እምነታችን ሲፈተን ብቻችንን አልነበርንም
እምነታችን ሲፈተን ብቻችንን አልነበርንም
ቪኪ ጤናማ፣ ደስ የምትልና ፍልቅልቅ ሕፃን ነበረች። ቪኪ በ1993 የጸደይ ወቅት ስትወለድ ደስታችን ወሰን አልነበረውም። የምንኖረው ደቡባዊ ስዊድን ውስጥ በምትገኝ ትንሽ ከተማ ውስጥ ሲሆን ሕይወት በጣም አስደሳች ነበር።
ይሁን እንጂ ቪኪ አንድ ዓመት ከስድስት ወር ሲሆናት ያ ሁሉ ደስታችን በንኖ ጠፋ። ለተወሰነ ጊዜ ጤና በማጣቷ ወደ ሆስፒታል ወሰድናት። ዶክተሩ ልጃችሁ ሊምፎብላስቲክ ሉኪሚያ የተባለ ነጭ የደም ሴሎችን የሚያጠቃ በሽታ ይዟታል ብሎ ሲነግረን እንዴት እንደ ደነገጥን ፈጽሞ አንረሳውም። ይህ በልጆች ላይ የሚከሰት የካንሰር ዓይነት ነው።
ትንሿ ልጃችን በዚህ ከባድ በሽታ መያዟን አምኖ መቀበል በጣም ከብዶን ነበር። ቪኪ ገና በአካባቢዋ ያሉትን ነገሮች ማስተዋል ከመጀመሯ ልትሞት ነው። ዶክተሩ እኛን ለማጽናናት ሲል በመጠኑም ቢሆን ስኬት ማምጣቱ አስተማማኝ የሆነ ሕክምና ሊያደርግላት እንደሚችል ነገረን። ይህም ብዙ ደም በደም ሥሯ መስጠትን የሚጠይቅ የኬሞቴራፒ ሕክምና ነበር። ይህ ደግሞ ሌላው አስደንጋጭ ነገር ነበር።
እምነታችን ተፈተነ
ልጃችንን በጣም ስለምንወዳት የተሻለ ሕክምና እንድታገኝ እንፈልጋለን። ይሁን እንጂ ደም መውሰድ ፈጽሞ የማይታሰብ ነው። ‘ከደም ራቁ’ ብሎ ክርስቲያኖችን በሚያዘው የአምላክ ቃል ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጽኑ እምነት አለን። (ሥራ 15:28, 29) ደም መውሰድ በራሱ አደጋ እንዳለውም እናውቃለን። በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደም ስለተሰጣቸው ለበሽታና ለሞት ተዳርገዋል። ያለን ብቸኛ አማራጭ ያለ ደም የሚሰጥ የተሻለ ደረጃ ያለው የሕክምና ዓይነት ማግኘት ነበር። ለእምነት የምናደርገው ውጊያ የጀመረው በዚህ መልኩ ነበር።
a ወዲያውም ያለ ደም የኬሞቴራፒ ሕክምና ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነ ሆስፒታልና ዶክተር ለማግኘት በአውሮፓ ወደሚገኙ የተለያዩ ሆስፒታሎች የፋክስ መልእክቶች ተላኩ። እኛን ለመርዳት ክርስቲያን ወንድሞች ያሳዩት ቅንዓትና ፍቅር በጣም የሚያበረታታ ነበር። እምነታችን የገጠመውን ፈተና የተጋፈጥነው ብቻችንን አልነበረም።
