በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቁጣው ቀን ሳይመጣ ይሖዋን ፈልጉ

የቁጣው ቀን ሳይመጣ ይሖዋን ፈልጉ

የቁጣው ቀን ሳይመጣ ይሖዋን ፈልጉ

“እግዚአብሔርን ፈልጉ፣ ጽድቅንም ፈልጉ፣ ትሕትናንም ፈልጉ፤ ምናልባት በእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።”​—⁠ሶፎንያስ 2:3

1. ሶፎንያስ ትንቢታዊ ሥራውን ሲጀምር የይሁዳ መንፈሳዊ ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

 ሶፎንያስ የነቢይነት ሥራውን የጀመረው በይሁዳ ታሪክ ውስጥ በጣም ወሳኝ በሆነ ወቅት ነው። የብሔሩ መንፈሳዊ ሁኔታ እጅግ አሽቆልቁሎ ነበር። ሕዝቡ በይሖዋ አምላክ ከመታመን ይልቅ መመሪያ ይጠይቁ የነበረው ከአረማዊ ካህናትና ከኮከብ ቆጣሪዎች ነበር። የበኣል አምልኮ ከመራባት ሥርዓተ አምልኮው ጋር በምድሪቱ በሙሉ ተስፋፍቶ ነበር። የሕዝቡ መሪዎች ማለትም መሳፍንቱ፣ መኳንንቱና ዳኞቹ ሊጠብቋቸው የሚገቡትን ሰዎች ይጨቁኑ ነበር። (ሶፎንያስ 1:​9፤ 3:​3) ይሖዋ ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት ሲል ‘እጁን ለመዘርጋት’ መወሰኑ ምንም አያስደንቅም!​—⁠ሶፎንያስ 1:​4

2. በይሁዳ የነበሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ምን ተስፋ ነበራቸው?

2 ሁኔታው ይህን ያህል የከፋ ቢሆንም የተስፋ ጭላንጭል ፈጽሞ የሌለው አልነበረም። በዚህ ጊዜ የአሞጽ ልጅ ኢዮስያስ ዙፋን ላይ ተቀምጧል። ኢዮስያስ ገና ልጅ የነበረ ቢሆንም ለይሖዋ ልባዊ ፍቅር ነበረው። አዲሱ ንጉሥ እውነተኛውን አምልኮ በይሁዳ መልሶ ቢያቋቁም አምላክን በታማኝነት ያገለግሉ የነበሩ ጥቂት ሰዎች ምንኛ ይጽናኑ ይሆን! ሌሎች ሰዎችም ከእነሱ ጋር ለመተባበር ይነሳሱ ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ከይሖዋ የቁጣ ቀን እንዲድኑ በር ይከፍትላቸዋል።

ለመዳን የሚያስፈልጉ ብቃቶች

3, 4. አንድ ግለሰብ ‘ከይሖዋ የቁጣ ቀን’ ለመትረፍ ማሟላት ያለበት ሦስት ብቃቶች ምንድን ናቸው?

3 ከይሖዋ የቁጣ ቀን ሊድኑ የሚችሉ ግለሰቦች ይኖሩ ይሆን? አዎን፣ በሶፎንያስ 2:​2, 3 ላይ የተዘረዘሩትን ሦስት ቅድመ ሁኔታዎች ካሟሉ ሊድኑ ይችላሉ። እነዚህን ቁጥሮች በምናነብበት ጊዜ በእነዚህ ብቃቶች ላይ ልዩ ትኩረት እናድርግ። ሶፎንያስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ትእዛዝ ሳይወጣ፣ ቀኑም እንደ ገለባ ሳያልፍ፣ የእግዚአብሔርም ቁጣ ትኩሳት ሳይመጣባችሁ፣ የእግዚአብሔርም ቁጣ ቀን ሳይደርስባችሁ . . . እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ፈልጉ፤ ጽድቅንም ፈልጉ፣ ትሕትናንም ፈልጉ፤ ምናልባት በእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።”

