በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በይሖዋ መንገድ መጓዛችንን መቀጠላችን ደስታና ጥንካሬ ሰጥቶናል

በይሖዋ መንገድ መጓዛችንን መቀጠላችን ደስታና ጥንካሬ ሰጥቶናል

የሕይወት ታሪክ

በይሖዋ መንገድ መጓዛችንን መቀጠላችን ደስታና ጥንካሬ ሰጥቶናል

በሉጄ ዲ ቫለንቲኖ እንደተነገረው

ይሖዋ “መንገዱ ይህች ናት በእርስዋም ሂድ” በማለት ያሳስበናል። (ኢሳይያስ 30:​21) ይህንን ምክር የመከተል ግብ ያወጣሁት ልክ የዛሬ 60 ዓመት ስጠመቅ ነበር። ይህንን ግብ እንዳወጣ የገፋፋኝ ከኢጣሊያ ተሰድደው በ1921 ዩ ኤስ ኤ፣ ኦሃዮ፣ ክሌቭላንድ የሰፈሩት ወላጆቼ ምሳሌነት ነበር። እዚያም ሦስት ልጆችን ማለትም ማይክ የተባለውን ታላቅ ወንድሜን ሊዲያ የተባለችውን ታናሽ እህቴን እና እኔን አሳድገዋል።

ላጆቼ የተለያዩ ሃይማኖቶችን የመረመሩ ሲሆን መጨረሻ ላይ ግን ተስፋ ቆርጠው አቆሙ። ከዚያም በ1932 አንድ ቀን አባባ በኢጣልያንኛ የሚተላለፍ የራዲዮ ፕሮግራም ይከታተል ነበር። ይህ ፕሮግራም በይሖዋ ምሥክሮች የሚተላለፍ ሲሆን አባባም በሰማው ነገር ተደሰተ። ተጨማሪ መረጃ እንደሚፈልግ የሚገልጽ ደብዳቤ ጽፎ በመላኩ ብሩክሊን ኒው ዮርክ ከሚገኘው ከይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት አንድ ኢጣሊያዊ ምሥክር ሊጎበኘን መጣ። ጎሕ እስኪቀድ ድረስ አስደሳች ውይይት ካደረጉ በኋላ ወላጆቼ እውነተኛውን ሃይማኖት እንዳገኙ ተገነዘቡ።

አባባና እማማ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ከመጀመራቸውም በላይ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾችን እቤታቸው በእንግድነት ይቀበሉ ነበር። በወቅቱ ገና ትንሽ ልጅ ብሆንም እነዚህ ወንድሞች በስብከቱ ሥራ አብሬያቸው እንድካፈል ያደርጉኝ ነበር። ይህም ይሖዋን ሙሉ ጊዜ ስለማገልገል እንዳስብ አደረገኝ። ከእነዚህ ጎብኚዎች መካከል አንዱ በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል ሆኖ የሚያገለግለው ኬሪ ደብሊዩ ባርበር ነበር። ብዙም ሳይቆይ የካቲት 1941 በ14 ዓመቴ ተጠመቅሁና በ1944 የዘወትር አቅኚ ሆኜ በክሌቭላንድ ማገልገል ጀመርኩ። ማይክ እና ሊዲያም የመጽሐፍ ቅዱስን የእውነት መንገድ መከተል ጀመሩ። ማይክ እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ ይሖዋን በታማኝነት ያገለገለ ሲሆን ሊዲያ ደግሞ ሃሮልድ ዌድነር ከተባለው ባለቤቷ ጋር ከ28 ለሚበልጡ ዓመታት በተጓዥነት ሥራ አገልግለዋል። ዛሬ ልዩ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ናቸው።

