በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በብርሃኑ የሚጓዙ የሚያገኙት ደስታ

በብርሃኑ የሚጓዙ የሚያገኙት ደስታ

በብርሃኑ የሚጓዙ የሚያገኙት ደስታ

“ኑ፣ በእግዚአብሔር ብርሃን እንሂድ።”​—⁠ኢሳይያስ 2:​5

1, 2. (ሀ) ብርሃን ምን ያህል አስፈላጊ ነው? (ለ) ጨለማ ምድርን እንደሚሸፍን የተነገረው ማስጠንቀቂያ ያን ያህል አሳሳቢ የሆነው ለምንድን ነው?

 ይሖዋ የብርሃን ምንጭ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “ፀሐይን በቀን የጨረቃንና የከዋክብትን ሥርዓት በሌሊት ብርሃን አድርጎ የሚሰጥ” በማለት ይጠራዋል። (ኤርምያስ 31:​35፤ መዝሙር 8:​3) ከፍተኛ መጠን ያለው ኃይል በማመንጨት የተወሰነውን በብርሃንና በሙቀት መልክ ወደ ሕዋ የምትልከውን ግዙፍ የኑክሌር እቶን ማለትም ፀሐይን የፈጠረው እርሱ ነው። ከዚህ ኃይል መካከል ወደ ምድራችን የሚመጣው እጅግ ጥቂቱ ብቻ ሲሆን በምድር ላይ ሕይወትን ጠብቆ ለማቆየት ይረዳል። የፀሐይ ብርሃን ባይኖር ኖሮ በሕይወት መኖር አንችልም ነበር። ምድርም ሕይወት አልባ ፕላኔት ትሆን ነበር።

2 ይህንን በአእምሯችን መያዛችን ነቢዩ ኢሳይያስ የገለጸው ሁኔታ ምን ያህል ከባድ መሆኑን እንድንረዳ ያስችለናል። እርሱም “እነሆ፣ ጨለማ ምድርን ድቅድቅ ጨለማም አሕዛብን ይሸፍናል” ብሏል። (ኢሳይያስ 60:​2) እርግጥ ይህ ቃል በቃል ጨለማን አያመለክትም። ኢሳይያስ ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት ብርሃን መስጠታቸውን የሚያቆሙበት ቀን ይመጣል ማለቱ አይደለም። (መዝሙር 89:​36, 37፤ 136:​7-9) ከዚያ ይልቅ እየተናገረ ያለው ስለ መንፈሳዊ ጨለማ ነው። መንፈሳዊ ጨለማ ሞት ያስከትላል። ቃል በቃል ብርሃን ካጣን መኖር እንደማንችል ሁሉ መንፈሳዊ ብርሃን ካላገኘንም ውሎ አድሮ መሞታችን የማይቀር ነው።​—⁠ሉቃስ 1:​79

3. ከኢሳይያስ ቃላት አንጻር ክርስቲያኖች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

3 ከዚህ አንፃር ሲታይ ኢሳይያስ የተናገራቸው ቃላት በጥንቱ ይሁዳ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ቢሆንም በጊዜያችንም ከፍተኛ ተፈጻሚነታቸውን እያገኙ በመሆኑ እነዚህን ቃላት ልብ ማለቱ ሊያሳስበን ይገባል። አዎን፣ በጊዜያችን ዓለም በመንፈሳዊ ጨለማ ተውጦ ይገኛል። እንዲህ ባለው አደገኛ ሁኔታ መንፈሳዊ ብርሃን ማግኘት ከምንም ነገር በላይ አስፈላጊ ነው። ክርስቲያኖች “ብርሃናችሁ . . . በሰው ፊት ይብራ” የሚለውን ኢየሱስ የተናገረውን ምክር መከተላቸው የተገባ የሚሆነው በዚህ ምክንያት ነው። (ማቴዎስ 5:​16) ታማኝ ክርስቲያኖች ቅን ለሆኑ ሰዎች ጨለማውን በማብራት ሕይወት የሚያገኙበትን አጋጣሚ ሊከፍቱላቸው ይችላሉ።​—⁠ዮሐንስ 8:​12

በእስራኤል የነበረው የጨለማ ዘመን

4. የኢሳይያስ ትንቢታዊ ቃላት የመጀመሪያ ፍጻሜያቸውን ያገኙት መቼ ነበር? በኢሳይያስ ዘመን የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

4 ኢሳይያስ ምድር በጨለማ መሸፈኗን በተመለከተ የተናገረው ትንቢት ይሁዳ በወደመችበትና ሕዝቦችዋ ወደ ባቢሎን በምርኮ በተወሰዱበት ጊዜ የመጀመሪያ ፍጻሜውን አግኝቷል። ይሁን እንጂ ከዚያን ጊዜ በፊት በራሱ በኢሳይያስ ዘመን እንኳ ሳይቀር ሕዝቡ በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ይገኝ ነበር። ኢሳይያስ “እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፣ ኑ፣ በእግዚአብሔር ብርሃን እንሂድ” በማለት ለአገሩ ሰዎች እንዲናገር የገፋፋውም ይኸው ነው።​—⁠ኢሳይያስ 2:​5፤ 5:​20

5, 6. በኢሳይያስ ዘመን ለነበረው ጨለማ አስተዋጽዖ ያደረጉት ነገሮች ምንድን ናቸው?

5 ኢሳይያስ በይሁዳ ምድር ትንቢት ይናገር የነበረው “በይሁዳ ነገሥታት በዖዝያንና በኢዮአታም በአካዝና በሕዝቅያስ ዘመን” ነበር። (ኢሳይያስ 1:​1) ይህ ወቅት ፖለቲካዊ አለመረጋጋት፣ ሃይማኖታዊ ግብዝነት፣ የፍርድ መድልዎና የድሆች ጭቆና የሚንጸባረቅበት ሥርዓት አልበኛ ዘመን ነበር። እንዲያውም እንደ ኢዮአታም ባሉ የታመኑ ነገሥታት ዘመን እንኳ ሳይቀር በኮረብቶች አናት ላይ ለሐሰት አማልክት የቆሙ መሠዊያዎች ይታዩ ነበር። ታማኝ ባልነበሩ ነገሥታት ዘመን ደግሞ ሁኔታው ተባብሶ ነበር። ለምሳሌ ያህል ክፉዉ ንጉሥ አካዝ ሞሎክ ለተባለው ጣዖት ልጁን መሥዋዕት አድርጎ እስከ ማቅረብ ደርሶ ነበር። ከዚህ የከፋ ምን ጨለማ አለ!​—⁠2 ነገሥት 15:​32-34፤ 16:​2-4

6 በወቅቱ የነበረው የዓለም ሁኔታም ራሱ ጭጋግ የሸፈነው ነበር። ሞዓብ፣ ኤዶምና ፍልስጥኤም በይሁዳ ድንበሮች ላይ ስጋት እንዲያጠላ አድርገዋል። ከይሁዳ ጋር የደም ትስስር የነበረው ቢሆንም ሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት በዚህ ወቅት የለየለት ጠላት ሆኖባቸው ነበር። ትንሽ ወደ ሰሜን ከፍ ብሎ ደግሞ ሦርያ የይሁዳን ሰላም ስጋት ላይ ጥላለች። ይበልጥ አደገኛ የነበረው ደግሞ ኃይሉን ለማስፋፋት አጋጣሚዎችን ይፈልግ የነበረው ጨካኙ አሦር ነው። ኢሳይያስ ትንቢት ይናገር በነበረበት ዘመን አሦራውያን እስራኤልን ሙሉ በሙሉ ድል አድርገው ከካርታ ላይ አጥፍተዋት የነበረ ሲሆን ይሁዳንም ለማጥፋት የቀራቸው በጣም ጥቂት ነበር። አሦር ከኢየሩሳሌም በስተቀር በይሁዳ ያሉትን የተመሸጉ ከተሞች ሁሉ የተቆጣጠረበትም ጊዜ ነበር።​—⁠ኢሳይያስ 1:​7, 8፤ 36:​1

7. እስራኤልና ይሁዳ ምን ጎዳና መርጠዋል? ይሖዋስ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው?

