በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የቤተ ክርስቲያን አባቶች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጠበቆች ናቸውን?

የቤተ ክርስቲያን አባቶች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጠበቆች ናቸውን?

የቤተ ክርስቲያን አባቶች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጠበቆች ናቸውን?

የክርስትናን እምነት እከተላለሁ የምትል ሆንህም አልሆንህ ስለ መጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ፣ ስለ ኢየሱስና ስለ ክርስትና ያለህ አመለካከት የቤተ ክርስቲያን አባቶች የሚባሉት ሰዎች ተጽዕኖ አለበት። ከእነርሱ መካከል አንዱ አፈ-ወርቅ ሌላው ደግሞ ታላቅ ተብለው ተጠርተዋል። ከዚህም ሌላ “የክርስቶስ ሕይወት ድንቅ መገለጫ” የሚል የወል መጠሪያ ተሰጥቷቸዋል። እነዚህ እነማን ናቸው? “የክርስትና” አስተሳሰብ ዛሬ ያለውን መልክ እንዲይዝ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩ የጥንት ሃይማኖታዊ ፈላስፎች፣ ጸሐፊዎች እና የሃይማኖት ምሁራን ሲሆኑ የቤተ ክርስቲያን አባቶች በመባል ይታወቃሉ።

“የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው ማለት አይደለም” ሲሉ የግሪክ ኦርቶዶክስ ሃይማኖታዊ ጥናት ፕሮፌሰር የሆኑት ደሚትሪዎስ ጄ ኮንስታንቴሎስ ተናግረዋል። “የአምላክን ቃል የሚገልጠው መንፈስ ቅዱስ በአንድ መጽሐፍ ገጾች ብቻ ሊወሰን አይችልም።” ታዲያ ሌላው መለኮታዊው ሐሳብ የተገለጠበት መጽሐፍ የትኛው ሊሆን ይችላል? ኮንስታንቴሎስ አንደርስታንዲንግ ዘ ግሪክ ኦርቶዶክስ ቸርች በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ “ቅዱስ ወጎችና ቅዱሳን ጽሑፎች የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው” ሲሉ አስተያየታቸውን አስፍረዋል።

ለእነዚህ “ቅዱስ ወጎች” መሠረት ከሆኑት ነገሮች መካከል የቤተ ክርስቲያን አባቶች ያስተማሯቸውና የጻፏቸው ነገሮች ይገኙባቸዋል። እነዚህ በሁለተኛውና በአምስተኛው መቶ ዘመን እዘአ መካከል የኖሩ የሃይማኖት ምሁራንና “የክርስትና” ፈላስፎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ዛሬ ባለው “የክርስትና” አስተሳሰብ ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩት እስከ ምን ድረስ ነው? ትምህርቶቻቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በጥብቅ የተመሠረቱ ናቸውን? አንድ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ ለክርስትና እውነት ጠንካራ መሠረት ነው የሚለው ነገር ምን ሊሆን ይገባል?

ታሪካዊው አጀማመር

በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ አጋማሽ ላይ ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች እምነታቸውን ከሮማውያን አሳዳጆቻቸውና ከመናፍቃን መከላከል ይዘው ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ብዙ ዓይነት ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች የሚንጸባረቁበት ወቅት ነበር። ስለ ኢየሱስ “መለኮትነት” እንዲሁም ስለ መንፈስ ቅዱስ ምንነትና አሠራር ይካሄድ የነበረው ሃይማኖታዊ ክርክር በምሁራን መካከል ብቻ ሳይሆን ከዚያም ያለፈ ክፍፍል ፈጥሮ ነበር። “የክርስትና” መሠረተ ትምህርቶችን በተመለከተ የተነሣው ከፍተኛ አለመግባባትና ሊታረቅ የማይችል ልዩነት ወደ ፖለቲካዊውና ባሕላዊው መስክም የዘለቀ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ሁከት፣ ብጥብጥ፣ የሕዝብ ዓመፅና አልፎ ተርፎም ጦርነት እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኗል። ታሪክ ጸሐፊው ፖል ጆንሰን እንዲህ ብለዋል:- “[የክህደት] ክርስትና በውዥንብር፣ በጭቅጭቅና በአለመግባባት ተጀምሮ በዚያው መልክ ቀጥሏል። . . . መካከለኛውና ምሥራቃዊው የሜድትራኒያን አካባቢ በአንደኛውና በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. ከሌላው ገንነው ለመታየት እርስ በርስ በሚፎካከሩ እጅግ በርካታ ሃይማኖታዊ አስተሳሰቦች ተጥለቅልቆ ነበር። . . . በመሆኑም ከመጀመሪያውም ቢሆን እምብዛም የጋራ ባሕርይ የሌላቸው በርካታ የክርስትና ዓይነቶች ነበሩ።”

በዚያ ዘመን “የክርስትና” ትምህርቶችን በፍልስፍና ቋንቋ ማብራራት አስፈላጊ እንደሆነ የሚያምኑ ጸሐፊዎችና ፈላስፎች እየተበራከቱ መጥተው ነበር። ወደ “ክርስትና” ከተለወጡ ብዙም ያልቆዩትን የተማሩ አረማውያን ፍላጎት ለማርካት ሲባል እነዚህ ሃይማኖታዊ ጸሐፊዎች ከዚያ ዘመን ቀደም ብለው በወጡ የዕብራይስጥና የግሪክኛ የጽሑፍ ሥራዎች ላይ አተኩረው ነበር። በግሪክኛ ከጻፈው ከሰማዕቱ ጀስቲን (ከ100 እዘአ ገደማ እስከ 165 እዘአ) አንስቶ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች ከግሪካውያን ባሕል የወረሱትን የፍልስፍና ቅርስ በማዋሃድ ረገድ ተክነው ነበር።

ይህ አካሄድ በእስክንድርያ በነ​በረው የግሪክኛ ጸሐፊ በኦሪጀን (ከ185 እዘአ ገደማ እስከ 254 እዘአ) የጽሑፍ ሥራዎች አማካኝነት በተጨባጭ የሚታይ ፍሬ አፍርቷል። ኦሪጀን ኦን ፈርስት ፕሪንሲፕልስ በተባለው ጽሑፉ ላይ ያቀረበው ሐሳብ “የክርስትናን” ዋነኛ ሃይማኖታዊ መሠረተ ትምህርቶች በግሪካውያን የፍልስፍና ቋንቋ ለማብራራት የተደረገ የመጀመሪያው የተቀናጀ ጥረት ነበር። የክርስቶስን “መለኮትነት” ለማስረዳትና ለማረጋገጥ የጣረው የኒቂያ ጉባኤ (በ325 እዘአ) “የክርስትናን” ቀኖና በመተንተን ረገድ ፈር ቀዳጅ የሆነ አብይ ክንውን ነበር። ይህ ጉባኤ አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤዎች ቀኖና ፍጹም ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ማብራራት ለጀመሩበት አዲስ ዘመን መባቻ ሆኗል።

ጸሐፊዎችና የተካኑ ተናጋሪዎች

በመጀመሪያው የኒቂያ ጉባኤ ወቅት የጻፈው የቂሣርያው ዩሴቢየስ ራሱን ከንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ ጋር አያይዞ ገልጿል። የኒቂያው ጉባኤ ከተደረገ ከ100 ትንሽ የሚበልጡ ዓመታት ካለፉ በኋላ የሃይማኖት ምሁራን (አብዛኛዎቹ በግሪክኛ የሚጽፉ ናቸው) የሕዝበ ክርስትና መለያ በሆነው የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ላይ ረጅም ጊዜ የፈጀና ያመረረ ክርክር አካሂደዋል። ከእነርሱ መካከል ዋነኞቹ ተከራካሪዎች የእስክንድርያው ሊቀ ጳጳስ አትናቴዎስ እንዲሁም ሌሎች በትንሿ እስያ የምትገኘው የቀጰዶቅያ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ማለትም ታላቁ ባሲል፣ ወንድሙ የኒሳው ግሪጎሪ እንዲሁም የእነርሱ ወዳጅ የሆነው የኔዚየንዘሱ ግሪጎሪ ናቸው።

