በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እርስ በርስ የሚረዳዳ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር

እርስ በርስ የሚረዳዳ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር

እርስ በርስ የሚረዳዳ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር

ለዓይን የሚያታክት ሕዝብ ይታያል። ብዙዎቹ አረጋውያን አንዳንዶቹ ደግሞ እንደ ልብ መራመድ የማይችሉ የአካል ጉዳተኞች ናቸው። ነፍሰ ጡር ሴቶችና ትንንሽ ልጆቻቸው ሥር ሥራቸው የሚሄዱ ወጣት ባልና ሚስቶችም ይገኙባቸዋል። እነዚህ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች በእርስ በርስ ጦርነት፣ በተፈጥሮ አደጋ ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ በጎረቤት አገር ጥገኞች ሆነው ለመኖር የተገደዱ ስደተኞች ናቸው። አንዳንዶቹ አካባቢያቸውን ጥለው ለመሰደድ ሲገደዱ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። ሕዝባዊ ዓመፅ ወይም የተፈጥሮ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል የሚጠቁም ፍንጭ ሲመለከቱ የተወሰኑ የቤት ዕቃዎችን ጠቅልለውና ልጆቻቸውን አንጠልጥለው ወደ ሰላማዊ አካባቢ ይሸሻሉ። ከዚያ ደግሞ ሁኔታዎች ወደ ቀድሞ ቦታቸው ሲመለሱ ብዙ ስደተኞች ወደ አካባቢያቸው ተመልሰው ቤቶቻቸውን ሠርተው እንደገና ኑሯቸውን ይጀምራሉ።

ባለፉት ዓመታት የመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ ከተለያዩ አገሮች ለሚመጡ ስደተኞች በሯን ክፍት አድርጋ ቆይታለች። በቅርቡ ብዙ የይሖዋ ምሥክሮችን ጨምሮ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች በጦርነት ከምትታመሰው ኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ ተሰድደው አንጻራዊ ሰላም ባለባት መካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ ለመጠለል ተገድደዋል።

ወንድሞች ደረሱላቸው

በመካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ የሚኖሩ ምሥክሮች ሰብዓዊ እርዳታ የማደራጀት መብት በማግኘታቸው በጣም ተደስተዋል። ተሰድደው ለሚመጡ ክርስቲያን ወንድሞች ማረፊያ ተዘጋጀላቸው። በመጀመሪያ ማረፊያ የተገኘው በግል መኖሪያ ቤቶች ውስጥ ሲሆን የስደተኞቹ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድ ተጨማሪ ማረፊያ እንደሚያስፈልግ ታመነበት። አንዳንድ የመንግሥት አዳራሾች ተከፋፍለው ወደ መኝታ ቤትነት ተለወጡ። የአካባቢው ምሥክሮች ተጨማሪ የኤሌክትሪክና የቧንቧ መስመሮች ለመዘርጋት እንዲሁም በዚያ ለሚኖሩ እንግዶች ምቾት ሲባል ወለሉን ሲሚንቶ ለማንጠፍ በፈቃደኝነት ሠርተዋል። የአካባቢው ወንድሞች ጊዜያዊ ማረፊያ ክፍሎቹን ሲሠሩ ስደተኞቹም አብረዋቸው ይሠሩ ነበር። ስደተኞቹ ሕይወትን ጠብቆ የሚያቆየውን መንፈሳዊ ምግብ እንዲያገኙ ለመርዳት ሲባል በሊንጋላ ቋንቋ ሁሉንም የክርስቲያናዊ ስብሰባ ፕሮግራሞች ለማከናወን ዝግጅት ተደረገ። በአካባቢው ምሥክሮችና በስደተኞቹ መካከል የታየው ትብብር ዓለም አቀፍ ወንድማማችነት እውን መሆኑን የሚያሳይ ነበር።

ተሰድደው የሚመጡ ቤተሰቦች አንድ ላይ የማይደርሱባቸው ጊዜያት አሉ። አንዳንድ ጊዜ ተለያይተው የነበሩ የአንድ ቤተሰብ አባላት እንደገና የሚገናኙት መድረሻቸው ላይ ነው። በደህና የደረሱ ስደተኞች ስም ዝርዝር በእያንዳንዱ የመንግሥት አዳራሽ ይቀመጥ የነበረ ሲሆን የጠፉትን ፈልጎ ለማግኘት አንዳንድ ዝግጅቶችም ተደርገው ነበር። በአገሪቱ ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ በበላይነት የሚመራው ቅርንጫፍ ቢሮ ገና በመንገድ ላይ ያሉ ምሥክሮችን ለመርዳትና የጠፉትን ፈልጎ ለማግኘት በየዕለቱ ሦስት መኪናዎችን ያሰማራ ነበር። እነዚህ መኪናዎች “መጠበቂያ ግንብ”⁠የይሖዋ ምሥክሮች” የሚል ትልቅ ምልክት ተለጥፎባቸዋል።

ከቤተሰቦቻቸው ተጠፋፍተው የነበሩና ተሰድደው የመጡ ሰባት ልጆች የይሖዋ ምሥክሮችን መኪና ሲመለከቱ ምን ያክል እንደተደሰቱ መገመት ትችላለህ። ወዲያው ወደ መኪናው ሮጠው የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን አስታወቁ። ወንድሞች መኪናው ላይ እንዲወጡ በመርዳት ወደ መንግሥት አዳራሹ ከወሰዷቸው በኋላ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ተገናኝተዋል።

እነዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች አንዴ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ያጋጠማቸውን እንደዚህ ያለውን ሁኔታ እንዲቋቋሙ ያስቻላቸው ምንድን ነው? በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ አስቀድሞ በተነገረው የመጨረሻው ዘመን ውስጥ እንደምንኖር ሙሉ እምነት አላቸው።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5፤ ራእይ 6:​3-8

በመሆኑም ይሖዋ አምላክ በቅርቡ ጦርነትን፣ ጥላቻን፣ ዓመፅንና ብጥብጥን እንደሚያስቆም ያውቃሉ። የዚያን ጊዜ ስደተኝነት የሚባል ነገር አይኖርም። እስከዚያው ድረስ ግን የይሖዋ ምሥክሮች ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 12:​14-26 ላይ ካሰፈረው ማሳሰቢያ ጋር በሚስማማ መንገድ እርስ በርስ ለመረዳዳት ጥረት ያደርጋሉ። ወንዝ፣ ድንበር፣ ቋንቋና ርቀት ቢለያቸውም አንዳቸው ለሌላው ያስባሉ። ስለዚህም አንድ ሰው ቢቸገር ለመርዳት ፈጥነው ይንቀሳቀሳሉ።​—⁠ያዕቆብ 1:​22-27

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

አፍሪካ

መካከለኛው አፍሪካ ሪፑብሊክ

የኮንጎ ዲሞክራቲክ ሪፑብሊክ

[ምንጭ]

Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.

[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሦስት የመንግሥት አዳራሾች ወደ ስደተኛ መቀበያ ማዕከልነት ተለውጠዋል

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ወዲያው ማብሰያ ቦታም ተዘጋጀ

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በየጊዜው አዳዲስ ስደተኞች ይመጣሉ

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ገና አራስ ሕፃናት፣ ግን ስደተኞች