7 የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝብ ይህን የመሰለ ከባድ መከራ ላይ የወደቀው እስራኤልና ይሁዳ ከሃዲ ሆነው በመገኘታቸው ምክንያት ነው። በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ እንደተጠቀሱት ሰዎች ‘በጨለማ መንገድ ይሄዱ ዘንድ የቀናውን መንገድ ትተዋል።’ (ምሳሌ 2:​13) ምንም እንኳ ይሖዋ በሕዝቡ ላይ ቢቆጣም ሙሉ በሙሉ ግን አልተዋቸውም። ከዚያ ይልቅ ይሖዋ በሕዝቡ መካከል በታማኝነት እርሱን ለማገልገል የሚፈልጉ ካሉ ለእነርሱ መንፈሳዊ ብርሃን ለመስጠት ሲል ኢሳይያስንና ሌሎች ነቢያትን አስነስቷል። በእነዚህ ነቢያት በኩል የበራው ብርሃን ምንኛ ታላቅ ዋጋ ያለው ነው። ሕይወት ሰጪ ብርሃን ነበር።

ዛሬ ያለው የጨለማ ዘመን

8, 9. በጊዜያችን ያለው ዓለም በጨለማ እንዲዋጥ ያደረጉት አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

8 በኢሳይያስ ዘመን የነበረው ሁኔታ በአሁኑ ጊዜ ከምናየው ነገር ጋር በእጅጉ የሚመሳሰል ነው። በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰብዓዊ መሪዎች ለይሖዋና እርሱ ዙፋን ላይ ላስቀመጠው ንጉሥ ለኢየሱስ ክርስቶስ ጀርባቸውን ሰጥተዋል። (መዝሙር 2:​2, 3) የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ መሪዎች መንጎቻቸውን አታልለዋል። እነዚህ መሪዎች አምላክን እናገለግላለን ቢሉም እውነታው ሲታይ ግን ብዙዎቹ የዚህ ዓለም አምላክ የሆኑትን ብሔረተኝነትን፣ ጦረኝነትን፣ ሃብትንና የታወቁ ግለሰቦችን የሚደግፉ ሲሆን ከአረማዊ መሠረተ ትምህርት በስተቀር የሚያስተምሩት ሌላ ነገር የለም።

9 በየአካባቢው የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች የዘር ማጽዳት ዘመቻና ሌሎች የጭካኔ ድርጊቶች በሚፈጸሙባቸው ጦርነቶችና በእርስ በርስ ግጭቶች ይካፈላሉ። ከዚህም በተጨማሪ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን ሥነ ምግባር ደግፈው ከመቆም ይልቅ እንደ ዝሙትና ግብረ ሰዶም የመሰሉ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ድርጊቶችን በዝምታ ያልፋሉ ወይም ሙሉ በሙሉ ይደግፋሉ። እንደነዚህ ያሉትን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ የአቋም ደረጃዎች ችላ ማለታቸው የሕዝበ ክርስትና መንጎች በጥንት ጊዜ የነበረ አንድ መዝሙራዊ “አያውቁም፣ አያስተውሉም፤ በጨለማ ውስጥ ይመላለሳሉ” በማለት እንደተናገረላቸው ዓይነት ሰዎች ሆነዋል። (መዝሙር 82:​5) በእርግጥም በጥንት ጊዜ እንደነበረችው ይሁዳ ሕዝበ ክርስትናም በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ትገኛለች።​—⁠ራእይ 8:​12

10. ዛሬ ባለው ጨለማ መካከል ብርሃን የፈነጠቀው እንዴት ነው? ቅን ሰዎች የተጠቀሙትስ እንዴት ነው?

