በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“በሕይወቴ ሙሉ የይሖዋ ጥሩነት አልተለየኝም!”

“በሕይወቴ ሙሉ የይሖዋ ጥሩነት አልተለየኝም!”

“በሕይወቴ ሙሉ የይሖዋ ጥሩነት አልተለየኝም!”

ኒው ዮርክ፣ ዩ ኤስ ኤ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የጽሑፍ ዝግጅት ክፍል ውስጥ የሚሠሩ ወንዶችና ሴቶች መጋቢት 1985 አንድ ምሽት ላይ የማይረሳ ጊዜ አሳልፈዋል። ካርል ኤፍ ክላይን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት 60 ዓመት የሞላው ያን ዕለት ነበር። ወንድም ክላይን “በሕይወቴ ሙሉ የይሖዋ ጥሩነት አልተለየኝም” በማለት በደስታ ተናገረ። መዝሙር 37:​4 በጣም የሚወደው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ እንደሆነ ገልጾላቸዋል። ከዚያም ቫዮሊን ሲጫወትላቸው ሁሉም ተደሰቱ።

በቀጣዮቹ 15 ዓመታት ወንድም ክላይን በጽሑፍ ዝግጅት ክፍል ውስጥ መሥራቱንና የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል ሆኖ ማገልገሉን የቀጠለ ሲሆን ጥር 3, 2001 በ95 ዓመቱ ምድራዊ ሕይወቱን በታማኝነት ጨርሷል።

ካርል የተወለደው በጀርመን ሲሆን ቤተሰቡ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሲዛወር በቺካጎ፣ ኢሊኖይስ ከተማ ዳርቻ አደገ። እሱም ሆነ ታናሽ ወንድሙ ቴድ መጽሐፍ ቅዱስን የማወቅ ከፍተኛ ፍላጎት ያደረባቸው ገና በወጣትነታቸው ነበር። ካርል በ1918 የተጠመቀ ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በ1922 ባደረጉት የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ያዳመጠው ንግግር ለመስክ አገልግሎት ምንጊዜም ከውስጡ የማይጠፋ ፍቅር አሳድሮበታል። በሕይወት እስከቆየበት እስከ መጨረሻ ሳምንት ድረስ በስብከቱ ሥራ ሳይካፈል አንዲት ሳምንት እንኳ እንድታልፍበት አይፈልግም ነበር።

ካርል በ1925 የዋናው መሥሪያ ቤት ባልደረባ የሆነ ሲሆን የሚሠራውም በኅትመት ክፍል ውስጥ ነበር። ለሙዚቃ ልዩ ፍቅር የነበረው ሲሆን ለተወሰኑ ዓመታት በክርስቲያን ራዲዮ ስርጭት ላይ በሚቀርበው የሙዚቃ ቡድን ውስጥ ቫዮሊን ይጫወት ነበር። ከዚያም በአገልግሎት ክፍል ውስጥ የሠራ ሲሆን በተለይ የዚህ ክፍል የበላይ ተመልካች ከነበረው ከቲ ጄ ሱሊቫን ጋር ተቀራርቦ በመሥራት አስደሳች ጊዜ አሳልፏል። በዚህ መሃል ቴድ አግብቶ ከባለቤቱ ከዶሪስ ጋር በፖርቶ ሪኮ በሚስዮናዊነት ያገለግል ነበር።

ካርል ክላይን ለግማሽ ምዕተ ዓመት በጽሑፍ ዝግጅት ክፍል ውስጥ የሠራ ሲሆን ምርምር ማድረግ ስለሚወድና ጥልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ስለነበረው ለክፍሉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ካርል በ1963 ቦሊቪያ በሚስዮናዊነት ታገለግል የነበረችውን ማርጋሬታ የምትባል ጀርመናዊት አገባ። እሷ የምታደርግለት ፍቅራዊ ድጋፍ ብዙዎች ጡረታ ከሚወጡበት ዕድሜ በኋላ እንኳ ለረጅም ጊዜ ፍሬያማ ሥራዎችን ለማከናወን አስችሎታል። በተለይ የጤና እክል ከገጠመው በኋላ ይህ የሚስቱ ድጋፍ በእጅጉ ጠቅሞታል። ካርል የነበረው ተፈጥሮአዊ ግልጽነት፣ ሙዚቀኛነቱ ካላበሰው ግለት ጋር ተዳምሮ በጉባኤ ውስጥና በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ የማይረሱ ንግግሮችን እንዲያቀርብ ረድቶታል። ከመሞቱ ከጥቂት ጊዜያት ቀደም ብሎ ብዙ አባላት ላሉት የኒው ዮርክ ቤቴል ቤተሰብ የማለዳ አምልኮ ላይ የዕለት ጥቅስ በመምራት ሁሉንም ማስደሰትና መጥቀም ችሏል።

ብዙ የመጠበቂያ ግንብ የዘወትር አንባቢዎች ጥቅምት 1, 1984 እትም ላይ በወጣው የሕይወት ታሪኩ ውስጥ የጠቀሳቸውን አስደሳች ተሞክሮዎች ያስታውሳሉ። የታሪኩ ባለቤት ለአምላክ ያደረና የታመነ ክርስቲያን በመሆን ተጨማሪ አሥራ አምስት ዓመታት ማሳለፉን በአእምሮህ ይዘህ ታሪኩን ብታነብ ወይም አንብበኸውም ከነበረ ደግመህ ብታነበው ትደሰታለህ።

ወንድም ክላይን ከጌታ ቅቡዓን መካከል አንዱ እንደመሆኑ መጠን ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ለመንገሥ ከልብ ይመኝ ነበር። ይሖዋ ይህን ምኞቱን እንደፈጸመለት እርግጠኞች ነን።​—⁠ሉቃስ 22:​28-30

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ካርል በ1943 ከቲ ጄ ሱሊቫን፣ ከቴድ እና ከዶሪስ ጋር

[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ካርል እና ማርጋሬታ በጥቅምት 2000