በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታዛዥነት—በልጅነት ሊሰጥ የሚገባ አስፈላጊ ትምህርት ነውን?

ታዛዥነት—በልጅነት ሊሰጥ የሚገባ አስፈላጊ ትምህርት ነውን?

ታዛዥነት—በልጅነት ሊሰጥ የሚገባ አስፈላጊ ትምህርት ነውን?

በአንድ ጋዜጣ ላይ የወጣ ርዕሰ አንቀጽ “ወላጆች ልጆቻቸው እንዲሁ ታዛዥ ከሚሆኑ ይልቅ የራሳቸው ስብዕና ያላቸው ቢሆኑላቸው ይመርጣሉ” ብሏል። ይህ አጭር ሪፖርት በኒው ዚላንድ ውስጥ በተካሄደ አንድ ጥናት ውጤት ላይ የተመሠረተ ነው። ጥናቱ “መልስ ከሰጡት መካከል ልጆች ታዛዥነትን ከቤት መማር አለባቸው የሚል አመለካከት ያላቸው 22 በመቶ” የሚሆኑት ብቻ እንደሆኑ አመልክቷል። በተጨማሪም በዛሬው ጊዜ ወላጆች እንደ መልካም ሥነ ምግባር፣ ራስን ችሎ መኖርና ኃላፊነት መሸከም የመሳሰሉትን ነገሮች ለልጆች ማስተማር ይበልጥ አስፈላጊ መሆኑን እንደሚያምኑ ጥናቱ ደርሶበታል።

በራስ መመራትና ራስ ወዳድነት በገነነበት በዚህ ዘመን አብዛኞቹ ሰዎች ስለ ታዛዥነትና ታዛዥነትን ለልጆች ስለማስተማር ያላቸው አመለካከት የደበዘዘ መሆኑ ምንም አያስገርምም። ይሁን እንጂ በልጅነት ታዛዥ መሆን ያረጀና ጊዜ ያለፈበት እንደሆነ ነገር መታየት አለበትን? ወይስ ልጆች መማር ካለባቸውና ሊጠቅማቸው ከሚችለው አስፈላጊ ትምህርት መካከል ነው? ከሁሉም በላይ የቤተሰብ ዝግጅት መሥራች የሆነው ይሖዋ አምላክ ለወላጆች ታዛዥ መሆንን እንዴት ይመለከተዋል? እንዲሁም ይህ ዓይነቱ ታዛዥነት የሚያስገኛቸው አንዳንድ ጥቅሞች ምንድን ናቸው?​—⁠ሥራ 17:​28፤ ኤፌሶን 3:​14, 15

“ይህ የሚገባ ነውና”

ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኤፌሶን ለነበረው የክርስቲያን ጉባኤ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ልጆች ሆይ፣ ለወላጆቻችሁ በጌታ ታዘዙ፣ ይህ የሚገባ ነውና።” (ኤፌሶን 6:​1) በመሆኑም እንዲህ ዓይነት ታዛዥነት የምናሳይበት ዋነኛው ምክንያት ከመለኮታዊ የአቋም ደረጃ አንጻር ትክክል ከሆነው ነገር ጋር የሚስማማ ስለሆነ ነው። ጳውሎስ እንደገለጸው “ይህ የሚገባ ነውና።”

በዚህ ረገድ የአምላክ ቃል “ለራስህ የሞ​ገስ ዘውድ፣ ለአንገትህም ድሪ ይሆንልሃል” በማለት ወላጅ በፍቅር የሚ​ሰጠው ሥልጠና ያማረ ጌጥ እንደሆነ፤ እንዲሁም “ለጌታ ደስ የሚያሰኝ” ነገር መሆኑን እንደሚገልጽ እናስተውላለን። (ምሳሌ 1:​8, 9፤ ቆላስይስ 3:​20) ከዚህ ፍጹም በተቃራኒ ለወላጅ አለመታዘዝ መለኮታዊ ተቀባይነት ያሳጣል።​—⁠ሮሜ 1:​30, 32

“መልካም እንዲሆንልህ”

ጳውሎስ ታዛዥነት የሚያስገኘውን ሌላ ጥቅም ሲጠቅስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤ እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት።” (ኤፌሶን 6:​2, 3፤ ዘጸአት 20:​12) አንድ ልጅ ወላጆቹን በመታዘዙ መልካም የሚሆንለት በምን መንገድ ነው?

በመጀመሪያ ደረጃ ወላጆች በዕድሜና በተሞክሮ ብልጫ ያላቸው መሆኑ እውነት አይደለምን? ምንም እንኳ ስለ ኮምፒውተር ወይም በትምህርት ቤት ስለሚሰጡ አንዳንድ ትምህርቶች ሰፊ እውቀት ላይኖራቸው ቢችልም ስለ ኑሮ እና በኑሮ ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መወጣትን በተመለከተ ከፍተኛ እውቀት አላቸው። በአንጻሩ ደግሞ ወጣቶች ከጉልምስና ጋር የሚመጣው ሚዛናዊ አስተሳሰብ ይጎድላቸዋል። በመሆኑም በችኮላ የመወሰን ዝንባሌ ስለሚኖራቸው አብዛኛውን ጊዜ ለእኩዮች ጎጂ ተጽእኖ በመሸነፍ ራሳቸውን ለጉዳት ይዳርጋሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ስንፍና በሕፃን ልብ ታስሮአል” ብሎ መናገሩ በጣም ትክክል ነው። ታዲያ መፍትሄው ምንድን ነው? “የተግሣጽ በትር ግን ከእርሱ ያርቃታል።”​—⁠ምሳሌ 22:​15

