የተስፋ መቁረጥን ስሜት መቋቋም ትችላለህ!
የተስፋ መቁረጥን ስሜት መቋቋም ትችላለህ!
በአንድ ወቅት አንድ ጠቢብ “በመከራ ቀን ብትላላ [“ተስፋ ብትቆርጥ፣” NW ] ጉልበትህ ጥቂት ነው” ሲል ጽፏል። (ምሳሌ 24:10) የተስፋ መቁረጥ ስሜት ተሰምቶህ የሚያውቅ ከሆነ በዚህ አባባል ሳትስማማ አትቀርም።
ተስፋ መቁረጥ የሚያስከትለው መዘዝ የማይነካው ሰው የለም። መጠነኛ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን ያህል ቆይቶ ሊጠፋ ይችላል። ሆኖም የስሜት መጎዳት ወይም ቅያሜ ሲኖር ችግሩ ረዘም ላለ ጊዜ ሊቆይ ይችላል። ለበርካታ ዓመታት ታማኝ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ተስፋ ከመቁረጣቸው የተነሳ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና በመስክ አገልግሎት መሳተፍ እንኳ አቁመዋል።
የተስፋ መቁረጥ ስሜት ቢያድርብህ እጅ አትስጥ! ባለፉት ዘመናት ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች የተስፋ መቁረጥ ስሜትን በተሳካ ሁኔታ ተቋቁመዋል። አንተም በአምላክ እርዳታ ልትቋቋመው ትችላለህ።
ሌሎች ስሜትህን ሲጎዱ
አንዳንድ ጊዜ አሳቢነት የጎደለው ቃል ሊሰነዘርብህ ወይም ግድየለሽነት የተሞላበት ድርጊት ሊፈጸምብህ እንደሚችል መጠበቅ አለብህ። ይሁን እንጂ የሌሎች አለፍጽምና ለይሖዋ የምታቀርበውን አገልግሎት እንዳያስተጓጉልብህ መከላከል ትችላለህ። አንድ ሰው ስሜትህን ከጎዳው የሳሙኤል እናት ሐና ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ በገጠማት ጊዜ ምን እንዳደረገች መመልከቱን ጠቃሚ ሆኖ ታገኘዋለህ።
ሐና ልጅ የመውለድ ከፍተኛ ፍላጎት ነበራት፤ ይሁን እንጂ መካን ነበረች። የባለቤቷ ሁለተኛ ሚስት ፍናና ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወልዳለታለች። ፍናና፣ ሐና ላደረባት ትካዜ አሳቢነት ከማሳየት ይልቅ እሷን እንደ ተቀናቃኝ አድርጋ በመመልከቷ ሐና “ታለቅስ ነበር፣ አንዳችም አትቀምስም ነበር።”—1 ሳሙኤል 1:2, 4-7
አንድ ቀን ሐና ለመጸለይ ወደ ማደሪያው ድንኳን ሄደች። የእስራኤል ሊቀ ካህን ዔሊ ከንፈሮቿ ሲንቀሳቀሱ ተመለከተ። ዔሊ፣ ሐና እየጸለየች መሆኗን ስላልተገነዘበ ሰክራለች ብሎ ደመደመ። “ስካርሽ እስከ መቼ ነው? የወይን ጠጅሽን ከአንቺ አርቂው” ሲል ተናገራት። (1 ሳሙኤል 1:12-14) ሐና እንዴት ተሰምቷት ሊሆን እንደሚችል መገመት ትችላለህ? ወደ ማደሪያው ድንኳን የመጣችው ማጽናኛ ለማግኘት ነበር። በእስራኤል ከፍተኛ ሥልጣን ካላቸው ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው ሰው በስህተት ይወቅሰኛል ብላ እንዳልጠበቀች የተረጋገጠ ነው!
