እውነተኛ ደስታ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?
እውነተኛ ደስታ ማግኘት የሚቻለው እንዴት ነው?
አንድ የቡዲዝም ሃይማኖታዊ መሪ የሆኑ ዳላይ ላማ “የሕይወታችን ዋነኛ ዓላማ ደስታ ማግኘት ነው ብዬ አምናለሁ” ሲሉ ተናግረዋል። ከዚያም አእምሮንና ልብን በማሰልጠን ወይም በመገሰጽ ደስታ ማግኘት ይቻላል ብለው እንደሚያምኑ አብራሩ። “አእምሮ” ይላሉ ሃይማኖታዊ መሪው “የተሟላ ደስታ ለማግኘት የሚያስፈልግ ብቸኛ መሣሪያ ነው።” እኚህ ሰው በአምላክ የማመኑ አስፈላጊነት አይታያቸውም። a
ከዚህ በተቃራኒ ግን በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት የነበረውንና በትምህርቱ ላለፉት ብዙ መቶ ዘመናት በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት የነካውን ኢየሱስን ተመልከት። ኢየሱስ የሰው ልጆች ደስተኛ እንዲሆኑ ይፈልጋል። ዝነኛ የተራራ ስብከቱን የጀመረው ደስተኛ ስለሚያደርጉ ዘጠኝ ነገሮች በመግለጽ ነው። (ማቴዎስ 5:1-12) በዚሁ የተራራ ስብከቱ ላይ አድማጮቹ ከሥነ ምግባር ውጭ የሆኑትን እንዲሁም ዓመፀኛነትና ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅባቸውን አስተሳሰቦች ሰላማዊ፣ ንጹህና ፍቅራዊ በሆኑ ሐሳቦች በመተካት አእምሮአቸውንና ልባቸውን እንዲመረምሩ፣ እንዲያጠሩና እንዲገስጹ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 5:21, 22, 27, 28፤ 6:19-21) ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መካከል አንዱ ቆየት ብሎ እንዳሳሰበው “እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፣ ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፣ መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን” እንዲህ ያሉትን ነገሮች ማሰባችንን መቀጠል ይኖርብናል።—ፊልጵስዩስ 4:8
ኢየሱስ እውነተኛ ደስታ ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት እንደሚነካም ያውቅ ነበር። እኛ ሰዎች በተፈጥሯችን ከሌሎች ሰዎች ጋር መቀላቀል እንወዳለን። ስለዚህ ራሳችንን የምናገልል ወይም ከምናገኛቸው ሰዎች ጋር ሁልጊዜ የምንጋጭ ከሆነ እውነተኛ ደስታ ሊኖረን አይችልም። ደስተኛ መሆን የምንችለው የምንወደድ ሆኖ ከተሰማንና እኛ ራሳችን ሌሎችን የምንወድ ከሆነ ብቻ ነው። ኢየሱስ እንዳስተማረው ደግሞ እንዲህ ላለው ፍቅር መሠረቱ ከአምላክ ጋር ያለን ዝምድና ነው። ኢየሱስ ሰዎች ከአምላክ ርቀው በራሳቸው ቢመሩ እውነተኛ ደስታ እንደማያገኙ በማስተማር ከዳላይ ላማ የተለየ አመለካከት እንዳለው አሳይቷል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው?—ማቴዎስ 4:4፤ 22:37-39
ስለሚያስፈልጓችሁ መንፈሳዊ ነገሮች አስቡ
ኢየሱስ ደስተኛ ያደርጋሉ ብሎ ከጠቀሳቸው ነገሮች መካከል “ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው” የሚለውም ይገኝበታል። (ማቴዎስ 5:3 NW ) ኢየሱስ እንዲህ ብሎ የተናገረው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እኛ ከእንስሳት በተለየ መልኩ መንፈሳዊ ፍላጎት አለን። በአምላክ አምሳል የተፈጠርን እንደመሆናችን መጠን እንደ ፍቅር፣ ፍትህ፣ ምሕረትና ጥበብ የመሳሰሉትን መለኮታዊ ባሕርያት በተወሰነ መጠን ማንጸባረቅ እንችላለን። (ዘፍጥረት 1:27፤ ሚክያስ 6:8፤ 1 ዮሐንስ 4:8) መንፈሳዊ ፍላጎታችን የሕይወታችንን ዓላማ መገንዘብንም ይጨምራል።