10 በዚህ ታላቅ ጨለማ መካከል ይሖዋ ቅን ለሆኑ ሰዎች ሲል ብርሃን እንዲፈነጥቅ አድርጓል። ለዚህም በምድር ላይ የሚገኙትን ቅቡዓን አገልጋዮቹን ማለትም ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ የሚጠቀም ሲሆን እነርሱም “በዓለም እንደ ብርሃን” በማብራት ላይ ናቸው። (ማቴዎስ 24:​45፤ ፊልጵስዩስ 2:​15) የባሪያው ክፍል በሚልዮን በሚቆጠሩ “ሌሎች በጎች” ተባባሪዎቹ እየታገዘ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተውን መንፈሳዊ ብርሃን ያንጸባርቃል። (ዮሐንስ 10:​16) በዚህ ድቅድቅ ጨለማ በዋጠው ዓለም ውስጥ ይህ ብርሃን ቅን ለሆኑ ሰዎች ተስፋ ይሰጣል፣ ከአምላክ ጋር ዝምድና እንዲመሠርቱና ከመንፈሳዊ ወጥመዶች እንዲርቁ ይረዳቸዋል። በእርግጥም ይህ ውድና ሕይወት ሰጪ ብርሃን ነው።

“ስምህንም አመሰግናለሁ”

11. ይሖዋ በኢሳይያስ ዘመን ምን መረጃ ሰጥቷል?

11 ጨለማ በዋጠው በኢሳይያስ ዘመንና ከዚያ ጊዜ በኋላ በነበረው ባቢሎናውያን የይሖዋን ሕዝብ በምርኮ አግዘው በወሰዱበት ጨለማው ይበልጥ ድቅድቅ በሆነበት ጊዜ ይሖዋ ምን ዓይነት መመሪያ ሰጥቷል? የሥነ ምግባር መመሪያ ከመስጠቱም በተጨማሪ ከሕዝቡ ጋር በተያያዘ ዓላማውን እንዴት እንደሚፈጽም አስቀድሞ በግልጽ አስቀምጧል። ለምሳሌ ያህል ከኢሳይያስ ምዕራፍ 25 እስከ 27 ድረስ የሚገኙትን ድንቅ ትንቢቶች እንመርምር። በእነዚህ ምዕራፎች ውስጥ ያሉት ቃላት ይሖዋ በዚያን ዘመን አንዳንድ ጉዳዮችን እንዴት ይይዝ እንደነበረና ዛሬም እንደሚይዝ ያመለክታሉ።

12. ኢሳይያስ ምን ከልብ የመነጨ ምስጋና አቅርቧል?

12 በመጀመሪያ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “አቤቱ አንተ አምላኬ ነህ፤ . . . ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ ስምህንም አመሰግናለሁ።” እንዴት ያለ ልባዊ ምስጋና ነው! ነቢዩ እንዲህ ያለ ጸሎት እንዲያቀርብ የገፋፋው ነገር ምንድን ነው? የቀረው የጥቅሱ ክፍል “ድንቅን ነገር የዱሮ ምክርን በታማኝነትና በእውነት አድርገሃል” በማለት ዋነኛው ምክንያት ምን እንደሆነ ይገልጽልናል።​—⁠ኢሳይያስ 25:​1

13. (ሀ) ኢሳይያስ ለይሖዋ የነበረውን አድናቆት ያጠናከረለት ምን ነገር ማወቁ ነው? (ለ) ከኢሳይያስ ምሳሌ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?

13 በኢሳይያስ ዘመን ይሖዋ ለእስራኤላውያን በርካታ ድንቅ ሥራዎችን ያደረገላቸው ሲሆን እነዚህም ድንቅ ሥራዎች በጽሑፍ ሰፍረዋል። ኢሳይያስ እነዚህን ጽሑፎች እንደሚያውቃቸው ግልጽ ነው። ለምሳሌ ያህል ይሖዋ ሕዝቡን ከግብፅ ባርነት ነፃ እንዳወጣና በቀይ ባሕር በቁጣ እየገሰገሰ ከነበረው የግብፅ ሠራዊት እንዳዳናቸው ያውቃል። ይሖዋ ሕዝቡን በምድረ በዳ እንደመራና ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዳገባቸው ያውቃል። (መዝሙር 136:​1, 10-26) እንደነዚህ ያሉት ታሪካዊ ዘገባዎች አምላክ ታማኝና እምነት የሚጣልበት አምላክ መሆኑን ያሳያሉ። ‘ምክሩ’ ወይም ያለማቸው ነገሮች በሙሉ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ። ኢየሱስ ከመለኮታዊ ምንጭ ያገኘው ትክክለኛ እውቀት በብርሃን መመላለሱን እንዲቀጥል አበርትቶታል። በዚህ ረገድ ለእኛ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። በጽሑፍ የሰፈረውን የአምላክ ቃል በጥንቃቄ በማጥናት በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ብናደርግ እኛም በብርሃኑ መመላለሳችንን ልንቀጥል እንችላለን።​—⁠መዝሙር 119:​105፤ 2 ቆሮንቶስ 4:​6

ከተማዋ ተደመሰሰች

14. ስለ አንድ ከተማ ምን ትንቢት ተነግሮ ነበር? ይህች ከተማ ማን ሳትሆን አትቀርም?

14 ለምሳሌ ያህል ከአምላክ ምክር አንዱ በኢሳይያስ 25:​2 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል። እንዲህ ይላል:- “ከተማይቱን የድንጋይ ክምር፣ የተመሸገችውን ከተማ ውድማ እንድትሆን፣ የኀጥኣንንም አዳራሽ ከተማ እንዳትሆን አድርገሃል፤ ከቶ አትሠራም።” ይህች ከተማ ማን ነች? ኢሳይያስ በትንቢታዊ ሁኔታ እየተናገረ ያለው ስለ ባቢሎን ሳይሆን አይቀርም። በእርግጥም ደግሞ ባቢሎን የድንጋይ ክምር ብቻ ሆናለች።

15. ዛሬ ያለችው “ታላቂቱ ከተማ” ማን ናት? ምንስ ይደርስባታል?

15 ኢሳይያስ የጠቀሳት ከተማ ዛሬ ሌላ አምሳያ ይኖራት ይሆን? አዎን። የራእይ መጽሐፍ “በምድር ነገሥታት ላይ የምትነግሥ ታላቂቱ ከተማ” በማለት ይናገራል። (ራእይ 17:​18) ይህች ከተማ የዓለም የሃሰት ሃይማኖት ግዛት የሆነችው “ታላቂቱ ባቢሎን” ናት። (ራእይ 17:​5) የታላቂቱ ባቢሎን ዋነኛ ክፍል ሕዝበ ክርስትና ስትሆን ቀሳውስቷም የይሖዋ ሕዝቦች የሚያከናውኑትን የመንግሥቱን የስብከት ሥራ በመቃወም ረገድ በግንባር ቀደምትነት ተሰልፈዋል። (ማቴዎስ 24:​14) ይሁን እንጂ እንደ ጥንትዋ ባቢሎን ሁሉ ታላቂቱ ባቢሎንም ዳግም ላትነሳ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ትጠፋለች።

16, 17. የይሖዋ ጠላቶች ጥንትም ሆነ አሁን ይሖዋን ያከበሩት እንዴት ነው?

