በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ጌታ በእውነት ተነሥቶአል”

“ጌታ በእውነት ተነሥቶአል”

“ጌታ በእውነት ተነሥቶአል”

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ጌታቸው በተገደለ ጊዜ ምን ያህል በሐዘን ተውጠው እንደነበር ገምት። ተስፋቸው ሁሉ የአርማትያሱ ዮሴፍ በመቃብር ውስጥ እንዳስቀመጠው አስከሬን በድን ሆኖ ነበር። ኢየሱስ የአይሁድን ሕዝብ ከሮም ቀንበር ነፃ ያወጣል የሚለው ተስፋቸው ሁሉ እንደ ጉም በኖ ጠፍቷል።

ሁሉም ነገር በዚህ አክትሞ ቢሆን ኖሮ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደ ብዙዎቹ መሲሕ ነን ባይ ተከታዮች ጠፍተው በቀሩ ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ሕያው ሆኗል! ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚናገሩት ሞቶ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በተለያዩ ወቅቶች ለተከታዮቹ ተገልጧል። በመሆኑም አንዳንዶቹ “ጌታ በእውነት ተነሥቶአል” ብለው ለመናገር ተገፋፍተዋል።​—⁠ሉቃስ 24:​34

ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስን እንደ መሲሕ አድርገው ያምኑበት ስለነበር ለዚህ እምነታቸው መከላከያ ማቅረብ ነበረባቸው። ከሞት መነሳቱንም መሲሕ ለመሆኑ እንደ ጠንካራ ማስረጃ አድርገው ያቀርባሉ። በእርግጥም፣ ‘ሐዋርያት የጌታን የኢየሱስ ክርስቶስን ትንሣኤ በታላቅ ኃይል ይመሰክሩ ነበር።’​—⁠ሥራ 4:​33

አንድ ሰው የኢየሱስ ትንሣኤ ሐሰት መሆኑን ለአንዱ ደቀ መዝሙር ማሳመን ችሎ ቢሆን ወይም የኢየሱስ ሥጋ በመቃብር ውስጥ እንደቀረ በማሳየት አረጋግጦ ቢሆን ኖሮ ክርስትና ገና ከጅምሩ በአጭሩ ተቀጭቶ በቀረ ነበር። ይሁን እንጂ አልተቀጨም። የኢየሱስ ተከታዮች ክርስቶስ ሕያው እንደሆነ ያውቁ ስለነበር ወደተለያዩ ቦታዎች ሄደው ትንሣኤውን ያወጁ ሲሆን እጅግ ብዙ ሰዎችም ከሞት በተነሳው በክርስቶስ አምነዋል።

አንተም በኢየሱስ ትንሣኤ ማመን የምትችለው ለምንድን ነው? ይህ ትክክለኛ ክንውን እንደሆነ የሚያረጋግጥ ምን ማስረጃ አለ?

ማስረጃውን መመርመር ያስፈለገው ለምንድን ነው?

አራቱም የወንጌል ዘገባዎች ስለ ኢየሱስ ትንሣኤ ይናገራሉ። (ማቴዎስ 28:​1-10፤ ማርቆስ 16:​1-8፤ ሉቃስ 24:​1-12፤ ዮሐንስ 20:​1-29) a ሌሎች የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ክርስቶስ ከሙታን መነሳቱን በእርግጠኝነት ይናገራሉ።

የኢየሱስ ተከታዮች ስለ ትንሣኤው ማወጃቸው ምንም አያስደንቅም! በእርግጥ አምላክ ከሞት አስነስቶት ከነበረ ይህ በዓለም ከተሰማው ዜና ሁሉ አቻ የማይገኝለት ዜና ነው። ይህም አምላክ አለ ማለት ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ኢየሱስ አሁን በሕይወት አለ ማለት ነው።

