በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ለታላላቅ ሥራዎቹ ይሖዋን አወድሱት!

ለታላላቅ ሥራዎቹ ይሖዋን አወድሱት!

ለታላላቅ ሥራዎቹ ይሖዋን አወድሱት!

“ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች . . . ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና።”​—⁠ሉቃስ 1:​46-49

1. እንዴት ላሉት ታላላቅ ሥራዎቹ ይሖዋን ማወደስ ይኖርብናል?

 ይሖዋ ላከናወናቸው ታላላቅ ሥራዎች ሊወደስ ይገባዋል። ነቢዩ ሙሴ እስራኤላውያን ከግብፅ ነፃ ስለወጡበት ሁኔታ ሲተርክ “እግዚአብሔር ያደረጋትን ታላቂቱን ሥራ ሁሉ ዓይኖቻችሁ አይተዋል” በማለት ተናግሯል። (ዘዳግም 11:​1-7) በተመሳሳይም መልአኩ ገብርኤል የኢየሱስን መወለድ ለድንግል ማርያም ባበሰራት ጊዜ “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች . . . ብርቱ የሆነ እርሱ በእኔ ታላቅ ሥራ አድርጎአልና” በማለት ተናገረች። (ሉቃስ 1:​46-49) እኛም የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ነፃ ለማውጣትም ሆነ ውድ ልጁ ተአምራዊ በሆነ መንገድ እንዲወለድ ለማድረግ ሲል እንዳከናወናቸው ላሉት ታላላቅ ሥራዎቹ ይሖዋን እናወድሳለን።

2. (ሀ) ‘የአምላክ ዘላለማዊ ዓላማ’ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ዘሮች ምን ትርጉም አለው? (ለ) ዮሐንስ በፍጥሞ ደሴት ሳለ የተመለከተው ምን ነበር?

2 ይሖዋ ያከናወናቸው ብዙዎቹ ታላላቅ ሥራዎች በመሲሑና በመንግሥቱ አገዛዝ አማካኝነት ታዛዥ የሰው ልጆችን ለመባረክ ካለው ‘ዘላለማዊ ዓላማ’ ጋር የተያያዙ ናቸው። (ኤፌሶን 3:​8-13) አረጋዊው ሐዋርያ ዮሐንስ ሰማይ ላይ በተከፈተ በር ራእይ እንዲመለከት ሲደረግ ይህ ዓላማ ደረጃ በደረጃ በመካሄድ ላይ ነበር። “ወደዚህ ውጣና ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚያስፈልገውን ነገር አሳይሃለሁ” የሚል እንደ መለከት ያለ ድምፅ ሰማ። (ራእይ 4:​1) ዮሐንስ “ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክር” በሮማ መንግሥት ፍጥሞ ወደምትባል ደሴት ተግዞ በተወሰደ ጊዜ ‘ኢየሱስ ክርስቶስ የገለጠለትን ራእይ’ ተቀበለ። ሐዋርያው የተመለከታቸውና የሰማቸው ነገሮች ስለ አምላክ ዘላለማዊ ዓላማ ብዙ ነገር የሚገልጡ ሲሆን ለእውነተኛ ክርስቲያኖች በሙሉ መንፈሳዊ የእውቀት ብርሃን ይፈነጥቃሉ እንዲሁም ወቅታዊ የሆነ ማበረታቻ ይሰጣሉ።​—⁠ራእይ 1:​1, 9, 10

3. ዮሐንስ በራእይ የተመለከታቸው 24 ሽማግሌዎች እነማንን ይወክላሉ?

