መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ጥራዝ
መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ጥራዝ
የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን ለማዘጋጀት ከነበራቸው ፍላጎት የተነሳ ኮዴክስ በመጠቀም ረገድ ግንባር ቀደም ሆነዋል። ኮዴክስ ጥቅልል ሳይሆን መጽሐፍ ነው። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች ሁሉንም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የያዘ አንድ ጥራዝ ወዲያውኑ ማዘጋጀት አልጀመሩም። መጽሐፍ ቅዱስን በአንድ ጥራዝ አዘጋጅቶ በሰፊው ለማሰራጨቱ ሥራ ፈር ቀዳጅ የሆነ ተግባር የተከናወነው በስድስተኛው መቶ ዘመን በፍሌቪየስ ካሲዮዶረስ አማካኝነት ነው።
ፍሌቪየስ ማግነስ ኦሬሊየስ ካሲዮዶረስ የተወለደው በ485-490 እዘአ በዛሬዋ ኢጣሊያ ደቡባዊ ጫፍ ትገኝ በነበረችው በካላብሪያ በአንድ ባለጠጋ ቤተሰብ ውስጥ ነበር። ባሕረ ገብ ምድሩ በመጀመሪያ በጎቶች ከዚያም በባይዛንታይኖች ተይዞ በነበረበት ሁከት የነገሠበት የኢጣሊያ የታሪክ ዘመን የኖረ ሰው ነው። ካሲዮዶረስ ዕድሜው ወደ 60 ወይም 70 ዓመት ተጠግቶ በነበረበት ጊዜ በስክዊላቼ ካላብሪያ በሚገኘው መኖሪያው አቅራቢያ የቪቬሪየምን ገዳምና ቤተ መጻሕፍት መሥርቷል።
ጠንቃቃ የመጽሐፍ ቅዱስ አዘጋጅ
ካሲዮዶረስን በዋነኝነት ካሳሰቡት ነገሮች አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ ለሰዎች የመዳረሱ ጉዳይ ነበር። ታሪክ ጸሐፊው ፒተር ብራውን እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “በካሲዮዶረስ እምነት የላቲን የሥነ ጽሑፍ ባሕል ቅዱሳን ጽሑፎችን ለማሠራጨቱ ተግባር ጥቅም ላይ ሊውል ይገባል። ጥንታዊ ጽሑፎችን ለማንበብና ለመገልበጥ ቀደም ሲል ጥቅም ላይ ውለው የነበሩት ዘዴዎች በሙሉ ቅዱሳን ጽሑፎችን ለመረዳትና በጥንቃቄ ለመገልበጥ ሊሠራባቸው ይገባል። ልክ አዲስ እንደተፈጠረ ዘዋሬ ሥርዓት የላቲን ባሕል በጠቅላላ ሰፊ በሆነው የአምላክ ቃል ፀሐይ ዙሪያ መሽከርከር ነበረበት።”
ካሲዮዶረስ ተርጓሚዎችንና የስዋሰው ምሁራንን በቪቬሪየም ገዳም አሰባስቦ መላውን መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ የማቀናበር ሥራ እንዲሠሩ በማድረግ አስደናቂ የሆነውን የጽሑፍ ዝግጅት ሥራ በበላይነት መርቷል። ሥራውን በአደራ የሰጠው ለጥቂት የተማሩ ሰዎች ብቻ ነበር። እነዚህ ሰዎች ገልባጮች ፈጥረዋቸዋል የሚባሉ ስህተቶችን በችኮላ ለማስተካከል እርምጃ እንዳይወሰድ የሚከታተሉ ነበሩ። የቋንቋውን ሰዋሰው በተመለከተ አንድ ዓይነት ጥያቄ ከተነሳ በጊዜው ተቀባይነት ከነበረው የላቲን አገባብ ይልቅ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ የእጅ ግልባጭ ቅጂዎችን ይከተሉ ነበር። ካሲዮዶረስ እንደሚከተለው ሲል መመሪያ ሰጥቶ ነበር:- “ከስዋሰው አንጻር እንግዳ የሆነ ነገር ቢገኝ . . . በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ነገር ግድፈት ይገኝበታል ተብሎ ስለማይታሰብ እንዳለ መቀመጥ አለበት። . . . መጽሐፍ ቅዱሳዊ አገላለጾች፣ ውስጠ ወይራና ፈሊጣዊ አነጋገሮች ከላቲን አንጻር ሲታዩ ባዕድ ሊመስሉ ቢችሉም ‘ዕብራዊ’ ቃናቸውን ጠብቀው እንደሚቀመጡት የተጸውኦ ስሞች ሁሉ እንዳሉ መቀመጥ ይገባቸዋል።”—ዘ ካምብሪጅ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ባይብል
ኮዴክስ ግራንዲየር
በቪቬሪየም ገዳም የተሰባሰቡት ገልባጮች ቢያንስ ሦስት ራሳቸውን የቻሉ የላቲን መጽሐፍ ቅዱስ እትሞችን የማዘጋጀት ተልዕኮ ሰጥቷቸው ነበር። ከእነዚህ አንዱ የሆነውና በዘጠኝ ጥራዞች የተዘጋጀው እትም በሁለተኛው መቶ ዘመን መጨረሻ አካባቢ የተሠራውን ጥንታዊ የላቲን ትርጉም የያዘ ሳይሆን አይቀርም። ሁለተኛው እትም ደግሞ ጄሮም በአራተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ አካባቢ ያጠናቀቀውን የላቲኑን ቩልጌት የያዘ ነው። ሦስተኛው ኮዴክስ ግራንዲየር ማለትም “ትልቁ ኮዴክስ” የሚባለው ከሦስት የመጽሐፍ ቅዱስ እትሞች የተውጣጣ ነው። የመጨረሻዎቹ ሁለት እትሞች ሁሉንም የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት አንድ ጥራዝ አድርገው ያጠቃለሉ ነበሩ።
ካሲዮዶረስ የላቲን መጽሐፍ ቅዱሶችን ፓንዴቲስ a መላውን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት አንድ ላይ ማዋሃድ የተለያዩ ጥራዞችን የማገላበጡን ጊዜ አባካኝ ሂደት ለማስቀረት ያለውን ጠቀሜታ እንደተገነዘበ ምንም ጥርጥር የለውም።
በሚል ስያሜ በአንድ ጥራዝ ለማዘጋጀት የመጀመሪያው ሰው የነበረ ይመስላል።ከደቡብ ኢጣሊያ ወደ ብሪታንያ ደሴቶች
ካሲዮዶረስ ከሞተ በኋላ ብዙም ሳይቆይ (በ583 እዘአ ገደማ ሳይሆን አይቀርም) የኮዴክስ ግራንዲየር ጉዞ ተጀመረ። በዚህ ጊዜ የቪቬሪየም ቤተ መጻሕፍት በሮም ወደሚገኘው የላተራን ቤተ መጻሕፍት ተዛውሮ እንደነበር ይታመናል። በ678 እዘአ የአንግሎ ሳክሶን አበምኔት የነበረው ቼልፍሪድ ከሮም ቆይታው ሲመለስ ኮዴክሱን ወደ ብሪታንያ ደሴቶች ይዞት መጣ። በቼልፍሪድ ሥር ወደ ነበሩትና በዛሬዋ ኖርዛምብሪያ በምትባለው የእንግሊዝ ግዛት ወደሚገኙት የዊርመዝ እና የጃሮ እህትማማች ገዳማት የመጣው በዚህ መንገድ ነው።
ቅልጥፍናው ለማረካቸው ለቼልፍሪድና ለመነኮሳቱ የካሲዮዶረስ ባለ አንድ ጥራዝ መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ ድንቅ ነገር እንደነበር ጥርጥር የለውም። በመሆኑም በጥቂት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ብቻ ሦስት ባለ አንድ ጥራዝ ሙሉ መጽሐፍ ቅዱሶችን ማዘጋጀት ችለዋል። ከእነዚህ መካከል ዛሬ ያለው ኮዴክስ አሚዮቲነስ በመባል የሚታወቀው እጅግ ግዙፍ የሆነ ጥንታዊ የእጅ ግልባጭ ቅጂ ብቻ ነው። እያንዳንዳቸው 51 ሴንቲ ሜትር በ33 ሴንቲ ሜትር ስፋት ያላቸው 2, 060 ከጥጃ ቆዳ የተሠሩ ገጾች ያሉት ሲሆን ሽፋኑ 25 ሳንቲ ሜትር ውፍረት ያለውና ጠቅላላ ክብደቱም 34 ኪሎ የሚመዝን ነው። ዛሬ ካሉት ባለ አንድ ጥራዝ የተሟሉ የላቲን መጽሐፍ ቅዱሶች ሁሉ እጅግ ጥንታዊ የሆነው ይህ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ይህንን ኮዴክስ በ1887 ያገኘው የ19ኛው መቶ ዘመን እውቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ሰው ፌንተን ጄ ኤ ሆርት ነው። ሆርት እንዲህ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል:- “በዚህ ዘመን እንኳ የሚኖር ሰው ይህንን ድንቅ [ጥንታዊ ቅጂ] ሲመለከት በከፍተኛ የአድናቆት ስሜት መዋጡ አይቀርም።”
ወደ ኢጣሊያ መመለስ
ካሲዮዶረስ ኃላፊነቱን ወስዶ ያዘጋጀው የመጀመሪያው ኮዴክስ ግራንዲየር ዛሬ የለም። ይሁን እንጂ የአንግሎ ሳክሶን አምሳያው ኮዴክስ አሚዮቲነስ ከተጠናቀቀ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ወደ ኢጣሊያ የመልስ ጉዞ ማድረግ ጀመረ። ቼልፍሪድ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ወደ ሮም ለመመለስ ወስኖ ስለ ነበር ለርዕሰ ሊቃነ ጳጳሱ ግሪጎሪ ሁለተኛ በስጦታ መልክ ለመስጠት ከሦስቱ የላቲን ቅጂዎቹ መካከል አንዱን ይዞ ሄደ። ቼልፍሪድ በ716 እዘአ በጉዞ ላይ እንዳለ በፈረንሳይ ላንግረስ ሲደርስ በሞት አንቀላፋ። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱሱ ከእርሱ ጋር ይጓዙ ከነበሩት ሰዎች ጋር ጉዞውን ቀጠለ። በመጨረሻም ይኸው ኮዴክስ በማዕከላዊ ኢጣሊያ በሚገኘው የማውንት አሚዮታ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ተቀምጧል። ኮዴክስ አሚዮቲነስ የሚለውን ስያሜም ያገኘው ከዚያ ነው። በ1782 ይህ የእጅ ግልባጭ በኢጣሊያ ፍሎረንስ ወደሚገኘው ሜዲሺያን ሎረንሺያን ቤተ መጻሕፍት የተወሰደ ሲሆን እጅግ ከፍተኛ ግምት ከሚሰጣቸው የቤተ መጻሕፍቱ ንብረቶች አንዱ ለመሆን በቅቷል።
የኮዴክስ ግራንዲየር ውጤት እኛንም ጭምር የሚመለከተን እንዴት ነው? ከካሲዮዶረስ ዘመን አንስቶ ገልባጮችና አታሚዎች መጽሐፍ ቅዱስን በአንድ ጥራዝ ማዘጋጀትን ምርጫቸው አድርገዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ መልክ መዘጋጀቱ እስከ ዛሬም ድረስ ሰዎች በቀላሉ እንዲያገላብጡትና በሕይወታቸው ላይ ከሚያሳድረው ተጽእኖ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል።—ዕብራውያን 4:12
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መላው መጽሐፍ ቅዱስ በግሪክኛ መሠራጨት የጀመረው ከአራተኛው ወይም ከአምስተኛው መቶ ዘመን አንስቶ ነው።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ኮዴክስ ግራንዲየር ያደረገው ጉዞ
ቪቬሪየም ገዳም
ሮም
ጃሮ
ዊርመዝ
ኮዴክስ አሚዮቲነስ ያደረገው ጉዞ
ጃሮ
ዊርመዝ
ማውንት አሚዮታ
ፍሎረንስ
[ምንጭ]
Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.
[በገጽ 30 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Above: Codex Amiatinus Left: Portrait of Ezra in the Codex Amiatinus
[ምንጭ]
Biblioteca Medicea Laurenziana, Firenze