4 ስለዚህ አንድ ሰው ለመዳን ከፈለገ (1) ይሖዋን፣ (2) ጽድቅንና (3) ትሕትናን መፈለግ ይኖርበታል። እነዚህ ብቃቶች በዛሬው ጊዜ ለእኛ ከፍተኛ ትርጉም ያላቸው ሊሆኑ ይገባል። ለምን? በሰባተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ፊት የፍርድ ቀን ተደቅኖ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም የሕዝበ ክርስትና ብሔራት፣ እንዲያውም ክፉዎች በሙሉ በመጪው “ታላቅ መከራ” ከይሖዋ ጋር ግንባር ለግንባር ይፋጠጣሉ። (ማቴዎስ 24:​21) በዚያ ጊዜ ከጥፋት ለመሰወር የሚፈልግ ሁሉ አሁኑኑ ወሳኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል። እንዴት? ጊዜው ከማለቁ በፊት ይሖዋን በመፈለግ፣ ጽድቅን በመፈለግና ትሕትናን በመፈለግ ነዋ!

5. በዛሬው ጊዜ ‘ይሖዋን መፈለግ’ ምን ነገር ያካትታል?

5 ‘ራሴን ወስኜ የተጠመቅሁና አምላክን የማገለግል የይሖዋ ምሥክር ነኝ። ታዲያ እነዚህን ብቃቶች አሟልቼ የለም እንዴ?’ ትል ይሆናል። ይህ ጉዳይ ራሳችንን ለይሖዋ በመወሰን ብቻ የሚያበቃ አይደለም። እስራኤል ራሱን ለይሖዋ የወሰነ ብሔር ነበር። ይሁን እንጂ በሶፎንያስ ዘመን የነበሩት የይሖዋ ሕዝቦች ይህን ውሳኔ ጠብቀው አልተገኙም። በዚህም የተነሳ በመጨረሻ አምላክ ብሔሩን እርግፍ አድርጎ ተወው። ዛሬም ቢሆን ‘ይሖዋን መፈለግ’ ከምድራዊ ድርጅቱ ጋር በመተባበር ከእርሱ ጋር ሞቅ ያለና የተቀራረበ ዝምድና መመሥረትንና ይህንንም ዝምድና ጠብቆ መኖርን ይጠይቃል። የአምላክን ስሜት በንቃት መከታተልና እርሱ ጉዳዮችን እንዴት እንደሚመለከት ማወቅ ማለት ነው። ቃሉን በጥንቃቄ በማንበብ፣ በማሰላሰልና ምክሩን በሕይወታችን በሥራ በማዋል ይሖዋን እንፈልጋለን። በተጨማሪም ልባዊ ጸሎት በማቅረብ የይሖዋን መመሪያ ስንጠይቅና የመንፈስ ቅዱሱን አመራር ስንከተል ከእሱ ጋር ያለን ዝምድና ጥልቀት እያገኘ ከመሄዱም በላይ እሱን ‘በፍጹም ልባችን፣ ነፍሳችንና ኃይላችን’ ለማገልገል እንገፋፋለን።​—⁠ዘዳግም 6:​5፤ ገላትያ 5:​22-25፤ ፊልጵስዩስ 4:​6, 7፤ ራእይ 4:​11

6. ‘ጽድቅን የምንፈልገው’ እንዴት ነው? በዚህ ዓለም እንኳ ይህ የሚቻል የሆነው ለምንድን ነው?

6 ሶፎንያስ 2:​3 ላይ የተጠቀሰው ሁለተኛው ብቃት ‘ጽድቅን መፈለግ’ ነው። አብዛኞቻችን ክርስቲያናዊ ጥምቀት የሚጠይቀውን ብቃት ለማሟላት አስፈላጊ የሆኑ ለውጦችን አድርገናል። ይሁን እንጂ የይሖዋን የጽድቅ ሕጎች በመላ ሕይወታችን ማክበራችንን መቀጠል ይኖርብናል። በዚህ ረገድ ጥሩ ጅምር የነበራቸው አንዳንድ ሰዎች በዓለም እንዲቆሽሹ ፈቅደዋል። የፆታ ብልግናን፣ መዋሸትንና ሌሎች ኃጢአቶችን እንደ ተራ ነገር በሚቆጥሩ ሰዎች ስለተከበብን ጽድቅን መፈለግ ቀላል አይደለም። ቢሆንም ይሖዋን ለማስደሰት ያለን ጠንካራ ፍላጎት ከዓለም ጋር በመዋሃድ ማንኛውንም በዓለም ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት ፍላጎት ሊያሸንፍ ይችላል። ይሁዳ የይሖዋን ሞገስ ያጣችው አረማውያን የሆኑ ጎረቤቶችዋን ለመምሰል ስለ ሞከረች ነው። ዓለምን ከመምሰል ይልቅ “ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው” በመኮትኮት ‘እግዚአብሔርን የምንመስል’ እንሁን።​—⁠ኤፌሶን 4:​24፤ 5:​1

7. ‘ትሕትናን የምንፈልገው’ እንዴት ነው?

