መበለትነት በሁለት ሴቶች ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ
መበለትነት በሁለት ሴቶች ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ
ሳንድራ በአውስትራሊያ የምትኖር መበለት ነች። ከጥቂት ዓመታት በፊት ባለቤቷ በሞተ ጊዜ ጭራሽ ያልጠበቀችው ነገር ሆኖባት ነበር። “በድንገት ባለቤቴንና ውድ ጓደኛዬን እንዳጣሁ ሳስብ የከንቱነት ስሜት አደረብኝ። ከሆስፒታል ወደ ቤት እንዴት እንደተመለስኩም ሆነ ከዚያ በኋላ ምን ሳደርግ እንደዋልኩ ፈጽሞ ትዝ አይለኝም። በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ፣ ያደረብኝ ፍርሃት ፋታ የማይሰጥ አካላዊ ስቃይ አስከተለብኝ።”
ሳንድራ ለስድስት ዓመታት ያህል በመበለትነት የኖረች በዕድሜ የምትበልጣት ኢሌን የምትባል ጓደኛ አለቻት። ኢሌን ባለቤቷ ዴቪድ ባደረበት የካንሰር በሽታ ከመሞቱ በፊት ለስድስት ወራት ያህል አስታምማው ነበር። ሐዘኗ መሪር ከመሆኑ የተነሳ ከባለቤቷ ሞት በኋላ ወዲያው ጊዜያዊ የማየት ችግር ገጥሟት ነበር። ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ አንድ ቀን ድንገት ራሷን ስታ ወደቀች። ዶክተሯ ባደረገላት ምርመራ አንድም የአካላዊ በሽታ ምልክት ሊያገኝባት አልቻለም። ይሁን እንጂ ኢሌን ያደረባትን ሐዘን በውስጧ አምቃ እንደያዘች ተገነዘበ። ስለዚህ ወደ ቤት ሄዳ እንደምንም ብላ ሐዘንዋን በለቅሶ እንድታወጣ መከራት። ኢሌን “ሐዘኔን ለመቋቋም ረጅም ጊዜ ወስዶብኛል” ስትል ሳትሸሽግ ተናግራለች። ብቸኝነት ሲሰማኝ ደግሞ “መኝታ ቤት ገብቼ ጭንቅላቴን ዴቪድ ልብሶች ውስጥ የመቅበር ልማድ ነበረኝ” ስትል አክላ ተናግራለች።
አዎን፣ የሚያፈቅሩትን የትዳር ጓደኛ በሞት ማጣት የተለያየ ዓይነት ስሜት ሊያሳድር ይችላል። ይህም የሆነበት ምክንያት መበለትነት እንዲያው ያለ ባል መኖር ብቻ ማለት ስላልሆነ ነው። ለምሳሌ ያህል ሳንድራ ለተወሰነ ጊዜ ማንነቷን እስከመጠራጠር ደርሳ ነበር። በቅርቡ ሐዘን እንደደረሰባቸው እንደ ሌሎች በርካታ መበለቶች ሁሉ እሷም ያለ ረዳት እንደቀረችና አለኝታ እንደሌላት ሆኖ ተሰምቷታል። ሳንድራ እንዲህ ስትል ታስታውሳለች:- “የመጨረሻ ውሳኔዎችን የሚያደርገው ባለቤቴ ስለነበር እሱን ድንገት ከአጠገቤ ሳጣ ይህ ኃላፊነት በእኔ ጫንቃ ላይ ወደቀ። ጥሩ እንቅልፍ አይወስደኝም ነበር። ከፍተኛ ድካም ይሰማኝ ነበር። ምን ማድረግ እንዳለብኝ ለማወቅ እቸገር ነበር።”
ሳንድራና ኢሌን የደረሰባቸው ነገር በዓለም ዙሪያ በየዕለቱ የሚከሰት ነው። በጥቅሉ በሽታ፣ አደጋዎች፣ ጦርነቶች፣ የዘር ማጥፋት ወንጀልና ዓመፅ ቁጥራቸው እያደገ የሚሄድ መበለቶች እንዲፈጠሩ እያደረጉ ነው። a አብዛኞቹ ሴቶች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ በመጋባት ሐዘናቸውን አምቀው ይቆዝማሉ። በመበለትነት የሚመሩትን ሕይወት ለመላመድ በትግል ላይ ያሉትን እነዚህን ሴቶች ለመርዳት ወዳጆቻቸውና ዘመዶቻቸው ምን ማድረግ ይችላሉ? ቀጥሎ ያለው ርዕስ አንዳንድ ጠቃሚ ሐሳቦች ይዟል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንድ ሴቶች ባሎቻቸው ጥለዋቸው በመሄዳቸው ምክንያት ከመበለቶች ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ሥር ይገኛሉ። ምንም እንኳ መለያየትና ፍቺ የራሳቸው የሆኑ ችግሮች የሚያስከትሉ ቢሆንም ቀጥሎ በቀረበው ርዕስ ውስጥ የተብራሩት በርካታ መሠረታዊ ሥርዓቶች በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሥር ላሉ ሴቶችም ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ።