በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በተፈለግኩበት ቦታ ሁሉ ማገልገል

በተፈለግኩበት ቦታ ሁሉ ማገልገል

የሕይወት ታሪክ

በተፈለግኩበት ቦታ ሁሉ ማገልገል

ጄምስ ቢ ቤሪ እንደተናገረው

ጊዜው 1939 ነበር። በዩናይትድ ስቴትስ የደረሰው ታላቅ የኢኮኖሚ ድቀት ኑሮውን ያከበደው ሲሆን በአውሮፓም የጦርነት ነጋሪት በመጎሰም ላይ ነበር። እኔና ታናሽ ወንድሜ ቤኔት ሥራ ፍለጋ ከሚሲሲፒ ወደ ሂዩስተን ቴክሳስ ሄድን።

አንድ ቀን የበጋው ወቅት ሊገባደድ አካባቢ በጥራት በማይሰማ የራዲዮ ጣቢያ የሂትለር ጦር ሠራዊት ወደ ፖላንድ ዘልቆ እንደገባ የሚገልጽ ዜና ሰማን። ወንድሜ “በቃ አርማጌዶን ጀመረ!” ሲል ተናገረ። ወዲያውኑ ሥራችንን ለቀቅን። ከዚያም በአቅራቢያችን ወደሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ በመሄድ ለመጀመሪያ ጊዜ በስብሰባ ላይ ተገኘን። ወደ መንግሥት አዳራሽ ለመሄድ የመረጥነው ለምን ነበር? እስቲ ከጅምሩ አንስቼ ልንገራችሁ።

በ1915 በሄብሮን፣ ሚሲሲፒ ውስጥ ተወለድኩ። የምንኖረው ገጠር ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች የሚጠሩበት ስም ነው) በዓመት አንድ ጊዜ ወደ አካባቢው እየመጡ በአንዱ ሰው ቤት ንግግር ይሰጡ ነበር። በዚህ ምክንያት ወላጆቼ ብዙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ነበሯቸው። እኔና ቤኔት ሲኦል እንደማያቃጥል፣ ነፍስ ሟች እንደሆነችና ጻድቃን በምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ ከእነዚህ ጽሑፎች ተረዳን። ያም ሆኖ ገና ብዙ ይቀረን ነበር። ትምህርት ከጨረስኩ በኋላ እኔና ወንድሜ ሥራ ፍለጋ ወደ ቴክሳስ ሄድን።

በመጨረሻ በመንግሥት አዳራሽ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ስንገናኝ አቅኚዎች ናችሁ ብለው ጠየቁን። እኛ አቅኚ ማለት የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ መሆኑን እንኳ አናውቅም ነበር። ከዚያም መስበክ እንፈልግ እንደሆነ ጠየቁን። “አዎን፣ እንፈልጋለን!” አልናቸው። እንዴት እንደምንሰብክ የሚያሳየን ሰው ይመድቡልናል ብለን አስበን ነበር። ከዚያ ይልቅ የአገልግሎት ክልል ካርታ ሰጡንና “እዚያ ሥሩ!” ብቻ አሉን። እኔና ቤኔት እንዴት እንደምንሰብክ የማናውቅ ከመሆናችንም በላይ ሁኔታው የሚያሳፍር መስሎ ስለታየን መሄዱንም አልወደድነውም። በመጨረሻ የአገልግሎት ክልል ካርታውን በፖስታ ቤት ላክንላቸውና ወደ ሚሲሲፒ ተመለስን!

የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የራሳችን ማድረግ

ወደ ቤት ከተመለስን በኋላ ለአንድ ዓመት ያክል የምሥክሮቹን ጽሑፎች በየዕለቱ ማለት ይቻላል እናነብ ነበር። ቤታችን መብራት አልነበረውም፤ ስለዚህ ማታ ማታ የምናነበው እሳት እያነደድን ነበር። በዚያን ወቅት የዞን አገልጋዮች ወይም ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎችንና በገለልተኛ ክልል የሚኖሩ ምሥክሮችን በመንፈሳዊ ለማበረታታት ይጎበኙ ነበር። ቴድ ክሌይን የሚባል የዞን አገልጋይ ጉባኤያችንን ሲጎበኝ ከቤት ወደ ቤት አብረነው እንድንሰብክ እኔንና ቤኔትን አብዛኛውን ጊዜ አንድ ላይ ይዞን ይሄድ ነበር። አቅኚነት ምን እንደሆነ አስረዳን።

