በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከሁሉ የተሻለ የሥራ መስክ ይሆንልህ ይሆን?

ከሁሉ የተሻለ የሥራ መስክ ይሆንልህ ይሆን?

ከሁሉ የተሻለ የሥራ መስክ ይሆንልህ ይሆን?

የተጠመቅህ ክርስቲያን ከሆንክ ለአምላክ ያለህ ፍቅር ፈቃዱን እንድታደርግ እንደሚገፋፋህ ምንም ጥርጥር የለውም። ከዚህም በላይ አገልግሎት በጣም የምትወደው የሥራ መስክ እንደሚሆንልህ የታወቀ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስም ቢሆን ተከታዮቹ በሙሉ ደቀ መዛሙርት አድራጊ የመሆን ተልዕኮ ሰጥቷቸዋል። (ማቴዎስ 28:​19, 20) እርግጥ ነው፣ ራስህን ለመቻል ሰብዓዊ ሥራ ትሠራ ይሆናል። ይሁን እንጂ የኢየሱስ ተከታይና የይሖዋ ምሥክር እንደመሆንህ መጠን ለመንግሥቱ የስብከት ሥራ በሕይወትህ ውስጥ የመጀመሪያውን ቦታ የምትሰጥ ክርስቲያን አገልጋይ ነህ።​—⁠ማቴዎስ 24:​14

ምናልባት በአሥራዎቹ ዕድሜ መጨረሻ ወይም በ20ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ትገኝ ይሆናል። በሕይወትህ ስለምታከናውናቸው ነገሮች የተለያዩ ሐሳቦች ወደ አእምሮህ ይመጡ ይሆናል። ያሉህን አማራጮች በምትመዝንበት ጊዜ እርካታ ለሚያስገኝልህ ነገር ቅድሚያ እንደምትሰጥ የታወቀ ነው።

በዴንማርክ የሚኖረው ዮርን ስላደረገው ምርጫ ምን እንዳለ ተመልከት። ዮርን “ይበልጥ አስፈላጊ በሆነው ሥራ ላይ ለማተኮር የሚያስችል ተስማሚ የሕይወት መንገድ” በማለት ያደረገውን ምርጫ ገልጾታል። በግሪክ የምትኖረው የ31 ዓመቷ ኢቫ “ሕይወቴን እኩዮቼ ከሚመሩት ሕይወት ጋር ሳወዳድረው ይበልጥ ትርጉም ያለው፣ ስኬታማና ይበልጥ አስደሳች እንደሆነ እገነዘባለሁ” በማለት ተናግራለች። እንደዚህ ያለ እርካታ የሚያስገኘው የትኛው የሥራ መስክ ነው? እንዲህ ያለውን የሕይወት ጎዳና ልትከተል የምትችለው እንዴት ነው?

አምላክ መንገዱን ይጠቁምህ ይሆን?

የሥራ መስክ መምረጥ እንዲህ የዋዛ አይደለም። እንዲያውም አንዳንዶች አምላክ እንዲሠሩ የሚፈልገውን ነገር እንዲያመለክታቸው ይፈልጋሉ።

ሙሴ በምድያም ሳለ ይሖዋ ወደ ግብፅ እንዲመለስና እስራኤላውያንን ከባርነት ነፃ እንዲያወጣ አዞታል። (ዘጸአት 3:​1-10) የአምላክ መልአክ እስራኤልን ከጭቆና ነፃ እንዲያወጣ ለተሾመው ለጌዴዎን ተገልጦለታል። (መሳፍንት 6:​11-14) ሳሙኤል ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ አድርጎ ዳዊትን እንዲቀባው አምላክ ሲያዝዘው ዳዊት በግ ይጠብቅ ነበር። (1 ሳሙኤል 16:​1-13) ዛሬ እንደዚህ በመሰሉ መንገዶች መመሪያ አይሰጠንም። ከዚህ ይልቅ ሁኔታዎችን አመዛዝነን አምላክ የሰጠንን ችሎታዎች እንዴት እንደምንጠቀምባቸው መወሰን ይኖርብናል።

ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ላሉ ክርስቲያን ወጣቶች “ሥራ የሞላበት ትልቅ በር” ከፍቶላቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 16:​9) እንዴት? ባለፉት አሥርተ ዓመታት የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ቁጥር ከ2, 125, 000 በላይ ጭማሪ በማሳየት በመላው ምድር ከ6, 000, 000 በላይ ደርሷል። እነዚህን ሁሉ ሰዎች በመንፈሳዊ ለመመገብና በመላው ዓለም ለሚከናወነው የስብከት ሥራ አስፈላጊ የሆኑትን በሚልዮን የሚቆጠሩ መጽሐፍ ቅዱሶች፣ መጽሐፎች፣ ብሮሹሮች፣ መጽሔቶችና ትራክቶች ለማዘጋጀት እርዳታ የሚያበረክተው ማን ነው? በመላው ዓለም የሚገኙ የቤቴል ቤተሰብ አባላት ይህን የተባረከ መብት አግኝተዋል።

በረከት የሚያስገኝ ሕይወት

ቤቴል ማለት “የአምላክ ቤት” ማለት ሲሆን የቤቴል ቤቶች በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤትና በቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ በፈቃደኝነት የሚያገለግሉ ሠራተኞች የሚኖሩባቸው ቦታዎች ናቸው። (ዘፍጥረት 28:​19የአዲሲቱ ዓለም ትርጉም የግርጌ ማስታወሻ) በዘመናችን የሚገኙ የቤቴል ቤተሰቦች ‘በጥበብ ከተሠሩና’ ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር ላይ ከተመሠረቱ በሚገባ ከተደራጁ ‘ቤተሰቦች’ ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ።​—⁠ምሳሌ 24:​3

እንደ አንድ ቤተሰብ ስለሚኖሩት ስለ ቤቴል ቤተሰብ ምን ማለት ይቻላል? ኢስቶንያ በሚገኘው የቤቴል ቤተሰብ አባል የሆነች አንዲት የ25 ዓመት እህት እንዲህ ትላለች:- “የይሖዋ ወዳጅ ከሆኑ ሰዎች ጋር አብሬ እንደምኖር ማወቄ ሁልጊዜ ያስደስተኛል። አሁንም ሆነ ወደፊት ቤቴል በማገልገል አገኘሁት የምለው ውድ ነገር ይህ ነው።”​—⁠መዝሙር 15:​1, 2

በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ 19, 500 የሚያክሉ ሰዎች በቤቴል የማገልገል መብት አግኝተዋል። (መዝሙር 110:​3 NW ) ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው ቤቴል ከሚያገለግሉት መካከል 46 በመቶ የሚሆኑት ከ19 እስከ 29 የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ልክ እንደ ኢሳይያስ እነርሱም “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” ብለዋል። (ኢሳይያስ 6:​8) ራሱን ለይሖዋ የወሰነው ኢሳይያስ በዚህ ጊዜ ለተጨማሪ የአገልግሎት መብት ራሱን በፈቃደኝነት ማቅረቡ ነበር። ይህ ደግሞ አንዳንድ የግል ጥቅሞችን መሥዋዕት ማድረግን የሚጠይቅ ነው። በቤቴል እያገለገሉ ያሉ ሰዎች ቤታቸውንና ያደጉበትን አካባቢ እንዲሁም እናቶቻቸውን፣ አባቶቻቸውን፣ ወንድሞቻቸውን፣ እህቶታቸውንና ጓደኞቻቸውን ትተዋል። “ስለ ወንጌል” ብለው ይህን መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኞች ሆነዋል።​—⁠ማርቆስ 10:​29, 30

