ድንቅ ነገር የሚያደርገውን ፈጣሪ ተመልከቱ!
ድንቅ ነገር የሚያደርገውን ፈጣሪ ተመልከቱ!
“ቁም፣ የእግዚአብሔርንም ተአምራት [“ድንቅ ሥራዎች፣” Nw ] አስብ።”—ኢዮብ 37:14
1, 2. በ1922 ምን አስደናቂ ነገር ተገኘ? ያገኙት ሰዎችስ ምን ተሰማቸው?
አርኪኦሎጂስቱና የእንግሊዙ ባላባት ውድ ሀብት በመፈለግ ለዓመታት አብረው ሲሠሩ ቆይተዋል። በመጨረሻም አርኪኦሎጂስቱ ሀዋርድ ካርተር እና ሎርድ ካርናርቨን ከብዙ ድካም በኋላ ኅዳር 26, 1922 የነገሥታት ሸለቆ በመባል በሚታወቀው በግብጽ ፈርዖኖች የመቃብር ሥፍራ የፈርዖን ቱታንክሀሜንን መቃብር አገኙ። ያገኙትን የታሸገ በር በመሰርሰሪያ በመብሳት ቀዳዳ አበጁለት። ካርተር በቀዳዳው በኩል በሻማ ብርሃን ወደ ውስጥ አጮልቆ ተመለከተ።
2 ካርተር በኋላ እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ሎርድ ካርናርቨን በጣም ከመጓጓቱ የተነሳ አላስችል ስላለው ‘የሚታይህ ነገር አለ?’ ሲል ጠየቀኝ። የምለው ጠፍቶኝ ‘አዎን፣ ድንቅ ነገሮች ይታዩኛል’ አልኩት።” በመቃብሩ ውስጥ ከነበሩት በሺዎች የሚቆጠሩ ውድ ነገሮች መካከል ከወርቅ የተሠራ አንድ ድፍን የሬሳ ሣጥን ይገኝበታል። ከእነዚህ “ድንቅ ነገሮች” መካከል አንዳንዶቹን በፎቶግራፍ አሊያም ሙዚየም ውስጥ ተቀምጠው አይተሃቸው ሊሆን ይችላል። እነዚህ በሙዚየም ውስጥ የተቀመጡ ነገሮች የቱንም ያህል ድንቅ ቢሆኑ ከአንተ ሕይወት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌላቸው የታወቀ ነው። እንግዲያው ያለምንም ጥርጥር ከአንተ ጋር ግንኙነት ባላቸውና አንተም ከፍ ያለ ግምት በምትሰጣቸው ነገሮች ላይ እናተኩር።
3. ለእኛ ትልቅ ዋጋ ሊኖራቸው ስለሚችሉ ድንቅ ነገሮች ማወቅ የምንችለው ከየት ነው?
3 ለምሳሌ ያህል ከብዙ መቶ ዘመናት በፊት ይኖር ስለነበረና ከማንኛውም የታወቀ የፊልም ተዋናይ፣ የስፖርት ጀግና ወይም የንጉሣን ቤተሰብ አባል ይበልጥ ሊታሰብ ስለሚገባው አንድ ሰው መለስ ብለህ አስብ። በምሥራቅ ካሉ ሰዎች ሁሉ ይልቅ ታላቅ ተብሏል። ስሙን ታውቀዋለህ፤ ኢዮብ ይባላል። ስለ እርሱ ብቻ የተጻፈ አንድ ሙሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አለ። ይሁን እንጂ በዘመኑ ይኖሩ ከነበሩ ሰዎች መካከል ኤሊሁ የሚባል አንድ ወጣት ኢዮብን ማረም አስፈልጎት ነበር። ኤሊሁ፣ ኢዮብ ከልክ በላይ ስለራሱና አብረውት ስለነበሩት ሰዎች እንደተጨነቀ ገለጸ። በኢዮብ ምዕራፍ 37 ላይ ለእያንዳንዳችን ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ቀጥተኛ የሆኑና ጥበብ የሞላባቸው ተጨማሪ ምክሮች እናገኛለን።—ኢዮብ 1:1-3፤ 32:1–33:12
4. ኤሊሁ በኢዮብ 37:14 ላይ የሚገኘውን ማሳሰቢያ እንዲሰጥ ያደረገው ምንድን ነው?
4 ሦስቱ የኢዮብ ጓደኛ ተብዬዎች ኢዮብ በሐሳብ አሊያም በድርጊት ስህተት ሠርቷል ብለው ባሰቡት አቅጣጫ ሁሉ ብዙ ተናግረው ነበር። (ኢዮብ 15: 1-6, 16፤ 22:5-10) ኤሊሁ ንግግራቸውን እስኪጨርሱ ድረስ በትዕግሥት ከጠበቀ በኋላ ማስተዋልና ጥበብ የተሞላበት ንግግር ተናገረ። ብዙ ጠቃሚ ነጥቦችን የተናገረ ቢሆንም የሚከተለውን ቁልፍ ነጥብ ልብ በል:- “ኢዮብ ሆይ፣ ይህን ስማ፤ ቁም፣ የእግዚአብሔርንም ተአምራት [“ድንቅ ሥራዎች፣” NW ] አስብ።”—ኢዮብ 37:14
ድንቅ ሥራዎችን የሠራው አምላክ
5. ኤሊሁ የጠቀሳቸው “የአምላክ ድንቅ ሥራዎች” ምን ነገሮችን ይጨምራሉ?
5 እዚህ ላይ ኤሊሁ፣ ኢዮብ በራሱ ወይም በኤሊሁ ወይም በሌላ በማንኛውም ሰው ላይ ትኩረት እንዲያደርግ እንዳልተናገረ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ኤሊሁ፣ ኢዮብም ሆነ እኛ የይሖዋ አምላክን ድንቅ ሥራዎችና መንገዶች ልብ እንድንል ጥበብ ያለበት ምክር ሰጥቷል። ‘የአምላክ ድንቅ ሥራዎች’ የሚለው ሐረግ ምን ነገሮችን የሚያካትት ይመስልሃል? ስለ ጤና፣ ስለ ገንዘብ ነክ ጉዳዮች፣ ስለ ወደፊቱ ሁኔታ፣ ስለ ቤተሰብህ፣ ስለ ሥራ ባልደረቦችህና ስለ ጎረቤቶችህ የምታስበው ሳያንስ ስለ አምላክ ሥራዎች ማሰብ ለምን አስፈለገ? የይሖዋ አምላክ ድንቅ ሥራዎች የእሱን ጥበብና በዙሪያችን ባሉት የፍጥረት ሥራዎቹ ላይ ያለውን ሥልጣን እንደሚጨምሩ ምንም ጥያቄ የለውም። (ነህምያ 9:6፤ መዝሙር 24:1፤ 104:24፤ 136:5, 6) ይህ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆንልህ በኢያሱ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝ አንድ ነጥብ ልብ በል።
6, 7. (ሀ) ይሖዋ በሙሴና በኢያሱ ዘመን ምን ድንቅ ሥራዎችን አከናውኗል? (ለ) በሙሴና በኢያሱ ዘመን ከተከናወኑት ከእነዚህ ድንቅ ሥራዎች አንዱን የማየት አጋጣሚ አግኝተህ ቢሆን ኖሮ ምን ምላሽ ትሰጥ ነበር?
6 ይሖዋ የጥንቶቹን እስራኤላውያን ነፃ ለማውጣት በጥንቷ ግብፅ ላይ መቅሰፍቶችን ከማውረዱም በላይ ቀይ ባሕርን በመክፈል ሙሴ እየመራ ነፃ እንዲያወጣቸው አድርጓል። (ዘጸአት 7:1–14:31፤ መዝሙር 106:7, 21, 22) በኢያሱ ምዕራፍ 3 ላይም የተጠቀሰ ተመሳሳይ ክንውን አለ። በሙሴ እግር የተተካው ኢያሱ የአምላክን ሕዝቦች እየመራ አንድ ትልቅ ወንዝ አሻግሮ ወደ ተስፋይቱ ምድር ማስገባት ነበረበት። ኢያሱ “ነገ እግዚአብሔር በመካከላችሁ ድንቅ ነገር ያደርጋልና ተቀደሱ” ሲል ተናግሯል። (ኢያሱ 3:5) ይህ ድንቅ ነገር ምን ነበር?