ሐና በዚህ ሁኔታ በቀላሉ ቅስሟ ሊሰበር ይችል ነበር። የዔሊ የሊቀ ካህንነት አገልግሎት ፍጻሜውን ካላገኘ በስተቀር ዳግመኛ ወደ ማደሪያው ድንኳን ድርሽ ላለማለት ምላ ውልቅ ብላ መሄድ ትችል ነበር። ሆኖም ሐና ከይሖዋ ጋር ያላትን ዝምድና ከፍ አድርጋ እንደተመለከተች ግልጽ ነው። እንዲህ ዓይነት እርምጃ መውሰዷ ይሖዋን እንደማያስደስተው ታውቃለች። የማደሪያው ድንኳን የንጹሕ አምልኮ ማዕከል ነበር። ይሖዋ በዚያ ስሙ እንዲጠራ አድርጓል። እንዲሁም ዔሊ አለፍጽምና ቢኖርበትም ይሖዋ የመረጠው ወኪሉ ነበር።
ሐና፣ ዔሊ ለሰነዘረባት ወቀሳ የሰጠችው አክብሮት የተሞላበት ምላሽ በዛሬው ጊዜ ለእኛ የላቀ ምሳሌ ይሆነናል። በተሳሳተ መንገድ ስትወቀስ ዝም ብላ ባታልፍም እንኳ ምላሽ የሰጠችው ከፍተኛ አክብሮት በተሞላበት ሁኔታ ነበር። “ጌታዬ ሆይ፣ አይደለም፣ እኔስ ልብዋ ያዘነባት ሴት ነኝ፤ ጠጅና ሌላ የሚያሰክር ነገር አልጠጣሁም፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ነፍሴን አፈሰስሁ፤ ኀዘኔና ጭንቀቴ ስለ በዛ እስከ አሁን ድረስ ተናግሬአለሁና ባሪያህን እንደ ምናምንቴ ሴት አትቁጠረኝ” ስትል መለሰችለት።—1 ሳሙኤል 1:15, 16
ሐና ስሜቷን በግልጽ ተናግራለችን? አዎን፣ ተናግራለች። ሆኖም ዔሊን በመዳፈር በስህተት ላቀረበው ወቀሳ አጸፋዊ ትችት ከመሰንዘር ይልቅ በዘዴ አነጋግራዋለች። እሱ ደግሞ በተራው እንዲህ ሲል በደግነት መልሶላታል:- 1 ሳሙኤል 1:17, 18
“በደኅና ሂጂ፣ የእስራኤልም አምላክ የለመንሽውን ልመና ይስጥሽ።” ጉዳዩ መፍትሔ ካገኘ በኋላ ሐና “መንገድዋን ሄደች በላችም፣ ፊትዋም ከእንግዲህ ወዲህ አዘንተኛ መስሎ አልታየም።”—ከዚህ ዘገባ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? ሐና የተፈጠረውን አለመግባባት ለማስወገድ ፈጣን እርምጃ ወስዳለች፤ ሆኖም ይህን ያደረገችው በከፍተኛ አክብሮት ነበር። በዚህም ምክንያት ከይሖዋም ሆነ ከዔሊ ጋር ጥሩ ዝምድና ይዛ መቀጠል ችላለች። ብዙውን ጊዜ ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት በማድረግና ትንሽ ብልሃት በመጠቀም ቀላል ችግሮች እየሰፉ እንዳይሄዱ መከላከል ይቻላል!
ከሌሎች ጋር የተፈጠረ አለመግባባትን በመፍታት ረገድ በሁለቱም ወገን ትሑት እና እንደ ሁኔታው ለመስተካከል ፈቃደኛ መሆን እንደሚጠይቅ መገንዘብ ያስፈልጋል። አንድ የእምነት ጓደኛህ የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ላደረግከው ጥረት ምላሽ ሳይሰጥ ቢቀር ይሖዋ በራሱ ጊዜና በራሱ መንገድ መፍትሔ እንደሚሰጥ በማመን ጉዳዩን በእሱ እጅ ልትተወው ትችላለህ።
የአገልግሎት መብት አጥተሃልን?
