በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እንደ አንድ አካል ነበርን

እንደ አንድ አካል ነበርን

የሕይወት ታሪክ

እንደ አንድ አካል ነበርን

ሜልባ ቤሪ እንደተናገረችው

በትዳር ዓለም አብረን በቆየንባቸው 57 ዓመታት ውስጥ በሺህ ለሚቆጠሩ ጊዜያት ስናደርግ እንደነበረው እኔና ባለቤቴ ሐምሌ 2, 1999 የይሖዋ ምሥክሮች በሚያደርጉት አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ነበርን። ሎይድ በሃዋይ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የአርብ ዕለቱን የመጨረሻ ንግግር እያቀረበ ነበር። ድንገት ተዝለፍልፎ ወደቀ። ነፍስ እንዲዘራ ለማድረግ ብዙ ቢሞከርም በሕይወት ሊቆይ አልቻለም። a

ይህን አሳዛኝ ክስተት እንድቋቋም ለመርዳት ሲረባረቡ የነበሩት እነዚያ የሃዋይ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ምንኛ ተወዳጅ ናቸው! ሎይድ በእነዚህም ሆነ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በሌሎች ብዙ ወንድሞችና እህቶች ሕይወት ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል።

ከእሱ ሞት በኋላ ባለፉት ወደ ሁለት የሚጠጉ ዓመታት ውስጥ ከእርሱ ጋር በውጭ አገር በሚስዮናዊነትና ብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ተመድበን ስንሠራ አንድ ላይ ያሳለፍናቸው ዓመታት ትዝ ይሉኛል። እንዲሁም በሲድኒ አውስትራሊያ ያሳለፍኩት የልጅነት ሕይወትና ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት እኔና ሎይድ ለመጋባት ባሰብንበት ወቅት የገጠሙንን ችግሮች ሁሉ አስታውሳለሁ። ይሁን እንጂ በመጀመሪያ እንዴት የይሖዋ ምሥክር እንደሆንኩና በ1939 ከሎይድ ጋር እንዴት እንደተዋወቅን ልንገራችሁ።

የይሖዋ ምሥክር የሆንኩት እንዴት ነው?

አፍቃሪና አሳቢ የሆኑት ወላጆቼ ጄምስ እና ሄንሬታ ጆንዝ ይባላሉ። በ1932 ትምህርቴን ስጨርስ ገና የ14 ዓመት ልጅ ነበርኩ። በወቅቱ ዓለም በከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት ውስጥ ወድቆ ነበር። ሁለቱን እህቶቼን ጨምሮ ቤተሰቤን ለመርዳት ስል ሥራ ያዝኩ። በጥቂት ዓመታት ውስጥ ጥሩ ደሞዝ የማገኝና የተወሰኑ ወጣት ሴቶች አለቃ ሆንኩ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በ1935 እናቴ ከአንድ የይሖዋ ምሥክር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፍ የተቀበለች ሲሆን ወዲያው እውነትን እንዳገኘች አመነች። ሌሎቻችን አበደች እንዴ ብለን አስበን ነበር። ይሁን እንጂ አንድ ቀን ሙታን የት ናቸው? የሚል ርዕስ ያለውን ቡክሌት አየሁና ርዕሱ ሳበኝ። ስለዚህ ተደብቄ አነበብኩት። ሕይወቴ የተለወጠው በዚያን ጊዜ ነበር! ወዲያው ከእናቴ ጋር የናሙና ጥናት ተብሎ ወደሚጠራውና በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ወደሚደረገው ስብሰባ መሄድ ጀመርኩ። የናሙና ጥናት (እንግሊዝኛ) የሚባለው ቡክሌት (እንደዚህ ያሉ ሦስት ቡክሌቶች ነበሩ) ጥያቄና መልስ እንዲሁም ለመልሱ ድጋፍ የሚሆኑ ጥቅሶች የያዘ ነበር።

በዚያው ጊዜ አካባቢ ሚያዝያ 1938 ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ የይሖዋ ምሥክሮችን ዋና መሥሪያ ቤት ወክሎ ሊጎበኘን መጣ። በሕዝብ ንግግር ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘሁት ተናጋሪው እሱ በነበረበት ዕለት ነው። ስብሰባውን ለማድረግ ታቅዶ የነበረው በሲድኒ ከተማ አዳራሽ ነበር፤ ሆኖም ተቃዋሚዎች በአዳራሹ ለመጠቀም ያገኘነውን ፈቃድ ለማሰረዝ ያደረጉት ጥረት ተሳካላቸው። ከዚያ ይልቅ ንግግሩ ይበልጥ ሰፊ በሆነው የሲድኒ ስፖርት ማዕከል ተደረገ። ተቃዋሚዎች ለመቃወም ባደረጉት ጥረት ስብሰባውን በሰፊው ስላስተዋወቁ 10, 000 ሰዎች በስብሰባው ላይ የተገኙ ሲሆን ይህ ቁጥር በወቅቱ በአውስትራሊያ ከነበሩት 1, 300 ምሥክሮች አንጻር ሲታይ በጣም የሚያስደንቅ ነው።

ብዙም ሳይቆይ ያለ ምንም ስልጠና ለመጀመሪያ ጊዜ በመስክ አገልግሎት ተካፈልኩ። ብዙ ሆነን ወደምንሰብክበት ክልል ስንደርስ ቡድኑን የሚመራው ወንድም “አንቺ የምታንኳኪው ያኛውን ቤት ነው” አለኝ። በጣም ከመፍራቴ የተነሳ በሩን የከፈተችልኝን ሴት “ሰዓት ስንት ነው?” ብዬ ጠየቅኳት። ወደ ውስጥ ገብታ ሰዓት አየችና ተመልሳ ነገረችኝ። በቃ ይኸው ነው። ወደ መኪናችን ተመለስኩ።

ይሁን እንጂ ተስፋ አልቆረጥኩም፤ ብዙም ሳይቆይ የመንግሥቱን መልእክት ዘወትር ለሰዎች ማካፈል ጀመርኩ። (ማቴዎስ 24:​14) መጋቢት 1939 በጎረቤታችን በዶርቲ ሃቺንግስ ቤት በሚገኝ መታጠቢያ ገንዳ ውስጥ በመጠመቅ ራሴን ለይሖዋ መወሰኔን አሳየሁ። በዚያን ጊዜ ወንድሞች ስላልነበሩ እንደተጠመቅኩ ክርስቲያን ወንዶች ብቻ ሊይዟቸው የሚገቡ የጉባኤ ኃላፊነቶች ተሰጡኝ።

ብዙውን ጊዜ ስብሰባዎቻችንን የምናደርገው በግል ቤቶች ውስጥ ነበር። ሆኖም አልፎ አልፎ ለሕዝብ ንግግር አዳራሽ እንከራይ ነበር። ከቅርንጫፍ ቢሯችን ከቤቴል አንድ መልከ መልካም ወጣት ወንድም የሕዝብ ንግግር ለመስጠት ጥቂት አባላት ወዳሉት ጉባኤያችን መጣ። እኔ አልተገነዘብኩትም እንጂ የመጣበት ሌላው ምክንያት ስለ እኔ ይበልጥ ለማወቅ ፈልጎ ነበር። አዎን፣ ከሎይድ ጋር የተዋወቅኩት በእንደዚህ ያለ አጋጣሚ ነበር።

ከሎይድ ቤተሰብ ጋር መተዋወቅ

ብዙም ሳይቆይ ይሖዋን በሙሉ ጊዜ የማገልገል ፍላጎት አደረብኝ። ይሁን እንጂ አቅኚ ለመሆን (በሙሉ ጊዜ የስብከት አገልግሎት ለመካፈል) ማመልከቻ ሳስገባ በቤቴል ማገልገል እፈልግ እንደሆነ ተጠየቅኩ። ስለዚህ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በጀመረበት ወር ማለትም መስከረም 1939 በሲድኒ ከተማ ዳርቻ ስትራትፊልድ የሚገኘው የቤቴል ቤተሰብ አባል ሆንኩ።

ታኅሣሥ 1939 ለአውራጃ ስብሰባ ወደ ኒው ዚላንድ ሄድኩ። ሎይድም ኒው ዚላንዳዊ ስለሆነ ወደዚያ ይሄድ ነበር። በአንድ መርከብ ስለተጓዝን እርስ በርስ ይበልጥ ተዋወቅን። ሎይድ ዊሊንግተን በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ከእናቱ፣ ከአባቱ እንዲሁም ከእህቶቹ ጋር ያስተዋወቀኝ ሲሆን በሌላ ጊዜም ክራይስትቸርች ወደሚገኘው ቤታቸው አብረን ሄደናል።

