ስለ ሙት ባሕር ጥቅልሎች ሐቁ ምንድን ነው?
ስለ ሙት ባሕር ጥቅልሎች ሐቁ ምንድን ነው?
አንዳንዶች የ20ኛው መቶ ዘመን ታላቅ አርኪኦሎጂያዊ ግኝት ብለው ለሚጠሩት ነገር መገኘት ምክንያት የሆነው ከዛሬ 50 ዓመት በፊት አንድ ወጣት ዘላን እረኛ ወደ አንድ ዋሻ ውስጥ የወረወረው ድንጋይ ነው። እረኛው የወረወረው ድንጋይ ማሰሮ ሲሰብር ሰማ። ከዚያም ወደ ውስጥ ገብቶ ሲመለከት የሙት ባሕር ጥቅልሎች የሚል ስያሜ የተሰጣቸውን የመጀመሪያዎቹን ጥቅልሎች አገኘ።
እነዚህ ጥቅልሎች የምሁራንንና የመገናኛ ብዙሃንን ትኩረት ከመሳባቸውም በላይ ከፍተኛ ውዝግብ አስነስተዋል። በሕዝቡ መካከልም ግራ የሚያጋቡና የተሳሳቱ መረጃዎች ተነዝተዋል። እነዚህ ጥቅልሎች የክርስትናንም ሆነ የአይሁድን እምነት የሚያናጉ እውነታዎችን ገሃድ ያወጣሉ በሚል ስጋት ሐቁን የሚያድበሰብሱ የሃሰት ወሬዎች ተናፍሰዋል። የሆነ ሆኖ የእነዚህ ጥቅልሎች ትክክለኛ ጠቀሜታ ምንድን ነው? አሁን ከ50 የሚበልጡ ዓመታት ካለፉ በኋላ ሐቁ ሊደረስበት ይችል ይሆን?
የሙት ባሕር ጥቅልሎች ምንድን ናቸው?
የሙት ባሕር ጥቅልሎች አብዛኞቹ በዕብራይስጥ፣ አንዳንዶቹ በአረማይክ፣ ጥቂቶቹ ደግሞ በግሪክኛ የተጻፉ የአይሁድ የእጅ ጽሑፎች ናቸው። ብዙዎቹ እነዚህ ጥቅልሎችና ቁርጥራጮች ከ2, 000 ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸው ሲሆኑ ከኢየሱስ ልደት በፊት ጀምሮ የነበሩ ናቸው። በዘላኖች እጅ ከተገኙት ከመጀመሪያዎቹ ጥቅልሎች መካከል የተለያየ መጠን ያለው ብልሽት የደረሰባቸው ሰባት ረጃጅም በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ ጽሑፎች ይገኛሉ። ተጨማሪ ዋሻዎች ሲፈተሹ ሌሎች ጥቅልሎችና በጣም ብዙ ቁርጥራጮች ተገኝተዋል። በ1947 እና በ1956 መካከል በነበሩት ዓመታት በሙት ባሕር አካባቢ በኩምራን አቅራቢያ ጥቅልሎች ያሉባቸው 11 ዋሻዎች ተገኝተዋል።
ጥቅልሎቹና ቁርጥራጮቹ በጠቅላላ በዓይነት በዓይነታቸው ከተለዩ በኋላ ሲቆጠሩ 800 ገደማ የሚደርሱ በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ ጽሑፎች ሆነዋል። አንድ አራተኛ ወይም ከ200 a
በላይ የሚሆኑት በእጅ የተገለበጡ ጥንታዊ ጽሑፎች ከዕብራይስጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፍ ውስጥ አንዳንድ ክፍሎችን የያዙ ናቸው። ሌሎቹ ጽሑፎች ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ያልሆኑ ጥንታዊ የአይሁድ ጽሑፎች ማለትም አዋልድ (አፖክራይፋ) እና ድርሳናት (ሲውዴፒግራፋ) ናቸው።የምሁራንን ትኩረት በእጅጉ የሳቡት አንዳንዶቹ ጥቅልሎች ቀደም ሲል ምንም የማይታወቁ መጻሕፍት ናቸው። እነዚህም የአይሁድ ሕግ ትርጉሞችን፣ በኩምራን አካባቢ የሚኖረው ማኅበረሰብ የሚመራባቸው ደንቦችን፣ ሃይማኖታዊ ግጥሞችንና ጸሎቶችን እንዲሁም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች አፈጻጸምና ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት ያለውን አመለካከት የሚያብራሩ ጽሑፎችን ያካትታሉ። ዛሬ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ሰፍረው ለሚገኙት ማብራሪያዎች መንገድ ጠራጊ የሆኑ ለየት ያሉ ማብራሪያዎችን የያዙ መጻሕፍትም አሉ።
የሙት ባሕር ጥቅልሎችን የጻፈው ማን ነው?
