በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ራስህን ለአምላክ ስትወስን ከገባኸው ቃል ጋር ተስማምተህ እየኖርክ ነውን?

ራስህን ለአምላክ ስትወስን ከገባኸው ቃል ጋር ተስማምተህ እየኖርክ ነውን?

ራስህን ለአምላክ ስትወስን ከገባኸው ቃል ጋር ተስማምተህ እየኖርክ ነውን?

“ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፣ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት።”​—⁠ቆላስይስ 3:​23

1. ሃይማኖታዊ ካልሆነ አቅጣጫ ስንመለከተው “ራስን መወሰን” የሚለው ሐረግ ምን ያመለክታል?

 ስፖርተኞች ለጥሩ ውጤት የሚበቁት እንዴት ነው? በቴኒስ፣ በእግር ኳስ፣ በቅርጫት ኳስ፣ በቤዝ ቦል፣ በሩጫ፣ በጎልፍ ወይም በሌላ በማንኛውም ስፖርት ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡት መላ ሕይወታቸውን ለስፖርት የሚያስገዙ ናቸው። የአካልና የአእምሮ ብቃት በአንደኛ ደረጃ የሚያስፈልጉ ነገሮች ናቸው። ይህ አባባል “ራስን መወሰን” የሚለው ሐረግ ካሉት በርካታ ትርጉሞች መካከል “ለአንድ ዓይነት አስተሳሰብ ወይም ድርጊት ራስን ሙሉ በሙሉ ማስገዛት” ከሚለው ትርጉም ጋር ይስማማል።

2. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ራስን መወሰን” የሚለው ሐረግ ምን ትርጉም አለው? አብራራ።

2 ይሁን እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ አኳያ “ራስን መወሰን” ምን ማለት ነው? “ራስን መወሰን” የሚለው ሐረግ “ተለይቶ መኖር፤ የተለዩ መሆን፤ መገለል” የሚል ትርጉም ካለው ከአንድ የዕብራይስጥ ግስ የተተረጎመ ነው። a በጥንቷ እስራኤል ሊቀ ካህናት ሆኖ ያገለግል የነበረው አሮን በዕብራይስጥ ቃላት “ቅድስና ለእግዚአብሔር [“ለይሖዋ፣” NW ]” የሚል ጽሕፈት የተቀረጸበት ከንጹሕ ወርቅ የተሠራ ‘የተቀደሰ የአክሊል ምልክት’ ያለበት መጠምጠሚያ ይለብስ ነበር። ይህም ሊቀ ካህናቱ “የአምላኩም ቅባት ዘይት ቅዱስነት በላዩ [ስለሆነ]” መቅደሱን ሊያረክስ የሚችል ምንም ዓይነት መጥፎ ነገር እንዳያደርግ እንደ ማሳሰቢያ ሆኖ ያገለግለዋል።​—⁠ዘጸአት 29:​6፤ 39:​30፤ ዘሌዋውያን 21:​12

3. ራስን ለአምላክ መወሰን አኗኗራችንን የሚነካው እንዴት ነው?

3 ከዚህ አገባብ መመልከት እንደምንችለው ራስን መወሰን ከበድ ተደርጎ የሚታይ ጉዳይ ነው። በፈቃደኝነት ተነሳስቶ ራስን የአምላክ አገልጋይ አድርጎ መለየትን ያመለክታል፤ ይህም ንጹሕ አኗኗር መከተልን ይጠይቃል። እንግዲያው ሐዋርያው ጴጥሮስ ይሖዋ “እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ” ብሎ መናገሩን የጠቀሰበት ምክንያት ይገባናል። (1 ጴጥሮስ 1:​15, 16) ራሳችንን ለአምላክ የወሰንን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን እስከ መጨረሻው ድረስ ታማኞች በመሆን ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን የመኖር ከባድ ኃላፊነት ተሸክመናል። ይሁን እንጂ በክርስትና ጎዳና ራስን ለአምላክ መወሰን ምን ነገሮችን ያካትታል?​—⁠ዘሌዋውያን 19:​2፤ ማቴዎስ 24:​13

4. ራስን ለአምላክ ወደመወሰን ደረጃ ላይ የምንደርሰው እንዴት ነው? ይህስ ከምን ነገር ጋር ሊመሳሰል ይችላል?

4 ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ፣ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስና በአምላክ ዓላማ ውስጥ ስለሚጫወተው ሚና ትክክለኛ እውቀት ካገኘን በኋላ አምላክን በፍጹም ልባችን፣ አሳባችን፣ ነፍሳችንና ኃይላችን ለማገልገል በግላችን ውሳኔ አደረግን። (ማርቆስ 8:​34፤ 12:​30፤ ዮሐንስ 17:​3) ይህም በግል እንደተደረገ ስዕለት ማለትም ያለ ምንም ገደብ ራስን ለአምላክ እንደመስጠት ተደርጎ ሊታይ ይችላል። ራሳችንን ለአምላክ የወሰንነው እንዲያው በስሜታዊነት አይደለም። በማስተዋል ችሎታችን ተጠቅመን በጥንቃቄና በጸሎት ያደረግነው ከበድ ያለ ውሳኔ ነው። በመሆኑም ለተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚቆይ ውሳኔ አይደለም። ማረስ ከጀመረ በኋላ ሥራው አድካሚ ስለሆነበት ወይም የመከሩ ጊዜ በጣም ሩቅ እንደሆነ ስለተሰማው አሊያም አዝመራው ሳይበላሽ ለፍሬ ይብቃ አይብቃ እርግጠኛ መሆን ስላልቻለ ብቻ ሥራውን እርግፍ አድርጎ እንደሚተው ገበሬ መሆን አንፈልግም። በመከራም በደስታም ጊዜ የቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶችን ‘እርፍ ጨብጠው የነበሩ’ የአንዳንድ ሰዎችን ምሳሌ እንመልከት።​—⁠ሉቃስ 9:​62፤ ሮሜ 12:​1, 2

ለአምላክ ያደረጉትን ውሳኔ እስከ መጨረሻው ጠብቀዋል

5. ራሱን ለአምላክ የወሰነ አገልጋይ በመሆን ረገድ ኤርምያስ ጉልህ ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው?

5 ኤርምያስ ከ40 ዓመታት (647-​607 ከዘአበ) ለሚበልጥ ጊዜ በኢ​የሩሳሌም ትንቢት ተናግሯል፤ ይህም ቀላል ሥራ አልነበ​ረም። የአቅም ገደቡን በሚገባ ያውቅ ነበር። (ኤርምያስ 1:​2-6) አንገተ ደንዳና የሆኑትን የይሁዳ ሰዎች በየዕለቱ ለመጋፈጥ ድፍረትና ጽናት ጠይቆበታል። (ኤር​ምያስ 18:​18፤ 38:​4-​6) ይሁን እንጂ ኤርምያስ ራሱን ለአምላክ የወሰነ እውነተኛ አገልጋይ ሆኖ ይገኝ ዘንድ በረዳው በይሖዋ አምላክ ላይ ታምኗል።​—⁠ኤርምያስ 1:​18, 19

6. ሐዋርያው ዮሐንስ ምን ምሳሌ ትቶልናል?

6 “ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ” በመመሥከሩ ምክንያት በእርጅና ዘመኑ ጠፍ ወደሆነችው ፍጥሞ ወደምትባል ደሴት በግዞት ስለተወሰደው ስለ ታማኙ ሐዋርያ ስለ ዮሐንስስ ምን ለማለት ይቻላል? (ራእይ 1:​9) ራሱን ለአምላክ ሲወስን ከገባው ቃል ጋር በመስማማት ለ60 ዓመታት በክርስትና ጎዳና ጸንቷል። ኢየሩሳሌም በሮማ ጦር ሠራዊት ከወደመች በኋላ በሕይወት ኖሯል። አንድ ወንጌል፣ ሦስት ደብዳቤዎችንና ስለ አርማጌዶን ጦርነት ቀደም ብሎ እንዲገነዘብ ያስቻለውን የራእይን መጽሐፍ የመጻፍ መብት አግኝቷል። አርማጌዶን በእሱ የሕይወት ዘመን እንደማይመጣ በተገነዘበ ጊዜ አገልግሎቱን አቆመ? የቸልተኝነት መንፈስ አደረበት? በጭራሽ። ‘ዘመኑ ቅርብ’ ቢሆንም እንኳ የተመለከታቸው ራእዮች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት ገና ወደፊት መሆኑን በማወቅ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ በታማኝነት ኖሯል።​—⁠ራእይ 1:​3፤ ዳንኤል 12:​4

ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ዘመናዊ ምሳሌዎች

7.በክርስትና ጎዳና ራስን ለአምላክ መወሰንን በተመለከተ አንድ ወንድም ግሩም ምሳሌ የሆነው እንዴት ነው?