እስር ወደፊት ለመግፋት ያደረግሁትን ቁርጥ ውሳኔ አጠነከረልኝ

በ1945 መጀመሪያ ላይ በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናዬ ሰይፋቸውን ማረሻ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ ከሚለው ከኢሳይያስ 2:​4 ምክር ጋር ተስማምቼ እንድመላለስ ስለገፋፋኝ ኦሃዮ በሚገኘው ቺሊኮትዝ ፌደራላዊ እስር ቤት እንድገባ ተደረገ። በአንድ ወቅት የእስር ቤቱ ባለ ሥልጣናት ምሥክር የሆኑት እስረኞች በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጁ ጽሑፎችን በተወሰነ መጠን እንዲያገኙ ፈቅደውላቸው ነበር። ይሁን እንጂ አቅራቢያቸው በሚገኘው ጉባኤ ውስጥ ያሉ ምሥክሮች እገዛ አደረጉላቸው። አንዳንድ ጊዜ ከእስር ቤቱ አጠገብ በሚገኙት ማሳዎች ውስጥ ጥቂት ጽሑፎች ጥለውላቸው ይሄዳሉ። በሚቀጥለው ቀን ጠዋት እስረኞቹ ወደሚሠሩባቸው ቦታዎች ሲወሰዱ እነዚህን ጽሑፎች ከወዳደቁበት ፈላልገው ያገኟቸውና ወደ እስር ቤቱ ያስገቧቸው ነበር። እኔ እስር ቤቱ ስደርስ ግን ተጨማሪ ጽሑፎችን እንድናገኝ ተፈቅዶልን ነበር። ይሖዋ የሚያቀርበው መንፈሳዊ ምግብ ያለው ዋጋማነት ምን ያህል ከፍተኛ እንደሆነ የተገነዘብኩት ያኔ ነው። ዛሬም አንድ አዲስ የመጠበቂያ ግንብ ወይም የንቁ! መጽሔት እትም ሲደርሰኝ ይህንን ትምህርት አስታውሳለሁ።

እስር ቤቱ ውስጥ ስብሰባዎች እንድናካሂድ ቢፈቀድልንም በስብሰባዎቹ ላይ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎች እንዲገኙ አይፈቀድላቸውም ነበር። ሆኖም አንዳንድ የእስር ቤቱ ባለ ሥልጣናትና እስረኞች በስብሰባዎች ላይ በድብቅ ይገኙ የነበረ ሲሆን አንዳንዶቹም እውነትን ተቀብለዋል። (ሥራ 16:​30-34) ወንድም ኤ ኤች ማክሚላን የሚያደርግልን ጉብኝቶች ከፍተኛ ማጽናኛ የምናገኝባቸው ወቅቶች ነበሩ። በእስር ቤት የምናሳልፈው ጊዜ ወደፊት ለሚጠብቀን ሥራ የሚያዘጋጀን እንጂ ከንቱ ሆኖ የሚቀር እንዳልሆነ ሁልጊዜ ያረጋግጥልን ነበር። ይህ በእድሜ የገፋ ውድ ወንድም ልቤን በጥልቅ የነካው ሲሆን በይሖዋ መንገድ ለመጓዝ ያደረግሁትን ቁርጥ ውሳኔ አጠንክሮልኛል።

የትዳር ጓደኛ አገኘሁ

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲያበቃ የእስር ቤት በሮች ተከፈቱ። እኔም በአቅኚነት ማገልገሌን ቀጠልኩ። ሆኖም በ1947 አባቴ ሞተ። ቤተሰቡን ለመደገፍ ሰብዓዊ ሥራ መሥራት ከመጀመሬም በተጨማሪ እኔና ባለቤቴ ከ30 ዓመታት በኋላ ላጋጠመን ፈተና መወጣጫ የሆነኝን የእሽት ሕክምና ችሎታ አዳበርኩ። ሆኖም አሁን የታሪኩን ቅደም ተከተል አዛንፌአለሁ። በመጀመሪያ ስለ ሚስቴ ልንገራችሁ።

