በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መናፍስታዊ እምነት መንፈሳዊ ፍላጎታችንን በእርግጥ ሊያረካልን ይችላልን?

መናፍስታዊ እምነት መንፈሳዊ ፍላጎታችንን በእርግጥ ሊያረካልን ይችላልን?

መናፍስታዊ እምነት መንፈሳዊ ፍላጎታችንን በእርግጥ ሊያረካልን ይችላልን?

ሁላችንም መንፈሳዊና ቁሳዊ ፍላጎቶች አሉን። ለዚህ ነው ብዙ ሰዎች የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? ሰዎች መከራ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው? ስንሞት ምን እንሆናለን? እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎችን የሚጠይቁት። ቅን ልብ ያላቸው ብዙ ሰዎች ለእነዚህና እነዚህን ለመሳሰሉ ሌሎች ጥያቄዎች የሙታን መናፍስት መልስ ይሰጡናል ብለው ተስፋ በማድረግ ወደ መናፍስት ጠሪዎች ይሄዳሉ። እንደዚህ ያለው ድርጊት መናፍስታዊ እምነት ተብሎ ይጠራል።

የመናፍስታዊ እምነት ተከታዮች በብዙ አገሮች ውስጥ የሚገኙ ሲሆን አንድ ላይ የሚሰበሰቡባቸው ቦታዎችና አብያተ ክርስቲያናት አሏቸው። ለምሳሌ ያህል በብራዚል በግምት 4, 000, 000 የሚያክሉ የመናፍስታዊ እምነት ተከታዮች፣ አለን ካርዲክ በሚል የብዕር ስም የሚጠራው የ19ኛው መቶ ዘመን ፈረንሳዊ የትምህርት ሊቅና ፈላስፋ የሆነው የኢፖሊት ሌዎ ዴኒዛር ሪቫይ ትምህርት ተከታዮች ናቸው። ካርዲክ ስለ መናፍስታዊ እምነት የማወቅ ፍላጎት ያደረበት በ1854 ነበር። ከዚያም መናፍስት ጠሪዎች ወደሚገኙባቸው ብዙ ቦታዎች በመሄድና ጥያቄዎችን በመጠየቅ ያገኘውን መልስ መዝግቦ በ1857 ዘ ቡክ ኦቭ ስፒሪትስ የሚባል መጽሐፍ አሳተመ። ዘ ሚድያንስ ቡክ እና ዘ ጎስፐል አኮርዲንግ ቱ ስፒሪቲዝም የሚባሉ ሌሎች ሁለት ጽሑፎችንም ለንባብ አብቅቷል።

መናፍስታዊ እምነት ቩዱ፣ ጥንቆላ፣ አስማት ወይም የሰይጣን አምልኮ ከመሳሰሉ ሃይማኖታዊ ድርጊቶች ጋር ግንኙነት አለው። ይሁን እንጂ የአለን ካርዲክ ትምህርት ተከታዮች እምነታቸው የተለየ እንደሆነ ይናገራሉ። ብዙውን ጊዜ በጽሑፎቻቸው ላይ መጽሐፍ ቅዱስን የሚጠቅሱ ሲሆን ኢየሱስን “መሪ እና ለመላው የሰው ዘር ምሳሌ” ይሉታል። የኢየሱስ ትምህርቶች “እንከን የለሽ መለኮታዊ ሕግ” መሆናቸውን ይናገራሉ። አለን ካርዲክ መናፍስታዊ ጽሑፎች የአምላክ ሕግ ለሰው ዘር የተገለጠባቸው ሦስተኛ ራእዮች እንደሆኑ አድርጎ ይመለከታቸዋል። የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ የሙሴና የኢየሱስ ትምህርቶች ናቸው።

መናፍስታዊ እምነት ባልንጀራን መውደድንና በበጎ አድራጎት ሥራዎች መካፈልን ስለሚያበረታታ የብዙዎችን ትኩረት ይስባል። የመናፍስታዊ እምነት አንዱ መርሕ “ያለ በጎ አድራጎት መዳን አይገኝም” የሚል ነው። ብዙዎቹ የመናፍስታዊ እምነት ተከታዮች ሆስፒታሎችን፣ ትምህርት ቤቶችንና ሌሎች ተቋማትን ማቋቋም በመሳሰሉ ማኅበራዊ ተግባራት በንቃት ይካፈላሉ። ይህ የሚያስመሰግን ተግባር ነው። ይሁን እንጂ መናፍስታዊ እምነቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተመዘገቡት የኢየሱስ ትምህርቶች ጋር ሲነጻጸሩ እንዴት ናቸው? እስቲ ሙታን ያላቸውን ተስፋ እና በሰዎች ላይ መከራ የሚደርስበትን ምክንያት እንደ ምሳሌ እንውሰድ።

ሙታን ምን ተስፋ አላቸው?