ታዛዥነት የሚያስገኘው ጥቅም በወላጅና በልጅ መካከል ካለው ዝምድና አልፎ ይሄዳል። የሰው ልጅ ኅብረተሰብ በተቃናና ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲንቀሳቀስ ትብብር አስፈላጊ ነው። ይህ ደግሞ ታዛዥነትን ይጠይቃል። ለምሳሌ ያህል፣ በትዳር ውስጥ ሰላም፣ ስምምነትና ደስታ እንዲሰፍን የሚያስችለው ለራስ ጥቅም መቆምና ለሌሎች መብትና ስሜት ግድ የለሽ መሆን ሳይሆን ሌላውን ለመጥቀም ፈቃደኛ መሆን ነው። በሥራው ዓለም ሠራተኞች ተገዢ መሆናቸው ለማንኛውም ሥራ ወይም ውጥን ስኬት አስፈላጊ ነገር ነው። መንግሥት በሚያወጣቸው ሕጎችና መመሪያዎች ረገድ ታዛዥነት ማሳየት አንድን ሰው እንዲያው ከቅጣት ማዳን ብቻ ሳይሆን በተወሰነ መጠን ደኅንነትና ጥበቃ ያስገኝለታል።​—⁠ሮሜ 13:​1-7፤ ኤፌሶን 5:​21-25፤ 6:​5-8

ለሥልጣን የማይገዙ ወጣቶች አብዛኛውን ጊዜ በኅብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያጣሉ። በአንጻሩ ደግሞ አንድ ሰው በልጅነቱ ታዛዥነትን መማሩ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ሊጠቅመው ይችላል። ታዛዥነትን በልጅነት መማር ምንኛ ጠቃሚ ነው!

ታዛዥነት የሚያስገኘው ታላቅ ወሮታ

ታዛዥነት አስደሳች የቤተሰብ ግንኙነትና ሌሎች ዘላቂ ጥቅሞች ከማስገኘቱም በተጨማሪ ከሁሉም በላይ ጠቃሚ የሆነውን ማለትም በሰውና በፈጣሪው መካከል ዝምድና ለመመሥረት የሚያስችለውን መሠረት ያስገኛል። ይሖዋ አምላክ “የሕይወት ምንጭ” እና ‘ታላቅ ፈጣሪ’ እንደመሆኑ መጠን የእኛ ፍጹም የሆነ ታዛዥነት ይገባዋል።​—⁠መክብብ 12:​1፤ መዝሙር 36:​9

“መታዘዝ” የሚለው ቃል በተለያየ አገባቡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ160 ጊዜ በላይ ይገኛል። በተጨማሪም የአምላክ ሕጎች፣ ሥርዓቶች፣ ትእዛዞች፣ ፍርዶችና ደንቦች በመቶዎች የሚቆጠሩ ጊዜያት ተጠቅሰው የሚገኙ ሲሆን ሁሉም ታዛዥ የመሆንን አስፈላጊነት ያሳያሉ። አምላክ የእሱን ሞገስ ለማግኘት ታዛዥነት የግድ እንደሚያስፈልግ ግልጽ አድርጎልናል። አዎን፣ ታዛዥነት ከይሖዋ ጋር ዝምድና ለመመሥረት አስፈላጊ የሆነ መሟላት ያለበት ብቃት ነው። (1 ሳሙኤል 15:​22) የሚያሳዝነው ግን፣ የሰው ልጅ ከመታዘዝ ይልቅ አለመታዘዝ ይቀናዋል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልብ አሳብ ከታናሽነቱ ጀምሮ ክፉ ነው” ይላል። (ዘፍጥረት 8:​21) በመሆኑም የታዛዥነትን ትምህርት በልጅነት ብቻ ሳይሆን በሕይወት ዘመን ሁሉ መማር አስፈላጊ ነው። እንዲህ ማድረግ ታላቅ ወሮታ ያስገኛል።

ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው ወላጆቻችሁን ታዘዙ የሚለው መመሪያ ድርብ ተፈጻሚነት ያለው ተስፋ ይዟል። ይህም “መልካም እንዲሆንልህ እድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም” እንደሚል አስታውሱ። በምሳሌ 3:⁠1, 2 ላይ ይህን ተስፋ የሚያጠናክር ሐሳብ እናገኛለን:- “ልጄ ሆይ፣ ሕጌን አትርሳ፣ ልብህም ትእዛዛቴን ይጠብቅ። ብዙ ዘመናትና ረጅም ዕድሜ ሰላምም ይጨምሩልሃልና።” ታዛዥ የሆኑ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ከይሖዋ ጋር የግል ዝምድና የሚመሠርቱ ሲሆን ሰላም በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ደግሞ የዘላለም ሕይወትን ታላቅ ወሮታ ያገኛሉ።​—⁠ራእይ 21:​3, 4

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ታዛዥነት በቤተሰብ ውስጥ፣ በሥራ ቦታና ከይሖዋ ጋር አስደሳች ዝምድና እንዲኖር ያደርጋል