የመንግሥቱን በረከቶች መውረስ ትችላለህ
የመንግሥቱን በረከቶች መውረስ ትችላለህ
ክርስቲያኑ ሐዋርያ ጳውሎስ በዘመኑ የነበሩትን ዋና ዋና ቋንቋዎች አቀላጥፎ ይናገር ነበር። ጳውሎስ በዛሬው ጊዜ ከዩኒቨርሲቲ ትምህርት ጋር ሊመጣጠን የሚችል ትምህርት ቀስሟል። አንድ የሮማ ዜጋ የሚያገኛቸው ጥቅሞችና መብቶች ሁሉ ነበሩት። (ሥራ 21:37-40፤ 22:3, 28) እነዚህ ሁሉ አጋጣሚዎች ጳውሎስን ሃብታምና ታዋቂ ሊያደርጉት ይችሉ ነበር። ሆኖም ጳውሎስ እንደሚከተለው ሲል ተናግሯል:- “ለእኔ ረብ የነበረውን ሁሉ ስለ ክርስቶስ እንደ ጉዳት ቈጥሬዋለሁ . . . ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ . . . ሁሉን እንደ ጉድፍ እቈጥራለሁ።” (ፊልጵስዩስ 3:7, 8) ጳውሎስ እንዲህ ብሎ የተናገረው ለምንድን ነው?
ቀድሞ የጠርሴሱ ሳውል በሚል መጠሪያና ‘በመንገድ ያሉትን’ በማሳደድ ይታወቅ የነበረው ጳውሎስ ከሞት የተነሳውንና ክብር የተላበሰውን ኢየሱስን ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከተመለከተ በኋላ አማኝ ሆነ። (ሥራ 9:1-19) ጳውሎስ ወደ ደማስቆ እየተጓዘ ሳለ በመንገድ የገጠመው ይህ ሁኔታ ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲህ ወይም ክርስቶስ በሌላ አባባል ተስፋ የተደረገበት መንግሥት የወደፊት ገዥ መሆኑን ያላንዳች ጥርጥር አረጋግጦለታል። በተጨማሪም ጳውሎስ ከላይ ከገለጸው ኃይለኛ አነጋገር መረዳት እንደሚቻለው ሁኔታው ሕይወቱን በከፍተኛ ደረጃ ለውጦታል። በሌላ አባባል ጳውሎስ በሃቀኝነት ከልቡ ንስሐ ገብቷል።—ገላትያ 1:13-16
ሥራ 3:19፤ ራእይ 2:5) ጳውሎስ ወደ ደማስቆ እየተጓዘ ሳለ በመንገድ ላይ የገጠመውን ወሳኝ ክስተት እንደ አንድ ስሜት ቀስቃሽ ትዕይንት ወይም እንደ አንድ ሃይማኖታዊ ገጠመኝ ብቻ አድርጎ አልተመለከተውም። ከዚያ ይልቅ ይህ ክስተት ክርስቶስን ሳያውቅ ይመላለስበት የነበረው የቀድሞ ሕይወቱ ከንቱ መሆኑን እንዲገነዘብ ያነቃው ያህል ነበር። ስለ ክርስቶስ ከቀሰመው አዲስ እውቀት ጥቅም ለማግኘት አኗኗሩን በመለወጥ ረገድ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለበትም ተገንዝቧል።—ሮሜ 2:4፤ ኤፌሶን 4:24
መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ንስሐ መግባት” የሚለው ቃል “አስቀድሞ ማወቅ” ከሚለው ቃል በተቃራኒ “ከጊዜ በኋላ ማወቅ” የሚል ፍቺ ካለው የግሪክኛ ቃል በቀጥታ የተተረጎመ ነው። ስለዚህ ንስሐ መግባት ማለት አንድ ሰው የቀድሞ መጥፎ አኗኗሩን እርግፍ አድርጎ ትቶ በአስተሳሰቡ፣ በዝንባሌው ወይም በዓላማው ረገድ የሚያደርገውን ለውጥ ይጨምራል። (በረከት ያስገኘ ለውጥ
ቀደም ሲል ጳውሎስ ስለ አምላክ አብዛኛውን እውቀት ያገኘው አባል ከነበረበት ሃይማኖታዊ ቡድን ማለትም ከፈሪሳውያን ነው። እምነታቸው በርካታ ሰብዓዊ ፍልስፍናዎችንና ወጎችን ያካተተ ነበር። በነበረው ሃይማኖታዊ ጥላቻ ምክንያት የጳውሎስ ቅንዓትና ጥረት የተሳሳተ አቅጣጫ ይዞ ነበር። አምላክን እያገለገለ እንዳለ ሆኖ ቢሰማውም በእርግጥ ከእርሱ ጋር እየተዋጋ ነበር።—ፊልጵስዩስ 3:5, 6
