በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አሉታዊ ስሜቶችን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?

አሉታዊ ስሜቶችን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?

አሉታዊ ስሜቶችን መቋቋም የሚቻለው እንዴት ነው?

● አሳፍ እንዲህ ሲል የተሰማውን ምሬት ገልጿል:- “በውኑ ልቤን በከንቱ አጸደቅሁ፣ እጆቼንም በንጽሕና በከንቱ አጠብሁ። ሁልጊዜም የተገረፍሁ ሆንሁ፣ መሰደቤም በማለዳ ነው።”—መዝሙር 73:​13, 14

● ባሮክ እንዲህ በማለት የተሰማውን ሐዘን ገልጿል:- “እግዚአብሔር በሕመሜ ላይ ኀዘንን ጨምሮብኛልና ወዮልኝ! በልቅሶዬ ጩኸት ደክሜአለሁ፣ ዕረፍትንም አላገኘሁም።” ​—⁠ኤርምያስ 45:​3

● ኑኃሚን እንዲህ ስትል የተሰማትን ምሬት ገልጻለች :- “ሁሉን የሚችል አምላክ አስመርሮኛልና ማራ በሉኝ እንጂ ኑኃሚን አትበሉኝ። በሙላት ወጣሁ፣ እግዚአብሔርም ወደ ቤቴ ባዶዬን መለሰኝ፤ እግዚአብሔር አዋርዶኛልና፣ ሁሉንም የሚችል አምላክ አስጨንቆኛልና ኑኃሚን ለምን ትሉኛላችሁ?” ​—⁠ሩት 1:​20, 21

መጽሐፍ ቅዱስ አልፎ አልፎ በተስፋ መቁረጥ ስሜት ስለተዋጡ ታማኝ የይሖዋ አምላኪዎች የሚናገሩ ብዙ ምሳሌዎች ይዟል። ሁላችንም ፍጽምና የጎደለን ሰዎች ስለሆንን አልፎ አልፎ እንዲህ ዓይነቱ ስሜት ሊሰማን ይችላል። አንዳንዶቻችን በአሳዛኝ ሁኔታዎች ውስጥ አልፈን ሊሆን ስለሚችል ከሌሎች በበለጠ እንዲህ ያለው ስሜት ሊሰማን አልፎ ተርፎም በተወሰነ መጠን ስለ ራሳችን ብቻ እያሰብን ልንተክዝ እንችላለን።

ይሁን እንጂ እንዲህ ያሉት ስሜቶች ቁጥጥር ካልተደረገባቸው ከሌሎችና ከይሖዋ አምላክ ጋር ያለህን ዝምድና ሊያበላሹብህ ይችላሉ። ስለ ራሷ ችግሮች ብቻ በማሰብ ትተክዝ የነበረች አንዲት ክርስቲያን እንዲህ በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች:- “በጉባኤ ውስጥ ካሉት ጋር ጓደኛ ለመሆን አልበቃም ብዬ አስብ ስለነበር በማኅበራዊ ዝግጅቶች ላይ እንድገኝ የሚቀርቡልኝን ግብዣዎች በሙሉ እሰርዝ ነበር።” እንዲህ ዓይነቱ ስሜት በአንድ ሰው ሕይወት ላይ ሊያስከትል የሚችለው ጉዳት ምንኛ ከባድ ነው! ታዲያ እንደዚህ የመሰሉትን ስሜቶች ለመቋቋም ምን ማድረግ ትችላለህ?

ወደ ይሖዋ ቅረብ

አሳፍ ተሰምቶት የነበረውን ግራ መጋባት ምንም ሳይሸሽግ በመዝሙር 73 ላይ አስፍሯል። እርሱ የሚገኝበትን ሁኔታ የተደላደለ ኑሮ ከሚመሩ ኃጢአተኞች ሁኔታ ጋር ሲያወዳድር የቅንዓት ስሜት አደረበት። አሳፍ አምላክ የለሾቹ ሰዎች ትዕቢተኞችና ዓመፀኞች ቢሆኑም እንኳ ቅጣት እንደማይደርስባቸው ሆኖ ተሰማው። ከዚያም አሳፍ በሕይወቱ ቀና ጎዳና መከተሉ ስለሚያስገኘው ጥቅም ያደረበትን ጥርጣሬ ገለጸ።​—⁠መዝሙር 73:​3-9, 13, 14

አንተስ ልክ እንደ አሳፍ በዓመፅ ድርጊታቸው የሚኩራሩ ሰዎች ስኬት ያገኙ መስለው እንደሚታዩ አስተውለሃልን? አሳፍ የተሰማውን አሉታዊ ስሜት የተቋቋመው እንዴት ነው? እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “አውቅም ዘንድ አሰብሁ፣ ይህ ግን በፊቴ ችግር ነበረ። ወደ እግዚአብሔር መቅደስ እስክገባ ድረስ፣ ፍጻሜያቸውንም እስካስተውል ድረስ።” (መዝሙር 73:​16, 17) አሳፍ በጸሎት ወደ ይሖዋ ዞር በማለት አዎንታዊ እርምጃዎች ወስዷል። ሐዋርያው ጳውሎስ ቆየት ብሎ እንደገለጸው አሳፍ በውስጡ ያለውን “መንፈሳዊ ሰው” በማነቃቃት ‘ፍጥረታዊው ሰው’ ያሳደረበትን ተፅእኖ ለመቋቋም ችሏል። አዲስ መንፈሳዊ ዕይታ በማግኘቱ ይሖዋ ክፋትን እንደሚጠላና የተወሰነው ጊዜ ሲደርስ ኃጢአተኞችን እንደሚያጠፋ ተገንዝቧል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 2:​14, 15

መጽሐፍ ቅዱስ በሕይወት እውነታዎች ላይ እንድታተኩር እንዲረዳህ መፍቀድህ ምንኛ አስፈላጊ ነው! ይሖዋ ኃጢአተኛ ሰዎች የሚያደርጉትን ነገር ሳይመለከት እንደማያልፍ ያሳስበናል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት ያስተምራል:- “አትሳቱ፤ እግዚአብሔር አይዘበትበትም። ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና፣ . . . መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት።” (ገላትያ 6:​7-9) ይሖዋ ኃጢአተኞችን ‘በድጥ ስፍራ አስቀምጧቸዋል። ወደ ጥፋትም ይጥላቸዋል።’ (መዝሙር 73:​18) በመጨረሻ መለኮታዊ ፍትህ ድል ያደርጋል።

ከይሖዋ መንፈሳዊ ማዕድ ሳታቋርጥ መመገብህም ሆነ ከአምላክ ሕዝቦች ጋር መቀራረብህ እምነትህ እንዲጠነክርና የተስፋ መቁረጥን ስሜት ወይም ሌሎች አሉታዊ ስሜቶችን እንድትቋቋም ይረዳሃል። (ዕብራውያን 10:​25) ልክ እንደ አሳፍ አንተም ወደ ይሖዋ በመቅረብ የእርሱን ፍቅራዊ ድጋፍ ማግኘት ትችላለህ። አሳፍ በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “እኔ ግን ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ፣ ቀኝ እጄንም ያዝኸኝ። በአንተ ምክር መራኸኝ፤ ከክብር ጋር ተቀበልኸኝ።” (መዝሙር 73:​23, 24) በልጅነቷ እንግልት የደረሰባት አንዲት ክርስቲያን እህት እነዚህ ቃላት ያዘሉትን ጥበብ ተገንዝባለች። “ከጉባኤው ጋር ተቀራርቤ መኖሬ ሕይወትን ከሌላ አቅጣጫ እንድመለከተው ረድቶኛል። ክርስቲያን ሽማግሌዎች ፖሊሶች ሳይሆኑ አፍቃሪ እረኞች መሆናቸውን በግልጽ መረዳት ችያለሁ” በማለት ተናግራለች። አዎን፣ አፍቃሪ ክርስቲያን ሽማግሌዎች የተጎዳን ስሜት በመጠገን ረገድ ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ።​—⁠ኢሳይያስ 32:​1, 2፤ 1 ተሰሎንቄ 2:​7, 8

የይሖዋን ተግሳጽ ተቀበል

የነቢዩ ኤርምያስ ጸሐፊ የነበረው ባሮክ የተሰጠው ሥራ ባሳደረበት የስሜት ውጥረት ምክንያት ተክዞ ነበር። ሆኖም ይሖዋ በእውነታው ላይ እንዲያተኩር በደግነት ረድቶታል። “ለራስህ ታላቅን ነገር ትፈልጋለህን? በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ፣ እነሆ፣ ክፉ ነገርን አመጣለሁና አትፈልገው፣ ይላል እግዚአብሔር፤ ነገር ግን በሄድህበት ስፍራ ሁሉ ነፍስህን እንደ ምርኮ አድርጌ እሰጥሃለሁ።”​—⁠ኤርምያስ 45:​2-5

ባሮክን ለጭንቀት የዳረጉት ነገሮች በራስ ወዳድነት ስሜት የሚከታተላቸው ግቦቹ እንደሆኑ ይሖዋ በማያሻማ መንገድ ገልጾለታል። ባሮክ ለራሱ ታላቅን ነገር እየፈለገ አምላክ በሰጠው ሥራ ደስታ ሊያገኝ አልቻለም። አንተም የተስፋ መቁረጥን ስሜት በመቋቋም ረገድ ሐሳብን ከሚከፋፍሉ ነገሮች መራቁና ከአምላካዊ ደስታ የሚገኘውን የአእምሮ ሰላም አጥብቆ መያዙ እጅግ ጠቃሚ ሆኖ ታገኘው ይሆናል።​—⁠ፊልጵስዩስ 4:​6, 7