ብዙ የመናፍስታዊ እምነት ተከታዮች በሪኢንካርኔሽን ያምናሉ። ስለ መናፍስታዊ ሥራዎች የሚገልጽ አንድ ጽሑፍ “ከመለኮታዊ ፍትህ ጽንሰ ሐሳብ ጋር የሚጣጣመው የሪኢንካርኔሽን መሠረተ ትምህርት ብቻ ነው። የወደፊቱ ጊዜ ምን እንደያዘ ማብራሪያ የሚሰጠንና ተስፋችንን የሚያጠነክርልን ይህ ትምህርት ብቻ ነው” በማለት ይገልጻል። የመናፍስታዊ እምነት ተከታዮች አንድ ሰው ሲሞት ነፍሱ፣ ልክ ከኩቡ እንደሚወጣ የቢራቢሮ እጭ አካሉን ለቅቃ ትወጣለች ይላሉ። ከጊዜ በኋላ ይህች ነፍስ በቀድሞ ሕይወት ከፈጸመችው ኃጢአት ለመንጻት እንደገና ሰው ሆና ትፈጠራለች ብለው ያምናሉ። ሆኖም ቀደም ሲል የተሠራው አይታሰብም። ዘ ጎስፐል አኮርዲንግ ቱ ስፒሪቲዝም የተባለው መጽሐፍ “አምላክ በቀድሞ ሕይወት የተሠራውን ኃጢአት እዚያው ተረስቶ እንዲቀር ማድረጉን የተሻለ ሆኖ አግኝቶታል” ይላል።

አለን ካርዲክ “ሪኢንካርኔሽንን አልቀበልም ማለት ክርስቶስ የተናገረውን አልቀበልም እንደ ማለት ይቆጠራል” በማለት ጽፏል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ሪኢንካርኔሽን” የሚል ቃልም ሆነ ሐሳብ ተናግሮ አያውቅም። (በገጽ 22 ላይ የሚገኘውን “መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሪኢንካርኔሽን ያስተምራልን?” የሚለውን ተመልከት።) ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ስለ ሙታን ትንሣኤ አስተምሯል። በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት ሦስት ሰዎችን ይኸውም በናይን ትኖር የነበረችውን መበለት ወንድ ልጅ፣ የምኩራብ አለቃውን ሴት ልጅ እና የቅርብ ወዳጁን አልዓዛርን ከሞት አስነስቷል። (ማርቆስ 5:​22-24, 35-43፤ ሉቃስ 7:​11-15፤ ዮሐንስ 11:​1-44) ከእነዚህ አስደናቂ ክንውኖች መካከል አንዱን እንመርምርና ኢየሱስ “ትንሣኤ” ሲል ምን ማለቱ እንደነበር እንመልከት።

የአልዓዛር ትንሣኤ

ኢየሱስ ወዳጁ አልዓዛር ታምሞ እንደነበረ ሰምቷል። ከሁለት ቀናት በኋላ ደቀ መዛሙርቱን “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ምን ለማለት እንደፈለገ ስላልገባቸው በግልጽ “አልዓዛር ሞተ” አላቸው። በመጨረሻ ኢየሱስ ወደ አልዓዛር መቃብር ሲደርስ ሰውዬው ከሞተ አራት ቀን ሆኖት ነበር። ያም ሆኖ ኢየሱስ መቃብሩ የተከደነበትን ድንጋይ እንዲያነሱት አዘዘ። ከዚያም ድምፁን ከፍ አድርጎ “አልዓዛር ሆይ፣ ወደ ውጭ ና” አለ። በዚህ ጊዜ አንድ አስደናቂ ነገር ተከሰተ። “የሞተውም እጆቹና እግሮቹ በመግነዝ እንደ ተገነዙ ወጣ፤ ፈቱትም በጨርቅ እንደ ተጠመጠመ ነበረ። ኢየሱስም:- ፍቱትና ይሂድ ተዉት አላቸው።”​—⁠ዮሐንስ 11:​5, 6, 11-14, 43, 44