7 በዘመናችንም በሺህ የሚቆጠሩ ታማኝ ክርስቲያኖች አርማጌዶንን በሕይወት ሊሻገሩ እንደማይችሉ ቢያውቁም እንኳ ራሳቸውን ለአምላክ ሲወስኑ የገ​ቡትን ቃል በቅንዓት የሙጥኝ ብለው ኖረዋል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል እንግሊዛዊው ኧርነስት ኢ ቢቨር ይገኝበታል። የይሖዋ ምሥክር የሆነው ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በጀመረበት በ1939 ሲሆን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር ሲል በአንድ የኅትመት ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ ይሠራው የነበረውን ጥሩ ገቢ የሚያስገኝለትን ፎቶግራፍ የማንሳት ሥራ ተወ። ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋሙን በመጠበቁ ምክንያት ለሁለት ዓመት ታስሯል። ቤተሰቡ በታማኝነት ከጎኑ የቆመ ሲሆን ሦስቱ ልጆቹ በ1950 በተካሄደው ኒው ዮርክ በሚገኘው ሚስዮናውያን በሚሠለጥኑበት የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት ገብተው ተምረዋል። ወንድም ቢቨር በስብከቱ ሥራ በከፍተኛ ቅናት ይካፈል ስለነበር ጓደኞቹ አርማጌዶን ኧርኒ የሚል ቅጽል ስም አውጥተውለት ነበር። ራሱን ለአምላክ ሲወስን የገባውን ቃል በታማኝነት የጠበቀ ሲሆን በ1986 እስከ ሞተበት ጊዜ ድረስ ሊመጣ ያለውን የአምላክን የጦርነት ቀን አውጆአል። ለአምላክ ያደረገውን ውሳኔ ከአምላክ ጋር ለተወሰነ ጊዜ የተደረገ ውል እንደሆነ አድርጎ አልተመለከተውም። b​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​58

8, 9. (ሀ) በፍራንኮ ግዛት ዘመን በስፔይን ይኖሩ የነበሩ በርካታ ወጣት ወንዶች ምን ምሳሌ ትተዋል? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች ማንሳቱ የተገባ ነው?

8 የማይቀዘቅዝ ቅንዓት በማሳየት ረገድ ሌላ ምሳሌ የምናገኘው ከስፔይን ነው። በፍራንኮ የግዛት ዘመን (1939-75) ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣት ምሥክሮች ክርስቲያናዊ ገለልተኝነታቸውን ጠብቀዋል። ብዙዎቹ አሥር ወይም ከዚያ የሚበልጥ ዓመት በጦር እስር ቤት ውስጥ አሳልፈዋል። ካሰስ ማርቲን የተባለ አንድ ምሥክር በተለያየ ጊዜ በድምሩ 22 ዓመት የሚደርስ እስር ተበይኖበት ነበር። ሰሜን አፍሪካ በሚገኝ በአንድ የጦር እስር ቤት ውስጥ ታስሮ እያለ አሰቃቂ በሆነ መንገድ ተደበደበ። ሁኔታው ቀላል ባይሆንም እንኳን ከአቋሙ ፍንክች አላለም።

9 እነዚህ ወጣቶች በተከታታይ ተደራራቢ ፍርድ ይበየንባቸው ስለነበር መቼ ከእስር እንደሚለቀቁ (ያውም የሚለቀቁ ከሆነ) አያውቁም ነበር። ቢሆንም እስር ቤት እያሉ ጽኑ አቋማቸውን ጠብቀዋል እንዲሁም በቅንዓት አገልግለዋል። በመጨረሻ በ1973 ሁኔታው እየተሻሻለ ሲሄድ ከእነዚህ ምሥክሮች መካከል ብዙዎቹ (በ30ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ይገኙ ነበር) ከእስር ቤት የተለቀቁ ሲሆን በቀጥታ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ገብተዋል። አንዳንዶቹ ልዩ አቅኚዎች ሌሎቹ ደግሞ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ሆኑ። እስር ቤት እያሉ ራሳቸውን ለአምላክ ሲወስኑ ከገቡት ቃል ጋር ተስማምተው ኖረዋል። ብዙዎቹም ከእስር ከተለቀቁበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ድረስ እንዲህ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። c እኛስ ዛሬ? የታመኑ ሆነው እንደተገኙት እንደነዚህ ሰዎች እኛም ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን ለገባነው ቃል ታማኝ ነንን?​—⁠ዕብራውያን 10:​32-34፤ 13:​3

ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን ለገባነው ቃል ተገቢ አመለካከት መያዝ

10. (ሀ) ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን የገባነውን ቃል መመልከት የሚኖርብን እንዴት ነው? (ለ) ይሖዋ ለእርሱ የምናቀርበውን አገልግሎት የሚመለከተው እንዴት ነው?

10 የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ያደረግነውን ውሳኔ የምንመለከተው እንዴት ነው? በሕይወታችን ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ እንዲይዝ አድርገናል? ወጣቶችም ሆን በዕድሜ የገፋን፣ ያገባንም ሆን ነጠላ፣ ጤናሞች ሆን የጤና እክል ያለብን ሁኔታችን ምንም ይሁን ምን አቅማችን የፈቀደልንን ያህል ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። አንድ ሰው አቅኚ፣ በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ፈቃደኛ ሠራተኛ፣ ሚስዮናዊ ወይም ተጓዥ የበላይ ተመልካች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲካፈል ሁኔታው ይፈቅድለት ይሆናል። በሌላው በኩል ደግሞ አንዳንድ ወላጆች የቤተሰቡን አካላዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶች ለማሟላት ደፋ ቀና ይሉ ይሆናል። ይሖዋ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በየወሩ የሚያሳልፉትን ጥቂት ሰዓት የሚመለከተው አንድ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ከሚመልሰው በርካታ ሰዓት አሳንሶ ነው? በጭራሽ። ይሖዋ የሌለንን ነገር እንድንሰጥ አይጠብቅብንም። ሐዋርያው ጳውሎስ የሚከተለውን መሠረታዊ ሥርዓት አስቀምጧል:- “በጎ ፈቃድ ቢኖር፣ እንዳለው መጠን የተወደደ ይሆናል እንጂ እንደሌለው መጠን አይደለም።”​—⁠2 ቆሮንቶስ 8:​12

11. መዳናችን የተመካው በምን ላይ ነው?

11 ያም ሆነ ይህ መዳናችን የተመካው እኛ በራሳችን ልናደርግ በምንችለው ነገር ላይ ሳይሆን ይሖዋ በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ባደረገልን ይገባናል በማንለው ደግነት ላይ ነው። ጳውሎስ “ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጐድሎአቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው [“ይገባናል በማንለው ደግነት፣” NW ] ይጸድቃሉ” በማለት በግልጽ አስቀምጦታል። ይሁን እንጂ የምናከናውነው ሥራ አምላክ በገባቸው ተስፋዎች ላይ ሕያው የሆነ እምነት እንዳለን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው።​—⁠ሮሜ 3:​23, 24፤ ያዕቆብ 2:​17, 18, 24

12. ሥራችንን ከሌሎች ጋር ማወዳደር የማይኖርብን ለምንድን ነው?

