥበቃና ጥሩ ችሎታ ያላቸው የጉባኤ አገልጋዮች ድጋፍ ያስፈልጋል። (ፊልጵስዩስ 1:​1) እንዲህ ያሉት መንፈሳዊ ወንዶች የሚሾሙት እንዴት ነው? ሕዝበ ክርስትና ውስጥ በሚሠራባቸው ዓይነት ዘዴዎች አይደለም። ለምሳሌ ያህል ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች በዲሞክራሲያዊ መንገድ ማለትም በጉባኤ ውስጥ ያለውን የአብዛኛውን ሰው ድምፅ በማግኘት የሚመረጡ አይደሉም። ከዚህ ይልቅ ሹመታቸው ቲኦክራሲያዊ ነው። ይህ ምን ማለት ነው?

6. (ሀ) እውነተኛ ቲኦክራሲ ምንድን ነው? (ለ) የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ አገልጋዮች ሹመት ቲኦክራሲያዊ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

6 በአጭር አገላለጽ እውነተኛው ቲኦክራሲ የአምላክ አገዛዝ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በፈቃደኛነት ራሳቸውን ለእርሱ አመራር የሚያስገዙ ሲሆን መለኮታዊውን ፈቃድ ለመፈጸምም እርስ በርሳቸው ይተባበራሉ። (መዝሙር 143:​10፤ ማቴዎስ 6:​9, 10) ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ወይም ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች እንዲሾሙ የድጋፍ ሐሳብ የማቅረቡና እነርሱን የመሾሙ ሂደት የሚከናወነው በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በተጠቀሰው ዝግጅት መሠረት በመሆኑ እነዚህ ኃላፊነት ያላቸው ወንዶች የሚሾሙት በቲኦክራሲያዊ መንገድ ነው። በእርግጥም ደግሞ ይሖዋ ‘በሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያለ ራስ’ እንደመሆኑ የሚታየው ድርጅቱ አሠራር ምን ዓይነት መሆን እንዳለበት የመወሰን መብት አለው።​—⁠1 ዜና መዋዕል 29:​11፤ መዝሙር 97:​9

7. የይሖዋ ምሥክሮች የሚተዳደሩት እንዴት ነው?

7 የይሖዋ ምሥክሮች በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ ብዙ ሃይማኖታዊ ቡድኖች እንደሚያደርጉት የሚመሩበት መንፈሳዊ አስተዳደር ምን ዓይነት መሆን እንዳለበት የሚወስኑት ራሳቸው አይደሉም። እነዚህ ቅን ልብ ያላቸው ክርስቲያኖች ከይሖዋ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምተው ለመመላለስ ይጥራሉ። በመካከላቸው ያሉ የበላይ ተመልካቾች የሚሾሙት በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በሚሠራባቸው ዓይነት የመስተዳድር ሥርዓቶች አይደለም። ዓለማዊ ባለ ሥልጣናት በእነዚህ ሰዎች ሹመት አሰጣጥ ውስጥ እጃቸውን ለማስገባት ቢሞክሩ የይሖዋ አገልጋዮች አቋማቸውን ለማላላት ፈቃደኛ አይሆኑም። ሐዋርያት በመጀመሪያው መቶ ዘመን “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” በማለት የወሰዱትን ግልጽ አቋም በጽናት ይከተላሉ። (ሥራ 5:​29) በዚህ መንገድ ምሥክሮቹ በሁሉም ነገር ለአምላክ ይገዛሉ። (ዕብራውያን 12:​9፤ ያዕቆብ 4:​7) ቲኦክራሲያዊውን አሠራር መከተል መለኮታዊ ሞገስ ያስገኛል።

8. ዲሞክራሲያዊና ቲኦክራሲያዊ አሠራሮች የሚለያዩት እንዴት ነው?

8 የታላቁ ቲኦክራት የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን በዲሞክራሲያዊና ቲኦክራሲያዊ አሠራሮች መካከል ያለውን ልዩነት ማስታወሳችን የተገባ ይሆናል። ዲሞክራሲያዊ ሂደት በእኩል መጠን መወከልን የሚጠይቅና ብዙውን ጊዜም ለኃላፊነትና ለምርጫ የሚያበቃውን አብላጫ ድምፅ ለማግኘት ዘመቻ በመካሄድ የሚታወቅ ነው። እንዲህ ያለው አሠራር በቲኦክራሲያዊ ሹመት ውስጥ ቦታ የለውም። ቲኦክራሲያዊ ሹመት ከሰው የሚመጣ ወይም ከአንድ ድርጅታዊ አካል የሚሰጥ አይደለም። ጳውሎስ “የአሕዛብ ሐዋርያ” ሆኖ በኢየሱስ እና በይሖዋ ስለ መሾሙ በመጥቀስ ለገላትያ ሰዎች ሲጽፍላቸው ሹመቱ ‘በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባነሣው በእግዚአብሔር አብ እንጂ በሰው እንዳልሆነ’ ተናግሯል።​—⁠ሮሜ 11:​13፤ ገላትያ 1:​1

በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ

9. የክርስቲያን የበላይ ተመልካቾችን ሹመት በተመለከተ ሥራ 20:​28 ምን ይላል?