ይህ ሪኢንካርኔሽን እንዳልነበረ ግልጽ ነው። ኢየሱስ የሞተው አልዓዛር እንደተኛ ወይም በድን እንደነበረ ተናግሯል። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ‘የማሰብ ችሎታው ሁሉ ጠፍቷል።’ ‘አንዳች አያውቅም’ ነበር። (መዝሙር 146:​4 NW ፤ መክብብ 9:​5) ትንሣኤ ያገኘው አልዓዛር በሪኢንካርኔሽን አማካኝነት መንፈስ የገባበት ሌላ ሰው አልነበረም። ባሕርይው፣ ዕድሜውና ትዝታው ምንም ያልተለወጠ ያው የቀድሞው አልዓዛር ነበር። በአጭር ተቀጭቶ የነበረው ሕይወት እንደገና የቀጠለ ሲሆን በመሞቱ ምክንያት አዝነው ከነበሩት ወዳጆቹና ዘመዶቹ ጋር ተቀላቀለ።​—⁠ዮሐንስ 12:​1, 2

አልዓዛር ከጊዜ በኋላ እንደገና ሞቷል። ታዲያ ትንሣኤ ማግኘቱ ምን ፋይዳ ነበረው? ኢየሱስ እንደፈጸማቸው ሌሎች ትንሣኤዎች ሁሉ የአልዓዛር ትንሣኤም አምላክ የታመኑ አገልጋዮቹ እሱ በቀጠረው ጊዜ ከሞት እንደሚያስነሳቸው በሰጠው ተስፋ ላይ ያለንን እምነት ያጠነክርልናል። ኢየሱስ የፈጸማቸው እነዚህ ተአምራት “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል” በማለት ለተናገራቸው ቃላት ይበልጥ ትርጉም እንዲኖራቸው ያደርጋል።​—⁠ዮሐንስ 11:​25

ኢየሱስ ወደፊት ስለሚሆነው ትንሣኤ ሲናገር “በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን [ድምፄን] የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ” ብሏል። (ዮሐንስ 5:​28, 29) የሞቱ ሰዎች እንደ አልዓዛር በትንሣኤ ይነሳሉ። ይህ ማለት ግን በስብሶ ምናልባትም ከሌሎች ሕያው ነገሮች ጋር ተዋህዶ የነበረውን አካል በትንሣኤ አማካኝነት ከመንፈሱ ጋር ማገናኘት ማለት አይደለም። ይህ ነው የማይባል ጥበብና ኃይል ያለው የሰማይና የምድር ፈጣሪ የሞቱ ሰዎችን ማስነሳት ፈጽሞ አይሳነውም።

ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረው የትንሣኤ ትምህርት አምላክ ሰዎችን በግለሰብ ደረጃ በጥልቅ እንደሚያፈቅር አያመለክትምን? ሆኖም ቀደም ሲል የተነሳው ሁለተኛ ጥያቄስ?

የሰው ዘር ሥቃይ የሚደርስበት ለምንድን ነው?

አብዛኛውን ጊዜ በሰው ዘር ላይ መከራ የሚደርሰው ጥበብ የጎደላቸው፣ ልምድ የሌላቸው ወይም ደግሞ ክፋት የተጠናወታቸው ሰዎች በሚያደርጓቸው ነገሮች የተነሳ ነው። ሰዎች በቀጥታ ተጠያቂ የማይሆኑባቸው አሳዛኝ ክስተቶችን በተመለከተስ ምን ለማለት ይቻላል? ለምሳሌ ያህል ድንገተኛ አደጋዎችና የተፈጥሮ አደጋዎች የሚያጋጥሙት ለምንድን ነው? አንዳንድ ሕፃናት አንድ ዓይነት እክል ኖሮባቸው የሚወለዱት ለምንድን ነው? አለን ካርዲክ እነዚህን ነገሮች እንደ ቅጣት ይመለከታቸዋል። “እየተቀጣን ከሆነ ኃጢአት ሠርተን ነበር ማለት ነው። ይህን ኃጢአት የፈጸምነው በአሁኑ ሕይወታችን ካልሆነ በቀደመው ሕይወታችን የፈጸምነው መሆን አለበት” በማለት ጽፏል። የመናፍስታዊ እምነት ተከታዮች “ጌታ ሆይ ሁለንተናህ ፍትህ ነው። አንተ ያዘዝክብኝ ሕመም ልቀበለው የሚገባኝ መሆን አለበት። . . . በቀድሞው ሕይወቴ የሠራሁትን ኃጢአት እንደሚያስተሰርይልኝና እምነቴን እንዲሁም ለተባረከው ፈቃድህ መገዛቴን ለማሳየት እንደፈተና አድርጌ እቀበለዋለሁ።”​—⁠ዘ ጎስፐል አኮርዲንግ ቱ ስፕሪቲዝም።

ኢየሱስ እንዲህ ያለ ነገር አስተምሯልን? በፍጹም። ኢየሱስ “ጊዜና እድል [“ያልታሰበ አጋጣሚ፣” NW ] ግን ሁሉን ይገናኛቸዋል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ አነጋገር በሚገባ ያውቃል። (መክብብ 9:​11) አንዳንድ ጊዜ መጥፎ ነገሮች እንዲያው ሊከሰቱ እንደሚችሉ ያውቃል። የግድ የኃጢአት ቅጣት መሆን የለባቸውም።

ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ ያጋጠመውን ሁኔታ ተመልከት:- “ሲያልፍም ከመወለዱ ጀምሮ ዕውር የሆነውን ሰው አየ። ደቀ መዛሙርቱም:- መምህር ሆይ፣ ይህ ሰው ዕውር ሆኖ እንዲወለድ ኃጢአት የሠራ ማን ነው? እርሱ ወይስ ወላጆቹ? ብለው ጠየቁት።” ኢየሱስ የሰጠው መልስ ትምህርት የሚገኝበት ነው:- “የእግዚአብሔር ሥራ በእርሱ እንዲገለጥ ነው እንጂ እርሱ ወይም ወላጆቹ ኃጢአት አልሠሩም። ይህን ብሎ ወደ መሬት እንትፍ አለ በምራቁም ጭቃ አድርጎ በጭቃው የዕውሩን ዓይኖች ቀባና:- ሂድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ አለው። . . . ስለዚህ ሄዶ ታጠበ እያየም መጣ።”​—⁠ዮሐንስ 9:​1-3, 6, 7

ለሰውዬው ዕውር ሆኖ መወለድ እሱም ሆነ ወላጆቹ ተጠያቂ አለመሆናቸውን ከኢየሱስ አነጋገር መረዳት ይቻላል። ስለሆነም ኢየሱስ ይህ ሰው በቀድሞ ሕይወቱ ለሠራው ኃጢአት ቅጣት እየተቀበለ እንዳለ የሚገልጽ ሐሳብ አልተናገረም። እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ ሰዎች ኃጢአት መውረሳቸውን ያውቃል። ሆኖም የወረሱት የአዳምን ኃጢአት እንጂ ከመወለዳቸው በፊት የሠሩትን ኃጢአት አይደለም። በአዳም ኃጢአት ምክንያት ሰዎች ሁሉ ለበሽታና ለሞት የሚጋለጥ ፍጽምና የሌለው አካል ይዘው ይወለዳሉ። (ኢዮብ 14:​4፤ መዝሙር 51:​5፤ ሮሜ 5:​12፤ 9:​11) እንዲያውም ኢየሱስ ተልኮ የመጣው ለዚህ ጉዳይ መፍትሔ ለማስገኘት ነበር። መጥምቁ ዮሐንስ ኢየሱስ “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” እንደሆነ ተናግሯል።​—⁠ዮሐንስ 1:​29 a

ኢየሱስ አንድ ቀን መጥቶ እንዲፈውሰው ሲል አምላክ ሰውዬውን ሆን ብሎ ዕውር አድርጎታል ብሎ እንዳልተናገረም ልብ በል። እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ምንኛ ጭካኔ ይሆን ነበር! እንዲህ ማድረጉ ለአምላክ ክብር ያመጣለት ነበርን? ከዚያ ይልቅ ዓይነ ስውሩ በተአምራዊ ሁኔታ መዳኑ ‘የአምላክ ሥራ እንዲገለጥ’ አድርጓል። ኢየሱስ እንዳከናወናቸው ሌሎች ብዙ ተዓምራት ሁሉ ይኼኛውም አምላክ በችግር ለሚሠቃየው የሰው ዘር ልባዊ ፍቅር እንዳለው የሚያንጸባርቅና በሰዎች ላይ የሚደርሰውን ሕመምና ሥቃይ እሱ በቀጠረው ጊዜ እንደሚያስወግድ የገባውን ቃል እንደሚፈጽም የሚያረጋግጥ ነው።​—⁠ኢሳይያስ 33:​24

የሰማዩ አባታችን ለሰው ዘር ሥቃይና መከራ መንስዔ ሳይሆን ‘ለሚለምኑት መልካም ነገሮችን’ ሰጪ መሆኑን ማወቃችን የሚያጽናና አይደለምን? (ማቴዎስ 7:​11) ማየት የተሳናቸው ሰዎች ዓይናቸው የሚበራበት፣ መስማት የተሳናቸው ሰዎች ጆሮ መስማት የሚጀምርበትና አንካሳዎች እንደልብ የሚራመዱበት፣ የሚዘሉበትና የሚሮጡበት ጊዜ ሲመጣ ይህ ልዑሉን አምላክ ምንኛ ያስከብረዋል!​—⁠ኢሳይያስ 35:​5, 6

መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ማርካት

ኢየሱስ “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” በማለት ተናግሯል። (ማቴዎስ 4:​4) አዎን መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ማርካት የምንችለው የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብና ከእርሱ ጋር በሚስማማ መንገድ ሕይወታችንን ስንመራ ነው። ወደ መናፍስት ጠሪዎች መሄዱ ፈጽሞ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ሊያረካልን አይችልም። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያለው ድርጊት አለን ካርዲክ የመጀመሪያ መለኮታዊ ሕግ ብሎ በሚጠራው መጽሐፍ ላይ የተወገዘ ነው።​—⁠ዘዳግም 18:​10-13

የመናፍስታዊ እምነት ተከታዮችን ጨምሮ ብዙዎች አምላክ ከሁሉም የበላይ የሆነ አካል፣ ዘላለማዊ፣ ፍጹም፣ ደግ፣ ጥሩ እና ፍትሐዊ መሆኑን ይቀበላሉ። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህም ይበልጥ የሚለው አለ። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ ይሖዋ የሚባል የግል ስም እንዳለውና እንደ ኢየሱስ ሁሉ ስሙን ማክበር እንዳለብን ይገልጻል። (ማቴዎስ 6:​9፤ ዮሐንስ 17:​6) ሰዎች ከእርሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት የሚችሉ ሕያው አካል እንደሆነም ይገልጻል። (ሮሜ 8:​38, 39) መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ አምላክ መሐሪ መሆኑንና ‘እንደ ኃጢአታችን እንደማያደርግብን፣ እንደ በደላችንም እንደማይከፍለን’ እንማራለን። (መዝሙር 103:​10) ሉዓላዊው ጌታ ይሖዋ በጽሑፍ በሰፈረው ቃሉ አማካኝነት ፍቅሩን፣ የበላይነቱንና ምክንያታዊነቱን ገልጦልናል። ታዛዥ ሰዎችን የሚመራውና ጥበቃ የሚያደርግላቸው እሱ ነው። ይሖዋንና ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ “የዘላለም ሕይወት” ያስገኛል።​—⁠ዮሐንስ 17:​3

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ ዓላማ ማወቅ የሚያስፈልገንን መረጃ ሁሉ የያዘ ሲሆን እሱን ማስደሰት ከፈለግን ማድረግ ያለብንን ይነግረናል። መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ መመርመሩ ለጥያቄዎቻችን እውነተኛና አርኪ መልስ ያስገኝልናል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ክፉውን ከደጉ መለየት የሚያስችል መመሪያ የሚሰጠን ሲሆን ጠንካራ እምነት እንድንገነባ ይረዳናል። በቅርቡ አምላክ ‘እንባዎችንም ሁሉ ከሰው ልጆች ዓይን እንደሚያብስ፣ ሞት ከእንግዲህ ወዲህ እንደማይሆን፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ እንደማይሆን፣ የቀደመው ሥርዓት እንደሚያልፍ’ ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ራእይ 21:​3, 4) ይሖዋ በኢየሱስ ክርስቶስ አማካኝነት የሰውን ዘር ከወረሰው ኃጢአትና ሞት ነፃ የሚያደርገው ሲሆን ታዛዥ ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ዘላለማዊ ሕይወት ያገኛሉ። በዚያን ጊዜ ቁሳዊውም ሆነ መንፈሳዊ ፍላጎቶቻቸው ሙሉ በሙሉ ይሟላላቸዋል።​—⁠መዝሙር 37:​10, 11, 29፤ ምሳሌ 2:​21, 22፤ ማቴዎስ 5:​5

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ኃጢአትና ሞት እንዴት እንደመጣ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት የተባለውን መጽሐፍ 6ኛ ምዕራፍ ተመልከት።

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሪኢንካርኔሽን ያስተምራልን?

