በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በኬንያ ምሥራቹ የተገባቸውን ሰዎች መፈለግ

በኬንያ ምሥራቹ የተገባቸውን ሰዎች መፈለግ

በኬንያ ምሥራቹ የተገባቸውን ሰዎች መፈለግ

ኬንያ ዕጹብ ድንቅ የተፈጥሮ ውበት ያላት አገር ናት። ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች፣ የተንጣለሉ ሜዳዎች፣ በጣም ሞቃታማ በረሃዎችና በበረዶ የተሸፈኑ ተራራዎች አገሪቱን ልዩ ውበት አጎናጽፈዋታል። ኬንያ በሚልዮን የሚቆጠሩ የዱር አራዊት የሚርመሰመሱባትና ሊጠፋ የተቃረበው አውራሪስ የሚገኝባት አገር ነች። በተጨማሪም አንድ ሰው ብዛት ያላቸውን ቀጭኔዎች መመልከት ይችላል።

ኃይለኛ የሆነውንና አስደናቂ የመብረር ችሎታ ያለውን ንሥርን ጨምሮ ማራኪ ዝማሬ የሚያሰሙ በተለያዩ ቀለማት ያሸበረቁ ብርቅዬ አእዋፋትም የሞሉባት አገር ናት። ዝሆኖችንና አንበሶችንም እንደልብ መመልከት ይቻላል። በኬንያ የሚታየው ማራኪ ነገርም ሆነ የሚሰማው ድምፅ የሚረሳ አይደለም።

ሆኖም ውበት በተላበሰችው በዚህች አገር የሚሰማ ሌላም ድምፅ አለ። ይህ ድምፅ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሲናገሩት የሚሰማ የተስፋ መልእክት ነው። (ኢሳይያስ 52:​7) መልእክቱ በዚያ የሚኖሩ ከ40 የሚበልጡ ጎሳዎች በሚጠቀሙባቸው ቋንቋዎች በመነገር ላይ ነው። ከዚህ አንጻር ስንመለከታት ኬንያ የተፈጥሮ ውበት ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ውበትም ያላት አገር ናት።

አብዛኞቹ ኬንያውያን ሃይማኖታዊ ዝንባሌ ስላላቸው ስለ መንፈሳዊ ጉዳዮች ለመወያየት ፈቃደኞች ናቸው። የአብዛኛው ሕዝብ ዝንባሌ ይህ ቢሆንም በብዙ አገሮች እንደሚታየው በኬንያም ለውጥ በመከሰቱ ሰዎችን አግኝቶ ማነጋገር ፈታኝ ሆኗል።

አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ሁኔታዎች ብዙዎች የአኗኗር ለውጥ እንዲያደርጉ አስገድዷቸዋል። ዱሮ ዱሮ እንደ ባህል ሆኖ ሴቶች ከማጀት አይወጡም ነበር። ዛሬ ዛሬ ግን የቢሮ ሠራተኞች ሆነው ወይም በየመንገዱ ፍራፍሬ፣ አትክልት፣ ዓሣ፣ ዘንቢል ሲሸጡ ይታያሉ። ወንዶች ቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ለማሟላት ደፋ ቀና ሲሉ ይውላሉ። ልጆች እንኳ በዚያች ትንሽ ክንዳቸው ሳሕን ታቅፈው የተቆላ ኦቾሎኒና የተቀቀለ እንቁላል እያዞሩ ይሸጣሉ። በዚህ ምክንያት ቀን ቀን ብዙ ሰዎች ቤታቸው አይውሉም። ከዚህም የተነሳ የመንግሥቱ ምሥራች አዋጅ ነጋሪዎች ማስተካከያዎችን ማድረግ ግድ ሆኖባቸዋል።

የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ዕለታዊ ሥራዎቻቸውን ለማከናወን ሲሉ ከቤት ውጪ በሚውሉ ሰዎች ላይ እንዲሁም በወዳጆቻቸው፣ በዘመዶቻቸው፣ በንግድ ሥራ ላይ በተሰማሩና በሥራ ባልደረቦቻቸው ላይ እንዲያተኩሩ ማበረታቻ ተሰጥቷቸው ነበር። ወንድሞችም ሰዎችን ሊገኙ በሚችሉበት በማንኛውም ቦታ በማነጋገር አስፈላጊውን ምላሽ ሰጥተዋል። (ማቴዎስ 10:​11) ሰፋ ያለ አመለካከት ለመያዝ የተደረገው ይህ ጥረት ውጤት አስገኝቶ ይሆን? አዎን አስገኝቷል! አንዳንድ ምሳሌዎችን ተመልከት።

ዘመዶች​—⁠ከሁሉ የቀረቡ ጎረቤቶቻችን

የኬንያ ዋና ከተማ የሆነችው ናይሮቢ ሦስት ሚልዮን የሚያክል ሕዝብ ይኖርባታል። በከተማዋ ምሥራቃዊ ክፍል የይሖዋ ምሥክሮችን የሚጠሉ ጡረታ የወጡ አንድ ሻለቃ አሉ። የሚገርመው ነገር የገዛ ልጃቸውም የይሖዋ ምሥክር መሆኑ ነው። አንድ ጊዜ በየካቲት ወር ውስጥ እኚህ ሰው በስምጥ ሸለቆ ውስጥ ናኩሩ በምትባል ከተማ የሚኖረውን ልጃቸውን ለመጠየቅ 160 ኪሎ ሜትር ተጉዘው ሄዱ። እዚያ በቆዩበት ጊዜ ልጃቸው ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት * የተባለውን መጽሐፍ በስጦታ አበረከተላቸው። አባትየው ስጦታውን ተቀብለው ወደ ቤታቸው ተመለሱ።

እኚህ ሰው ቤት ሲደርሱ መጽሐፉን ለባለቤታቸው የሰጧቸው ሲሆን እሳቸውም መጽሐፉን ያዘጋጁት የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን ስላላወቁ ማንበብ ጀመሩ። ቀስ በቀስ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እየተነኩ ሲመጡ ያገኙትን እውቀት ለባለቤታቸው ያካፍሉ ጀመር። እሳቸውም የማወቅ ጉጉት ስላደረባቸው ማንበብ ጀመሩ። መጽሐፉን ማን እንዳዘጋጀው ሲረዱ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች እውነቱ እንዳልተነገራቸው ተገነዘቡ። በአካባቢያቸው ካሉ ምሥክሮች ጋር ተገናኙና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረላቸው። መጽሐፉን በግላቸው ባነበቡበት ወቅት ክርስቲያኖች ትንባሆ ማጨስም ሆነ መሸጥ እንደማይገባቸው ተገንዝበው ነበር። (ማቴዎስ 22:​39፤ 2 ቆሮንቶስ 7:​1) ያለ አንዳች ማመንታት በሱቃቸው የሚገኙ ሲጋራዎችን በሙሉ አስወገዱ። ከተወሰኑ ወራት በኋላ ያልተጠመቁ አስፋፊዎች የሆኑ ሲሆን ብዙም ሳይቆይ በአውራጃ ስብሰባ ላይ ተጠመቁ።

ቆሻሻ ውስጥ የተገኘ ውድ ነገር

በመዲናዋ አንዳንድ ወረዳዎች ውስጥ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ትፍግፍግ ብለው የሚኖሩባቸው መንደሮች አሉ። በእነዚህ መንደሮች ከጭቃ፣ ከእንጨት፣ ከብረታ ብረት ወይም ከቆርቆሮ የተሠሩ በጣም ብዙ መደዳ ቤቶች አሉ። ሰዎች በኢንዱስትሪዎችና በፋብሪካዎች ውስጥ ሥራ ማግኘት ካልቻሉ የራሳቸውን ሥራ ይፈጥራሉ። የጁዋ ካሊ (በስዋሂሊ “ጠራራ ፀሐይ” ማለት ነው) ሠራተኞች ፀሐይ ላይ ተቀምጠው ከአሮጌ ጎማ በረባሶ ጫማ ወይም ከተጣሉ ጣሳዎች ኩራዝ ይሠራሉ። ሌሎች ደግሞ ከተከመሩ ቆሻሻዎች ውስጥ እንደገና ለአገልግሎት የሚውሉ ወረቀቶች፣ ጣሳዎችና ጠርሙሶች ለማግኘት ይፈላልጋሉ።

ከቆሻሻ ውስጥ ውድ ነገር ሊገኝ ይችላል? አዎን! አንድ ወንድም እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ፈርጠም ያለ ሰውነት ያለው፣ የተዘበታተለ ልብስ የለበሰና አስፈሪ ገጽታ ያለው ሰው የተጣሉ ጋዜጦችንና መጽሔቶችን በማዳበሪያ አጭቆ ትላልቅ ስብሰባዎች ወደምናደርግበት አዳራሽ ግቢ ገባ። ዊልያም እንደሚባል ከነገረኝ በኋላ ‘አዲስ መጠበቂያ ግንብ አለህ?’ ብሎ ጠየቀኝ። ምን ሊያደርገው ፈልጎ ነው የሚል ስጋት አደረብኝ። አምስት መጽሔቶችን ሳሳየው ሁሉንም ተራ በተራ ተመለከታቸውና ‘ሁሉንም እወስዳቸዋለሁ’ አለኝ። በጣም ተገርሜ ወደ ውስጥ ገባሁና በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ አመጣሁ። a ከዚያም ስለ ገነት የሚገልጸውን ሥዕል አሳየሁትና ያለ ክፍያ መጽሐፍ ቅዱስ እንደምናስጠና ነገርኩት። ቀጥሎ ‘ዊልያም ነገ መጥተህ ለምን ማጥናት አንጀምርም?’ የሚል ሐሳብ አቀረብኩለት። በማግስቱ መጣ!

“አንድ እሑድ ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ስብሰባ መጣ። ያን ዕለት እኔ የሕዝብ ንግግር እየሰጠሁ ነበር። ዊልያም ወደ ውስጥ እንደገባ አድማጮችን ቃኘት አደረገ፤ እኔንም መድረክ ላይ ቆሜ አየኝና በፍጥነት ከአዳራሹ ወጥቶ ሄደ። በሌላ ቀን ለምን እንዲህ እንዳደረገ ጠየቅኩት። እንደማፈር ብሎ ‘ሁሉም ንጹሖች ስለነበሩ አፍሬ ነው’ አለኝ።

“ዊልያም በጥናቱ እየበረታ ሲመጣ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በሕይወቱ ላይ ለውጥ ማምጣት ጀመረ። ሰውነቱን ታጠበ፣ ፀጉሩን ተስተካከለ፣ ንፁሕና ሥርዓታማ ልብስ ለበሰ እንዲሁም ብዙም ሳይቆይ በስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ መገኘት ጀመረ። ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለው መጽሐፍ ሲወጣ እሱን ማጥናት ጀመርን። በመሃሉ በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ተመዝግቦ ሁለት ጊዜ ንግግር ያቀረበ ሲሆን ያልተጠመቀ አስፋፊ ሆነ። በልዩ ስብሰባ ላይ ተጠምቆ መንፈሳዊ ወንድሜ ሲሆን በማየቴ በጣም ተደስቻለሁ።”

ዊልያም ለመጀመሪያ ጊዜ መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ያገኘው የት ነው? “በቆሻሻ ውስጥ ከወረቀት ጋር የተጣሉ ጥቂት መጽሔቶች አገኘሁ” ሲል ተናግሯል። አዎን፣ ፈጽሞ ባልተጠበቀ ቦታ ውድ ነገር አገኘ!

በሥራ ቦታ መመሥከር

በሥራ ቦታ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት ለመስጠት አጋጣሚዎችን ሁልጊዜ በንቃት እንጠቀምባቸዋለን? በናይሮቢ በአንድ ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለው ጄምስ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የደረሰው በዚህ መንገድ ነበር። እሱም በተራው ምሥራቹን ለሌሎች ለማድረስ ተመሳሳይ ዘዴ በመጠቀም የተዋጣለት ሆኗል። ለምሳሌ ያህል አንድ ቀን ጄምስ የሥራ ባልደረባው ቢሮ ውስጥ “ኢየሱስ ያድናል” የሚል ባጅ ደረቱ ላይ ለጥፎ ተመለከተ። ልክ እንደ ወንጌላዊው ፊልጶስ “እነዚህ ቃላት ምን ትርጉም እንዳላቸው ታውቃለህ?” ሲል ባልደረባውን ጠየቀው። (ሥራ 8:​30) ይህ ጥያቄ ጥሩ ውይይት ከፈተ። ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የተጀመረ ሲሆን ሰውዬው ከጊዜ በኋላ ተጠመቀ። ጄምስ ሌላም ውጤት አግኝቶ ይሆን? እስቲ እሱ ራሱ ይንገረን:-

“እኔና ቶም አንድ ኩባንያ ውስጥ እንሠራለን። ብዙውን ጊዜ በመሥሪያ ቤታችን ሰርቪስ አብረን እንሄዳለን። አንድ ቀን ጠዋት አጋጣሚ ሆኖ ጎን ለጎን ተቀመጥን። ከመጽሐፎቻችን መካከል አንዱን እያነበብኩ ስለነበር መጽሐፉን ለቶም በደንብ እንዲታየው አድርጌ ያዝኩት። እንዳሰብኩት ያነበበው ነገር ትኩረቱን የሳበው ሲሆን እኔም መጽሐፉን በደስታ አዋስኩት። ባነበበው ነገር በጣም ስለተደነቀ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግለት ተስማማ። አሁን እሱና ባለቤቱ የተጠመቁ የይሖዋ አገልጋዮች ናቸው።”

ጄምስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ብዙውን ጊዜ መሥሪያ ቤት በምሳ እረፍት ላይ አስደሳች ውይይት ይነሳል። በተለያዩ ቀናት ኢፍሬምንም ሆነ ዋልተርን ያነጋገርኳቸው እንደዚህ ባለው አጋጣሚ ነበር። ሁለቱም የይሖዋ ምሥክር መሆኔን ያውቁ ነበር። ኢፍሬም የይሖዋ ምሥክሮች ለምን እንደሚጠሉ ለማወቅ ይፈልግ ነበር። ዋልተር በይሖዋ ምሥክሮችና በሌሎች ሃይማኖቶች መካከል ስላለው ልዩነት ጥያቄዎች ነበሩት። ሁለቱም ከቅዱሳን ጽሑፎች በሰጠኋቸው መልስ በጣም ስለረኩ ጥናት ለመጀመር ተስማሙ። ኢፍሬም ፈጣን እድገት አደረገ። ከጊዜ በኋላ እሱና ባለቤቱ ራሳቸውን ለይሖዋ ወስነው ተጠመቁ። አሁን እሱ በሽማግሌነት የሚያገለግል ሲሆን ባለቤቱ የዘወትር አቅኚ ናት። ሆኖም ዋልተር በገጠመው ከባድ ተቃውሞ የተነሳ የሚያጠናበትን መጽሐፍ አልፈልግም ብሎ እስከመወርወር ደርሶ ነበር። ይሁን እንጂ ባለመሰልቸት አነጋግረው ስለነበር እንደገና ጥናቱን ቀጠለ። እሱም እንዲሁ ሽማግሌ ሆኖ በማገልገል ላይ ነው።” ጄምስ በሥራ ቦታ መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነት በመስጠቱ በአጠቃላይ 11 ሰዎች እውነተኛ ክርስቲያኖች ለመሆን በቅተዋል።

