በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የይሖዋ የፍርድ ቀን ቀርቧል!

የይሖዋ የፍርድ ቀን ቀርቧል!

የይሖዋ የፍርድ ቀን ቀርቧል!

“ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል፤ የእግዚአብሔር ቀን ድምፅ ቀርቦአል እጅግም ፈጥኖአል።”​ሶፎንያስ 1:​14

1. አምላክ በሶፎንያስ በኩል ያስተላለፈው ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው?

 ሖዋ አምላክ በክፉዎች ላይ እጁን የሚዘረጋበት ጊዜ ቀርቧል። አድምጡ! ማስጠንቀቂያው እንዲህ ይላል:- ‘ሰውን አጠፋለሁ፤ ሰውን ከምድር ፊት እቈርጣለሁ።’ (ሶፎንያስ 1:​3) ልዑል ጌታ የሆነው ይሖዋ እነዚህን ቃላት ያስነገረው የታማኙ ንጉሥ ሕዝቅያስ የልጅ ልጅ፣ ልጅ ሳይሆን በማይቀረው በነቢዩ ሶፎንያስ በኩል ነው። ጥሩ ንጉሥ በነበረው በኢዮስያስ ዘመን የተነገረው ይህ የፍርድ መልእክት በይሁዳ ምድር ለሚኖሩ ኃጢአተኞች በጎ ነገር አልያዘላቸውም።

2. ኢዮስያስ የወሰደው እርምጃ የይሖዋን የፍርድ ቀን ሊያስቀር ያልቻለው ለምንድን ነው?

2 ሶፎንያስ በድፍረት የተናገረው ትንቢት ወጣቱ ኢዮስያስ የይሁዳን ምድር ከርኩስ አምልኮ ማጽዳቱ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ይበልጥ ሳያስገነዝበው አልቀረም። ይሁን እንጂ ንጉሡ ምድሪቱን ከሐሰት ሃይማኖት ለማጥራት የወሰደው እርምጃ ከሕዝቡ መካከል ክፋትን ጨርሶ ለማስወገድም ሆነ ‘ኢየሩሳሌምን በንጹሕ ደም የሞላው’ አያቱ ንጉሥ ምናሴ ለሠራው ኃጢአት ሥርየት ሊያስገኝ አልቻለም። (2 ነገሥት 24:​3, 4፤ 2 ዜና መዋዕል 34:​3) ስለዚህ የይሖዋ የፍርድ ቀን መምጣቱ የማይቀር ነበር።

3. ‘ከይሖዋ የቁጣ ቀን’ በሕይወት መትረፍ እንደምንችል እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

3 ቢሆንም ከዚያ አስፈሪ ቀን በሕይወት የሚተርፉ ይኖራሉ። በመሆኑም የአምላክ ነቢይ የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሰጥቷል:- “ትእዛዝ ሳይወጣ፣ ቀኑም እንደ ገለባ ሳያልፍ፣ የእግዚአብሔርም ቁጣ ትኩሳት ሳይመጣባችሁ፣ የእግዚአብሔርም ቁጣ ቀን ሳይደርስባችሁ ተሰብሰቡ፣ ተከማቹም። እናንተ ፍርዱን የጠበቃችሁ የምድር ትሑታን ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ፈልጉ፤ ጽድቅንም ፈልጉ፣ ትሕትናንም ፈልጉ፤ ምናልባት በእግዚአብሔር ቁጣ ቀን ትሰወሩ ይሆናል።” (ሶፎንያስ 2:​2, 3) ከይሖዋ የፍርድ ቀን በሕይወት የመትረፍ ተስፋ በአእምሯችን ይዘን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነውን የሶፎንያስ መጽሐፍ እንመርምር። የተጻፈው በይሁዳ ምድር በ648 ከዘአበ ሲሆን በትኩረት ልንከታተለው የሚገባ የአምላክ ‘ትንቢታዊ ቃል’ ክፍል ነው።​—⁠2 ጴጥሮስ 1:​19

ይሖዋ እጁን ዘረጋ

4, 5. ሶፎንያስ 1:​1-3 በይሁዳ ይኖሩ በነበሩት ክፉ ሰዎች ላይ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