16 ኢሳይያስ “የተመሸገችውን ከተማ” በተመለከተ ምን ተጨማሪ ትንቢት ተናግሯል? ኢሳይያስ ከይሖዋ ጋር ሲነጋገር “ኃያላኑ ወገኖች ያከብሩሃል፣ የጨካኞች አሕዛብ ከተማም ትፈራሃለች” ብሏል። (ኢሳይያስ 25:​3) “የጨካኞች አሕዛብ ከተማ” የተባለችው ይቺ ክፉ ከተማ ይሖዋን የምታከብረው እንዴት ነው? በባቢሎን ኃያል ንጉሥ በናቡከደነፆር ላይ የደረሰውን አስታውስ። ድክመቱን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ የሚያባንን ነገር ከገጠመው በኋላ የይሖዋን ታላቅነትና ሁሉን ማድረግ የሚያስችል ኃይል ያለው መሆኑን አምኖ ለመቀበል ተገድዷል። (ዳንኤል 4:​34, 35) ይሖዋ ኃይሉን በሚጠቀምበት ጊዜ ጠላቶቹ እንኳን ሳይቀሩ ሳይወዱ በግድ ታላላቅ ሥራዎቹን አምነው ለመቀበል ይገደዳሉ።

17 ታላቂቱ ባቢሎን የይሖዋን ኃያል ሥራዎች አምና እንድትቀበል ተገድዳ ታውቃለች? አዎን። በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት የተቀቡት የይሖዋ አገልጋዮች በመከራ ሥር ሆነው ይሰብኩ ነበር። በ1918 በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በአመራር ቦታ ላይ የነበሩት ወንዶች ሲታሠሩ በመንፈሳዊ ምርኮ ተወሰዱ። የተደራጀው የስብከት ሥራ ያቆመ ያህል ሆኖ ነበር። ከዚያም በ1919 ይሖዋ ወደ ቀድሞው ቦታቸው በመመለስና በመንፈሱ ሕያው ሆነው እንዲንቀሳቀሱ በማድረግ በመላው ምድር ለሚገኙ ሰዎች ምሥራቹን የመስበኩን ተልዕኮ እንዲወጡ አደረገ። (ማርቆስ 13:​10) በተቃዋሚዎቻቸው ላይ የሚደርሰው ይህ ነገር በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ተተንብዮአል። እነዚህም “ፍርሃት ያዛቸው፣ ለሰማዩም አምላክ ክብር ሰጡ።” (ራእይ 11:​3, 7, 11-13) ሁሉም ሃይማኖታቸውን ለውጠዋል ማለት ሳይሆን ልክ ኢሳይያስ እንደተነበየው ይሖዋ በዚህ ወቅት የገለጠውን ኃያል ሥራውን አምነው ለመቀበል ተገድደዋል።

“ለድሀው መጠጊያ”

18, 19. (ሀ) ተቃዋሚዎች የይሖዋን ሕዝቦች ጽኑ አቋም ለማላላት ያልቻሉት ለምንድን ነው? (ለ) ‘የጨካኞች ዝማሬ የሚዋረደው’ እንዴት ነው?

18 አሁን ኢሳይያስ ይሖዋ በብርሃን የሚመላለሱትን ሰዎች በደግነት በሚይዝበት መንገድ ላይ በማተኮር ለይሖዋ እንዲህ በማለት ይናገራል:- “የጨካኞችም ቁጣ እስትንፋስ ቅጥርን እንደሚመታ ዐውሎ ነፋስ በሆነ ጊዜ፣ ለድሀው መጠጊያ፣ ለችግረኛው በጭንቁ ጊዜ መጠጊያ፣ ከውሽንፍር መሸሸጊያ ከሙቀትም ጥላ ሆነሃል። እንደ ሙቀት በደረቅ ስፍራ የኀጥኣንን ጩኸት ዝም ታሰኛለህ፤ ሙቀትም በደመና ጥላ እንዲበርድ እንዲሁ የጨካኞች ዝማሬ ይዋረዳል።”​—⁠ኢሳይያስ 25:​4, 5

19 ከ1919 ጀምሮ ጨካኝ ሰዎች የእውነተኛዎቹን አምላኪዎች ጽኑ አቋም ለማላላት ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም። ይሁን እንጂ አልተሳካላቸውም። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ ለሕዝቡ መጠጊያና መሸሸጊያ ነው። እንደ እሳት ከሚፋጀው ስደት የሚከላከል ጥላና እንደ አውሎ ነፋስ ካለው ተቃውሞ የሚጠብቅ ቅጥር ይሆንላቸዋል። በአምላክ ብርሃን የምንመላለስ ሁላችን ‘የጨካኞች ዝማሬ የሚዋረድበትን’ ጊዜ በትምክህት እንጠባበቃለን። አዎን፣ የይሖዋ ጠላቶች የማይኖሩበትን ጊዜ በናፍቆት እንጠብቃለን።

20, 21. ይሖዋ ያዘጋጀው ግብዣ ምንድን ነው? በአዲሱ ዓለም ይህ ግብዣ ምን ነገሮችን ይጨምራል?

20 ይሖዋ ሕዝቦቹን ከችግር ከመጠበቅ የበለጠ ነገርም ያደርጋል። እንደ አንድ አፍቃሪ አባት የሚያስፈልጋቸውን ነገር ያሟላላቸዋል። ሕዝቡን በ1919 ከታላቂቱ ባቢሎን ነፃ ካወጣ በኋላ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ በማቅረብ የድል ግብዣ አድርጎላቸዋል። ይህ በኢሳይያስ 25:​6 ላይ እንደሚከተለው ተተንበዮ ነበር:- “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ለሕዝብ ሁሉ በዚህ ተራራ ላይ ታላቅ የሰባ ግብዣ፣ ያረጀ የወይን ጠጅ፣ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፣ የጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ ያደርጋል።” እንደዚህ ካለው ግብዣ መካፈል በመቻላችን ምንኛ ተባርከናል! (ማቴዎስ 4:​4) ‘የይሖዋ ማዕድ’ በተትረፈረፉ መልካም ነገሮች ተሞልቷል። (1 ቆሮንቶስ 10:​21) “በታማኝና ልባም ባሪያ” በኩል በመንፈሳዊ የሚያስፈልጉን ነገሮች ሁሉ ይደርሱናል።

21 አምላክ የሚያቀርበው ይህ የተትረፈረፈ ማዕድ ከዚህም የበለጠ ትርጉም አለው። ዛሬ ያለው መንፈሳዊ ድግስ አምላክ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖረውን የተትረፈረፈ ሰብዓዊ ማዕድ ያስታውሰናል። ይህ “የሰባ ግብዣ” በዚያን ጊዜ የተትረፈረፈ ሰብዓዊ ምግብንም ይጨምራል። በዚያን ጊዜ በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ የሚራብ ሰው አይኖርም። የኢየሱስ መገኘት ‘ምልክት’ አካል እንደሚሆን በትንቢት የተነገረለት ‘የምግብ እጥረት’ በሚታይበት በዛሬው ጊዜ በዚህ ችግር ለሚሠቃዩት የታመኑ ወዳጆቻችን ይህ እንዴት ያለ እፎይታ ይሆናል! (ማቴዎስ 24:​3, 7 NW ) መዝሙራዊው የተናገራቸው ቃላት በእጅጉ ያጽናኗቸዋል። እንዲህ ብሏል:- “በምድሩ ላይ በቂ እህል ይኑር፤ ተራራዎች በሰብል ይሸፈኑ።”​—⁠መዝሙር 72:​16 የ1980 ትርጉም

22, 23. (ሀ) የሚወገደው “መጋረጃ” ወይም “መሸፈኛ” ምንድን ነው? ደግሞስ እንዴት? (ለ) ‘የይሖዋ ሕዝቦች ስድብ’ የሚወገደው እንዴት ነው?

