በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰብዓዊ ድክመቶችን ማሸነፍ

ሰብዓዊ ድክመቶችን ማሸነፍ

ሰብዓዊ ድክመቶችን ማሸነፍ

“ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነው።”​—⁠ሮሜ 8:​6

1. አንዳንዶች ሰብዓዊ አካልን እንዴት አድርገው ይመለከቱታል? የትኛውን ጥያቄስ መመርመር ይኖርብናል?

 “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ።” (መዝሙር 139:​14) መዝሙራዊው ዳዊት ከይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች መካከል ስለ አንዱ ማለትም ስለ ሰብዓዊው አካል ካሰላሰለ በኋላ ከላይ ያለውን በማለት ዘምሯል። አንዳንድ የሃይማኖት አስተማሪዎች በትክክለኛ እውቀት ላይ ተመሥርተው ተመሳሳይ የሆነ ውዳሴ ከማሰማት ይልቅ ሰብዓዊ አካልን ኃጢአት አድብቶ የሚቀመጥበት ቦታና የኃጢአት መሣሪያ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። አካል “የድንቁርና ካባ፣ የመጥፎ ምግባር ጎሬ፣ የሙስና ማሠሪያ፣ የጨለማ ማጎሪያ፣ ደስታና እርካታ የራቀው ሕይወት፣ ተንቀሳቃሽ ሬሳ፣ ተንቀሳቃሽ መቃብር” ተብሎ ተጠርቷል። እርግጥ ሐዋርያው ጳውሎስም “በሥጋዬ በጎ ነገር እንዳይኖር አውቃለሁ” በማለት ተናግሯል። (ሮሜ 7:​18) ታዲያ እንዲህ ሲባል ከኃጢአት ፈጽሞ መላቀቅ አንችልም ማለት ነው?

2. (ሀ) ‘ስለ ሥጋ ማሰብ’ ማለት ምን ማለት ነው? (ለ) አምላክን ለማስደሰት በሚፈልጉ ሰዎች ውስጥ ‘በሥጋ’ እና ‘በመንፈስ’ መካከል ምን ዓይነት ውጊያ ይካሄዳል?

2 ቅዱሳን ጽሑፎች አንዳንድ ጊዜ ከዓመፀኛው አዳም ኃጢአት የወረሰውንና ፍጽምና የጎደለውን ሰው ለማመልከት ‘ሥጋ’ የሚለውን ቃል ይጠቀማሉ። (ኤፌሶን 2:​3፤ መዝሙር 51:​5፤ ሮሜ 5:​12) ከአዳም የወረስነው ነገር ‘የሥጋ ድካም’ አስከትሎብናል። (ሮሜ 6:​19) በተጨማሪም ጳውሎስ “ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነው” በማለት አስጠንቅቋል። (ሮሜ 8:​6) “ስለ ሥጋ ማሰብ” ማለት ለኃጢአተኛው ሥጋ ምኞቶች መገዛትና ለሚያሳድረው ግፊት መሸነፍ ማለት ነው። (1 ዮሐንስ 2:​16) ስለዚህ አምላክን ለማስደሰት ጥረት በምናደርግበት ጊዜ በመንፈሳዊነታችንና ‘የሥጋ ሥራ’ እንድንፈጽም ያልተቋረጠ ግፊት በሚያሳድርብን በኃጢአተኛው ዝንባሌያችን መካከል ዘወትር ውጊያ ይካሄዳል። (ገላትያ 5:​17-23፤ 1 ጴጥሮስ 2:​11) ጳውሎስ እንዲህ ያለ ሥቃይ የሞላበት ውጊያ በውስጡ እንደሚካሄድ ከገለጸ በኋላ “እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ! ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል?” በማለት በምሬት ተናግሯል። (ሮሜ 7:​24) ጳውሎስ ምንም ፈተና መቋቋም የማይችል ሰው ነበር ማለት ነው? እንደዚያ እንዳልሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ያደርግልናል!

የፈተናና የኃጢአት ምንነት

3. ብዙ ሰዎች ኃጢአትንና ፈተናን የሚመለከቷቸው እንዴት ነው? ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ካለው አመለካከት እንድንርቅ የሚያስጠነቅቀን እንዴት ነው?