ይህ እኛን የሚነካን እንዴት ነው? ኢየሱስ፣ “እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት” በማለት ጸልዮአል። (ዮሐንስ 17:​3) አዎን፣ ሕይወት የሚያሰጠውን ስለ ኢየሱስና ስለ አባቱ የሚናገረውን እውቀት ልናገኝ እንችላለን። ይህን እውቀት ተግባራዊ ካደረግን ብንሞት እንኳ ኢየሱስ ትንሣኤ እንዳገኘ ሁሉ እኛም ትንሣኤ ልናገኝ እንችላለን። (ዮሐንስ 5:​28, 29) የነገሥታት ንጉሥ በሆነው ክብር በተጎናጸፈው ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በሚገዛው በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ሥር በምትተዳደረው ምድራዊ ገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ሊኖረን ይችላል።​—⁠ኢሳይያስ 9:​6, 7፤ ሉቃስ 23:​43፤ ራእይ 17:​14

ስለዚህ ኢየሱስ በእርግጥ ከሞት ተነስቷል ወይስ አልተነሳም የሚለው ጥያቄ በጣም አንገብጋቢ ነው። የአሁኑን ሕይወታችንንም ሆነ የወደፊት ተስፋችንን ይነካል። ኢየሱስ እንደሞተና እንደተነሳ የሚያረጋግጡ አራት ማስረጃዎችን እንድትመረምር የምንጋብዝህም ለዚህ ነው።

ኢየሱስ በተሰቀለበት እንጨት ላይ በእርግጥ ሞቷል

አንዳንድ ተጠራጣሪዎች ኢየሱስ መሰቀሉ እውነት ቢሆንም በተሰቀለበት እንጨት ላይ እንዳለ አልሞተም ይላሉ። ሊሞት ተቃርቦ የነበረ ይሁን እንጂ የመቃብሩ ቅዝቃዜ ነፍስ እንዲዘራ አድርጎታል የሚል አመለካከት አላቸው። ሆኖም መቃብር ውስጥ የተቀመጠው የኢየሱስ በድን አስከሬን መሆኑን የተገኙት ማስረጃዎች በሙሉ ያረጋግጣሉ።

ኢየሱስ የተገደለው በአደባባይ እንደመሆኑ መጠን በተሰቀለበት እንጨት ላይ እንዳለ መሞቱን የሚያረጋግጡ ምሥክሮች አሉ። ከገዳዮቹ አንዱ የሆነው የጦር መኮንን ኢየሱስ እንደሞተ አረጋግጧል። የዚህ የጦር መኮንን አንዱ ሥራ ኢየሱስ መሞቱን ማረጋገጥ ነበር። ከዚህም በላይ የሮማው ገዥ ጴንጤናዊው ጲላጦስ የአርማትያሱ ዮሴፍ የኢየሱስን አስከሬን እንዲወስድ የሚፈቅድለት ኢየሱስ መሞቱን ካረጋገጠ በኋላ ብቻ ነው።​—⁠ማርቆስ 15:​39-46

መቃብሩ ባዶ ሆኖ ተገኘ

መቃብሩ ባዶ ሆኖ መገኘቱ ኢየሱስ ትንሣኤ እንዳገኘ የሚያረጋግጥ ለደቀ መዛሙርቱ የመጀመሪያ ማስረጃ ሲሆን ይህም እስከ አሁን ድረስ ሊታበል የማይችል ሃቅ ነው። ኢየሱስ የተቀበረው ማንም ባልተቀበረበት አዲስ መቃብር ውስጥ ነበር። መቃብሩ በተሰቀለበት አካባቢ የሚገኝ በመሆኑ ከተቀበረ በኋላ ማንም ሰው በቀላሉ ሊያገኘው የሚችልበት ቦታ ነበር። (ዮሐንስ 19:​41, 42) ኢየሱስ ከሞተ በኋላ በሁለተኛው ቀን ጠዋት ላይ የኢየሱስ ወዳጆች ወደ መቃብሩ በሄዱ ጊዜ በድኑን እንዳላገኙ ሁሉም የወንጌል ዘገባዎች ይናገራሉ።​—⁠ማቴዎስ 28:​1-7፤ ማርቆስ 16:​1-7፤ ሉቃስ 24:​1-3፤ ዮሐንስ 20:​1-10