ከእርሱ ጋር መስበካችን አምላክን ይበልጥ ስለማገልገል እንድናስብ አደረገን። ስለዚህ ወንድም ክሌይን ሚያዝያ 18, 1940 ቤኔትን፣ እህታችንን ቬልቫንና እኔን አጠመቀን። ወላጆቻችን በጥምቀት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙ ሲሆን በውሳኔያችን ተደስተው ነበር። እነሱም ከሁለት ዓመት በኋላ ተጠመቁ። አባባ በ1956 እንዲሁም እማማ በ1975 እስከሞቱበት ጊዜ ድረስ አምላክን በታማኝነት አገልግለዋል።

ወንድም ክሌይን አቅኚ መሆን እችል እንደሆነ ሲጠይቀኝ ብሆን ደስ እንደሚለኝ ነገር ግን ገንዘብም ሆነ ልብስ እንደሌለኝ ነገርኩት። “ስለእሱ አትጨነቅ፣ እሱን በእኔ ተወው” አለኝ። እንዳለውም አደረገልኝ። በመጀመሪያ የአቅኚነት ማመልከቻዬን ላከልኝ። ከዚያም 300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ወደሚገኘው ኒው ኦርሊንስ ወሰደኝና በአንድ የመንግሥት አዳራሽ ፎቅ ላይ የሚገኙትን ጥሩ ጥሩ ክፍሎች አሳየኝ። ለአቅኚዎች የተዘጋጁ ነበሩ። ብዙም ሳይቆይ ወደዚያ ተዛወርኩና አቅኚነትን ተያያዝኩት። በኒው ኦርሊንስ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ልብስ፣ ገንዘብና ምግብ በመስጠት አቅኚዎችን ይረዱ ነበር። ቀን ቀን ወንድሞች ምግብ አምጥተው በር ላይ ወይም አንዳንዴ ማቀዝቀዣ ውስጥ አስቀምጠውልን ይሄዳሉ። በአቅራቢያችን ምግብ ቤት የነበረው አንድ ወንድም ሆቴሉ ሊዘጋ ሲል እየሄድን የተረፈ ሥጋ፣ ዳቦና የመሳሰሉ ምግቦችን እንድንወስድ ይጋብዘን ነበር።

የተቀሰቀሰብን የሕዝብ ረብሻ

ከጊዜ በኋላ ጃክሰን ሚሲሲፒ ውስጥ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። እኔና ወጣት የአገልግሎት ጓደኛዬ የሕዝብ ረብሻ የተቀሰቀሰብን ሲሆን የአካባቢው የሕግ አስከባሪ አካላትም ለረብሻው ድጋፍ የሚሰጡ ይመስል ነበር! በቀጣዩ ምድባችን በኮሎምበስ ሚሲሲፒም ሁኔታው ተመሳሳይ ነበር። ለሁሉም ዘሮችና ከተለያዩ አገሮች ለመጡ ሰዎች ስለምንሰብክ አንዳንድ ነጮች ይጠሉን ነበር። ብዙዎች ሕዝብን በመንግሥት ላይ ለመቀስቀስ እንደምንሞክር ይሰማቸዋል። የቀድሞ የአሜሪካ ወታደሮችን ያቀፈውና ከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት ያለው ድርጅት አዛዥም ተመሳሳይ አመለካከት ነበራቸው። ሕዝቡ በቁጣ ተነሳስቶ እንዲያጠቃን ብዙ ጊዜ ቅስቀሳ አድርገዋል።

በኮሎምበስ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቃት በደረሰብን ቀን መንገድ ላይ መጽሔት እያበረከትን እያለ ሕዝቡ ግልብጥ ብሎ መጣብን። ገፍተው ገፍተው ከአንድ መደብር መስታወት ጋር አጣበቁን። ወሬ ለማየት ብዙ ሕዝብ ተሰበሰበ። ወዲያው ፖሊስ ደረሰና ወደ ፍርድ ቤት ወሰደን። ሕዝቡ ፍርድ ቤት ድረስ ተከትሎን በመምጣት በተወሰነ ቀን ውስጥ ከተማውን ለቅቀን ካልወጣን እንደማይምሩን በባለ ሥልጣናቱ ፊት ዛቱብን! ለጊዜውም ቢሆን ከተማውን ለቅቆ መውጣት እንደሚሻል ተሰማን። ሆኖም ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ተመለስንና ስብከታችንን ቀጠልን።

ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ስምንት ወሮበሎች ከበቡንና ይዘዋቸው ወደ መጡት ሁለት መኪናዎች እየገፈታተሩ አስገቡን። ወደ ጫካ ወስደው ልብሳችንን ካስወለቁን በኋላ በእኔ ቀበቶ እያንዳንዳችንን 30 ጊዜ ገረፉን! ሽጉጥ ሌላው ቀርቶ ገመድ ጭምር ስለያዙ በጣም ፈርተን ነበር። አስረው ወንዝ ውስጥ የሚጥሉን መስሎኝ ነበር። ጽሑፎቻችንን ብጭቅጭቅ አድርገው በታተኑ፣ የሸክላ ማጫወቻችንንም ጉቶ ላይ ፈጥፍጠው ሰባበሩብን።

ከገረፉን በኋላ ልብሳችንን ለብሰን ወደ ኋላ ዞር ሳንል በጫካው ውስጥ መንገዳችንን ይዘን እንድንሄድ ነገሩን። እየሄድን እያለ ገልመጥ ለማለት ብንሞክር ተኩሰው እንደሚገድሉንና ደማችን ደመ ከልብ ሆኖ እንደሚቀር አሰብን! ይሁን እንጂ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ መኪናቸውን አስነስተው ሲሄዱ ሰማን።

ሌላ ጊዜ ደግሞ በቁጣ የገነፈለ ሕዝብ ግልብጥ ብሎ ወጥቶ ያባርረን ጀመር። ስለዚህ ልብሳችንን በአንገታችን ላይ ጠምጥመን ወንዙን በዋና አቋርጠን አመለጥን። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ሕዝብን በመንግሥት ላይ ለመቀስቀስ ሞክረዋል በሚል ተከስሰን ታሰርን። ፍርድ ቤት ሳንቀርብ ለሦስት ሳምንት በእስር ቆየን። ወሬው በመላው ኮሎምበስ ውስጥ ተናፍሷል። ሌላው ቀርቶ በኮሎምበስ አቅራቢያ የሚገኝ የአንድ ኮሌጅ ተማሪዎች ችሎቱን ለመከታተል ቀደም ብለው ከክፍል እንዲወጡ ተፈቀደላቸው። በቀጠሮው ቀን ፍርድ ቤቱ ግጥም ብሎ ስለሞላ ያለው አማራጭ መቆም ብቻ ነበር! መንግሥት ሁለት ሰባኪዎችን፣ ከንቲባውንና ፖሊስ ለምሥክርነት አቁሞ ነበር።

ጂ ሲ ክላርክ የሚባል የይሖዋ ምሥክር የሆነ አንድ ጠበቃና ባልደረባው እኛን ወክለው ለመከራከር ተልከው መጡ። ሕዝብን በመንግሥት ላይ ለማነሳሳት ሞክረዋል የሚለው ክስ አንድም ማስረጃ ስለሌለው ፍርድ ቤቱ በነፃ እንዲያሰናብተን ጠየቁ። ከወንድም ክላርክ ጋር የሚሠራው ጠበቃ የይሖዋ ምሥክር ባይሆንም ስለ እኛ ጠንካራ የመከላከያ ሐሳብ አቀረበ። አንድ ጊዜ ዳኛውን “ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮች ንክ ናቸው ይላሉ። ንክ? ቶማስ ኤዲሰንም ንክ ተብሏል!” ከዚያም ወደ መብራቱ በማመልከት “ይህን አምፑል ይመልከቱ!” አለ። አምፑል የፈለሰፈውን ኤዲሰንን አንዳንዶች ንክ አድርገው ይቆጥሩት ይሆናል። እጅግ ጠቃሚ የሆነ ነገር ማበርከቱን ግን ማንም ሊክድ አይችልም።