ጥንታዊ መዛግብት የተዘጋጁበትን ዘመን ለማወቅ የሚረዱ የተለያዩ ዘዴዎች እነዚህ ጥቅልሎች የተገለበጡት ወይም የተጠናቀሩት በሦስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ እና በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ መሆኑን ይጠቁማሉ። በ70 እዘአ ቤተ መቅደሱ ከመጥፋቱ በፊት ከኢየሩሳሌም የሸሹ አይሁዶች እነዚህን ጥቅልሎች በዋሻዎቹ ውስጥ ሳይደብቋቸው እንዳልቀሩ አንዳንድ ምሁራን ሐሳብ ያቀርባሉ። ይሁን እንጂ በጥቅልሎቹ ላይ ምርምር የሚያካሂዱ አብዛኞቹ ምሁራን ይህ ሐሳብ ከራሳቸው ከጥቅልሎቹ ይዘት ጋር የሚስማማ ሆኖ አላገኙትም። አብዛኞቹ ጥቅልሎች በኢየሩሳሌም የነበሩ የሃይማኖት መሪዎች ከነበራቸው አመለካከት ጋር የሚቃረኑ አመለካከቶችንና ልማዶችን ያንጸባርቃሉ። እነዚህ ጥቅልሎች አምላክ ካህናቱንም ሆነ በኢየሩሳሌም ያለውን የቤተ መቅደስ አገልግሎት እንደተወና በምትኩ እነሱ በምድረ በዳ የሚያካሂዱትን አምልኮ እንደተቀበለ አድርገው የሚያምኑ ሰዎችን ያቀፈ አንድ ቡድን እንደነበረ ይገልጻሉ። በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ የሚገኙ የሃይማኖት መሪዎች እንዲህ ዓይነት ሐሳብ የያዙ ጥቅልሎችን ጭምር ይደብቃሉ ብሎ መገመት የማይመስል ነገር ነው።
በኩምራን አንድ የገልባጮች ቡድን የነበረ ቢሆንም እንኳ አብዛኞቹ ጥቅልሎች በእነዚህ አማኞች አማካኝነት ከሌላ አካባቢ ተሰብስበው ወደዚያ የተወሰዱ ሳይሆኑ አይቀሩም። የሙት ባሕር ጥቅልሎች የብዙ ዓይነት መጻሕፍት ስብስብ ናቸው ሊባል ይችላል። እንደ አንድ ቤተ መጻሕፍት ሁሉ እነዚህ ስብስቦችም የአንባቢዎቻቸውን ሃይማኖታዊ አመለካከት ብቻ ሳይሆን በርካታ የተለያዩ ሐሳቦችን የሚያንጸባርቁ መጻሕፍትን አካትተው የያዙ ናቸው። ይሁን እንጂ በብዙ ቅጂዎች የተገኙት መጻሕፍት ከሌሎቹ መጻሕፍት ይበልጥ የሃይማኖታዊ ቡድኑን አመለካከትና እምነት የሚያንጸባርቁ ሊሆኑ ይችላሉ።
የኩምራን ነዋሪዎች ኤሴናውያን ናቸውን?