እጅግ አስደናቂ ውጤት

በቪክቶሪያ ሐይቅ ዳርቻ በምትገኝ አንዲት አነስተኛ መንደር በአንድ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የሟች ወዳጆችና ዘመዶች ተሰብስበዋል። አንድ አረጋዊ ምሥክርም ከለቀስተኞቹ መካከል ነበር። ዶሊ ወደምትባል አንዲት መምህር ጠጋ ብሎ ሙታን ስለሚገኙበት ሁኔታና ይሖዋ ሞትን ለዘላለም ለማስወገድ ስላለው ዓላማ ገለጸላት። በፊቷ ላይ የሚነበበውን ደስታ በመመልከት “ወደምትኖሪበት ከተማ ስትመለሺ አንድ ሚስዮናዊ ወንድማችን መጥቶ መጽሐፍ ቅዱስን ያስተምርሻል” በማለት አረጋገጠላት።

ዶሊ የምትኖርበት ከተማ በኬንያ ውስጥ በትልቅነቱ ሦስተኛ ነው። በወቅቱ በከተማው ውስጥ የሚያገለግሉት አራት ሚስዮናውያን ብቻ ነበሩ። አረጋዊው ወንድም ዶሊን እንዲያነጋግሯት የትኛውንም ሚስዮናዊ አልጠየቀም። ብቻ አግኝተው እንደሚያነጋግሯት ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነበር። እንዳሰበውም አግኝተዋታል! ከጥቂት ጊዜ በኋላ አንዲት ሚስዮናዊት እህት ዶሊን አገኘቻትና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመሩ። አሁን ዶሊ የተጠመቀች እህት ሆናለች፤ ትንሿ ልጅ በቲኦክራሲያዊ አገልግሎት ትምህርት ቤት የተመዘገበች ሲሆን ሁለት ወንዶች ልጆችዋም ተጠምቀዋል። እሷም በአቅኚዎች አገልግሎት ትምህርት ቤት ተካፍላለች።

የተገኘውን ጭማሪ ለማስተናገድ የተደረገ እንቅስቃሴ

መደበኛ ላልሆነ ምሥክርነት ትኩረት መሰጠቱ በኬንያ ውስጥ ብዙ ሰዎች ምሥራቹን እንዲሰሙ አስችሏል። ከ15, 000 የሚበልጡ አስፋፊዎች በጣም አስፈላጊ በሆነ በዚህ ሥራ በትጋት እየተካፈሉ ሲሆን ባለፈው ዓመት ከ41, 000 የሚበልጡ ሰዎች በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝተው ነበር። በመላው ኬንያ የጉባኤ ተሰብሳቢዎች ቁጥር ብዙውን ጊዜ ከአስፋፊዎች ቁጥር ሁለት እጥፍ ይበልጣል። በዚህ ምክንያት ተጨማሪ የመንግሥት አዳራሾች መገንባት አስፈለገ።

የመንግሥት አዳራሾች በትላልቅ ከተማዎችም ሆነ ራቅ ብለው በሚገኙ አካባቢዎች በመሠራት ላይ ናቸው። የመንግሥት አዳራሽ ከተሠራባቸው ቦታዎች አንዱ ከናይሮቢ በስተ ሰሜን ምሥራቅ 320 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው ሳምቡሩ የሚባለው ገለልተኛ ክልል ነው። በ1934 ከተማዋ ማራለል (በሳምቡሩ ቋንቋ የሚያንጸባርቅ ማለት ነው) የሚል ስያሜ የተሰጣት ሲሆን ይህንንም ስያሜ ያገኘችው የመጀመሪያው የቆርቆሮ ክዳን ቤት ፀሐይ ሲያርፍበት ያንጸባርቅ ስለነበረ ነው። ከስልሳ ሁለት ዓመት በኋላ በማራለል የቆርቆሮ ክዳን ያለው ሌላ አዳራሽ ተሠራ። ይኸኛውም አዳራሽ ቢሆን የእውነተኛ አምልኮ ቦታ ስለሆነ “ያብረቀርቃል” ወይም “ያንጸባርቃል” ሊባል ይቻላል።