3 ዮሐንስ በዚያ በተከፈተለት በር በኩል እንደ ነገሥታት ዙፋን ላይ የተቀመጡና አክሊል የደፉ 24 ሽማግሌዎችን ተመልክቷል። በአምላክ ፊት ወድቀው “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፣ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል” በማለት ተናገሩ። (ራእይ 4:​10, 11) እነዚህ ሽማግሌዎች አምላክ ቃል የገባላቸውን ከፍተኛ ቦታ የተቀበሉትን ከሙታን የተነሱትን ቅቡዓን በሙሉ ያመለክታሉ። ከፍጥረት ጋር በተያያዙ ታላላቅ ሥራዎቹ የተነሳ ይሖዋን ለማወደስ ተገፋፍተዋል። እኛም ብንሆን የይሖዋ ‘ዘላለማዊ ኃይልና አምላክነት’ መግለጫ የሆኑትን ነገሮች ስንመለከት እንደነቃለን። (ሮሜ 1:​20) እንዲሁም ስለ ይሖዋ ይበልጥ እያወቅን በሄድን መጠን ድንቅ ለሆኑት ሥራዎቹ እርሱን እንድናወድስ የሚያደርጉን ተጨማሪ ምክንያቶች እናገኛለን።

የይሖዋን ድንቅ ሥራዎች ተናገሩ!

4, 5. ዳዊት ይሖዋን እንዴት እንዳወደሰ የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ጥቀስ።

4 መዝሙራዊው ዳዊት አምላክ ላከናወናቸው ታላላቅ ሥራዎች ውዳሴ አቅርቧል። ለምሳሌ ያህል ዳዊት እንዲህ በማለት ዘምሯል:- “በጽዮን ለሚኖር ለእግዚአብሔር ዘምሩ፣ በአሕዛብም መካከል አደራረጉን ንገሩ፤ አቤቱ፣ እዘንልኝ፣ ጠላቶቼም የሚያመጡብኝን መከራ እይ፣ ከሞት ደጆች ከፍ ከፍ የምታደርገኝ፤ ምስጋናውን ሁሉ እናገር ዘንድ፤ በጽዮን ልጅ በደጆችዋ በማዳንህ ደስ ይለኛል።” (መዝሙር 9:​11, 13, 14) ዳዊት የቤተ መቅደሱን ንድፍ ለልጁ ለሰሎሞን ከሰጠ በኋላ እንዲህ በማለት አምላክን በመባረክ ውዳሴ አሰማ:- “አቤቱ፣ . . . ታላቅነትና ኃይል፣ ክብርም፣ ድልና ግርማ ለአንተ ነው፤ መንግሥት የአንተ ነው፣ አንተም በሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ያልህ ራስ ነህ። . . . አሁንም እንግዲህ፣ አምላካችን ሆይ፣ እንገዛልሃለን፣ ለክቡር ስምህም ምስጋና እናቀርባለን።”​—⁠1 ዜና መዋዕል 29:​10-13

5 ቅዱሳን ጽሑፎች ዳዊት እንዳደረገው አምላክን እንድናወድስ ይጋብዙናል፣ አዎን፣ አጥብቀው ይመክሩናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የመዝሙር መጽሐፍ ለአምላክ የቀረቡ በርካታ የውዳሴ መግለጫዎችን ይዟል። ከእነዚህ መዝሙሮች ውስጥ ግማሽ የሚያክሉት ደግሞ ንጉሥ ዳዊት ያቀናበራቸው ናቸው። ዳዊት ዘወትር ይሖዋን ያወድስና ያመሰግን ነበር። (መዝሙር 69:​30) ከዚህም በላይ ዳዊትና ሌሎች ያቀናበሯቸው ግጥሞችና መዝሙሮች ከጥንት ጀምሮ ይሖዋን ለማወደስ ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

6. በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት መዝሙራት ለእኛ ጠቃሚ ሆነው የተገኙት እንዴት ነው?

6 መዝሙራት ለይሖዋ አምላኪዎች ምንኛ ጠቃሚ ናቸው! አምላክ ለእኛ ጥቅም ሲል ስላደረጋቸው ድንቅ ነገሮች ሁሉ ልናመሰግነው በምንፈልግበት ጊዜ አእምሯችን በመዝሙራት ውስጥ ወደሚገኙት ውብ ቃላት ዞር ማለቱ አይቀርም። ለምሳሌ ያህል፣ ሌሊቱ አልፎ አዲስ ቀን ሲጠባ እንደሚከተለው ያሉ መግለጫዎችን ለመጠቀም እንገፋፋ ይሆናል:- “እግዚአብሔርን ማመስገን መልካም ነው፣ ልዑል ሆይ፣ ለስምህም ዝማሬ ማቅረብ፤ በማለዳ ምሕረትን፣ በሌሊትም እውነትህን ማውራት . . . አቤቱ፣ በሥራህ ደስ አሰኝተኸኛልና፤ በእጅህም ሥራ ደስ ይለኛልና።” (መዝሙር 92:​1-4) ለመንፈሳዊ እድገታችን እንቅፋት ሆኖ የቆየ አንድ ችግር በምናሸንፍበት ጊዜ እንደሚከተለው በማለት እንደዘመረው መዝሙራዊ እኛም የተሰማንን ደስታና የአመስጋኝነት ስሜት በጸሎት ለመግለጽ እንፈልግ ይሆናል። “ኑ፣ በእግዚአብሔር ደስ ይበለን፤ ለአምላክ ለመድኃኒታችን እልል እንበል። በምስጋና ወደ ፊቱ እንድረስ፣ በዝማሬም ለእርሱ እልል እንበል።”​—⁠መዝሙር 95:​1, 2

7. (ሀ) ክርስቲያኖች የሚዘምሯቸውን በርካታ መዝሙሮች በተመለከተ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ምንድን ነው? (ለ) በስብሰባዎች ላይ ቀደም ብለን እንድንገኝና እስኪያልቅ ድረስ እንድንቆይ የሚያደርገን አንደኛው ምክንያት ምንድን ነው?

7 ብዙውን ጊዜ በጉባኤ ስብሰባዎች፣ በወረዳና በልዩ ስብሰባዎች እንዲሁም በሌሎች ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ድምፃችንን ከፍ አድርገን በመዘመር ይሖዋን እናወድሳለን። ከእነዚህ መዝሙሮች መካከል አብዛኞቹ በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ ከሚገኙት በመንፈስ አነሳሽነት ከሰፈሩት ሐሳቦች የተወሰዱ መሆናቸው ትኩረት የሚስብ ነው። በዛሬው ጊዜ ይሖዋን የምናወድስባቸው ውብ የመዝሙሮች ስብስብ በማግኘታችን ምንኛ ደስተኞች ነን! ስብሰባዎቻችን ላይ ቀደም ብለን እንድንገኝና እስከ መጨረሻው ድረስ እንድንቆይ የሚያደርገን አንዱ ጥሩ ምክንያት አምላክን በመዝሙር ለማወደስ ያለን ፍላጎት ነው። እንዲህ ማድረጋችን ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር በመሆን ይሖዋን በመዝሙርና በጸሎት ለማወደስ ያስችለናል።

“እናንት ሕዝቦች ያህን አወድሱ!”

8. “ሃሌ ሉያ” የሚለው ቃል ምን መልእክት የያዘ ነው? ብዙውን ጊዜስ ምን ተብሎ ይተረጎማል?

8 “ሃሌ ሉያ” የሚለው ከዕብራይስጥ በቀጥታ የተወሰደው ቃል ይሖዋን የማወደስ ሐሳብ የያዘ ሲሆን ብዙውን ጊዜ “ያህን አወድሱ” ተብሎ ይተረጎማል። ለምሳሌ ያህል በመዝሙር 135:​1-3 ላይ “ሃሌ ሉያ። የእግዚአብሔርን [“የይሖዋን፣” NW ] ስም አመስግኑ፤ እናንተ የእግዚአብሔር ባሪያዎች ሆይ፣ አመስግኑት፣ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ፣ በአምላካችን ቤት አደባባይ የምትቆሙ። እግዚአብሔር ቸር ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤ ለስሙ ዘምሩ፣ መልካም ነውና” የሚል ሞቅ ያለ ግብዣ እናገኛለን!

9. ይሖዋን እንድናወድስ የሚገፋፋን ምንድን ነው?