በዚያ ዘመን የነበሩ ጸሐፊዎችና ሰባኪዎች ኃይለኛ ተናጋሪዎች ነበሩ። የኔዚየንሰሱ ግሪጎሪና ጆን ክሪሶስተም (“አፈ-ወርቅ” ማለት ነው) በግሪክኛ እንዲሁም የሚላኑ አምብሮስም ሆነ የሂፖው አውጉስቲን በላቲን የተካኑ ተናጋሪዎች ነበሩ። በሌላ አባባል በዘመናቸው በጣም የተከበረና የተወደደ በነበረው የኪነ ጥበብ ዘርፍ እጅግ የተዋጣላቸው ሰዎች ነበሩ። በዘመኑ ሰፊ ተደማጭነት የነበረው ጸሐፊ አውጉስቲን ነበር። ሃይማኖታዊ ጽሑፎቹ ዛሬ ያለውን “የክርስትና” አስተሳሰብ በእጅጉ ቀርጸዋል። የዘመኑ ታላቅ የጽሑፍ ሰው የሆነው ጄሮም ከመጀመሪያው ቋንቋ የላቲኑን ቩልጌት የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሠርቷል።

ይሁን እንጂ አሁን በጣም አስፈላጊ የሆኑ የሚከተሉት ጥያቄዎች ይነሳሉ:- እነዚያ የቤተ ክርስቲያን አባቶች መጽሐፍ ቅዱስን በጥብቅ ተከትለዋልን? ትምህርቶቻቸው በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች ላይ በጥብቅ የተመሠረቱ ናቸውን? የጽሑፍ ሥራዎቻቸው ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት ለማግኘት የሚያስችል አስተማማኝ መመሪያ የሚገኝባቸው ናቸውን?

የአምላክ ትምህርት ወይስ የሰው?

የግሪክ ኦርቶዶክስ ሊቀ ጳጳስ የሆነው የጲስድያ ሜቶዲየስ የግሪክ ባሕልና ፍልስፍና ዛሬ ላለው “የክርስትና” አስተሳሰብ መንገድ እንደጠረገ ለማሳየት በቅርቡ ዘ ሄለኒክ ፔደስታል ኦቭ ክርስቺያኒቲ የተባለ መጽሐፍ ጽፏል። በዚሁ መጽሐፉ ውስጥ እንደሚከተለው ብሎ ለመጻፍ ምንም አላቅማማም:- “ሁሉም ታዋቂ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለማለት ይቻላል የግሪካውያንን ትምህርት እጅግ ጠቃሚ እንደሆኑ አድርገው የተመለከቷቸው ሲሆን እነዚሁኑ ትምህርቶች ከጥንቷ ግሪክ በመዋስ የክርስትናን እውነት ለመረዳትና በትክክል ለማብራራት ተጠቅመውባቸዋል።”

ለምሳሌ ያህል አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ሥላሴ ናቸው የሚለውን ሐሳብ ተመልከት። ብዙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ከኒቂያው ጉባኤ በኋላ ጠንካራ የሥላሴ አማኞች ሆነዋል። ጽሑፎቻቸውና ማብራሪያዎቻቸው ሁሉ ሥላሴ የሕዝበ ክርስትና መሠረተ ትምህርቶች ማዕዘን እንዲሆን ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል። ይሁን እንጂ የሥላሴ ትምህርት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛልን? የለም አይገኝም። ታዲያ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ከየት አመጡት? ኤ ዲክሽነሪ ኦቭ ሪሊጂየስ ኖውሌጅ ብዙ ሰዎች ሥላሴ “ከአረማውያን ሃይማኖቶች ተወስዶ በክርስትና እምነት ላይ የተለጠፈ ቅጥያ ነው” እንደሚሉ ጠቅሷል። ዘ ፓጋኒዝም ኢን አወር ክርስቺያኒቲ እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ይሰጣል:- [የሥላሴ] አመጣጥ ሙሉ በሙሉ አረማዊ ነው።” a​—⁠ዮሐንስ 3:​16፤ 14:​28

ወይም ደግሞ ነፍስ አትሞትም የሚለውን ትምህርት ማለትም ሥጋ ከሞተ በኋላ በሕይወት የምትቀጥል አካል አለች የሚለውን እምነት እንደ ምሳሌ አድርገህ ውሰድ። ከዚያ ቀደም ከሞት በኋላ በሕይወት የምትቀጥል ነፍስ አለች የሚል ትምህርት ጨርሶ ላልነበረው ሃይማኖት ይህንን ትምህርት ለማስተዋወቅ እንደ መሣሪያ ሆነው ያገለገሉት የቤተ ክርስቲያን አባቶች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ነፍስ እንደምትሞት በግልጽ ይናገራል:- “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች።” (ሕዝቅኤል 18:​4) የቤተ ክርስቲያን አባቶች ነፍስ አትሞትም የሚለውን እምነት እንዲይዙ መሠረት የሆናቸው ነገር ምንድን ነበር? “አምላክ መንፈሳዊ የሆነች ነፍስ ፈጥሮ በጽንስ ጊዜ በአካሉ ውስጥ በመጨመር ሰው ምሉዕ ሕያው አካል እንዲሆን ያደርጋል የሚለው የክርስትና ንድፈ ሐሳብ በየዘመናቱ እየዳበረ የመጣው የክርስትና ፍልስፍና ፍሬ ነው። የነፍስ መንፈሳዊ ባሕርይ ተቀባይነት ያገኘው በምሥራቅ በኦሪጀን በምዕራብ ደግሞ በቅዱስ አውጉስቲን አማካኝነት ብቻ ሲሆን የፍልስፍና ንድፈ ሐሳቡ እንዲዳብርም ያደረጉት እነዚሁ ሰዎች ናቸው . . . [የአውጉስቲን መሠረተ ትምህርት] . . . ከኒዮፕላቶኒዝም የወረሳቸው (አንዳንድ ጉድለቶችን ጨምሮ) ብዙ ነገሮች አሉ” ሲል ኒው ካቶሊክ ኢንሳይክሎፔዲያ ዘግቧል። ፕሬስባይቴሪያን ላይፍ የተባለው መጽሔት እንዲህ ይላል:- “ነፍስ አትሞትም የሚለው ንድፈ ሐሳብ በጥንቶቹ ምሥጢራዊ ሃይማኖታዊ ቡድኖች ውስጥ የበቀለና በፈላስፋው ፕላቶ የዳበረ የግሪካውያን ንድፈ ሐሳብ ነው።” b

የክርስትና እውነት ጠንካራ መሠረት

የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ታሪካዊ አጀማመርና የትምህርቶቻቸውን ምንጭ በተመለከተ ካደረግነው ከዚህ አጭር ምርመራም በኋላ አንድ ቅን ልብ ያለው ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ትምህርት የእምነቱ መሠረት አድርጎ ሊይዝ ይገባዋልን? ብለን መጠየቃችን ተገቢ ይሆናል። ለዚህ ጥያቄ መልሱን መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ይስጠን።

አንደኛ ነገር ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ “አባት” የሚለውን ሃይማኖታዊ መጠሪያ መጠቀም ትክክል እንዳልሆነ ሲገልጽ “አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም:- አባት ብላችሁ አትጥሩ” ብሏል። (ማቴዎስ 23:​9) የትኛውንም ሃይማኖታዊ ሰው ለማመልከት “አባት” የሚለውን ቃል መጠቀም ክርስቲያናዊም ቅዱስ ጽሑፋዊም አይደለም። በጽሑፍ የሰፈረው የአምላክ ቃል የተጠናቀቀው በ98 እዘአ ዮሐንስ በጻፋቸው መጻሕፍት ነው። በመሆኑም እውነተኛ ክርስቲያኖች መለኮታዊ ራእይዎችን ፍለጋ ወደ ሰዎች የሚሄዱበት ምንም ምክንያት የለም። ስለ ሰው ወግ ሲሉ ‘የአምላክን ቃል እንዳይሽሩ’ ይጠነቀቃሉ። ከአምላክ ቃል ይልቅ የሰው ወግ እንዲቀድም መፍቀድ መንፈሳዊ ሞት ሊያስከትል ይችላል። ኢየሱስ “ዕውርም ዕውርን ቢመራው ሁለቱም ወደ ጕድጓድ ይወድቃሉ” ሲል አስጠንቅቋል።​—⁠ማቴዎስ 15:​6, 14

አንድ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው ከአምላክ ቃል ውጭ ሌላ ራእይ ሊገለጥለት ያስፈልገዋልን? አያስፈልገውም። የራእይ መጽሐፍ በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው ጽሑፍ ላይ አንዳች ነገር መጨመር እንደማይቻል ሲያስጠነቅቅ “ማንም በዚህ ላይ አንዳች ቢጨምር እግዚአብሔር በዚህ መጽሐፍ የተጻፉትን መቅሠፍቶች ይጨምርበታል” በማለት ይናገራል።​—⁠ራእይ 22:​18

የክርስትና እውነት በጽሑፍ በሰፈረው በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። (ዮሐንስ 17:​17፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​16፤ 2 ዮሐንስ 1-4) ይህንን እውነት በትክክለኛ መንገድ መረዳታችን በዓለማዊ ፍልስፍና ላይ የተመካ አይደለም። መለኮታዊውን ራእይ በሰብዓዊ ጥበብ ለማብራራት የሞከሩትን ሰዎች በሚመለከት ሐዋርያው ጳውሎስ ያነሳቸውን ጥያቄዎች መድገሙ ተገቢ ይሆናል:- “ጥበበኛ የት አለ? ጻፊስ የት አለ? የዚች ዓለም መርማሪስ የት አለ? እግዚአብሔር የዚችን ዓለም ጥበብ ሞኝነት እንዲሆን አላደረገምን?”​—⁠1 ቆሮንቶስ 1:​20

ከዚህም በላይ እውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ “የእውነት ዓምድና መሠረት” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 3:​15) የበላይ ተመልካቾቹ በጉባኤ ውስጥ የትምህርቱን ጥራት በመከታተል ምንም ዓይነት የሚበክል መሠረተ ትምህርት ሾልኮ እንዳይገባ ይጠብቃሉ። (2 ጢሞቴዎስ 2:​15-18, 25, 26) ጉባኤውን ‘ከሐሰተኛ ነቢያት፣ ከሐሰተኛ አስተማሪዎችና ከሚያጠፋ ኑፋቄ’ ይጠብቃሉ። (2 ጴጥሮስ 2:​1) ከሐዋርያት ሞት በኋላ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ‘የሚያስቱ መናፍስትና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠው የአጋንንት ትምህርት’ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሥር ሰድዶ እንዲስፋፋ ፈቅደዋል።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 4:​1, 2

የዚህ ክህደት ውጤት ዛሬ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ በግልጽ ይታያል። ዛሬ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ የሚንጸባረቁት እምነቶችና ልማዶች ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ፍጹም የተለዩ ናቸው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a በይሖዋ ምሥክሮች የታተመውን በሥላሴ ማመን ይገባሃልን? በተባለው ብሮሹር ላይ ስለ ሥላሴ መሠረተ ትምህርት ጥልቀት ያለው ማብራሪያ ማግኘት ይቻላል።

b መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነፍስ የሚሰጠውን ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የታተመውን ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር የተባለ መጽሐፍ ገጽ 97-104 እንዲሁም 374-78 ተመልከት።

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የቀጰዶቅያ አባቶች

መነኩሴ የነበረው ጸሐፊው ካሊስቶስ እንዳለው “የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን . . . ለአራተኛው መቶ ዘመን ጸሐፊዎች በተለይ ደግሞ ‘ሦስቱ ታላቅ የሃይማኖት መሪዎች’ ለምትላቸው ለኔዚየንዘሱ ግሪጎሪ፣ ለታላቁ ባሲል እንዲሁም ለጆን ክሪሶስተም የጠለቀ አክብሮት አላት።” እነዚህ የቤተ ክርስቲያን አባቶች የሚያስተምሩት ነገር በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረተ ነበርን? ታላቁ ባሲልን በተመለከተ ዘ ፋዘርስ ኦቭ ዘ ግሪክ ቸርች የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “የጽሑፍ ሥራዎቹ ከፕላቶ፣ ከሆሜር እንዲሁም ከታሪክ ጸሐፊዎችና ከተካኑ ተናጋሪዎች ጋር የነበረውን የጠበቀ ትስስር የሚያንጸባርቅ ሲሆን በአጻጻፍ ስልቱም ላይ ተጽዕኖ አሳድረው ነበር። . . . ባሲል ‘በግሪክኛው’ ጸንቷል።” የኔዚየንዘሱ ግሪጎሪ ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። “በእርሱ እምነት የቤተ ክርስቲያን ድልና ታላቅነት ይበልጥ የሚገንነው የጥንቱን ባሕል ወጎች ሙሉ በሙሉ በመቀበሏ ነው።”