ይህንን መንፈሳዊ ፍላጎት ማርካት የምንችለው እንዴት ነው? በማይጨበጥ ነገር ላይ በማሰላሰል ወይም የራስን ሐሳብና ስሜት በማብሰልሰል አይደለም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ እንደተናገረው “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም።” (ማቴዎስ 4:4) ኢየሱስ ለሕይወታችን በጣም አስፈላጊ የሆነው “ቃል ሁሉ” ምንጭ አምላክ ነው ማለቱን አስተውል። ለአንዳንዶቹ ጥያቄዎች መልሱን ሊሰጠን የሚችለው አምላክ ብቻ ነው። ስለ ሕይወት ዓላማና ለደስታ ቁልፍ ስለሆነው ነገር የሚሰጡ አስተያየቶች እንደ አሸን በፈሉበት በዛሬው ጊዜ እንዲህ ያለው ማስተዋል በጣም አስፈላጊ ነው። የመጻሕፍት መደብሮች መደርደሪያዎቻቸውን ያጨናነቁት ለአንባቢዎቻቸው ጤናን፣ ሃብትን እንዲሁም ደስታን እንደሚያስገኙ ተስፋ በሚሰጡ መጻሕፍት ነው። በደስታ ላይ ብቻ ያተኮሩ የኢንተርኔት ገጾችም ተዘጋጅተዋል።
የሆነ ሆኖ በእነዚህ መስኮች የሚንጸባረቀው ሰብዓዊ አስተሳሰብ ብዙውን ጊዜ የተሳሳተ ሲሆን የራስ ወዳድነት ፍላጎቶችን ወደ ማርካት ያዘነብላል። ውስን በሆነ እውቀትና ልምድ ላይ የተመካና አብዛኛውን ጊዜም በተሳሳቱ አስተሳሰቦች ላይ የተመሠረተ ነው። ለምሳሌ ያህል የራስ አገዝ መጻሕፍት አዘጋጆች “የዝግመተ ለውጥን” ንድፈ ሐሳብ የጽሑፎቻቸው መሠረት አድርገው መጠቀማቸው እየተለመደ መጥቷል። ይህ ንድፈ ሐሳብ የሰብዓዊ ስሜት መሠረቱ ቅድመ አያቶቻችን ናቸው ተብለው የሚታመኑት እንስሳት ናቸው በሚል ግምት ላይ የተመሠረተ ነው። እውነታው ግን የፈጣሪያችንን ሚና በማይቀበል ንድፈ ሐሳብ ላይ ተመሥርቶ ደስታ ለማግኘት የሚደረግ ማንኛውም ጥረት ውጤት አይኖረውም። እንዲያውም ይህን የመሰለው ጥረት ውሎ አድሮ ለብስጭት መዳረጉ የማይቀር ነው። አንድ ጥንታዊ ነቢይ “ጥበበኞች አፍረዋል . . . እነሆ፣ የእግዚአብሔርን ቃል ጥለዋል፤ ምን ዓይነት ጥበብ አላቸው?” ሲል ተናግሯል።—ኤርምያስ 8:9
ይሖዋ አምላክ ፈጣሪያችን ስለሆነ እውነተኛ ደስታ የሚሰጠን ነገር ምን እንደሆነ ያውቃል። ሰውን ምድር ላይ ያስቀመጠበትን ምክንያትና ወደፊት ምን ተስፋ እንዳለን ያውቃል። ይህንንም እውቀት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ገልጾልናል። አምላክ በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የገለጸው እውቀት ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች አዎንታዊ ምላሽ እንዲሰጡ በማድረግ በውስጣቸው ደስታን ይፈጥርላቸዋል። (ሉቃስ 10:21፤ ዮሐንስ 8:32) ይህንንም ሁለቱ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከገጠማቸው ነገር ማየት ይቻላል። ኢየሱስ በመሞቱ በጣም አዝነው የነበረ ቢሆንም አምላክ የሰው ልጆችን ለማዳን ባደረገው ዝግጅት ውስጥ ኢየሱስ የሚጫወተውን ሚና ከሞት ከተነሣው ከራሱ ከኢየሱስ አፍ ከሰሙ በኋላ እንዲህ አሉ:- “በመንገድ ሲናገረን መጻሕፍትንም ሲከፍትልን ልባችን ይቃጠልብን አልነበረምን?”—ሉቃስ 24:32
የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሕይወታችንን እንዲመራ ስንፈቅድ እንዲህ ያለው ደስታ ጥልቅ እየሆነ ይሄዳል። በዚህ ረገድ ደስታ ከቀስተ ደመና ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ቀስተ ደመና ተስማሚ ሁኔታዎች ሲኖሩ ይወጣል፤ ሁኔታዎች በጣም ሲመቻቹለት ደግሞ ይበልጥ ይደምቃል እንዲያውም ድርብ ቀስተ ደመና ይሆናል። የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ተግባራዊ ማድረግ ደስታችንን ይበልጥ ጥልቅ ሊያደርገው የሚችለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ ጥቂት ምሳሌዎች እንመልከት።
ኑሯችሁን ቀላል አድርጉት
በመጀመሪያ ደረጃ ኢየሱስ ሃብትን አስመልክቶ የሰጠውን ምክር ተመልከቱ። ሃብትን ዋነኛ የሕይወት ግብ አድርጎ ማሳደድን በተመለከተ ምክር ከሰጠ በኋላ አንድ እንግዳ የሆነ ነገር ተናገረ። “ዓይንህ እንግዲህ ጤናማ [“ቀና፣” NW ] ብትሆን፣ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል።” (ማቴዎስ 6:19-22) በመሠረቱ ኢየሱስ ይህን ሲል ሃብትን፣ ሥልጣንን ወይም ሰዎች ለራሳቸው የሚያወጧቸውን የተለያዩ ዓይነት ግቦች የምናሳድድ ከሆነ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች ያመልጡናል ማለቱ ነው። ኢየሱስ በሌላም አጋጣሚ እንደተናገረው “የሰው ሕይወት በገንዘቡ ብዛት አይደለም።” (ሉቃስ 12:15) በጣም አስፈላጊ ለሆኑ ነገሮች ማለትም ከአምላክ ጋር ላለን ዝምድና፣ ለቤተሰብ ጉዳዮችና ከዚህ ጋር ለሚዛመዱ ሌሎች ነገሮች ቅድሚያ የምንሰጥ ከሆነ ‘ዓይናችን ቀና’ በሌላ አባባል በአንድ ነገር ላይ ያተኮረ ይሆናል።
ኢየሱስ ብሕትውናን ማበረታታቱ እንዳልነበር ልብ በል። ራሱ ኢየሱስም ቢሆን ባሕታዊ አልነበረም። (ማቴዎስ 11:19፤ ዮሐንስ 2:1-11) በሌላ በኩል ኢየሱስ ሕይወትን ሃብት ለመሰብሰብ የሚያስችል አጋጣሚ እንደሆነ አድርገው ብቻ የሚመለከቱ ሰዎች ከሕይወት ሊያገኙ የሚችሉትን ብዙ ነገር ያጣሉ በማለት አስተምሯል።
በዩ ኤስ ኤ ሳንፍራንሲስኮ የሚኖሩ አንድ የሥነ ልቦና ሐኪም ገና በልጅነታቸው በጣም ሃብታም ስለሚሆኑ ሰዎች ሲናገሩ ገንዘብ ማለት እንዲህ ላሉት ሰዎች “የውጥረትና የግራ መጋባት ምንጭ” ነው ብለዋል። አክለውም እንዲህ ያሉት ሰዎች “ሁለት ወይም ሦስት ቤት፣ መኪና እና ሌሎች ነገሮችን በመግዛት ገንዘባቸውን ያጠፋሉ። ሆኖም እንዲህ ማድረጋቸው እንዳልበጃቸው [ደስታ እንዳላስገኘላቸው ማለት ነው] ሲያውቁ በጭንቀት ይዋጣሉ፣ ባዶነት ይሰማቸዋል እንዲሁም በሕይወታቸው ምን እንደሚያደርጉ ግራ ይገባቸዋል።” ከዚህ በተቃራኒ ግን ኢየሱስ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ በመስጠት በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ቀለል ያለ ሕይወት ስለመምራት የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ያደረጉ ሰዎች እውነተኛ ደስታ ማግኘታቸው የማይቀር ነው።
ቶም የተባለ በሃዋይ የሚኖር የሕንጻ ሠራተኛ በፓስፊክ ደሴቶች የአምልኮ ቦታዎችን ለመገንባት በሚደረገው እንቅስቃሴ ለመካፈል ራሱን በፈቃደኝነት አቀረበ። በእነዚህ ደሴቶች የሚኖሩ ሰዎች በቁሳዊ ነገሮች ረገድ ያላቸው ጥቂት ቢሆንም ቶም ስለ እነዚህ ትሁት ሰዎች አንድ ነገር ተገነዘበ። እንዲህ ብሏል:- “በእነዚህ ደሴቶች የሚኖሩ ክርስቲያን ወንድሞቼና እህቶቼ እውነተኛ ደስታ አላቸው። ገንዘብና ቁሳዊ ሃብት ለደስታ ቁልፍ አለመሆናቸውን ይበልጥ እንድገነዘብ ረድተውኛል።” በደሴቶቹ ከእርሱ ጋር አብረው የሠሩት ፈቃደኛ ሠራተኞች ምን ያህል ረክተው እንደሚኖሩም አስተውሏል። ቶም “ብዙ ገንዘብ ማግኘት ቢችሉም ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ በመስጠት ቀለል ያለ ሕይወት መምራትን መርጠዋል” ሲል ተናግሯል። ቶም በእነዚህ ምሳሌዎች በመገፋፋት ለቤተሰቡና ለመንፈሳዊ ነገሮች ተጨማሪ ጊዜ ማዋል ይችል ዘንድ ኑሮውን ቀላል አደረገ። ቶም እንዲህ ያለ ለውጥ በማድረጉ ፈጽሞ አልተቆጨም።
ደስታና ለራስ ጥሩ ግምት ማሳደር
ዋጋ እንዳለን የሚሰማን ወይም ለራሳችን ጥሩ ግምት ያለን መሆኑ ለደስታ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። አንዳንዶች በሰብዓዊ አለፍጽምና እንዲሁም ይህ አለፍጽምና በሚያስከትላቸው መዘዞች ምክንያት ስለ ራሳቸው አሉታዊ አመለካከት ያድርባቸዋል። ብዙዎች ደግሞ እንዲህ ያለው ስሜት የሚሰማቸው ገና ከልጅነታቸው ጀምሮ ነው። ይህን ሥር የሰደደ ስሜት ማስወገድ ቀላል ባይሆንም የማይቻል ግን አይደለም። መፍትሄው የአምላክን ቃል ተግባራዊ ማድረግ ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ፈጣሪ ስለ እኛ ምን እንደሚሰማው ይገልጽልናል። ከማንኛውም ሰብዓዊ አመለካከት እንዲያውም ከራሳችን አመለካከት እንኳ ሳይቀር የበለጠ ግምት ሊሰጠው የሚገባው የእርሱ አመለካከት አይደለምን? አምላክ ራሱ ፍቅር ስለሆነ የሚያየን ያላንዳች መድልዎ ወይም ከክፋት ነጻ በሆነ መንገድ ነው። አምላክ የሚመለከተን በእኛነታችን ሲሆን የሚጠብቅብንም መሆን የምንችለውን ብቻ ነው። (1 ሳሙኤል 16:7፤ 1 ዮሐንስ 4:8) እንዲያውም አምላክ እርሱን ለማስደሰት የሚፈልጉትን ሰዎች ምንም ያህል አለፍጽምና ቢኖርባቸው እንደ ውድ ማለትም እንደተመረጠ እቃ አድርጎ ይመለከታቸዋል።—ዳንኤል 9:23፤ ሐጌ 2:7
እርግጥ አምላክ ድክመቶቻችንንም ሆነ የምንሠራቸውን ማናቸውንም ኃጢአቶች ችላ ብሎ ያልፋል ማለት አይደለም። ትክክል የሆነውን ለማድረግ ጠንክረን እንድንሠራ የሚጠብቅብን ቢሆንም ይህን ስናደርግ ድጋፍ ይሰጠናል። (ሉቃስ 13:24) ያም ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስ “አባት ለልጆቹ እንደሚራራ እንዲሁ እግዚአብሔር ለሚፈሩት ይራራል” በማለት ይናገራል። በተጨማሪም “አቤቱ፣ ኃጢአትንስ ብትጠባበቅ፣ አቤቱ፣ ማን ይቆማል? ይቅርታ ከአንተ ዘንድ ነውና” ይላል።—መዝሙር 103:13፤ 130:3, 4
ስለዚህ ራስህን በአምላክ ዓይን ማየትን ተማር። አምላክ ለእርሱ ፍቅር ያላቸውን ሰዎች ራሳቸውን የማይጠቅሙ እንደሆኑ አድርገው ሊያስቡ ቢችሉም እንኳ እርሱ እንደተመረጠ እቃ አድርጎ እንደሚያያቸውና እንደሚተማመንባቸው ማወቅ የአንድን ሰው ደስታ በመጨመር ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል።—1 ዮሐንስ 3:19, 20
ተስፋ—ለደስታ ዋነኛው ቁልፍ
በቅርቡ በሰፊው ተቀባይነትን ያገኘው ፖዘቲቭ ሳይኮሎጂ የተሰኘ ንድፈ ሐሳብ አዎንታዊ አስተሳሰብ በመያዝና በግል ጠንካራ ጎኖች ላይ በማተኮር የሚዳብረው ብሩህ አመለካከት ወደ ደስታ ሊመራ እንደሚችል ይገልጻል። ስለ ሕይወትና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩህ አመለካከት መያዝ ለደስታችን አስተዋጽኦ ያደርጋል የሚለውን ሐሳብ የማይቀበሉ ሰዎች ጥቂት ናቸው። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለው ብሩህ አመለካከት በእውነታ እንጂ እንዲሁ በምኞት ላይ የተመሠረተ መሆን የለበትም። ከዚህም በላይ የትኛውም ዓይነት ብሩህ አመለካከት ወይም አዎንታዊ አስተሳሰብ ጦርነትን፣ ረሃብን፣ በሽታን፣ ብክለትን፣ እርጅናን፣ ሕመምን ወይም ሞትን አያስወግድም። እነዚህ ደግሞ የብዙ ሰዎችን ደስታ የሚነጥቁ ነገሮች ናቸው። የሆነ ሆኖ ብሩህ አመለካከት የራሱ የሆነ ድርሻ አለው።