3 በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ኃጢአት የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ አይቀበሉም። አንዳንዶች ሰዎች የሚሠሯቸውን ጥቃቅን ስሕተቶች ለመግለጽ “ኃጢአት” የሚለውን ቃል ጊዜ እንዳለፈበት አነጋገር አድርገው በመመልከት በቀልድ መልክ ሲጠቀሙበት ይሰማል። “መልካም ቢሆን ወይም ክፉ እንዳደረገ፣ እያንዳንዱ በሥጋው የተሠራውን በብድራት ይቀበል ዘንድ ሁላችን በክርስቶስ በፍርድ ወንበር ፊት ልንገለጥ ይገባናልና” የሚለውን አልተገነዘቡም። (2 ቆሮንቶስ 5:​10) ሌሎች ደግሞ “ማንኛውንም ነገር መቋቋም እችላለሁ፣ ፈተናን መቋቋም ግን አልችልም!” የሚል የተጋነነ ሐሳብ ይሰነዝራሉ። አንዳንድ ሰዎች ምግብን፣ ፆታን፣ ጨዋታን ወይም በሥራ ስኬት ማግኘትን ጨምሮ ቅጽበታዊ ደስታ ያስገኛሉ ለሚባሉ ነገሮች ከፍተኛ ግምት በሚሰጥ ባሕል ውስጥ ይኖራሉ። ሁሉንም ነገር ማግኘት ብቻ ሳይሆን አሁኑኑ ማግኘት ይፈልጋሉ! (ሉቃስ 15:​12 የ1980 ትርጉም ) ለጊዜው ከሚያገኙት ደስታ አሻግረው ‘እውነተኛ ሕይወት’ የሚገኝበትን ጊዜ አይመለከቱም። (1 ጢሞቴዎስ 6:​19) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በጥንቃቄ እንድናስብና በመንፈሳዊም ሆነ በሌላ መንገድ ጉዳት ላይ ሊጥለን ከሚችል ከማንኛውም ነገር በመራቅ አርቀን የምንመለከት እንድንሆን ያስተምረናል። በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ አንድ ምሳሌ “ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጐዳሉ” በማለት ይናገራል።​—⁠ምሳሌ 27:​12

4. በ1 ቆሮንቶስ 10:​12, 13 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ጳውሎስ የሰጠው ምክር ምንድን ነው?

4 ጳውሎስ ልቅ በሆነ ሥነ ምግባር በምትታወቀው በቆሮንቶስ ከተማ ይኖሩ ለነበሩ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ፈተና እና ኃጢአት ያላቸውን ኃይል በተመለከተ ትክክለኛ የሆነ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። እንዲህ አለ:- “ስለዚህ እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ። ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፣ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።” (1 ቆሮንቶስ 10:​12, 13) ወጣትም ሆንን በዕድሜ የገፋን፣ ወንድም ሆንን ሴት ሁላችንም በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ ወይም በሌላ አካባቢ የተለያዩ ፈተናዎች ይገጥሙናል። ስለዚህ የጳውሎስን ቃላት እንመርምርና ለእኛ ምን ትርጉም እንዳላቸው እንመልከት።

ከመጠን በላይ በራሳችሁ አትተማመኑ

5. ከመጠን በላይ በራስ መተማመን አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው?

5 ጳውሎስ “እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” በማለት ጽፏል። በራሳችን የሥነ ምግባር ጥንካሬ ከመጠን በላይ መተማመን አደገኛ ነው። እንዲህ ያለው ዝንባሌ የኃጢአትን ምንነትና ያለውን ኃይል በተመለከተ ማስተዋል እንደጎደለን የሚያሳይ ነው። እንደ ሙሴ፣ ዳዊት፣ ሰሎሞንና ሐዋርያው ጴጥሮስ ያሉ ሰዎች በኃጢአት ከወደቁ እኛን ፈጽሞ እንደማይነካን አድርገን ማሰብ ይኖርብናልን? (ዘኁልቁ 20:​2-13፤ 2 ሳሙኤል 11:​1-27፤ 1 ነገሥት 11:​1-6፤ ማቴዎስ 26:​69-75) ምሳሌ 14:​16 “ጠቢብ ሰው ይፈራል ከክፉም ይሸሻል፤ ሰነፍ ግን ራሱን ታምኖ ይኰራል” በማለት ይናገራል። ከዚህም በላይ ኢየሱስ “መንፈስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 26:​41) ፍጹም ያልሆነ ማንኛውም ሰው መጥፎ ለሆነ ምኞት የተጋለጠ ስለሆነ የጳውሎስን ማስጠንቀቂያ በቁም ነገር መመልከትና ፈተናዎችን መቋቋም ይኖርብናል፤ እንደዚያ ካላደረግን በኃጢአት ልንሸነፍ እንችላለን።​—⁠ኤርምያስ 17:​9

6. ራሳችንን ለፈተና ማዘጋጀት ያለብን መቼና እንዴት ነው?

6 ድንገት ሊከሰት ለሚችል ችግር አስቀድሞ መዘጋጀትም ጥበብ ነው። ንጉሥ አሳ የሰላሙ ወቅት ምሽግ ለመሥራት የሚያስችል ትክክለኛ ጊዜ እንደሆነ ተገንዝቧል። (2 ዜና መዋዕል 14:​2, 6, 7) ጥቃት ከጀመረ በኋላ ከመሯሯጥ ቀደም ብሎ መዘጋጀት አስፈላጊ መሆኑን አውቋል። በተመሳሳይም ፈተናዎች በሚያጋጥሙበት ጊዜ ምን ማድረግ እንደሚገባ የስሜት መረበሽ በማይኖርበት ሰላማዊ በሆነ ወቅት መወሰን የተሻለ ነው። (መዝሙር 63:​6) ዳንኤልና ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው ጓደኞቹ ለይሖዋ ሕግ ታማኝ መሆን እንዳለባቸው ውሳኔ ላይ የደረሱት የንጉሡን ምግብ እንዲመገቡ ከመገደዳቸው በፊት ነው። በዚህም የተነሳ ርኩስ የሆነ ምግብ ላለመመገብ የወሰዱትን ቁርጥ አቋም የሙጥኝ ለማለት ፈጽሞ አላመነቱም። (ዳንኤል 1:​8) ፈታኝ ሁኔታዎች ከመከሰታቸው በፊት በሥነ ምግባር ንጹህ ሆነን ለመኖር የወሰድነውን ቁርጥ አቋም እናጠንክር። እንደዚያ ካደረግን ኃጢአትን የመቋቋም ችሎታው ይኖረናል።

7. ሌሎች ፈተናን ተቋቁመው እንዳሸነፉ ማወቁ የሚያጽናና የሆነው ለምንድን ነው?

7 “ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም” የሚሉት የጳውሎስ ቃላት ምንኛ የሚያጽናኑ ናቸው! (1 ቆሮንቶስ 10:​13) ሐዋርያው ጴጥሮስ “በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ [ዲያብሎስን] ተቃወሙት” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 5:​9) አዎን፣ ሌሎችም ተመሳሳይ ፈተናዎች ደርሰውባቸው በአምላክ እርዳታ በተሳካ ሁኔታ ተቋቁመዋቸዋል። እኛም ልንቋቋማቸው እንችላለን። ይሁን እንጂ ብልሹ በሆነ ዓለም ውስጥ የምንኖር እውነተኛ ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ ሁላችንም ፈተና እንደሚደርስብን ልንጠብቅ እንችላለን። ታዲያ ሰብዓዊ ድክመትንና ኃጢአት እንድንሠራ የሚደርስብንን ፈተና በድል እንደምንወጣ እንዴት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን?

ፈተናን መቋቋም እንችላለን!

8. ከፈተና መራቅ የሚቻልበት አንዱ መሠረታዊ መንገድ ምንድን ነው?

