ከድህነት ጋር የሚደረገውን ውጊያ በድል መወጣት ይቻል ይሆን?
ከድህነት ጋር የሚደረገውን ውጊያ በድል መወጣት ይቻል ይሆን?
በኒው ዮርክ ከተማ የሚገኘውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚጎበኙ ሰዎች በኢኮኖሚና ማኀበራዊ ጉዳዮች ምክር ቤት ሕንጻ የሕዝብ መተላለፊያ ጣሪያ ላይ በግልጽ የሚታዩ የውኃ ቧንቧዎች እንዲሁም የኤሌክትሪክና የስልክ መሥመሮች ይመለከታሉ። አስጎብኚው እንደሚከተለው ሲል ያብራራል:- “ይህ ‘ያላለቀ’ ጣሪያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኢኮኖሚያዊና በማኅበራዊ ጉዳዮች ረገድ የሚያከናውነው ተግባር መቋጫ የሌለው በመሆኑ የዓለምን ሕዝብ የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ሁልጊዜ የተሻለ ነገር ማድረግ እንደሚቻል የሚያሳይ ምሳሌያዊ ማሳሰቢያ ተደርጎ መታየቱ የተለመደ ነው።”
ምንም እንኳ ምክር ቤቱ የቆመለት በጎ ዓላማ ሁሉም ሰው ከፍተኛ የኑሮ ደረጃ እንዲኖረው ሁኔታዎችን ማመቻቸት ቢሆንም ሥራው የሚያልቅ አይመስልም። ኢየሱስ ክርስቶስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ምድራዊ አገልግሎቱን ሲያከናውን “የጌታ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፣ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና” ብሎ መናገሩ ትኩረት የሚስብ ነው። (ሉቃስ 4:17-19) ኢየሱስ የሰበከው “ወንጌል” ምን ነበር? “ለችግረኛው በጭን[ቅ] ጊዜ መጠጊያ” የሆነው ይሖዋ አምላክ ኢየሱስ ክርስቶስን ንጉሥ አድርጎ በመሾም ስለሚያቋቁመው መንግሥት የሚናገር መልእክት ነው። ይህ መንግሥት የሚያከናውነው ምንድን ነው? ኢሳይያስ አስቀድሞ እንዲህ በማለት ትንቢት ተናግሮአል:- “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ለሕዝብ ሁሉ . . . ታላቅ የሰባ ግብዣ፣ ያረጀ የወይን ጠጅ፣ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፣ የጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ ያደርጋል። ሞትን ለዘላለም ይውጣል፣ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል።”—ኢሳይያስ 25:4-6, 8
የአምላክ መንግሥት ‘የዓለምን ሕዝብ የኑሮ ደረጃ በማሻሻል’ ድህነትን የሚያስወግደው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ትፈልጋለህ? ብቃት ያለው አስተማሪ መጥቶ መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን በመሰሉ ጉዳዮች ላይ ምን እንደሚል እንዲያሳይህ ከታች ያለውን መረጃ ተመልከት።