12 በአምላክ አገልግሎት የምናሳልፈውን ሰዓት፣ የምናበረክታቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ወይም የምንመራቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ብዛት ከሌሎች ጋር ማወዳደሩ አስፈላጊያችን አይደለም። (ገላትያ 6:​3, 4) በክርስቲያናዊ አገልግሎት ስለምናከናውነው ነገር የሚከተሉትን ኢየሱስ የተናገራቸውን ትሕትናን የሚያንጸባርቁ ቃላት ማስታወስ ይኖርብናል:- “እንዲሁ እናንተ ደግሞ የታዘዛችሁትን ሁሉ ባደረጋችሁ ጊዜ:- የማንጠቅም ባሪያዎች ነን፣ ልናደርገው የሚገባንን አድርገናል በሉ።” (ሉቃስ 17:​10) ደግሞስ ‘የታዘዝነውን ሁሉ’ አድርገናል ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር የምንችለው ምን ያህል ነን? ስለዚህ ጥያቄው፣ ለአምላክ የምናቀርበው አገልግሎት ጥራት ምን ያህል መሆን አለበት? የሚል ነው።​—⁠2 ቆሮንቶስ 10:​17, 18

እያንዳንዱን ቀን ዋጋማ በሆነ መንገድ መጠቀም

13. ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን የገባነውን ቃል ስንፈጽም ምን ዓይነት ዝንባሌ ሊኖረን ይገባል?

13 ጳውሎስ ለሚስቶች፣ ለባሎች፣ ለልጆች፣ ለወላጆችና ለአገልጋዮች ምክር ከሰጠ በኋላ “ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፣ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት፣ ከጌታ የርስትን ብድራት እንድትቀበሉ ታውቃላችሁና፤ የምታገለግሉት ጌታ ክርስቶስ ነውና” በማለት ጽፏል። (ቆላስይስ 3:​23, 24) ይሖዋን የምናገለግለው በምናከናውነው ነገር በሰዎች ለመደነቅ ብለን አይደለም። ኢየሱስ ክርስቶስ የተወውን ምሳሌ በመከተል አምላክን ለማገልገል እንጥራለን። በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ለአጭር ጊዜ ይቆይ የነበረውን አገልግሎቱን በጥድፊያ ስሜት አከናውኗል።​—⁠1 ጴጥሮስ 2:​21

14. ጴጥሮስ የመጨረሻውን ቀን በማስመልከት ምን ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል?

14 ሐዋርያው ጴጥሮስም የጥድፊያ ስሜት እንደነበረው አሳይቷል። ስለ ክርስቶስ መገኘት እንደ ራሳቸው ምኞት ጥያቄ የሚያነሱ ዘባቾች ማለትም ከሃዲዎችና ተጠራጣሪዎች በመጨረሻው ቀን እንደሚነሱ በሁለተኛው ደብዳቤው አስጠንቅቋል። ይሁን እንጂ ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል:- “ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፣ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል። የጌታው ቀን ግን እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል።” አዎን፣ የይሖዋ ቀን መምጣቱ የማይቀር ነው። ስለዚህ አምላክ በገባቸው ተስፋዎች ላይ ያለን እምነት ምን ያህል እርግጠኛና ጠንካራ እንደሆነ በየዕለቱ ልናስብበት የሚገባ ጉዳይ መሆን ይኖርበታል።​—⁠2 ጴጥሮስ 3:​3, 4, 9, 10

15. በሕይወታችን የምናሳልፈውን እያንዳንዱን ቀን መመልከት ያለብን እንዴት ነው?

15 ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ተስማምተን ለመኖር እያንዳንዱ ቀን ለይሖዋ ውዳሴ በሚያመጣ መንገድ መጠቀም ይኖርብናል። በእያንዳንዱ ቀን መጨረሻ ላይ የቀኑን ውሏችንን መለስ ብለን ስንመለከት ለይሖዋ ስም ቅድስናና ለመንግሥቱ ምሥራች መታወጅ ያበረከትነው አንድ ዓይነት አስተዋጽኦ እንዳለ መመልከት እንችላለን? ምናልባት በንጹሕ አኗኗራችን፣ ባደረግነው የሚያንጽ ጭውውት አሊያም ለቤተሰብ ወይም ለጓደኞቻችን ባሳየነው ፍቅራዊ አሳቢነት ይህን አድርገን ሊሆን ይችላል። ያገኘናቸውን አጋጣሚዎች ክርስቲያናዊ ተስፋችንን ለሌሎች ለማካፈል ተጠቅመንባቸዋል? አምላክ ስለገባቸው ተስፋዎች በቁም ነገር እንዲያስብበት ያደረግነው ሰው አለ? በምሳሌያዊ አነጋገር መንፈሳዊ የባንክ ሒሳባችንን በማሳደግ በየዕለቱ በመንፈሳዊ ዓይን ዋጋ ያለው ሃብት እናጠራቅም።​—⁠ማቴዎስ 6:​20፤ 1 ጴጥሮስ 2:​12፤ 3:​15፤ ያዕቆብ 3:​13

እይታችን ጥርት ያለ ይሁን

16. ሰይጣን አምላክን ለማገልገል ያደረግነውን ውሳኔ ለማዳከም በምን ዘዴዎች ሊጠቀም ይችላል?

