ሲረል እና መቶድየስ—ፊደል የቀረጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች
ሲረል እና መቶድየስ—ፊደል የቀረጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች
“ሕዝባችን ተጠምቋል፤ ግን አስተማሪ የለንም። ግሪክኛም ሆነ ላቲን አንችልም። . . . ፊደሎችንም ሆነ ትርጉማቸውን አናውቅም፤ ስለዚህ የቅዱሳን ጽሑፎችን ቃላትና ትርጉም የሚያስተምሩ አስተማሪዎችን ላክልን።” —የሞራቪያ ልዑል ራስቴስላፍ 862 እዘአ
ዛሬ ከ435 ሚልዮን በላይ የሚሆኑት የስላቭ ቋንቋ ቤተሰብ ተናጋሪዎች በቋንቋቸው የተተረጎመውን መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ይችላሉ። a ከእነዚህ መካከል 360 ሚልዮን የሚሆኑት የሚጠቀሙት በሲሪሊክ ፊደላት ነው። ሆኖም ከ1, 200 ዓመታት በፊት ቅድመ አያቶቻቸው ይናገሯቸው ከነበሩት የቋንቋ ቤተሰቦች መካከል ፊደል ያለው ወይም በጽሑፍ የሰፈረ አንድም ቋንቋ አልነበረም። ሲረል እና መቶድየስ የተባሉ ሁለት ወንድማማቾች ይህ ሁኔታ እንዲስተካከል እርዳታ አበርክተዋል። ለአምላክ ቃል ፍቅር ያላቸው ሰዎች እነዚህ ሁለት ወንድማማቾች የወሰዱት ድፍረት የሚጠይቅ እርምጃም ሆነ የፈጠራ ጥረታቸው መጽሐፍ ቅዱስን ጠብቆ ለማቆየትና በስፋት ለማዳረስ በሚደረገው ጥረት ረገድ አዲስ ምዕራፍ እንደከፈተ ይገነዘባሉ። ለመሆኑ እነዚህ ወንድማማቾች እነማን ናቸው? ምንስ እንቅፋቶች ገጥመዋቸው ነበር?
“ፈላስፋው” እና አገረ ገዢው
ሲረል (ከ827-869 እዘአ፣ የመጀመሪያ ስሙ ቆስጠንጢኖስ ነበር) እና መቶድየስ (ከ825-885 እዘአ) የተወለዱት በግሪክ ተሰሎንቄ በንጉሣን ቤተሰብ ውስጥ ነው። በዚያን ዘመን ተሰሎንቄ ሁለት ቋንቋ የሚነገርባት ከተማ ነበረች። ነዋሪዎቿ ግሪክኛና የስላቭ ቋንቋ ይናገሩ ነበር። ሲረል እና መቶድየስ የደቡባዊ ስላቮችን ቋንቋ ጠንቅቀው እንዲያውቁ የረዳቸው በሚኖሩበት አካባቢ በርካታ ስላቮች መኖራቸውና በግሪክና በስላቭ ማኅበረሰብ መካከል የጠበቀ መቀራረብ መኖሩ ሳይሆን አይቀርም። እንዲያውም አንድ የመቶድየስ የሕይወት ታሪክ ጸሐፊ እናታቸው የስላቭ ዝርያ እንዳላት ገልጿል።
ሲረል አባቱ ከሞተ በኋላ የባይዛንታይን ግዛት ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ቁስጥንጥንያ ሄደ። እዚያም በንጉሠ ነገሥቱ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተማረ ሲሆን እውቅ ከሆኑ ምሁራን ጋር የመተዋወቅ አጋጣሚ አግኝቷል። ከዚያም በምሥራቅ አካባቢ ከታነጹት የቤተ ክርስቲያን ሕንፃዎች ሁሉ በጣም በታወቀው በአይያ ሶፊያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ዐቃቤ መጻሕፍት ከመሆኑም በላይ ከጊዜ በኋላ የፍልስፍና ፕሮፌሰር ለመሆን በቅቷል። እንዲያውም ሲረል በትምህርት ባገኘው የላቀ ውጤት የተነሳ ፈላስፋው የሚል ቅጽል ስም አትርፏል።
በዚህ ጊዜ መቶድየስ ደግሞ የአባቱን ፈለግ በመከተል የፖለቲካ አስተዳደርን ሞያ ተከታተለ። ብዙ ስላቮች በሚኖሩበት በአንድ የባይዛንታይን የጠረፍ አውራጃ አስተዳዳሪ
(አገረ ገዢ) እስከመሆን ደርሶ ነበር። ይሁን እንጂ አገረ ገዢነቱን ለቅቆ በትንሿ እስያ ባለችው በቢታንያ ወደሚገኝ አንድ ገዳም ገባ። በ855 እዘአ ሲረልም እዚያው ገዳም ገብቶ ከእርሱ ጋር መኖር ጀመረ።በ860 እዘአ የቁስጥንጥንያው ፓትሪያርክ እነዚህን ሁለት ወንድማማቾች ሚስዮናውያን አድርጎ ወደ ሌላ አገር ላካቸው። ከእስልምና፣ ከአይሁድና ከክርስትና እምነት የቱን እንደሚይዙ ግራ ተጋብተው ወደ ነበሩ ከጥቁር ባሕር በስተ ሰሜን ወደሚኖሩት ከዛር ወደተባሉት ሕዝቦች ላካቸው። ሲረል እግረ መንገዱን በክራይሚያ በምትገኘው በከርሰኔዝ ለተወሰነ ጊዜ ቆይታ አድርጎ ነበር። አንዳንድ ምሁራን ሲረል እዚያ በቆየበት ጊዜ የዕብራይስጥና የሳምራውያንን ቋንቋ ከመማሩም በላይ የዕብራይስጥን ቋንቋ ሰዋሰው ወደ ከዛር ሕዝብ ቋንቋ ተርጉሟል የሚል እምነት አላቸው።
ከሞራቪያ የቀረበ ጥሪ
በ862 እዘአ የሞራቪያ (ከዛሬዋ ቼክ በስተ ምሥራቅ፣ ከስሎቫኪያና ከሃንጋሪ ደግሞ በስተ ምዕራብ ትገኛለች) ልዑል በመግቢያው አንቀጽ ላይ እንደሰፈረው ቅዱሳን ጽሑፎችን የሚያስተምሩ አስተማሪዎች እንዲልክለት ለባይዛንታይን ንጉሠ ነገሥት ለማይክል ሳልሳዊ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። የስላቭ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑት የሞራቪያ ሰዎች ቀደም ሲል ከምሥራቅ የፍራንካውያን መንግሥት (የአሁኖቹ ጀርመንና ኦስትሪያ) በመጡ ሚስዮናውያን አማካኝነት ከቤተ ክርስቲያን ትምህርቶች ጋር ተዋውቀው ነበር። ሆኖም የጀርመን ጎሣዎች እያሳደሩ ያሉት ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ተጽእኖ ራስቴስላፍን በእጅጉ አሳስቦት ነበር። ከቁስጥንጥንያ ጋር ሃይማኖታዊ ትስስር መፍጠር የሕዝቦቹን ፖለቲካዊም ሆነ ሃይማኖታዊ ራስ ገዝ አስተዳደር ጠብቆ ለማቆየት ይበጃል ብሎ አስቧል።
ንጉሠ ነገሥቱ፣ መቶድየስንና ሲረልን ወደ ሞራቪያ ለመላክ ወሰነ። እነዚህ ሁለት ወንድማማቾች በትምህርትም ሆነ በቋንቋ ለዚህ ተልእኮ ብቁ ነበሩ። ንጉሠ ነገሥቱ ሁለቱ ወንድማማቾች ወደ ሞራቪያ እንዲሄዱ ለማሳመን “እናንተ ሁለታችሁም የተሰሎንቄ ተወላጆች ናችሁ፤ የተሰሎንቄ ሰዎች በጠቅላላ ደግሞ ጥርት ያለ የስላቭ ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው” እንዳላቸው አንድ የዘጠንኛው መቶ ዘመን የሕይወት ታሪክ ጸሐፊ ገልጸዋል።
ፊደልና የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም
ሲረል እሱና ወንድሙ ወደዚያ ከመሄዳቸው በፊት በነበሩት ወራት ለስላቮች ፊደል በመቅረፅ ለተልእኮው ዝግጅት አደረገ። ሲረል ለንግግር ድምፀት ልዩ ትኩረት ይሰጥ እንደነበር ይነገርለታል። ስለሆነም የግሪክና የዕብራይስጥ ፊደላትን በመጠቀም በስላቮን ቋንቋ ለእያንዳንዱ የንግግር ድምፅ ፊደል ለመቅረፅ ጥረት አድርጓል። b ሲረል ለዚህ የፊደል ቀረፃ መሠረት ለመጣል መንቀሳቀስ የጀመረው ቀደም ባሉት በርካታ ዓመታት እንደሆነ አንዳንድ ተመራማሪዎች ይገምታሉ። አሁንም ቢሆን ሲረል የቀረፀው ፊደል ይህ ነበር ብሎ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም።—“ሲሪሊክ ወይስ ግላገለቲክ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
በዚሁ ጊዜ ሲረል መጽሐፍ ቅዱስ የመተርጎም ሥራውን ወዲያው ጀመረ። ሲረል አዲስ በቀረፀው ፊደል በመጠቀም “በመጀመሪያ ቃል ነበረ . . .” የሚለውን የዮሐንስ ወንጌል የመጀመሪያ ሐረግ ከግሪክ ወደ ስላቮን በመተርጎም ሥራውን እንደጀመረና ከዚያም አራቱን ወንጌሎች፣ የጳውሎስን ደብዳቤዎችና የመዝሙር መጽሐፍን እንደተረጎመ ይነገራል።
ይሠራ የነበረው ብቻውን ነበር? መቶድየስ ሳያግዘው አይቀርም። ከዚህም በላይ ዘ ካምብሪጅ ሜዲቫል ሂስትሪ የተባለው መጽሐፍ እንደሚከተለው ይላል:- “በተለይ የግሪክ ትምህርት ያላቸው የስላቭ ተወላጅ የሆኑ ሌሎች ሰዎች ሳያግዙት እንዳልቀሩ መገመት ይቻላል። በጣም ጥንታዊ የሆኑትን ትርጉሞች ብንመረምር . . . በከፍተኛ ደረጃ የጎለበተ የስላቮን ቋንቋ መጠቀሙን ስናይ የስላቭ ተወላጅ የሆኑ ሌሎች ሰዎች አግዘውታል የሚለውን ግምት ይበልጥ ያጠናክርልናል።” ቀጥሎ እንደምንመለከተው ቀሪውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ያጠናቀቀው መቶድየስ ነው።
“የጭቃ ጅራፍ”
ሲረልና መቶድየስ ተልእኳቸውን ለመጀመር በ863 እዘአ ሞራቪያ ሲደርሱ ሞቅ ያለ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። ሥራቸው መጽሐፍ ቅዱስን እንዲሁም ሃይማኖታዊ ደንቦች የሚገኙባቸው መጻሕፍትን ከመተርጎም ባሻገር ለተወሰኑ የአካባቢው ነዋሪዎች አዲስ የተቀረጸውን የስላቮን ፊደል ማስተማርን ይጨምር ነበር።
ሆኖም ሁሉም ነገር ቀላል ነበር ማለት አይደለም። በሞራቪያ የነበሩ ፍራንካውያን ቀሳውስት በስላቮን ቋንቋ መጠቀምን አጥብቀው ተቃወሙ። ለአምልኮ ተቀባይነት ያላቸው ቋንቋዎች ሦስት ሲሆኑ እነሱም ላቲን፣ ግሪክና ዕብራይስጥ ብቻ ናቸው የሚል አቋም ነበራቸው። ሁለቱ ወንድማማቾች አዲስ ፊደል የቀረፁለትን ቋንቋ በተመለከተ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን ድጋፍ ለማግኘት በ867 እዘአ ወደ ሮም ተጓዙ።
ሲረልና መቶድየስ በጉዟቸው ላይ፣ ቬኒስ ሲደርሱ ከሦስቱ ቋንቋዎች ውጭ መጠቀም የለብንም የሚል እምነት ያላቸው አንድ የላቲን ቀሳውስት ቡድን አጋጠማቸው። በመካከለኛው መቶ ዘመን የነበረ አንድ የሲረል የሕይወት ታሪክ ጸሐፊ ጳጳሳቱ፣ ቀሳውስቱና መነኩሳቱ በሲረል ላይ “የጭቃ ጅራፋቸውን እንዳወረዱበት” ተናግሯል። ይህ ዘገባ ሲረል “ደግሞም መለከት የማይገለጥን ድምፅ ቢሰጥ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል? እንዲሁ እናንተ ደግሞ የተገለጠውን ቃል በአንደበት ባትናገሩ ሰዎች የምትናገሩትን እንዴት አድርገው ያስተውሉታል? ለነፋስ የምትናገሩ ትሆናላችሁና” የሚለውን 1 ቆሮንቶስ 14:8, 9ን በመጥቀስ እንደመለሰላቸው ይገልጻል።
በመጨረሻም ሁለቱ ወንድማማቾች ሮም ሲደርሱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ዳግማዊ አንድሪያን በስላቮን ቋንቋ እንዲጠቀሙ ሙሉ ፈቃድ ሰጡአቸው። ከተወሰኑ ወራት በኋላ ሲረል እዚያው ሮም እያለ በጠና ታመመና ሁለት ወር እንኳ ሳይሞላው በ42 ዓመቱ ሞተ።
መቶድየስ ወደ ሞራቪያ ተመልሶ በኔትራ ከተማ (በአሁኗ ስሎቫኪያ) አካባቢ ሥራውን እንዲቀጥል ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ዳግማዊ አንድሪያን አበረታቱት። ሊቀ ጳጳሱ በአካባቢው ያላቸውን ተደማጭነት ለማጠናከር በማሰብ ለመቶድየስ በስላቮን ቋንቋ እንዲጠቀም የሚፈቅድ ደብዳቤና የጳጳስነት ሹመት ሰጥተው ላኩት። ሆኖም በ870 እዘአ የፍራንካውያን ጳጳስ ሄርማንሪክ በኔትራ ልዑል በመታገዝ መቶድየስ እንዲያዝና እንዲታሰር አደረገ። መቶድየስ በደቡብ ምሥራቅ ጀርመን በሚገኝ አንድ ገዳም ለሁለት ዓመት ተኩል ታሰረ። በመጨረሻም የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዳግማዊ አንድሪያን ተተኪ የሆኑት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጆን ስምንተኛ መቶድየስ ከእስር እንዲለቀቅና ወደ ሃገረ ስብከቱ እንዲመለስ ትእዛዝ ከማስተላለፋቸውም በላይ የስላቮንን ቋንቋ ለአምልኮ በመጠቀም ረገድ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ድጋፍ እንዳለው በድጋሚ አረጋገጡ።
ይሁን እንጂ የፍራንካውያን ቀሳውስት ተቃውሞ አላቆመም። መቶድየስ አጥጋቢ የመከራከሪያ ነጥብ በማቅረብ መናፍቅ ነው በሚል የቀረበበትን ክስ ውድቅ ያደረገ ሲሆን ከርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጆን ስምንተኛ የስላቭ ቋንቋ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲሠራበት ግልጽ ፈቃድ የሚሰጥ ማረጋገጫ ለማግኘት በቅቷል። የመቶድየስ ሕይወት “ብዙ መንከራተት፣ ረሀብና እርዛት፣ ስቃይ፣ ጥላቻና ስደት . . . አልፎ ተርፎ በእስር መንገላታት የሞላበት ነበር” ሲሉ አሁን ያሉት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዳግማዊ ጆን ፖል ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። የሚገርመው ደግሞ ስደቱ የደረሰበት የራሷ የሮም ቤተ ክርስቲያን ደጋፊዎች በሆኑ ጳጳሳትና መሳፍንት መሆኑ ነው።
ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ተተረጎመ
መቶድየስ ምንም እንኳ የከረረ ተቃውሞ ቢገጥመውም አጭር የእጅ ጽሕፈት በሚጽፉ በርካታ ሰዎች በመታገዝ ቀሪውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ወደ ስላቮን ቋንቋ ተርጉሞ ጨረሰ። ይህን ከባድ ሥራ በስምንት ወር ጊዜ ውስጥ እንዳጠናቀቀ ይነገራል። ሆኖም የመቃብያንን አዋልድ መጻሕፍት አልተረጎመም።
ዛሬ፣ የሲረልንና የመቶድየስን የትርጉም ሥራ ጥራት
በትክክል መገምገም አስቸጋሪ ነው። የመጀመሪያው የትርጉም ሥራ ወደተሠራበት ዘመን የሚጠጋ ዕድሜ ያላቸው እስከ አሁን ያሉ ጥንታዊ ቅጂዎች በጣም ጥቂት ናቸው። የቋንቋ ምሁራን እነዚህን እንደናሙና የሚያገለግሉ ብርቅዬ ጥንታዊ ቅጂዎች በመመርመር የትርጉም ሥራው ትክክለኛና ለዛ ያለው እንደነበር መገንዘብ ችለዋል። አወር ስላቪክ ባይብል የተባለው የሥነ ጽሑፍ ሥራ ሁለቱ ወንድማማቾች “ብዙ አዳዲስ ቃላትንና አገላለጾችን መፍጠር ነበረባቸው . . . ይህንንም በፍጹም ትክክለኝነት ከማከናወናቸውም በላይ የስላቭ ቋንቋ ገላጭ በሆኑ በርካታ ቃላት እንዲዳብር አድርገዋል” ሲል ገልጿል።ዘላለማዊ ቅርስ
መቶድየስ በ885 እዘአ ከሞተ በኋላ የእሱ ተከታዮች በተቃዋሚዎቻቸው በፍራንካውያን አማካኝነት ከሞራቪያ ተባረሩ። ከዚያም በቦሔሚያ፣ በደቡባዊ ፖላንድና በቡልጋሪያ በስደተኝነት መኖር ጀመሩ። የሲረልና የመቶድየስ የትርጉም ሥራ በዚህ መንገድ ቀጥሎ የነበረ ከመሆኑም በላይ ይበልጥ እየተስፋፋ ሊሄድ ችሏል። በሁለቱ ወንድማማቾች አማካኝነት በጽሑፍ መስፈር የጀመረውና ይበልጥ ዘላቂ የመሆን ባሕርይ የተላበሰው የስላቮን ቋንቋ ይበልጥ እየዳበረና እየጎለበተ ሄዶ የኋላ ኋላ የተለያዩ ቋንቋዎች መገኛ ሆኗል። ዛሬ የስላቭ ቋንቋ ቤተሰብ 13 የተለያዩ ቋንቋዎችንና በጣም ብዙ ቀበሌኛዎችን ያቀፈ ነው።
ከዚህም በላይ ሲረልና መቶድየስ መጽሐፍ ቅዱስን ለመተርጎም ሲሉ የወሰዱት ቆራጥነት የሚጠይቅ እርምጃ ዛሬ የተለያዩ የቅዱሳን ጽሑፎች የስላቭ ቋንቋ ትርጉሞችን በማስገኘት ፍሬ ሊያፈራ ችሏል። እነዚህን ቋንቋዎች የሚናገሩ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የአምላክን ቃል በራሳቸው ቋንቋ ማንበብ በመቻላቸው ተጠቅመዋል። የከረረ ተቃውሞ ቢኖርም እንኳ ‘የአምላካችን ቃል ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል’ የሚሉት ቃላት ምንኛ እውነተኛ ናቸው!—ኢሳይያስ 40:8
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የስላቭ ቋንቋዎች የሚባሉት በምሥራቅና በመካከለኛው አውሮፓ የሚነገሩ ቋንቋዎች ሲሆኑ የሩሲያ፣ የዩክሬይን፣ የሰርብ፣ የፖላንድ፣ የቼክ፣ የቡልጋሪያና የመሳሰሉትን ቋንቋዎች ይጨምራሉ።
b በዚህ ርእስ ውስጥ የተሠራበት “ስላቮን” የሚለው ቃል ሲረል እና መቶድየስ ለተልእኳቸውና ለሥነ ጽሑፍ ሥራቸው የተጠቀሙበትን የስላቭ ቋንቋ ያመለክታል። ዛሬ አንዳንዶች “የጥንቱ ስላቮን” ወይም “ጥንታዊ የቤተ ክርስቲያን ስላቮን” የሚሉትን አገላለጾች ይጠቀማሉ። በዘጠንኛው መቶ ዘመን እዘአ ስላቮች አንድ የጋራ ቋንቋ እንዳልነበራቸው የቋንቋ ምሁራን ይስማማሉ።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ሲሪሊክ ወይስ ግላገለቲክ?
የቋንቋ ምሁራን ሲረል የቀረፀው ፊደል የትኛው እንደነበር እርግጠኛ ስላልሆኑ የቀረፀው ፊደል ምን ዓይነት ነው የሚለው ጉዳይ ከፍተኛ ውዝግብ አስነስቷል። በግሪክ ቋንቋ የማይገኙ የስላቮን ቋንቋ ድምፆችን የሚወክሉ አሥራ ሁለት ተጨማሪ ፊደላት ቢቀረፁም ሲሪሊክ እየተባለ የሚጠራው ፊደል በአብዛኛው ከግሪክኛው ፊደል ጋር ይመሳሰላል። ሆኖም አንዳንዶቹ ጥንታዊ የስላቮን ጽሑፎች ግላገለቲክ እየተባለ የሚጠራ በጣም ለየት ያለ ፊደል የሚጠቀሙ ሲሆን ብዙ ምሁራን ሲረል የቀረፀው ይህን ፊደል ነው ብለው ያምናሉ። ከግላገለቲክ ፊደላት መካከል ጥቂቶቹ ከግሪክኛ ወይም ከዕብራይስጥ ቅጥልጥል ፊደላት የመጡ ይመስላሉ። አንዳንዶቹ ፊደላት ደግሞ በመካከለኛው ዘመን ይሠራባቸው ከነበሩ የማናበቢያ ምልክቶች የመጡ ሊሆኑ ይችላሉ። ሆኖም አብዛኞቹ ፍጹም አዲስ የተቀረፁና ረቀቅ ያሉ ፊደላት ናቸው። ግላገለቲክ ፊደላት ፈጽሞ የተለዩና አዲስ የተቀረጹ ይመስላሉ። የሆነ ሆኖ አንዳንዶቹ ከስሎቫኒክ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ከሌላቸው 22 ከሚያክሉት ሌሎች ቋንቋዎች በስተቀር አሁን ያሉት የሩሲያ፣ የዩክሬይን፣ የሰርቢያ፣ የቡልጋሪያና የመቄዶንያ ፊደላት ከሲሪሊክ ፊደላት የመጡ ናቸው።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የባልቲክ ባሕር
(ፖላንድ)
ቦሄሚያ (ቼኪያ)
ሞራቪያ (ምሥራቅ ቼኪያ፣ ምዕራብ ስሎቫኪያ፣ ምዕራብ ሃንጋሪ)
ኔትራ
ምሥራቃዊ የፍራንካውያን መንግሥት (ጀርመንና ኦስትሪያ)
ኢጣሊያ
ቬኒስ
ሮም
የሜድትራንያን ባሕር
ቡልጋሪያ
ግሪክ
ተሰሎንቄ
(ክሪሚያ)
ጥቁር ባሕር
ቢታንያ
ቁስጥንጥንያ (ኢስታንቡል)
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1581 የስላቮን መጽሐፍ ቅዱስ በሲሪሊክ ፊደላት
[ምንጭ]
መጽሐፍ ቅዱስ:- Narodna in univerzitetna knjiz̆nica-Slovenija-Ljubljana