በምትኩ በቤቴል እንዴት ያለ መንፈሳዊ በረከቶችን አግኝተዋል! በሩሲያ የቤቴል ቤተሰብ አባል የሆነች አንዲት ወጣት “የራስን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ በአዲሱ ዓለም ለምንመራው ሕይወት የሚጠቅሙ ብዙ ነገሮችን እንማራለን። በበኩሌ ከይሖዋ የማገኘው በረከት ከከፈልኳቸው መሥዋዕቶች እጅግ የላቀ ነው ለማለት እችላለሁ” ስትል ተናግራለች።​—⁠ሚልክያስ 3:​10

የቤቴል ሕይወት

የቤቴል ሕይወት ምን ይመስላል? የቤቴል ሕይወት በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድርና አርኪ አልፎ ተርፎም አስደሳች መሆኑን የቤቴል ቤተሰብ አባላት ይስማማሉ። የ43 ዓመቱ የንስ ቤቴል በሚያከናውነው አገልግሎት ይደሰታል። ለምን? “በጣም አስፈላጊ የሆነ አንድ ተግባር ዳር ለማድረስ ቀና ደፋ ከሚሉ ሰዎች መካከል እንዳለሁ ሆኖ ስለሚሰማኝ ነው። የይሖዋ ሥራ እስከ ምን ድረስ እየተሠራ እንዳለና ምን ያክል ጠቃሚ እንደሆነ ለመረዳት ችያለሁ” በማለት ተናግሯል።

በቤቴል ከሰኞ እስከ ቅዳሜ ያሉት ቀናት የሚጀምሩት በማለዳ አምልኮ ነው። ይህ ተሞክሮ ባለው ሽማግሌ የሚመራ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ውይይት ነው። በየሳምንቱ ሰኞ ማታ በመጠበቂያ ግንብ አማካኝነት አንድ ሰዓት የሚፈጅ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚደረግ ሲሆን አልፎ አልፎ ደግሞ በተለይ ለቤቴል ቤተሰብ ተስማሚ ሆነው የተዘጋጁ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረቱ ንግግሮች ከጥናቱ በኋላ ይቀርባሉ።

አንድ ሰው ወደ ቤቴል ሲመጣ በመጀመሪያ የሚያደርገው ነገር ምንድን ነው? አዲስ አባላትን ከቤቴል ሕይወት ጋር ለማስተዋወቅ በቤቴል የሚገኙ የጎለመሱ ወንድሞች የቤቴል አገልግሎትን የሚመለከቱ የተለያዩ ንግግሮች ያቀርቡላቸዋል። በመጀመሪያው ዓመት በርከት ላሉ ሣምንታት አንድ አዲስ የቤቴል ቤተሰብ አባል ቅዱሳን ጽሑፎችን የመረዳት ችሎታውን ማስፋት ይችል ዘንድ በየሣምንቱ በሚካሄድ ግሩም ሆኖ በተዘጋጀ ትምህርት ቤት ይካፈላል። አዲስ የቤቴል ቤተሰብ አባላት ልዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም ይኖራቸዋል። በመጀመሪያው ዓመት የቤቴል አገልግሎታቸው ወቅት መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር አንብበው ይጨርሳሉ።

የዚህ ሁሉ ሥልጠና ዓላማ ምንድን ነው? በሆንግ ኮንግ የቤቴል ቤተሰብ አባል የሆነው የ33 ዓመቱ ጃሽዋ እንዲህ በማለት መልስ ሰጥቷል:- “ቤቴል ለይሖዋ ያለኝን አድናቆት በጥልቅ ጨምሮልኛል። አብዛኛውን የዕድሜያቸውን ክፍል ይሖዋን በማገልገል ካሳለፉ ተሞክሮ ካካበቱ ከብዙ ወንድሞች ጋር ወዳጅነት መመሥረት እችላለሁ። በተለይ ደግሞ በማለዳ አምልኮና በቤተሰብ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት በመሳሰሉ መንፈሳዊ ፕሮግራሞች ላይ እገኛለሁ። ከዚህም በተጨማሪ ሥርዓታማና ቀላል የሆነው የቤቴል ሕይወት ያስደስተኛል። ይህም አስፈላጊ ካልሆነ ጭንቀት ገላግሎኛል። እንዲሁም አንዳንድ ችግሮችን ክርስቲያናዊ በሆነ መንገድ እንዴት መፍታት እንደሚቻል የተማርኩ ሲሆን ይህም ሁልጊዜ ጠቃሚ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።”

