በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አደጋ በተሞላ ዓለም አስተማማኝ ሕይወት ማግኘት

አደጋ በተሞላ ዓለም አስተማማኝ ሕይወት ማግኘት

አደጋ በተሞላ ዓለም አስተማማኝ ሕይወት ማግኘት

ፈንጂ በተቀበረበት አካባቢ መጓዝ አደገኛ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ፈንጂዎቹ የተቀበሩባቸውን ቦታዎች የሚያሳይ ካርታ ብታገኝ አትጠቀምም? በተጨማሪም የተለያየ ዓይነት ያላቸውን ፈንጂዎች መለየት የሚያስችል ሥልጠና ወስደህስ ከሆነ? ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ይህን የመሰለው እውቀት ለአካል ጉዳተኝነት ወይም ለሞት የመጋለጥህን አጋጣሚ በእጅጉ ሊቀንሰው ይችላል።

መጽሐፍ ቅዱስ ከካርታውና ፈንጂዎቹ የተቀበሩበትን ቦታ ለመለየት ከሚያስችለው ሥልጠና ጋር ሊመሳሰል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ከአደጋዎች መራቅ እንዲሁም በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች መወጣት የምንችልበትን መንገድ በተመለከተ አቻ የማይገኝለት ጥበብ ይዟል።

በምሳሌ 2:​10, 11 ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን አጽናኝ ተስፋ ተመልከት:- “ጥበብ ወደ ልብህ ትገባለችና፣ እውቀትም ነፍስህን ደስ ታሰኛለችና፤ ጥንቃቄ ይጠብቅሃል፣ ማስተዋልም ይጋርድሃል።” እዚህ ላይ የተጠቀሱት ጥበብና ማስተዋል ምንጫቸው ሰብዓዊ ሳይሆን መለኮታዊ ነው። “የሚሰማኝ [አምላካዊ ጥበብን ማለት ነው] ግን በእርጋታ ይቀመጣል፣ ከመከራም ሥጋት ያርፋል።” (ምሳሌ 1:​33) እስቲ መጽሐፍ ቅዱስ ደህንነታችን አስተማማኝ እንዲሆንና ብዙዎቹን ችግሮች እንድናስወግድ ሊረዳን የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።

ሞት ሊያስከትሉ ከሚችሉ አደጋዎች መጠበቅ

በቅርቡ የዓለም የጤና ድርጅት (WHO) ያወጣው አሃዝ በዓለም ዙሪያ በመኪና አደጋ ሳቢያ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር በዓመት ወደ 1, 171, 000 አካባቢ እንደሚደርስ ያሳያል። ወደ 40 ሚልዮን የሚጠጉ ሌሎች ሰዎች የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን ከ8 ሚልዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ ዘላቂ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል።

መኪና በምንነዳበት ወቅት ሙሉ በሙሉ ከአደጋ መጠበቅ እንችላለን ማለት ባይሆንም የትራፊክ ሕጎችን መታዘዛችን የተሻለ ዋስትና ሊያስገኝልን ይችላል። የትራፊክ ሕጎችን የሚያወጡትንና የሚያስፈጽሙትን የመንግሥት ባለ ሥልጣናት አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣኖች ይገዛ።” (ሮሜ 13:​1) ብዙውን ጊዜ ከዚህ ምክር ጋር ተስማምተው በሚነዱ አሽከርካሪዎች ላይ አሰቃቂ አደጋ የመድረሱ አጋጣሚ በእጅጉ ይቀንሳል።

በጥንቃቄ እንድንነዳ የሚገፋፋን ሌላው ምክንያት ደግሞ ለሕይወት ያለን አክብሮት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ሲናገር “የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነው” ይላል። (መዝሙር 36:​9) ስለዚህ ሕይወት መለኮታዊ ስጦታ ነው። በመሆኑም ይህንን ስጦታ ከማንም ላይ የመውሰድም ሆነ ሕይወትን አቅልሎ የመመልከት መብት የለንም። እርግጥ ይህ የራሳችንንም ሕይወት ይጨምራል።​—⁠ዘፍጥረት 9:​5, 6