8 ‘የኃጢአት ባሪያ’ ከመሆን መላቀቅ የሚቻልበት አንዱ መሠረታዊ ዘዴ በተቻለ መጠን ከፈተና መራቅ ነው። (ሮሜ 6:​6 የ1980 ትርጉም ) ምሳሌ 4:​14, 15 “በኀጥኣን መንገድ አትግባ፣ በክፉ ሰዎችም ጎዳና አትሂድ። ከእርስዋ ራቅ፣ አትሂድባትም፤ ፈቀቅ በል ተዋትም” በማለት አጥብቆ ይመክረናል። አንዳንድ ሁኔታዎች ወደ ኃጢአት ሊመሩ እንደሚችሉ ብዙውን ጊዜ አስቀድመን እናውቃለን። ስለዚህ ክርስቲያን እንደመሆናችን መጠን ማድረግ ያለብን ግልጽ የሆነው ነገር ‘መራቅ’ ማለትም በውስጣችን መጥፎ ምኞትና ርኩስ ስሜት እንዲቀሰቀስ ሊያደርግ ከሚችል ከማንኛውም ሰው፣ ከማንኛውም ነገር እንዲሁም ከማንኛውም ቦታ መራቅ ነው።

9. ፈተና ላይ ሊጥሉ ከሚችሉ ሁኔታዎች መሸሽ በቅዱሳን ጽሑፎች ጠበቅ ተደርጎ የተገለጸው እንዴት ነው?

9 ፈተናን ማሸነፍ የሚያስችል ሌላው መሠረታዊ እርምጃ ፈተና ላይ ሊጥል ከሚችል ሁኔታ መሸሽ ነው። ጳውሎስ “ከዝሙት ሽሹ” በማለት ምክር ለግሷል። (1 ቆሮንቶስ 6:​18) እንዲሁም “ጣዖትን ከማምለክ ሽሹ” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 10:​14) በተጨማሪም ሐዋርያው ለቁሳዊ ብልጥግና ተገቢ ያልሆነ ምኞት ከማዳበርና “ከክፉ የጒልማሳነት ምኞት” እንዲሸሽ ጢሞቴዎስን አስጠንቅቆታል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 2:​22፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:​9-11

10. ከፈተና መሸሽ ጠቃሚ መሆኑን የትኞቹ ሁለት ተቃራኒ ምሳሌዎች ያሳያሉ?

10 የእስራኤል ንጉሥ የነበረውን የዳዊትን ሁኔታ ተመልከት። ከቤተ መንግሥቱ ሰገነት ላይ ሆኖ አንዲት ቆንጆ ሴት ገላዋን ስትታጠብ ተመለከተ። ይህም በልቡ ውስጥ መጥፎ ምኞት እንዲቀጣጠል አደረገ። ከሰገነቱ ዘወር በማለት ለፈተና ከሚያጋልጠው ሁኔታ መሸሽ ነበረበት። ከዚያ ይልቅ ስለ ሴትዬዋ ማለትም ስለ ቤርሳቤህ ማጠያየቅ ጀመረ። ይህም መጥፎ ውጤት አስከትሎበታል። (2 ሳሙኤል 11:​1–12:​23) በሌላው በኩል ደግሞ ዮሴፍ፣ በፆታ ስሜት ያበደችው የጌታው ሚስት አብሯት እንዲተኛ በጎተጎተችው ጊዜ ምን እርምጃ ወሰደ? ዘገባው “ይህንም ነገር በየዕለቱ ለዮሴፍ ትነግረው ነበር፤ እርሱም ከእርስዋ ጋር ይተኛ ዘንድ ከእርስዋም ጋር ይሆን ዘንድ አልሰማትም” በማለት ይነግረናል። ዮሴፍ የሙሴ ሕግ ሳይኖር እንኳ (ያኔ ገና አልተሰጠም ነበር) “እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ?” በማለት መልሶላታል። አንድ ቀን ልብሱን ተጠማጥማ ይዛ “ከእኔ ጋር ተኛ” አለችው። ዮሴፍ እዛው ቆይቶ ሁኔታውን ለማስረዳት ሙከራ አደረገ? በጭራሽ። “ሸሸ ወደ ውጭም ወጣ።” ዮሴፍ የፆታ ፈተና እንዲያሸንፈው ፈጽሞ ዕድል አልሰጠም። ከዚያ ይልቅ ሸሽቶ አመለጠ!​—⁠ዘፍጥረት 39:​7-16

11. አንድ ፈተና በተደጋጋሚ እየተቀሰቀሰ ቢያስቸግረን ምን ልናደርግ እንችላለን?