9 አስደናቂ የሆኑትን የአምላክን የፍጥረት ሥራዎችና ለእኛ ጥቅም ሲል ያከናወናቸውን ሥራዎቹን ሁሉ በምናስብበት ጊዜ ከልብ በመነጨ የአድናቆት ስሜት እርሱን ለማወደስ እንገፋፋለን። ይሖዋ በጥንት ጊዜ ለነበሩ ሕዝቦቹ ያደረጋቸውን አስደናቂ ነገሮች በምናስብበት ጊዜ በከፍተኛ ድምፅ እንድናወድሰው ልባችን ይገፋፋናል። ይሖዋ ወደፊት በሚያደርጋቸው ታላላቅ ሥራዎቹ ላይ በምናሰላስልበት ጊዜ ውዳሴያችንንና አመስጋኝነታችንን ለመግለጽ የሚያስችሉ መንገዶችን እንፈልጋለን።

10, 11. በሕይወት መኖር መቻላችን ራሱ አምላክን እንድናወድስ ምክንያት የሚሆነን እንዴት ነው?

10 በሕይወት መኖራችን ራሱ ይሖዋን እንድናወድስ በቂ ምክንያት ይሆነናል። ዳዊት እንዲህ በማለት ዘምሯል:- “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፣ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች።” (መዝሙር 139:​14) አዎን፣ “ግሩምና ድንቅ” ሆነን ተፈጥረናል። እንደ ማየት፣ መስማትና ማሰብ ያሉ አስደናቂ ስጦታዎች አሉን። ታዲያ ሕይወታችንን ለፈጣሪያችን ውዳሴ በሚያመጣ መንገድ መምራት አይገባንምን? ጳውሎስም “የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትሆኑ ወይም ማናቸውን ነገር ብታደርጉ ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” በማለት ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሐሳብ ጽፏል።​—⁠1 ቆሮንቶስ 10:​31

11 ይሖዋን ከልብ የምንወድደው ከሆነ ሁሉን ነገር ለእርሱ ክብር እናደርጋለን። ኢየሱስ የመጀመሪያው ትእዛዝ “በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም አሳብህ በፍጹምም ኃይልህ ጌታ አምላክህን ውደድ” የሚለው እንደሆነ ተናግሯል። (ማርቆስ 12:​30፤ ዘዳግም 6:​5) በእርግጥም ይሖዋ ፈጣሪና ‘የበጎ ስጦታ ሁሉ የፍጹምም በረከት ሁሉ’ ምንጭ እንደመሆኑ መጠን ልንወደውና ልናወድሰው ይገባናል። (ያዕቆብ 1:​17፤ ኢሳይያስ 51:​13፤ ሥራ 17:​28) የማሰብ ችሎታን፣ መንፈሳዊነትን፣ አካላዊ ጥንካሬን፣ በአጠቃላይ ስብዕናችንንና ችሎታዎቻችንን ያገኘነው ከይሖዋ ነው። ፈጣሪያችን እንደመሆኑ መጠን ልንወድደውና ልናወድሰው ይገባናል።

12. ይሖዋ ስላደረጋቸው ታላላቅ ሥራዎችና በመዝሙር 40:​5 ላይ ስላሉት ቃላት ምን ይሰማሃል?

12 ይሖዋ ያደረጋቸው ታላላቅ ሥራዎች እርሱን እንድንወድደውና እንድናወድሰው የሚያደርጉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ምክንያቶችን ይሰጡናል! ዳዊት “አቤቱ አምላኬ፣ ያደረግኸው ተአምራት ብዙ ነው፣ አሳብህንም ምንም የሚመስለው የለም፤ ባወራም ብናገርም ከቍጥር ሁሉ በዛ” በማለት ዘምሯል። (መዝሙር 40:​5) ዳዊት ይሖዋ ያደረጋቸውን ድንቅ ሥራዎች በሙሉ ቆጥሮ መጨረስ አልቻለም፤ እኛም አንችልም። ይሁን እንጂ ድንቅ ሥራዎቹን እንድንገነዘብ የሚያደርጉ ነገሮች በሚያጋጥሙን ጊዜ ሁሉ አምላክን ከማወደስ ወደኋላ ማለት አይገባንም።

ከአምላክ ዘላለማዊ ዓላማ ጋር የተያያዙ ሥራዎች

13. ተስፋችን ከአምላክ ታላላቅ ሥራዎች ጋር በቅርብ የተሳሰረ የሆነው እንዴት ነው?

13 የወደፊቱ ተስፋችን ከአምላክ ