በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአምላክን ድንቅ ሥራዎች በትኩረት ተመልከቱ

የአምላክን ድንቅ ሥራዎች በትኩረት ተመልከቱ

የአምላክን ድንቅ ሥራዎች በትኩረት ተመልከቱ

“አቤቱ አምላኬ፣ ያደረግኸው ተአምራት ብዙ ነው፣ አሳብህንም ምንም የሚመስለው የለም፤ ባወራም ብናገርም ከቍጥር ሁሉ በዛ።”​—⁠መዝሙር 40:​5

1, 2. የአምላክን ድንቅ ሥራዎች በተመለከተ ምን ማስረጃ አለን? ይህስ ምን እንድናደርግ ሊገፋፋን ይገባል?

 መጽሐፍ ቅዱስን በምታነብበት ጊዜ አምላክ ለጥንት ሕዝቦቹ ለእስራኤላውያን ድንቅ ነገሮችን እንዳደረገላቸው በግልጽ ማስተዋል ትችላለህ። (ኢያሱ 3:​5፤ መዝሙር 106:​7, 21, 22) በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ በዚያ መንገድ በሰዎች ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ ባይገባም እንኳ በአካባቢያችን ድንቅ የሆኑ ሥራዎቹን በብዛት ልንመለከት እንችላለን። ስለዚህ እኛም ልክ እንደ መዝሙራዊው “አቤቱ፣ ሥራህ እጅግ ብዙ ነው፤ ሁሉን በጥበብ አደረግህ፣ ምድርም ከፍጥረትህ ተሞላች” ለማለት በቂ ምክንያት አለን።​—⁠መዝሙር 104:​24፤ 148:​1-5

2 በዛሬው ጊዜ በርካታ ሰዎች ለፈጣሪ ሥራ ግልጽ ማስረጃ የሚሆኑትን እንዲህ ያሉ ነገሮች ችላ ይላሉ ወይም ለመቀበል አይፈልጉም። (ሮሜ 1:​20) ሆኖም እኛ በእነዚህ ነገሮች ላይ ማሰላሰላችንና በፈጣሪያችን ፊት ስላለን ቦታና በእሱ ዘንድ ስላለብን ግዴታ ተገቢ መደምደሚያ ላይ መድረሳችን አስፈላጊ ነው። በኢዮብ ምዕራፍ 38 እስከ 41 ላይ የተገለጹት ሐሳቦች በዚህ ረገድ ትልቅ እገዛ ያደርጉልናል። ምክንያቱም ይሖዋ በእነዚህ ምዕራፎች ላይ አንዳንድ አስደናቂ ሥራዎቹን በመጥቀስ ኢዮብ በትኩረት እንዲያስብባቸው አድርጓል። እስቲ አምላክ ካነሳቸው ትልቅ ትርጉም ያዘሉ ጥያቄዎች መካከል አንዳንዶቹን መርምር።

ታላቅ ኃይል የተንጸባረቀባቸው ድንቅ ሥራዎች

3. በኢዮብ 38:​22, 23, 25-29 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው መሠረት አምላክ ስለ ምን ነገሮች ጠይቋል?

3 በአንድ ወቅት አምላክ ኢዮብን እንዲህ በማለት ጠይቆት ነበር:- “በውኑ ወደ በረዶው ቤተ መዛግብት ገብተሃልን? የበረዶውንስ ቅንጣት ቤተ መዛግብት አይተሃልን? ይኸውም ለመከራ ጊዜ ለሰልፍና ለጦርነት ቀን የጠበቅሁት ነው።” በብዙ የምድር ክፍል በረዶ የተለመደ ነገር ነው። አምላክ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ሣሩንም እንዲያበቅል፣ ማንም በሌለባት ምድር ላይ፣ ሰውም በሌለባት ምድረ በዳ ላይ ዝናብን ያዘንብ ዘንድ፣ ለፈሳሹ ውኃ መንዶልዶያውን፣ ወይስ ለሚያንጐደጉድ መብረቅ መንገድን ያበጀ ማን ነው? በውኑ ለዝናብ አባት አለውን? ወይስ የጠልን ነጠብጣብ የወለደ ማን ነው? በረዶስ ከማን ማኅፀን ወጣ? የሰማዩንስ አመዳይ ማን ወለደው?”​—⁠ኢዮብ 38:​22, 23, 25-29

4-6. የሰው ልጅ ስለ በረዶ ያለው እውቀት የተሟላ አይደለም የምንለው ከምን አንጻር ነው?