ለሰብዓዊ ሕይወት አክብሮት ማሳየት ማለት መኪናችንና ቤታችን በተቻለ መጠን ለአደጋ የሚያጋልጡ አለመሆናቸውን በሚገባ ማረጋገጥንም ይጨምራል። በጥንቱ የእስራኤል ሕዝብ መካከል ጥንቃቄ በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ቅድሚያ የሚሰጠው ነገር ነበር። ለምሳሌ፣ አንድ ቤት በሚሠራበት ወቅት ቤተሰቡ ብዙ ነገር የሚያከናውንበት የቤቱ ጣሪያ መከታ እንዲኖረው የአምላክ ሕግ ያዝዝ ነበር። “ማንም ከእርሱ ወድቆ ደሙን በቤትህ ላይ እንዳታመጣ በጣራው ዙሪያ መከታ አድርግለት።” (ዘዳግም 22:​8) ለጥንቃቄ ሲባል የተሰጠው ይህ ሕግ ሳይጠበቅ ቀርቶ አንድ ሰው ከጣሪያው ላይ ቢወድቅ አምላክ የቤቱን ባለቤት ተጠያቂ ያደርገው ነበር። በዚህ ሕግ ውስጥ የተንጸባረቀውን ፍቅራዊ መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ በሥራ ቦታ እንዲሁም በመዝናኛ ቦታ እንኳ ሳይቀር ሊደርስ የሚችለውን አደጋ እንደሚቀንስ ምንም ጥርጥር የለውም።

ሞት ከሚያስከትሉ ሱሶች መራቅ

የዓለም የጤና ድርጅት እንዳመለከተው ከሆነ በአሁኑ ጊዜ በዓለም ውስጥ ከአንድ ቢልዮን በላይ አጫሾች ይገኛሉ። በዓመት ወደ አራት ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች ትምባሆ ባስከተለው መዘዝ ሳቢያ የሚሞቱ ሲሆን ይህ ቁጥር በሚቀጥሉት 20 እና 30 ዓመታት ውስጥ ወደ 10 ሚልዮን ከፍ እንደሚል ይገመታል። ሌሎች በሚልዮን የሚቆጠሩ አጫሾችና ‘ያዝናናሉ የሚባልላቸውን’ ዕፆች የሚወስዱ ሰዎች ደግሞ በዚህ ሱስ ምክንያት ጤንነታቸው ይቃወሳል እንዲሁም ሕይወታቸው ይመሰቃቀላል።

የአምላክ ቃል ትምባሆንና አደገኛ ዕፆችን አስመልክቶ በቀጥታ የሚናገረው ነገር ባይኖርም መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ከእነዚህ ልማዶች ሊጠብቁን ይችላሉ። ለምሳሌ 2 ቆሮንቶስ 7:​1 የሚከተለውን ምክር ይሰጣል:- “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ።” ትምባሆና አደገኛ ዕፆች አካላችንን ጎጂ በሆኑ በርካታ ኬሚካሎች እንደሚበክሉት ወይም እንደሚያረክሱት ምንም ጥርጥር የለውም። ከዚህም በተጨማሪ አምላክ ሰውነታችን “ቅዱስ” እንዲሆን ማለትም ንጹህና የጸዳ እንዲሆን ይፈልጋል። (ሮሜ 12:​1) እነዚህን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረግ አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ሊያጋጥሙት የሚችሉትን የጎሉ አደጋዎች ይቀንሳል ቢባል አትስማማም?

አደገኛ ልማዶችን ማሸነፍ

ብዙ ሰዎች በምግብና በመጠጥ ረገድ ሚዛናቸውን አይጠብቁም። ከመጠን በላይ መብላት የስኳር በሽታ፣ ካንሰር እና የልብ ህመም ሊያስከትል ይችላል። የአልኮል መጠጦችን አላግባብ መውሰድ ደግሞ ለመጠጥ ሱስ፣ ለኮምትሬ (cirrhosis)፣ ለቤተሰብ መፈራረስ፣ ለትራፊክ አደጋዎችና ለመሳሰሉት ተጨማሪ ችግሮች ይዳርጋል። በሌላው በኩል ደግሞ እወፍራለሁ በሚል ስጋት የተሳሳተ የአመጋገብ ልማድ ማዳበር አደገኛ ሊሆን አልፎ ተርፎም እንደ አኖሬክሲያ ነርቮሳ የመሰሉ ለሕይወት አስጊ የሆኑ የአመጋገብ ልማድ መዛባት ችግሮች ሊያስከትል ይችላል።

መጽሐፍ ቅዱስ የሕክምና መጽሐፍ ባይሆንም እንኳ በመብላትና በመጠጣት ረገድ ልከኛ የመሆንን አስፈላጊነት አስመልክቶ ቀጥተኛ ምክር ይሰጣል። “ልጄ ሆይ፣ ስማ ጠቢብም ሁን፣ ልብህንም በቀናው መንገድ ምራ። የወይን ጠጅ ከሚጠጡ ጋር አትቀመጥ ለሥጋም ከሚሣሡ ጋር፤ ሰካርና ሆዳም ይደኸያሉና።” (ምሳሌ 23:​19-21) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ መብላትና መጠጣት አስደሳች ነገር እንደሆነ ይናገራል። “ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ ደስ ይለው ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው።”​—⁠መክብብ 3:​13

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት እንደሚጠቅም’ በመጥቀስ አካላዊ እንቅስቃሴ ስለማድረግ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን ያበረታታል። አክሎም “እግዚአብሔርን መምሰል [“ለአምላክ ያደሩ መሆን፣” NW ] ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው፣ ለነገር ሁሉ ይጠቅማል” በማለት ይናገራል። (1 ጢሞቴዎስ 4:​8) ታዲያ ‘ለአምላክ ያደሩ መሆን አሁንም እንኳ የሚጠቅመው’ እንዴት ነው? በማለት ትጠይቅ ይሆናል። በብዙ መንገዶች ይጠቅማል። በጣም አስፈላጊ የሆነውን የአንድን ሰው መንፈሳዊ አድማስ ከማስፋቱም በላይ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላምና ራስን መግዛት የመሳሰሉትን ጠቃሚ ባሕርያት ለማፍራት ያስችላል። እነዚህ ባሕርያት ደግሞ አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝና ለጥሩ ጤንነት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ።​—⁠ገላትያ 5:​22, 23

የጾታ ብልግና የሚያስከትላቸው አስከፊ መዘዞች

በዛሬው ጊዜ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የሥነ ምግባር ደንብ የሚባለውን ነገር ሁሉ እርግፍ አድርገው ትተውታል። የኤድስ ወረርሽኝ የዚህ አንዱ ውጤት ነው። የዓለም የጤና ድርጅት እንዳለው ከሆነ የኤድስ ወረርሽኝ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስከ አሁን ከ16 ሚልዮን የሚልቁ ሰዎች በበሽታው የሞቱ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ወደ 34 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች ኤድስ አማጭ በሆነው በኤች አይ ቪ ቫይረስ ተለክፈዋል። ብዙዎቹ የኤድስ ተጠቂዎች በበሽታው የተያዙት የሴሰኝነት ኑሮ በመኖራቸው፣ የአደገኛ ዕፅ ሱሰኞች በተጠቀሙባቸው የተበከሉ መርፌዎች በመጠቀማቸው ወይም የተበከለ ደም በመውሰዳቸው ምክንያት ነው።

ልቅ የፆታ ግንኙነት ከሚያስከትላቸው ሌሎች መዘዞች መካከል ኸርፒዝ፣ ጨብጥ፣ ሄፓታይተስ ቢ እና ሲ እንዲሁም ቂጥኝ ይገኙበታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን እንዲህ ያሉት የሕክምና አጠራሮች አይታወቁ እንጂ በጾታ ግንኙነት የሚተላለፉት በጊዜው የተለመዱ አንዳንድ በሽታዎች የሚያጠቋቸው የሰውነት ክፍሎች ይታወቁ ነበር። ለምሳሌ ያህል ምሳሌ 7:​23 ዝሙት የሚያስከትለውን አስከፊ ውጤት ‘ጉበትን እንደሚሰነጥቅ ፍላጻ’ አድርጎ ይገልጸዋል። አብዛኛውን ጊዜ ሄፓታይተስ ጉበትን እንደሚያጠቃ ሁሉ ቂጥኝም የሚያጠቃው ጉበትን ነው። አዎን፣ ክርስቲያኖች ‘ከደምና ከዝሙት’ እንዲርቁ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር ምንኛ ወቅታዊና ፍቅራዊ ነው!​—⁠ሥራ 15:​28, 29