የኢየሱስ ወዳጆች መቃብሩን ባዶ ሆኖ በማግኘታቸው እንደተደነቁ ሁሉ ጠላቶቹም ተገርመዋል። ጠላቶቹ እርሱን ለመግደልና ለመቅበር ለረዥም ጊዜ ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ግባቸውን ዳር ካደረሱ በኋላም ጠባቂ አቁመው መቃብሩን አትመውበት ነበር። የሆነ ሆኖ በሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ጠዋት ላይ መቃብሩ ባዶ ሆኖ ተገኝቷል።

የኢየሱስ ወዳጆች በድኑን ከመቃብሩ ውስጥ አውጥተው ወስደውት ይሆን? ወንጌሎች እንደሚያሳዩት ከእርሱ ሞት በኋላ በከፍተኛ ሐዘን ተውጠው ስለነበር እንዲህ ሊያደርጉ ይችላሉ ብሎ መገመት አስቸጋሪ ነው። ከዚህም በላይ ደቀ መዛሙርቱ ሐሰት እንደሆነ ለሚያውቁት ነገር ስደትና ሞት ለመቀበል ፈቃደኛ ይሆናሉ ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው።

ታዲያ በድኑን ማን ወሰደው? የኢየሱስ ጠላቶች ወስደውት ይሆናል ብሎ መገመት መቼም አስቸጋሪ ነው። ወስደውት እንኳን ቢሆን ኢየሱስ ትንሣኤ እንዳገኘና ሕያው እንደሆነ የሚናገሩትን የደቀ መዛሙርቱን አፍ ለማዘጋት ሲሉ ከጊዜ በኋላ ለእይታ እንደሚያቀርቡት ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ድርጊቱን የፈጸመው አምላክ ስለሆነ እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አልተከሰተም።

ሳምንታት ካለፉ በኋላ የኢየሱስ ጠላቶች ጴጥሮስ እንደሚከተለው በማለት የሰጠውን ምሥክርነት ፈጽሞ ሊቃወሙ አልቻሉም:- “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፣ ይህን ቃል ስሙ፤ ራሳችሁ እንደምታውቁ፣ የናዝሬቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመካከላችሁ በእርሱ በኩል ባደረገው ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ፤ እርሱንም በእግዚአብሔር በተወሰነው አሳቡና በቀደመው እውቀቱ ተሰጥቶ በዓመፀኞች እጅ ሰቅላችሁ ገደላችሁት። እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው፣ ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና። ዳዊት ስለ እርሱ እንዲህ ይላልና:- ጌታን ሁልጊዜ በፊቴ አየሁት፣ እንዳልታወክ በቀኜ ነውና። ስለዚህ ልቤን ደስ አለው፣ ልሳኔም ሐሤት አደረገ፣ ደግሞም ሥጋዬ በተስፋ ያድራል፤ ነፍሴን በሲኦል አትተዋትምና፣ ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትሰጠውም።”​—⁠ሥራ 2:​22-27

ትንሣኤ ያገኘውን ኢየሱስን በርካታ ሰዎች አይተውታል

የወንጌል ጸሐፊው ሉቃስ በሐዋርያት መጽሐፍ ላይ እንዲህ ብሏል:- “ደግሞ አርባ ቀን እየታያቸው ስለ እግዚአብሔርም መንግሥት ነገር እየነገራቸው፣ በብዙ ማስረጃ ከሕማማቱ በኋላ ሕያው ሆኖ ለእነርሱ [ለሐዋርያቱ] ራሱን [ኢየሱስ] አሳያቸው።” (ሥራ 1:​2, 3) በርካታ ደቀ መዛሙርት ትንሣኤ ያገኘውን ኢየሱስን በተለያዩ ወቅቶች በአትክልት ቦታ፣ ምግብ እየተመገቡ ሳለ፣ በጥብርያዶስ ባሕር አቅራቢያ አይተውታል።​—⁠ማቴዎስ 28:​8-10፤ ሉቃስ 24:​13-43፤ ዮሐንስ 21:​1-23