9 ጳውሎስ በኤፌሶን ይኖሩ የነበሩትን የበላይ ተመልካቾች በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት በአምላክ የተሾሙ መሆናቸውን አሳስቧቸዋል። እንዲህ ብሏል:- “በገዛ ደሙ [“ልጁ ደም፣” NW ] የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት [“የበላይ ተመልካቾች”፣ NW ] አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” (ሥራ 20:​28፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) እነዚያ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች የአምላክን መንጋ በእረኝነት የመጠበቅ ሥራቸውን ሲያከናውኑ የመንፈስ ቅዱስን አመራር መከተላቸውን መቀጠል ነበረባቸው። አንድ በኃላፊነት ላይ ያለ ሰው መለኮታዊውን መስፈርት ሳያሟላ ከቀረ መንፈስ ቅዱስ ጊዜውን ጠብቆ ከቦታው እንዲነሳ ያደርጋል።

10. መንፈስ ቅዱስ በቲኦክራሲያዊ ሹመት ውስጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወተው እንዴት ነው?

10 መንፈስ ቅዱስ ቁልፍ ሚና የሚጫወተው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ መንፈሳዊ የበላይ ተመልካቾች ለሚሆኑት ሰዎች የተዘረዘረው ብቃት በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ነው። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስና ለቲቶ በጻፋቸው ደብዳቤዎች ላይ የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ አገልጋዮች ሊያሟሏቸው የሚገቡትን ብቃቶች ዘርዝሯል። በአጠቃላይ 16 የተለያዩ ብቃቶችን ጠቅሷል። ለምሳሌ ያህል የበላይ ተመልካቾች የማይነቀፉ፣ በልማዳቸው ልከኞች የሆኑ፣ ጤናማ አስተሳሰብ ያላቸው፣ ሥርዓታማ፣ እንግዳ ተቀባይ፣ ለማስተማር የሚበቁና በቤተሰብ ራስነታቸው ምሳሌ የሚሆኑ ሊሆኑ ይገባል። በአልኮል መጠጦች ረገድ ሚዛናዊ፣ ገንዘብ የማይወዱ እንዲሁም ራሳቸውን የሚገዙ ሊሆኑ ይገባል። በተመሳሳይም የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን የሚጣጣሩት ወንዶች ሊያሟሏቸው የሚገቡ ከፍ ያሉ ብቃቶች ተዘርዝረዋል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 3:​1-10, 12, 13፤ ቲቶ 1:​5-9

11. በጉባኤ ውስጥ ለኃላፊነት ቦታ ለመብቃት የሚጣጣሩ ወንዶች ሊያሟሏቸው ከሚገቡት ብቃቶች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

11 እነዚህን ብቃቶች ስንመረምር በይሖዋ አምልኮ ውስጥ ግንባር ቀደም ሆነው የሚያገለግሉት ወንዶች በክርስቲያናዊ አኗኗራቸው ምሳሌ ሊሆኑ እንደሚገባ እንገነዘባለን። በጉባኤ ውስጥ ወደ ኃላፊነት ቦታ ለመድረስ የሚጣጣሩ ሁሉ መንፈስ ቅዱስ በእነርሱ ላይ እየሠራ እንዳለ የሚያሳዩ ሊሆኑ ይገባል። (2 ጢሞቴዎስ 1:​14) መንፈስ ቅዱስ በእነዚህ ሰዎች ላይ እንደ “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት” ያሉትን ፍሬዎች እያፈራ እንዳለ መታየት ይኖርበታል። (ገላትያ 5:​22, 23) እንዲህ ያሉት ፍሬዎች ከእምነት ባልንጀሮቻቸውም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ይንጸባረቃሉ። እርግጥ አንዳንዶች የተወሰኑ የመንፈስ ፍሬዎችን በማሳየት ረገድ ልቀው ሲገኙ ሌሎች ደግሞ ለበላይ ተመልካቾች የወጡትን ሌሎች ብቃቶች በላቀ ደረጃ ሊያሟሉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ የበላይ ተመልካች ወይም የጉባኤ አገልጋይ ለመሆን ተስፋ የሚያደርጉ ሁሉ በመላው አኗኗራቸው መንፈሳዊ ወንዶች መሆናቸውንና አምላክ በቃሉ ውስጥ ያሰፈረውን ብቃት የሚያሟሉ መሆናቸውን በግልጽ ማሳየት ይኖርባቸዋል።

12. በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ ናቸው ሊባሉ የሚችሉት እነማን ናቸው?

12 ጳውሎስ ምንም ሳያመነታ ሌሎች እርሱን እንዲመስሉ አጥብቆ ሊያሳስብ የቻለው እርሱ ራሱ ‘ፍለጋውን እንድንከተል ምሳሌ የተወልንን’ ኢየሱስ ክርስቶስን ይመስል ስለነበረ ነው። (1 ጴጥሮስ 2:​21፤ 1 ቆሮንቶስ 11:​1) በመሆኑም ቅዱስ ጽሑፋዊውን ብቃት አሟልተው የበላይ ተመልካቾች ወይም የጉባኤ አገልጋዮች ሆነው የሚሾሙት ወንዶች በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ ናቸው ሊባል ይችላል።

13. በጉባኤ ውስጥ ለሚያገለግሉት ወንዶች የድጋፍ ሐሳብ የሚያቀርቡትን መንፈስ ቅዱስ የሚረዳቸው እንዴት ነው?

13 የበላይ ተመልካቾች ለኃላፊነት ሲታጩና ሲሾሙ መንፈስ ቅዱስ ሚና የሚጫወተው እንዴት እንደሆነ የሚጠቁም ሌላም ነገር አለ። ኢየሱስ ‘በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጥ’ ተናግሯል። (ሉቃስ 11:​13) በመሆኑም በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሽማግሌዎች ወንዶችን ለጉባኤ ኃላፊነት ለማጨት በሚሰበሰቡበት ጊዜ የአምላክ መንፈስ እንዲመራቸው ይጸልያሉ። ለሚያቀርቡት የድጋፍ ሐሳብ መሠረት አድርገው የሚጠቀሙት በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ውስጥ ተመዝግቦ የሚገኘውን ሐሳብ ሲሆን መንፈስ ቅዱስም ለኃላፊነት የሚታጨው ሰው እነዚህን ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች ያሟላ እንደሆነና እንዳልሆነ እንዲያስተውሉ ይረዳቸዋል። ለኃላፊነት እንዲታጭ የድጋፍ ሐሳቡን ሲያቀርቡ ውጫዊ ሁኔታ፣ የትምህርት ደረጃ ወይም ተፈጥሮአዊ ችሎታ ተጽዕኖ እንዲያደርጉባቸው አይፈቅዱም። ትኩረት ሊያደርጉበት የሚገባው ጉዳይ የጉባኤው አባላት መንፈሳዊ ምክር ለማግኘት ሳያመነቱ ወደ እርሱ እንዲሄዱ የሚጋብዝ መንፈሳዊነት ያለው ሰው በመሆኑ ላይ ነው።

14. ከ⁠ሥራ 6:​1-3 ምን እንማራለን?

14 የሽማግሌዎች አካላት ሽማግሌ ወይም የጉባኤ አገልጋይ ሆነው ለሚያገለግሉት ወንድሞች የድጋፍ ሐሳብ በማቅረብ ረገድ ከተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ጋር የሚተባበሩ ቢሆንም ሹመቱ የሚከናወነው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይሠራበት የነበረውን ሥርዓት በመከተል ነው። በአንድ ወቅት መንፈሳዊ ብቃቱ ያላቸው ወንዶች አንድን በጣም አስፈላጊ ጉዳይ እንዲከታተሉ አስፈልጎ ነበር። የአስተዳደር አካሉ የሚከተለውን መመሪያ አስተላለፈ:- “በመልካም የተመሰከረላቸውን መንፈስ ቅዱስና ጥበብም የሞላባቸውን ሰባት ሰዎች ከእናንተ ምረጡ፣ ለዚህም ጉዳይ እንሾማቸዋለን።” (ሥራ 6:​1-3) የድጋፍ ሐሳቡን ያቀረቡት በቦታው የነበሩት ወንዶች ቢሆኑም ሹመቱን ያጸደቁት ግን በኢየሩሳሌም የነበሩ ኃላፊነት ያላቸው ወንዶች ናቸው። ዛሬም አሠራሩ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ ነው።

15. የአስተዳደር አካሉ ወንዶችን በመሾሙ ተግባር የሚጫወተው ሚና ምንድን ነው?