የሪኢንካርኔሽንን ትምህርት የሚደግፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ይኖር ይሆን? በሪኢንካርኔሽን የሚያምኑ ሰዎች እንደ ማስረጃ የሚጠቀሙባቸውን አንዳንድ ጥቅሶች ተመልከት:-

“ነቢያት ሁሉና ሕጉ እስከ ዮሐንስ ድረስ ትንቢት ተናገሩ . . . ይመጣ ዘንድ ያለው ኤልያስ ይህ ነው።”​—⁠ማቴዎስ 11:​13, 14

መጥምቁ ዮሐንስ ዳግም የተወለደ ኤልያስ ነውን? ዮሐንስ “ኤልያስ ነህን?” ተብሎ ሲጠየቅ በግልጽ “አይደለሁም” በማለት መልሷል። (ዮሐንስ 1:​21) ይሁን እንጂ ዮሐንስ “በኤልያስ መንፈስና ኃይል” ከመሢሁ ቀድሞ እንደሚመጣ ትንቢት ተነግሮ ነበር። (ሉቃስ 1:​17፤ ሚልክያስ 4:​5, 6) በሌላ አነጋገር መጥምቁ ዮሐንስ ኤልያስ የተባለው ከኤልያስ ጋር የሚነጻጸር ሥራ ስላከናወነ ነው።

“ሰው ዳግመኛ ካልተወለደ በቀር የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያይ አይችልም አለው። ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል ስላልሁህ አታድንቅ።”​—ዮሐንስ 3:​3, 7

ከጊዜ በኋላ አንድ ሐዋርያ “ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን በመነሣቱ ለሕያው ተስፋና ለማይጠፋ፣ እድፈትም ለሌለበት፣ ለማያልፍም ርስት እንደ ምሕረቱ ብዛት ሁለተኛ የወለደን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ” በማለት ጽፏል። (1 ጴጥሮስ 1:​3, 4፤ ዮሐንስ 1:​12, 13) በግልጽ እንደተቀመጠው ኢየሱስ ስለ ዳግም መወለድ ሲናገር ወደፊት ስለሚከናወን ሪኢንካርኔሽን መናገሩ ሳይሆን ተከታዮቹ ገና በሕይወት እያሉ ስለሚያጋጥማቸው መንፈሳዊ ሁኔታ መጥቀሱ ነበር።

“ሰው ከሞተ በኋላ ለዘላለም ይኖራል:- ምድራዊ ሕይወቴ ሲያከትም እንደገና የምመለስበትን ጊዜ እጠባበቃለሁ።”​—⁠ዘ ጎስፐል አኮርዲንግ ቱ ስፒሪቲዝም በተባለው መጽሐፍ ላይ ተጠቅሶ የሚገኘው የኢዮብ 14:​14 “ግሪክኛ ትርጉም።”

ሪቫይዝድ ስታንዳርድ ቨርዥን ይህን ጥቅስ “አንድ ሰው ቢሞት እንደገና ተመልሶ በሕይወት መኖር ይችላልን? ነፃ እስከምወጣበት ጊዜ ድረስ የሰልፌን ዘመን በትዕግሥት እጠባበቃለሁ” በማለት ተርጉሞታል። በዚህ ጥቅስ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ስታነብ ሙታን “ነፃ እስከሚወጡ” ድረስ በመቃብር ውስጥ እንደሚጠብቁ ትገነዘባለህ። (ቁጥር 13) የሚጠባበቁት ከሕልውና ውጪ ሆነው ነው። “የሞተ ሰው አይሰማም አይለማም፤ አንዴ ከሞተ ሞተ ነው።”​—⁠ኢዮብ 14:​10 የባግስተር ሰፕቱጀንት ትርጉም።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የትንሣኤ ተስፋ አምላክ በግለሰብ ደረጃ በጥልቅ እንደሚያስብልን ያሳያል

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አምላክ በሰው ዘር ላይ የሚደርሰውን ሥቃይና መከራ ሁሉ ያስወግዳል