ተቺዎች ኢየሱስ እንደታየ በሚገልጹት በእነዚህ ዘገባዎች ትክክለኛነት ላይ ጥያቄ ያስነሳሉ። ጸሐፊዎቹ ፈጥረው የጻፏቸው ዘገባዎች ናቸው በማለት ይናገራሉ፤ አሊያም እርስ በርስ የሚጋጩ የሚመስሉ ዘገባዎችን ይጠቅሳሉ። እንዲያውም በወንጌል ዘገባዎች ውስጥ የሚገኙት ጥቃቅን ልዩነቶች ምንም ዓይነት አሻጥር እንዳልተካሄደ የሚያረጋግጡ ናቸው። አንድ ጸሐፊ የክርስቶስን ምድራዊ ሕይወት በማስመልከት በሌላ ቦታ ሰፍሮ የሚገኘውን ተመሳሳይ ታሪክ የሚያሟላ ተጨማሪ ዝርዝር ማስፈሩ ስለ ኢየሱስ ያለንን ግንዛቤ እንድናሰፋ ያስችለናል።

ከትንሣኤው በኋላ የታየው ኢየሱስ በእውን የታየ ነው ወይም እንዲሁ ቅዠት ነው? በጣም በርካታ ሰዎች ኢየሱስን ያዩት በመሆናቸው እንዲህ ያለው የመከራከሪያ ሐሳብ ተዓማኒነት አይኖረውም። ከእነዚህ መካከል ዓሣ አጥማጆች፣ ሴቶች፣ አንድ የመንግሥት ሠራተኛና ሌላው ቀርቶ ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ የሚያረጋግጥ የማያሻማ ማስረጃ ከተመለከተ በኋላ ያመነው ተጠራጣሪው ቶማስ ይገኙበታል። (ዮሐንስ 20:​24-29) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በተደጋጋሚ ጊዜ ትንሣኤ ያገኘውን ጌታቸውን እንደተመለከቱት ወዲያው አላወቁትም ነበር። በአንድ ጊዜ ከ500 የሚበልጡ ሰዎች የተመለከቱት ሲሆን ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን ወቅት እንደ ማስረጃ አድርጎ በማቅረብ ትንሣኤን በማስመልከት የመከላከያ ሐሳብ ባቀረበ ጊዜ ብዙዎቹ በሕይወት ነበሩ።​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​6

ሕያው የሆነው ኢየሱስ በሰዎች ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል

የኢየሱስ ትንሣኤ እንዲያው የማወቅ ጉጉት የሚቀሰቅስ ወይም ትኩረት የሚስብ የመከራከሪያ ነጥብ እንደሆነ ተደርጎ መታየት አይኖርበትም። ኢየሱስ ሕያው መሆኑ በየትኛውም ቦታ በሚኖሩ ሰዎች ሕይወት ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል። ከመጀመሪያው መቶ ዘመን አንስቶ ግድ የለሽ የነበሩ ወይም ክርስትናን በጥብቅ ይቃወሙ የነበሩ በርካታ ሰዎች ተለውጠው ይህ እውነተኛ ሃይማኖት መሆኑን አምነው ተቀብለዋል። እንዲለወጡ ያደረጋቸው ምንድን ነው? አምላክ ኢየሱስን ከሞት እንዳስነሳውና በሰማይ ታላቅ መንፈሳዊ ፍጡር እንዳደረገው ከቅዱሳን ጽሑፎች ጥናታቸው ማረጋገጫ ማግኘታቸው ነው። (ፊልጵስዩስ 2:​8-11) በኢየሱስና ይሖዋ አምላክ በክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ባደረገው የመዳን ዝግጅት ላይ እምነት ነበራቸው። (ሮሜ 5:​8) እነዚህ ሰዎች የአምላክን ፈቃድ በማድረጋቸውና ከኢየሱስ ትምህርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ በመመላለሳቸው እውነተኛ ደስታ አግኝተዋል።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ አስብ። ክብር፣ ሥልጣን ወይም ሃብት የሚያስገኝ አልነበረም። ከዚህ በተቃራኒ የመጀመሪያዎቹ በርካታ ክርስቲያኖች ‘የገንዘባቸውን ንጥቂያ በደስታ ተቀብለዋል።’ (ዕብራውያን 10:​34) ክርስትና መሥዋዕታዊ ኑሮ መኖርን የሚጠይቅና ብዙውን ጊዜም ለሰማዕትነት ለሚዳርግ ስደት የሚያጋልጥ ነበር።