ሦስቱን ሰዎች በተመለከተ ፕሮፌሰር ፓናዮቲስ ክሪስቶ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ከአዲስ ኪዳን ትእዛዝ ጋር ለመስማማት አልፎ አልፎ ‘ከፍልስፍናና ከከንቱ መታለል’ [ቆላስይስ 2:​8] ስለመጠበቅ ማስጠንቀቂያ ይሰጡ የነበረ ቢሆንም ፍልስፍናንና ከፍልስፍና ጋር የሚዛመዱ ሌሎች ሐሳቦችን በጥንቃቄ ያጠኑ የነበረ ሲሆን ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ አበረታትተዋል።” በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው እንዲህ ያሉት የቤተ ክርስቲያን አስተማሪዎች መጽሐፍ ቅዱስ ሐሳባቸውን ለመደገፍ በቂ እንዳልሆነ ተሰምቷቸው ነበር። ሌላ እንደ ባለ ሥልጣን የሚጠቅሱት አምድ መፈለጋቸው ትምህርቶቻቸው ለመጽሐፍ ቅዱስ ባዕድ ናቸው ማለት ነውን? ሐዋርያው ጳውሎስ “ልዩ ልዩ ዓይነት በሆነ በእንግዳ ትምህርት አትወሰዱ” ሲል ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።​—⁠ዕብራውያን 13:​9

[ምንጭ]

© Archivo Iconografico, S.A./CORBIS

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

የእስክንድርያው ሲረል ሞገደኛው የቤተ ክርስቲያን አባት

በጣም አወዛጋቢ ከሆኑት የቤተ ክርስቲያን አባቶች አንዱ የእስክንድርያው ሲረል (ከ375 እዘአ ገደማ እስከ 444 እዘአ) ነው። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ጸሐፊ የሆኑት ሃንስ ፎን ኮፐንሃውዘን ስለ እርሱ ሲናገሩ “ቀኖናዊ፣ ዓመፀኛና መሠሪ እንዲሁም ባለው ቦታ ወይም በሥልጣኑ ክብር በጣም የሚኩራራ ሰው” መሆኑን ከገለጹ በኋላ እንደሚከተለው በማለት አክለው ተናግረዋል:- “የእርሱን ታላቅነትና ሥልጣን ለማስፋፋት የሚበጅ ሆኖ ካልታየው በስተቀር ምንም ነገር ትክክል መስሎ አይታየውም። . . . የሚጠቀምባቸው ዘዴዎች ጭከና የተንጸባረቀባቸውና ይሉኝታ የለሽ መሆናቸው ምንም አይቆረቁረውም።” ሲረል በእስክንድርያ ሊቀ ጳጳስ ሆኖ ሳለ በጉቦና በስም ማጥፋት ዘመቻ የቁስጥንጥንያውን ሊቀ ጳጳስ ከሥልጣናቸው ለማውረድ ሞክሮ ነበር። ታዋቂዋ ፈላስፋ ሃይፓሺያ በ415 እዘአ በአሰቃቂ ሁኔታ እንድትገደል ያደረገው እርሱ እንደሆነም ይነገራል። የሲረልን ሃይማኖታዊ ጽሑፎች በተመለከተ ኮፐንሃውዘን እንዲህ ብለዋል:- “እምነትን በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎችን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ብቻ ተመሥርቶ ከመመለስ ይልቅ እውቅና ካገኙ ምንጮች ተስማሚ የሆኑ ጥቅሶችን ተጠቅሞ የመመለስን ልማድ አስጀምሯል።”

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጄሮም

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

Garo Nalbandian