ሰዎች በተሳሳተ መንገድ እንደሚረዱህ ይሰማሃልን?
ሰዎች በተሳሳተ መንገድ እንደሚረዱህ ይሰማሃልን?
አንቶንዮ በጣም ተረብሿል። ድንገት፣ ምንም በማያውቀው ምክንያት ጥሩ ወዳጁ የሆነው ሊዮናርዶ እንደ ማኩረፍ ብሎታል። a በተለያዩ አጋጣሚዎች አንቶንዮ ሰላም ሲለው ዝም ብሎታል። አብረው በሚሆኑበት ጊዜም ዝም ዝም ይባባላሉ። አንቶንዮ ጓደኛዬ በተሳሳተ መንገድ የተረዳው አንድ ያደረግሁት ወይም የተናገርሁት ነገር ይኖራል የሚል ስጋት አድሮበታል። ነገሩ ምን ይሆን?
አለመግባባት ብዙ ጊዜ ሊከሰት የሚችል ነገር ነው። አብዛኞቹ አለመግባባቶች ጥቃቅንና በቀላሉ ሊፈቱ የሚችሉ ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዴ የሚከሰተው አለመግባባት ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት ተደርጎም ላይሳካና ለብስጭት ሊዳርግ ይችላል። አለመግባባቶች የሚከሰቱት ለምንድን ነው? አለመግባባቱ የተፈጠረባቸውን ሰዎችስ የሚነካው እንዴት ነው? ሌሎች ያደረግከውን ነገር በተሳሳተ መንገድ ቢረዱት ምን ማድረግ ትችላለህ? ሌሎች ስለአንተ የፈለገውን ቢያስቡ በእርግጥ ለውጥ ያመጣልን?
ልንሸሸው የማንችለው ሐቅ
ሌሎች ሰዎች አስተሳሰባችንንና ውስጣዊ ስሜታችንን ማንበብ ስለማይችሉ ይዋል ይደር እንጂ አንድ ሰው የተናገርነውን ወይም ያደረግነውን ነገር በተሳሳተ መንገድ መተርጎሙ የማይቀር ነው። አለመግባባት የሚፈጠርባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። አንዳንድ ጊዜ ሐሳባችንን የሚፈለገውን ያህል በግልጽና በትክክል ማስረዳት ይሳነናል። በአካባቢው ያለ ጫጫታና ሐሳብ የሚከፋፍሉ ሌሎች ነገሮች ሰዎች የምንናገረውን የተሟላ ትኩረት ሰጥተው ለማዳመጥ አዳጋች ሊያደርግባቸው ይችላል።
አንዳንድ ድርጊቶችና ባሕርያት በቀላሉ በተሳሳተ መንገድ ሊተረጎሙ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል ዓይናፋር የሆነ ሰው የማይቀረብ፣ ግዴለሽ ወይም ኩራተኛ ተደርጎ በተሳሳተ መንገድ ሊፈረጅ ይችላል። አንድ ሰው ቀደም ሲል በሕይወቱ ውስጥ ያሳለፋቸው ነገሮች ለአንዳንድ ሁኔታዎች የታሰበበት ሳይሆን ስሜታዊ ምላሽ እንዲሰጥ ያደርጉት ይሆናል። የባሕልና የቋንቋ ልዩነቶች ሰዎች በቀላሉ እንዳይግባቡ ሊያደርጉ ይችላሉ። የተዛባ ወሬና ሐሜት ከታከለበት ደግሞ መጀመሪያ የተነገረው ወይም የተደረገው ነገር የተሳሳተ ትርጉም ቢሰጠው ሊያስገርመን አይገባም። እርግጥ ነው፣ የተናገሩት ወይም ያደረጉት ነገር የተሳሳተ ትርጉም እንደተሰጠው ለሚሰማቸው ሰዎች ይህ ሁሉ እምብዛም መጽናኛ አይሆናቸውም።