7 ከይሖዋ የቁጣ ቀን መትረፍ ከፈለግን ሶፎንያስ 2:​3 ላይ የተጠቀሰው ሦስተኛው ነጥብ “ትሕትናን” መፈለግ ነው። በየቀኑ ትሁታን ካልሆኑ ወንዶች፣ ሴቶችና ወጣቶች ጋር እንገናኛለን። የዋህ መሆን ለእነዚህ ሰዎች ደካማነት ነው። እሺ ባይ መሆንም ትልቅ ድክመት እንደሆነ ይታሰባል። “መብታቸውና” ምርጫቸው እንደ ሆነ የሚያስቡትን ነገር በውድም ሆነ በግድ ሊሟላላቸው እንደሚገባ ስለሚያምኑ በቃኝ ማለትን የማያውቁ፣ ራስ ወዳዶችና ሐሳበ ግትሮች ናቸው። ከእነዚህ ዝንባሌዎች መካከል ጥቂቶቹ ሊጋቡብን ቢጀምሩ ምንኛ አሳዛኝ ይሆናል! ‘ትሕትናን የምንፈልግበት’ ጊዜ አሁን ነው። እንዴት? የአምላክን ተግሳጽ በትሕትና በመቀበልና ከፈቃዱ ጋር በመስማማት ለእሱ ተገዥ በመሆን ነው።

መሰወራችን “ምናልባት” የተባለው ለምንድን ነው?

8. ሶፎንያስ 2:​3 ላይ የተሠራበት “ምናልባት” የሚለው ቃል ምን ያመለክታል?

8 ሶፎንያስ 2:​3 “ምናልባት በእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል” እንደሚል ልብ በል። ሶፎንያስ ‘ለምድር ትሑታን’ በተናገረው ቃል ላይ “ምናልባት” የሚለውን ቃል የተጠቀመው ለምንድን ነው? እነዚህ ትሑታን ሰዎች ተገቢ የሆኑ እርምጃዎች ቢወስዱም እንኳ በራሳቸው ሊመኩ አይችሉም። የሕይወታቸውን ጎዳና በታማኝነት አጠናቅቀው አልጨረሱም። አንዳንዶቻቸው በኃጢአት ሊወድቁ ይችላሉ። የእኛም ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም። ኢየሱስ “እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል” ብሏል። (ማቴዎስ 24:​13) አዎን፣ ከይሖዋ ቁጣ መዳናችን የተመካው በእሱ ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር ማድረጋችንን በመቀጠላችን ላይ ነው። ይህን ለማድረግ ቆርጠሃል?

9. ወጣቱ ንጉሥ ኢዮስያስ የወሰዳቸው ገንቢ እርምጃዎች ምንድን ናቸው?

9 በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ንጉሥ ኢዮስያስ ለሶፎንያስ ቃል ምላሽ በመስጠት ‘ይሖዋን ለመፈለግ’ ተነሳስቷል። ቅዱሳን ጽሑፎች እንዲህ ይላሉ:- “[ኢዮስያስ] በነገሠም በስምንተኛው ዓመት ገና ብላቴና [ወደ 16 ዓመት ገደማ] ሳለ የአባቱን የዳዊትን አምላክ ይፈልግ ጀመር።” (2 ዜና መዋዕል 34:​3) በተጨማሪም ኢዮስያስ ‘ጽድቅን መፈለጉን’ ቀጥሏል። እንዲህ የሚል እናነባለን:- “በአሥራ ሁለተኛውም ዓመት [ኢዮስያስ 20 ዓመት በሆነው ጊዜ] ይሁዳንና ኢየሩሳሌምን ከኮረብታው መስገጃዎችና ከማምለኪያ ዐፀዶቹ፣ ከተቀረጹትና ቀልጠው ከተሠሩት ምስሎች ያነፃ ጀመር። የበኣሊምንም መሠዊያዎች በፊቱ አፈረሱ።” (2 ዜና መዋዕል 34:​3, 4) ኢዮስያስ ‘ትሕትናንም ፈልጓል።’ በመሆኑም ምድሪቱን ከጣዖት አምልኮና ከሌሎች የሐሰት ሃይማኖት ልማዶች በማንጻት ይሖዋን ለማስደሰት በትሕትና እርምጃ ወስዷል። በዚህ እርምጃው ሌሎች ትሑታን ሰዎች ምን ያህል ተደስተው ይሆን!

