ሕይወታችንን ስጋት ላይ በሚጥሉ ሁኔታዎች ሥር መኖር
ሕይወታችንን ስጋት ላይ በሚጥሉ ሁኔታዎች ሥር መኖር
“እንቅልፍን ጨምሮ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የምናደርገው እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ሕልውናችንን ስጋት ላይ ከሚጥሉ ችግሮች ነፃ አይደለም።”—ዲስከቨር መጽሔት
ሕይወት ፈንጂዎች በተቀበሩበት አካባቢ ከመጓዝ ጋር ይመሳሰላል። ምክንያቱም አብዛኛውን ጊዜ ያላንዳች ማስጠንቀቂያ አደጋ ወይም ሞት በማንኛውም ሰዓት ሊያጋጥም ስለሚችል ነው። አደጋ ሊያስከትሉ የሚችሉት ሁኔታዎች ከአገር አገር የሚለያዩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል የመኪና አደጋ፣ የእርስ በርስ ጦርነት፣ ረሃብ፣ ኤድስ፣ ካንሰር፣ የልብ ሕመምና ሌሎችም ይገኙበታል። ለምሳሌ ያህል ኤድስ በቅርቡ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ ከሳሃራ በታች ባሉ አገሮች “በመላው አፍሪካ በተካሄዱት የእርስ በርስ ጦርነቶች ካለቁት ሰዎች በ10 እጅ የሚበልጥ ቁጥር ያላቸውን የ2.2 ሚልዮን ሰዎች ሕይወት በመቅጠፍ” ቁጥር አንድ ገዳይ ሆኖ እንደተገኘ ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ወርልድ ሪፖርት የተባለው ጋዜጣ ዘግቧል።
ይሁን እንጂ በዓለም ላይ የሰዎችን ሕይወት ለማራዘምና የበሽታ እንዲሁም የአካል ጉዳት ተጠቂ የመሆናቸውን አጋጣሚ ለመቀነስ ሲባል በብዙ ቢልዮን የሚቆጠር ገንዘብ ይጠፋል። ለምሳሌ፣ ጤናማ የአመጋገብና የአጠጣጥ ልማድ ማዳበርን እንዲሁም የሰውነት እንቅስቃሴ ማድረግን የመሳሰሉ በሰፊው የሚነገርላቸው ሐሳቦች በተወሰነ መጠን ጥሩ ውጤት ሊያመጡ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ጉልህ በሆኑት በሁሉም የሕይወት ዘርፎች መመሪያ ሊሆንልህና ይበልጥ ዋስትና ያለው ሕይወት እንድትመራ ሊረዳህ የሚችል አስተማማኝ የመረጃ ምንጭ አለ። ይህ ምንጭ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ጤንነታችንንና ደህንነታችንን የሚመለከቱ ዘርፈ
ብዙ ጉዳዮችን እንዴት መመልከት እንዳለብን የሚያሳዩ መመሪያዎች ይዟል። እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ለእያንዳንዱ ችግር ዝርዝር ማብራሪያ አይሰጥም። ሆኖም የአመጋገብ ልማድን፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን፣ አስተሳሰብን፣ የጾታ ግንኙነትን፣ የአልኮል መጠጦችን፣ ትምባሆን፣ ለመዝናናት ተብለው የሚወሰዱ ዕፆችንና ሌሎች ብዙ ጉዳዮችን በተመለከተ ልንመራባቸው የምንችላቸውን ግሩም መሠረታዊ ሥርዓቶች ይዟል።
የገንዘብ ዋስትና አለመኖሩም ሕይወት ለብዙዎች እንዲከብድ አድርጓል። በዚህም መስክ ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ ይረዳናል። ገንዘብንና የገንዘብ አያያዝን በተመለከተ ጥበብ ያለበት አመለካከት እንዲኖረን ብቻ ሳይሆን የተሻልን ተቀጣሪ ወይም አሠሪ መሆን የምንችልበትንም መንገድ ይጠቁመናል። በአጭር አነጋገር መጽሐፍ ቅዱስ ኢኮኖሚያዊ ዋስትና እና አካላዊ ደህንነት እንድናገኝ የሚረዳ መጽሐፍ ብቻ ሳይሆን ለሕይወት ጭምር የሚጠቅም አስተማማኝ መመሪያ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ ምን ያህል ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል ማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ እባክህ የጀመርከውን ንባብ ቀጥል።