4 ሩጫ በበዛበት ማኅበረሰብ ውስጥ የሚኖሩና በሥራ ጠባያቸው ምክንያት ከቦታ ወደ ቦታ የሚዘዋወሩ አንዳንድ ሰዎች በረዶ ችግር ፈጣሪ ከመሆኑ ሌላ የሚታያቸው ነገር አይኖር ይሆናል። ሆኖም በረዶ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ የሚያስችሉ ግሩም አጋጣሚዎችን በመፍጠር የክረምቱን ወቅት አስደሳች ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽዖ ያለው ነገር እንደሆነ አድርገው የሚመለከቱ ብዙ ሰዎችም አሉ። አምላክ ካነሳቸው ጥያቄዎች አንጻር ስለ በረዶ ጠለቅ ያለ እውቀት አለህ? ሌላው ቀርቶ ምን እንደሚመስልስ ታውቃለህ? በብዛት የተቆለለ በረዶ ምን እንደሚመስል በፎቶግራፍ ወይም ደግሞ በዓይናችን አይተን ይሆናል። ይሁን እንጂ ስለ እያንዳንዱ የበረዶ ቅንጣትስ ምን ማለት ይቻላል? ምናልባትም ምንጫቸውን በማጥናት ምን እንደሚመስሉ ያገኘኸው እውቀት አለ?

5 አንዳንዶች ስለ በረዶ ቅንጣቶች በማጥናትና ፎቶግራፍ በማንሳት ብዙ አሥርተ ዓመታት አሳልፈዋል። አንዷ የበረዶ ቅንጣት ብቻ ከመቶ በማያንሱ አንዳቸው ከሌላው ጋር የማይመሳሰል ቅርጽና ውበት ባላቸው እንደ መስተዋት ያሉ የበረዶ ብናኞች የተገነባች ትሆናለች። አትሞስፌር የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:- “የበረዶ ቅንጣቶች በቅርጽና በመልክ የማይመሳሰሉ መሆናቸው ምንም አያጠያይቅም። ሳይንቲስቶች የበረዶ ቅንጣቶች እርስ በርስ እንዳይመሳሰሉ የሚያግድ የተፈጥሮ ሕግ የለም በማለት አበክረው የሚናገሩ ቢሆንም ሁለት አንድ ዓይነት ቅርጽ ያላቸው የበረዶ ቅንጣቶች ተገኝተው አያውቁም። አጉሊ መነጽር በመጠቀም የበረዶ ቅንጣቶችን በማጥናትና ፎቶግራፍ በማንሳት ከ40 የሚበልጡ ዓመታት ያሳለፉት . . . ዌልሰን ኤ ቤንትሊ ባደረጉት መጠነ ሰፊ ምርምር አንድ ጊዜም እንኳን ፍጹም ተመሳሳይ የሆኑ ቅንጣቶች አላገኙም።” አንድ ዓይነት የሚመስሉ ሁለት የበረዶ ቅንጣቶች እንዲያው በአጋጣሚ ቢገኙ እንኳ እጅግ ብዙ ዓይነት የበረዶ ቅንጣቶች ከመኖራቸው አንጻር ሲታይ በዚህ አስደናቂ እውነታ ላይ የሚያመጣው ለውጥ ይኖራልን?

6 አምላክ “ወደ በረዶው ቤተ መዛግብት ገብተሃልን?” በማለት ያቀረበውን ጥያቄ አስታውስ። ብዙዎች የበረዶ ቤተ መዝገብ ደመና ነው ይላሉ። ታዲያ ወደዚህ ቤተ መዛግብት ገብተህ ሕልቆ መሳፍርት የሌለው ኅብር ያላቸውን የበረዶ ቅንጣቶች ዝርዝር እየመዘገብህና እንዴት ሊፈጠሩ እንደቻሉ እያጠናህ እንዳለህ አድርገህ በዓይነ ሕሊናህ ልትመለከት ትችላለህ? አንድ የሳይንስ ኢንሳይክሎፔዲያ እንዲህ ይላል:- “የደመና ነጠብጣቦች ከዜሮ በታች በ40 ዲግሪ ፋራናይት (40 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ) እንዲቀዘቅዙ የሚያደርጉት የበረዶ ዕምብርቶች ባሕርይና አመጣጥ እስከ አሁን ድረስ በግልጽ አይታወቅም።”​—⁠መዝሙር 147:​16, 17፤ ኢሳይያስ 55:​9, 10

7. የሰው ልጅ ስለ ዝናብ ያለው እውቀት ምን ያህል ነው?

7 ስለ ዝናብስ ምን ሊባል ይችላል? አምላክ ኢዮብን “በውኑ ለዝናብ አባት አለውን? ወይስ የጠልን ነጠብጣብ የወለደ ማን ነው?” በማለት ጠይቆት ነበር። ቀደም ሲል የተጠቀሰው የሳይንስ ኢንሳይክሎፔዲያ እንዲህ ይላል:- “የከባቢ አየር እንቅስቃሴ እጅግ የተወሳሰበ በመሆኑና በአየር ውስጥ ያለው የተንና የሌሎች ቅንጣቶች ይዘት እጅግ የተለያየ በመሆኑ ደመናና ጠል ስለሚፈጠርበት መንገድ ዘርዘር ያለና አጠቃላይ የሆነ ንድፈ ሐሳብ መስጠት ፈጽሞ የማይቻል ይመስላል።” በአጭሩ ሳይንቲስቶች ስለ ዝናብ ዝርዝር ንድፈ ሐሳቦችን ቢያቀርቡም የተሟላ ማብራሪያ መስጠት ግን አልቻሉም። ቢሆንም ዝናብ ምድራችንን በማጠጣት እጽዋት እንዲለመልሙ ስለሚያደርግ በሕይወት ለመኖርና ለመደሰት እንደቻልን ታውቃለህ።

8. በሥራ 14:​17 ላይ የሚገኘው የጳውሎስ አነጋገር ተገቢ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

8 ሐዋርያው ጳውሎስ ከደረሰበት መደምደሚያ ጋር አትስማማም? እነዚህ ድንቅ ሥራዎች ከበስተጀርባቸው ስላለው አካል የሚሰጡትን ምሥክርነት እንዲያስተውሉ ሌሎችን አጥብቆ አሳስቧል። ጳውሎስ ስለ ይሖዋ አምላክ እንዲህ ብሏል:- “ከዚህም ሁሉ ጋር መልካም ሥራ እየሠራ፣ ከሰማይ ዝናብን ፍሬ የሚሆንበትንም ወራት ሲሰጠን፣ ልባችንንም በመብልና በደስታ ሲሞላው ራሱን ያለ ምስክር አልተወም።”​—⁠ሥራ 14:​17፤ መዝሙር 147:​8

9. የአምላክ ድንቅ ሥራዎች የታላቅ ኃይሉ መግለጫ የሆኑት እንዴት ነው?

9 የእነዚህ ድንቅና ጠቃሚ ሥራዎች ባለቤት ይህ ነው የማይባል ጥበብና ኃይል እንዳለው አያጠያይቅም። ኃይሉ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ ለማየት የሚከተለውን አስብ:- በየቀኑ 45, 000፣ በዓመት ደግሞ ከ16 ሚልዮን በላይ ነጎድጓዳማ ወዠቦች እንደሚኖሩ ይገመታል። ይህ ማለት በዚህ ቅጽበት እንኳ በመላው ዓለም 2, 000 የሚያክሉ ነጎድጓዳማ ወዠቦች ተፈጥረዋል። በአንድ ነጎድጓዳማ ወዠብ ወቅት ብቻ የሚፈጠረውን የደመናት ስብስብ የሚንጠው ኃይል በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ከተጣሉት ከአሥሩ ወይም ከዚያ ከሚበልጡት የኑክሌር ቦምቦች ኃይል ጋር የሚተካከል ነው። ከዚህ ኃይል ውስጥ ጥቂቱ መብረቅ ሆኖ ይታይሃል። መብረቅ እጅግ አስደናቂ ከመሆኑም በተጨማሪ ዕፅዋት እንደ ተፈጥሯዊ ማዳበሪያ የሚጠቀሙባቸው የናይትሮጅን ዓይነቶች ከአፈር ጋር እንዲደባለቁ ያደርጋል። ስለዚህ መብረቅ በገሐድ የሚታይ ኃይል ከመሆኑም ባሻገር ከፍተኛ ጥቅም ያስገኛል።​—⁠መዝሙር 104:​14, 15

ምን ብለህ ትደመድማለህ?

10. በኢዮብ 38:​33-38 ላይ የሚገኙትን ጥያቄዎች እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?

10 ራስህን በኢዮብ ቦታ አድርግና ሁሉን የሚችለው አምላክ እየጠየቀህ እንዳለ አድርገህ አስብ። ብዙ ሰዎች ድንቅ ለሆኑት የአምላክ ሥራዎች የሚገባውን ያህል ትኩረት እንደማይሰጡ ትስማማ ይሆናል። ይሖዋ በኢዮብ 38:​33-38 ላይ ያለውን ጥያቄ ይጠይቀናል:- “የሰማይን ሥርዓት ታውቃለህን? በምድርስ ላይ እንዲሠለጥን ልታደርግ ትችላለህን? የውኆች ብዛት ይሸፍንህ ዘንድ ቃልህን ወደ ደመናት ታነሣ ዘንድ ትችላለህን? መብረቆች ሄደው:- እነሆ፣ እዚህ አለን ይሉህ ዘንድ ልትልካቸው ትችላለህን? በውስጡስ ጥበብን ያኖረ፣ ለሰውስ ልብ ማስተዋልን የሰጠ ማን ነው? የሰማይን ደመና በጥበቡ ሊቈጥር የሚችል ማን ነው? ትቢያ በተበጠበጠ ጊዜ፣ ጓሎቹም በተጣበቁ ጊዜ፣ የሰማይን ረዋት ሊያዘነብል የሚችል ማን ነው?”

11, 12. አምላክ ድንቅ ሥራዎችን እንደሚፈጽም የሚያረጋግጡ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

11 ኤሊሁ ለኢዮብ ካነሳለት ነጥቦች መካከል ለመዳሰስ የሞከርነው ጥቂቶቹን ብቻ ነው። ይሖዋ “እንደ ሰው ወገብህን ታጠቅ” በማለት ለኢዮብ ካቀረበለት ጥያቄዎች መካከልም የተወሰኑትን ተመልክተናል። (ኢዮብ 38:​3) “የተወሰኑትን” ያልነው አምላክ በምዕራፍ 38 እና 39 ላይ ያነሳቸው ሌሎች አስደናቂ የሆኑ የተፈጥሮ ገጽታዎችም ስላሉ ነው። ለምሳሌ ያህል የሰማይ ከዋክብትን ክምችት አንስቷል። ሕጋቸውን ወይም ሥርዓታቸውን ሁሉ ጠንቅቆ የሚያውቅ ማን ነው? (ኢዮብ 38:​31-33) በተጨማሪም ይሖዋ የኢዮብ ትኩረት እንደ አንበሳና ቁራ፣ እንደ በረሃ ፍየልና የሜዳ አህያ፣ እንደ ጎሽና ሰጎን ከዚያም እንደ ብርቱው ፈረስና ንስር ባሉት ፍጥረታት ላይ እንዲያተኩር አድርጓል። ከዚያም ለእነዚህ የተለያዩ እንስሳት የተለያየ ባሕርይ በመስጠት በሕይወት እንዲኖሩና እንዲያድጉ ያደረጋቸው እሱ እንደሆነ አምላክ ለኢዮብ ጥያቄ አቅርቦለታል። በተለይ ፈረሶችን ወይም ሌሎች እንስሳትን የምትወድ ከሆነ እነዚህን ምዕራፎች ማጥናት ሊያስደስትህ ይችላል።​—⁠መዝሙር 50:​10, 11

12 በተጨማሪም ስለ ሁለት የተለዩ ፍጥረታት እንዲመልስለት ይሖዋ ለኢዮብ በድጋሚ ያቀረበው ጥያቄ የሚገኝባቸውን ምዕራፍ 40 እና 41ን ልትመረምር ትችላለህ። እነዚህ ፍጥረታት ግዙፍ ሰውነትና ጠንካራ አካል ያለው ጉማሬ (ብሄሞት) እና ኃይለኛው የናይል አዞ (ሌዋታን) ናቸው። ሁለቱም ቢሆኑ ትኩረታችንን ሊስቡ የሚገባቸው ድንቅ ፍጥረታት ናቸው። እስቲ አሁን ወደ ምን መደምደሚያ ላይ መድረስ እንዳለብን እንይ።

13. አምላክ ያቀረበለት ጥያቄ ኢዮብን የነካው እንዴት ነው? እኛንስ እንዴት ሊነካን ይገባል?

13 ኢዮብ ምዕራፍ 42 የአምላክ ጥያቄዎች በኢዮብ ላይ ምን ውጤት እንደነበራቸው ያሳየናል። ቀደም ሲል ኢዮብ ለራሱና ለሌሎች ሰዎች ከመጠን ያለፈ ትኩረት ሰጥቶ ነበር። ኢዮብ አምላክ ባቀረባቸው ጥያቄዎች አማካኝነት የተሰጠውን ግልጽ እርማት ከተቀበለ በኋላ የአስተሳሰብ ለውጥ አደረገ። እንዲህ በማለት ተናዝዟል:- “ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደ ሆንህ፣ አሳብህም ይከለከል ዘንድ ከቶ እንደማይቻል አወቅሁ። ያለ እውቀት ምክርን የሚሰውር ማን ነው? ስለዚህ እኔ የማላስተውለውን፣ የማላውቀውንም ድንቅ ነገር ተናግሬአለሁ።” (ኢዮብ 42:​2, 3) አዎን፣ ኢዮብ የአምላክን ሥራዎች ልብ ብሎ ከተመለከተ በኋላ እነዚህ ነገሮች እርሱ ሊገነዘብ ከሚችለው በላይ ድንቅ እንደሆኑ ተናግሯል። እኛም እስከ አሁን የተመለከትናቸው እነዚህ ድንቅ የፍጥረት ሥራዎች የአምላክን ታላቅ ጥበብና ኃይል በእኩል ደረጃ እንድናደንቅ ሊያደርጉን ይገባል። ውጤቱስ ምን ይሆናል? ከፍተኛ በሆነው ኃይሉና ችሎታው ተደንቀን ዝም ማለት ብቻ ነው? ወይስ ከዚያ ያለፈ ልናደርገው የሚገባ ነገር ይኖራል?

14. ዳዊት ለአምላክ ድንቅ ሥራዎች ምላሽ የሰጠው እንዴት ነው?

14 በመዝሙር 86 ላይ ዳዊት የተጠቀመባቸውን ከዚህ ጋር ተዛማጅነት ያላቸውን አገላለጾች የምናገኝ ሲሆን ዳዊት ከዚያ ቀደም ብሎ በሚገኝ መዝሙር ላይ እንደሚከተለው ብሏል:- “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፣ የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል። ቀን ለቀን ነገርን ታወጣለች፣ ሌሊትም ለሌሊት እውቀትን ትናገራለች።” (መዝሙር 19:​1, 2) ሆኖም ዳዊት ሌላም ነገር ጨምሮ ተናግሯል። መዝሙር 86:​10, 11 ላይ እንደሚከተለው እናነባለን:- “አቤቱ፣ ድንቅ የምታደርግ አንተ ታላቅ ነህና፣ አንተም ብቻህን ታላቅ አምላክ ነህና። አቤቱ፣ መንገድህን ምራኝ፣ በእውነትህም እሄዳለሁ፤ ስምህን ለመፍራት ልቤ ደስ ይለዋል።” ዳዊት ለፈጣሪ አስደናቂ የፍጥረት ሥራዎች የነበረው አድናቆት አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲያድርበት አድርጎታል። ይህ የሆነበትን ምክንያት መረዳት አትቸገርም። ዳዊት እነዚህን ድንቅ ሥራዎች ሊሠራ የሚችለውን አምላክ ማሳዘን አልፈለገም። እኛም አንፈልግም።

15. ዳዊት ለአምላክ የነበረው አክብሮታዊ ፍርሃት ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው?

15 አምላክ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ኃይል ስላለው የእሱን ሞገስ ባጡ ሰዎች ሁሉ ላይ ይህን ኃይሉን ሊጠቀም እንደሚችል ዳዊት ተገንዝቦ መሆን አለበት። ይህ ደግሞ ከባድ ጥፋት ይሆንባቸዋል። አምላክ ኢዮብን እንዲህ በማለት ጠይቆታል:- “በውኑ ወደ በረዶው ቤተ መዛግብት ገብተሃልን? የበረዶውንስ ቅንጣት ቤተ መዛግብት አይተሃልን? ይኸውም ለመከራ ጊዜ ለሰልፍና ለጦርነት ቀን የጠበቅሁት ነው።” በረዶ፣ የበረዶ ድንጋይ፣ ነፋስ ቀላቅሎ የሚዘንብ ዝናብ፣ ነፋስና መብረቅ አምላክ ሊጠቀምባቸው የሚችሉ የጦር መሣሪያዎች ናቸው። እንዴት ያለ አስገራሚ አቅም ያላቸው የተፈጥሮ ኃይሎች ናቸው!​—⁠ኢዮብ 38:​22, 23

16, 17. አምላክ ያለውን እጅግ ታላቅ ኃይል ለማስረዳት ምን ነገር እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል? አምላክስ ይህን የመሰለውን ኃይሉን ቀደም ባሉት ጊዜያት እንዴት ተጠቅሞበታል?

16 በአካባቢህ በአውሎ ነፋስ፣ በኃይለኛ ዶፍ ወይም በጎርፍ ምክንያት የደረሰ ጥፋት ካለ ታስታውስ ይሆናል። በምሳሌ ለማስረዳት ያህል በ1999 መጨረሻ አካባቢ በደቡብ ምዕራብ አውሮፓ የአየር ሁኔታ ጠበብትን ባስደነገጠ ከባድ ወዠብ ተመትቶ ነበር። የአውሎ ነፋሱ ፍጥነት በሰዓት 200 ኪሎ ሜትር ደርሶ የነበረ ሲሆን በሺህ የሚቆጠሩ የቤት ጣሪያዎችን ገነጣጥሏል፣ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎችን ገንድሷል፣ ከባድ ተሽከርካሪዎችን ገልብጧል። ምን ያህል ጥፋት እንደደረሰ ለመገመት ሞክር። ይህ ወዠብ 270 ሚልዮን የሚያክሉ ዛፎችን ከሥራቸው መንግሏል ወይም ከግንዳቸው ሰብሯል። ከፓሪስ ውጭ በሚገኘው የቬርሳይ መናፈሻ ብቻ 10, 000 የሚሆኑ ዛፎች ወድመዋል። በሚልዮን የሚቆጠሩ ቤተሰቦች መብራት ተቋርጦባቸዋል። የሟቾች ቁጥር 100 ደርሶ ነበር። ይህ ሁሉ ጥፋት የደረሰው በአጭር ጊዜ ውስጥ ነበር። እንዴት ያለ ኃይል ነው!

17 አንድ ሰው ወዠብ ማንም ሊያዘውና ሊቆጣጠረው የማይችል ድንገተኛ ክስተት ነው ብሎ ሊያስብ ይችላል። ይሁን እንጂ ለኃይሉ ዳርቻ የሌለውና ድንቅ ነገሮችን የሚያደርገው አምላክ እንደነዚህ ያሉትን ኃይሎች ተቆጣጥሮ ለተወሰነ ዓላማ ቢጠቀምባቸው ውጤቱ ምን ይሆናል? በአብርሃም ዘመን ይህን የመሰለ ነገር አድርጎ ነበር። አብርሃም የምድር ሁሉ ፈራጅ ሰዶምና ገሞራ የተባሉትን ሁለት ከተሞች ክፋት እንደመዘነ አወቀ። ምግባራቸው በጣም ተበላሽቶ ስለነበረ የክፋታቸው እሮሮ ወደ አምላክ ደርሶ ነበር። እርሱም ጻድቅ የሆኑ ሁሉ ለጥፋት ከተወሰኑት ከተሞች የሚወጡበትን መንገድ አዘጋጀ። ተመዝግቦ የሚገኘው ታሪክ “እግዚአብሔርም” በእነዚህ ከተሞች ላይ “ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ እሳትና ዲን አዘነበ” በማለት ይናገራል። ጻድቃንን አድኖ በጣም ክፉ የነበሩትን ሰዎች ማጥፋቱ እጅግ ድንቅ ሥራ ነበር።​—⁠ዘፍጥረት 19:​24

18. ኢሳይያስ ምዕራፍ 25 የሚጠቅሳቸው ድንቅ ነገሮች ምንድን ናቸው?