ክብርንና ሃብትን እናንሳ ካልን አንዳንዶች የክርስቶስ ተከታዮች ከመሆናቸው በፊት ከፍተኛ ክብርና ደህና ሀብት ነበራቸው። የጠርሴሱ ሳዖል ታዋቂ በነበረው የሕግ አስተማሪ በገማልያል ሥር የተማረ ሲሆን በአይሁዳውያን ዘንድ ከፍተኛ ክብር እያገኘ መጥቶ ነበር። (ሥራ 9:​1, 2፤ 22:​3፤ ገላትያ 1:​14) ሆኖም ሳውል ተለውጦ ሐዋርያው ጳውሎስ ተባለ። እሱም ሆነ ሌሎች በርካታ ሰዎች ይህ ዓለም ለሚያቀርበው ክብርና ሥልጣን ጀርባቸውን ሰጥተዋል። ለምን? አምላክ በገባቸው ተስፋዎች ላይ የተመሠረተውን እውነተኛውን የተስፋ መልእክትና ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት መነሣቱን የሚገልጸውን ሃቅ ለማሰራጨት እንዲህ ያለውን ለውጥ አድርገዋል። (ቆላስይስ 1:​28) በእውነት ላይ እንደተመሠረተ ለሚያውቁት ነገር ሥቃይ ለመቀበል ፈቃደኞች ነበሩ።

በዛሬው ጊዜ ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። እነዚህን ሰዎች በመላው ዓለም በሚገኙ በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ ልታገኛቸው ትችላለህ። ምሥክሮቹ እሁድ ሚያዝያ 8, 2001 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ በሚከበረው የክርስቶስ ሞት በዓል ላይ እንድትገኝ ሞቅ ያለ ግብዣ ያደርጉልሃል። በዚህ በዓል ላይና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት በመንግሥት አዳራሾቻቸው ውስጥ በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ ብትገኝ በጣም ደስ ይላቸዋል።

ስለ ኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ብቻ ሳይሆን ስለ ሕይወት ታሪኩና ስላስተማራቸው ትምህርቶች ለምን ተጨማሪ ትምህርት አትቀስምም? ወደ እርሱ እንድንቀርብ ይጋብዘናል። (ማቴዎስ 11:​28-30) ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገልጸውን ትክክለኛ እውቀት ለማግኘት አሁኑኑ እርምጃ ውሰድ። እንዲህ ማድረግህ በውድ ልጁ በሚተዳደረው በአምላክ መንግሥት ሥር የዘላለም ሕይወት ሊያስገኝልህ ይችላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የወንጌል ዘገባዎች ትክክለኛ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ለማግኘት በግንቦት 15, 2000 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ወንጌሎች​—⁠እውነተኛ ታሪክ ናቸው ወይስ ተረት?” የሚለውን ተመልከት።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች በመሆን እውነተኛ ደስታ አግኝተዋል

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

From the Self-Pronouncing Edition of the Holy Bible, containing the King James and the Revised versions