22 አሁን ደግሞ ቀጥሎ የተጠቀሰውን ይበልጥ አስገራሚ የሆነ ተስፋ ተመልከት። ኢሳይያስ ኃጢአትንና ሞትን ‘ከመጋረጃ’ ወይም ‘ከመሸፈኛ’ ጋር በማወዳደር እንዲህ ይላል:- “በዚህም ተራራ ላይ በወገኖች ሁሉ ላይ የተጣለውን መጋረጃ፣ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋውን መሸፈኛ [ይሖዋ] ያጠፋል።” (ኢሳይያስ 25:​7) እስቲ አስበው! ዛሬ የሰውን ልጅ እንደ ብርድ ልብስ ጀቡነው የያዙት ኃጢአትና ሞት ይወገዳሉ። ታዛዥና ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆች ከኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ጊዜ በናፍቆት እንጠባበቃለን!​—⁠ራእይ 21:​3, 4

23 ይህን ድንቅ ጊዜ በማስመልከት ነቢዩ የሚከተለውን ማረጋገጫ ይሰጠናል:- “[አምላክ] ሞትን ለዘላለም ይውጣል፣ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፣ የሕዝቡንም ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና።” (ኢሳይያስ 25:​8) በተፈጥሯዊ ምክንያቶች የሚሞት ወይም የሚወደውን ሰው በሞት በማጣቱ ምክንያት እንባውን የሚያፈስስ ሰው አይኖርም። እንዴት ያለ የተባረከ ጊዜ ይሆናል! ከዚህም በላይ በአምላክም ሆነ በአገልጋዮቹ ላይ እስከ ዛሬ ድረስ ሲሰነዘር የኖረው ነቀፋና የውሸት ፕሮፓጋንዳ የሚሰማበት የምድር ክፍል አይኖርም። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ የእነዚህ ሁሉ ምንጭ የሆነውን የሐሰት አባት ማለትም ሰይጣን ዲያብሎስን ከዘር ማንዘሮቹ ጋር ያስወግዳል።​—⁠ዮሐንስ 8:​44

24. በብርሃን የሚመላለሱ ሁሉ ይሖዋ ላደረገላቸው ድንቅ ሥራዎች ምን ምላሽ ይሰጣሉ?

24 የይሖዋ ኃይል መግለጫ ስለሆኑት እነዚህን ስለመሳሰሉ ነገሮች በማሰላሰል በብርሃን የሚመላለሱ ሁሉ እንደሚከተለው ለማለት ይነሳሳሉ:- “እነሆ፣ አምላካችን ይህ ነው፤ ተስፋ አድርገነዋል፣ ያድነንማል፤ እግዚአብሔር ይህ ነው፤ ጠብቀነዋል፤ በማዳኑ ደስ ይለናል ሐሤትም እናደርጋለን።” (ኢሳይያስ 25:​9) በቅርቡ ጻድቅ የሰው ልጆች ከልባቸው የሚደሰቱበት በቂ ምክንያት አላቸው። ጨለማው ሙሉ በሙሉ ይገፈፋል። ታማኝ አገልጋዮቹ ከዘላለም እስከ ዘላለም የይሖዋ ብርሃን እንደፈነጠቀላቸው ይኖራሉ። ከዚህ የበለጠ ክብራማ ተስፋ ሊኖር ይችላልን? በጭራሽ ሊኖር አይችልም!

ልታብራራ ትችላለህን?

• ዛሬ በብርሃን መመላለስ የግድ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

• ኢሳይያስ የይሖዋን ስም ያወደሰው ለምንድን ነው?

• ጠላቶች የአምላክን ሕዝቦች ጽኑ አቋም ፈጽሞ ማላላት የማይችሉት ለምንድን ነው?

• በብርሃን የሚመላለሱት ሰዎች ምን የተትረፈረፈ በረከት ይጠብቃቸዋል?

[የጥናት እትም]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሁዳ ነዋሪዎች ልጆቻቸውን ለሞሎክ ሠውተዋል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢሳይያስ ስለ ይሖዋ ታላላቅ ሥራዎች ማወቁ የይሖዋን ስም እንዲያወድስ አነሳስቶታል

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጻድቃን የይሖዋ ብርሃን ለዘላለም እንደፈነጠቀላቸው ይኖራሉ