ሕንድ—“ኅብር ያለው አንድነት”
የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
ሕንድ—“ኅብር ያለው አንድነት”
“ኅብር ያለው አንድነት” የሚለው ሐረግ በሕንድ ያለውን ብሔራዊ ውህደት ለማመልከት የሚያገለግል መፈክር ነው። በባሕል፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በጎሳ፣ በአለባበስና በአመጋገብ ረገድ ሰፊ ልዩነት ባላት በዚህች አገር ውስጥ አንድነት እንዲኖር ማድረግ ቀላል አይደለም። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለውን አንድነት ሕንድ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች አስተዳደር ቢሮ ውስጥ ማየት ይቻላል። በዚህ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ ከተለያዩ ግዛቶችና ክልሎች የመጡ እንዲሁም በርካታ የተለያዩ ቋንቋዎች የሚናገሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች የሚኖሩ ቢሆንም በመካከላቸው ግን አንድነት አለ።
• እስቲ በሕንድ ሰሜናዊ ምዕራብ ጫፍ ከምትገኘው ፑንጃብ ከመጣችው ሮዝሮኒ ከተባለች ወጣት ጋር እናስተዋውቅህ። ሮዝሮኒ በትምህርት ቤት ሳለች አንዲት የክፍሏ ተማሪ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀምራ ነበር። ይህች ወጣት ሮዝሮኒም መጽሐፍ ቅዱስ እንድታጠና ጥረት ታደርግ ነበር። አብረዋት የሚማሩት ልጆች የእንግሊዝኛ ችሎታ ውስን በመሆኑና በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት በፑንጃቢ ቋንቋ ስላልነበረ ወጣቷ የመጠበቂያ ግንብ ርዕሶቹን ወደ ፑንጃቢ ቋንቋ እንድትተረጉምላት ሮዝሮኒን ጠየቀቻት። ሮዝሮኒ በመጠበቂያ ግንብ መጽሔቱ ላይ ባነበበችው ነገር በጥልቅ በመነካቷ የቤተሰብ ተቃውሞ ቢገጥማትም እንኳ እድገት አድርጋ ራሷን ለይሖዋ አምላክ ወሰነች። በዛሬው ጊዜ ሮዝሮኒ ሕንድ በሚገኘው ቤቴል ውስጥ በማገልገል ላይ ስትሆን ክርስቲያናዊ ጽሑፎችን ወደ ፑንጃቢ ቋንቋ በመተርጎም ለእውነት ዓይኗን የከፈተላትን ሥራ በመሥራት ላይ ትገኛለች!
• ከሌላኛው የሕንድ ክፍል ማለትም ከካራላ ደቡባዊ ምዕራብ ግዛት የመጣውን ቢዞን ተመልከት። ቢዞን በብሔራዊ ክብረ በዓላት ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆኑና ገለልተኛ አቋም በመውሰዱ ምክንያት ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተባረረ። ረዥም ጊዜ የወሰደው የፍርድ ሂደት ለንጹሕ አምልኮ ትልቅ ምዕራፍ በከፈተ ድል ከተጠናቀቀ በኋላ ቢዞን ወደ ትምህርት ገበታው እንዲመለስ ተደረገ። a ቢዞን ኮሌጅ ገብቶ ትምህርቱን ቢቀጥልም እዚያ ሰፍኖ የተመለከተው ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ መንፈስ ሕሊናውን ስለረበሸው በመጀመሪያው ሴሚስተር አቋርጦ ወጣ። ዛሬ በቤቴል አሥር ዓመታት ካሳለፈ በኋላ ከፍተኛ ትምህርት በመከታተል ካገኘው ይልቅ ከተለያየ ወገን በተውጣጣና አንድነት ባለው ቤተሰብ መካከል በመኖሩ ያገኘው ጥቅም እንደሚልቅ ይሰማዋል።
• ኖርማ እና ሊሊ ዕድሜያቸው ከሰባ ዓመት በላይ ሲሆን ለብዙ ዓመታት መበለት ሆነው ኖረዋል። ሁለቱም በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከ40 የሚበልጡ ዓመታት አሳልፈዋል። ሊሊ የታሚል ቋንቋ ተርጓሚ ሆና በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ 20 ለሚያክሉ ዓመታት አገልግላለች። ኖርማ በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ መሥራት የጀመረችው ከ13 ዓመት በፊት ባሏ ከሞተ በኋላ ነበር። ታታሪና ጠንቃቃ ሠራተኞች በመሆን ከሚያሳዩት ምሳሌነት ሌላ በቤቴል ቤተሰቡ መካከል አንድነት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ አበርክተዋል። እንግዶችን በደስታ መቀበልና የብዙ ዓመታት ክርስቲያናዊ ኑሮ ያስገኘላቸውን ደስታ በማካፈል ከወጣት የቤተሰቡ አባላት ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስደስታቸዋል። ወጣት የቤተሰቡ አባላትም በተራቸው በየክፍላቸው ይጋብዟቸዋል። እንዲሁም አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ አንዳንድ ነገሮችን በማድረግ ያግዟቸዋል። ምንኛ ግሩም ምሳሌዎች ናቸው!
እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች በብዙ ቦታዎች ለጠብና ለመከፋፈል ምክንያት የሚሆኑትን ልዩነቶች በማስወገድ ሕንድ የሚገኘው አንድነት ያለው የቤቴል ቤተሰብ አባላት ሆነው ሌሎችን በደስታ ያገለግላሉ።—መዝሙር 133:1
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የኀዳር 1, 1987 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 21ን ተመልከት።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
ከበስተጀርባ ያለው ሥዕል:- Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.