የመንግሥቱ ምሥራች ምንድን ነው?
የመንግሥቱ ምሥራች ምንድን ነው?
ባለፈው ዓመት በዓለም ዙሪያ በሚገኙ 235 አገሮች ውስጥ የሚኖሩ 6, 035, 564 ወጣቶችና አረጋውያን ስለ መንግሥቱ ምሥራች ለሌሎች ሰዎች በመንገር 1, 171, 270, 425 ሰዓታት አሳልፈዋል። በአንደበታቸው ከማስረዳታቸውም በላይ ነገሩን ለማስታወቅና ለማብራራት ከ700 ሚልዮን የሚበልጡ ጽሑፎች ለሕዝብ አበርክተዋል። በሺህዎች የሚቆጠሩ የቴፕና የቪዲዮ ካሴቶችም አሰራጭተዋል። ታዲያ ይህ “ነገር” ምንድን ነው?
“ይህ” የአምላክ መንግሥት ምሥራች ነው። በእርግጥም፣ “ይህ የመንግሥት ምሥራች” በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ የዛሬውን ያህል በስፋት የተሰበከበት ወቅት የለም።—ማቴዎስ 24:14
ይህንን ዓለም አቀፍ የስብከትና የማስተማር ሥራ የሚያከናውኑት ራሳቸውን በፈቃደኝነት ያቀረቡ ግለሰቦች ናቸው። ከዓለማዊ አመለካከት አንፃር እነዚህ ግለሰቦች ለሥራው የማይበቁ ሊመስሉ ይችላሉ። ታዲያ ከድፍረታቸውና ከስኬታቸው በስተጀርባ ያለው ነገር ምንድን ነው? ለዚህ በዋነኛነት አስተዋጽኦ ያደረገው ነገር የመንግሥቱ ምሥራች ያለው ኃይል ሲሆን የሰው ዘሮች ስለሚፈስሱላቸው በረከቶች ይናገራል። እነዚህ በረከቶች ሁሉም ሰው ሊያገኛቸው የሚናፍቃቸው እንደ ደስታ፣ ከኢኮኖሚ ችግር መላቀቅ፣ መልካም አስተዳደር፣ ሰላምና ደህንነት ያሉትን አልፎ ተርፎም ብዙ ሰዎች ይሆናል ብለው እንኳን የማይገምቱትን የዘላለም ሕይወት ሳይቀር ያካተቱ ናቸው! ይህ በእርግጥም የሕይወትን ትርጉምና ዓላማ ለማወቅ ለሚፈልጉ ሰዎች ምሥራች ነው። አዎን፣ ለመንግሥቱ ምሥራች እወጃ አዎንታዊ ምላሽ ከሰጠህና ከዚህ ጋር የሚስማማ እርምጃ ከወሰድክ እነዚህንና ሌሎች ተጨማሪ በረከቶችን ልታገኝ ትችላለህ።
መንግሥቱ ምንድን ነው?
ታዲያ ምሥራች እንደሆነ ተደርጎ የሚሰበከው መንግሥት ምንድን ነው? በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ፤ መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለው እንዲጸልዩለት የተማሩት መንግሥት ነው።—ማቴዎስ 6:9, 10
ይህ ከ2,500 ዓመታት በፊት ዕብራዊው ነቢይ ዳንኤል “በእነዚያም ነገሥታት ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት ያስነሳል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ ትፈጫቸዋለች፣ ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች” በማለት የተናገረለት መንግሥት ነው።—ዳንኤል 2:44
ስለዚህ ምሥራቹ አምላክ አሁን በምድር ላይ ያለውን ክፋት አስወግዶ ሰላም የሰፈነበት አገዛዝ ለማምጣት ስለሚጠቀምበት መንግሥት ወይም መስተዳድር የሚናገር ነው። ይህ መንግሥት ፈጣሪ ለሰው ዘሮችና ለምድር የነበረውን የመጀመሪያ ዓላማ እውን ያደርጋል።—ዘፍጥረት 1:28
“መንግሥተ ሰማያት ቀርባለች”
የመንግሥቱን ምሥራች ለመጀመሪያ ጊዜ ለሕዝብ ያወጀው የዛሬ 2,000 ዓመት ገደማ በአለባበሱና በባሕርይው የብዙዎችን ትኩረት የሳበውና ውስን የአምላክ አገልጋይ የነበረው መጥምቁ ዮሐንስ ሲሆን ይህ ሰው ዘካርያስ የተባለ የአንድ አይሁዳዊ ካህንና ኤልሳቤጥ የተባለች ሚስቱ ልጅ ነው። ዮሐንስ ከግመል ፀጉር የተሠራ ልብስ ይለብስና ጥላ እንደሆነለት እንደ ነቢዩ ኤልያስ በወገቡ ላይ ከቆዳ የተሠራ ጠፍር ይታጠቅ ነበር። ይሁን እንጂ የብዙዎችን ትኩረት የሳበው “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” በማለት ያውጅ የነበረው መልእክት ነው።—ማቴዎስ 3:1-6
ዮሐንስን ያዳምጡ የነበሩት ሰዎች እውነተኛውን አምላክ እናመልካለን ይሉ የነበሩት አይሁዳውያን ሲሆኑ ወደ 1,500 ከሚጠጉ ዓመታት በፊት እንደ አንድ ብሔር ሆነው የሕጉን ቃል ኪዳን በሙሴ በኩል ተቀብለው ነበር። ዕጹብ ድንቅ የሆነው ቤተ መቅደስ አሁንም በኢየሩሳሌም ይገኝ የነበረ ሲሆን ሕጉ በሚያዘው መሠረት መሥዋዕቶችም ይቀርቡበት ነበር። አይሁዶች አምልኳቸው በአምላክ ፊት ተቀባይነት እንዳለው አድርገው ያስቡ ነበር።
ዮሐንስን ካዳመጡ በኋላ ግን አንዳንዶቹ አምልኳቸው እነርሱ እንደሚያስቡት እንዳልሆነ መገንዘብ ጀመሩ። የግሪክ ባሕልና ፍልስፍና የአይሁድን ሃይማኖታዊ ትምህርት በክሎት ነበር። አምላክ በሙሴ በኩል የሰጣቸው ሕግ ሰው ሠራሽ በሆኑ እምነቶችና ወጎች ከመበረዙም በላይ ዋጋ እንዲያጣ ተደርጎ ነበር። (ማቴዎስ 15:6) ደንዳናና ምሕረተ ቢስ በሆኑት ሃይማኖታዊ መሪዎች በተሳሳተ መንገድ ይመራ የነበረው አብዛኛው ሕዝብ አምላክን ተቀባይነት ባለው መንገድ ማምለኩን አቁሞ ነበር። (ያዕቆብ 1:27) በአምላክና በሕጉ ቃል ኪዳን ላይ ስለሠሩት ኃጢአት ንስሐ መግባት ነበረባቸው።
በወቅቱ ብዙዎቹ አይሁዳውያን ቃል የተገባለትን መሲህ ወይም ክርስቶስ መገለጥ ይጠባበቁ ነበር። እንዲያውም አንዳንዶቹ ዮሐንስን “ይህ ክርስቶስ ይሆንን?” ብለው አስበው ነበር። ይሁን እንጂ ዮሐንስ መሲሑ እርሱ እንዳልሆነና ከዚያ ይልቅ ‘የጫማውን ጠፍር መፍታት የማይገባኝ’ በማለት ወደ አንድ ሌላ ሰው መርቷቸዋል። (ሉቃስ 3:15, 16) ዮሐንስ ኢየሱስን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ሲያስተዋውቅ “እነሆ፣ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” በማለት ተናግሯል!—ዮሐንስ 1:29
ዮሐንስ ሕዝቡን ወደ ሕይወትና ወደ ደስታ የሚወስዳቸውን መንገድ እየጠቆማቸው ወይም በሌላ አባባል ‘የዓለምን ኃጢአት ወደሚያስወግደው’ ወደ ኢየሱስ እየመራቸው ስለነበር ይህ በእርግጥም ምሥራች ሊባል ይችላል። ከአዳምና ከሔዋን የተገኘው መላው የሰው ዘር ኃጢአትንና ሞትን ወርሷል። ሮሜ 5:19 እንዲህ ይላል:- “በአንዱ ሰው [በአዳም] አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደሆኑ፣ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ [በኢየሱስ] መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።” ኢየሱስ ልክ ለመሥዋዕት እንደሚቀርብ በግ ‘ኃጢአትን በማስወገድ’ የሰው ልጆች ከተዘፈቁበት አሳዛኝ ሁኔታ እንዲወጡ ያደርጋል። መጽሐፍ ቅዱስ “የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው” በማለት ይናገራል።—ሮሜ 6:23
በማርቆስ 1:14, 15 ላይ የሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “ዮሐንስም አልፎ ከተሰጠ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና:- ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ እያለ ወደ ገሊላ መጣ።”
ፍጹም የነበረውና እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው ኢየሱስ ምሥራቹን የመስበኩን ሥራ ተያያዘው።ለኢየሱስ መልእክት አዎንታዊ ምላሽ የሰጡና በምሥራቹ ያመኑ ሁሉ እጅግ ተባርከዋል። ዮሐንስ 1:12 እንዲህ ይላል:- “ለተቀበሉት [ኢየሱስን] ሁሉ ግን፣ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው።” የእግዚአብሔር ልጆች በመሆን የዘላለም ሕይወት ሽልማት ለማግኘት ይጠባበቃሉ።—1 ዮሐንስ 2:25
ይሁን እንጂ የመንግሥቱን በረከቶች የመውረስ መብት ያገኙት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ሰዎች ብቻ አይደሉም። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው በዛሬው ጊዜ የአምላክ መንግሥት ምሥራች በመላው ምድር ላይ በመታወጅና ስለ መንግሥቱ ትምህርት በመሰጠት ላይ ነው። ስለዚህ አሁንም ቢሆን የመንግሥቱን በረከቶች ማግኘት ይቻላል። እነዚህን በረከቶች ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርብሃል? የሚቀጥለው ርዕስ ይህንን ያብራራል።