7 ይሖዋ እንቅፋት የሆነባቸውን ውኃ ማለትም የዮርዳኖስን ወንዝ ከፍሎ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናትን በደረቅ ምድር እንዳሻገረ ታሪኩ ይገልጻል። (ኢያሱ 3:7-17) በዚህ ቦታ ኖረን ቢሆንና ወንዙ ተከፍሎ ያ ሁሉ ሕዝብ ሲሻገር ብንመለከት በዚህ በጣም ድንቅ የሆነ ክንውን እንደምንገረም አያጠራጥርም! አምላክ በፍጥረት ላይ ያለውን ኃይል ያሳየ ነበር። ይሁን እንጂ በዚሁ በእኛም ዘመን ከዚህ የማይተናነሱ ድንቅ ነገሮች አሉ። ከእነዚህ ነገሮች አንዳንዶቹ ምን እንደሆኑና ለእነዚህ ድንቅ ነገሮች ለምን ትኩረት መስጠት እንደሚገባን ለማየት እንድንችል ኢዮብ ምዕራፍ 37:5-7ን ትኩረት ሰጥተን እንመርምር።
8, 9. ኢዮብ 37:5-7 የሚጠቅሳቸው ድንቅ ሥራዎች ምንድን ናቸው? እኛ ስለ እነዚህ ድንቅ ሥራዎች ማሰብ የሚገባን ለምንድን ነው?
8 ኤሊሁ “እግዚአብሔር በድምፁ ድንቅኛ ያንጐደጉዳል፤ እኛም የማናስተውለውን ታላቅ ነገር ያደርጋል” ሲል ተናግሯል። ኤሊሁ “ድንቅኛ” ያለው የትኛውን የአምላክ ሥራ አስቦ ነው? በረዶንና ውሽንፍርን ይጠቅሳል። እነዚህ ነገሮች በእርሻው ላይ የሚሠራውን ገበሬ ሥራውን ስለሚያስተጓጉሉበት የአምላክን ሥራዎች ቆም ብሎ ለማሰብ ጊዜና ምክንያት እንዲያገኝ ያደርጉታል። እኛ ገበሬዎች ላንሆን እንችላለን፤ ቢሆንም እንደምንኖርበት አካባቢ መጠኑ ይለያይ እንጂ በረዶና ዝናብ እንቅስቃሴዎቻችንን ሊያስተጓጉሉብን ይችላሉ። ታዲያ በዚህ ጊዜ ከእነዚህ ድንቅ ነገሮች በስተጀርባ ያለው ኃይል ማን እንደሆነና ምን ትርጉም እንዳላቸው አስበን እናውቃለን? አንተ በግልህ ስለ እነዚህ ነገሮች ትንሽ ቆም ብለህ አስበህ ታውቃለህ?
9 በኢዮብ ምዕራፍ 38 ላይ እንደምናነበው ይሖዋ አምላክ ራሱ ጥልቅ ትርጉም ያላቸው ጥያቄዎችን ለኢዮብ ባቀረበበት ወቅት የተጠቀመው ተመሳሳይ ዘዴ ነው። ምንም እንኳ ፈጣሪያችን እነዚህን ጥያቄዎች ያቀረበው ለኢዮብ ቢሆንም በእኛ፣ በዝንባሌያችን፣ በሕልውናችንና በወደፊት ሕይወታችን ላይ ለውጥ እንደሚያመጡ የታወቀ ነው። ስለዚህ አምላክ የጠየቃቸውን ጥያቄዎችና እነዚህ ጥያቄዎች በሕይወታችን ላይ የሚኖራቸውን ትርጉም እንመልከት። አዎን፣ ኢዮብ 37:14 እንደሚመክረን እናድርግ።
10. ኢዮብ ምዕራፍ 38 እኛን ሊነካን የሚገባው እንዴት ነው? ምን ጥያቄዎችንስ ያነሳል?
10 ምዕራፍ 38 “እግዚአብሔርም በዐውሎ ነፋስ ውስጥ ሆኖ ለኢዮብ መለሰ እንዲህም አለ:- ያለ እውቀት በሚነገር ቃል ምክርን የሚያጨልም ይህ ማነው? እንግዲህ እንደ ሰው ወገብህን ታጠቅ፤ እጠይቅሃለሁ፣ አንተም ተናገረኝ” በማለት ይጀምራል። (ኢዮብ 38:1-3) ይህ ቀጥሎ ለሚሆነው ነገር የሚያዘጋጅ ጥያቄ ነበር። ይህ ጥያቄ ኢዮብ በአጽናፈ ዓለም ፈጣሪ ፊት እንደቆመና ለእሱ መልስ መስጠት እንዳለበት በመገንዘብ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል ረድቶታል። እኛም ሆን በዚህ ዘመን ያለ ማንኛውም ሰው እንዲህ የመሰለውን አስተሳሰብ መያዙ ጥሩ ነው። ከዚያም አምላክ ኤሊሁ ከጠቀሳቸው ጋር የሚመሳሰሉ ነጥቦችን ያነሳል። “ምድርን በመሠረትሁ ጊዜ አንተ ወዴት ነበርህ? ታስተውል እንደ ሆንህ ተናገር። ብታውቅስ መሠፈሪያዋን የወሰነ፣ በላይዋስ የመለኪያ ገመድ የዘረጋ ማን ነው? አጥቢያ ኮከቦች በአንድነት ሲዘምሩ፣ የእግዚአብሔርም ልጆች ሁሉ እልል ሲሉ፣ መሠረቶችዋ በምን ላይ ተተክለው ነበር? የማዕዘንዋንስ ድንጋይ ያቆመ ማን ነው?”—ኢዮብ 38:4-6
11. ኢዮብ 38:4-6 ምን እንድንገነዘብ ሊያደርገን ይገባል?
11 ምድር በተሠራችበት ጊዜ ኢዮብ የት ነበር? ከመካከላችንስ በዚያን ጊዜ በሕይወት የነበረ ሰው ይገኛል? ከመካከላችን የምድርን የአሠራር ንድፍ ያወጣ ወይም ያንን ንድፍ ተጠቅሞ በማስመሪያ እየለካ ያስቀመጣት ይኖራልን? እንደማይኖር ግልጽ ነው! በዚህ ጊዜ የሰው ልጆች ገና ወደ ሕልውና አልመጡም። አምላክ ምድራችንን ልክ እንደ ሕንፃ በመውሰድ “የማዕዘንዋንስ ድንጋይ ያቆመ ማን ነው?” በማለት ይጠይቃል። በዚህች ምድር ላይ ተመቻችተን ለመኖር የቻልነው ፀሐይ በትክክለኛው ርቀት ላይ ስለተቀመጠች እንደሆነ እናውቃለን። መጠኗም ቢሆን ትክክለኛ ነው። ምድራችን አሁን ካላት መጠን ብትተልቅ ኖሮ ሃይድሮጂን የተባለው ጋዝ ከባቢ አየራችንን ለቅቆ መውጣት ስለማይችል ምድር ለመኖሪያነት የማትመች ትሆን ነበር። ‘የማዕዘንዋን ድንጋይ’ ትክክለኛው ቦታ ላይ ያስቀመጠ አንድ አካል እንዳለ ግልጽ ነው። ታዲያ ለዚህ ሁሉ መመስገን የሚገባው ማን ነው? ኢዮብ? እኛ? ወይስ ይሖዋ አምላክ?—ምሳሌ 3:19፤ ኤርምያስ 10:12
ማን ሊመልስ ይችላል?
12. በኢዮብ 38:6 ላይ የሚገኘው ጥያቄ ስለ ምን ነገር እንድናስብ ያደርገናል?
12 በተጨማሪም አምላክ “መሠረቶችዋ በምን ላይ ተተክለው ነበር?” የሚል ጥያቄ አንስቷል። ይህ ጥሩ ጥያቄ አይደለምን? እኛ ኢዮብ የማያውቀውን ስበት የሚባል ቃል እናውቅ ይሆናል። እንዲያውም አብዛኞቻችን ምድራችን ከቦታዋ ሳትዛነፍ በሌላ አነጋገር መሠረቶችዋ ተተክለው እንድትኖር ያስቻላት ግዙፍ መጠን ያላት የፀሐይ ስበት እንደሆነ እንገነዘባለን። ይሁን እንጂ ስበት ምን እንደሆነስ ሙሉ በሙሉ የሚረዳ ማን ነው?
13, 14. (ሀ) ስበትን በተመለከተ አምነን መቀበል ያለብን ነገር ምንድን ነው? (ለ) ኢዮብ 38:6 ጎላ አድርጎ ለሚገልጸው ሁኔታ ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት ይኖርብናል?
13 ዘ ዩኒቨርስ ኤክስፕሌይንድ የሚል ርዕስ ያለው በቅርቡ የታተመ አንድ መጽሐፍ ‘ከተፈጥሮ ኃይሎች ሁሉ የስበትን ያህል በብዙ ሰዎች ዘንድ የታወቀ፣ ሆኖም በቂ ግንዛቤ ያልተገኘበት ርዕሰ ጉዳይ የለም’ በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል። አክሎም “የስበት ኃይል ምንም ዓይነት መጓጓዣ መንገድ ሳይኖረው ባዶውን ሕዋ በቅጽበት ያቋርጣል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ስበት የሚጓዘው ግራቪቶንስ የሚባሉ ቅንጣቶች በሚፈጥሩት ሞገድ ሳይሆን እንደማይቀር የፊዚክስ ሊቃውንት ግምታዊ ሐሳብ መሰንዘር ጀምረዋል። . . . ይሁን እንጂ ግራቪቶንስ የሚባሉ ቅንጣቶች መኖራቸውን በእርግጠኝነት ሊናገር የሚችል ሰው የለም።” ይህ ምን ማለት እንደሆነ አስብ።
14 ይሖዋ እነዚህን ጥያቄዎች ለኢዮብ ካቀረበለት ወዲህ ሳይንስ የ3, 000 ዓመታት እድገት አድርጓል። ያም ሆኖ እኛም ሆን የፊዚክስ ሊቃውንት ምድራችን እኛን በሕይወት ለማኖር በሚያስችላት ቦታ ላይ ምህዋሯን ጠብቃ እንድትኖር ስለሚያደርጋት ስበት ምንነት ሙሉ ማብራሪያ መስጠት አንችልም። (ኢዮብ 26:7፤ ኢሳይያስ 45:18) ይህን ያነሳነው ሁላችንም ስለ ስበት ምሥጢር ለማወቅ ጥልቅ ጥናት ማካሄድ እንደሚያስፈልገን ለማሳሰብ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይህን አንድ የአምላክ ድንቅ ሥራ ብቻ በትኩረት መመልከታችን እንኳ ስለ እሱ ያለንን አመለካከት ሊነካው እንደሚገባ ለማሳሰብ ነው። ስለ አምላክ ታላቅነት፣ ጥበብና እውቀት ያለህ አድናቆት እንዲጨምር አድርጓልን? ስለ ፈቃዱ ተጨማሪ ትምህርት መቅሰም አስፈላጊ የሆነበትንስ ምክንያት ይበልጥ አስገንዝቦሃል?
15-17. (ሀ) ኢዮብ 38:8-11 የሚያተኩረው በምን ላይ ነው? ወደየትኞቹ ጥያቄዎችስ ይመራል? (ለ) ስለ ውቅያኖሶችና በምድር የተለያዩ ክፍሎች ስለመገኘታቸው ያለውን እውቀት በተመለከተ ምን ነገር አምኖ መቀበል ግድ ነው?
15 ፈጣሪ ጥያቄዎቹን በዚህ ብቻ አላቆመም። “ከማኅፀን እንደሚወጣ በወጣ ጊዜ፣ ባሕርን በመዝጊያዎች የዘጋ ማን ነው? ደመናውን ለልብሱ፣ ጨለማንም ለመጠቅለያው አደረግሁ፤ ድንበሩን በዙሪያው አድርጌ፣ መወርወሪያዎቹንና መዝጊያዎቹን አኑሬ:- እስከዚህ ድረስ ድረሺ፣ አትለፊ፤ በዚህም ለትዕቢተኛው ማዕበልሽ ገደብ ይሁን አልሁ።”—ኢዮብ 38:8-11
16 እዚህ ላይ የተጠቀሰው ባሕርን ስለመዝጋት የሚገልጸው ሐሳብ አሕጉሮችን፣ ውቅያኖሶችንና የባሕር ሞገዶችን ይጨምራል። የሰው ልጅ እነዚህን ነገሮች ማጥናት ከጀመረ ምን ያህል ዓመት ሆኖታል? የሰው ልጅ ለብዙ ሺህ ዓመታት ይህን ጉዳይ በተመለከተ ሲያጠና የኖረ ቢሆንም በተለይ ባለፈው መቶ ዘመን በዚህ መስክ ጥልቀት ያለው ምርምር አካሂዷል። ስለ እነዚህ ነገሮች መታወቅ የሚገባው ነገር ሁሉ ታውቆ ሳያልቅ አይቀርም ብለህ ትገምት ይሆናል። ይሁን እንጂ በዚህ በያዝነው 2001 እንኳ ወደ ትላልቅ ቤተ መጻሕፍት ሄደህ ወይም ሰፊ ምርምር ለማድረግ የሚያስችለውን ኢንተርኔት በመጠቀም በዚህ መስክ ምን ያህል እውቀት እንደተገኘ ጥልቅ ምርምር ብታደርግ ምን ታገኛለህ?
17 ሰፊ ተቀባይነት ባገኘ አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ላይ የሚከተለውን ሐሳብ ታገኛለህ:- “በአሕጉር የተከፋፈለው የብስና የውቅያኖስ ዝብጦች እንዲሁም ዋና ዋና መልከአ ምድራዊ ገጽታዎች በየስፍራው መገኘታቸው ለበርካታ ዓመታት ለሳይንሳዊ ምርምርና ንድፈ ሐሳብ ራስ ምታት ሆኖ ቆይቷል።” ይህ ኢንሳይክሎፔዲያ ይህን ካለ በኋላ መልስ ሊሆኑ ይችላሉ ብሎ ያሰባቸውን አራት ማብራሪያዎች ይጠቅስና “እነዚህ በርካታ ከሆኑት መላ ምቶች ጥቂቶቹ ብቻ” እንደሆኑ ይገልጻል። ደግሞም እንደምታውቀው መላ ምት “ሊለወጥ የሚችል ጊዜያዊ ማብራሪያ ከማቅረብ የማያልፍ ተጨባጭ ማስረጃ የሌለው ሐሳብ” ነው።
18. ኢዮብ 38:8-11 ወደ ምን መደምደሚያ ይመራሃል?
18 ታዲያ ይህ በኢዮብ 38:8-11 ላይ የሚገኙት ጥያቄዎች ወቅታዊ መሆናቸውን አያስገነዝበንም? ፕላኔታችን አሁን ያላትን መልክ ይዛ በመገኘቷ ከመካከላችን ሊመሰገን የሚገባው እንደሌለ የተረጋገጠ ነው። ጨረቃን በአብዛኛው በባሕር ዳርቻዎችም ሆነ በግል በእኛ ላይ ጉዳት የማያደርስ የባሕር ሞገድ መፍጠር የሚያስችል የስበት ኃይል ኖሯት እንድትቀመጥ ያደረግነው እኛ አይደለንም። ይህን ያደረገው የድንቅ ነገሮች ሠሪ መሆኑን ታውቃለህ።—መዝሙር 33:7፤ 89:9፤ ምሳሌ 8:29፤ ሥራ 4:24፤ ራእይ 14:7
ለይሖዋ የሚገባውን ክብር ስጡት
19. በኢዮብ 38:12-14 ላይ የሚገኘው ውስጠ ወይራ አነጋገር የሚገልጸው በግዑዙ ዓለም ያለ እውነታ ምንድን ነው?