እነዚህን ጥቅልሎች ያሰባሰቡት የኩምራን ነዋሪዎች ከሆኑ ነዋሪዎቹ እነማን ነበሩ? እነዚህ ጥቅልሎች የኤሴናውያን ማኅበረሰብ ንብረቶች ናቸው የሚል ሐሳብ ለመጀመሪያ ጊዜ ያቀረቡት በ1947 በኢየሩሳሌም ለሚገኘው ለሂብሩው ዩኒቨርሲቲ ሦስት ጥቅልሎችን የተረከቡት ፕሮፌሰር ኤሊኤዘር ሱከኒክ ናቸው።
ኤሴናውያን የመጀመሪያው መቶ ዘመን ታሪክ ጸሐፊዎች የሆኑት ጆሴፈስ፣ የእስክንድሪያው ፊሎ እና አረጋዊው ፕሊኒ የጠቀሷቸው ከአይሁድ የተገነጠሉ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ናቸው። የኤሴናውያን ትክክለኛ አመጣጥ በመላ ምት ላይ የተመሠረተ ቢሆንም በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የመቃብያንን ዓመፅ ተከትሎ ሁከት ተቀስቅሶ በነበረበት ወቅት የተነሱ ሳይሆኑ አይቀሩም። b ጆሴፈስ ኤሴናውያን በዚያ ወቅት ስለመኖራቸው የጠቀሰው ሃይማኖታዊ አመለካከታቸው ከፈሪሳውያንና ከሰዱቃውያን አመለካከት የሚለይበትን መንገድ በዝርዝር በጻፈ ጊዜ ነው። ፕሊኒ በሙት ባሕር አካባቢ በኢያሪኮና በዓይንጋዲ መካከል አንድ የኤሴናውያን ማኅበረሰብ ይኖር እንደነበር ጠቅሷል።
ጆሴፈስ ወደ አራት ሺህ እንደሚጠጉ ከገመታቸው “የኤሴን ንቅናቄ አባላት መካከል በኩምራን ይኖሩ የነበሩት ጥቂቶቹ ብቻ ነበሩ” ሲሉ የሙት ባሕር ጥቅልሎች ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ጄምስ ቫንደርካም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ምንም እንኳ ሁሉም ተስማሚ ነው ባይባልም የኩምራን መጻሕፍት የሚሰጡት ገለጻ በዚያን ወቅት ከነበረ ከታወቀ ሌላ ማንኛውም አይሁዳዊ ቡድን ይበልጥ ለኤሴናውያን የሚስማማው ይመስላል።
አንዳንዶች ክርስትና የተመሠረተው ኩምራን ውስጥ ነው ይላሉ። ሆኖም ኩምራን በነበረው የሃይማኖት ቡድንና በጥንት ማቴዎስ 15:1-20፤ ሉቃስ 6:1-11) በተጨማሪም ኤሴናውያን ከሌላው ማኅበረሰብ ራሳቸውን ስለማግለላቸው፣ በነፍስ አለመሞትና በዕድል ስለማመናቸው፣ ለብሕትውና አጽንኦት ስለመስጠታቸውና በአምልኮታችን ከመላእክት ጋር እንካፈላለን ስለሚለው ምሥጢራዊ ንድፈ ሐሳባቸው ብዙ ማለት ይቻላል። ይህ አመለካከታቸው ኢየሱስም ሆነ የጥንት ክርስቲያኖች ካስተማሩት ትምህርት ጋር ፍጹም የሚቃረን ነው።—ማቴዎስ 5:14-16፤ ዮሐንስ 11:23, 24፤ ቆላስይስ 2:18፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:1-3
ክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ አመለካከት መካከል በርካታ ጉልህ ልዩነቶችን መመልከት ይቻላል። የኩምራን ጽሑፎች በጣም ጥብቅ የሰንበት ሕጎችና ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው የመንጻት ሥርዓት እንደነበር ይገልጻሉ። (የተድበሰበሰ ሐቅም ሆነ ተደብቆ የቀረ ጥቅልል የለም
የሙት ባሕር ጥቅልሎች ከተገኙ በኋላ ባሉት ዓመታት የመጀመሪያዎቹን ግኝቶች በዓለም ዙሪያ ያሉ ምሁራን በቀላሉ እንዲያገኟቸው ለማድረግ ሲባል የተለያዩ ጽሑፎች ተዘጋጅተዋል። ዋሻ ቁጥር 4 በመባል በሚታወቀው ዋሻ ውስጥ የተገኙት በሺዎች የሚቆጠሩት ቁርጥራጮች ግን በጣም አስቸጋሪ ነበሩ። እነዚህ ቁርጥራጮች (የዚያን ጊዜ የዮርዳኖስ ክፍል በነበረው) በምሥራቃዊ ኢየሩሳሌም በሚገኘው የፍልስጥኤም አርኪኦሎጂያዊ ሙዚየም ውስጥ በተቋቋመው አንድ አነስተኛ ዓለም አቀፍ የምሁራን ቡድን እጅ ነበሩ። በዚህ ቡድን ውስጥ አንድም አይሁዳዊ ወይም እስራኤላዊ ምሁር አልተጨመረም ነበር።
ይህ የምሁራን ቡድን የምርምር ውጤቱን አትሞ ይፋ እስኪያደርግ ድረስ እነዚህ ጥቅልሎች በምንም መንገድ በሰው እጅ እንዳይደርሱ የሚከለክል መመሪያ አውጥቶ ነበር። የቡድኑ አባላት ብዛት ከተወሰነ ቁጥር እንዳይበልጥ ተደርጎ ነበር። አንድ የቡድኑ አባል ቢሞት እሱን የሚተካ አንድ አዲስ ምሁር ብቻ ይጨመር ነበር። ሥራው በርከት ያለ ቁጥር ያላቸውን ምሁራን ያቀፈ ቡድን የሚጠይቅ ከመሆኑም በላይ በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ በጥንታዊው ዕብራይስጥና አረማይክ ቋንቋ የላቀ ክህሎት አስፈልጎ ነበር። “የፈለገውንም ያህል ችሎታ ቢኖራቸው በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩት ቁርጥራጮች በስምንት ሊቃውንት ብቻ ሊሠሩ ይችላሉ ብሎ ማሰብ ዘበት ነው” ሲሉ ጄምስ ቫንደርካም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በ1967 በተደረገው የስድስቱ ቀን ጦርነት ምሥራቃዊ ኢየሩሳሌም ከነጥቅልሎቿ በእስራኤል ቁጥጥር ስር ወደቀች፤ ሆኖም በጥቅልሎቹ ላይ ምርምር የሚያደርገውን ቡድን በተመለከተ ምንም ዓይነት የፖሊሲ ለውጥ አልተደረገም። በዋሻ ቁጥር 4 የተገኙት ጥቅልሎች ሳይታተሙ ዓመታት ብቻ ሳይሆን አሥርተ ዓመታት በማለፋቸው በርካታ ምሁራን ተቃውሟቸውን ማሰማት ጀመሩ። በ1977 የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ጌዛ ቨርመሽ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት የ20ኛው መቶ ዘመን የምሁራን ቅሌት ሲሉ ጠርተውታል። ጥቅልሎቹ የያዙት የክርስትናን እምነት የሚያጋልጥ ሐሳብ ገሀድ እንዳይወጣ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሆን ብላ ለመደበቅ እየጣረች እንዳለች የሚገልጽ ወሬ ይናፈስ ጀመር።
በመጨረሻም በ1980ዎቹ የቡድኑ አባላት ቁጥር ወደ 20 ምሁራን ከፍ እንዲል ተደረገ። ከዚያም በ1990 አዲስ በተሾሙት ዋና አዘጋጅ ኢማኑኤል ቶቭ (ኢየሩሳሌም በሚገኘው ሂብሩ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩ) አመራር ቡድኑ ከ50 በላይ ምሁራንን እንዲያቅፍ ተደርጓል። የተቀሩት ጥቅልሎች ምሁራዊ ትንተና ታክሎባቸው ታትመው የሚወጡበት ቀን ተቆረጠ።