የሥራችን መታገድ

ቅዳሜ ጥር 18, 1941 የመንግሥት ባለ ሥልጣናት የማኅበሩን ንብረት ለመውረስ ወደ ስድስት ገደማ የሚደርሱ ጥቋቁር ሊሞዚን መኪናዎች እየነዱ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው መጡ። ወደ ዋናው ቤቴል መግቢያ በር ላይ በምትገኝ አነስተኛ እንግዳ መቀበያ ክፍል ውስጥ እሠራ ስለነበር በመጀመሪያ ያየኋቸው እኔ ነኝ። ከ18 ሰዓታት ገደማ በፊት እገዳ እንደሚጣል ሰምተን ስለነበር በቅርንጫፍ ቢሮው ውስጥ የነበሩ ጽሑፎችን በሙሉ ማለት ይቻላል እንዲሁም ፋይሎች ወደ ሌላ ቦታ ተወስደው ነበር። በቀጣዩ ሳምንት ሎይድን ጨምሮ አምስት የቤቴል ቤተሰብ አባላት ታሰሩ።

የታሰሩት ወንድሞች ከምንም ነገር በላይ መንፈሳዊ ምግብ እንደሚፈልጉ አውቅ ነበር። ሎይድን ለማበረታታት “የፍቅር ደብዳቤዎች” ልጽፍለት ወሰንኩ። የፍቅር ደብዳቤ አስመስዬ ከጀመርኩ በኋላ ሙሉውን መጠበቂያ ግንብ እገለብጥለትና በመጨረሻ ላይ ከፍቅረኛህ ብዬ ፈርሜበት እልክለት ነበር። ሎይድ አራት ወር ከአሥራ አምስት ቀን ከታሰረ በኋላ ተፈታ።

ጋብቻ እና የሙሉ ጊዜ አገልግሎት

በ1940 የሎይድ እናት አውስትራሊያን ለመጎብኘት ሲመጡ ለመጋባት እንዳሰብን ነገራቸው። የዚህ የነገሮች ሥርዓት መጨረሻ መቅረቡን በመግለጽ እንዳያገባ መከሩት። (ማቴዎስ 24:​3-14) ለማግባት ማሰቡን ለጓደኞቹም ነገራቸው። ሆኖም ስለጋብቻ ባነሳ ቁጥር እንዳያገባ ይመክሩት ነበር። በመጨረሻ በየካቲት 1942 አንድ ቀን ሎይድ ለማንም ሳይናገር እኔንና ለሌላ ሰው እንዳይናገሩ ቃል ያስገባቸውን አራት ምሥክሮች ወደ ማዘጋጃ ቤት ይዞን ሄዶ ተጋባን። በወቅቱ በአውስትራሊያ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች የጋብቻ ሥነ ሥርዓቶችን እንዲያስፈጽሙ የሚያስችል ዝግጅት አልነበረም።

ተጋብተን በቤቴል ማገልገላችንን መቀጠል ስለማንችል በልዩ አቅኚነት መሥራት እንፈልግ እንደሆነ ተጠየቅን። ፈቃደኞች በመሆናችን ዋገ ዋገ በምትባል የገጠር ከተማ እንድናገለግል ተመደብን። በስብከት ሥራችን ላይ የተጣለው እገዳ ገና ስላልተነሳና ምንም ዓይነት የገንዘብ ድጋፍ ስላልነበረን ሸክማችንን በይሖዋ ላይ መጣል ነበረብን።​—⁠መዝሙር 55:​22

ባለ ሁለት ፔዳል ብስክሌት እየነዳን ወደ ገጠራማ ክልሎች እንሄድና በጣም ጥሩ ሰዎችን አግኝተን ረጅም ውይይት እናደርግ ነበር። ብዙዎቹ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ የምናቀርብላቸውን ግብዣ አይቀበሉም። ይሁን እንጂ ሥራችንን በጣም የወደደ አንድ ባለ ሱቅ በየሳምንቱ ፍራፍሬና አትክልት ይሰጠን ነበር። በዋገ ዋገ ስድስት ወር ከቆየን በኋላ እንደገና ወደ ቤቴል ተጠራን።

የቤቴል ቤተሰብ ግንቦት 1942 ስትራትፊልድ የሚገኘውን ቢሮ ለቅቆ ወደ የግል መኖሪያ ቤቶች ተዛወረ። እንዳይያዙ በመፍራት ቤተሰቡ በየሁለት ሳምንቱ ለማለት ይቻላል ቤት ይቀያይር ነበር። እኔና ሎይድ በነሐሴ ወደ ቤቴል ስንመለስ አንደኛው ቤት ውስጥ ነበሩ። ቀን ቀን በድብቅ በሚንቀሳቀስ በአንድ የማተሚያ ማሽን ላይ እንድንሠራ ተመደብን። በመጨረሻ በሥራችን ላይ የተጣለው እገዳ ሰኔ 1943 ተነሳ።

ለሚስዮናዊ አገልግሎት መዘጋጀት

በሚያዝያ 1947 ኒው ዮርክ ዩ ኤስ ኤ ሳውዝ ላንሲንግ በሚገኘው የጊልያድ መጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ለመካፈል የማመልከቻ ቅጽ ተላከልን። በመሃሉ በአውስትራሊያ የሚገኙ ጉባኤዎችን በመጎብኘት በመንፈሳዊ እንድናበረታቸው ተመድበን ነበር። ከጥቂት ወራት በኋላ በ11ኛው የጊልያድ ክፍል እንድንማር ተጠራን። አንዳንድ ጉዳዮቻችንን መልክ ለማስያዝና ዕቃችንን ለማሰናዳት የሦስት ሳምንት ጊዜ ነበረን። ቤተሰቦቻችንንና ጓደኞቻችንን ተሰናብተን ታኅሣሥ 1947 ከእኛ ጋር ለትምህርት ቤቱ ከተጋበዙ ሌሎች 15 የአውስትራሊያ ምሥክሮች ጋር ወደ ኒው ዮርክ አቀናን።

በጊልያድ ትምህርት ቤት የቆየንባቸው ጥቂት ወራት ሳይታወቁን አለፉና በሚስዮናዊነት እንድናገለግል ጃፓን ተመደብን። ወደ ጃፓን ለመሄድ የሚያስችለውን ፈቃድ ለማግኘት ጊዜ ስለሚወስድ ሎይድ እዚያው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ እንዲያገለግል ተመደበ። እንድንጎበኛቸው የተመደብንባቸው ጉባኤዎች ከሎስ አንጀለስ አንስቶ እስከ ሜክሲኮ ድንበር ይደርሱ ነበር። መኪና ስላልነበረን የይሖዋ ምሥክሮች በየሳምንቱ ከአንዱ ጉባኤ ወደሚቀጥለው ጉባኤ ያጓጉዙን ነበር። ሰፊ ክልል አቅፎ የነበረው ያ ወረዳ በአሁኑ ጊዜ እያንዳንዳቸው አሥር የሚያክሉ ወረዳዎችን የያዙ ሦስት የእንግሊዝኛና ሦስት የስፓንኛ ተናጋሪ አውራጃዎች ያቀፈ ሆኗል!

በድንገት፣ ጥቅምት 1949 ቀድሞ ወታደሮች ታመላልስ በነበረች መርከብ ተሳፍረን ወደ ጃፓን ተጓዝን። የመርከቢቱ አንደኛው ወገን ለወንዶች ሌላኛው ደግሞ ለሴቶችና ለሕፃናት የተመደበ ነበር። ዮኮሃማ ልንደርስ አንድ ቀን ሲቀረን ታይፉን የተባለ ከባድ አውሎ ነፋስ አጋጠመን። አውሎ ነፋሱ ዳመናውን ስላባረረው በማግሥቱ ጠዋት ጥቅምት 31 ፀሐይ ስትወጣ የፉጂ ተራራ ግርማ ሞገስ ተላብሶ ወለል ብሎ ታየን። እንዴት ባለ አስደሳች ቀን ወደ አዲሱ ምድባችን ደረስን!

