በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአስተዳደር አካሉን ከሕጋዊ ማኅበር የሚለየው ምንድን ነው?

የአስተዳደር አካሉን ከሕጋዊ ማኅበር የሚለየው ምንድን ነው?

የአስተዳደር አካሉን ከሕጋዊ ማኅበር የሚለየው ምንድን ነው?

የፔንስልቬኒያ መጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ከጥር 1885 ጀምሮ ዓመታዊ ስብሰባዎችን ሲያደርግ ቆይቷል። ቅቡዓን ክርስቲያኖች እየተሰበሰቡ በነበሩበት በ19ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ አካባቢ የዚህ ማኅበር ዲሬክተሮችና ኃላፊዎች ሰማያዊ ተስፋ ያላቸው ወንድሞች ነበሩ። እስከ አሁንም ድረስ ማኅበሩ ሲከተለው የቆየው አሠራር ይህ ነው ለማለት ይቻላል።

በአንድ ወቅት ብቻ ለየት ያለ ሁኔታ ነበር። ምድራዊ ተስፋ ካላቸው ‘የሌሎች በጎች’ ክፍል አባልና በወቅቱ የማኅበሩ የሕግ አማካሪ የነበረው ሄይደን ሲ ከቪንግተን በ1940 የማኅበሩ ዲሬክተር ሆኖ ተመርጦ ነበር። (ዮሐንስ 10:​16) ከ1942 እስከ 1945 የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኖ አገልግሏል። ይሖዋ የፔንስልቬኒያው ማኅበር ዲሬክተሮችና ኃላፊዎች በሙሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች እንዲሆኑ የሚፈልግ ይመስላል ከሚለው በወቅቱ ከነበረው አመለካከት ጋር በመስማማት ወንድም ከቪንግተን የማኅበሩ ዲሬክተርነቱን በገዛ ፈቃዱ ለቀቀ። ሄይደን ሲ ከቪንግተንን በመተካት ሊማን ኤ ስዊንግል የዲሬክተሮች ቦርድ አባል ሲሆን ፍሬድሪክ ደብሊዩ ፍራንዝ ደግሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆኖ ተመረጠ።

የይሖዋ አገልጋዮች የፔንስልቬኒያው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ዲሬክተሮችና ኃላፊዎች በሙሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖች መሆን አለባቸው የሚል እምነት ያደረባቸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በወቅቱ የፔንስልቬኒያው ማኅበር ዲሬክተሮችና ኃላፊዎች በመንፈስ ከተቀቡ ወንዶች ብቻ ከተገነባው የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል ጋር አንድ እንደሆኑ ተደርገው ይታዩ ስለነበረ ነው።

ታሪካዊ የሆነ ዓመታዊ ስብሰባ

የፔንስልቬኒያው ማኅበር አባላት ጥቅምት 2, 1944 በፒትስበርግ አድርገውት በነበረው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ የማኅበሩን ቻርተር የሚያሻሽሉ ስድስት ድምፀ ውሳኔዎችን አሳለፉ። ቻርተሩ ለማኅበሩ ሥራ የገንዘብ መዋጮ የሚያደርጉ ድምፅ የመስጠት መብት እንዲኖራቸው ያደርግ የነበረ ሲሆን ሦስተኛው ማሻሻያ ግን ይህን ዝግጅት የሚያስቀር ነበር። በዚያ ዓመታዊ ስብሰባ ላይ የቀረበው ሪፖርት እንደሚከተለው ይላል:- “የማኅበሩ አባላት ቁጥር ከ500 የማይበልጥ ይሆናል . . . የሚመረጠው እያንዳንዱ አባል የማኅበሩ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ወይም የይሖዋ ምሥክሮች ካምፓኒ [ጉባኤ] የከፊል ጊዜ አገልጋይ መሆንና የጌታን መንፈስ የሚያንጸባረቅ መሆን አለበት።”