ለምሳሌ ያህል አና በዕለቱ ከሥራ ቀርታ ስለነበረች አንዲት ጓደኛዋ ተወዳጅነት በቅንነት አውርታ ነበር። የተናገረችው ነገር በተዛባ መንገድ ተወራ። ከዚያም ጓደኛዋ አንድ አብሯት የሚሠራ ሰው ስላቀረባት ቀንታ ይህን እንደተናገረች በመግለጽ በብዙዎች ፊት በቁጣ ስትዘልፋት አና ፈጽሞ ያልጠበቀችው ነገር በመሆኑ ግራ ተጋባች። አና የተናገረችው ነገር ፈጽሞ የተሳሳተ ትርጉም ተሰጥቶት የነበረ ሲሆን እሷን ለማስቀየም ብላ የተናገረችው ምንም ነገር እንደሌለ ጓደኛዋን ለማሳመን ያደረገችው ጥረት መና ሆኖ ቀረ። ሁኔታው ከፍተኛ ውጥረት ያስከተለ ከመሆኑም በላይ አና የተፈጠረውን አለመግባባት ሙሉ በሙሉ ለማስተካከል ረጅም ጊዜ ወስዶባታል።
ሌሎች ለአንተ የሚኖራቸው ግምት በአብዛኛው የተመካው አስተሳሰብህን በሚረዱበት መንገድ ነው። ስለዚህ ሰዎች ውስጣዊ ዝንባሌህን በተሳሳተ መንገድ ሲረዱት መናደድህ ያለ ነገር ነው። ሰው በተሳሳተ መንገድ የሚረዳኝ ለምንድን ነው ብለህ ትበሳጭ ይሆናል። በአንተ አመለካከት እንዲህ ዓይነቱ አስተያየት የተዛባ፣ ነቀፋ አዘል ወይም ሙሉ በሙሉ ስህተት ነው። እንዲሁም የተሳሳተ ግምት የያዙ ሰዎች ያላቸውን አመለካከት ከፍ አድርገህ የምትመለከት ከሆነ በሚናገሩት ነገር ስሜትህ በጥልቅ ሊጎዳ ይችላል።
ሰዎች አንተን የሚረዱበት መንገድ ሊያናድድህ ቢችልም እንኳ ሌሎች የሚሰጡትን አስተያየት ማክበርህ ተገቢ ነው። የሌሎችን አስተሳሰብ መናቅ ክርስቲያናዊ ባሕርይ አይደለም። እንዲሁም ንግግራችን ወይም ድርጊታችን በሌሎች ሰዎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዲያሳድር አንፈልግም። (ማቴዎስ 7:12፤ 1 ቆሮንቶስ 8:12) ስለዚህ አልፎ አልፎ አንድ ሰው ስለ አንተ ያለውን የተዛባ አመለካከት ለማስተካከል ጥረት ሊጠይቅብህ ይችላል። ሆኖም በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት ስለማግኘት ከልክ በላይ መጨነቅ ለራስህ አክብሮት እንድታጣ ወይም የማትፈለግ ሆኖ እንዲሰማህ ስለሚያደርግ መጥፎ ውጤት አለው። ደግሞም የአንተ እውነተኛ ማንነት የሚመካው ሌሎች ስለ አንተ ባላቸው አመለካከት አይደለም።
በአንጻሩ ደግሞ የተሰነዘረብህ ወቀሳ አግባብነት ያለው መሆኑን ትገነዘብ ይሆናል። ይህም ቢሆን ጭንቀት ሊፈጥርብህ ይችላል። ይሁን እንጂ የራስህን አለፍጽምና ሳታንገራግር በሐቀኝነት አምነህ ከተቀበልክ ይህ አስፈላጊውን ለውጥ እንድታደርግ የሚያነሳሳህ ጥሩ አጋጣሚ ሊሆንልህ ይችላል።
አስከፊ መዘዝ
አለመግባባት አስከፊ መዘዝ ሊያስከትልም ላያስከትልም ይችላል። ለምሳሌ ያህል አንድ ምግብ ቤት ውስጥ አንድ ሰው ጮክ ብሎ ሲናገር ብትሰማ ይህ ሰው በጣም ተጫዋች ነው አሊያም ደግሞ ጉረኛ ነው ብለህ ትደመድም ይሆናል። ተሳስተህ ሊሆን ይችላል። እያነጋገረው ያለው ሰው የመስማት ችግር ሊኖርበት ይችላል። ወይም ደግሞ ሱቅ ውስጥ ስትሸጥ ያገኘሃት አንዲት ሴት እንዲሁ ሁኔታዋን ስታይ ጥሩ ሰው እንዳልሆነች ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም አንድ የረበሻት ነገር ስላለ ሊሆን ይችላል። ምንም እንኳ እንዲህ ዓይነት አለመግባባቶች መጥፎ ስሜት ሊያሳድሩ ቢችሉም አስከፊ ወይም ዘላቂ መዘዝ ላያስከትሉ ይችላሉ። አንዳንድ ጊዜ ግን ሌሎችን በተሳሳተ መንገድ መረዳት ከባድ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። በጥንቷ እስራኤል ታሪክ የተፈጸሙ ሁለት ክስተቶችን ተመልከት።