የወረዳው ፍርድ ቤት የመሃል ዳኛ የምሥክሮችን ቃል ካደመጡ በኋላ አቃቤ ሕጉን “እነዚህ ሰዎች ሕዝብን በመንግሥት ላይ ለማነሳሳት ስለ መሞከራቸው አንድም ማስረጃ እንኳ ማቅረብ አልቻልክም፤ ስለዚህ ይህን ሥራ የመሥራት መብት አላቸው። ከዚህ በኋላ ማስረጃ እስካላገኘህ ድረስ እነዚህን ሰዎች እዚህ ችሎት ፊት አቅርበህ የመንግሥትን ሰዓትና ገንዘብ እንዲሁም የእኔን ጊዜ በከንቱ አታባክን!” አሉት። እኛ ረታን!

ሆኖም ከችሎቱ በኋላ ዳኛው ወደ ክፍላቸው አስጠሩን። የከተማው ሕዝብ በጠቅላላ ውሳኔያቸውን እንደሚቃወም ያውቃሉ። ስለሆነም “በሕጉ መሠረት ፈርጃለሁ፤ ሆኖም እኔ በግል የምመክራችሁ ግን ከተማውን ለቅቃችሁ ውጡ፤ ያለበለዚያ ይገድሏችኋል!” ሲሉ አስጠነቀቁን። የዳኛው አባባል ትክክል እንደሆነ እናውቅ ስለነበር ከተማውን ለቅቀን ሄድን።

ከዚያ በኋላ በቴኔሲ ክላርክስቪሌ በልዩ አቅኚነት በማገልገል ላይ ከነበሩት ከቤኔት እና ከቬልቫ ጋር መሥራት ጀመርኩ። ከጥቂት ወራት በኋላ በፓሪስ ኬንታኪ ተመደብን። እኔና ቤኔት አንድ ልዩ ግብዣ የቀረበልን በዚያ አካባቢ ዓመት ከመንፈቅ ሠርተን ጉባኤ ለማቋቋም ጥቂት ሲቀረን ነበር።

ወደ ሚስዮናዊ አገልግሎት

በጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ክፍል እንድንማር በደብዳቤ ጥሪ ሲቀርብልን ‘እነዚህ ሰዎች ተሳስተዋል! ሁለት ተራ የሚሲሲፒ ወጣቶችን እንዴት ወደዚህ ትምህርት ቤት ይጋብዛሉ?’ የሚል ሐሳብ መጣብን። የሚፈልጉት የተማሩ ሰዎች ብቻ መስሎን ነበር፤ ያም ሆነ ይህ ግብዣውን ተቀብለን ሄድን። በክፍሉ ውስጥ 100 ተማሪዎች የነበሩ ሲሆን ትምህርቱ አምስት ወር ይወስዳል። የምረቃው ሥነ ሥርዓት ጥር 31, 1944 ሲሆን በባዕድ አገር ተመድበን ለማገልገል ጓጉተን ነበር። ሆኖም በዚያ ወቅት ፓስፖርትና ቪዛ ማግኘት ረጅም ጊዜ ይወስድ ስለነበረ ከምረቃው በኋላ ተማሪዎች በጊዜያዊነት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ይመደባሉ። እኔና ቤኔት በአላባማና በጆርጂያ ለተወሰነ ጊዜ በአቅኚነት ካገለገልን በኋላ በመጨረሻ ዌስት ኢንዲስ ባርባዶስ ተመደብን።