ከጃፓናውያን ጋር መሥራት

ወደ መውረጃው ስንቃረብ ጥቁር ፀጉር ያላቸው ብዙ ሰዎች አየን። ገና ከሩቅ ከፍተኛ የኳኳታ ድምፅ ስንሰማ ‘ሰዎቹ እንዴት ይንጫጫሉ!’ ብለን አስበን ነበር። እያንዳንዱ ሰው ያደረገው የእንጨት ሶል ያለው ጫማ ከእንጨቱ ወለል ጋር ሲገናኝ ይንኳኳል። የዚያን ዕለት ዮኮሃማ ካደርን በኋላ ባቡር ተሳፍረን ሚስዮናዊ ሆነን ወደተመደብንበት ወደ ኮቤ አቀናን። አብሮን ጊልያድ የተማረውና ጥቂት ወራት ቀደም ብሎ ጃፓን የደረሰው ዳን ሃስለት እዚያ የሚስዮናውያን ቤት ተከራይቶ ነበር። ቤቱ የሚያምር፣ ትልቅ፣ በምዕራባውያን የቤት አሠራር የተሠራና ባለ ሁለት ፎቅ ሕንፃ ሲሆን ውስጡ ግን ወና ነበር!

እንደ ፍራሽ እንዲሆነን ግቢው ውስጥ የበቀለውን ረጃጅም ሣር አጭደን ወለሉ ላይ አነጠፍን። በየሻንጣዎቻችን ከያዝናቸው ንብረቶች በስተቀር አንዳች ሳይኖረን የሚስዮናዊነትን ሕይወት እንዲህ ባለ ሁኔታ ጀመርን። ቤቱን ለማሞቅና ምግብ ለማብሰል የሚረዳን ሂባቺ የሚባል አነስተኛ የከሰል ምድጃ አገኘን። ሎይድ አንድ ቀን ማታ ፔርሲ እና ኢልማ ኢዝሎብ የተባሉ ሚስዮናውያን ራሳቸውን ስተው አገኛቸው። መስኮቶቹን ከፋፍቶ ንጹህና ቀዝቃዛ አየር እንዲገባ በማድረግ ነፍስ እንዲዘሩ አደረጋቸው። እኔም አንድ ቀን በከሰል ምድጃ ላይ ምግብ እያበሰልኩ እያለሁ ሞቼ ነበር። ከአንዳንድ ነገሮች ጋር መለማመድ ጊዜ ይወስዳል!

ለቋንቋው ቅድሚያውን በመስጠት ለአንድ ወር ያህል በቀን 11 ሰዓት ጃፓንኛ አጠናን። ከአንድ ወር በኋላ ለመግቢያ የሚሆን አንድ ወይም ሁለት ዓረፍተ ነገር በወረቀት ላይ ጽፈን አገልግሎት ጀመርን። አገልግሎት በጀመርኩበት በመጀመሪያው ዕለት በደግነት ያነጋገረችኝን ሚዮ ታካጂ የምትባል ተወዳጅ ሴት አገኘሁ። ተመላልሶ መጠየቅ በማደርግላት ጊዜ በጥናቷ እስክትገፋ ድረስ የጃፓንኛ/እንግሊዝኛ መዝገበ ቃላት እየተጠቀምን ለመግባባት ጥረት እናደርግ ነበር። እንዲሰፋ የተደረገው የጃፓን ቅርንጫፍ ቢሮ በ1999 ለአምላክ አገልግሎት የተወሰነ ዕለት ከሚዮ እና ቀደም ሲል ካስጠናኋቸው ብዙ ተወዳጅ ሰዎች ጋር እንደገና ተገናኘን። ከሃምሳ ዓመታት በኋላ እንኳ ይሖዋን ለማገልገል አቅማቸው የሚፈቅድላቸውን ያህል መንግሥቱን በቅንዓት እያወጁ ነው።

ሚያዝያ 1, 1950 በኮቤ 180 የሚያክሉ ሰዎች በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝተው ነበር። በጣም የሚገርመው ነገር በማግሥቱ ጠዋት 35 ሰዎች በመስክ አገልግሎት ለመካፈል መጡ። እያንዳንዱ ሚስዮናዊ ሦስት ወይም አራት አዲስ ሰው ይዞ አገልግሎት ወጣ። የቤት ባለቤቶች ያነጋግሩ የነበረው ቋንቋውን በደንብ የማላውቀውን እኔን ሳይሆን አብረውኝ የሄዱ በመታሰቢያው በዓል ላይ የተገኙ ጃፓናውያንን ነበር። ስለምን እንደሚነጋገሩ ባላውቅም እነርሱ ውይይታቸውን አያቆሙም። በጣም ደስ የሚለኝ ነገር ከእነዚህ አዳዲስ ሰዎች አንዳንዶቹ በእውቀት አድገው እስከ አሁን በስብከቱ ሥራ እየተካፈሉ ነው።

አስደሳችና አርኪ የሥራ ምድቦች

በኮቤ እስከ 1952 ድረስ በሚስዮናዊነት ከሠራን በኋላ ሎይድ የቅርንጫፍ ቢሮውን በበላይነት እንዲያስተዳድር ኃላፊነት ስለተሰጠው ቶኪዮ ተመደብን። ከጊዜ በኋላ በሥራ ምክንያት በመላው ጃፓንና ወደ ሌሎች አገሮች ይጓዝ ጀመር። አንድ ጊዜ ናታን ኤች ኖር ከዋናው መሥሪያ ቤት ወደ ቶኪዮ በመጣ ጊዜ “በነገራችን ላይ ባለቤትሽ በሚቀጥለው የዞን ጉብኝቱ የት እንደሚሄድ ታውቂያለሽ? ወደ አውስትራሊያና ወደ ኒው ዚላንድ ነው” አለኝ። አክሎም “ወጪሽን የምትሸፍኚ ከሆነ አብረሽው መሄድ ትችያለሽ” አለኝ። እንዴት ደስ የሚል ነገር ነው! የሚገርመው ከአገራችን ከወጣን ዘጠኝ ዓመት ሆኖናል።

ወዲያው ለቤተሰቦቻችን ደብዳቤ ጻፍንላቸው። እናቴ የአውሮፕላን ትኬቴን ቻለችኝ። እኔና ሎይድ በተመደብንባቸው ቦታዎች ላይ ሥራ ይበዛብን ስለነበረ እንዲሁም ገንዘብ ስላልነበረን ቤተሰቦቻችንን የምንጠይቅበት አጋጣሚ አልነበረንም። ስለዚህ ይህ የጸሎቴ መልስ ሆነ። ለመገመት እንደምትችሉት እናቴ እኔን በማየቷ በጣም ተደስታለች። “እኔ ገንዘብ አጠራቅምልሽና በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ትመጫለሽ” ብላኝ ነበር። እንዲህ ተባብለን የተለያየን ቢሆንም የሚያሳዝነው በቀጣዩ ሐምሌ ወር አረፈች። በአዲሱ ዓለም ውስጥ ዳግም የምንገናኝ መሆኑ ምንኛ አስደሳች ነው!

እስከ 1960 ድረስ የሥራ ምድቤ በሚስዮናዊነት ማገልገል ብቻ የነበረ ሲሆን ከዚያ በኋላ ግን “ከዛሬ ጀምሮ ለመላው የቤቴል ቤተሰብ አባላት ልብስ እንድታጸጂና እንድትተኩሺ ዝግጅት ተደርጓል” የሚል ደብዳቤ ደረሰኝ። በወቅቱ የቤቴል ቤተሰብ አባላት አሥራ ሁለት አካባቢ ስለነበርን ከሚስዮናዊነት በተጨማሪ ይህንን ሥራ ማከናወን እችል ነበር።

በ1962 በጃፓናውያን ባህላዊ ቤት አሠራር የተሠራው ቤታችን ፈርሶ ባለ ስድስት ፎቅ አዲስ የቤቴል ቤት በቀጣዩ ዓመት ተጠናቀቀ። አዳዲስ ወጣት የቤቴል ወንድሞች ክፍላቸውን ንጹሕና ሥርዓታማ አድርገው እንዲይዙ እንድረዳ ተመደብኩ። እንደባህል ሆኖ ጃፓን ውስጥ ወንዶች የቤት ውስጥ ሥራ መሥራት አይማሩም። ትኩረት የሚሰጠው ለትምህርታቸው ስለሆነ ሁሉንም ነገር እናታቸው ትሠራላቸዋለች። ብዙም ሳይቆይ እኔ እናታቸው እንዳልሆንኩ ተረዱ። ከጊዜ በኋላ ብዙዎቹ እድገት አድርገው በድርጅቱ ውስጥ አዳዲስ የኃላፊት ቦታዎችን ተረክበዋል።