15 የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴዎችን አባላት በሙሉ በቀጥታ ይሾማል። የአስተዳደር አካሉ እንዲህ ያለውን ከበድ ያለ ኃላፊነት ሊሸከሙ የሚችሉት እነማን እንደሆኑ ሲወስን የሚከተሉትን የኢየሱስ ቃላት ያስታውሳል:- “ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል፣ ብዙ አደራም ከተሰጠው ከእርሱ አብዝተው ይሹበታል።” (ሉቃስ 12:​48) የአስተዳደር አካሉ የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባላትን ከመሾም በተጨማሪ የቤቴል ሽማግሌዎችንና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችንም ይሾማል። ይሁን እንጂ የተወሰኑ ሌሎች ሹመቶችን እንዲያጸድቁ እምነት የሚጣልባቸው ወንድሞችን ይወክላሉ። ለዚህም ቢሆን ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ አለ።

‘አንተን እንዳዘዝሁህ ሹም’

16. ጳውሎስ ቲቶን በቀርጤስ የተወው ለምን ነበር? ይህስ በዛሬው ጊዜ በቲኦክራሲያዊ መንገድ ስለሚሰጠው ሹመት ምን የሚጠቁመው ነገር አለ?

16 ጳውሎስ የሥራ አጋሩ ለሆነው ለቲቶ እንደሚከተለው ብሎታል:- “ስለዚህ ምክንያት የቀረውን እንድታደራጅ በየከተማውም፣ እኔ አንተን እንዳዘዝሁ፣ ሽማግሌዎችን እንድትሾም በቀርጤስ ተውሁህ።” (ቲቶ 1:​5) ከዚያም ጳውሎስ እንዲህ ላለው ኃላፊነት የሚበቁ ወንዶችን ለመለየት የሚያስፈልጉትን ብቃቶች ዘርዝሮለታል። በመሆኑም ዛሬ የአስተዳደር አካሉ ብቃት ያላቸውን ወንዶች በየቅርንጫፍ ቢሮው በመሾም እርሱን ወክለው የሽማግሌዎችን እና የጉባኤ አገልጋዮችን ሹመት እንዲያጸድቁ ያደርጋል። የአስተዳደር አካሉን ወክለው የሚሠሩት ወንድሞች እንዲህ ያለውን ሹመት በሚሰጡበት ጊዜ ቅዱስ ጽሑፋዊውን መመሪያ በትክክል እንዲያስተውሉና እንዲከተሉ ጥንቃቄ ይደረጋል። በመሆኑም ብቃት ያላቸው ወንዶች በዓለም ዙሪያ በሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ እንዲያገለግሉ የሚሾሙት በአስተዳደር አካሉ አመራር ነው።

17. የበላይ ተመልካቾች እና የጉባኤ አገልጋዮች ሆነው እንዲሾሙ የድጋፍ ሐሳብ የሚቀርብላቸው ወንዶች ጉዳይ በቅርንጫፍ ቢሮው የሚያዘው እንዴት ነው?

17 የበላይ ተመልካቾች ወይም የጉባኤ አገልጋዮች እንዲሾሙ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ የድጋፍ ሐሳብ በሚቀርብበት ጊዜ ተሞክሮ ያላቸው ወንድሞች ይህንን ሹመት ለማጽደቅ በአምላክ መንፈስ አመራር ይታመናሉ። እነዚህ ወንዶች ፈጥነው እጃቸውን ከጫኑ በግለሰቡ ኃጢአት ሊተባበሩ እንደሚችሉ ስለሚገነዘቡ ተጠያቂነት እንዳለባቸው ይሰማቸዋል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 5:​22

18, 19. (ሀ) አንዳንድ ሹመቶች ይፋ የሚሆኑት እንዴት ነው? (ለ) አጠቃላዩ የድጋፍ ሐሳብ የማቅረብና የሹመት ሂደት የሚከናወነው እንዴት ነው?

18 አንዳንድ ሹመቶች ሕጋዊ ሰውነት ያለው ድርጅት ማኅተም በሰፈረበት ደብዳቤ አማካኝነት ይፋ ይሆናሉ። እንዲህ ያለው ደብዳቤ በጉባኤው ውስጥ ያሉ ከአንድ በላይ ወንድሞችን ለመሾም ሊያገለግል ይችላል።

19 የቲኦክራሲያዊ ሹመት ምንጭ ይሖዋ ሲሆን እርሱም ይህንን በልጁ በኩልና በሚታየው ምድራዊ መገናኛ መስመር ማለትም ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ እንዲሁም በአስተዳደር አካሉ በኩል ያስፈጽማል። (ማቴዎስ 24:​45-47) እንዲህ ያለው የድጋፍ ሐሳብ የማቅረብና ሹመት የመስጠት ሂደት የሚመራው በመንፈስ ቅዱስ ነው። ይህ የሆነው ብቃቶቹ የተዘረዘሩት በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው የአምላክ ቃል ውስጥ በመሆኑና የሚሾሙትም ግለሰቦች የዚህን መንፈስ ፍሬ ማፍራታቸውን በግልጽ ስለሚያሳዩ ነው። በመሆኑም ሹመቱ በመንፈስ ቅዱስ የተሰጠ እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ይገባል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ አገልጋዮች የሚሾሙት በቲኦክራሲያዊ መንገድ እንደነበር ሁሉ ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።

ለይሖዋ አመራር አመስጋኞች ነን

20. በ⁠መዝሙር 133:​1 ላይ ያለውን የዳዊት ስሜት የምንጋራው ለምንድን ነው?

20 በመንግሥቱ የስብከት ሥራ መንፈሳዊ ብልጽግናና ቲኦክራሲያዊ ጭማሪ በተገኘበት በዛሬው ጊዜ የበላይ ተመልካቾችንና የጉባኤ አገልጋዮችን የመሾሙ ተግባር በዋነኛነት የይሖዋ እጅ ያለበት በመሆኑ በጣም አመስጋኞች ነን። ይህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ዝግጅት የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን በመካከላችን የአምላክ ከፍተኛ የጽድቅ የአቋም ደረጃዎች እንዲከበሩ ይረዳል። ከዚህም በላይ እነዚህ ወንዶች የሚያሳዩት ክርስቲያናዊ መንፈስና የሚያደርጉት ልባዊ ጥረት በይሖዋ አገልጋዮች መካከል ላለው ድንቅ ሰላምና አንድነት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። እንደ መዝሙራዊው ዳዊት ሁሉ እኛም “ወንድሞች በኅብረት ቢቀመጡ፣ እነሆ፣ መልካም ነው፣ እነሆም፣ ያማረ ነው” ለማለት እንገፋፋለን።​—⁠መዝሙር 133:​1

21. ኢሳይያስ 60:​17 ዛሬ ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?

21 ይሖዋ በቃሉና በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት ለሚሰጠን መመሪያ ምንኛ አመስጋኞች ነን! ደግሞም በ⁠ኢሳይያስ 60:​17 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት ቃላት በእርግጥም ትርጉም ያዘሉ ናቸው:- “በናስ ፋንታ ወርቅን፣ በብረትም ፋንታ ብርን፣ በእንጨትም ፋንታ ናስን፣ በድንጋይም ፋንታ ብረትን አመጣለሁ። አለቆችሽንም ሰላም፣ የበላይ ገዢዎችሽንም ጽድቅ አደርጋለሁ።” ቲኦክራሲያዊ አሠራሮች በይሖዋ ሕዝብ መካከል ደረጃ በደረጃ በተሟላ መንገድ ሥራ ላይ እየዋሉ ሲመጡ በመላው የአምላክ ድርጅት ውስጥ እነዚህን በረከቶች ለማየት ችለናል።

22. ስለ ምን ነገር አመስጋኞች ነን? ምን ለማድረግስ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል?

22 በመካከላችን ላለው ቲኦክራሲያዊ ዝግጅት ከልብ አመስጋኞች ነን። በቲኦክራሲያዊ መንገድ የተሾሙ የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ አገልጋዮች የሚያከናውኑትን አድካሚና አርኪ ሥራ ከልብ እናደንቃለን። መንፈሳዊ ብልጽግና ያጎናጸፈንና አትረፍርፎ የባረከንን ሰማያዊ አባታችንን ከልብ እናወድሳለን። (ምሳሌ 10:​22) እንግዲያውስ ከይሖዋ ድርጅት ጋር እኩል መራመዳችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ለይሖዋ ታላቅና ቅዱስ ስም ክብርና ውዳሴ እጅ ለእጅ ተያይዘን መሥራታችንን እንቀጠል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ አገልጋዮች ሹመት ዲሞክራሲያዊ ሳይሆን ቲኦክራሲያዊ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

• ኃላፊነት ያላቸው ክርስቲያን ወንዶች በመንፈስ ቅዱስ የሚሾሙት እንዴት ነው?

• የአስተዳደር አካሉ በበላይ ተመልካቾችና በጉባኤ አገልጋዮች ሹመት ረገድ የሚጫወተው ሚና ምንድን ነው?

• ቲኦክራሲያዊ ሹመትን በተመለከተ ለይሖዋ አመስጋኞች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች በቲኦክራሲያዊ መንገድ ተሹመው የማገልገል መብት አግኝተዋል