መጽሐፍ ቅዱስ ብሩህ አመለካከት የሚለውን ቃል ከመጠቀም ይልቅ ይበልጥ ኃይል ያለውን ተስፋ የሚል ቃል መጠቀሙ ትኩረት የሚስብ ነው። ቫይንስ ኮምፕሊት ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸውን “ተስፋ” የሚለውን ቃል ሲተረጉም “በእርግጠኝነት ይመጣል ተብሎ የሚጠበቅ በጎ ነገር . . . አንድን መልካም ነገር በጉጉት መጠበቅ” በማለት አስቀምጦታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት ተስፋ የሚለው ቃል ስለ አንድ ሁኔታ ብሩህ አመለካከት ከመያዝ የበለጠ ነገርን ይጨምራል። የአንድ ሰው ተስፋ የተገነባበትንም ነገር ያመለክታል። (ኤፌሶን 4:4፤ 1 ጴጥሮስ 1:3) ለምሳሌ ያህል የክርስትና ተስፋ ቀደም ባለው አንቀጽ ላይ የተገለጹት መጥፎ ሁኔታዎች በቅርቡ እንደሚወገዱ የሚገልጽ ነው። (መዝሙር 37:9-11, 29) ይሁን እንጂ የክርስቲያን ተስፋ ከዚህ የበለጠ ነገርንም ይጨምራል።
ክርስቲያኖች ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ፍጹም ሕይወት የሚያገኙበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። (ሉቃስ 23:42, 43) ራእይ 21:3, 4 ደግሞ ይህንን ተስፋ ሰፋ አድርጎ ሲገልጽ እንዲህ ይላል:- “እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ . . . እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።”
እንዲህ ያለውን ተስፋ ፍጻሜ ለማየት የሚጠብቅ ማንኛውም ሰው ዛሬ የሚፈልገውን ያህል የተመቻቸ ሁኔታ ባይኖረውም ደስተኛ የሚሆንበት ምክንያት አለው። (ያዕቆብ 1:12) እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት በዚህ ተስፋ ላይ እምነት መጣል የምትችልበት ምክንያት ምን እንደሆነ ለምን አትመረምርም? መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ በማንበብ ተስፋህን አጠንክር። እንዲህ ማድረግህ አንተን በመንፈሳዊ ከማበልጸጉም በተጨማሪ ሰዎችን ደስታ ከሚነሷቸው ነገሮች እንድትጠበቅ ይረዳሃል። እንዲሁም ጥልቅ እርካታ ይሰጥሃል። አዎን፣ ለእውነተኛ ደስታ ትልቁ ቁልፍ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ ነው። (መክብብ 12:13) መጽሐፍ ቅዱስን በመታዘዝ ላይ የተመሠረተ ሕይወት ደስተኛ ያደርጋል። ምክንያቱም ኢየሱስ “ብፁዓንስ [“ደስተኞችስ፣” NW ] የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው” ብሏል።—ሉቃስ 11:28
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ለአንድ የቡድሃ እምነት ተከታይ በአምላክ ማመን አስፈላጊ ነገር አይደለም።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሃብትን በማግበስበስ፣ ራስን በማግለል ወይም ውስን በሆነው ሰብዓዊ እውቀት ላይ በመታመን ደስታ ማግኘት አይቻልም
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክን ቃል በመታዘዝ ላይ የተመሠረተ ሕይወት ደስተኛ ያደርጋል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የክርስትና ተስፋ አንድን ሰው ደስተኛ ያደርገዋል