በ1949 አንድ ከሰዓት በኋላ መንግሥት አዳራሽ ውስጥ ሳለሁ ስልኩ ጮኸ። ሳነሳው አንድ ደስ የሚል ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ:- “ክርስቲን ጀንቸር እባላለሁ። የይሖዋ ምሥክር ነኝ። እዚህ ክሌቭላንድ የመጣሁት ሥራ ለመፈለግ ነው፤ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት እፈልጋለሁ።” የእኛ የመንግሥት አዳራሽ እርሷ ከምትኖርበት አካባቢ ርቆ የሚገኝ ቢሆንም ድምፅዋን ስለወደድኩት አቅጣጫውን ጠቆምኳትና እኔ የሕዝብ ንግግር በምሰጥበት ቀን እሁድ እንድትመጣ አበረታታኋት። እሁድ ዕለት መንግሥት አዳራሽ ለመገኘት የመጀመሪያው ሰው ብሆንም አንዲትም አዲስ እህት ብቅ አላለችም። ንግግሬን ጀምሬ እስክጨርስ ዓይኔን ወደ በሩ ወርወር ባደርግም ማንም ብቅ ሳይል ቀረ። በሚቀጥለው ቀን ስልክ ደውዬ ስጠይቃት መንገዱ ግራ ስላጋባት መምጣት እንዳልቻለች ነገረችኝ። እኔም ተገናኝተን ሁኔታዎቹን ይበልጥ በተሻለ መልኩ ላብራራላት እንደምችል ገለጽኩላት።

ከቺኮዝላቫኪያ ተሰድደው የመጡት ወላጆቿ ሙታን የት ናቸው? (እንግሊዝኛ) የተባለውን ቡክሌት ካነበቡ በኋላ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር መሰብሰብ እንደጀመሩ ተረዳሁ። ከዚያም በ1935 ተጠመቁ። በ1938 የክርስቲን አባት ክላይማር ፔንሲልቬንያ ዩ ኤስ ኤ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ የቡድን አገልጋይ (በአሁኑ ጊዜ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካች እንደሚባለው ማለት ነው) ሆኖ ማገልገል ጀመረ። ክርስቲንም በ1947 በ16 ዓመቷ ተጠመቀች። መንፈሳዊ አስተሳሰብ ባላት በዚህች ቆንጆ እህት ፍቅር ወዲያው ተነደፍኩ። ሰኔ 24, 1950 ተጋባን። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ክርስቲን የአምላክን መንግሥት ፍላጎቶች ለማስቀደም ሁልጊዜ ፈቃደኛ የሆነች ታማኝ የትዳር ጓደኛዬ ሆናለች። ይህች ልባም ሴት ቀሪ ሕይወቷን ከእኔ ጋር ለማሳለፍ በመምረጧ ይሖዋን አመሰግነዋለሁ።​—⁠ምሳሌ 31:​10

ያልታሰበ አስደሳች ዜና

ኅዳር 1, 1951 ሁለታችንም አቅኚ ሆነን ማገልገል ጀመርን። ከሁለት ዓመት በኋላ ቶሌዶ ኦሃዮ ውስጥ በተደረገ አንድ ትልቅ ስብሰባ ላይ ወንድም ሁጎ ራመርና ወንድም አልበርት ሽሮደር ለሚስዮናዊ አገልግሎት ፍላጎት ያለውን አንድ የአቅኚዎች ቡድን አነጋገሩ። እኛም በዚህ ቡድን ውስጥ ነበርን። በክሌቭላንድ በአቅኚነት ማገልገላችንን እንድንቀጥል ማበረታቻ የተሰጠን ቢሆንም ልክ በወሩ አንድ ያልታሰበ አስደሳች ዜና ደረሰን። የካቲት 1954 በሚጀምረው በ23ኛው የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እንድንካፈል ተጋበዝን!