በ1991 ያልተጠበቀ እመርታ ታየ። በመጀመሪያ ኤ ፕሪሊሚናሪ ኤዲሽን ኦቭ ዚ አንፐብሊሽድ ዴድ ሲ ስክሮልስ የተባለ መጽሐፍ ታትሞ ወጣ። ይህ መጽሐፍ የተዘጋጀው በኮምፒውተር በመታገዝና ቡድኑ ያዘጋጀውን ኮንኮርዳንስ መሠረት በማድረግ ነበር። ከዚያም በመቀጠል በካሊፎርንያ ሳን ማሪኖ የሚገኘው ሀንቲንግተን ቤተ መጻሕፍት የጥቅልሎቹን የተሟላ ፎቶግራፍ ለሚፈልግ ለማንኛውም ምሁር ማቅረብ እንደሚችል አስታወቀ። ብዙም ሳይቆይ ኤ ፋክሲማይል ኤዲሽን ኦቭ ዚ ዴድ ሲ ስክሮልስ የተባለው ጽሑፍ መታተም ቀደም ሲል ሳይታተሙ ቀርተው የነበሩትን ጥቅልሎች ፎቶግራፍ በቀላሉ ማግኘት እንዲቻል አድርጓል።
ስለዚህ ካለፈው አሥርተ ዓመት ወዲህ የሙት ባሕር ጥቅልሎች በሙሉ ምርምር ለማድረግ በሚያስችል መንገድ ተዘጋጅተው ቀርበዋል። በዚህ ላይ የሚደረገው ምርምር ተድበስብሶ የቀረ ሐቅም ሆነ የተደበቀ ጥቅልል አለመኖሩን ለማወቅ ያስችላል። የሙት ባሕር ጥቅልሎች የመጨረሻ እትም አሁን በመታተም ላይ ስለሆነ የተሟላ ጥናት ማካሄድ የሚቻለው ከእንግዲህ በኋላ ይሆናል። በሙት ባሕር ጥቅልሎች ላይ ምርምር የሚያደርግ አዲስ የምሁራን ቡድን ተነስቷል። ሆኖም ይህ የምርምር ውጤት ለመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ምን ትርጉም ይኖረው ይሆን?
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a አፖክራይፋ (ቃል በቃል ሲተረጎም “ስውር”) እና ሲውዴፒግራፋ (ቃል በቃል ሲተረጎም “የሐሰት ፈጠራ ጽሑፎች”) ከሦስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ እስከ አንደኛው መቶ ዘመን እዘአ ድረስ የነበሩትን የአይሁድ ጽሑፎች የሚያመለክቱ ናቸው። የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አዋልድ መጻሕፍትን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አድርጋ ተቀብላቸዋለች። ሆኖም የአይሁድና የፕሮቴስታንት ሃይማኖቶች እነዚህን መጻሕፍት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አድርገው አልተቀበሏቸውም። ድርሳናት አብዛኛውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ላይ የፈጠራ ታሪኮች በመጨማመር በታወቁ የመጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ስም የሚጻፉ መጻሕፍት ናቸው።
b “መቃብያን እነማን ነበሩ?” የሚለውን በኅዳር 15, 1998 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 21-4 ላይ የሚገኘውን ርእስ ተመልከት።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጥንታዊ ጥቅልሎች ከተገኙባቸው በሙት ባሕር አቅራቢያ ከሚገኙ ዋሻዎች መካከል አንዳንዶቹ እነዚህ ናቸው
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
የጥቅልል ቁርጥራጭ:- ገጽ 3, 4, እና 6:- Courtesy of Israel Antiquities Authority
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Courtesy of Shrine of the Book, Israel Museum, Jerusalem