የቤቴል ቤተሰብ አባላት አብዛኛውን ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን በፈቃደኛነት ራሳቸውን ያቀረቡበትን ሥራ ለመሥራት ያውላሉ። ይህም ጉልበታቸውንና እውቀታቸውን በአንደኛ ደረጃ በቤቴል የተሰጣቸውን ሥራ ለማከናወን ይጠቀሙበታል ማለት ነው። የሚሠሩ የተለያዩ ዓይነት ሥራዎች አሉ። አንዳንዶች ለተለያዩ ጉባኤዎች የሚላኩ መጻሕፍት ለማዘጋጀት በማተሚያ ማሽኖች ላይ ወይም በመጠረዣ ክፍል ውስጥ ይሠራሉ። ሌሎች ደግሞ በወጥ ቤት፣ በመመገቢያ ክፍል ወይም በልብስ ንጽሕና ክፍል ያገለግላሉ። የጽዳት፣ የግብርና፣ የግንባታና የመሳሰሉ ሥራዎችም አሉ። አንዳንዶች በእነዚህ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ መሣሪያዎችን የመጠገን ኃላፊነት አላቸው። ሌሎች ደግሞ የጤና አገልግሎት ይሰጣሉ ወይም ቢሮ ውስጥ ይሠራሉ። በቤቴል ውስጥ የሚከናወን ማንኛውም ሥራ ትጋት ማሳየትን የሚጠይቅ ቢሆንም የሚክስ ነው። በቤቴል የሚከናወነው ሥራ የመንግሥቱን ጥቅሞች የሚያራምድና አምላክን ከማፍቀር የሚመነጭ በመሆኑ ልዩ እርካታ ያስገኛል።

የቤቴል ቤተሰብ አባላት የሥራቸውን ፍሬ ወደሚቀምሱባቸው ወደ ተለያዩ ጉባኤዎች ይመደባሉ። ጉባኤው በሚያደርጋቸው ስብሰባዎች ላይ የሚገኙ ሲሆን በስብከቱ ሥራም ይካፈላሉ። በዚህ መንገድም የቤቴል ቤተሰብ አባላት በጉባኤዎቻቸው ውስጥ ካሉ ወንድሞችና እህቶች ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ይመሠርታሉ።​—⁠ማርቆስ 10:​29, 30

በብሪታንያ የቤቴል ቤተሰብ አባል የሆነችው ካንቢ “ለጉባኤው ከፍ ያለ አድናቆት አለኝ! በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስገኝና በአገልግሎት ስካፈል ተወዳጅ ወንድሞችን፣ እህቶችን፣ ልጆችን እንዲሁም በዕድሜ የገፉ አረጋውያንን ስለማገኝ እምነቴ ይጠናከራል! ምንም ነገር ቢያጋጥማቸው ፈጽሞ አይቀሩም። ይህ ደግሞ በቤቴል አገልግሎት በቅንዓት እንድካፈል ረድቶኛል።”