ስለሆነም ከዚያን ጊዜ ወዲህ የማኅበሩ ዲሬክተሮች ለኃላፊነት የሚመረጡት የመንግሥቱን ሥራ ለማካሄድ የሚያደርጉት የገንዘብ መዋጮ ምንም ይሁን ምን ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ያደሩ ግለሰቦች በሚሰጡት ድምፅ ሆነ። ይህም በ⁠ኢሳይያስ 60:​17 ላይ በትንቢት ከተነገረው ደረጃ በደረጃ የሚከናወን የማጥራት ሥራ ጋር የሚስማማ ነበር:- “በናስ ፋንታ ወርቅን፣ በብረትም ፋንታ ብርን፣ በእንጨትም ፋንታ ናስን፣ በድንጋይም ፋንታ ብረትን አመጣለሁ። አለቆችሽንም ሰላም፣ የበላይ ገዢዎችሽንም ጽድቅ አደርጋለሁ።” ስለ ‘አለቆችና’ ‘የበላይ ገዢዎች’ የሚናገረው ይህ ትንቢት በይሖዋ ሕዝቦች መካከል የድርጅታዊ አሠራር ማሻሻያዎች እንደሚኖሩ ይጠቁማል።

ድርጅቱ ከቲኦክራሲያዊ አሠራር ጋር የተስማማ እንዲሆን የተወሰደው ይህ በጣም አስፈላጊ የሆነ እርምጃ ተግባራዊ የሆነው በዳንኤል 8:​14 ላይ የተገለጹት “ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ማታና ጥዋት” ባበቁበት ወቅት ነበር። በዚህ ጊዜ ‘መቅደሱ ነጽቶ’ ነበር።

ሆኖም በ1944 ከተደረገው ታሪካዊ ዓመታዊ ስብሰባ በኋላም መልስ ያላገኘ ወሳኝ ጥያቄ ይቀር ነበር። የአስተዳደር አካሉ ሰባት አባላት ካሉት ከፔንስልቬኒያው ማኅበር ዲሬክተሮች ቦርድ ጋር አንድ እንደሆነ ተደርጎ የሚታይ ከነበረ የአስተዳደር አካሉ አባላት ብዛት ከሰባት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሊበልጥ አይችልም ማለት ነውን? ከዚህም በላይ ዲሬክተሮቹ የሚመረጡት በማኅበሩ አባላት ስለሆነ የማኅበሩ አባላት ዓመታዊ ስብሰባ ባደረጉ ቁጥር የአስተዳደር አካሉን አባላት ይመርጣሉ ማለት ነውን? የፔንስልቬኒያው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ዲሬክተሮችና ኃላፊዎች ከአስተዳደር አካሉ አባላት ጋር አንድ ናቸው ወይስ የተለዩ ናቸው?

ሌላ ታሪካዊ የሆነ ዓመታዊ ስብሰባ

ጥቅምት 1, 1971 በተደረገው ዓመታዊ ስብሰባ ላይ እነዚህ ጥያቄዎች መልስ አግኝተዋል። በዚህ ወቅት ንግግር ካደረጉት ወንድሞች አንዱ “የታማኝና ልባም ባሪያ” የአስተዳደር አካል ሕልውናውን ያገኘው የፔንስልቬኒያው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ከመቋቋሙ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት እንደሆነ አመለከተ። (ማቴዎስ 24:​45-47) የአስተዳደር አካል የተቋቋመው የፔንስልቬኒያው ማኅበር ከመቋቋሙ ከ1, 800 ዓመታት በፊት ማለትም በ33 እዘአ በጰንጠቆስጤ ዕለት ነው። የመጀመሪያው የአስተዳደር አካል አባላት 7 ወንዶች ሳይሆኑ 12 ሐዋርያት ነበሩ። በኋላ ግን ‘በኢየሩሳሌም ያሉ ሐዋርያትና ሽማግሌዎች’ አመራር በሚሰጡበት ወቅት ቁጥሩ እንደጨመረ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል።​—⁠ሥራ 15:​2

በ1971 ያው ተናጋሪ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር አባላት የአስተዳደር አካሉን ቅቡዓን አባላት ሊመርጡ እንደማይችሉ አብራርቷል። ለምን? እንዲህ አለ:- “ምክንያቱም ‘የባሪያው’ ክፍል የአስተዳደር አካል የሚሾመው በሰው አይደለም። የሚሾመው . . . የእውነተኛው ክርስቲያን ጉባኤ ራስና ‘የታማኝና ልባም ባሪያ’ ክፍል ጌታና አለቃ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።” ስለዚህ የአስተዳደር አካል አባላት በየትኛውም ሕጋዊ ማኅበር አባላት በድምፅ ብልጫ እንደማይመረጡ ግልጽ ሆነ።