11 ሸሽቶ ማምለጥ አንዳንድ ጊዜ እንደ ፈሪነት ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል። ይሁን እንጂ ከአንድ ፈታኝ ከሆነ ሁኔታ ሸሽቶ መራቅ ብዙውን ጊዜ መወሰድ ያለበት የጥበብ እርምጃ ነው። ምናልባትም በሥራ ቦታ ተደጋጋሚ ፈተና ያጋጥመን ይሆናል። ሥራ መቀየር ባንችልም እንኳ ፈታኝ ከሆኑ ሁኔታዎች ዘወር ማለት የምንችልባቸው ሌሎች መንገዶች ሊኖሩ ይችላሉ። ስህተት እንደሆነ ከምናውቀው ከማንኛውም ነገር መሸሽ ይኖርብናል፤ እንዲሁም ትክክል የሆነውን ነገር ብቻ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን። (አሞጽ 5:​15) በሌላ ቦታ ደግሞ ከፈተና መሸሽ በኢንተርኔት አማካኝነት ወሲባዊ ሥዕሎችን ከመመልከትና አጠያያቂ ከሆኑ የመዝናኛ አካባቢዎች መራቅን የሚጠይቅ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም አንድን መጽሔት ማስወገድ ወይም አምላክን የሚወድዱና እኛን ለመርዳት የሚያስችል አቅም ያላቸውን አዳዲስ ወዳጆችን ማፍራት ማለት ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 13:​20) ኃጢአት እንድንፈጽም የሚገፋፋን ፈተና ምንም ይሁን ምን በቆራጥነት ከዚህ ፈተና ከሸሸን ጥበበኞች ነን።​—⁠ሮሜ 12:​9

ጸሎት የሚያስገኘው እርዳታ

12. “ወደ ፈተና አታግባን” ብለን ስንጸልይ አምላክን ምን ብለን መጠየቃችን ነው?

12 ጳውሎስ የሚከተለውን አበረታች ማረጋገጫ ሰጥቷል:- “ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፣ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።” (1 ቆሮንቶስ 10:​13) ይሖዋ እኛን የሚያግዝበት አንደኛው መንገድ ፈተናዎችን መቋቋም እንችል ዘንድ እንዲረዳን ለምናቀርበው ጸሎት መልስ በመስጠት ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ “ከክፉም አድነን እንጂ ወደ ፈተና አታግባን” ብለን እንድንጸልይ አስተምሮናል። (ማቴዎስ 6:​13) እንዲህ ዓይነት ልባዊ ጸሎት ካቀረብን ይሖዋ ፈተና ውስጥ እንድንገባ አይፈቅድም። ከሰይጣንና መሠሪ ከሆኑት ድርጊቶቹ ይጠብቀናል። (ኤፌሶን 6:​11የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) ፈተናዎችን ለይተን እንድናውቅ በማድረግና እነርሱን መቋቋም የሚያስችል ጥንካሬ በመስጠት እንዲረዳን አምላክን መጠየቅ ይኖርብናል። በምንፈተንበት ጊዜ በፈተናው እንወድቅ ዘንድ እንዳይፈቅድ ከተማጸንነው ‘በክፉው’ ማለትም በሰይጣን እንዳንሸነፍ ይረዳናል።