ኒው ዮርክ ሳውዝ ላንሲንግ ወደሚገኘው የጊልያድ ትምህርት ቤት ስንጓዝ ክርስቲን በጣም ከመፍራቷ የተነሳ ያለማቋረጥ “ቀስ ብለህ ንዳ!” ትለኝ ነበር። “ክርስቲን፣ ከዚህ በላይ፤ አንደኛውኑ እንቁም ብትይኝ አይሻልም?” አልኳት። ትምህርት ቤቱ ግቢ ውስጥ ከደረስን በኋላ ግን ይበልጥ የመረጋጋት ስሜት ተሰማን። ወንድም ናታን ኖር የተማሪዎቹን ቡድን ከተቀበለ በኋላ አካባቢውን አስጎበኘን። ከመንግሥቱ ጋር በተያያዘ ቆጣቢ የመሆንን አስፈላጊነት ጠበቅ አድርጎ በመግለጽ በውኃና በኤሌክትሪክ አጠቃቀማችን ረገድ እንዴት ጠንቃቆች መሆን እንደምንችል አስረዳን። ይህ ምክር አእምሮአችን ውስጥ በመስረጹ ይኸው እስከ ዛሬ ድረስ እንሠራበታለን።

ወደ ሪዮ መብረር

ብዙም ሳይቆይ ተመረቅንና ታኅሣሥ 10, 1954 ብርዳማዋን የኒው ዮርክ ከተማ ለቅቀን አዲሷ ምድባችን ወደሆነችውና ብራዚል ውስጥ ወደምትገኘው ሞቃታማዋ ሪዮ ዲ ጃኔሮ ስንበርር ደስታችን ወሰን አልነበረውም። ፒተር እና ቢሊ ካርቤሎ የተባሉ ሚስዮናውያን ባልና ሚስት ከእኛ ጋር አብረው ተጉዘው ነበር። በረራው ፖርቶሪኮ፣ ቬኔዝዌላ እንዲሁም ደቡብ ብራዚል በምትገኘው ቢለም ውስጥ ትንሽ ቆይታ ማድረግን ጨምሮ በአጠቃላይ ሃያ አራት ሰዓት የሚፈጅ ነበር። ይሁን እንጂ ሞተሩ ላይ ችግር በመፈጠሩ ሪዮ ዲ ጃኔሮን የተመለከትናት ከሰላሳ ስድስት ሰዓታት በኋላ ነበር። ምንኛ አስደናቂ ዕይታ ነው! የከተማዋ መብራቶች ልክ በጥቁር ምንጣፍ ላይ እንዳሉ እሳታማ አልማዞች ያንጸባርቃሉ። የጨረቃዋ ብርማ ብርሃን በጉዋናባራ ቤይ ውኃዎች ላይ የሚያምር ብርቅርቅታ ፈጥሯል።

ብዙዎቹ የቤቴል ቤተሰብ አባላት እኛን ለመቀበል አየር ማረፊያው ድረስ መጥተው ነበር። ሞቅ ያለ አቀባበል ካደረጉልን በኋላ በመኪና ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ወሰዱን። ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት ሲል ብንተኛም ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ያቃጨለው ደወል የሚስዮናዊ አገልግሎታችን የመጀመሪያ ቀን መጀመሩን አበሰረን!

በመጀመሪያ ያገኘነው ትምህርት

ብዙም ሳይቆይ አንድ አስፈላጊ ነገር ተማርን። አንድ ምሽት ከአንድ ምሥክር ቤተሰብ ጋር አሳለፍን። ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ለመመለስ ስንዘጋጅ የቤቱ ባለቤት “አይሆንም፣ እየዘነበ ስለሆነ መሄድ አትችሉም” ሲል ተቃወመን። እንድናድርም አጥብቆ ለመነን። ሳቅ አልኩና “እንዴ፣ እኛም አገር እኮ ይዘንባል” አልኩት። ከዚያም ወጥተን ሄድን።