16 የምንኖረው ለክርስቲያኖች እያደር አስቸጋሪ እየሆነ በሚሄድ ጊዜ ውስጥ ነው። ሰይጣንና ወኪሎቹ በጥሩና በመጥፎ፣ በንጹሕና በቆሻሻ፣ በጥሩ ሥነ ምግባርና በመጥፎ ሥነ ምግባር፣ ግብረገብነት ባለውና ግብረገብነት በሌለው መካከል ያለውን ልዩነት ለማደብዘዝ ጥረት ያደርጋሉ። (ሮሜ 1:​24-28፤ 16:​17-19) ብዛት ባላቸው የቴሌቪዥን ጣቢያዎች በሚተላለፉ ፕሮግራሞች ወይም በኢንተርኔት አማካኝነት ልባችንንና አእምሯችንን በቀላሉ ለማበላሸት ይሞክራል። መንፈሳዊ እይታችን ሊደበዝዝ ወይም ሊጠፋና መሠሪ ዘዴዎቹን መለየት ሊያቅተን ይችላል። ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለን አድናቆት እየቀነሰ ከሄደ ራሳችንን ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን ለመኖር ያደረግነውን ቁርጥ አቋም ሊያዳክምብንና አጥብቀን የያዝነውን “ዕርፍ” ቀስ በቀስ እንድናላላ ሊያደርገን ይችላል።​—⁠ሉቃስ 9:​62፤ ፊልጵስዩስ 4:​8

17. ጳውሎስ የሰጠው ምክር ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ጠብቀን እንድንኖር ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?

17 ስለዚህ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ጉባኤ የጻፈው የሚከተለው መልእክት ለጊዜያችንም በጣም ወቅታዊ ነው:- “ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነውና፤ ከዝሙት እንድትርቁ፣ እግዚአብሔርን እንደማያውቁ አሕዛብ በፍትወት ምኞት አይደለም እንጂ፣ ከእናንተ እያንዳንዱ የራሱን ዕቃ በቅድስናና በክብር ያገኝ ዘንድ [ይወ]ቅ።” (1 ተሰሎንቄ 4:​3-5) ራሳቸውን ለአምላክ ሲወስኑ የገቡትን ቃል ችላ ያሉ አንዳንዶች የጾታ ብልግና በመፈጸም ከክርስቲያን ጉባኤ ተወግደዋል። ከአምላክ ጋር የመሠረቱት ዝምድና እንዲዳከም በመፍቀዳቸው በሕይወታቸው ውስጥ ለይሖዋ ይሰጡት የነበረው የላቀ ግምት ጠፍቷል። ሆኖም ጳውሎስ “ለርኩሰት ሳይሆን እግዚአብሔር በቅድስና ጠርቶናልና። እንግዲህ የሚጥል ሰውን የጣለ አይደለም፣ መንፈስ ቅዱስን በእናንተ እንዲኖር የሰጠውን እግዚአብሔርን ነው እንጂ” በማለት ጽፏል።​—⁠1 ተሰሎንቄ 4:​7, 8

ቁርጥ ውሳኔህ ምንድን ነው?

18. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን አለበት?

18 ራሳችንን ለይሖዋ አምላክ ስንወስን የገባነውን ቃል በቁም ነገር የምንመለከት ከሆነ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን ይኖርበታል? በአኗኗራችንም ሆነ በአገልግሎታችን ጥሩ ሕሊና ለመያዝ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን። ጴጥሮስ “በክርስቶስ ያለውን መልካሙን ኑሮአችሁን የሚሳደቡ ሰዎች ክፉን እንደምታደርጉ በሚያሙበት ነገር እንዲያፍሩ በጎ ሕሊና ይኑራችሁ” በማለት አጥብቆ መክሯል። (1 ጴጥሮስ 3:​16) በምንከተለው ክርስቲያናዊ አኗኗር የተነሳ መከራ ልንቀበልና እንግልት ሊደርስብን ይችላል። ክርስቶስም ቢሆን በእምነቱና ለአምላክ ታማኝ በመሆኑ ምክንያት ተመሳሳይ ችግር ደርሶበት ነበር። ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል:- “ክርስቶስም በሥጋ ስለ እኛ መከራን ስለ ተቀበለ፣ ከእንግዲህ ወዲህ በሥጋ ልትኖሩ በቀረላችሁ ዘመን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሰው ምኞት እንዳትኖሩ፣ እናንተ ደግሞ ያን አሳብ እንደ ዕቃ ጦር አድርጋችሁ ያዙት፣ በሥጋ መከራን የተቀበለ ኃጢአትን ትቶአልና።”​—⁠1 ጴጥሮስ 4:​1

19. ስለ እኛ ምን እንዲባልልን እንፈልጋለን?

19 ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን ከገባነው ቃል ጋር ተስማምተን ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ ማድረጋችን በመንፈሳዊ፣ በሥነ ምግባርና በአካል ከታመመው ከሰይጣን ዓለም መደለያዎች ይጠብቀናል። ይሁን እንጂ ከዚህም በላይ ሰይጣንና የእርሱ ወኪሎች ሊሰጡን ከሚችሉት ከማንኛውም ነገር የሚልቀውን የአምላክን ሞገስ እንደምናገኝ እርግጠኞች እንሆናለን። እንግዲያው መጀመሪያ እውነትን ሲሰማ የነበረው ፍቅር ጠፍቷል የምንባል ዓይነት ሰዎች አንሁን። ከዚያ ይልቅ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በትያጥሮን ለነበረው ጉባኤ የተባለው ለእኛም የሚባልልን ዓይነት ሰዎች ሆነን እንገኝ:- “ሥራህንና ፍቅርህን እምነትህንም አገልግሎትህንም ትዕግሥትህንም ከፊተኛውም ሥራህ ይልቅ የኋለኛው እንዲበዛ አውቃለሁ።” (ራእይ 2:​4, 18, 19) አዎን፣ ለአምላክ ያደረግነውን ውሳኔ በተመለከተ ለብ ያልን አንሁን። ከዚያ ይልቅ እስከ መጨረሻው ቀናተኞች በመሆን “በመንፈስ የምንቃጠል እንሁን።”​—⁠ሮሜ 12:​11፤ ራእይ 3:​15, 16

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a የሚያዝያ 15, 1987 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 31ን ተመልከት።

b ስለ ኧርነስት ቢቨር ተጨማሪ ዘገባ ለማግኘት የመጋቢት 15, 1980 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 8-11ን ተመልከት።

c ኒው ዮርክ በሚገኘው በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን የ1978 የይሖዋ ምሥክሮች የዓመት መጽሐፍ (እንግሊዝኛ) ገጽ 156-8, 201-18ን ተመልከት።

ታስታውሳለህ?

• ራስን ለአምላክ መወሰን ምን ነገሮችን ይጨምራል?

• ጥንትም ሆነ ዛሬ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ምን ምሳሌዎች አሉን?

• ለአምላክ የምናቀርበውን አገልግሎት እንዴት መመልከት አለብን?

• ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን የገባነውን ቃል በተመለከተ ቁርጥ ውሳኔያችን ምን መሆን አለበት?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኤርምያስ አስከፊ በደል የደረሰበት ቢሆንም እንኳ በታማኝነት ጸንቷል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኧርነስት ቢቨር ለልጆቹ ቅንዓት የተሞላበት ክርስቲያናዊ ምሳሌ ትቶላቸዋል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በስፔይን ታስረው የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ወጣት ምሥክሮች ጽኑ አቋማቸውን ጠብቀዋል

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በእያንዳንዱ ቀን በመንፈሳዊ ሁኔታ ዋጋ ያለው ነገር እናከናውን