13. ቀጣይ የሆነ ፈተና በሚያጋጥመን ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

13 በተለይ ደግሞ ፈተናው በተደጋጋሚ ጊዜ የሚያስቸግረን ከሆነ አምርረን መጸለይ ይኖርብናል። አንዳንድ ፈተናዎች በውስጣችን ከፍተኛ ውጊያ ሊፈጥሩብን ይችላሉ። ከአስተሳሰባችንና ከዝንባሌያችን ጋር የሚደረገው እንዲህ ያለው ውጊያ ደግሞ ምን ያህል ደካማ እንደሆንን በሚገባ እንድናስተውል ያደርገናል። (መዝሙር 51:​5) ለምሳሌ ያህል የተውናቸው አንዳንድ መጥፎ ልማዶች ወደ አእምሯችን እየመጡ ቢያሠቃዩን ምን ማድረግ እንችላለን? ወደነዚህ ልማዶች እንድንመለስ ብንፈተንስ? እነዚህን ስሜቶች እንዲሁ አምቀን ለመያዝ ከመሞከር ይልቅ ጉዳዩን በጸሎት (አስፈላጊ ከሆነም በተደጋጋሚ) ለይሖዋ አቅርበው። (መዝሙር 55:​22) በቃሉና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አማካኝነት አእምሯችንን ርኩስ ከሆኑ ዝንባሌዎች እንድናጠራ ሊረዳን ይችላል።​—⁠መዝሙር 19:​8, 9

14. ፈተናን ለመቋቋም ጸሎት የግድ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

14 ኢየሱስ ሐዋርያቱ በጌቴሰማኒ የአትክልት ሥፍራ ዓይናቸው በእንቅልፍ ከብዶ በተመለከተ ጊዜ “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ፤ መንፈስ ተዘጋጅታለች ሥጋ ግን ደካማ ነው” በማለት አሳሰባቸው። (ማቴዎስ 26:​41) ፈተናን ማሸነፍ የሚቻልበት አንደኛው መንገድ ፈተና የሚመጣባቸውን የተለያዩ መንገዶችና የረቀቁ ዘዴዎች ማወቅና በንቃት በመከታተል ነው። ፈተናውን በብቃት መዋጋት እንችል ዘንድ ሳንዘገይ መጸለያችንም እጅግ አስፈላጊ ነው። ፈተና ደካማ ጎናችንን ለይቶ የሚያጠቃ በመሆኑ ብቻችንን ልንቋቋመው አንችልም። አምላክ የሚሰጠው ጥንካሬ የሰይጣንን ጥቃት ለመመከት የሚያስችለንን መከላከያ ስለሚደግፍልን ጸሎት የግድ አስፈላጊ ነው። (ፊልጵስዩስ 4:​6, 7) ‘የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች’ የሚሰጡት መንፈሳዊ እርዳታና ጸሎትም ሊያስፈልገን ይችላል።​—⁠ያዕቆብ 5:​13-18

ፈተናን በጽናት ተቋቋሙ

15. ፈተናን መቋቋም ምን ነገር ማድረግን ይጨምራል?

15 የሚቻል በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ ከፈተና ከመራቅ በተጨማሪ ፈተናው እስኪያልፍ ወይም ሁኔታው እስኪለወጥ ድረስ በጽናት መቋቋም ይገባናል። ኢየሱስ ሰይጣን በፈተነው ጊዜ ዲያብሎስ ትቶት እስኪሄድ ድረስ ተቃውሞታል። (ማቴዎስ 4:​1-11) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ዲያብሎስን . . . ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል” በማለት ጽፏል። (ያዕቆብ 4:​7) መቃወም የምንጀምረው አስተሳሰባችንን በአምላክ ቃል በመሙላትና ያወጣቸውን የአቋም ደረጃዎች ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ ነው። ከድካማችን ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውን ቁልፍ ጥቅሶች በማስታወስና በማሰላሰል ይህን ልናደርግ እንችላለን። የሚያሳስበንን ነገር የምናዋየውና መጥፎ ነገር እንድንፈጽም በምንፈተንበት ጊዜ የምናማክረው አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ምናልባትም አንድ ሽማግሌ ማግኘትም ጥበብ ነው።​—⁠ምሳሌ 22:​17

16. በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆነን መኖር የምንችለው እንዴት ነው?

