በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ ምሥክሮች ጽኑ እምነት በመያዝ ወደፊት ይገሰግሳሉ!

የይሖዋ ምሥክሮች ጽኑ እምነት በመያዝ ወደፊት ይገሰግሳሉ!

የይሖዋ ምሥክሮች ጽኑ እምነት በመያዝ ወደፊት ይገሰግሳሉ!

የዓመታዊ ስብሰባ ሪፖርት

አለመተማመንና ጥርጣሬ በነገሠበት በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ጽኑ እምነት ያላቸው ክርስቲያኖች በመሆናቸው ለየት ብለው ይታያሉ። ይህም ቅዳሜ ጥቅምት 7, 2000 ጀርሲ ሲቲ በሚገኘው ኒው ጀርሲ የይሖዋ ምሥክሮች ትልቅ የስብሰባ አዳራሽ ውስጥ በተካሄደው የፔንስልቬኒያው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማህበር ዓመታዊ ስብሰባ ላይ ግልጽ ተደርጓል። a

የስብሰባው ሊቀ መንበርና የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ጆን ኢ ባር በመክፈቻ ንግግሩ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር:- “በምድር ላይ ካሉት በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል የይሖዋ ውድ ልጅ ክርስቶስ ኢየሱስ በአሁኑ ጊዜ በሰማይ ዙፋን ላይ ተቀምጦ በጠላቶቹ መካከል በመግዛት ላይ እንደሚገኝ የምናውቀውና የምናምነው እኛ ነን።” እንዲህ ያለው ጽኑ እምነት ከዓለም ዙሪያ በቀረቡት ስድስት ስሜት ቀስቃሽ ሪፖርቶች ላይ ተንጸባርቆ ነበር።

በሄይቲ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አማካኝነት ከመናፍስታዊ ድርጊቶች መላቀቅ

በሄይቲ መናፍስታዊ ድርጊቶች በሰፊው የተለመዱ ናቸው። የቅርንጫፍ ቢሮው ኮሚቴ አስተባባሪ የሆነው ጆን ኖርመን “ብዙውን ጊዜ ሰዎች ራሳቸውን ለመጠበቅ ሲሉ የቩዱ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን ያከናውናሉ” ሲል ተናገረ። አንድ ጠንቋይ በአደጋ ምክንያት አንድ እግሩን ሲያጣ ጥርጣሬ አደረበት። ‘መናፍስት የሚጠብቁኝ ከሆነ እንዴት እንዲህ ያለ ነገር በእኔ ላይ ይደርሳል?’ ሲል አሰበ። የይሖዋ ምሥክሮች ለሌሎች ብዙ ሰዎች እንዳደረጉት ሁሉ ይህንንም ሰው እውነትን በማስተማር ከመናፍስታዊ ድርጊቶች እንዲላቀቅ ረድተውታል። ሚያዝያ 19, 2000 በተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ከጠቅላላው የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር በ4 እጅ የሚበልጡ ሰዎች መገኘታቸው በሄይቲ ወደፊት ጭማሪ ሊኖር እንደሚችል የሚያሳይ ማስረጃ ነው።

በኮሪያ ሰፊ ክልል የታየ ቅንዓት

በኮሪያ 40 በመቶ የሚያክሉት የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ይገኛሉ። የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴው አስተባባሪ የሆነው ሚልተን ሃሚልተን “በዚህ ታላቅ የአዋጅ ነጋሪዎች ሠራዊት አማካኝነት ከ47 ሚልዮን በላይ ነዋሪዎች ያሉት ክልላችን በወር አንድ ጊዜ ይሸፈናል” በማለት ተናግሯል። በተለይ በምልክት ቋንቋ ተናጋሪ ጉባኤዎች ውስጥ ያለው ጭማሪ የሚያስደንቅ ነው። በአንድ የምልክት ቋንቋ ተናጋሪ ጉባኤዎች ወረዳ ውስጥ 800 የሚያክሉ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በመመራት ላይ ሲሆኑ ይህም እያንዳንዱ አስፋፊ በአማካይ አንድ ጥናት አለው ማለት ነው። የሚያሳዝነው ወጣት ወንድሞች በገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት አሁንም ወኅኒ ይወርዳሉ። ይሁን እንጂ የእስር ቤቱ ባለ ሥልጣናት እነዚህን የታመኑ ክርስቲያኖች ከማድነቃቸውም በላይ አብዛኛውን ጊዜ ታማኝነትን የሚጠይቁ ሥራዎች ይሰጧቸዋል።

በሜክሲኮ የተገኘው ጭማሪ የሚጠይቀውን ነገር ማሟላት

ነሐሴ 2000 በሜክሲኮ 533, 665 የደረሰ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች የመስክ አገልግሎታቸውን ሪፖርት አድርገዋል። ከአስፋፊዎቹ በሦስት እጥፍ የሚበልጡ ሰዎች በመታሰቢያው በዓል ላይ ተገኝተዋል። የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴው አስተባባሪ ሮበርት ትሬሲ “ለዚህ ዓመት ያወጣነው እቅድ 240 ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾችን መገንባት ነው” ካለ በኋላ “ቢሆንም ገና ብዙ ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾች ያስፈልጉናል” በማለት አክሎ ተናግሯል።

በሜክሲኮ የሚገኙት ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች አርአያ የሚሆኑ ናቸው። አንድን ወጣት አስመልክቶ አንድ የካቶሊክ ቄስ እንዲህ ብሏል:- “ከተከታዮቼ መካከል ልክ እንደ እርሱ ያለ አንድ ሰው እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ። እነዚህ ሰዎች ያላቸውን ጠንካራ የፈቃደኝነት መንፈስና ጥበብ የሞላበትን የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃቀማቸውን አደንቃለሁ። ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ቢሆን እንኳ ለአምላክ ይቆማሉ።”