ከፍተኛ ሙቀት ባለበት በአንድ የበጋ ቀን አንዲት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ቅርንጫፍ ቢሮውን ስትጎበኝ የገላ መታጠቢያ ክፍሎቹን በብሩሽ እየፈተግኩ ሳጸዳ አየችኝ። “ይህን ሥራ የምትሠራልሽን ሠራተኛ ልቀጥርልሽ እንደምፈልግ እባክሽ ለኃላፊው ንገሪው” አለችኝ። ስለ መልካም አሳቢነቷ እንደማደንቅ ከነገርኳት በኋላ በይሖዋ ድርጅት ውስጥ የሚሰጠኝን ማንኛውንም ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ እንደሆንኩ ገለጽኩላት።

ብዙም ሳይቆይ እኔና ሎይድ በጊልያድ 39ኛ ክፍል እንድንማር ጥሪ ቀረበልን! በ1964 በ46 ዓመቴ እንደገና ትምህርት ቤት መግባት እንዴት ያለ አስደሳች መብት ነው! ትምህርቱ በተለይ የተዘጋጀው በቅርንጫፍ ቢሮዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ኃላፊነታቸውን በሚገባው እንዲወጡ ለመርዳት ነበር። አሥር ወር ከተማርን በኋላ እዚያው ጃፓን ተመደብን። በዚህ ጊዜ በጃፓን ከ3, 000 የሚበልጡ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ነበሩ።

ፈጣን እድገት በመታየቱ በ1972 የምሥክሮች ቁጥር ከ14, 000 በላይ የደረሰ ሲሆን በደቡብ ቶኪዮ በናሙዙ ባለ አምስት ፎቅ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ ተገንብቶ ነበር። የፉጂ ተራራ ከዚህ ቦታ ሆኖ ሲታይ በጣም ያስደስታል። አዲስ የመጡት ግዙፍ የማተሚያ ማሽኖች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከአንድ ሚልዮን የሚበልጡ የጃፓንኛ መጽሔቶችን ያትሙ ጀመር። ሆኖም ከፊታችን አንድ ለውጥ ይጠብቀን ነበር።

በ1974 መገባደጃ ላይ ሎይድ ብሩክሊን ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የአስተዳደር አካል አባል ሆኖ እንዲያገለግል የሚገልጽ ደብዳቤ ደረሰው። በመጀመሪያ ‘በቃ እኔና ሎይድ መለያየታችን ነው ማለት ነው። ያም ሆነ ይህ ሎይድ ሰማያዊ ተስፋ ስላለውና እኔ ደግሞ ምድራዊ ተስፋ ስላለኝ ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ መለያየታችን እንደሆነ አይቀርም። እንግዲህ ሎይድ እኔን ጥሎ ወደ ብሩክሊን መሄድ ሊኖርበት ይችላል ማለት ነው’ ብዬ አስቤ ነበር። ሆኖም ብዙም ሳይቆይ አስተሳሰቤን አስተካክዬ በመጋቢት 1975 በፈቃደኛነት ከሎይድ ጋር ወደ ብሩክሊን ሄድኩ።

በዋናው መሥሪያ ቤት ያገኘናቸው በረከቶች

ሎይድ ወደ ብሩክሊን ይሂድ እንጂ ልቡ ጃፓን በመቅረቱ ሁልጊዜ የሚያወራው ጃፓን እያለን ስላጋጠሙን ነገሮች ነው። ሆኖም ልባችንን ለማስፋት የሚያስችሉ አጋጣሚዎች ተከፍተውልናል። ሎይድ ባለፉት 24 ዓመታት ጊዜ ውስጥ በመላው ዓለም መጓዝ በሚጠይቀው በዞን የበላይ ተመልካችነት በጣም ብዙ ያገለገለ ሲሆን እኔም በዓለም ዙሪያ ብዙ ጊዜያት አብሬው ሄጃለሁ።