ተናጋሪው በመቀጠል የሚከተለውን ትልቅ ግምት የሚሰጠው መግለጫ አቀረበ:- “የአስተዳደር አካሉ ሊቀ መንበር ብቻ እንጂ እንደ ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ገንዘብ ያዥና ጸሐፊ፣ ምክትል ገንዘብ ያዥና ጸሐፊ የመሳሰሉ የማኅበሩ ዲሬክተሮች ቦርድ ያለው ዓይነት የኃላፊነት ቦታዎች የሉትም።” ለብዙ ዓመታት የፔንስልቬኒያው ማኅበር ፕሬዚዳንት የአስተዳደር አካሉ ዋና አባል ነበር። ከዚህ በኋላ ግን እንዲህ ያለው አሠራር ይቀራል። የአስተዳደር አካል አባላት እኩል ተሞክሮ ወይም ችሎታ ባይኖራቸውም እኩል ኃላፊነት ግን ይኖራቸዋል። ተናጋሪው አክሎም:- “ማንኛውም የአስተዳደር አካል አባል በወቅቱ የማኅበሩ . . . ፕሬዚዳንት ባይሆንም የአስተዳደር አካል ሊቀ መንበር ሊሆን ይችላል። . . . ይህ ሙሉ በሙሉ የተመካው በአስተዳደር አካሉ ውስጥ ሊቀ መንበር ለመሆን በወጣው ዙር ላይ ይሆናል።”

በ1971 በተደረገው በዚህ ታሪካዊ ስብሰባ በመንፈስ የተቀቡ አባላት ባሉት የአስተዳደር አካልና በፔንስልቬኒያው ማኅበር ዲሬክተሮች መካከል ያለው ልዩነት በግልጽ ተቀመጠ። የሆነ ሆኖ የአስተዳደር አካል አባላት የማኅበሩ ዲሬክተሮችና ኃላፊዎች ሆነው ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። ሆኖም ዛሬ የሚከተለው ጥያቄ ይነሳል:- የፔንስልቬኒያው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ዲሬክተሮች የግድ የአስተዳደር አካል አባላት መሆን አለባቸው የሚል ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት አለን?

መልሱ የለም ነው። የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠቀሙበት ሕጋዊ አካል የፔንስልቬኒያው ማኅበር ብቻ አይደለም። ሌሎች ሕጋዊ አካላትም አሉ። የኒው ዮርኩ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ከእነዚህ አንዱ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያለውን ሥራችንን የሚያካሂደው ይህ ማኅበር ነው። ምንም እንኳ ዲሬክተሮቹና ኃላፊዎቹ በአብዛኛው “ከሌሎች በጎች” የተውጣጡ ቢሆኑም ይሖዋ ይህን ማኅበር እንደባረከው ምንም ጥርጥር የለውም። በብሪታንያ ደግሞ ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማኅበር አለ። በሌሎች አገሮችም የመንግሥቱን ፍላጎቶች ለማስፋፋት የሚያገለግሉ ሌሎች ሕጋዊ አካላት አሉ። ሁሉም በመተጋገዝ ስምም ሆነው የሚሠሩ ሲሆን ምሥራቹ በምድር ዙሪያ እንዲሰበክ በማድረግ ረገድ የሚጫወቱት ሚና አላቸው። እነዚህ ማኅበራት የሚገኙበት አገር የትም ይሁን የት ወይም ዲሬክተሮቻቸው ወይም ኃላፊዎቻቸው ማንም ይሁን ማን እነዚህ ሕጋዊ አካላት ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ የሚመሩ ሲሆን የአስተዳደር አካል ሥራውን ለማካሄድ እንደ መሣሪያ አድርጎ ይጠቀምባቸዋል። ስለዚህ እነዚህ ሕጋዊ አካላት የመንግሥቱን ፍላጎቶች በማራመድ ረገድ የራሳቸው የሥራ ድርሻ ያበረክታሉ።