በኬንያ በጣም ርቆ በሚገኘው በዚህ ክልል የመጀመሪያውን የመንግሥት አዳራሽ ለመሥራት 15 አስፋፊዎች ብዙ ደክመዋል። ገንዘባቸው በጣም አነስተኛ ስለነበር ወንድሞች በአካባቢው በሚገኙ የግንባታ ዕቃዎች ለመጠቀም ተገደዋል። ለግድግዳው የሚሆን ጠርብ እንጨት ከማገሩ በኋላ ቀይ አፈር አቡክተው መረጉት። ከዚያም እበትና አመድ አንድ ላይ አቡክተው ግድግዳውን የለሰኑት ሲሆን ይህ መሆኑ ለተወሰኑ ዓመታት እንዲቆይ ያደርገዋል።

ወንድሞች አዳራሹን የሚሠሩበትን አጣና ለማግኘት ዛፍ ለመቁረጥ የሚያስችላቸው ፈቃድ አወጡ። ሆኖም በጣም ቅርብ ነው የሚባለው ጫካ 10 ኪሎ ሜትር ያህል ይርቃል። ወንድሞችና እህቶች ጫካ ሄደው ዛፎችን ቆርጠውና መልምለው ወደ ግንባታው ቦታ ተሸክመው ማጓጓዝ ነበረባቸው። ወንድሞች አንድ ቀን ከጫካ ሲመለሱ ፖሊስ ካስቆማቸው በኋላ ፈቃዳችሁ አይሠራም አላቸው። ፖሊሱ ልዩ አቅኚውን ዛፍ ስለቆረጠ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ነገረው። የአካባቢው ሕዝብና ፖሊስ በደንብ የሚያውቃት በዚያ የምትኖር አንዲት እህት ፖሊሱን:- “ወንድማችንን የምታስር ከሆነ እኛንም አብረህ ማሰር አለብህ፤ ምክንያቱም ዛፍ የቆረጥነው ሁላችንም ነን!” አለችው። ፖሊሱ ሁሉም እንዲሄዱ ፈቀደላቸው።

ጫካው ውስጥ የዱር አራዊት ስላሉ ወደዚያ መሄድ አደጋ ሊያስከትል ይችላል። አንድ ቀን አንዲት እህት የቆረጠችው ዛፍ መሬት ላይ ዧ ብሎ ሲወድቅ አንድ አውሬ ከተኛበት ተስፈንጥሮ ሲሮጥ አየች። በጨረፍታ ያየችው አውሬ ድኩላ መስሏት ነበር። ሆኖም ኮቴውን አይታ አንበሳ እንደነበረ ተረዳች! ወንድሞች ይህን የመሰለ አደጋ ቢያጋጥማቸውም አዳራሹን ሠርተው የጨረሱ ሲሆን ቦታው ለይሖዋ “አንጸባራቂ” ውዳሴ የሚያመጣ ሆኗል።

የካቲት 1, 1963 በኬንያ ቲኦክራሲያዊ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠው ቀን ነው። በዚህ ዕለት 7.4 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው አንድ ክፍል ቤት የመጀመሪያው ቅርንጫፍ ቢሮ በመሆን ተከፈተ። በኬንያ ቲኦክራሲያዊ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ከፋች የሆነው ሌላው ዕለት ደግሞ ጥቅምት 25, 1997 ነው። በዚህ ዕለት በ7, 800 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የተሠራው አዲሱ የቤቴል ቤት ለአምላክ አገልግሎት ተወሰነ! ከሦስት ዓመት ከፍተኛ ድካም በኋላ የተገኘ ታላቅ ውጤት ነበር። ከ25 አገሮች የመጡ ፈቃደኛ ሠራተኞች አረም ወርሶትና ጨቅይቶ የነበረውን 3.2 ሄክታር ቦታ አስተካክለው 80 የቤቴል ቤተሰብ አባላትን የሚይዝ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ በመሥራት ማራኪ ዕይታ ያለው አካባቢ አደረጉት።

ይሖዋ ለሕዝቡ ስላደረገው ነገር እሱን የምናመሰግንበት በቂ ምክንያት አለን። ኬንያ አስደናቂ መንፈሳዊ ውበት የሞላባት አገር እንድትሆን አገልጋዮቹ ልባቸውን አስፍተው ምሥራቹ የተገባቸውን ሰዎች እንዲፈልጉ ብርታት ስለሰጣቸው ምስጋና ይድረሰው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።