10. በ607 ከዘአበ በይሁዳ ላይ የደረሰው ነገር ምን ነበር? ሆኖም በሕይወት የተረፉት እነማን ነበሩ?

10 በኢዮስያስ ዘመን ብዙ አይሁዳውያን ወደ ይሖዋ ተመልሰዋል። ንጉሡ ከሞተ በኋላ ግን አብዛኞቹ ወደ ቀድሞ መንገዳቸው ማለትም በአምላክ ዘንድ ፈጽሞ ተቀባይነት ወደሌላቸው ልማዶች ተመልሰዋል። ይሖዋ ባስተላለፈው ብያኔ መሠረት በ607 ከዘአበ ባቢሎናውያን ይሁዳን አሸንፈው ዋና ከተማዋን ኢየሩሳሌምን አወደሙ። ሆኖም ከጥፋቱ የዳኑ ነበሩ። ነቢዩ ኤርምያስ፣ ኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ፣ የኢዮናዳብ ዝርያዎች እንዲሁም ለአምላክ ታማኝ የነበሩ ሌሎች ሰዎች ከይሖዋ የቁጣ ቀን ተሰውረዋል።​—⁠ኤርምያስ 35:​18, 19፤ 39:​11, 12, 15-18

የአምላክ ጠላቶች ተጠንቀቁ!

11. በዛሬው ጊዜ ለአምላክ ታማኝ መሆን ተፈታታኝ የሆነው ለምንድን ነው? ሆኖም የይሖዋ ሕዝብ ጠላቶች የትኛውን ጉዳይ ቢያጤኑበት ይበጃቸዋል?

11 በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ የይሖዋ ቁጣ የሚገለጥበትን ቀን ስንጠብቅ ‘ልዩ ልዩ ፈተና ይደርስብናል።’ (ያዕቆብ 1:​2) ለአምልኮ ነፃነት ትልቅ ዋጋ እንሰጣለን በሚሉ በርካታ አገሮች መሠሪ ቀሳውስት ከዓለማዊ ባለ ሥልጣናት ጋር ያላቸውን ቅርርብ በመጠቀም በአምላክ ሕዝቦች ላይ አሰቃቂ ስደት አስነስተዋል። ይሉኝታ የሌላቸው ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮችን ስም በማጥፋት “አደገኛ ኑፋቄዎች” ናቸው ይላሉ። አምላክ እንደነዚህ ያሉትን ድርጊቶች ስለሚያውቅ ከቅጣት አያመልጡም። ጠላቶቹ እንደ ፍልስጤማውያን ባሉ የጥንት የአምላክ ሕዝቦች ጠላቶች ላይ ምን እንደደረሰ ቢገነዘቡ ይበጃቸዋል። ትንቢቱ እንዲህ ይላል:- “ጋዛ ትበረበራለች፣ አስቀሎናም ባድማ ትሆናለች፤ አዛጦንንም በቀትር ወደ ውጭ ያሳድዱአታል። አቃሮንም ትነቀላለች።” የፍልስጥኤማውያን ከተሞች የሆኑት ጋዛ፣ አስቀሎና፣ አዛጦንና አቃሮን ይወድማሉ።​—⁠ሶፎንያስ 2:​4-7

12. ፍልስጥኤም፣ ሞአብና አሞን ምን ነገር ደርሶባቸዋል?