ብጥብጥ በሰፈነባት ሴራሊዮን የአቋም ጽናት ማሳየት

ሚያዝያ 1991 በሴራሊዮን የእርስ በርስ ጦርነት ሲፈነዳ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል፣ ቆስለዋል ወይም የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴው አስተባባሪ ቢል ካዋን “ጦርነትና ችግር በሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት አድርሰዋል” በማለት ገልጿል። “ለመልእክታችን ግድ​የለሾች የነበሩ ብዙ ሰዎች አሁን በጉጉት ያዳምጣሉ። ሰዎች ማንም ሳይጋብዛቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ወደ መንግሥት አዳራሾቻችን ሲገቡ መመልከት የተለመደ ነገር ሆኗል። ብዙውን ጊዜ ወንድሞችን መንገድ ላይ አስቁመው መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያስጠኗቸው ይጠይቋቸዋል።” በአገሪቱ የሰፈነው አለመረጋጋት እንደቀጠለ ቢሆንም የመንግሥቱ የስብከት ሥራ በሴራሊዮን ፍሬ እያፈራ ነው።

በደቡብ አፍሪካ የተካሄደ መጠነ ሰፊ የግንባታ ፕሮግራም

በአሁኑ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር ባሉት ክልሎች በሺህዎች የሚቆጠሩ የመንግሥት አዳራሾች ያስፈልጋሉ። እስካሁን ድረስ በመቶዎች የሚቆጠሩ አዳራሾች ተገንብተዋል። የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል የሆነው ጆን ኪኮት “ወንድሞች ቀድሞ ያደርጉት እንደነበረው በደሳሳ ቤቶች ወይም ዛፍ ጥላ ሥር መሰብሰባቸውን አቁመው ተስማሚ መቀመጫዎች ባሏቸው አዳራሾች ውስጥ በመሰብሰብ ላይ ናቸው” ሲል ተናግሯል። “ከእነዚህ የመንግሥት አዳራሾች መካከል አብዛኞቹ ምንም የተጋነነ ነገር ባይኖራቸውም ብዙውን ጊዜ በአካባቢው ካሉት ቤቶች ሁሉ ይልቅ ዓይን የሚስቡ ሆነው ይገኛሉ። በአንዳንድ ቦታዎች አንድ የመንግሥት አዳራሽ በተገነባ በዓመቱ የጉባኤው አባላት ቁጥር ከእጥፍ በላይ ጨምሮ እንደሚገኝ ተስተውሏል።”

የዩክሬን አዲስ የምሥክሮች ትውልድ

በ2000 የአገልግሎት ዓመት ዩክሬን 112, 720 የደረሰ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር አግኝታለች። ከእነዚህ ውስጥ ከ50, 000 በላይ የሚሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተማሩት ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ነው። የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴው አስተባባሪ ጆን ዲደር “እውነትም ይሖዋ ስሙን የሚያውጅ በወጣቶች የተገነባ አዲስ የምሥክሮች ትውልድ አስነስቷል!” ካለ በኋላ “ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ50 ሚልዮን በላይ መጽሔቶች አበርክተናል። ይህም ከአገሪቱ የሕዝብ ቁጥር ጋር የሚመጣጠን ነው። በእያንዳንዱ ወር ፍላጎት ካሳዩና ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ከሚፈልጉ ሰዎች በአማካይ እስከ አንድ ሺህ ደብዳቤዎች ይደርሱናል” ሲል ገልጿል።

ሌሎች የፕሮግራሙ ስሜት ቀስቃሽ ክፍሎች

የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ዳንኤል ሲድሊክ የሚመስጥ ንግግር አቅርቧል። በዚህ መጽሔት ላይ የወጣው “የአስተዳደር አካሉን ከሕጋዊ ማኅበር የሚለየው ምንድን ነው?” የሚለው ርዕስ በዚህ አዲስ ነገር የሚያሳውቅ ንግግር ላይ የተመሠረተ ነው።

የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ቴዎዶር ጃራዝ ደግሞ “የበላይ ተመልካቾችና የጉባኤ አገልጋዮች ቲኦክራሲያዊ በሆነ መንገድ የተሾሙ ናቸው” በሚል ርዕስ ስሜት ቀስቃሽ የሆነ ንግግር አቅርቧል። በዚህ መጽሔት ላይ ከወጡት ርዕሶች መካከል አንደኛው በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነው።

ይህ ዓመታዊ ስብሰባ የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ዴቪድ ስፕሌን በ2001 የዓመት ጥቅስ ላይ ተመስርቶ ያቀረበውን የሚያነቃቃ ንግግር ያካተተ ነበር። ጥቅሱ “ምሉዓን ሆናችሁና በአምላክ ፈቃድ ሁሉ ጽኑ እምነት ኖሯችሁ [ቁሙ]” በሚሉት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት ላይ የተመሠረተ ነው። (ቆላስይስ 4:​12) በዓለም ዙሪያ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመላው ምድር በታማኝነት በመስበክ ይህንን ለማድረግ ቆርጠዋል።​—⁠ማቴዎስ 24:​14

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ የተገናኙትን በተለያየ ቦታ የሚገኙ አድማጮች ጨምሮ በጠቅላላው 13, 082 ተሰብሳቢዎች የፕሮግራሙ ታዳሚዎች ነበሩ።