መበለቲቱ ኑኃሚን ባሏና ሁለት ወንዶች ልጆቿ በሞዓብ ሲሞቱ ያደረባት የተስፋ መቁረጥ ስሜት ራሷን ከሌሎች እንድታገል አላደረጋትም። ሆኖም በእርስዋና በሁለቱ ምራቶቿ ላይ የደረሰው መከራ ለተወሰነ ጊዜ በጣም እንድትመረር አድርጓት እንደነበር የሚያሳይ ፍንጭ አለ። ይህንንም ሁለቱ ምራቶቿ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ በነገረቻቸው ጊዜ ከጠቀሰችው መረዳት ይቻላል። “የእግዚአብሔር እጅ በእኔ ወጥቶአልና ከእናንተ የተነሣ እጅግ ተመርሬአለሁ።” እንደገናም ቤተ ልሔም ስትደርስ “ሁሉን የሚችል አምላክ አስመርሮኛልና ማራ [“መራራ”] በሉኝ እንጂ ኑኃሚን [“ደስታዬ”] አትበሉኝ” በማለት ተናግራለች።​—⁠ሩት 1:​13, 20

ሆኖም ኑኃሚን በሐዘን በመዋጥ ራሷን ከይሖዋም ሆነ ከሕዝቦቹ አላገለለችም። በሞዓብ ሳለች ይሖዋ “ሕዝቡን እንደጎበኘ እንጀራም እንደሰጣቸው” ሰማች። (ሩት 1:​6) ለእርሷ ከሁሉ የተሻለው ቦታ በይሖዋ ሕዝቦች መካከል መሆኑን ተገንዝባ ነበር። ኑኃሚን ከምራቷ ከሩት ጋር ወደ ይሁዳ የተመለሰች ሲሆን ሩት የሚቤዣትንና ዋርሳቸው የሆነውን ቦኤዝን እንዴት መቅረብ እንደምትችል ጥንቃቄ የተሞላበት መመሪያ ሰጥታታለች።

ዛሬም በተመሳሳይ የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ታማኝ ግለሰቦች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በሥራ በመጠመድ ያለባቸውን የስሜት ውጥረት በተሳካ ሁኔታ በመቋቋም ላይ ናቸው። ልክ እንደ ኑኃሚን እነርሱም የአምላክን ቃል በየዕለቱ በማንበብ መንፈሳዊ ነገሮችን በትኩረት መከታተላቸውን ቀጥለዋል።

አምላካዊ ጥበብን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች አንድ ሰው ያሉበትን አሉታዊ ስሜቶች በመቋቋም ረገድ ማስተዋል እንዲያገኝ ይረዱታል። አሳፍ ከይሖዋ ቤተ መቅደስ እርዳታ ለማግኘት ጥረት ያደረገ ሲሆን ይሖዋንም በትዕግሥት ተጠባብቋል። ባሮክ ለተሰጠው ምክር አዎንታዊ ምላሽ በመስጠት ቁሳዊ ነገሮች ሐሳቡን እንዳይከፋፍሉበት አድርጓል። ኑኃሚን ወጣቷ ሩትን በእውነተኛው አምላክ አምልኮ ውስጥ ለምታገኘው መብት በማዘጋጀት በይሖዋ ሕዝቦች መካከል በንቃት ተመላልሳለች።​—⁠1 ቆሮንቶስ 4:​7፤ ገላትያ 5:​26፤ 6:​4

ይሖዋ በቡድን እና በግለሰብ ደረጃ ለሕዝቡ በሰጣቸው መለኮታዊ ድሎች ላይ በማሰላሰል አንተም የተስፋ መቁረጥንም ሆነ ሌሎች አሉታዊ ስሜቶችን መቋቋም ትችላለህ። ለዚህም ይሖዋ ለአንተ ቤዛ በማቅረብ ባሳየው ታላቅ የፍቅር መግለጫ ላይ አሰላስል። በክርስቲያናዊ የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ላለው እውነተኛ ፍቅር አድናቆት ይኑርህ። ሕይወትህ ከፊትህ በሚጠብቅህ በአምላክ አዲስ ዓለም ላይ እንዲያተኩር አድርግ። ልክ እንደ አሳፍ አን​ተም “ለእኔ ግን ወደ እግ​ዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል፤ መታመኛዬም እግዚአ​ብሔር ነው” ለማለት ያብቃህ።​—⁠መዝሙር 73:​28