ገንዘብን መውደድ የሚያስከትለው ወጥመድ

ብዙ ሰዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ ሃብታም ለመሆን በማሰብ ገንዘባቸውን ሊያሟጥጡባቸው የሚችሉ እርምጃዎች ይወስዳሉ። የሚያሳዝነው እንዲህ ያሉትን አደገኛ እርምጃዎች መውሰድ ብዙውን ጊዜ ለኪሳራ ወይም ለድህነት ይዳርጋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ አንድን የአምላክ አገልጋይ በተመለከተ “ለጐደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም” ይላል። (ኤፌሶን 4:​28) እውነት ነው፣ ጠንካራ ሠራተኛ ሁልጊዜ ሃብታም ይሆናል ማለት አይደለም። ሆኖም እንዲህ ያለው ሰው የአእምሮ ሰላምና ለራሱ አክብሮት ሊኖረው ከመቻሉም በላይ በጎ ለሆነ ዓላማ ሊውል የሚችል ገንዘብም ሊኖረው ይችላል።

መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ያስጠነቅቃል:- “ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ [“የቆረጡ፣” NW  ] በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፣ አንዳንዶችም ይህን ሲመኙ፣ . . . በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ።” (1 ጢሞቴዎስ 6:​9, 10) ‘ባለ ጠጎች ለመሆን የቆረጡ’ ብዙዎች ሃብት እንደሚያገኙ አይካድም። ይሁን እንጂ ይህ ምን ዋጋ አስከፍሏቸዋል? ጤናቸው፣ የቤተሰብ ሕይወታቸው፣ መንፈሳዊነታቸውና እንቅልፋቸው ሳይቀር መቃወሱ እውነት አይደለምን?​—⁠መክብብ 5:​12

አስተዋይ ሰው “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት” እንዳልሆነ ይገነዘባል። (ሉቃስ 12:​15) በብዙ ኅብረተሰቦች ዘንድ ገንዘብና አንዳንድ ቁሳዊ ንብረቶች አስፈላጊ ነገሮች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስም “ገንዘብ ጥላ” እንደሆነ ይናገራል። ሆኖም አክሎ “የእውቀትም ብልጫዋ ጥበብ ገንዘብ ላደረጋት ሕይወትን እንድትሰጥ ነው” ይላል። (መክብብ 7:​12) ትክክለኛ እውቀትና ጥበብ ከገንዘብ በተለየ መልኩ በሁሉም ሁኔታዎች በተለይ ግን ሕይወታችንን በሚነኩ ጉዳዮች ረገድ ሊረዳን ይችላል።​—⁠ምሳሌ 4:​5-9

ጥበብ ራሱ ይጠብቀናል

እውነተኛ ጥበብ በቅርቡ ‘ገንዘብ ያደረጓትን’ ሰዎች ‘ሕይወት’ አስገራሚ በሆነ መንገድ ትጠብቃለች። በሌላ አባባል በፍጥነት በመገስገስ ላይ ካለውና አምላክ ክፉዎችን ከሚያጠፋበት “ታላቅ መከራ” ትጠብቃቸዋለች። (ማቴዎስ 24:​21) መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው በዚያን ጊዜ ሰዎች ገንዘባቸውን “እንደ ጉድፍ” በጎዳናዎቹ ላይ ይጥላሉ። ለምን? ምክንያቱም ‘በእግዚአብሔር የመዓት ቀን’ ወርቅም ሆነ ብር ሕይወት እንደማይገዛላቸው የሚገነዘቡት ከሚደርስባቸው መከራ ስለሚሆን ነው። (ሕዝቅኤል 7:​19) በአንጻሩ ግን አስተዋይ በመሆንና በሕይወታቸው ውስጥ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያውን በመስጠት ‘በሰማይ መዝገብ የሰበሰቡ’ “እጅግ ብዙ ሰዎች” ኪሳራ ከማያስከትለው ከዚህ መዋዕለ ንዋይ ተጠቃሚ ከመሆናቸውም በላይ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ።​—⁠ራእይ 7:​9, 14፤ 21:​3, 4፤ ማቴዎስ 6:​19, 20

እንዲህ ያለውን አስተማማኝ ተስፋ ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ እንዲህ ሲል መልሷል:- “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።” (ዮሐንስ 17:​3) በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህንን እውቀት የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ አግኝተዋል። እንዲህ ያሉት ሰዎች አስደናቂ ተስፋ ያላቸው ከመሆኑም በላይ አሁንም እንኳ በተወሰነ መጠን ሰላምና ደህንነት አግኝተው ይኖራሉ። ሁኔታው ልክ መዝሙራዊው እንደገለጸው ነው:- “በሰላም እተኛለሁ አንቀላፋለሁም፤ አቤቱ፣ አንተ ብቻህን በእምነት አሳድረኸኛልና።”​—⁠መዝሙር 4:​8

የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በጤናህና በሕይወትህ ላይ ሊደርሱ የሚችሉትን አደጋዎች ሊቀንስ የሚችል ሌላ የመረጃ ምንጭ አለ? የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል የመለወጥ ኃይል ያለውም ሆነ አደጋ በሞላበት በዛሬው ዓለም አስተማማኝ ሕይወት እንድትመራ ሊረዳህ የሚችል ሌላ መጽሐፍ የለም። ለምን ይህንን መጽሐፍ በጥልቀት አትመረምረውም?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ለመጽሐፍ ቅዱስ ምስጋና ይግባውና የተሻለ ጤና እና አስተማማኝ ሕይወት ማግኘት ይቻላል

ጄን a የተባለች አንዲት ወጣት ከሕይወት እውነታዎች ለማምለጥ ስትል ማሪዋና፣ ትምባሆ፣ ኮኬይን፣ አምፌተሚን፣ ኤል ኤስ ዲ እና ሌሎችንም አደገኛ መድኃኒቶች ከመውሰዷም በተጨማሪ ጠጪ ሆና ነበር። ጄን እንዳለችው ከሆነ ባሏም ቢሆን ከእርሷ የተሻለ አልነበረም። የወደፊቱ ሁኔታቸው ተስፋ አስቆራጭ ይመስል ነበር። በኋላ ግን ጄን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘች። ከዚያም በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና መጠበቂያ ግንብ እንዲሁም የእሱ ተጓዳኝ የሆነውን ንቁ! መጽሔት ማንበብ ጀመረች። ያነበበችውንም ለባሏ ታካፍለው ነበር። ሁለቱም ከምሥክሮቹ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። ለይሖዋ ከፍተኛ የአቋም ደረጃዎች ያላቸው አድናቆት እያደገ ሲመጣ ማንኛውንም ዓይነት ሱስ የሚያስይዝ ነገር መውሰዳቸውን አቆሙ። ውጤቱስ ምን ሆነ? የተወሰኑ ዓመታት ካለፉ በኋላ ጄን “አዲሱ ሕይወታችን ታላቅ ደስታ አምጥቶልናል” በማለት ጻፈች። “ቃሉ ላለው የማጥራት ኃይልና አሁን መምራት ለቻልነው ነጻና ጤናማ ሕይወት ይሖዋን በጣም አመሰግነዋለሁ።”

ሐቀኛ ሠራተኛ ሆኖ መገኘት ያለውን ጥቅም ኩርት ካጋጠመው ነገር በግልጽ መመልከት ይቻላል። ኩርት የሚሠራው ከኮምፒውተር ጥገና ጋር የተያያዘ ሥራ ነው። በአንድ ወቅት አንድ አዲስ መሣሪያ መግዛት ሲያስፈልግ አሠሪው ዕቃውን በጥሩ ዋጋ እንዲገዛ ለኩርት ኃላፊነቱን ሰጠው። ኩርት ተስማሚ ከሆነ አቅራቢ ዕቃውን በጥሩ ዋጋ አግኝቶ ከሻጩ ጋር በዋጋ ተስማማ። ይሁን እንጂ የድርጅቱ ሂሳብ ሠራተኛ የዕቃውን ዋጋ ከተስማሙበት ወደ 40, 000 (የአሜሪካን ዶላር) በሚጠጋ ገንዘብ አሳንሶ በስህተት ጻፈው። ኩርት የተሠራውን ስህተት በመገንዘብ ኩባንያውን አነጋገረ። የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ በሥራ ዓለም ባሳለፋቸው 25 ዓመታት ውስጥ እንዲህ ያለ ሐቀኝነት ፈጽሞ አይቶ እንደማያውቅ ተናገረ። ኩርትም ሕሊናው በመጽሐፍ ቅዱስ እንደሰለጠነ አስረዳው። በውጤቱም ሥራ አስኪያጁ ለሠራተኞቹ ይሰጣቸው ዘንድ በሥራ ቦታ ሐቀኝነት ስለማሳየት የሚናገሩ 300 የንቁ! መጽሔት ቅጂዎች እንዲመጡለት ጠየቀ። የኩርት ሐቀኝነት የሥራ እድገት አስገኝቶለታል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ስሞቹ ተቀይረዋል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ . . . አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ።”​—ኢሳይያስ 48:​17