ሕጋዊ አካላት መኖራቸው ለእኛ ጠቃሚ ነው። እግረ መንገዳችንንም የአምላክ ቃል በሚጠይቀው መሠረት አካባቢያዊም ሆነ ብሔራዊ ሕግጋትን እንታዘዛለን። (ኤርምያስ 32:​11፤ ሮሜ 13:​1) ሕጋዊ አካላት መጽሐፍ ቅዱስን፣ መጻሕፍትን፣ መጽሔቶችን፣ ብሮሹሮችንና ሌሎች ጽሑፎችን በማተም የመንግሥቱን መልእክት ለማሰራጨት የሚያስፈልገንን ሁሉ ያቀርቡልናል። በተጨማሪም ከንብረት ባለቤትነት፣ ከእርዳታ፣ ትላልቅ ስብሰባ የሚደረግባቸውን ቦታዎች ከመከራየትና ከመሳሰሉት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ እንደ ሕጋዊ መሣሪያ ሆነው ያገለግላሉ። እነዚህ ሕጋዊ አካላት ለሚሰጡት አገልግሎት አመስጋኞች ነን።

የይሖዋን ስም ማሳወቅ

ማኅበሩ ለተቋቋመበት ተቀዳሚ ዓላማ አጽንዖት ለመስጠት ሲባል በ1944 የፔንስልቬኒያው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ቻርተር ሁለተኛ አንቀጽ ማሻሻያ ተደርጎበታል። በቻርተሩ መሠረት የማኅበሩ ተቀዳሚ ዓላማ የሚከተለውን ይጨምራል:- “ለስሙ፣ ለቃሉና ሁሉን ቻይ ለሆነው ለይሖዋ አምላክ ልዕልና ምሥክር ይሆን ዘንድ በክርስቶስ ኢየሱስ ስለሚመራው የአምላክ መንግሥት ምሥራች ለአሕዛብ ሁሉ መስበክ።”

‘ታማኝና ልባም ባሪያ’ ከ1926 ጀምሮ የይሖዋን ስም በስፋት ሲያሳውቅ ቆይቷል። በተለይም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን ስም የተቀበሉበት 1931 ትኩረት የሚስብ ዓመት ነበር። (ኢሳይያስ 43:​10-12) ለአምላክ ስም ትኩረት ከሰጡ የማኅበሩ ጽሑፎች መካከል የሚከተሉት የእንግሊዝኛ ጽሑፎች የሚጠቀሱ ናቸው:- ይሖዋ (1934) “ስምህ ይቀደስ” (1961) እና “አሕዛብ እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ”​—⁠እንዴት? (1971)

በተለይም በ1960 በእንግሊዝኛ ታትሞ የወጣው መላው የቅዱሳን ጽሑፎች የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም ሳይጠቀስ የማይታለፍ ነው። በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ቴትራግራማተን በሚገኙበት ቦታ ሁሉ የይሖዋን ስም ይዟል። በተጨማሪም ከፍተኛ ጥንቃቄ የተሞላበት ጥናትና ምርምር ከተደረገ በኋላ መለኮታዊው ስም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በ237 ቦታዎች እንዲገባ ተደርጓል። ይሖዋ፣ ‘ባሪያውና’ የአስተዳደር አካሉ በተለያየ መንገድ ስሙ በምድር ዙሪያ እንዲታወቅ ለማድረግ የማተሚያ ዘዴዎችንና ሕጋዊ አካላትን እንዲጠቀሙ ስለፈቀደ ምንኛ አመስጋኞች ነን!

የአምላክን ቃል በስፋት ማሰራጨት

የይሖዋ ሕዝቦች ዘወትር ስለ ስሙ በመመስከር እንዲሁም በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችንና ራሱን መጽሐፍ ቅዱስን በማተምና በማሰራጨት ለቃሉ ድጋፋቸውን ሲሰጡ ቆይተዋል። በ1900ዎቹ መጀመሪያ ላይ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በቤንጃሚን ዊልሰን የተዘጋጀውን ዚ ኢፋቲክ ዲያግሎት የተባለውን ግሪክኛውን ቃል በቃል በእንግሊዝኛ የሚያስቀምጠውን የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች እትም የባለቤትነት መብት ተረክቦ አሳትሟል። ማኅበሩ 500 ገጽ ተጨማሪ መግለጫ (appendix) ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ያዘጋጁትን የኪንግ ጀምስ ቨርሽን አሳትሟል። ማኅበሩ በ1942 ኪንግ ጀመስ ቨርሽንን ከሕዳግ ማጣቀሻ ጋር አሳትሟል። ከዚያም በ1944፣ መለኮታዊውን ስም የሚጠቀመውን በ1901 የተዘጋጀውን አሜሪካን ስታንዳርድ ቨርሽን ማሳተም ጀመረ። በ1972 ማኅበሩ ያሳተመው በስቴፈን ቲ ባይንግተን የተዘጋጀው ዘ ሊቪንግ ባይብል የተባለው መጽሐፍ ቅዱስም በይሖዋ ስም ይጠቀማል።

የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠቀሙባቸው ሕጋዊ አካላት እነዚህ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች እንዲታተሙና እንዲሰራጩ ረድተዋል። ከዚህ ሁሉ በላይ ግን በመጠበቂያ ግንብ ማኅበርና ከቅቡዓን የይሖዋ ምሥክሮች በተውጣጣው የአዲሲቱ ዓለም የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ኮሚቴ መካከል የነበረው ትብብር የላቀ ግምት የሚሰጠው ነው። የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም በ38 ቋንቋዎች በሙሉ ወይም በከፊል ከ106, 400, 000 በላይ በሚሆኑ ቅጂዎች መታተሙ ያስደስተናል። የፔንስልቬኒያው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር በእርግጥም የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ነው!

‘ታማኙ ባሪያ በጌታው ንብረት ሁሉ ላይ ተሾሟል።’ ይህም በዩ ኤስ ኤ ኒው ዮርክ ግዛት የሚገኘውን ዋና መሥሪያ ቤትና በዓለም ዙሪያ የሚገኙትን 110 ቅርንጫፍ ቢሮዎች ይጨምራል። የባሪያው ክፍል አባላት በአደራ የተሰጣቸውን ንብረት ስለተጠቀሙበት መንገድ እንደሚጠየቁ ያውቃሉ። (ማቴዎስ 25:​14-30) ሆኖም ይህ ሁኔታ ‘ባሪያው’ ሕግ ነክና የአስተዳደር ሥራዎችን የማከናወኑን ኃላፊነት ‘ከሌሎች በጎች’ መካከል ብቃት ላላቸው የበላይ ተመልካቾች እንዳይሰጥ አያግደውም። እንዲያውም እንዲህ ማድረጋቸው የአስተዳደር አካል አባላት “ለጸሎትና ቃሉን ለማገልገል” ይበልጥ ጊዜ እንዲኖራቸው ያደርጋል።​—⁠ሥራ 6:​4

“የታማኝና ልባም ባሪያ” ወኪል የሆነው የአስተዳደር አካል የዚህ ዓለም ሁኔታዎች እስከ ፈቀዱ ድረስ በሕጋዊ አካላት መጠቀሙን ይቀጥላል። ይህም ለአሠራር አመቺ ይሆናል ማለት እንጂ የግድ አስፈላጊ ነው ማለት አይደለም። አንድ ሕጋዊ አካል በመንግሥት ድንጋጌ ቢታገድ የስብከቱ ሥራ ይቀጥላል። አሁንም እንኳ በሥራው ላይ እገዳ በተጣለባቸውና ሕጋዊ አካላት በሌሉባቸው አገሮች የመንግሥቱ መልእክት እየታወጀ፣ ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ እየተከናወነና ቲኦክራሲያዊ ጭማሪ እየተገኘ ነው። ይህም ሊሆን የቻለው የይሖዋ ምሥክሮች ሲተክሉና ሲያጠጡ ‘አምላክ ማሳደጉን በመቀጠሉ ነው።’​—⁠1 ቆሮንቶስ 3:​6, 7

ወደፊትም ቢሆን ይሖዋ የሕዝቦቹን መንፈሳዊም ሆነ ቁሳዊ ፍላጎት ማሟላቱን እንደሚቀጥል እርግጠኞች ነን። እሱም ሆነ ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ የመንግሥቱ ስብከት ሥራ እንዲጠናቀቅ ከሰማይ አስፈላጊውን መመሪያና ድጋፍ መስጠታቸውን ይቀጥላሉ። የአምላክ አገልጋዮች በመሆን የምናከናውነው ማንኛውም ነገር ‘በይሖዋ መንፈስ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም።’ (ዘካርያስ 4:​6) በዚህ በመጨረሻው ቀን እንድንሠራው የሰጠንን ሥራ ማጠናቀቅ የምንችለው ይሖዋ በሚሰጠው ብርታት መሆኑን ስለምናውቅ መለኮታዊ ድጋፍ ለማግኘት እንጸልያለን!