እውነተኛ ደስታ ማግኘት ትችላለህ?
እውነተኛ ደስታ ማግኘት ትችላለህ?
ጆርጅ ሁሉንም ሰው የሚቀበለው በፈገግታ ነው። ለእርሱ ሕይወት ማለት ሊደሰቱበት የሚገባ ውድ ስጦታ ነው። ጆርጅ እርጅና ተጫጭኖት እያለም እንኳ ደስታውና ብሩህ አመለካከቱ የእርሱ መለያ ምልክቶች ነበሩ። እስከሞተበት ቀን ድረስ በደስተኛነቱ የሚታወቅ ሰው ነበር። አንተስ እንደ ጆርጅ ደስተኛ ነህ? እያንዳንዱን አዲስ ቀን ልትደሰትበት የሚገባ ስጦታ እንደሆነ አድርገህ ትመለከተዋለህ? ወይስ የእያንዳንዱን አዲስ ቀን መጥባት ስታስብ የመሰላቸት ብሎም የጭንቀት ስሜት ያድርብሃል? ደስታህን የሚያሳጣህ ነገር አለን?
ደስታ አንጻራዊ ዘለቄታ ያለው የደህንነት ስሜት የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ደስታ ከእርካታ እስከ ውስጣዊና እውነተኛ ሐሴት ባሉት ስሜቶች እንዲሁም ይህ ዓይነቱ ሁኔታ በቀጠለ በሚለው ተፈጥሮአዊ ፍላጎት ይንጸባረቃል። እንዲህ ዓይነቱ ደስታ በእርግጥ አለን?
በዛሬው ጊዜ ያለው ኅብረተሰብ ለደስታ ብቸኛው ቁልፍ ሃብት ነው የሚለውን አመለካከት በማራመድ ላይ ሲሆን በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሃብታም ለመሆን በሚያደርጉት መፍጨርጨር ሕይወታቸው በሩጫ የተሞላ ሆኗል። ይህንን ለማድረግ ሲሉም ብዙዎች ከሌሎች ጋር ያላቸውን ዝምድናም ሆነ በሕይወት ውስጥ አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ነገሮችን መሥዋዕት ያደርጋሉ። በኩዪሳ ላይ እንዳሉ ጉንዳኖች እነርሱም መቋጫ በሌለው ጥድፊያ ላይ ስለሚሆኑ በሕይወታቸው ምን እየሠሩ እንዳሉ ወይም ከሌሎች ጋር ስላላቸው ግንኙነት እንኳ የሚያስቡበት ጊዜ አይኖራቸውም። በሎስ አንጀለስ ታይምስ ላይ የወጣ አንድ ሪፖርት እንደዘገበው “ጭንቀት እንዳለባቸው በምርመራ የተረጋገጠላቸው ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ” ምንም አያስደንቅም። “ሰዎች በጭንቀት መያዝ የሚጀምሩበት ዕድሜ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ሲሆን . . . ጭንቀትን ለመቋቋም ተብለው የሚወሰዱ መድኃኒቶች የመድኃኒት አምራች ኩባንያዎች በብዛት ገበያ ላይ ከሚያቀርቧቸው መድኃኒቶች ተርታ ተመድበዋል።” በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ችግሮቻቸውን ለመርሳት በሕግ የተከለከሉ አደገኛ መድኃኒቶችን ወይም የአልኮል መጠጦችን ይወስዳሉ። አንዳንዶች ሲጨነቁ ጊዜያቸውን በአስረሽ ምችው ያሳልፋሉ። “ሴቶች ጭንቀት ሲገጥማቸው ወደ ገበያ በመውጣት ጭንቀታቸውን የማቃለል ከፍተኛ
ዝንባሌ እንዳላቸው” አንድ ጥናት ማመልከቱን ዘ ጋርዲያን የተሰኘው የብሪታንያ ጋዜጣ ዘግቧል። “ሴቶች ሲጨነቁ ወደ ገበያ በመውጣት ረገድ ወንዶችን በሦስት እጥፍ ይበልጣሉ።”ይሁን እንጂ እውነተኛ ደስታ በገበያ ስፍራ፣ በመጠጥ ጠርሙስ፣ በእንክብል፣ በመርፌ ወይም በባንክ ሒሳብ ደብተር ውስጥ አይገኝም። ደስታ በገንዘብ የሚገዛ ሳይሆን በነፃ የሚገኝ ነው። እንዲህ ያለውን ውድ ስጦታ ከየት ማግኘት እንችላለን? በሚቀጥለው ርዕስ በዚህ ጥያቄ ላይ እንወያያለን።