19 በኢዮብ 38:12-14 ላይ በተዘዋዋሪ መንገድ በተገለጸው መሠረት ምድር በራሷ ዛቢያ ላይ በመዞርዋ የሰው ልጆች ሊመሰገኑ አይችሉም። ይህ የምድር መሽከርከር ብዙውን ጊዜ አስደናቂ ውበት ተላብሶ የሚታየውን የማለዳ ወገግታ ያስገኛል። ጀንበሯ ከፍ እያለች በሄደች መጠን ያረፈበትን የማኅተም ቅርጽ ተቀብሎ በግልጽ እንደሚያሳይ ሸክላ የምድራችን ገጽታዎች መታየት ይጀምራሉ። ትንሽ እንኳ ቆም ብለን ስለ ምድር እንቅስቃሴ ብናስብ መደነቃችን አይቀርም። ምክንያቱም አሁን ካላት በበለጠ በፍጥነት የምትሾር ቢሆን ኖሮ በቀላሉ መገመት እንደምንችለው በጣም አደገኛ ይሆን ነበር። የአዟዟሯ ፍጥነት ቢቀንስ ቀኑና ሌሊቱ በጣም ረዣዥም ስለሚሆን ከፍተኛ የሆነ ሙቀትና ቅዝቃዜ ይፈራረቅ ነበር። ይህ ደግሞ የሰውን ልጅ ሕይወት አደጋ ላይ ይጥለዋል። የምድርን ፍጥነት የወሰነው አንድ የሰዎች ቡድን ሳይሆን አምላክ በመሆኑ ደስ ሊለን ይገባል?—መዝሙር 148:1-5
20. በኢዮብ 38:16, 18 ላይ ለቀረቡት ጥያቄዎች የምትሰጠው ምላሽ ምንድን ነው?
20 አሁን ደግሞ አምላክ እነዚህን ተጨማሪ ጥያቄዎች እየጠየቀህ እንዳለ አድርገህ አስብ:- “ወደ ባሕር ምንጭስ ውስጥ ገብተሃልን? በቀላዩስ መሠረት ውስጥ ተመላልሰሃልን?” አንድ የውቅያኖስ ተመራማሪ እንኳ ለእነዚህ ጥያቄዎች ሙሉ የአዎንታ መልስ መስጠት አይችልም! “ምድርንስ በስፋትዋ አስተውለሃታልን? ሁሉን አውቀህ እንደ ሆነ ተናገር።” (ኢዮብ 38:16, 18) ሁሉንም የምድር ክፍል ይቅርና አብዛኛውንስ ተዘዋውረህ ለማየት ችለሃል? በምድር ላይ የሚገኙትን ውብና አስደናቂ አካባቢዎች በሙሉ አይቶ ለመጨረስ የስንት ሰው ዕድሜ ያስፈልጋል? በዚህ ዓይነት የምታሳልፈው ዕድሜስ ምን ያህል አስደሳች ይሆን ነበር!
21. (ሀ) በኢዮብ 38:19 ላይ የሚገኙት ጥያቄዎች ምን ሳይንሳዊ ጥያቄ ያስነሳሉ? (ለ) ስለ ብርሃን ያሉት እውነታዎች ምን እንድናደርግ ሊገፋፉን ይገባል?
21 በተጨማሪም በኢዮብ 38:19, 20 ላይ የሚገኙትን የሚከተሉትን አመራማሪ ጥያቄዎች ተመልከቱ:- “የብርሃን መኖሪያ መንገድ የት ነው? የጨለማውስ ቦታ ወዴት አለ?” ብርሃን በኩሬ ላይ እንደሚታየው አዝዋሪት በሞገድ መልክ ይጓዛል የሚለው አመለካከት ከብዙ ዓመታት በፊት ጀምሮ በሰፊው ሲታመንበት የቆየ ነገር እንደነበር ሳታውቅ አትቀርም። በ1905 ደግሞ አልበርት አንስታይን ብርሃን የኃይል ቅንጣት ባሕርይ አለው የሚል ንድፈ ሐሳብ አቀረበ። ይህ ንድፈ ሐሳብ ለጉዳዩ እልባት አስገኝቷልን? በቅርቡ የታተመ አንድ ኢንሳይክሎፔዲያ እንዲህ ሲል ይጠይቃል:- “ብርሃን ሞገድ ነው ወይስ ቅንጣት?” መልሱን ሲሰጥ “[ሞገድና ቅንጣት] በጣም የተለያዩ ነገሮች በመሆናቸው [ብርሃን] ሁለቱንም ሊሆን አይችልም። ከሁሉም የተሻለው መልስ ብርሃን ሁለቱንም አይደለም የሚለው ነው” ብሏል። ይህንን ድንቅ የአምላክ ሥራ በተመለከተ የተሟላ ማብራሪያ መስጠት የሚችል ሰው ባይኖርም ከፀሐይ የሚመጣውን ሙቀት (በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ) ማግኘታችን አልቀረም። እፅዋት ብርሃን የማግኘታቸው ውጤት የሆኑትን ምግብና ኦክሲጅን እናገኛለን። ማንበብ፣ የምንወዳቸውን ሰዎች መልክ ማየት፣ የፀሐይ መጥለቅ ያለውን ውበት ወዘተ መመልከት እንችላለን። ታዲያ ይህን በምናደርግበት ጊዜ ስለ ድንቅ ሥራዎቹ አምላክን ማመስገን አይገባንም?—መዝሙር 104:1, 2፤ 145:5፤ ኢሳይያስ 45:7፤ ኤርምያስ 31:35
22. የጥንቱ ዳዊት ለአምላክ ድንቅ ሥራዎች ምን ምላሽ ሰጥቶ ነበር?
22 በይሖዋ ድንቅ ሥራዎች ላይ የምናሰላስለው እንዲያው በአክብሮታዊ ፍርሃት ወይም በግርምት በመዋጥ ተደምመን እንድንቀር ብቻ ነውን? በፍጹም። የጥንቱ መዝሙራዊ የአምላክን ሥራዎች በሙሉ መረዳትም ሆነ ተናግሮ መጨረስ እንደማይቻል ገልጿል። ዳዊት “አቤቱ አምላኬ፣ ያደረግኸው ተአምራት ብዙ ነው፣ . . . ባወራም ብናገርም ከቍጥር ሁሉ በዛ” ሲል ተናግሯል። (መዝሙር 40:5) ይሁን እንጂ ስለ እነዚህ ታላላቅ ሥራዎች ከመናገር ዝም እላለሁ ማለቱ እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። በመዝሙር 9:1 ላይ የሚገኘው “አቤቱ፣ በልቤ ሁሉ አመሰግንሃለሁ፣ ተአምራትህንም ሁሉ እነግራለሁ” የሚለው ሐሳብ የዳዊትን ቁርጥ ውሳኔ ያረጋግጣል።
23. ስለ አምላክ ድንቅ ሥራዎች ምን ይሰማሃል? ሌሎችንስ መርዳት የምትችለው እንዴት ነው?
23 እኛስ ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ መገፋፋት አይኖርብንምን? ለአምላክ ታላቅ ሥራዎች ያለን አድናቆት እስከ አሁን ስላደረገውና ወደፊት ስለሚያደርገው ነገር እንድንናገር ሊገፋፋን አይገባምን? መልሱ ግልጽ ነው “ክብሩን ለአሕዛብ ተአምራቱንም ለወገኖች ሁሉ” መንገር አለብን። (መዝሙር 96:3-5) አዎን፣ ስለ እሱ የተማርነውን ለሌሎች በመንገር ለአምላክ ድንቅ ሥራዎች ያለንን ከትሑት ልብ የመነጨ አድናቆት መግለጽ እንችላለን። ምንም እንኳ ለፈጣሪ ደንታ በሌለው ማኅበረሰብ ውስጥ ቢያድጉም አዎንታዊ የሆነውና አዲስ ነገር የሚያሳውቀው አቀራረባችን የአምላክን ሕልውና እንዲቀበሉ ዓይናቸውን ሊያበራላቸው ይችላል። ከዚህም በላይ ‘ሁሉን ስለ ፈጠረው’ እና ድንቅ ነገሮችን ስለሚያደርገው ስለ ይሖዋ ለማወቅ እንዲሁም እሱን ለማገልገል እንዲነሳሱ ሊያደርጋቸው ይችላል።—ራእይ 4:11
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• በኢዮብ 37:14 ላይ የሚገኘው ማሳሰቢያ ስለየትኞቹ የአምላክ ሥራዎች እንድታስብ ያደርግሃል?
• ሳይንስ ሙሉ በሙሉ ሊያብራራቸው ያልቻላቸው በኢዮብ ምዕራፍ 37 እና 38 ላይ ጎላ ብለው የተገለጹ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
• ስለ አምላክ ድንቅ ሥራዎች ምን ይሰማሃል? ምንስ ለማድረግ ትገፋፋለህ?
[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ባሕርን በመዝጊያ የዘጋና ባለበት ቦታ እንዲቀመጥ ያደረገ ማን ነው?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ የፈጠራቸውን በምድር ላይ የሚገኙ ውብ ቦታዎች በሙሉ የጎበኘ ማን ነው?