12 ትንቢቱ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “በሕዝቤም ላይ ያላገጡባትን፣ በድንበራቸውም ላይ እየታበዩ የተናገሩባትን የሞዓብን ማላገጥና የአሞንን ልጆች ስድብ ሰምቻለሁ።” (ሶፎንያስ 2:​8) እርግጥ፣ ግብፅና ኢትዮጵያ በባቢሎናውያን ወራሪዎች እጅ ጥቃት ደርሶባቸዋል። ሆኖም የአብርሃም ወንድም ልጅ የነበረው የሎጥ ተወላጆች በሆኑት በሞዓብና በአሞን ላይ አምላክ የበየነው ፍርድ ምን ነበር? ይሖዋ እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “በእርግጥ ሞዓብ እንደ ሰዶም፣ የአሞንም ልጆች እንደ ገሞራ” ይሆናሉ። ኩሩዎቹ ሞዓብና አሞን በሰዶምና ገሞራ ላይ ከደረሰው ጥፋት እንደተረፉትና ቅድመ አያቶቻቸው እንደነበሩት እንደ ሁለቱ የሎጥ ሴት ልጆች ከአምላክ ፍርድ አያመልጡም። (ሶፎንያስ 2:​9-12፤ ዘፍጥረት 19:​16, 23-26, 36-38) ዛሬ የፍልስጥኤም ከተሞች የት ናቸው? በአንድ ወቅት ኩሩዎች የነበሩት ሞዓብና አሞንስ? ምንም ያህል ፍለጋ ብታደርጉ እንኳ ልታገኟቸው አትችሉም።

13. በነነዌ በመሬት ቁፋፎ የተገኘው ምንድን ነው?

13 በሶፎንያስ ዘመን የአሦር አጼያዊ መንግሥት ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይገኝ ነበር። የመሬት ቁፋሮ ተመራማሪ የሆኑት አውስተን ላያርድ የአሦር ዋና ከተማ በነበረችው በነነዌ በቁፋሮ ስላገኙት የአንድ ቤተ መንግሥት ክፍል ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል:- “ኮርኒሶቹ . . . በአራት ማዕዘናት የተከፋፈሉ፣ በአበባዎች ወይም በእንስሳት ሥዕሎች ያሸበረቁ ናቸው። እያንዳንዱ ክፍል በሚያማምሩ ጠርዞችና ቅርጾች የተከበበ ከመሆኑም በላይ አንዳንዶቹ በዝሆን ጥርስ የተለበጡ ናቸው። የክፍሎቹ ግድግዳዎችና ቅስቶች በወርቅና በብር የተለበጡ ከመሆናቸውም በላይ እንደ ዝግባ ካሉት ብርቅ እንጨቶች በቀር ተራ የሆኑ እንጨቶች አልገቡባቸውም።” በሶፎንያስ ትንቢት ላይ እንደተነገረው አሦር የምትጠፋ ሲሆን ዋና ከተማዋ ነነዌ ደግሞ “ባድማ” ትሆናለች።​—⁠ሶፎንያስ 2:​13

14. የሶፎንያስ ትንቢት በነነዌ ላይ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነበር?

14 ሶፎንያስ ይህን ትንቢት ከተናገረ ከ15 ዓመት በኋላ ቤተ መንግሥቷ የፍርስራሽ ክምር በመሆን ኃያል የነበረችው ነነዌ ወደመች። አዎን፣ ኩሩዋ ከተማ ትቢያ ሆነች። የጥፋቷ ስፋት ቀጥሎ ባሉት ቃላት በጥሩ ሁኔታ ተተንብዮአል:- “ይብራና ጃርት [በወደቁት] በዓምዶችዋ መካከል ያድራሉ፤ ድምፃቸው በመስኮቶችዋ ይጮኻል . . . በመድረኮችዋ ላይ ጥፋት ይሆናል።” (ሶፎንያስ 2:​14, 15) ግዙፎቹ የነነዌ ሕንፃዎች ለይብራና ለጃርት መኖሪያነት ካልሆነ በቀር ለምንም የማይጠቅሙ ይሆናሉ። በንግድ እንቅስቃሴ ምክንያት የሚሰሙ ጫጫታዎች፣ የጦረኞች ጩኸት፣ የካህናት ዝማሬ ከከተማይቱ ጎዳናዎች ይወገዳሉ። በአንድ ወቅት ይሰማ በነበረው የከተማ ትርምስ ምትክ ከመስኮት የሚሰማ ጭው ያለ ድምፅ ወይም የአእዋፍ ጩኸት ወይም የነፋስ ሽውታ ብቻ ይሰማል። ሁሉም የአምላክ ጠላቶች ይህን የመሰለ ዕጣ ይደርስባቸዋል!