ምን ልናደርግ እንችላለን? ስዊድን በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር የሚንቀሳቀሰውን የሆስፒታል መረጃ አገልግሎት ዴስክ እገዛ ጠየቅን።በሰዓታት ጊዜ ውስጥ ሕክምናውን ለመስጠት ፈቃደኛ የሆነ ዶክተርና ሆስፒታል ጀርመን ሆምበርግ/ሳር ውስጥ ተገኘ። ቪኪን ዶክተሩ ፊት ለማቅረብ በቀጣዩ ቀን ወደ ጀርመን እንድንበር ዝግጅት ተደረገ። እዚያ ስንደርስ ሆምበርግ ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ወንድሞችና አንዳንድ ዘመዶቻችን እኛን ለመቀበል በቦታው ተገኝተው ነበር። እንዲሁም የአካባቢውን የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ ወክሎ የመጣ አንድ ወንድም ሞቅ ያለ አቀባበል አደረገልን። ከዚያም አብሮን ሆስፒታል ድረስ በመሄድ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ አድርጎልናል። በማናውቀው አገር እንኳ ሳይቀር ከጎናችን ቆመው ድጋፍ የሚሰጡን መንፈሳዊ ወንድሞች እንዳሉን በማወቃችን ተጽናንተናል።
በሆስፒታል ግራፍ የሚባል ዶክተር ማግኘታችንም ተጨማሪ ማጽናኛ ሆኖልናል። የሰው ችግር የሚገባው ሰው ነው። ቪኪን ያለ ደም ለማከም የቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ቃል ገባልን። በደሟ ውስጥ ያለው የሂሞግሎቢን መጠን ወደ አምስት ግራም በዴሲ ሊትር ዝቅ ቢል እንኳ ሕክምናውን ያለ ደም ለመቀጠል ፈቃደኛ መሆኑን ገለጸልን። በሽታው ቶሎ መታወቁና ቶሎ ወደ ሆስፒታል መምጣቷ ሕክምናው የተሳካ እንዲሆን የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ እንደከፈተ ገለጸልን። በቪኪ ዓይነት ሁኔታ የኬሞቴራፒ ሕክምና ያለ ደም ሲሰጥ ይህ የመጀመሪያው እንደሆነም ሳይሸሽግ ነግሮናል። ዶክተር ግራፍ ቪኪን ለመርዳት ያደረገውን ቁርጥ ውሳኔና ያሳየውን ድፍረት አድንቀናል። ለዚህም በጣም አመስጋኞች ነን።
የገንዘብ ችግር
አሁን ጥያቄው የቪኪን የሕክምና ወጪ መሸፈን የምንችለው እንዴት ነው? የሚለው ነበር። ሁለት ዓመት ለሚፈጀው ለዚህ ሕክምና ወደ 150,000 የሚጠጋ የጀርመን ደች ማርክ እንደሚያስፈልግ ሲነገረን ደነገጥን። ትንሽ እንኳ ወደዚህ መጠን የሚጠጋ ገንዘብ አልነበረንም። ሕክምናው ወዲያው መጀመር ነበረበት። ሕክምናውን ለማግኘት ስንል ስዊድንን ለቅቀን በመምጣታችን ጀርመን ውስጥ ምንም ዓይነት የጤና ኢንሹራንስ አልነበረንም። በጠና የታመመችውን ልጃችንን ለማከም ብቃት ያላቸው የሕክምና ባለሙያዎች ዝግጁ ሆነው ቢጠብቁም ሕክምናውን ለመጀመር የሚያስችል በቂ ገንዘብ ግን አልነበረንም።
ይሁን እንጂ ሆስፒታሉ በቅድሚያ 20, 000 የጀርመን ማርክ ከከፈልንና ቀሪውን ክፍያ ደግሞ እንደምናጠናቅቅ ከፈረምን ሕክምናውን መጀመር እንደሚችል ቃል ገባልን። ያጠራቀምናት ትንሽ ገንዘብ አፍቃሪ ወዳጆችና ዘመዶች ከለገሱት እርዳታ ጋር ተዳምሮ 20,000 የጀርመን ማርክ ለመክፈል ቻልን። ሆኖም የቀረውስ ገንዘብ?
በዚህም ጊዜ ቢሆን ለእምነት በምናደርገው ትግል ብቻችንን አለመሆናችንን መገንዘብ ችለናል። እኛ የማናውቀው አንድ መንፈሳዊ ወንድም የቀረውን ገንዘብ ለመክፈል ኃላፊነቱን ወሰደ። ይሁን እንጂ ሌላ ዝግጅት አድርገን ስለነበር የዚህን ወንድም ልግስና መቀበል አላስፈለገንም።
የሕክምና ባለሙያዎች ሥራቸውን ጀመሩ
የኬሞቴራፒ ሕክምናው ተጀመረ። ቀናትና ሳምንታት ነጎዱ። አንዳንድ ጊዜ ሁኔታው ለእኛም ሆነ ለትንሿ ልጃችን በጣም ከባድና አድካሚ ይሆንብን ነበር። በሌላው በኩል ደግሞ ቪኪ ለውጥ እያሳየች በመጣች ቁጥር ደስታችን ይጨምርና ልባችን በጥልቅ የአመስጋኝነት ስሜት ይሞላ ነበር። ሕክምናው ስምንት ወራት የሚያክል ጊዜ ፈጀ። በዚህ ወቅት በደሟ ውስጥ የነበረው የመጨረሻው አነስተኛ የሄሞግሎቢን መጠን ስድስት ግራም በዴሲ ሊትር ቢሆንም ዶክተር ግራፍ ቃሉን ጠብቋል።
ከስድስት ዓመታት በኋላ ከሰረሰሯ በተወሰደ ፈሳሽ ላይ የተደረገላት የመጨረሻ ምርመራ የበሽታው ምልክት ጨርሶ እንደሌለባት ያሳያል። አሁን ቪኪ ደስተኛ ልጅ ስትሆን ምንም ዓይነት የበሽታው ምልክት አይታይባትም። ይህ በሽታ የያዛቸው ብዙ ልጆች ደም እየወሰዱ
የኬሞቴራፒ ሕክምና ተደርጎላቸውም እንኳ እንደሚሞቱ ስለምናውቅ ቪኪ ሙሉ በሙሉ መዳኗ ለእኛ ልክ እንደ ተአምር ነው።ለእምነት ያደረግነው ውጊያ በድል ተጠናቅቋል። ይሁን እንጂ ለዚህ የበቃነው ዘመዶቻችን፣ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም የሕክምና ባለሙያዎች ባደረጉልን እርዳታ ነው። የሆስፒታል መረጃ አገልግሎት የ24 ሰዓት ድጋፍ አልተለየንም። ዶክተር ግራፍና የሥራ ባልደረቦቹ ሙሉ እውቀታቸውን ተጠቅመው ቪኪ የምታገግምበትን መንገድ ፈጥረዋል። ለዚህ ሁሉ ከልብ አመስጋኞች ነን።
እምነታችን ተጠናከረ
ይሁን እንጂ ከማንም በላይ ለፍቅራዊ እንክብካቤውና በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ላገኘነው ብርታት አምላካችንን ይሖዋን በጣም እናመሰግነዋለን። ያሳለፍነውን ጊዜ ቆም ብለን ስናስብ ከዚህ ከደረሰብን አስጨናቂ ሁኔታ ጠቃሚ ትምህርት እንዳገኘንና ሁኔታው እምነታችንን እንዳጠነከረው ይሰማናል።
አሁን ከልብ የምንመኘው ነገር ቢኖር ከይሖዋ ጋር ያለንን የተቀራረበ ዝምድና ጠብቆ መኖርንና ልጃችን ከእርሱ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምቶ መኖር ያለውን ጥቅም እንድትገነዘብ መርዳትን ነው። አዎን፣ በመጪው ምድራዊ ገነት ውስጥ ለሚገኘው ሕይወት የሚያበቃ ጥሩ መንፈሳዊ ውርሻ ልንሰጣት እንፈልጋለን።—ተጽፎ የተላከልን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ብሩክሊን የሚገኘው የሆስፒታል መረጃ አገልግሎት ዴስክ በዓለም ዙሪያ ያሉትን የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች በበላይነት ይቆጣጠራል። በእነዚህ ኮሚቴዎች ውስጥ የታቀፉት በሕክምና ባለሙያዎችና የይሖዋ ምሥክር በሆኑ ታካሚዎች መካከል የትብብር መንፈስ እንዲሰፍን ለማድረግ የሚያስችላቸውን ሥልጠና የወሰዱ ፈቃደኛ ክርስቲያኖች ናቸው። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ዙሪያ ከ1, 400 የሚበልጡ የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ከ200 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ ይገኛሉ።