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እንደቀጠለ ሲሆን ባርባዶስን ጨምሮ በብዙ አገሮች በይሖዋ ምሥክሮች ሥራና በጽሑፎቻቸው ላይ እገዳ ተጥሎ ነበር። ጉምሩክ ላይ ባለሥልጣኖች የያዝናቸውን ሻንጣዎች ሲፈትሹ የደበቅናቸውን ጽሑፎች አገኙ። ‘አለቀልን’ ብለን አሰብን። ሆኖም አንደኛው ባለሥልጣን “ዕቃችሁን በመበርበራችን እናዝናለን፤ እነዚህ ጽሑፎችን ወደ ባርባዶስ ማስገባት ክልክል ነው” አለን። ያም ሆኖ ጽሑፎቹን በሙሉ ይዘን እንድናልፍ ፈቀደልን! ከጊዜ በኋላ ለመንግሥት ባለሥልጣናት ስንመሠክር በጽሑፎቹ ላይ እገዳ የተጣለበትን ምክንያት እንደማያውቁ ነገሩን። እገዳው ከጥቂት ወራት በኋላ ተነሳ።

በባርባዶስ አገልግሎታችን አመርቂ ውጤት አስገኝቷል። እያንዳንዳችን 15 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እንመራ የነበረ ሲሆን ብዙዎቹ ጥናቶቻችን በመንፈሳዊ እድገት አድርገዋል። አንዳንዶቹ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት በመጀመራቸው ተደስተናል። ይሁን እንጂ ጽሑፎች ታግደው ስለነበር ወንድሞች ስብሰባዎች እንዴት እንደሚመሩ አያውቁም ነበር። ሆኖም በአጭር ጊዜ ውስጥ ጥሩ ችሎታ ያላቸው በርካታ ወንድሞች ማሰልጠን ቻልን። ብዙ ጥናቶቻችን በክርስቲያናዊ አገልግሎት መካፈል እንዲጀምሩና ጉባኤው እድገት እንዲያደርግ በመርዳታችን ተደስተናል።

ቤተሰብ ማስተዳደር

በባርባዶስ ዓመት ከስድስት ወር ገደማ ከቆየሁ በኋላ ቀዶ ሕክምና ማድረግ ስላስፈለገኝ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መመለስ ግድ ሆነብኝ። እዚያም በደብዳቤ እንጻጻፍ የነበረችውን ዶርቲ የምትባል የይሖዋ ምሥክር አገባሁ። ከዚያም ባለቤቴና እኔ ታላሃሲ ፍሎሪዳ ውስጥ በአቅኚነት ያገለገልን ሲሆን ከስድስት ወር በኋላ አንድ የይሖዋ ምሥክር ሥራ ስላገኘልኝ ወደ ኬንታኪ ሊዊቬል ተዛወርን። ወንድሜ ቤኔት እዚያው ባርባዶስ ቆይቶ ለብዙ ዓመታት አገልግሏል። ከጊዜ በኋላ እሱም አንዲት ሚስዮናዊ አግብቶ በአቅራቢያው ባሉ ደሴቶች በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ማገልገል ቀጠለ። የኋላ ኋላ በጤና ማጣት ምክንያት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመለሱ። ቤኔት በ1990 በ73 ዓመቱ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ በስፓንኛ ተናጋሪ ጉባኤዎች ውስጥ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት አገልግሏል።

ዶርቲ በ1950 የመጀመሪያ ልጃችንን ዳርሊን ወለደች። በመጨረሻም አምስት ልጆችን የወለድን ሲሆን ሁለተኛው ልጃችን ዴሪክ በሁለት ዓመት ከስድስት ወሩ በማጅራት ገትር በሽታ ሞተብን። ሆኖም ሌስሊ በ1956 እንዲሁም ኤቨረት በ1958 ተወለዱ። እኔና ዶርቲ ልጆቻችንን በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት መሠረት ለማሳደግ ጥረት አድርገናል። ሳምንታዊ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራማችንን ለመከተልና ጥናቱን ለልጆቹ አስደሳች አድርገን ለማቅረብ ሁልጊዜ ጥረት እናደርግ ነበር። ዳርሊ፣ ሌስሊ እና ኤቨረት ልጆች እያሉ ምርምር አድርገው ከሳምንት በኋላ መልስ እንዲሰጡ በየጊዜው ጥያቄዎች እንጠይቃቸዋለን። እንዲሁም ከቤት ወደ ቤት እንደሚያገለግሉ አስመስለው ያሳዩናል። አንደኛው ቁም ሳጥን ውስጥ ይገባና ባለቤት ይሆናል። ሌላው ከውጪ ቆሞ ያንኳኳል። አንዱ ሌላውን ለማሳመን አስቂኝ ቃላትን ይጠቀማል፤ ሆኖም ሁኔታው ለስብከቱ ሥራ ፍቅር እንዲያድርባቸው ረድቷቸዋል። እኛም ዘወትር አብረናቸው እንሰብካለን።