15. በፍልስጥኤም፣ በሞአብ፣ በአሞንና በአሦር ላይ ከደረሰው ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

15 በፍልስጥኤም፣ በሞዓብ፣ በአሞንና በአሦር ላይ ከደረሰባቸው ነገር ምን መማር እንችላለን? የይሖዋ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ጠላቶቻችንን የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለም። አምላክ ሕዝቡን የሚቃወሙት ሰዎች የሚያደርጉትን ያያል። ይሖዋ ከዚህ ቀደም በጠላቶቹ ላይ እርምጃ ወስዷል። ዛሬም ፍርዱ በመላይቱ ምድር ላይ ይመጣል። ሆኖም ከጥፋቱ የሚድኑ ‘ከብሔራት ሁሉ የተውጣጡ እጅግ ብዙ ሰዎች’ ይኖራሉ። (ራእይ 7:​9) አንተም ይሖዋን፣ ጽድቅንና ትሕትናን በመፈለግ ከቀጠልክ ከእነርሱ መካከል ለመሆን ትችላለህ።

ቅሌታም ጥፋተኞች ወዮላቸው!

16. የሶፎንያስ ትንቢት የይሁዳን መሳፍንትና ሃይማኖታዊ መሪዎች በተመለከተ ምን ይላል? እነዚህ ቃላትስ በሕዝበ ክርስትና ላይ ተፈጻሚነት የሚኖራቸው ለምንድን ነው?

16 የሶፎንያስ ትንቢት እንደገና በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ አነጣጥሯል። ሶፎንያስ 3:​1, 2 እንዲህ ይላል:- “ለዓመፀኛይቱና ለረከሰች ለአስጨናቂይቱም ከተማ ወዮላት! ድምፅን አልሰማችም፣ ተግሣጽንም አልተቀበለችም፤ በእግዚአብሔርም አልታመነችም፣ ወደ አምላክዋም አልቀረበችም።” ይሖዋ ሕዝቦቹን ለመገሠፅ ያደረገው ጥረት ተቀባይነት ማጣቱ ምንኛ የሚያሳዝን ነው! በእርግጥም የመሳፍንቱ፣ የመኳንንቱና የፈራጆቹ ክፋት የሚያስጠላ ነበር። ሶፎንያስ ስለ ሃይማኖታዊ መሪዎቹ ዕፍረተ ቢስነት እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ነቢያቶችዋ ቅሌታሞችና ተንኰለኞች ሰዎች ናቸው፤ ካህናቶችዋም መቅደሱን አርክሰዋል፣ በሕግም ላይ ግፍ ሠርተዋል።” (ሶፎንያስ 3:​3, 4) እነዚህ ለዛሬዎቹ የሕዝበ ክርስትና ነቢያትና ካህናት ምንኛ የሚስማሙ ቃላት ናቸው! ከቅሌታቸው የተነሳ መለኮታዊውን ስም ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻቸው አውጥተዋል። እናመልከዋለን የሚሉትን አምላክ የማያስከብሩ መሠረተ ትምህርቶች ያስተምራሉ።

17. ሰዎች ቢሰሙም ባይሰሙም ምሥራቹን ማወጃችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?

17 ይሖዋ ሊወስድ ስላለው እርምጃ የጥንት ሕዝቦቹን በአሳቢነት አስጠንቅቋል። አገልጋዮቹ የሆኑትን እንደ ሶፎንያስና ኤርምያስ ያሉ ነቢያቱን እንዲሁም ሌሎችን በመላክ ሕዝቦቹ ንሥሐ እንዲገቡ ተማጽኗል። አዎን፣ “እግዚአብሔር . . . ክፋትን አያደርግም፤ ፍርዱን በየማለዳው ወደ ብርሃን ያወጣል፣ ሳያወጣውም አይቀርም።” ምላሹ ምን ነበር? ሶፎንያስ “ዓመፀኛው ግን እፍረትን አያውቅም” ብሏል። (ሶፎንያስ 3:​5) በአሁኑ ጊዜም ተመሳሳይ የሆነ ማስጠንቀቂያ እየተሰማ ነው። የምሥራቹ አስፋፊ ከሆንክ በዚህ የማስጠንቀቅ ሥራ እየተካፈልክ ነው። ምሥራቹን አለማሰለስ ማወጅህን ቀጥል! ሰዎቹ ቢሰሙም ባይሰሙም ሥራህን በታማኝነት እስካከናወንክ ድረስ አገልግሎትህ በአምላክ ዘንድ የተሳካ ነው። የአምላክን ሥራ በቅንዓት በመሥራትህ ምንም የምታፍርበት ምክንያት የለም።

18. ሶፎንያስ 3:​6 ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ይሆናል?