ሪዮ ዙሪያዋን በተራሮች የተከበበች በመሆኗ ዝናብ ሲዘንብ ውኃው ፈጥኖ ወደ ከተማው የሚፈስ ሲሆን ብዙውን ጊዜም ጎርፍ ያስከትላል። ብዙም ሳይቆይ እስከ ጉልበታችን በደረሰው ውኃ ውስጥ እየተንቦጫረቅን መሄድ ጀመርን። ቅርንጫፍ ቢሮው አካባቢ ያሉት መንገዶች በጎርፍ ከመጥለቅለቃቸው የተነሳ ውኃው ደረታችን ደረሶ ነበር። በመጨረሻም ሰውነታችን ሙሉ በሙሉ በውኃ ርሶ ቤቴል ደረስን። በሚቀጥለው ቀን ክርስቲን ሕመም ተሰማት። ምርመራ ስታደርግ የአንጀት ተስቦ በሽታ እንደያዛት ተነገራት። ይህ በሽታ ለረዥም ጊዜ አቅም አሳጥቷት ነበር። ያም ሆነ ይህ አዲስ ሚስዮናውያን እንደመሆናችን መጠን ተሞክሮ ያካበቱ የአገሩ ተወላጅ ምሥክሮች የሰጡንን ምክር መስማት ነበረብን።

በሚስዮናዊነትና በተጓዥነት ሥራችን የወሰድናቸው የመጀመሪያ እርምጃዎች

ከዚህ አሳዛኝ ጅምር በኋላ የመስክ አገልግሎታችንን በከፍተኛ የጉጉት ስሜት ተያያዝነው። ላገኘነው ሰው ሁሉ በፖርቱጋል ቋንቋ የተዘጋጀ መግቢያ እናነብለታለን። ቋንቋውን በመናገር ረገድ ሁለታችንም ተመሳሳይ እድገት ያደረግን ይመስል ነበር። አንድ የቤት ባለቤት ክርስቲንን “አንቺ የምትይው ገብቶኛል። የእርሱ ግን ምንም አልገባኝም” ይላታል ወደ እኔ እየጠቆመ። ሌላኛው የቤት ባለቤት ደግሞ “አንተ የምትለው ገብቶኛል። እርሷ የምትለው ግን ጨርሶ አልገባኝም” ይለኛል። ያም ሆኖ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት ከ100 የሚበልጡ የመጠበቂያ ግንብ ኮንትራቶች በማስገባታችን በጣም ተደሰትን። እንዲያውም ብራዚል ውስጥ በሚስዮናዊነት ባገለገልንበት በመጀመሪያው ዓመት በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቻችን መጠመቃቸው ይህ ሚስዮናዊ ምድባችን ምን ያህል ፍሬያማ ሊሆን እንደሚችል ፍንጭ ሰጥቶናል።

በ1950ዎቹ አጋማሽ ላይ ብቃት ያላቸው ወንድሞች እጥረት ስለነበር በብራዚል የሚገኙ ብዙ ጉባኤዎች በወረዳ የበላይ ተመልካቾች በቋሚነት አይጎበኙም ነበር። ስለዚህ ቋንቋውን ገና በመማር ላይ የምገኝና በፖርቱጋል ቋንቋ የሕዝብ ንግግር ሰጥቼ የማላውቅ ብሆንም በ1956 በሳኦ ፖውሎ ግዛት የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ።

በመጀመሪያ የጎበኘነው ጉባኤ የወረዳ የበላይ ተመልካች ጉብኝት ከተደረገለት ሁለት ዓመት አልፎት ስለነበር የሕዝብ ንግግሩን ለመስማት ሁሉም ጓጉተው ነበር። ያንን ንግግር ለማዘጋጀት በፖርቱጋል ቋንቋ ከተዘጋጁት የመጠበቂያ ግንብ ርዕሶች ላይ አንቀጾችን ቆራረጥኩና በወረቀት ላይ ለጠፍኳቸው። ንግግሩን በምሰጥበት ቀን የመንግሥት አዳራሹ ጢም ብሎ ሞልቶ ነበር። በመድረኩ ላይ ሳይቀር ተቀምጠው ንግግሩ የሚጀምርበትን ሰዓት በጉጉት ይጠባበቃሉ። ንግግሩ አይ፣ ንባቡ ብል ይሻላል ተጀመረ። ትንሽ ቆየት ብዬ ቀና ስል ልጆች እንኳ ሳይቀሩ አንድም የሚንቀሳቀስ ሰው አልነበረም። ሁሉም አፍጥጠው ይመለከቱኝ ነበር። እንዲህ ብዬ አሰብኩ:- ‘አይ ቫለንቲኖ፣ ቋንቋህ ምንኛ ተሻሽሏል! ሰዎቹ እኮ በትኩረት እየተከታተሉህ ነው።’ ዓመታት ካለፉ በኋላ ይህንኑ ጉባኤ በድጋሚ ለመጎብኘት በሄድኩ ጊዜ በመጀመሪያው የጉብኝት ስብሰባ ላይ የነበረ አንድ ወንድም እንዲህ አለኝ:- “ያን ጊዜ የሰጠኸንን የሕዝብ ንግግር ታስታውሳለህ? ከተናገርከው መካከል አንድም ቃል አልገባንም።” እኔም ብሆን አብዛኛው የንግግሩ ክፍል እንዳልገባኝ ገለጽኩለት።