16 ቅዱሳን ጽሑፎች አዲሱን ሰው እንድንለብስ አጥብቀው ያሳስቡናል። (ኤፌሶን 4:​24) ይህም ይሖዋ እንዲቀርጸንና እንዲለውጠን መፍቀድ ማለት ነው። ጳውሎስ ለሥራ ባልደረባው ለጢሞቴዎስ ሲጽፍ “ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል። መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፣ የተጠራህለትንም . . . የዘላለምን ሕይወት ያዝ” ብሎታል። (1 ጢሞቴዎስ 6:​11, 12) ስለ አምላክ ባሕርያት የጠለቀ እውቀት ለማግኘት የአምላክን ቃል በትጋት በማጥናት እንዲሁም ሕይወታችንንም ካወጣቸው የአቋም ደረጃዎች ጋር አስማምተን በመምራት ‘ጽድቅን መከታተል’ እንችላለን። ምሥራቹን መስበክና በስብሰባዎች መገኘትን በመሰሉ ክርስቲያናዊ እንቅስቃሴዎች የተሟላ ተሳትፎ ማድረግም እጅግ አስፈላጊ ነው። ወደ አምላክ መቅረብና ባደረጋቸው መንፈሳዊ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ መጠቀም በመንፈሳዊ እንድናድግና በሥነ ምግባር ንጹሕ ሆነን እንድንመላለስ ይረዳናል።​—⁠ያዕቆብ 4:​8

17. አምላክ ፈተና በሚገጥመን ጊዜ እንደማይተወን እንዴት እናውቃለን?

17 ምንም ዓይነት ፈተና ቢደርስብን አምላክ ፈተናውን መቋቋም እንችል ዘንድ ከሚሰጠን አቅም በላይ ሊሆን እንደማይችል ጳውሎስ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። ‘መጽናት እንችል ዘንድ’ ይሖዋ ‘መውጫውን ደግሞ ያደርግልናል።’ (1 ቆሮንቶስ 10:​13) በእርግጥም፣ አምላክ በእሱ ላይ መደገፋችንን ከቀጠልን በቂ መንፈሳዊ ጥንካሬ አጥተን ጽኑ አቋማችንን መጠበቅ እስኪሳነን ድረስ ፈተናው ከባድ እንዲሆንብን አይፈቅድም። በእርሱ ፊት መጥፎ የሆነውን ነገር እንድናደርግ የሚገፋፋንን ፈተና በብቃት እንድንቋቋም ይፈልጋል። ከዚህም በላይ “አልለቅህም ከቶም አልተውህም” በማለት በገባው ቃል ላይ እምነት ሊኖረን ይችላል።​—⁠ዕብራውያን 13:​5

18. ሰብዓዊ ድክመቶችን ልናሸንፍ እንደምንችል እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

18 ጳውሎስ ከሰብዓዊ ድካም ጋር የሚያደርገው ትግል ውጤት ምን እንደሚሆን ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። ሥጋዊ ፍላጎቶቹን መቆጣጠር እንደማይችል ምስኪን ሰው አድርጎ ራሱን አልቆጠረም። ከዚያ ይልቅ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፣ ነፋስን እንደሚጐስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም፤ ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጐሰምሁ አስገዛዋለሁ።” (1 ቆሮንቶስ 9:​26, 27) እኛም ፍጹም ባልሆነው ሥጋችን ላይ ጦርነት ልናውጅ እንችላለን። አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን በቅዱሳን ጽሑፎች፣ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና በጎለመሱ ክርስቲያን ባልንጀሮቻችን አማካኝነት ቀና በሆነው ጎዳና መጓዛችንን እንድንቀጥል ዘወትር ማሳሰቢያዎችን ይሰጠናል። ከእርሱ በምናገኘው እርዳታ ሰብዓዊ ድክመቶችን ልናሸንፍ እንችላለን!

ታስታውሳለህን?

• ‘ስለ ሥጋ ማሰብ’ ማለት ምን ማለት ነው?

• ራሳችንን ለፈተና ማዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?

• ፈተናን ለማሸነፍ ምን ልናደርግ እንችላለን?

• ፈተናን በማሸነፍ ረገድ ጸሎት ምን ሚና ይጫወታል?

• ሰብዓዊ ድክመቶችን ማሸነፍ እንደሚቻል እንዴት እናውቃለን?

[የጥናት እትም]

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መጽሐፍ ቅዱስ ምንም ነገር ማድረግ የማንችል የሥጋዊ ምኞቶቻችን ምርኮኞች እንደሆንን አድርጎ አያስተምርም

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከፈተና መሸሽ ከኃጢአት መራቅ የሚያስችል አንዱ መሠረታዊ ዘዴ ነው