4 ወደ ሶፎንያስ የመጣው “የእግዚአብሔር ቃል” ቀደም ሲል በተጠቀሱት የማስጠንቀቂያ ቃላት ይጀምራል። አምላክ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ነገርን ሁሉ ከምድር ፊት ፈጽሜ አጠፋለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር። ሰውንና እንስሳን አጠፋለሁ፤ የሰማይን ወፎችና የባሕርን ዓሣዎች ማሰናከያንም ከኃጢአተኞች ጋር አጠፋለሁ፤ ሰውንም ከምድር ፊት እቈርጣለሁ፣ ይላል እግዚአብሔር።”​—⁠ሶፎንያስ 1:​1-3

5 አዎን፣ ይሖዋ በይሁዳ ምድር የተንሰራፋውን ክፋት ወደ ፍጻሜው ያመጣዋል። አምላክ ‘ነገርን ሁሉ ከምድር ፊት ለማጥፋት’ መሣሪያ አድርጎ የሚጠቀመው ማንን ይሆን? ሶፎንያስ ትንቢቱን የተናገረው በ659 ከዘአበ በጀመረው የንጉሥ ኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት መጀመሪያ ላይ ሳይሆን ስለማይቀር ትንቢታዊዎቹ ቃላት በይሁዳ ምድርና በዋና ከተማዋ በኢየሩሳሌም ላይ በ607 ከዘአበ በባቢሎናውያን አማካኝነት ስትጠፋ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። በዚያን ወቅት በይሁዳ ይኖሩ በነበሩት ክፉ ሰዎች ላይ ‘ጥፋት’ ደርሷል።

6-8. ሶፎንያስ 1:​4-6 ላይ በትንቢት የተነገረው ምንድን ነው? ትንቢቱስ በጥንቷ ይሁዳ ላይ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነበር?

6 ሶፎንያስ 1:​4-6 አምላክ በሐሰተኛ አምላኪዎች ላይ የሚወስደውን እርምጃ ሲተነብይ እንዲህ ይላል:- “እጄንም በይሁዳ ላይ በኢየሩሳሌምም በሚኖሩት ሁሉ ላይ እዘረጋለሁ፤ ከዚህም ስፍራ የበኣልን ቅሬታና የጣዖታቱን ካህናት ስም አጠፋለሁ፤ በሰገነትም ላይ ለሰማይ ሠራዊት የሚሰግዱትን፣ በእግዚአብሔርና በንጉሣቸው በሚልኮም ምለው የሚሰግዱትን፣ እግዚአብሔርንም ከመከተል የተመለሱትን፣ እግዚአብሔርንም ያልፈለጉትንና ያልጠየቁትን አጠፋለሁ።”

7 የይሖዋ እጅ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ላይ ተዘርግቷል። የከነዓናውያን የመራባት አምላክ የሆነውን በኣልን የሚያመልኩትን ሁሉ በሞት ለመቁረጥ ወስኗል። የበኣል አምላኪዎች አማልክቶቻቸው በተወሰኑ አካባቢዎች ላይ ሥልጣን ወይም ባለቤትነት እንዳላቸው ስለሚያምኑ በአካባቢው የሚገኙትን የተለያዩ አማልክት ሁሉ በኣል ብለው ይጠሩ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ሞዓባውያንና ምድያማውያን ያመልኩት የነበረ በኣል የተባለ አምላክ በፌጎር ተራራ ይገኝ ነበር። (ዘኁልቁ 25:​1, 3, 6) ይሖዋ የበኣልን ካህናትና ከነዚህ ካህናት ጋር በመተባበር የአምላክን ሕግ የሚጥሱትን ከሃዲ ሌዋውያን ካህናት ከመላው ይሁዳ ያጠፋል።​—⁠ዘጸአት 20:​2, 3

8 በተጨማሪም አምላክ በከዋክብት ቆጠራ ድርጊቶች በመካፈልና ፀሐይን በማምለክ ‘ለሰማይ ሠራዊት የሚሰግዱትን’ ይቆርጣል። (2 ነገሥት 23:​11፤ ኤርምያስ 19:​13፤ 32:​29) ከዚህም በላይ ‘በይሖዋና በሚልኮም እየማሉ’ እውነተኛውን አምልኮ ከሐሰተኛው ጋር ለመቀላቀል የሚሞክሩትን ሁሉ ያጠፋል። ሚልኮም የአሞናውያን ዋነኛ አምላክ የሆነው የሞሎክ ሌላ መጠሪያ ሊሆን ይችላል። የሞሎክ አምልኮ ሕፃናትን መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብን ይጨምር ነበር።​—⁠1 ነገሥት 11:​5፤ ኤርምያስ 32:​35

የሕዝበ ክርስትና ፍጻሜ ቀርቧል!

9. (ሀ) ሕዝበ ክርስትና ጥፋተኛ የሆነችው በምን ረገድ ነው? (ለ) በይሁዳ ከነበሩት እምነት አጉዳዮች በተለየ መልኩ ምን ለማድረግ መወሰን ይኖርብናል?

9 ይህ ሁሉ በሐሰት አምልኮና በኮከብ ቆጠራ የተዘፈቀችውን ሕዝበ ክርስትና ያስታውሰናል። በቀሳውስት ደጋፊነት በተካሄዱ ውጊያዎች መሠውያ ላይ በሚልዮን የሚቆጠር ሕይወት ለመሥዋዕት በማቅረብ ረገድ የተጫወተችው ሚና በእርግጥም የሚዘገንን ነው! ‘ይሖዋን ከመከተል ወደኋላ ተመልሰው’ ግድ የለሾች የሆኑትንና ይሖዋንና መመሪያውን መፈለግ ያቆሙትን የይሁዳን ከዳተኞች ከመምሰል እንራቅ። ከዚህ ይልቅ ለአምላክ ያለንን ፍጹም አቋም እንጠብቅ።

10. ሶፎንያስ 1:​7 የያዘውን ትንቢታዊ ቁም ነገር ምን ብለህ ትገልጸዋለህ?

10 የሚከተሉት የነቢዩ ቃላት በይሁዳ በነበሩትም ክፉዎች ሆነ በዛሬው ጊዜ ባሉት ክፉዎች ሁሉ ላይ ተፈጻሚነት አላቸው። ሶፎንያስ 1:​7 እንዲህ ይላል:- “የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና፣ እግዚአብሔር መሥዋዕትን አዘጋጅቶአልና፣ የጠራቸውንም ቀድሶአልና በጌታ በእግዚአብሔር ፊት ዝም በሉ።” እነዚህ ‘የተጠሩ ሰዎች’ የይሁዳ ጠላቶች የሆኑት ከለዳውያን እንደሆኑ ግልጽ ነው። ‘መሥዋዕቱ’ ዋና ከተማዋን ጨምሮ ይሁዳ ነች። በመሆኑም ሶፎንያስ አምላክ ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት ያለውን ዓላማ አስታውቋል። ከዚህም በላይ ትንቢቱ የሕዝበ ክርስትናን ጥፋት አመልክቷል። እንዲያውም ዛሬ የአምላክ የፍርድ ቀን እጅግ ስለቀረበ ዓለም ባጠቃላይ ‘በይሖዋ ፊት ዝም ማለት’ እና የኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮች በሆኑት ‘ታናሹ መንጋ’ እና በአጋሮቻቸው “ሌሎች በጎች” አማካኝነት የሚናገረውን ማዳመጥ አለበት። (ሉቃስ 12:​32፤ ዮሐንስ 10:​16) ለማዳመጥ ፈቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው የአምላክ መንግሥት ተቀናቃኞች የሆኑ ሰዎች ሁሉ ጥፋት ይጠብቃቸዋል።​—⁠መዝሙር 2:​1, 2

በቅርቡ የልቅሶ ቀን ይሆናል!

11. የሶፎንያስ 1:​8-11 መሠረታዊ ትርጉም ምንድን ነው?

11 የይሖዋን ቀን በማስመልከት ሶፎንያስ 1:​8-11 የሚከተለውን ይጨምራል:- “በእግዚአብሔርም መሥዋዕት ቀን አለቆችንና የንጉሥን ልጆች እንግዳ ልብስ የሚለብሱትንም ሁሉ እቀጣለሁ። በዚያም ቀን በመድረኩ ላይ የሚዘልሉትን፣ የጌታቸውን ቤት ዓመፃንና ሽንገላን የሚሞሉትን እቀጣለሁ። በዚያ ቀን፣ ይላል እግዚአብሔር፣ ከዓሣው በር የጩኸት ድምፅ፣ ከከተማውም በሁለተኛው ክፍል ውካታ፣ ከኮረብቶቹም ታላቅ ሽብር ይሆናል። እናንተ በመክቴሽ የምትኖሩ ሆይ፣ የከነዓን ሕዝብ ሁሉ ጠፍተዋልና፣ ብርም የተሸከሙ ሁሉ ተቈርጠዋልና አልቅሱ።”

12. አንዳንዶች ‘እንግዳ ልብስ ለብሰው’ የታዩት እንዴት ነው?

12 ከንጉሥ ኢዮስያስ በኋላ ኢዮአካዝ፣ ኢዮአቄም እና ዮአኪን በየተራ ይነግሣሉ። ከዚያ በኋላ በሚመጣው በሴዴቅያስ ዘመነ መንግሥት ኢየሩሳሌም ትጠፋለች። ምንም እንኳ እንዲህ ዓይነት ጥፋት ቢደቀንባቸውም አንዳንዶች የአጎራባች ብሔራትን ተቀባይነት ለማግኘት ሲሉ ‘እንግዳ ልብስ’ ለብሰዋል። በተመሳሳይ በዛሬው ጊዜ ብዙዎች የይሖዋ ድርጅት ክፍል አለመሆናቸውን በተለያዩ መንገዶች ግልጽ አድርገዋል። የሰይጣን ድርጅት አባላት መሆናቸውን በግልጽ በማሳየታቸው ቅጣታቸውን ይቀበላሉ።

13. ከሶፎንያስ ትንቢት ጋር በሚስማማ መንገድ ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ሲያጠቁ ምን መፈጸም ነበረበት?

13 ይሁዳ ለፍርድ የምትቀርብበት ‘ያ ቀን’ ይሖዋ ክፋትን ለማስወገድና የበላይነቱን ለማረጋገጥ በጠላቶቹ ላይ የቅጣት እርምጃ ከሚወስድበት የይሖዋ ቀን ጋር ተመሳሳይ ይሆናል። ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን በሚያጠቁበት ጊዜ ከዓሣ በር ጩኸት ይመጣል። ይህ በር እንዲህ ያለ ስያሜ የተሰጠው ዓሣ ከሚሸጥበት ገበያ አጠገብ ይገኝ ስለነበር ሳይሆን አይቀርም። (ነህምያ 13:​16) የባቢሎን ጭፍሮች ሁለተኛው ክፍል ተብሎ ይጠራ ወደነበረው አካባቢ ይገባሉ። “ከኮረብቶችም ታላቅ ሽብር” የተባለውም ባቢሎናውያኑ እየገሰገሱ ሲመጡ የሚሰማውን ድምፅ የሚያመለክት ሊሆን ይችላል። የመክቴሽ ምናልባትም የላይኛው ታይሮፕያን ሸለቆ ነዋሪዎች ‘ያለቅሳሉ።’ የሚያለቅሱት ለምንድን ነው? ‘ብር የሚሸከሙትን’ ጨምሮ ማንኛውም የንግድ እንቅስቃሴ ስለሚቆም ነው።

14. አምላክ አምላኪዎቹ ነን በሚሉ ላይ የሚያደርገው ምርመራ ምን ያህል ስፋት ይኖረዋል?

14 ይሖዋ አምላኪዎቹ ነን በሚሉ ላይ የሚያደርገው ምርመራ ምን ያህል ስፋት ይኖረዋል? ትንቢቱ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “በዚያም ዘመን ኢየሩሳሌምን በመብራት እመረምራለሁ፤ በአተላቸውም ላይ የሚቀመጡትን፣ በልባቸውም:- እግዚአብሔር መልካምን አያደርግም፣ ክፉም አያደርግም የሚሉትን ሰዎች እቀጣለሁ። ብልጥግናቸውም ለምርኮ ይሆናል፣ ቤቶቻቸውም ይፈርሳሉ፤ ቤቶችንም ይሠራሉ፣ ነገር ግን አይቀመጡባቸውም፤ ወይንንም ይተክላሉ፣ የወይን ጠጁን ግን አይጠጡም።”​—⁠ሶፎንያስ 1:​12, 13

15. (ሀ) የኢየሩሳሌም ከሃዲ ካህናት ምን ይጠብቃቸው ነበር? (ለ) በዛሬው ጊዜ ያሉ የሐሰት ሃይማኖት ተከታዮች ምን ይጠብቃቸዋል?

15 ከሃዲዎቹ የኢየሩሳሌም ካህናት የይሖዋን አምልኮ ከሐሰት ሃይማኖት ጋር እየቀላቀሉ ነበር። ምንም አይደርስብንም ብለው ቢያስቡም እንኳ አምላክ መሸሸጊያቸው ካደረጉት መንፈሳዊ ጨለማ መሃል ደማቅ ብርሃን ባለው መብራት ፈልጎ ያመጣቸዋል። ከሚታወጀውና ከሚወርደው መለኮታዊ ቅጣት አንዳቸውም ሊያመልጡ አይችሉም። ቸልተኞቹ ከሃዲዎች በወይን ጠጅ ጋን ግርጌ እንደሚገኝ አተላ ተደላድለው ተቀምጠዋል። በሰዎች ጉዳይ ላይ መለኮታዊ ጣልቃገብነት ይኖራል በሚል መግለጫ መረበሽ አልፈለጉም። ሆኖም በእነሱ ላይ ከሚፈጸመው የአምላክ ፍርድ ማምለጥ አይችሉም። በተጨማሪም የሕዝበ ክርስትና አባላትንና ከይሖዋ አምልኮ ክደው የወጡ አንዳንድ ሰዎችን ጨምሮ በዛሬው ጊዜ ያሉ የሐሰት ሃይማኖት ተከታዮች ማምለጫ አይኖራቸውም። ጊዜያችን ‘የመጨረሻው ቀን’ መሆኑን በመካድ በልባቸው “እግዚአብሔር መልካምን አያደርግም ክፉም አያደርግም” ይላሉ። ምንኛ ተሳስተዋል!​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5፤ 2 ጴ⁠ጥ​ሮስ 3:​3, 4, 10

16. በይሁዳ ላይ መለኮታዊ ፍርድ ሲወርድ ምን መፈጸም ነበረበት? ይህን ማወቃችንስ እንዴት ሊነካን ይገባል?

16 ባቢሎናውያን ሃብታቸውን እንደሚዘርፉ፣ ቤቶቻቸውን እንደሚያፈርሱና የወይን ምርታቸውን እንደሚወስዱባቸው ከሃዲ ለሆኑት አይሁዳውያን ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። መለኮታዊው ፍርድ በይሁዳ ላይ በወረደበት ጊዜ ቁሳዊ ነገሮች ምንም ዋጋ አልነበራቸውም። የይሖዋ የቅጣት ፍርድ በአሁኑ የነገሮች ሥርዓት ላይ በሚወርድበት ጊዜ ተመሳሳይ ሁኔታ ይኖራል። ስለዚህ መንፈሳዊ አመለካከት በመያዝና በሕይወታችን ውስጥ የይሖዋን አገልግሎት በማስቀደም ‘በሰማይ ሃብት እናከማች።’​—⁠ማቴዎስ 6:​19-21, 33

“ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል”

17. በሶፎንያስ 1:​14-16 መሠረት የይሖዋ የፍርድ ቀን ምን ያህል ቅርብ ነው?

17 የይሖዋ የፍርድ ቀን ምን ያህል ቀርቧል? በሶፎንያስ 1:​14-16 መሠረት አምላክ የሚከተለውን ዋስትና ይሰጣል:- “ታላቁ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአል፤ የእግዚአብሔር ቀን ድምፅ ቀርቦአል እጅግም ፈጥኖአል፤ ኃያሉም በዚያ በመራራ ልቅሶ ይጮኻል። ያ ቀን የመዓት ቀን፣ የመከራና የጭንቀት ቀን፣ የመፍረስና የመጥፋት ቀን፣ የጨለማና የጭጋግ ቀን፣ የደመናና የድቅድቅ ጨለማ ቀን፣ በተመሸጉ ከተሞችና በረዘሙ ግንቦች ላይ የመለከትና የሰልፍ ጩኸት ቀን ነው።”

18. የይሖዋ የፍርድ ቀን ገና ብዙ ይቀረዋል ብለን መደምደም የሌለብን ለምንድን ነው?

18 ኃጢአተኛ የሆኑ የይሁዳ ካህናት፣ መሳፍንትና ሕዝብ ‘ታላቁ የይሖዋ ቀን ቅርብ’ እንደሆነ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። ለይሁዳ ‘የይሖዋ ቀን እጅግ ፈጣን’ ይሆንባታል። በተመሳሳይ በጊዜያችን ማንም ሰው ይሖዋ በክፉዎች ላይ የሚያመጣው የቅጣት ፍርድ ገና ሩቅ ነው ብሎ አያስብ። ከዚህ ይልቅ አምላክ በይሁዳ ላይ ፈጥኖ እርምጃ እንደወሰደ ሁሉ ጥፋት የሚያመጣበትንም ቀን ‘ያፋጥነዋል።’ (ራእይ 16:​14, 16) ይህ ቀን ምሥክሮቹ የሚያሰሙትን የይሖዋን ማስጠንቀቂያ ችላ ለሚሉና እውነተኛውን አምልኮ ለመቀበል እምቢተኛ ለሆኑ ሁሉ በጣም መራራ ጊዜ ይሆንባቸዋል!

19, 20. (ሀ) የአምላክ ቁጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ የተፈጸመባቸው አንዳንድ ገጽታዎች ምንድን ነበሩ? (ለ) ይህ የነገሮች ሥርዓት ከሚጠብቀው ጥፋት አንጻር ሲታይ ምን ጥያቄዎች ይነሳሉ?

19 የአምላክ ቁጣ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ በተገለጠበት ጊዜ “የመከራና የጭንቀት ቀን” ሆኖባቸው ነበር። የይሁዳ ነዋሪዎች ከፊታቸው የተደቀነው ሞትና ጥፋት ከሚያስከትልባቸው የአእምሮ ጭንቀት በተጨማሪ ባቢሎናውያኑ ወራሪዎች ብዙ መከራ አድርሰውባቸዋል። ያ ወቅት በጭስና በእልቂት የተሞላ ስለሆነ በምሳሌያዊ አነጋገር ብቻ ሳይሆን ምናልባትም ቃል በቃል “የጨለማና የጭጋግ ቀን” ሆኗል። “የመለከትና የሰልፍ ጩኸት ቀን” ቢሆንም ማስጠንቀቂያ መሰጠቱ ምንም ፋይዳ አልነበረውም።

20 ባቢሎናውያን ‘ረዥም ግንቦችን’ ሲደረማምሱ በጥበቃ ላይ የነበሩ የኢየሩሳሌም ጉበኞች የሚደርስላቸው አጥተዋል። በዘመናችንም የዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ምሽጎች ዒላማቸውን ብቻ መርጠው የሚያወድሙትን የአምላክ ሰማያዊ ጦር መሣሪያዎች መመከት የማይችሉ ይሆናሉ። ከጥፋቱ ለመትረፍ ተስፋ ታደርጋለህን? ‘የሚወድዱትን ሁሉ ከሚጠብቀው፣ ኃጢአተኞችንም ሁሉ ከሚያጠፋው’ ከይሖዋ ጎን በመሆን ጽኑ አቋም ይዘሃልን?​—⁠መዝሙር 145:​20

21, 22. ሶፎንያስ 1:​17, 18 በጊዜያችን ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት ይሆናል?

21 በሶፎንያስ 1:​17, 18 ላይ የተተነበየው የፍርድ ቀን እንዴት አስፈሪ ነው! ይሖዋ አምላክ እንዲህ ይላል:- “በእግዚአብሔርም ላይ ኃጢአት ሠርተዋልና እንደ ዕውር እስኪሄዱ ድረስ ሰዎችን አስጨንቃለሁ፤ ደማቸውም እንደ ትቢያ፣ ሥጋቸውም እንደ ጉድፍ ይፈስሳል። በእግዚአብሔርም ቁጣ ቀን ብራቸውና ወርቃቸው ሊያድናቸው አይችልም፤ እርሱም በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ፈጥኖ ይጨርሳቸዋልና ምድር ሁሉ በቅንዓቱ እሳት ትበላለች።”

22 ይሖዋ በሶፎንያስ ዘመን እንዳደረገው ሁሉ በቅርቡ ማስጠንቀቂያውን ለመስማት እምቢተኛ በሆኑ ‘በምድር ነዋሪዎች ሁሉ ላይ’ ታላቅ ጭንቀት ያመጣል። በአምላክ ላይ ኃጢአት ስለሠሩ የመዳኛው መንገድ ጠፍቷቸው እንደ እውር ይደነባበራሉ። በይሖዋ ፍርድ ቀን ደማቸው ምንም ዋጋ እንደሌለው “ትቢያ” ይፈስሳል። አምላክ የእነዚህን ክፉዎች አስከሬን በምድር ሁሉ ላይ “እንደ ጉድፍ” እንዲወድቅ ስለሚያደርግ በእርግጥም ፍጻሜያቸው አሳፋሪ ይሆናል።

23. ክፉ አድራጊዎች ‘ከይሖዋ የቁጣ ቀን’ ማምለጥ ባይችሉም እንኳ የሶፎንያስ ትንቢት ምን ተስፋ ይዟል?

23 ከአምላክና ከሕዝቦቹ ጋር የሚዋጉትን ሊያድን የሚችል አንዳች ኃይል አይኖርም። ወርቅም ሆነ ብር በይሁዳ የነበሩትን ክፉዎች ሊያድን እንዳልቻለ ሁሉ ሕዝበ ክርስትናንና የቀረውን የነገሮች ሥርዓትም የደለበ ሃብትና ጉቦ ‘ከይሖዋ ቁጣ ቀን’ ሊያድናቸው አይችልም። በዚያ የፍርድ ቀን አምላክ ክፉዎችን ፈጽሞ ሲያጠፋ “ምድር ሁሉ” በቅንዓቱ እሳት ትበላለች። በአምላክ ትንቢታዊ ቃል ላይ እምነት ስላለን ‘የፍጻሜው ዘመን’ ውስጥ ጠልቀን እንደገባን እርግጠኞች ነን። (ዳንኤል 12:​4) የይሖዋ የፍርድ ቀን ቀርቧል፤ ደግሞም በቅርቡ በጠላቶቹ ላይ በቀሉን ያወርዳል። ሆኖም የሶፎንያስ ትንቢት የሚዘረጋው የመዳን ተስፋ አለ። ስለዚህ ከይሖዋ የቁጣ ቀን ለመሰወር ምን ማድረግ ይፈለግብናል?

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• የሶፎንያስ ትንቢት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

• ሕዝበ ክርስትና እና በጊዜያችን ያሉ ክፉዎች ሁሉ ምን ይጠብቃቸዋል?

• የይሖዋ የፍርድ ቀን ገና ሩቅ ነው ብለን ማሰብ የሌለብን ለምንድን ነው?

[የጥናት እትም]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሶፎንያስ የይሖዋ የፍርድ ቀን ቅርብ መሆኑን በድፍረት አውጆአል

[ምንጭ]

From the Self-Pronouncing Edition of the Holy Bible, containing the King James and the Revised versions

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ቀን በይሁዳና በኢየሩሳሌም ላይ በባቢሎናውያን እጅ በ607 ከዘአበ መጥቷል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይሖዋ ክፉዎችን ሲያጠፋ በሕይወት ለመትረፍ ተስፋ ታደርጋለህን?