18 ከጊዜ በኋላ ደግሞ ይሖዋ በጥንቷ የባቢሎን ከተማ ምናልባትም በኢሳይያስ ምዕራፍ 25 ላይ በተጠቀሰችው ከተማ ላይ የጥፋት ፍርድ በየነ። አምላክ አንዲት ከተማ የፍርስራሽ ክምር እንደምትሆን ተንብዮ ነበር። “ከተማይቱን የድንጋይ ክምር፣ የተመሸገችውን ከተማ ውድማ እንድትሆን፣ የኃጥአንንም አዳራሽ ከተማ እንዳትሆን አድርገሃል፤ ከቶ አትሠራም።” (ኢሳይያስ 25:​2) በአሁኑ ጊዜ የጥንቷ ባቢሎን የነበረችበትን አካባቢ የሚጎበኙ ጎብኚዎች ይህ ሁሉ በትክክል መፈጸሙን ሊያረጋግጡ ይችላሉ። የባቢሎን ጥፋት እንዲያው ያጋጣሚ ክስተት ነው? በፍጹም አይደለም። ከዚህ ይልቅ በሚከተለው የኢሳይያስ አባባል እኛም ልንስማማ እንችላለን:- “አቤቱ፣ አንተ አምላኬ ነህ፤ ድንቅን ነገር የዱሮ ምክርን በታማኝነትና በእውነት አድርገሃልና ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ ስምህንም አመሰግናለሁ።”​—⁠ኢሳይያስ 25:​1

ወደፊት የሚከናወኑ ድንቅ ሥራዎች

19, 20. ኢሳይያስ 25:​6-8 ምን ፍጻሜ ያገኛል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን?

19 አምላክ ከላይ የተጠቀሰው ትንቢት ጥንት ፍጻሜውን እንዲያገኝ እንዳደረገ ሁሉ ወደፊትም ድንቅ ነገር ያደርጋል። አምላክ ስለሚያደርጋቸው “ድንቅ ሥራዎች” ከሚናገረው እዚህ የኢሳይያስ ትንቢት ውስጥ ወደፊት የሚፈጸም አስተማማኝ ትንቢትም እናገኛለን። ይህ ትንቢት በባቢሎን ላይ እንደተፈጸመው ትንቢት በትክክል እንደሚፈጸም የተረጋገጠ ነው። ቃል የተገባልን ‘አስደናቂ’ ተስፋ ምንድን ነው? ኢሳይያስ 25:​6 እንዲህ ይላል:- “የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔርም ለሕዝብ ሁሉ በዚህ ተራራ ላይ ታላቅ የሰባ ግብዣ፣ ያረጀ የወይን ጠጅ፣ ቅልጥም የሞላባቸው የሰቡ ነገሮች፣ የጥሩና ያረጀ የወይን ጠጅ ግብዣ ያደርጋል።”

20 ይህ ከፊታችን በሚመጣው የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ በእርግጠኝነት ይፈጸማል። በዚያን ወቅት የሰው ልጅ በአሁኑ ጊዜ ብዙዎችን እየደቆሱ ካሉት ችግሮች ይገላገላል። እንዲያውም በኢሳይያስ 25:​7, 8 ላይ የሚገኘው ትንቢት አምላክ የመፍጠር ኃይሉን በመጠቀም በዘመናት ሁሉ ሆኖ የማያውቅ ነገር እንደሚያደርግ ዋስትና ይሰጠናል። “በዚህም ተራራ ላይ በወገኖች ሁሉ ላይ የተጣለውን መጋረጃ፣ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተዘረጋውን መሸፈኛ ያጠፋል። ሞትን ለዘላለም ይውጣል፣ ጌታ እግዚአብሔርም ከፊት ሁሉ እንባን ያብሳል፣ የሕዝቡንም ስድብ ከምድር ሁሉ ላይ ያስወግዳል፤ እግዚአብሔር ተናግሮአልና።” ሐዋርያው ጳውሎስ ከጊዜ በኋላ ከዚህ ትንቢት በመጥቀስ አምላክ ሙታንን በማስነሳት ወደ ሕይወት ከሚመልስበት ሁኔታ ጋር አያይዞታል። ይህ እንዴት ያለ ድንቅ ሥራ ይሆናል!​—⁠1 ቆሮንቶስ 15:​51-​54

21. አምላክ ሙታንን በተመለከተ ምን ድንቅ ሥራ ያከናውናል?

21 የሐዘንና የመከራ እንባ ፈጽሞ የሚጠፋበት ሌላው ምክንያት የሰው ልጆች ከነበሩባቸው አካላዊ እክሎችና ሕመሞች ነፃ ስለሚሆኑ ነው። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ማየት ለተሳናቸው ብርሃን፣ መስማት ለተሳናቸው የመስማት ችሎታ፣ ለአካል ጉዳተኞች የተሟላ አካል በመመለስ ብዙዎችን ፈውሷል። ዮሐንስ 5:​5-9 ለ38 ዓመታት ሽባ ሆኖ የኖረን አንድ ሰው እንደፈወሰ ይገልጻል። ይህን የተመለከቱ ሰዎች በጣም ድንቅ የሆነ ተዓምር በማለት ተናግረው ነበር። በእርግጥም ነበር! ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከዚህ ይበልጥ አስደናቂ የሆነ ነገር ማለትም የሙታን ትንሣኤም እንደሚያከናውን ተናግሯል። “በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ።”​—⁠ዮሐንስ 5:​28, 29

22. ድሆችና የተጠቁ ሰዎች የወደፊቱን ጊዜ በተስፋ ሊጠባበቁ የሚችሉት ለምንድን ነው?

22 ይህን የተናገረው ይሖዋ በመሆኑ ይህ መፈጸሙ የማይቀር ነው። ታላቅ ኃይሉን ተቆጣጥሮ ሲጠቀምበት ውጤቱ በጣም አስደናቂ እንደሚሆን እርግጠኛ ሁን። መዝሙር 72 ንጉሥ በሆነው በልጁ አማካኝነት ምን እንደሚያደርግ ይገልጻል። በዚያን ጊዜ ጻድቃን ያብባሉ። ሰላም ይትረፈረፋል። አምላክ ድሆችንና የተጠቁ ሰዎችን ነፃ ያወጣል። የሚከተለውን ተስፋ ሰጥቷል:- “በምድር ውስጥ በተራሮች ላይ መጠጊያ ይሆናል፤ ፍሬውም ከሊባኖስ ይልቅ ከፍ ከፍ ይላል፤ እንደ ምድር ሣር በከተማ ይበቅላል።”​—⁠መዝሙር 72:​16

23. የአምላክ ድንቅ ሥራዎች ምን እንድናደርግ ሊገፋፉን ይገባል?

23 በእርግጥም የይሖዋን ድንቅ ሥራዎች በሙሉ ማለትም ከአሁን በፊት ያደረጋቸውን፣ በአሁኑ ጊዜ እያደረጋቸው ያሉትን እንዲሁም ወደፊት በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚያደርጋቸውን ሥራዎች ልብ እንድንል የሚያስገድዱ በጣም ብዙ ምክንያቶች አሉ። “ብቻውን ተአምራትን የሚያደርግ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ። የምስጋናው ስም ለዓለምና ለዘላለም ይባረክ፤ ምስጋናውም ምድርን ሁሉ ይምላ። ይሁን፤ ይሁን።” (መዝሙር 72:​18, 19) ይህ ለዘመዶቻችንም ሆነ ለሌሎች ሰዎች ሞቅ ባለ ስሜት ዘወትር ልንናገርለት የሚገባ ርዕሰ ጉዳይ ነው። አዎን፣ “ምስጋናና ኃይሉን፣ ያደረገውንም ተኣምራት [“ድንቅ ሥራ፣” NW ]” እንናገር።​—⁠መዝሙር 78:​3, 4፤ 96:​3, 4

እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?

• ለኢዮብ የቀረቡለት ጥያቄዎች ሰብአዊ እውቀት ውስን መሆኑን የሚያጎሉት እንዴት ነው?

በኢዮብ ምዕራፍ 37-41 ላይ ለምሳሌ ያህል ከተጠቀሱት የአምላክ ድንቅ ሥራዎች መካከል አንተን በጣም ያስደነቀህ ምንድን ነው?

• ከአምላክ ድንቅ ሥራዎች መካከል የተወሰኑትን ከመረመርን በኋላ ምን ምላሽ መስጠት ይኖርብናል?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አንዳቸው ከሌላው ፈጽሞ ስለማይመሳሰሉት የበረዶ ቅንጣቶችና አስፈሪ ኃይል ስላለው መብረቅ ስታስብ ምን ይሰማሃል?

[ምንጭ]

snowcrystals.net

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክ ድንቅ ሥራዎች ዘወትር ከሌሎች ጋር የምታደርገው ውይይት ክፍል እንዲሆኑ አድርግ