የአሞን ንጉሥ ናዖስ በሞተ ጊዜ በአባቱ ምትክ መግዛት የጀመረውን ልጁን ሐኖንን እንዲያጽናኑት ዳዊት መልእክተኞችን ላከ። ይሁን እንጂ መልእክተኞቹ የመጡበት ዓላማ የአሞናውያንን ክልል ለመሰለል እንደሆነ ተደርጎ በተሳሳተ መንገድ ተተረጎመ። ይህም ሐኖን በመጀመሪያ መልእክተኞቹን አዋርዶ እንዲመልሳቸው ከዚያም እስራኤልን ለመውጋት እንዲያነሳ አደረገው። በዚህ ሳቢያ ቢያንስ 47, 000 ሰዎች አልቀዋል። ይህ ሁሉ የደረሰው በጥሩ ዓላማ የተደረገ ነገር በተሳሳተ መንገድ በመተርጎሙ ምክንያት ነው።—1 ዜና መዋዕል 19:1-19
በእስራኤል ታሪክ መጀመሪያ ላይ የተከሰተ አንድ ሌላ አለመግባባት ከዚህ በተለየ መንገድ መፍትሄ አግኝቷል። የሮቤል፣ የጋድና የምናሴ ነገድ እኩሌታ በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ አንድ ትልቅ መሠዊያ ሠሩ። የቀሩት እስራኤላውያን መሠዊያውን የእምነት አጉዳይነትና በይሖዋ ላይ የማመፅ ድርጊት አድርገው ተመለከቱት። በመሆኑም ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ አንድ ላይ ተሰባሰቡ። እስራኤላውያኑ ምንም ዓይነት ከባድ እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት ክህደት እንደሆነ ስለቆጠሩት ድርጊት የተሰማቸውን ንዴት ለመግለጽ መልእክተኞች ላኩ። እንዲህ ማድረጋቸው መልካም ነበር፤ ምክንያቱም መሠዊያውን የሠሩት ነገዶች ከእውነተኛው አምልኮ የመራቅ ዓላማ እንደሌላቸው ገልጸዋል። ከዚህ ይልቅ መሠዊያው ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት የሚያሳይ ሐውልት ሆኖ እንዲያገለግል የቆመ ነበር። ይህ አለመግባባት እልቂት ሊያስከትል ይችል ነበር። ሆኖም በጥበብ በመመራት እንዲህ ዓይነቱን አስከፊ መዘዝ ማስቀረት ተችሏል።—ኢያሱ 22:10-34
በፍቅር መንፈስ ጉዳዩን ግልጽ ማድረግ
እነዚህን ዘገባዎች በማወዳደር ትምህርት ማግኘት ይቻላል። ጉዳዩን ግልጽ ማድረግ የጥበብ እርምጃ እንደሆነ የታወቀ ነው። በሁለተኛው ክስተት ላይ ሁለቱ ወገኖች በመነጋገራቸው ብቻ ምን ያህል ሕይወት እንደተረፈ ማን ያውቃል? አብዛኛውን ጊዜ የአንድን ሰው ትክክለኛ ሐሳብ ሳትረዳ በመቅረትህ ለሕይወት የሚያሰጋ ነገር አይፈጥር ይሆናል። ይሁን እንጂ ወዳጅነታችሁ አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል። ስለዚህ አንድ ሰው ተገቢ ያልሆነ ነገር እንዳደረገብህ ከተሰማህ ሁኔታውን በትክክል መረዳትህን እርግጠኛ ነህን? ወይስ በተሳሳተ መንገድ ተርጉመኸዋል? የሰውየው ውስጣዊ ግፊት ምን ነበር? ጠይቀው። በተሳሳተ መንገድ እንደተረዳህ ይሰማሃልን? የተሰማህን ንገረው። ኩራት እንቅፋት እንዲሆንብህ አትፍቀድ።
ኢየሱስ አለመግባባቶችን ለመፍታት የሚያስችል ግሩም ማበረታቻ ሰጥቷል:- “እንግዲህ መባህን በመሠዊያው ላይ ብታቀርብ፣ በዚያም ወንድምህ አንዳች በአንተ ላይ እንዳለው ብታስብ፣ በዚያ በመሠዊያው ፊት መባህን ትተህ ሂድ፣ አስቀድመህም ከወንድምህ ጋር ታረቅ፣ በኋላም መጥተህ መባህን አቅርብ።” (ማቴዎስ 5:23, 24) ስለዚህ መደረግ ያለበት ተገቢ ነገር ሌሎችን ሳትጨምር ሰውየውን ለብቻው ቀርበህ ማነጋገር ነው። ያስቀየመህ ሰው የአንተን ቅር መሰኘት መጀመሪያ የሰማው ከሌላ ሰው ከሆነ ጥሩ አይሆንም። (ምሳሌ 17:9) ግብህ በፍቅር መንፈስ ሰላም መፍጠር ሊሆን ይገባል። ችግሩን በረጋ መንፈስ ግልጽ በሆነና በሚገባ እንዲሁም ከነቀፋ ነፃ በሆነ አነጋገር አስረዳ። ሁኔታው ያሳደረብህን ስሜት ግለጽ። ከዚያም የሌላውን ወገን አመለካከት በቀና ልብ አዳምጥ። በመጥፎ ለመተርጎም አትቸኩል። ሌላው ወገን መጥፎ ዝንባሌ የለውም ብለህ ለማመን ፈቃደኛ ሁን። ፍቅር ‘ሁሉን እንደሚያምን’ አስታውስ።—1 ቆሮንቶስ 13:7
እርግጥ ነው፣ አለመግባባቶች ከተወገዱም በኋላ እንኳ የስሜት መጎዳት ወይም በቀላሉ የማይሻሩ መጥፎ ውጤቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ምን ማድረግ ይቻላል? አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ልባዊ ይቅርታ መጠየቅ እንዲሁም ችግሩን ለመፍታት መውሰድ የሚያስፈልገውን ምክንያታዊ እርምጃ ሁሉ መውሰድ የተገባ ይሆናል። እንደዚህ ዓይነት ሁኔታዎች በሚፈጠሩበት ጊዜ ተበድያለሁ ባዩ ወገን ቀጥሎ ያለውን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ምክር መከተል አለበት:- “እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት።”—ቆላስይስ 3:13, 14፤ 1 ጴጥሮስ 4:8
ፍጹማን እስካልሆንን ድረስ አለመግባባትና የስሜት መጎዳት መከሰቱ የማይቀር ነገር ነው። ማንኛውም ሰው ቢሆን ሊሳሳት ወይም አሳቢነት አሊያም ደግነት የጎደለው በሚመስል ሁኔታ ሊናገር ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ ሥጋውን ሁሉ ደግሞ ሊገታ የሚችል ፍጹም ሰው ነው።” (ያዕቆብ 3:2) ይሖዋ አምላክ ይህን አሳምሮ ስለሚያውቅ ቀጥሎ ያለውን መመሪያ ሰጥቶናል:- “በነፍስህ ለቁጣ ችኩል አትሁን፣ ቁጣ በሰነፍ ብብት ያርፋልና። ባሪያህ ሲረግምህ እንዳትሰማ በሚጫወቱበት ቃል ሁሉ ልብህን አትጣል፤ አንተ ደግሞ ሌሎችን እንደ ረገምህ ልብህ ያውቃልና።”—መክብብ 7:9, 21, 22
‘ይሖዋ ልብን ይመዝናል’