በሌሎች አገሮች የሚኖሩ ክርስቲያን ወንድሞችን መጎብኘት መቻሌ ብዙዎቹ በምን ዓይነት ሁኔታዎች ውስጥ እየኖሩ ሥራቸውን እንደሚያከናውኑ አይቼ እንዳደንቅ ረድቶኛል። በሰሜን አፍሪካ ያገኘኋት አንዲት የአሥር ዓመት ልጅ ፈጽሞ አትረሳኝም። የአምላክን ስም በጣም ስለምትወድድ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት አንድ ሰዓት ተኩል በእግሯ ትጓዛለች። ኢንቴሊያ ከቤተሰቦቿ ከፍተኛ ስደት ቢደርስባትም ራሷን ለይሖዋ ወሰነች። አንድ ጊዜ እሷ ያለችበትን ጉባኤ ስንጎበኝ በተናጋሪው አናት ትክክል ከተሰቀለው በጣም ደብዛዛ ብርሃን ካለው አምፑል በስተቀር ሌላ መብራት ስላልነበረ የመሰብሰቢያ ቦታው ጨለማ ውጦት ነበር። እንደዚያ ባለ ጨለማ ውስጥ ወንድሞችና እህቶች በጣም ደስ የሚል መዝሙር ሲዘምሩ መስማት የሚያስገርም ነበር።

በሕይወታችን ውስጥ ከፍተኛ ግምት የምንሰጠው አጋጣሚ የተከሰተው እኔና ሎይድ ታኅሣሥ 1998 ኩባ በተደረገው “የአምላክ የሕይወት መንገድ” አውራጃ ስብሰባ ላይ በተገኘን ጊዜ ነበር። ወንድሞችና እህቶች ብሩክሊን ከሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት አንዳንዶች መጥተው ስለጎበኟቸው አድናቆታቸውንና ደስታቸውን ሲገልጹ በመስማታችን ምንኛ ተደስተን ነበር! ለይሖዋ ከፍተኛ የውዳሴ ድምፅ በቅንዓት ከሚያሰሙ ተወዳጅ ወንድሞችና እህቶች ጋር የመተዋወቅ አጋጣሚ አግኝቻለሁ።

ከአምላክ ሕዝቦች ጋር በአንድነት መኖር

የትውልድ አገሬ አውስትራሊያ ቢሆንም የይሖዋ ድርጅት በሚልከኝ በማንኛውም ቦታ የማገኛቸውን ሰዎች አፈቅራለሁ። በጃፓንም የሆነው ይኸው ሲሆን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከ25 ለሚበልጡ ዓመታት ስኖር ያጋጠመኝም ተመሳሳይ ነው። ባለቤቴን በሞት ሳጣ ወደ አእምሮዬ የመጣው ወደ አውስትራሊያ መመለስ ሳይሆን ይሖዋ በመደበኝ ቦታ ይኸውም በብሩክሊን መቆየት ነው።

አሁን ወደ 80ዎቹ ገብቻለሁ። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለ61 ዓመታት ካገለገልኩ በኋላም እንኳ ይሖዋ እዚህ ቦታ ታስፈልጊያለሽ በሚለኝ በማንኛውም ቦታ እሱን ለማገልገል ፈቃደኛ ነኝ። ይሖዋ በእርግጥም እንክብካቤ አድርጎልኛል። ይሖዋን ከሚያፈቅር ተወዳጅ የትዳር ጓደኛዬ ጋር 57 ዓመታት አብሬ በመኖሬ በጣም ተጠቅሜያለሁ። ይሖዋ ሁላችንንም መባረኩን እንደሚቀጥል እርግጠኛ ነኝ። እንዲሁም የሠራነውንና ለስሙም ያሳየነውን ፍቅር እንደማይረሳ አውቃለሁ።​—⁠ዕብራውያን 6:​10

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የጥቅምት 1, 1999 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 16 እና 17⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1956 ከእናቴ ጋር

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1950ዎቹ መባቻ ላይ ከሎይድና በጃፓን ከነበረ አንድ የአስፋፊዎች ቡድን ጋር

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጃፓን ከመጀመሪያዋ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዬ ከሚዮ ታካጂ ጋር በ1950ዎቹ መጀመሪያ እና በ1999

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጃፓን ከሎይድ ጋር መጽሔት ስናበረክት