አንድ መነጽር ሠሪ የዘራው ዘር
አንድ መነጽር ሠሪ የዘራው ዘር
በዩክሬይን ለቪፍ የሚኖር አንድ መነጽር ሠሪ ያደረገው ጥረት ከተወሰኑ አገሮች ባሻገር 2, 000 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ በምትገኘው በእስራኤሏ ሃይፋ ከተማ ከተቋቋመ የይሖዋ ምሥክሮች የሩስያ ቋንቋ ጉባኤ ጋር ምን ግንኙነት አለው? ይህ ጉዳይ በመክብብ 11:6 ላይ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ትክክል መሆኑን የሚያሳይ ታሪክ ነው:- “ማናቸው እንዲበቅል . . . አታውቅምና በማለዳ ዘርህን ዝራ፣ በማታም እጅህን አትተው።”
የታሪኩ መነሻ በዝርያዋ አይሁዳዊ የሆነችው ወጣቷ ኤላ በለቪፍ ትኖር ወደነበረበት ወቅት ይመልሰናል። ጊዜው 1990 ሲሆን ኤላና ቤተሰቧ ጓዛቸውን ጠቅልለው ወደ እስራኤል ለመሄድ በዝግጅት ላይ ነበሩ። መሄጃቸው ከመድረሱ ከጥቂት ጊዜ በፊት ኤላ የይሖዋ ምሥክር የሆነ መነጽር ሠሪ ዘንድ ቀጠሮ ነበራት። በዚያን ወቅት በዩክሬይን የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በእገዳ ሥር ነበር። ቢሆንም መነጽር ሠሪው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ እምነቱን ለኤላ
ለማካፈል ውይይት ከፈተ። አምላክ የግል ስም እንዳለው ሲነግራት ተገረመች። ይህ የኤላን ጉጉት የቀሰቀሰ ከመሆኑም በላይ አስደሳች የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይት አደረጉ።ኤላ በውይይቱ በጣም ከመደሰቷ የተነሳ በቀጣዩ ሳምንት ለመገናኘት ዝግጅት ያደረገች ሲሆን ከዚያ በኋላም እንደገና ለመገናኘት ሌላ ቀጠሮ ያዘች። ፍላጎቷ እያደገ ሄደ፤ ሆኖም አንድ ችግር ገጠማት። ቤተሰቡ ወደ እስራኤል የሚሄድበት ጊዜ በፍጥነት ቀረበ። ኤላ ማወቅ ያለባት ብዙ ነገር ይቀራታል! የቀረውን ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ለመጠቀም እስከምትሄድበት ቀን ድረስ በየቀኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግላት ጠየቀች። ኤላ መጀመሪያ እስራኤል እንደደረሰች ጥናቷን ባትቀጥልም እንኳ የእውነት ዘር በልቧ ሥር ሰድዶ ነበር። በዓመቱ መገባደጃ ላይ እንደገና መጽሐፍ ቅዱስን በቁም ነገር ማጥናቷን ቀጠለች።
በፋርስ ባሕረ ሰላጤ ጦርነት ሲፈነዳ እስራኤል ከኢራቅ በተወነጨፉ ሚሳኤሎች ተደበደበች። ይህ ሰዎችን ሁሉ የሚያነጋግር ጉዳይ ሆኖ ነበር። አንድ ቀን የገበያ አዳራሽ ውስጥ ኤላ በቅርቡ ወደ እስራኤል የመጡ ሩሲያኛ ተናጋሪ ቤተሰብ የሚያወሩት ጉዳይ ድንገት ወደ ጆሮዋ ጥልቅ አለ። ኤላ ገና መጽሐፍ ቅዱስ እያጠናች ብትሆንም እንኳ ወደዚህ ቤተሰብ ቀርባ መጽሐፍ ቅዱስ ሰላም የሰፈነበት ዓለም እንደሚመጣ ስለሚናገረው ተስፋ ነገረቻቸው። ከዚህ የተነሳ አያትየው ጋሊና፣ እናትየው ናታሻ፣ ወንዱ ልጅ ሳሻ (አሪኤል) እና ሴቷ ልጅ ኢላና፣ በኤላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ መገኘት ጀመሩ።
ሳሻ ብዙ ፈተናዎች ቢገጥሙትም ወደ ጥምቀት ደረጃ ለመድረስ የመጀመሪያው የቤተሰቡ አባል ሆነ። ምንም እንኳ የላቀ ውጤት የሚያመጣ ተማሪ ቢሆንም በትምህርት ቤቱ ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ የተካተተውንና ግዴታ የሆነውን ለውትድርና የሚያዘጋጅ ሥልጠና ለመውሰድ ክርስቲያናዊ ህሊናው ስላልፈቀደለት ከትምህርት ቤት ተባረረ። (ኢሳይያስ 2:2-4) የሳሻ ጉዳይ በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው የእስራኤል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተመራ ሲሆን ፍርድ ቤቱ ሳሻ ትምህርቱን ማጠናቀቅ እንዲችል ወደ ትምህርት ገበታው እንዲመለስ ወሰነ። ወሬው በመላ አገሪቱ በስፋት ተናፈሰ። ከዚህ የተነሳ ብዙ እስራኤላውያን ስለ ይሖዋ ምሥክሮች እምነት ማወቅ ቻሉ። a
ሳሻ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ በይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተሠማራ። ዛሬ ልዩ አቅኚና የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ ያገለግላል። እህቱ ኢላና እንደ እሱ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተሠማርታለች። እናታቸውና አያታቸው ሁለቱም የተጠመቁ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። መነጽር ሠሪው የዘራው ዘር ፍሬ ማፍራቱን ቀጥሎ ነበር!
በመሀሉ ኤላ መንፈሳዊ እድገት ማድረጓን የቀጠለች ሲሆን ብዙም ሳይቆይ ከቤት ወደ ቤት መስበክ ጀመረች። ኤላ የመጀመሪያውን በር ስታንኳኳ በቅርቡ ከዩክሬይን የመጣችውን ፋኢናን አገኘቻት። ፋኢና የመንፈስ ጭንቀት ነበረባት። ኤላ የፋኢናን በር ከማንኳኳቷ ከጥቂት ጊዜ በፊት ይህች በጭንቀት የተዋጠች ሴት “ማን መሆንህን አላውቅም፤ የምትሰማኝ ከሆንክ ግን እርዳኝ” ስትል ወደ አምላክ ጸልያ እንደነበር ከጊዜ በኋላ አወቀች። ከኤላ ጋር አስደሳች ውይይት አደረጉ። ፋኢና በርካታ ጥያቄዎች ያቀረበች ከመሆኑም በላይ የተሰጣትን መልስ በጥንቃቄ አጤነች። ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንደሚያስተምሩ አምና ተቀበለች። ከጉባኤው ጋር እና በስብከቱ ሥራ ሰፋ ያለ ጊዜ ማሳለፍ እንድትችል የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን የምትከታተልበትን ፕሮግራም አስተካከለች። ፋኢና ግንቦት 1994 ላይ ተጠመቀች። በኮምፒውተር መስክ የግማሽ
ቀን ሥራ በመሥራት ራሷን እየረዳች እሷም በአቅኚነት አገልግሎት ተሠማራች።ኅዳር 1994 ላይ ኤላ በስብከቱ ሥራ ተሠማርታ እያለች ድንገት በጠና ታመመች። ሆስፒታል ሄዳ በተደረገላት ምርመራ የደም መፍሰስ ችግር የሚያስከትል የአንጀት አልሰር እንደያዛት ታወቀ። አመሻሹ ላይ የኤላ የሄሞግሎቢን መጠን ወደ 7.2 ወርዶ ነበር። ኤላ ባለችበት ጉባኤ የሚገኝ የአካባቢ ሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ (HLC) ሊቀ መንበር የሆነ አንድ ሽማግሌ ለዶክተሮቹ ያለ ደም የሚካሄዱ በርካታ የሕክምና አሠራሮችን አስመልክተው የወጡ ጽሑፎችን ሰጣቸው። b ኤላ በተሳካ ሁኔታ ያለ ደም ቀዶ ሕክምና የተደረገላት ከመሆኑም በላይ ሙሉ በሙሉ አገገመች።—ሥራ 15:28, 29
የኤላ የማሕፀን ሐኪም የሆነው አይሁዳዊው የጀርመን ተወላጅ ካርል በሁኔታው በጣም ተገረመ። በኋላም ከናዚዎች ጭፍጨፋ የተረፉት ወላጆቹ የይሖዋ ምሥክሮችን ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ ያውቋቸው እንደነበር ትዝ አለው። ካርል በርካታ ጥያቄዎችን አቀረበ። ምንም እንኳ ካርል ጊዜው በሕክምና ሙያው የተጣበበ ቢሆንም በቋሚነት መጽሐፍ ቅዱስ የሚያጠናበት ጊዜ መደበ። በቀጣዩ ዓመት በሳምንታዊ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመረ።
መነጽር ሠሪው የዘራው ዘር ያስገኘው ውጤት ምን ሆነ? ሳሻና ቤተሰቡ ምን ላይ እንደደረሱ ቀደም ሲል አይተናል። ኤላ ደግሞ በልዩ አቅኚነት ታገለግላለች። በቅርቡ የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው ሴት ልጅዋ ኢና አቅኚ ሆና ማገልገል ጀምራለች። ፋኢናም ልዩ አቅኚ ሆና ታገለግላለች። የኤላ የማሕፀን ሐኪም የሆነው ካርል በአሁኑ ጊዜ የተጠመቀ ምሥክርና የጉባኤ አገልጋይ ሲሆን ለታካሚዎቹና ለሌሎች ሰዎች የመፈወስ ኃይል ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በማካፈል ላይ ይገኛል።
የሃይፋ የዕብራይስጥ ጉባኤ ክፍል ሆኖ እንቅስቃሴውን የጀመረው በእስራኤል የሰፈሩ የሩስያኛ ተናጋሪዎች ትንሽ ቡድን በአሁኑ ጊዜ ከ120 በላይ የመንግሥቱን አስፋፊዎች ያቀፈ ቀናተኛ የሩስያ ቋንቋ ጉባኤ ሆኗል። በተወሰነ መጠን ይህ ጭማሪ ሊገኝ የቻለው በለቪፍ የሚኖር አንድ መነጽር ሠሪ ዘር ለመዝራት የሚያስችለውን አጋጣሚ በመጠቀሙ ነው!
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የኅዳር 8, 1994 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 12-15ን ተመልከት።
b የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች በታካሚውና በሆስፒታል ባለሙያዎች መካከል መግባባት እንዲፈጠር በመርዳት በዓለም ዙሪያ የይሖዋ ምሥክሮችን ወክለው ይቀርባሉ። በተጨማሪም በአዳዲስ የሕክምና ግኝቶች ላይ የተመሠረቱ አማራጭ የሕክምና ዘዴዎችን በተመለከተ መረጃ ያቀርባሉ።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ዩክሬይን
እስራኤል
[ምንጭ]
Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤላ እና ሴት ልጅዋ ኢና
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሃይፋ የሚገኝ ደስተኛ የሩሲያኛ ተናጋሪ ምሥክሮች ቡድን። ከግራ ወደ ቀኝ:- ሳሻ፣ ኢላና፣ ናታሻ፣ ጋሊና፣ ፋኢና፣ ኤላ፣ ኢና እና ካርል