አንዳንዶች በአምላክ አገልግሎት የነበራቸውን ውድ የአገልግሎት መብት ለማጣት በመገደዳቸው ምክንያት አዝነዋል። ወንድሞቻቸውን ማገልገል ያስደስታቸዋል፤ ሆኖም የአገልግሎት መብቱን ሲያጡ ለይሖዋ ወይም ለድርጅቱ የሚያበረክቱት ምንም ጠቀሜታ እንደሌለ ሆኖ ይሰማቸዋል። እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ዮሐንስ ማርቆስ ተብሎም የሚጠራውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነውን የማርቆስን ምሳሌ በመመርመር ጠለቅ ያለ ግንዛቤ ማግኘት ትችላለህ።—ሥራ 12:12
ማርቆስ፣ ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር በመጀመሪያው ሚስዮናዊ ጉዟቸው አብሯቸው የሄደ ቢሆንም በጉዟቸው አጋማሽ ላይ ትቷቸው ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። (ሥራ 13:13) በርናባስ ከጊዜ በኋላ በሌላ ጉዞ ላይ ማርቆስ አብሯቸው እንዲሄድ ፈለገ። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል:- “ጳውሎስ ግን ይህን ከእነርሱ ጋር ሊወስድ አልፈቀደም፣ ከእነርሱ ዘንድ ከጵንፍልያ ተለይቶ ነበርና፣ ወደ ሥራም ከእነርሱ ጋር አልመጣም ነበርና።” በርናባስ በዚህ አልተስማማም። ዘገባው በመቀጠል ‘ስለዚህም [ጳውሎስና በርናባስ] እርስ በርሳቸው እስኪለያዩ ድረስ መከፋፋት ሆነ፣ በርናባስም ማርቆስን ይዞ በመርከብ ወደ ቆጵሮስ ሄደ። ጳውሎስ ግን ሲላስን መርጦ ወጣ’ ሲል ይናገራል።—ሥራ 15:36-40
ማርቆስ የተከበረው ሐዋርያ ጳውሎስ ከእሱ ጋር መሥራት እንዳልፈለገና የእሱን ብቃት በተመለከተ የተፈጠረው ውዝግብ ለጳውሎስና ለበርናባስ መለያየት ምክንያት እንደሆነ ሲያውቅ እጅግ ሳያዝን አልቀረም። ሆኖም ጉዳዩ በዚህ አላበቃም።
ጳውሎስና ሲላስ አሁንም የጉዞ ጓደኛ ማግኘት ያስፈልጋቸው ነበር። ወደ ልስጥራን ሲደርሱ ማርቆስን ሊተካ የሚችል ጢሞቴዎስ የሚባል ወጣት አገኙ። ጢሞቴዎስ በተመረጠበት ወቅት ከተጠመቀ ገና ሁለት ወይም ሦስት ዓመት ቢሆነው ነው። በአንጻሩ ማርቆስ የክርስቲያን ጉባኤ አባል የሆነው ከራሱ ከጳውሎስ በፊት ክርስትና ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ነው። ሆኖም የአገልግሎት መብቱን ያገኘው ጢሞቴዎስ ነበር።—ሥራ 16:1-3
ማርቆስ እሱን የተካው ብዙ ተሞክሮ የሌለው በዕድሜ የሚያንሰው ሰው እንደሆነ ሲያውቅ ምን ተሰምቶት ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ ምንም አይነግረንም። የሆነ ሆኖ ማርቆስ በይሖዋ አገልግሎት በንቃት መሳተፉን እንደቀጠለ ይጠቁመናል። ክፍት በሆኑለት የአገልግሎት መብቶች ተጠቅሟል። ምንም እንኳ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ማገልገል ባይችልም የበርናባስ የትውልድ አገር ወደሆነችው ወደ ቆጵሮስ ከበርናባስ ጋር ሄዷል። በተጨማሪም ማርቆስ ከጴጥሮስ ጋር በባቢሎን አገልግሏል። በመጨረሻም በሮም ከጳውሎስና ከጢሞቴዎስ ጋር የመሥራት አጋጣሚ አግኝቷል። (ቆላስይስ 1:1፤ 4:10፤ 1 ጴጥሮስ 5:13) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ማርቆስ በመንፈስ አነሳሽነት ከአራቱ ወንጌሎች አንዱን ለመጻፍ በቅቷል!
ይህ ሁሉ ጠቃሚ ትምህርት ይዟል። ማርቆስ ስላጣው መብት ከልክ በላይ በመጨነቅ ክፍት የሆኑለትን የአገልግሎት መብቶች ከማድነቅ ወደኋላ አላለም። ማርቆስ በይሖዋ አገልግሎት ራሱን አስጠምዷል፤ ይሖዋም ባርኮታል።
ስለዚህ አንተም የአገልግሎት መብት ካጣህ ተስፋ አትቁረጥ። አዎንታዊ አመለካከት ከያዝክና ራስህን በሥራ ካስጠመድክ ሌሎች መብቶች ልታገኝ ትችላለህ። በጌታ ሥራ ብዙ የሚሠራ አለ።—1 ቆሮንቶስ 15:58
ታማኝ አገልጋይ ተስፋ ሊቆርጥ ይችላል
ለእምነት በብርቱ መጋደል እንዲህ የዋዛ አይደለም። አልፎ አልፎ ተስፋ መቁረጥ ሊሰማህ ይችላል። በዚህ
ጊዜ አንድ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ ፈጽሞ እንዲህ ሊሰማው አይገባም ብለህ በማሰብ ተስፋ በመቁረጥህ ምክንያት የበደለኛነት ስሜት ያድርብህ ይሆናል። ጉልህ ስፍራ ከነበራቸው የእስራኤል ነቢያት አንዱ የሆነውን የኤልያስን ሁኔታ ተመልከት።አክራሪ የበኣል አምልኮ አራማጅ የሆነችው የእስራኤል ንግሥት ኤልዛቤል፣ ኤልያስ የበኣል ነቢያትን እንደፈጀ ስትሰማ እንደምታስገድለው ዛተች። ኤልያስ ከኤልዛቤል የሚያይሉ ጠላቶችን ተጋፍጧል፤ ሆኖም በድንገት ከፍተኛ የተስፋ መቁረጥ ስሜት ስላደረበት ሞትን ተመኘ። (1 ነገሥት 19:1-4) እንዴት እንዲህ ሊሰማው ቻለ? አንድ የዘነጋው ነገር ነበር።
ኤልያስ ይሖዋን የብርታቱ ምንጭ አድርጎ መጠባበቅ እንዳለበት ዘነጋ። ኤልያስ የሞተውን ልጅ እንዲያስነሳና የበኣል ነቢያትን እንዲጋፈጥ ኃይል የሰጠው ማን ነበር? ይሖዋ ነው። ይሖዋ የንግሥት ኤልዛቤልን ቁጣ እንዲጋፈጥ ኃይል ሊሰጠው እንደሚችል ምንም አያጠራጥርም።—1 ነገሥት 17:17-24፤ 18:21-40፤ 2 ቆሮንቶስ 4:7
ማንኛውም ሰው ለጊዜው በይሖዋ ላይ ያለውን ትምክህት ሊያጣ ይችላል። ልክ እንደ ኤልያስ አንተም አንድ ችግር ሲያጋጥምህ ‘ላይኛይቱን ጥበብ’ ተጠቅመህ ከመፍታት ይልቅ ሰብዓዊ አስተሳሰብ ትይዝ ይሆናል። (ያዕቆብ 3:17) ሆኖም ኤልያስ ለጊዜው በማፈግፈጉ ምክንያት ይሖዋ አልተወውም።
ኤልያስ ማንም አያገኘኝም ብሎ ወዳሰበበት ወደ ቤርሳቤህ ከዚያም ወደ ምድረ በዳ ሸሽቶ ሄደ። ሆኖም ይሖዋ ያለበትን ቦታ አውቋል። የሚያጽናናው መልአክ ላከለት። መልአኩ ለኤልያስ ትኩስ ዳቦና ጥም የሚያረካ ውኃ አቀረበለት። ኤልያስ እረፍት ከወሰደ በኋላ መልአኩ ከይሖዋ ተጨማሪ ማበረታቻ ወደሚያገኝበት ወደ ኮሬብ ተራራ 300 ኪሎ ሜትር ገደማ እንዲጓዝ ነገረው።—1 ነገሥት 19:5-8
ኤልያስ ኮሬብ ተራራ ሲደርስ እምነት የሚያጠናክሩትን የይሖዋን ኃይል መግለጫዎች ተመለከተ። ከዚያም ይሖዋ ረጋና ዝግ ባለ ድምፅ ብቻውን አለመሆኑን አረጋገጠለት። ይሖዋ አልተወውም፤ ደግሞም ኤልያስ አይወቅ እንጂ ከጎኑ የተሰለፉ 7, 000 ወንድሞች ነበሩት። በመጨረሻም ይሖዋ የሚያከናውነውን ሥራ ሰጠው። ይሖዋ፣ ኤልያስ የእሱ ነቢይ ሆኖ ማገልገሉን እንዲያቆም አላደረገውም!—1 ነገሥት 19:11-18
እርዳታ ማግኘት ይቻላል
አልፎ አልፎ መጠነኛ የተስፋ መቁረጥ ስሜት የሚሰማህ ከሆነ ጥቂት ተጨማሪ እረፍት ከወሰድክ ወይም ገንቢ ምግብ ከተመገብክ የተሻለ ስሜት ሊሰማህ ይችል ይሆናል። በ1977 እስከ ሞተበት ዕለት ድረስ የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ናታን ኤች ኖር አንድ ሰው ከባድ መስለው ታይተውት የነበሩት ችግሮች ሌሊት በቂ እንቅልፍ አግኝቶ ሲነሳ አብዛኛውን ጊዜ ቀላል እንደሚሆኑለት ተናግሯል። ሆኖም ችግሩ ቀጣይነት ካለው እንዲህ ዓይነቱ መፍትሔ በቂ ሊሆን ስለማይችል ያደረብህን የተስፋ መቁረጥ ስሜት ለመዋጋት እርዳታ ማግኘት ያስፈልግሃል።
ይሖዋ ኤልያስን እንዲያበረታታው መልአክ ልኮለታል። ዛሬ አምላክ በጉባኤ ሽማግሌዎችና በሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች አማካኝነት ማበረታቻ ይሰጣል። በእርግጥም ሽማግሌዎች ‘ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ሊሆኑ’ ይችላሉ። (ኢሳይያስ 32:1, 2) ሆኖም ከእነሱ ማበረታቻ ለማግኘት ቅድሚያውን መውሰድ ሊኖርብህ ይችላል። ኤልያስ ያን ያህል ተስፋ ቢቆርጥም ከይሖዋ መመሪያ ለመቀበል እስከ ኮሬብ ተራራ ድረስ ተጉዟል። በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት ብርታት የሚሰጥ መመሪያ እናገኛለን።
ባገኘነው እርዳታ የስሜት መጎዳትንና የአገልግሎት መብት ማጣትን የመሳሰሉ ፈተናዎችን በቆራጥነት ስንጋፈጥ ወሳኝ በሆነ አንድ አከራካሪ ጉዳይ ረገድ ከይሖዋ ጎን መቆማችንን እናሳያለን። አከራካሪው ጉዳይ ምንድን ነው? ሰይጣን ሰዎች ይሖዋን የሚያገለግሉት ለግል ጥቅማቸው ሲሉ ብቻ ነው ብሎ ይከራከራል። በሕይወታችን ውስጥ ሁሉም ነገር የተቃና ሆኖ ባለበት ጊዜ አምላክን ማገልገላችንን እንደማናቆም ሰይጣን በሚገባ ያውቃል። ሆኖም ችግሮች ሲያጋጥሟቸው አምላክን ማገልገላቸውን ያቆማሉ ሲል ይከራከራል። (ኢዮብ ምዕራፍ 1 እና 2) ተስፋ መቁረጥ ቢያጋጥመንም በይሖዋ አገልግሎት በጽናት በመቀጠል ዲያብሎስ ለሚሰነዝረው ስም የማጥፋት ውንጀላ መልስ በማስገኘት ረገድ የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን።—ምሳሌ 27:11
ሐና፣ ማርቆስና ኤልያስ ለአጭር ጊዜ ደስታቸው እንዲጠፋባቸው ያደረገ ችግር ደርሶባቸዋል። ይሁን እንጂ የደረሰባቸውን ችግር በመቋቋም ሕይወታቸውን በተሳካ መንገድ መምራት ችለዋል። በይሖዋ እርዳታ አንተም የተስፋ መቁረጥን ስሜት መቋቋም ትችላለህ!