ጳውሎስ ስለ ክርስቶስና እርሱ በአምላክ ዝግጅት ውስጥ ስላለው ሚና ትክክለኛ እውቀት ካገኘ በኋላ ከፊቱ ያለው ምርጫ ሁለት ብቻ እንደሆነ ተገነዘበ። ፈሪሳዊ ሆኖ ሥልጣንና ክብሩን እንደጠበቀ ይቀጥል ወይስ አኗኗሩን ለውጦ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት አስፈላጊውን ሁሉ ያድርግ? ደስ የሚለው ግን ጳውሎስ ትክክለኛ ምርጫ አድርጓል። እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “በወንጌል አላፍርምና፤ አስቀድሞ ለአይሁዳዊ ደግሞም ለግሪክ ሰው፣ ለሚያምኑ ሁሉ የእግዚአብሔር ኃይል ለማዳን ነውና።” (ሮሜ 1:16) ጳውሎስ ስለ ክርስቶስና ስለ መንግሥቱ የሚናገረው ምሥራች ቀናተኛ ሰባኪ ሆኗል።
ከብዙ ዓመታት በኋላ ጳውሎስ ለክርስቲያን ባልንጀሮቹ እንዲህ ብሏቸዋል:- “እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቈጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፤ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ከፍ ከፍ ያለውን የእግዚአብሔርን መጥራት ዋጋ እንዳገኝ ምልክትን እፈጥናለሁ።” (ፊልጵስዩስ 3:13, 14) ጳውሎስ ከአምላክ እንዲርቅ ያደረገውን የአኗኗር ዘይቤ በፈቃደኝነት ትቶ ከአምላክ ዓላማ ጋር የሚስማሙ ግቦችን በሙሉ ልቡ በመከታተሉ ከምሥራቹ ጥቅም አግኝቷል።
አንተስ ምን ምላሽ ትሰጣለህ?
ምናልባትም አንተ የመንግሥቱን ምሥራች የሰማኸው በቅርቡ ይሆናል። ፍጹም በሆነ ገነት ውስጥ ለዘላለም ስለ መኖር የሚናገረው ተስፋ ማራኪ ሆኖ ይታይሃል? ሁላችንም ሰላምና ደህንነት በሰፈነበት ሁኔታ ሥር የመኖር ምኞት በውስጣችን ስላለ ይህ ተስፋ ቢማርክህ ምንም አያስደንቅም። አምላክ በልባችን ውስጥ “ዘላለምነትን” እንዳስቀመጠ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (መክብብ 3:11) ስለዚህ ሰዎች በሰላምና በደስታ ለዘላለም የሚኖሩበትን ጊዜ ተስፋ ማድረጋችን የሚጠበቅ ነገር ነው። የመንግሥቱ ምሥራች የሚናገረውም ይህንኑ ነው።
ሆኖም ይህ ተስፋ እውን እንዲሆንልህ ምርምር በማድረግ የምሥራቹን ምንነት መገንዘብ ይኖርብሃል። ሐዋርያው ጳውሎስ የሚከተለውን ማሳሰቢያ ሰጥቷል:- “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ [ነው]።” (ሮሜ 12:2) በመሆኑም ልክ እንደ ጳውሎስ አንተም እውቀትና ማስተዋል ካገኘህ በኋላ ምርጫ ማድረግ ይኖርብሃል።
በሌላው በኩል የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ የምታምንባቸው አንዳንድ ነገሮች ይኖሩ ይሆናል። ሳውል ሐዋርያው ጳውሎስ ከመባሉ በፊት ስለ አምላክ ፈቃድ የራሱ የሆነ አስተሳሰብ እንደነበረው አስታውስ። ታዲያ አምላክ ተአምራዊ በሆነ ራእይ እንዲገልጥልህ ከመጠበቅ ይልቅ ለምን ጉዳዩን ራስህ አታጤነውም? ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ:- ‘ከሰዎችና ከምድር ጋር በተያያዘ የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ በትክክል አውቃለሁ? የማምንባቸው ነገሮች ትክክል መሆናቸውን ለማረጋገጥ ምን ማስረጃ ማቅረብ እችላለሁ? ያሉኝ ማስረጃዎች በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ብርሃን ሲመረመሩ ትክክለኛ ሆነው ይገኛሉ?’ ሃይማኖታዊ አምነትህን በዚህ መንገድ መመርመርህ ምንም ጉዳት አያስከትልብህም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉን ፈትኑ፤ መልካሙንም ያዙ” በማለት ስለሚመክር እምነትህን በዚህ መንገድ ለመመርመር መፈለግ ይኖርብሃል። (1 ተሰሎንቄ 5:20, 21) ደግሞስ በጣም አስፈላጊ የሆነው ነገር የአምላክን ሞገስ ማግኘቱ አይደለም?—ዮሐንስ 17:3፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4
ሃይማኖታዊ መሪዎች ዘላለማዊ የሆነ የወደፊት ተስፋ እንዳለን ይነግሩን ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ያለው ተስፋ በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ላይ እስካልተመሠረተ ድረስ የአምላክን መንግሥት በረከቶች ሊያስገኝልን አይችልም። ኢየሱስ በዝነኛው የተራራ ስብከቱ ላይ የሚከተለውን ኃይለኛ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል:- “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፣ ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።”—ማቴዎስ 7:21
ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት በረከቶች ለመውረስ የአባቱን ፈቃድ ማድረግ አንደኛው ብቃት እንደሆነ ጠበቅ አድርጎ መናገሩን ልብ በል። በሌላ አባባል ከውጭ ሲታዩ ሃይማኖተኛ መስሎ መታየት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያስገኛል ማለት አይደለም። እንዲያውም ኢየሱስ በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “በዚያ ቀን ብዙዎች:- ጌታ ሆይ፣ ጌታ ሆይ፣ በስምህ ትንቢት አልተናገርንምን፣ በስምህስ አጋንንትን አላወጣንምን፣ በስምህስ ብዙ ተአምራት አላደረግንምን? ይሉኛል። የዚያን ጊዜም:- ከቶ አላወቅኋችሁም፤ እናንተ ዓመፀኞች፣ ከእኔ ራቁ ብዬ እመሰክርባቸዋለሁ።” (ማቴዎስ 7:22, 23) ከዚህ በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው በጣም አስፈላጊ የሆነው ነገር የመንግሥቱን ምሥራች ምንነት በትክክል መገንዘባችንና ከመልእክቱ ጋር ተስማምተን መኖራችን ነው።—ማቴዎስ 7:24, 25
እርዳታ ማግኘት ይቻላል
የይሖዋ ምሥክሮች ከ100 ለሚበልጡ ዓመታት የአምላክን መንግሥት ምሥራች ሲሰብኩ ቆይተዋል። ራሳቸው በሚሰጡት ምሥክርነትና በታተሙ ጽሑፎች አማካይነት ስለ መንግሥቱ፣ መንግሥቱ ስለሚያመጣቸው በረከቶችና እነዚህን በረከቶች ለማግኘት አንድ ሰው ማሟላት ስላለበት ነገር ትክክለኛ እውቀት እንዲቀስሙ በዓለም ዙሪያ የሚገኙትን ሰዎች በመርዳት ላይ ናቸው።
አንተም የይሖዋ ምሥክሮች ለሚሰብኩት መልእክት አዎንታዊ ምላሽ እንድትሰጥ እናበረታታሃለን። ምሥራቹን በመቀበልና ከመልእክቱ ጋር በሚስማማ መንገድ በመኖር አሁን ብቻ ሳይሆን ወደፊት የአምላክ መንግሥት መላውን ምድር በሚገዛበት ወቅት የሚፈስሱትን ታላላቅ በረከቶች መውረስ ትችላለህ።—1 ጢሞቴዎስ 4:8
የአምላክ መንግሥት በረከቶች የሚፈስሱበት ጊዜ በጣም ስለቀረበ አሁኑኑ እርምጃ ውሰድ!
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች ራሳቸው በሚሰጡት ምሥክርነትና በታተሙ ጽሑፎች አማካይነት የአምላክን መንግሥት ምሥራች ይሰብካሉ