በወረዳ ሥራ በተካፈልኩበት በመጀመሪያው ዓመት ዘካርያስ 4:​6ን በተደጋጋሚ አነብብ ነበር። “በመንፈሴ እንጂ በኃይልና በብርታት አይደለም” የሚሉት ቃላት የመንግሥቱን ሥራ የሚያሳድገው የይሖዋ መንፈስ ብቻ መሆኑን እንዳስታውስ ያደርጉኛል። የአቅም ገደቦች እያሉብንም እንኳ ሥራው እድገት ማድረጉን ቀጥሏል።

በጉዟችን ላይ ያጋጠሙን ፈተናዎችና በረከቶች

የወረዳ ሥራ ማለት የጽሕፈት መኪና፣ በካርቶን ውስጥ የታጨቁ ጽሑፎች፣ ሻንጣዎችና ቦርሳዎች ጭኖ ከቦታ ቦታ መዘዋወር ማለት ነው። ክርስቲን ከአንድ አውቶቡስ ወደ ሌላኛው አውቶቡስ ለመሳፈር በምንጣደፍበት ጊዜ አንዳንድ እቃዎችን እንዳንረሳ በዕቃዎቹ ላይ ቁጥር ጻፈችባቸው። ቀጣዩ ምድባችን ለመድረስ በተበላሹ መንገዶች ላይ ለአሥራ አምስት ሰዓታት በአውቶቡስ መጓዛችን የተለመደ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ጉዞው በጣም ያስፈራ ነበር። በተለይ ከተቃራኒ አቅጣጫ የሚመጡ ሁለት አውቶቡሶች ሊፈርስ በደረሰ ድልድይ ላይ በጣም ተጠጋግተው ሲተላለፉ ማየት በጣም አስፈሪ ነው። በባቡር፣ በመርከብና በፈረስም ተጉዘናል።

በ1961 ከአንድ ጉባኤ ወደ ሌላ ጉባኤ ሳይሆን ከአንዱ ወረዳ ወደ ሌላ ወረዳ በመጓዝ በአውራጃ ሥራ መካፈል ጀመርን። በሳምንቱ ውስጥ ባሉት በአብዛኞቹ ምሽቶች በይሖዋ ድርጅት የተዘጋጁትን ፊልሞች በተለያዩ ቦታዎች እናሳይ ነበር። የአካባቢው ቄሶች ፊልሞቹ እንዳይታዩ ለማድረግ የሚሸርቡትን ሴራ ለማክሸፍ ብዙውን ጊዜ ፈጣን እርምጃ እንወስድ ነበር። በአንድ ከተማ አንድ የአዳራሽ ባለቤት ከእኛ ጋር የገባውን ኮንትራት እንዲሰርዝ ቄሱ አስገድዶ አሳመነው። ብዙ ቀን የፈጀ ፍለጋ ካደረግን በኋላ ሌላ ቦታ አገኘን። ይሁን እንጂ አዳራሽ ማግኘታችንን ለማንም ሰው ሳንነግር ሰዎችን በመጀመሪያ አግኝተነው ወደነበረው ቦታ መጋበዛችንን ቀጠልን። ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት ክርስቲን ቀስ ብላ ወደ መጀመሪያው አዳራሽ ሄደችና ፊልሙን ለማየት የሚፈልጉትን ሰዎች አዲሱን አድራሻ ጠቆመቻቸው። በዚያ ምሽት ዘ ኒው ወርልድ ሶሳይቲ ኢን አክሽን የሚል ተስማሚ ርዕስ የነበረውን ፊልም 150 ሰዎች ተመልክተውታል።

በገለልተኛ አካባቢዎች የምናደርጋቸው ጉብኝቶች አንዳንድ ጊዜ ኃይላችንን የሚያሟጥጡብን ቢሆኑም እዚያ የሚኖሩት ትሁት ወንድሞች ለእነዚህ ጉብኝቶች ከፍተኛ አድናቆት ነበራቸው። አነስተኛ በሆኑት ቤቶቻቸው እኛን በእንግድነት ለመቀበል ደስተኞች ከመሆናቸው የተነሳ ከእነርሱ ጋር መሆን በመቻላችን ይሖዋን ዘወትር እናመሰግነው ነበር። ከእነርሱ ጋር ወዳጅነት መመስረታችን ብዙ በረከቶችን አምጥቶልናል። (ምሳሌ 19:​17፤ ሐጌ 2:​7) ከ21 ለሚበልጡ ዓመታት በብራዚል በሚስዮናዊ አገልግሎት ካሳለፍን በኋላ ይህንን ሥራችንን ለማቆም ስንገደድ ምንኛ አዝነን ነበር!

ችግር ሲገጥመን ይሖዋ መውጫውን አሳየን

በ1975 ክርስቲን ቀዶ ሕክምና ተደረገላት። በተጓዥነት ሥራ የቀጠልን ብንሆንም የክርስቲን ጤና ግን እያሽቆለቆለ ሄደ። የተሻለ ሕክምና እንድታገኝ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ መመለስ እንዳለብን ተገነዘብን። ሚያዝያ 1976 ሎንግ ቢች ካሊፎርኒያ ከደረስን በኋላ እናቴ ጋር አረፍን። ለሁለት አሥርተ ዓመታት በውጭ አገር ከኖርን በኋላ የገጠመንን እንዲህ ያለውን ችግር እንዴት እንደምንወጣው ግራ ተጋባን። የእሽት ህክምና መስጠት ጀመርኩና ከዚህ በማገኘው ገቢ ራሳችንን ማስተዳደር ቻልን። የካሊፎርኒያ ግዛት ክርስቲን ሆስፒታል ተኝታ ሕክምና እንዲደረግላት ቢፈቅድም ዶክተሮቹ ክርስቲንን ያለ ደም ለማከም ፈቃደኞች ባለመሆናቸው ክርስቲን ከቀን ወደ ቀን እየተዳከመች መጣች። በጣም ስለተጨነቅን መመሪያ እንዲሰጠን ይሖዋን ተማጸንነው።

አንድ ከሰዓት በኋላ በመስክ አገልግሎት ላይ እንዳለሁ አንድ የሐኪም ቢሮ ተመለከትኩና በድንገት ወደ ውስጥ ለመግባት ወሰንኩ። ሐኪሙ ወደ ቤቱ ለመሄድ በመዘጋጀት ላይ የነበረ ቢሆንም ግባ አለኝና ለሁለት ሰዓታት ተነጋገርን። ከዚያም እንዲህ አለ:- “ሚስዮናዊ ሆናችሁ የምታከናውኑትን ሥራ አደንቃለሁ። ስለዚህ ባለቤትህን ያለ ምንም ክፍያና ያለ ደም አክምልሃለሁ።” ጆሮዬን ማመን አቃተኝ።

ይህ ደግና የተከበረ የሕክምና ባለሙያ ክርስቲን እርሱ ወደሚሠራበት ሆስፒታል እንድትዛወር አደረገ። እዚያም እርሱ ክትትል ስላደረገላት ብዙም ሳይቆይ ጤናዋ ተሻሻለ። በዚያ አስቸጋሪ ጊዜ ይሖዋ መውጫውን ስላሳየን ምንኛ አመስጋኞች ነን!