የቤቴል ሕይወት እንዲያው ሁልጊዜ በሥራ፣ በስብሰባ፣ በመስክ አገልግሎትና በጥናት ብቻ የተወሰነ አይደለም። ቤተሰቡ የሚዝናናባቸውም ጊዜያት አሉት። አልፎ አልፎ አዝናኝና በመንፈሳዊ የሚያድሱ “የቤተሰብ ምሽት” ፕሮግራሞች የሚዘጋጁ ሲሆን በዚህ ፕሮግራም ላይ ብዙዎች ያላቸውን ተሰጥኦ ለማየትና በቤቴል የሚያገለግሉ ሌሎች ሰዎች ካሳለፏቸው የሕይወት ተሞክሮዎች የሚያበረታቱ ነገሮችን ለመቅሰም አጋጣሚ ይሰጣል። ሌላው አስደሳች ነገር ደግሞ እርስ በርስ የሚደረገው ጤናማና ገንቢ የሆነ ማኅበራዊ ጥየቃ ነው። አንዳንድ የመዝናኛ ዓይነቶችም ያሉ ሲሆን ለግል ንባብና ምርምር ለማድረግ የሚረዱ ቤተ መጻሕፍት ተደራጅተዋል። በገበታ ላይ የሚደረገው አስደሳች ጭውውትም ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም።

በኢስቶንያ የቤቴል ቤተሰብ አባል የሆነው ቶም “ከቤቴል ትንሽ እልፍ ብሎ ባለው ባሕር አጠገብ አንድ የሚያምር ደን ያለ ሲሆን እኔና ባለቤቴ እዚያ እየሄድን እንሸራሸራለን። አልፎ አልፎ ከጉባኤና ከቤቴል ጓደኞቼ ጋር ሆኜ ጎልፍ፣ ሆኪ እንዲሁም ቴኒስ እጫወታለሁ። ጥሩ የአየር ሁኔታ በሚኖርበት ጊዜ በብስክሌት ራቅ ያለ ቦታ ደርሰን እንመለሳለን” ብሏል።

ብቃቱን ለማሟላት ምን ልታደርግ ትችላለህ?

እርግጥ ነው፣ ቤቴል በአንደኛ ደረጃ የጎለመሱ ክርስቲያኖች ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት የሚያቀርቡበትና በመላው ዓለም ለሚገኙ የእምነት አጋሮቻቸው የሚሠሩበት ቦታ ነው። የቤቴል ቤተሰብ አባላት ሊያሟሏቸው የሚገቡ አንዳንድ ብቃቶች አሉ። ለቤቴል አገልግሎት ብቁ ለመሆን ምን ልታደርግ ትችላለህ?

ተቀባይነት አግኝተው በቤቴል ለማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር ያገለግል እንደነበረው እንደ ጢሞቴዎስ በጉባኤያቸው ጥሩ አቋም ሊኖራቸው ይገባል። (1 ጢሞቴዎስ 1:​1, 2) ጢሞቴዎስ ‘በልስጥራንና በኢቆንዮን ያሉ ወንድሞች በመልካም መስክረውለታል።’ (ሥራ 16:​2) ጢሞቴዎስ በዕድሜ ትንሽ ቢሆንም የቅዱሳን ጽሑፎች እውቀት የነበረው ሲሆን በእውነት ውስጥም ጠንካራ መሠረት ነበረው። (2 ጢሞቴዎስ 3:​14, 15) በተመሳሳይም ለቤቴል አገልግሎት ተቀባይነት ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንዲኖራቸው ያስፈልጋል።

የቤቴል ቤተሰብ አባላት የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ሊኖራቸው ይገባል። ጢሞቴዎስ ከራሱ ይልቅ የመንግሥቱን ፍላጎቶች የማስቀደም ፍላጎትና የራሱን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ስለነበረው ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ ሊጽፍለት ችሏል:- “እንደ እርሱ ያለ፣ ስለ ኑሮአችሁ በቅንነት የሚጨነቅ፣ ማንም የለኝምና፤ ሁሉ የራሳቸውን ይፈልጋሉና፣ የክርስቶስ ኢየሱስን አይደለም። ነገር ግን ልጅ ለአባቱ እንደሚያገለግል ከእኔ ጋር ሆኖ ለወንጌል እንደ አገለገለ መፈተኑን ታውቃላችሁ።”​—⁠ፊልጵስዩስ 2:​20-22

የቤቴል አገልግሎት መንፈሳዊ የሆኑ ወንዶችንና ሴቶችን የሚጠይቅ ነው። ለቤቴል ቤተሰብ አባላት የተደረገው ዝግጅት በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎችና በመስክ አገልግሎት ላይ ዘወትር በመገኘት እንዲሁም ከጎለመሱ ክርስቲያኖች ጋር አብሮ በመሰብሰብ በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ያስችላቸዋል። ስለሆነም በቤቴል የሚሠሩ ሰዎች ጳውሎስ “እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ፤ ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ፣ እንደ ተማራችሁም በሃይማኖት ጽኑ፣ ምስጋናም ይብዛላችሁ” በማለት የሰጠውን ምክር እንዲከተሉ ይረዳቸዋል።​—⁠ቆላስይስ 2:​6, 7

በቤቴል በሚከናወነው የሥራ ጠባይ ምክንያት ለዚህ የአገልግሎት መብት ተቀባይነት ያገኙ ሁሉ አካላዊ ጥንካሬና ጥሩ ጤንነት ያላቸው መሆን አለባቸው። እስከ አሁን የጠቀስናቸውን ብቃቶች የምታሟላ ከሆነና ዕድሜህ 19 ወይም ከዚያ በላይ ከሆነ እንዲሁም ከተጠመቅህ ቢያንስ አንድ ዓመት የሞላህ ከሆንክ የቤቴልን አገልግሎት እንድታስብበት እናበረታታሃለን።

ሁላችንም ድርሻ አለን

ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ሁላችንም በሕይወታችን ውስጥ ለመንግሥቱ ጉዳዮች የመጀመሪያውን ቦታ መስጠትና ለይሖዋ የምናቀርበውን አገልግሎት በሙሉ ነፍስ ማከናወን እንደምንፈልግ የታወቀ ነው። (ማቴዎስ 6:​33፤ ቆላስይስ 3:​23) በቤቴል በማገልገል ላይ የሚገኙትን ቅዱስ አገልግሎታቸውን እዚያው ማቅረባቸውን እንዲቀጥሉ ልናበረታታቸው እንችላለን። በተለይ ደግሞ ለቤቴል አገልግሎት ብቃቱ ያላቸው ወጣት ወንድሞች እዚህ ልዩ መብት ላይ ለመድረስ እንዲጣጣሩ ማበረታቻ ሊሰጣቸው ይገባል።

የቤቴል አገልግሎት በእርግጥም ከሁሉ የተሻለ የሥራ መስክና በመንፈሳዊ የሚያረካ የሕይወት መንገድ ነው። ከ20 ዓመቱ አንስቶ በቤቴል ማገልገል ለጀመረው ለኒክ እንደዚያ ሆኖለታል። በቤቴል አሥር ዓመት ካገለገለ በኋላ “ይገባኛል ለማልለው ደግነቱ ይሖዋን ሁልጊዜ በጸሎት አመሰግነዋለሁ። ከዚህ የበለጠ ምን ልጠይቀው እችላለሁ? እዚህ ይሖዋን ለማገልገል የአቅማቸውን ያክል በሚጥሩ ታማኝ ክርስቲያኖች መካከል እንኖራለን” በማለት ተናግሯል።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሽማግሌዎችና ወላጆች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

ሽማግሌዎችና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ለቤቴል እንዲያመለክቱ በተለይ ወጣት ወንዶችን ማበረታታት ይገባቸዋል። በቅርቡ መደበኛ ባልሆነ መንገድ በወጣት የቤቴል ቤተሰብ አባላት ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳመለከተው 34 በመቶ የሚሆኑት የቤቴል አገልግሎትን ግብ እንዲያደርጉ በአንደኛ ደረጃ ማበረታቻ የሰጧቸው ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ናቸው። ጉባኤዎቻቸው እነርሱን በማጣታቸው ቅር ይሰኙ ይሆናል። ጢሞቴዎስ በልስጥራንና በኢቆንዮን በሚኖሩ ሌሎች ወጣቶች ላይ በጎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ሽማግሌዎች የሚያውቁ ቢሆንም ከጳውሎስ ጋር ከማገልገል ወደኋላ እንዲል እንዳላደረጉት ማስታወሱ ጥሩ ነው። ጢሞቴዎስ ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር መሄዱ ጉባኤውን ከፍተኛ ጉዳት ላይ ይጥለዋል የሚል መደምደሚያ ላይ አልደረሱም።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:​14