አንድ ሰው ስለ አንተ ያደረበትን አፍራሽ አመለካከት ማስተካከል ቢያቅትህስ? ተስፋ አትቁረጥ። አቅምህ በፈቀደልህ መጠን ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማዳበርህንና ማሳየትህን ቀጥል። ማሻሻል ያለብህን ነገር ለማሻሻል ይሖዋ እንዲረዳህ ጠይቀው። እውነተኛ ማንነትህ የሚለካው በሌሎች አመለካከት አይደለም። በትክክል ‘ልብን መመዘን’ የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። (ምሳሌ 21:2) ኢየሱስ እንኳ በሰዎች ዘንድ እንደ አልባሌ ተቆጥሮ ተንቋል። ይሁን እንጂ ይህ ይሖዋ ለእሱ ባለው አመለካከት ላይ ያመጣው ለውጥ አልነበረም። (ኢሳይያስ 53:3) ምንም እንኳ አንዳንዶች በተሳሳተ መንገድ ሊረዱህ ቢችሉም ይሖዋ ሁኔታህን እንደሚረዳ እርግጠኛ በመሆን ለእሱ ‘ልብህን ማፍሰስ’ ትችላለህ። ምክንያቱም ‘ሰው እንዲያይ ይሖዋ አያይምና፤ ሰው ፊትን ያያል፣ ይሖዋ ግን ልብን ያያል።’ (መዝሙር 62:8፤ 1 ሳሙኤል 16:7) መልካም የሆነውን ማድረግህን ከቀጠልክ በአንተ ላይ መጥፎ አመለካከት ያላቸው ሰዎች የኋላ ኋላ ስህተታቸውን ተገንዝበው አመለካከታቸውን ይለውጡ ይሆናል።—ገላትያ 6:9፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:15
በዚህ ርዕስ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው አንቶንዮ ትዝ ይልሃል? ቅዱስ ጽሑፋዊውን ምክር ለመከተል እንደምንም ብሎ ራሱን አደፋፈረና እሱን የሚያስቀይም ምን ነገር እንዳደረገ በመጠየቅ ጓደኛውን ሊዮናርዶን አነጋገረው። ውጤቱ ምን ሆነ? ሊዮናርዶ የሚለው ጠፋው። አንቶንዮ እሱን የሚያናድድ አንዳችም ነገር አለማድረጉን ነገረው። እንዲሁም ለእሱ ከወትሮው የተለየ ፊት ለማሳየት ሆነ ብሎ ያደረገው አለመሆኑን አረጋገጠለት። ያኮረፈ መስሎ የታየው ምናልባት ሐሳብ ውስጥ ስለነበረ ይሆናል። ሊዮናርዶ ሳያውቀው የጓደኛውን ስሜት በመጉዳቱ ይቅርታ የጠየቀው ከመሆኑም በላይ ጉዳዩን አንስቶ ስላነጋገረውም አመሰገነው። በማከልም ለወደፊቱ በሌሎች ላይ ተመሳሳይ ስሜት ላለማሳደር ይበልጥ ጥንቃቄ እንደሚያደርግ ተናገረ። በመካከላቸው የተፈጠረው ውጥረት በቀላሉ የተወገደ ሲሆን ሁለቱ ጓደኛሞች እንደ ወትሮው የቅርብ ወዳጆች ሆኑ።
ሌሎች በተሳሳተ መንገድ እንደተረዱን ሲሰማን ደስ አይለንም። ሆኖም ነገሮችን ግልጽ ለማድረግ የቻልከውን ሁሉ ካደረግህና የፍቅርንና የይቅር ባይነትን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ ካዋልክ አንተም ጥሩ ውጤት ልታገኝ ትችላለህ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ ርዕስ ውስጥ አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አለመግባባቶችን በፍቅርና በይቅር ባይነት መንፈስ ግልጽ ማድረግ አስደሳች ውጤት ሊያስገኝ ይችላል