በ1973 የመጨረሻው ልጃችን ኤልተን ሲወለድ ዶርቲ 50 እኔ ደግሞ 60 ዓመት ሆኖን ነበር። የጉባኤያችን ወንድሞችና እህቶች ውስጥ አብርሃምና ሣራ ብለው ይጠሩናል! (ዘፍጥረት 17:​15-17) ብዙውን ጊዜ ታላላቆቹ ኤልተንን አገልግሎት ይዘውት ይወጡ ነበር። ወንድማማቾችና እህትማማቾች፣ ወላጆችና ልጆች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማካፈል በአንድነት መሥራታቸው ለሌሎች ትልቅ ምሥክርነት እንደሚሰጥ ይሰማናል። ታላላቆቹ ለኤልተን ትራክት ይሰጡትና በየተራ እሽኮኮ ይሉታል። ሰዎች በራቸውን ከፍተው የደስ ደስ ያለው ትንሽ ልጅ ታላቅ ወንድሙ እሽኮኮ ብሎት ሲመለከቱ ሁልጊዜ ማለት ይቻላል የሚነገራቸውን ያዳምጡ ነበር። ውይይቱ ሲያበቃ ኤልተን ትራክቱን ለሰውዬው ሰጥቶ ጥቂት ቃላትን እንዲናገር አስተምረውታል። ስብከት የጀመረው በዚህ ሁኔታ ነበር።

ሰዎች ይሖዋን እንዲያውቁ ለብዙ ዓመታት ስንረዳ ቆይተናል። በ1970ዎቹ መገባደጃ ላይ ይበልጥ እርዳታ በሚያስፈልገው ጉባኤ ለማገልገል ከሊዊቬል ወደ ሼልቢቬል ኬንታኪ ተዛወርን። እዚያም ጉባኤው እድገት ሲያደርግ ብቻ ሳይሆን መሬት አግኝተን የመንግሥት አዳራሽ እንድንሠራም እገዛ አድርጌያለሁ። በኋላ ከዚያ ብዙም በማይርቅ ሌላ ጉባኤ ውስጥ እንድናገለግል ተጠየቅን።

በቤተሰባችን ውስጥ ያጋጠሙን ያልተጠበቁ ሁኔታዎች

ልጆቼ በሙሉ በይሖዋ መንገድ መመላለሳቸውን ቀጥለዋል ብዬ መናገር ብችል እንዴት ደስ ባለኝ ነበር፤ ዳሩ ምን ያደርጋል አልሆነም። አድገው ራሳቸውን ከቻሉ በኋላ በሕይወት ካሉት አራት ልጆቻችን መካከል ሦስቱ የእውነትን መንገድ ትተዋል። ይሁን እንጂ ልጃችን ኤቨረት የእኔን አርዓያ ተከትሎ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመረ። ከጊዜ በኋላ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ያገለገለ ሲሆን በ1984 በጊልያድ 77ኛ ክፍል እንዲካፈል ተጠራ። ከተመረቀ በኋላ በምዕራብ አፍሪካ በምትገኘው በሴራ ሊዮን ተመደበ። በ1988 ማርዮን የምትባል ከቤልጅየም የመጣች አቅኚ አገባ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በሚስዮናዊነት አብረው አገልግለዋል።