በተለይ ክርስቲያን ወላጆች በዚህ ረገድ በልጆቻቸው ላይ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ መሆን አለባቸው። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጥናት እንዳመለከተው ጥያቄ ከቀረበላቸው መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት የቤቴል አገልግሎትን ግብ እንዲያደርጉ በዋነኛነት ያበረታቷቸው ወላጆቻቸው እንደሆኑ ተናግረዋል። ለጥቂት ዓመታት ቤቴል ያገለገለች አንዲት እህት “ወላጆቼ ይሖዋን በማገልገል ያሳለፉት የሕይወት ተሞክሮ ቤቴል እንድገባ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያሳዩትን ምሳሌነት መመልከቴ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከሁሉ የተሻለና ይበልጥ አርኪ የሆነ የሥራ መስክ እንደሆነ አስገንዝቦኛል” ብላለች።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የቤቴል አገልግሎታቸውን እንደ ውድ ነገር ይመለከቱታል

“በቤቴል የማደርገውን አገልግሎት እንደ ውድ ነገር እመለከተዋለሁ። ቀኑን ሙሉ ይሖዋን እንደማገለግልና ነገም ከነገ ወዲያም ወደፊትም እንዲሁ ማድረጌን እንደምቀጥል መገንዘቤ እርካታ ይሰጠኛል። ይህም በጎ ህሊና እንዲኖረኝ ከማድረጉም በላይ ከተለያዩ አፍራሽ ስሜቶች ይገላግለኛል።”

“ቤቴል ሐሳብህ ሳይከፋፈል ሙሉ ጊዜህንና ጉልበትህን ለይሖዋ አገልግሎት የምታውልበት ቦታ ነው። ይህ ውስጣዊ ደስታ ያስገኛል። እንዲሁም የይሖዋን ድርጅት ከተለያየ አቅጣጫ የማየት አጋጣሚ ያስገኝልሃል። ወደ ድርጅቱ የእንቅስቃሴ ማዕከል ይበልጥ እንደተጠጋህ የሚሰማህ ሲሆን ይህም ይበልጥ ደስተኛ ያደርግሃል።”

“የቤቴል አገልግሎት አቻ የማላገኝለት ከሁሉ የተሻለ ቦታ ነው። እዚህ የምታገኘው ትምህርት ማብቂያ የለውም። እንዲሁም እዚህ የሚገኘው ትምህርት የራስን ፍላጎት ለማሳካት ሳይሆን ይሖዋን ለማገልገል ነው። እዚህ ድካሜ ፈጽሞ ከንቱ አይሆንም።”

“በቤቴል ተሰጥኦዎቼን መጠቀሜ ይሖዋን ለማገልገልና ወንድሞቼን ለመጥቀም እየተጠቀምኩባቸው እንዳለሁ ስለሚሰማኝ የእርካታና የሰላም ስሜት ይሰጠኛል።”

“ቤቴል ከመግባቴ በፊት በነበረኝ ሥራ እውነተኛ እርካታና ደስታ አላገኘሁበትም። ቤቴል ከሚገኙ ወንድሞችና እህቶች ጋር በመሥራት ወንድሞቼንና እህቶቼን የማገለግልበትን ጊዜ ለብዙ ዓመታት ስናፍቅ ቆይቻለሁ። ቤቴል የገባሁትም ለዚሁ ነው። ጥረቴ ሌሎችን በመንፈሳዊ እንደሚጠቅምና ይሖዋን እንደሚያስከብር ስለማውቅ እውነተኛ እርካታ አግኝቻለሁ።”