ላትቪያ ለምሥራቹ አዎንታዊ ምላሽ ሰጠች
የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
ላትቪያ ለምሥራቹ አዎንታዊ ምላሽ ሰጠች
የአምላክ ፈቃድ “ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ” እንዲደርሱ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) ለብዙ ዓመታት ምሥራቹን የመስማት አጋጣሚ ያልነበራቸው ሰዎች አሁን ምሥራቹን በመስማት ላይ ናቸው! የሚከተሉት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት እንደ ሌሎቹ አገሮች ሁሉ በላትቪያም በሁሉም እድሜ ክልል የሚገኙና የተለያየ አስተዳደግ ያላቸው ሰዎች ለመልእክቱ አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ላይ ናቸው።
• በምሥራቃዊ ላትቪያ በምትገኝ ሪዜክኔ በተባለች ከተማ አንዲት እናት በአሥራዎቹ ዕድሜ ከምትገኝ ልጅዋ ጋር ሆና አንዲትን ሴት አቅጣጫ እንድታሳያቸው ጠየቀቻት። ከይሖዋ ምሥክሮች አንዷ የሆነችው ይህች ሴት የሚያስፈልጋቸውን መረጃ ከሰጠቻቸው በኋላ ምሥክሮቹ በሚያደርጉት ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ጋበዘቻቸው።
እናትየዋም ሆነች ልጅትዋ ሃይማኖታዊ ዝንባሌ ያላቸው ስለነበሩ ወደ ስብሰባው ለመሄድ ወሰኑ። በስብሰባው ላይ ተገቢ ያልሆነ ነገር ቢመለከቱ ግን ወዲያውኑ ስብሰባውን አቋርጠው እንደሚወጡ መንገድ ላይ እያሉ ተስማሙ። ይሁን እንጂ ስብሰባው በጣም አስደሳች ከመሆኑ የተነሣ አቋርጦ የመሄዱ ሐሳብ ጨርሶ ወደ አእምሮአቸው አልመጣም። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀበሉና በስብሰባዎች ላይ አዘውትረው መገኘት ጀመሩ። በሦስት ወር ጊዜ ውስጥም በስብከቱ ሥራ መካፈል እንደሚፈልጉና የሚጠመቁበትን ጊዜ በጉጉት እንደሚጠባበቁ ገልጸዋል።
• አንድ ምሥክር በምዕራባዊ ላትቪያ በምትገኝ ከተማ ውስጥ ከምትኖር አና የተባለች የ85 ዓመት ባልቴት ጋር ተገናኘ። አና ልባዊ ፍላጎት በማሳየት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማች። ሆኖም ልጅዋና ሌሎቹ የቤተሰቧ አባላት አጥብቀው ተቃወሟት። አና የደረሰባት ተቃውሞም ሆነ እርጅና ወይም ያለባት የጤና እክል ጥናቷን እንዲያስተጓጉልባት አልፈቀደችም።
አንድ ቀን ለመጠመቅ እንዳሰበች ለልጅዋ ነገረቻት። ልጅዋም “ከተጠመቅሽ አረጋውያንን ለሚንከባከብ ድርጅት ወስጄ እሰጥሻለሁ” በማለት መለሰችላት። ሆኖም እንዲህ ያለው ማስፈራሪያ አናን ወደ ኋላ እንድታፈገፍግ አላደረጋትም። አካላዊ ሁኔታዋ ስላልፈቀደላት በራስዋ ቤት ውስጥ ተጠመቀች።
የአና ልጅ ለዚህ ምን ምላሽ ሰጠች? አመለካከቷ በመለወጡ ከጥምቀቱ በኋላ ለእናቷ ልዩ ምግብ አዘጋጀችላት። ከዚያም እናቷን “በመጠመቅሽ ምን ይሰማሻል?” ብላ ስትጠይቃት አና “እንደገና የተወለድኩ ያክል!” በማለት መልሳላታለች።
• በታኀሣሥ 1998 ሁለት ምሥክሮች አንድ ጡረታ የወጣ የቀድሞዋ የሶቭየት ሕብረት የጦር መኮንን አገኙ። በፈጣሪ ያምን ስለነበር መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠና የቀረበለትን ግብዣ ተቀበለ። በኋላ ሚስቱም በጥናቱ ላይ መገኘት ጀመረች። ብዙም ሳይቆይ ሁለቱም ፈጣን እድገት በማድረግ ያልተጠመቁ አስፋፊዎች ሆኑ። በተከታዩ የበጋ ወቅት የቀድሞው የጦር መኮንን ተጠመቀ። እነዚህ ባልና ሚስት ለመንፈሳዊ ነገሮች ያላቸው ከፍተኛ ፍቅር ሁሉንም የጉባኤ አባላት አበረታትቷል። ከዚህም በተጨማሪ ሁለቱም በአካባቢው የሚገኝ አንድ የመኖሪያ ቤት ፈርሶ ጥሩ የመንግሥት አዳራሽ ሲገነባ በሥራው ተካፍለዋል።