18 የአምላክ የቅጣት ፍርድ በሕዝበ ክርስትና ላይ በሚደርሰው ጥፋት ላይ ብቻ ተወስኖ አይቀርም። ይሖዋ መላውን ብሔራት አውግዟል:- “አሕዛብን አጥፍቻለሁ፤ ግንቦቻቸው ሁሉ ፈርሰዋል፤ መንገዳቸውን ማንም እንዳያልፍባት ምድረ በዳ አድርጌአለሁ፣ ከተሞቻቸውም . . . ፈርሰዋል።” (ሶፎንያስ 3:​6) እነዚህ ቃላት በጣም አስተማማኝ ከመሆናቸው የተነሳ ይሖዋ ስለ ጥፋቱ የተናገረው እንደተፈጸመ አድርጎ ነው። በፍልስጥኤም፣ በሞዓብና በአሞን ከተማዎች ላይ የደረሰው ምንድን ነው? የአሦራውያን ዋና ከተማ በነበረችው በነነዌስ ላይ? በነዚህ ከተሞች ላይ የደረሰው ጥፋት ለዛሬዎቹ ብሔራት ማስጠንቀቂያ ይሆናቸዋል። አምላክ አይዘበትበትም።

ይሖዋን መፈለጋችሁን ቀጥሉ

19. የትኞቹን አእምሮ የሚያመራምሩ ጥያቄዎች መጠየቅ እንችላለን?

19 በሶፎንያስ ዘመን በክፋት ‘ድርጊታቸውን ሁሉ ባረከሱት’ ሰዎች ላይ የአምላክ ቁጣ ወርዶ ነበር። (ሶፎንያስ 3:​7) በእኛም ጊዜ ተመሳሳይ ነገር ይፈጸማል። የይሖዋ ቁጣ ቀን ቅርብ እንደሆነ ማስረጃዎቹ ይታዩሃል? ቃሉን አዘውትረህ፣ በየዕለቱ በማንበብ ‘ይሖዋን መፈለግህን’ ቀጥለሃል? ከአምላክ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምተህ በንጹሕ ሥነ ምግባር በመመላለስ ‘ጽድቅን በመፈለግ’ ላይ ነህ? እንዲሁም ለአምላክና አምላክ ላዘጋጀው የመዳን ዝግጅት ራስህን በማስገዛት እንዲሁም ገር በመሆን ‘ትሕትናን በመፈለግ’ ላይ ነህ?

20. በሶፎንያስ ትንቢት ላይ በተከታታይ ከቀረቡት የመጨረሻ በሆነው ርዕስ ላይ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

20 በታማኝነት ይሖዋን፣ ጽድቅንና ትሕትናን መፈለጋችንን ከቀጠልን አሁንም ቢሆን አዎን፣ በዚህ እምነት ፈታኝ በሆነው ‘የመጨረሻ ቀን’ እንኳ ብዙ በረከቶች እናገኛለን። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5፤ ምሳሌ 10:​22) ሆኖም እንዲህ ብለን መጠየቃችን ተገቢ ነው:- ‘በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ አገልጋዮች እንደ መሆናችን መጠን እየተባረክን ያለነው በምን መንገድ ነው? የሶፎንያስ ትንቢት በፍጥነት እየቀረበ ካለው የይሖዋ የቁጣ ቀን ለሚሰወሩ ሰዎች ወደፊት የሚፈጸሙ ምን በረከቶች ይዞላቸዋል?’

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ሰዎች ‘ይሖዋን መፈለግ’ የሚችሉት እንዴት ነው?

• ‘ጽድቅን መፈለግ’ ምን ነገር ያካትታል?

• ‘ትሕትናን መፈለግ’ የምንችለው እንዴት ነው?

• ይሖዋን፣ ጽድቅንና ትሕትናን መፈለጋችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና ከልብ በመጸለይ ይሖዋን እየፈለግህ ነውን?

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እጅግ ብዙ ሰዎች ይሖዋን መፈለጋቸውን በመቀጠላቸው ከይሖዋ የቁጣ ቀን በሕይወት ይተርፋሉ