አዳዲስ ምድቦች

ክርስቲን ካገገመች በኋላ አቅኚዎች ሆነን ማገልገል ጀመርን። በሎንግ ቢች የሚኖሩ በርካታ ሰዎች የይሖዋ አምላኪዎች እንዲሆኑ መርዳት በመቻላችን ተደስተናል። በ1982 ደግሞ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በወረዳ ሥራ እንድንካፈል ተጠየቅን። ይሖዋ በዚህ በምንወደው የአገልግሎት ዘርፍ እንደገና ሊጠቀምብን በመፈለጉ በየዕለቱ እናመሰግነዋለን። ለተወሰነ ጊዜ በካሊፎርኒያ ካገለገልን በኋላ በኒው ኢንግላንድ ማለትም የፖርቱጋል ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ አንዳንድ ጉባኤዎችን በሚያቅፈው ወረዳ ውስጥ ማገልገል ጀመርን። በኋላም ቤርሙዳ በዚህ ወረዳ ውስጥ ተካተተ።

ከአራት አስደሳች ዓመታት በኋላ አንድ ሌላ ምድብ ተቀበልን። በመረጥነው ቦታ ልዩ አቅኚዎች ሆነን እንድናገለግል ግብዣ ቀረበልን። የተጓዥ ሥራችንን በማቆማችን መጀመሪያ ላይ ብናዝንም አዲሱን ምድባችንን ተቀብለን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ አደረግን። ግን የት? በተጓዥ ሥራ ላይ እንዳለን ኒው ቤድፎርድ ማሳቹሴትስ የሚገኘው የፖርቱጋል ቋንቋ ተናጋሪ ጉባኤ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተገንዝቤ ስለነበር ወደ ኒው ቤድፎርድ አመራን።

እዚያም ስንደርስ ጉባኤው በጣም ትልቅ ግብዣ አድርጎ ተቀበለን። ይህም ምን ያህል የምንፈለግ መሆናችንን አስገነዘበን! እንባ አውጥተን አለቀስን። ሁለት ሕፃናት ልጆች ያሏቸው አንድ ወጣት ባልና ሚስት የራሳችንን አፓርታማ እስክናገኝ ድረስ በደግነት ቤታቸው ተቀበሉን። ይሖዋ ይህንን የልዩ አቅኚነት ምድብ እኛ ከጠበቅነው በላይ ባርኮታል። ከ1986 ጀምሮ በዚህ ከተማ የሚኖሩ 40 የሚያህሉ ሰዎች ምሥክር እንዲሆኑ ረድተናቸዋል። መንፈሳዊ ቤተሰቦቻችን ናቸው። በተጨማሪም አምስት የአገሩ ተወላጅ ወንድሞች እድገት አድርገው ለመንጋው አሳቢ የሆኑ እረኞች ሲሆኑ የማየት መብት አግኝቻለሁ። ፍሬያማ በሆነ ሚስዮናዊ ምድብ እንዳገለገልኩ ያክል ነው።

ያሳለፍነውን ጊዜ ወደ ኋላ መለስ ብለን ስንመለከት ከወጣትነታችን ጀምረን ይሖዋን በማገልገላችንና እውነትን የሕይወታችን መንገድ በማድረጋችን ደስተኞች ነን። እርግጥ ነው፣ አሁን የዕድሜ መግፋትና የጤና እክሎች ተጽእኖ ቢያደርጉብንም በይሖዋ መንገድ መጓዛችንን መቀጠላችን አሁንም ቢሆን ደስታና ጥንካሬ ይሰጠናል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሪዮ ዲ ጃኔሮ እንደደረስን

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኒው ቤድፎርድ ማሳቹሴትስ የሚገኘው መንፈሳዊ ቤተሰባችን