ሦስቱ ልጆቻችን በአሁኑ ጊዜ እርካታ ወደፊት ደግሞ ገነት በምትሆነው ምድር የዘላለም ሕይወት የማግኘት አስደሳች ተስፋ ካዘለው የሕይወት መንገድ መውጣታቸው እንደ ማንኛውም ወላጅ ሁሉ እኛንም አሳዝኖናል። አንዳንድ ጊዜ ራሴን እወቅሳለሁ። ሆኖም ይሖዋ ፍጡሮቹን በፍቅርና በደግነት የሚይዝ እንዲሁም ፈጽሞ የማይሳሳት ቢሆንም አንዳንድ መንፈሳዊ ልጆቹ ወይም መላእክት እሱን ማገልገል እንዳቆሙ ሳስብ እጽናናለሁ። (ዘዳግም 32:​4፤ ዮሐንስ 8:​44፤ ራእይ 12:​4, 9) ይህ ሁኔታ አንድ ወላጅ ልጆቹን በይሖዋ መንገድ ለማሳደግ ምንም ያክል ቢጥር አንዳንድ ልጆች እውነትን ከመቀበል ወደኋላ ሊሉ እንደሚችሉ አስገንዝቦኛል።

ዛፍ ኃይለኛ ነፋስ ሲነፍስ ዘንበል ብሎ እንደሚያሳልፈው ሁሉ እኛም መከራና ችግር ሲያጋጥመን እንደአመጣጡ ማሳለፍን ተምረናል። መጽሐፍ ቅዱስን ዘወትር ማጥናትና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ባለፉት ዓመታት ችግሮችን እንደ አመጣጣቸው ለማሳለፍና መንፈሳዊ መዳን ለማግኘት ብርታት ጨምሮልናል። በዕድሜ እየገፋሁ ስሄድ ቀደም ሲል የሠራኋቸው ስህተቶች ትዝ ሲሉኝ በመልካም ጎኑ ልመለከተው እሞክራለሁ። ደግሞም ታማኝ ሆነን ከቀጠልን እንደዚህ ያሉ ተሞክሮዎች ለመንፈሳዊ እድገት ይረዳሉ። እኛ የምንማር ከሆንን አሉታዊ የሆኑ የሕይወት ገጠመኞች አንድ አዎንታዊ የሆነ ነገር አስተምረው ሊያልፉ ይችላሉ።​—⁠ያዕቆብ 1:​2, 3

አሁን እኔና ዶርቲ እንደዱሮው በይሖዋ አገልግሎት የምንፈልገውን ያህል ለመካፈል የሚያስችል ጤንነትና ብርታት የለንም። ሆኖም ክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የሚያደርጉልንን ድጋፍ በእጅጉ እናደንቃለን። ወንድሞች ስብሰባ ላይ ባገኙን ቁጥር እዚያ መገኘታችን በጣም እንዳስደሰታቸው ይነግሩናል። ቤታችንንና መኪናችንን ከመጠገን አንስቶ በሚቻላቸው ሁሉ እየረዱን ናቸው።

አልፎ አልፎ ረዳት አቅኚ ሆነን የምናገለግል ሲሆን ፍላጎት ያላቸውን ሰዎችም እናስጠናለን። አፍሪካ ተመድቦ ስለሚያገለግለው ልጃችን አዲስ ነገር ስንሰማ በጣም ደስ ይለናል። ቤት ውስጥ ያለነው ሁለታችን ብቻ ብንሆንም የቤተሰብ ጥናታችን አልተቋረጠም። በእነዚህ ሁሉ ዓመታት ይሖዋን ማገልገል በመቻላችን በጣም ደስተኞች ነን። ይሖዋ ‘ያደረግነውን ሥራና ለስሙ ያሳየነውን ፍቅር እንደማይረሳ’ ማረጋገጫ ሰጥቶናል።​—⁠ዕብራውያን 6:​10

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቴድ ክሌይን ሚያዝያ 18, 1940 እኔን፣ ቬልቫን እና ቤኔትን ሲያጠምቀን

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1940ዎቹ መጀመሪያ ላይ እና በ1997 ከባለቤቴ ከዶርቲ ጋር

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የሰላሙ መስፍን” በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን የሕዝብ ንግግር በባርባዶስ የከተማ አውቶቡስ ስናስተዋውቅ

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወንድሜ ቤኔት በሚስዮናውያን ቤት ፊት ለፊት ቆሞ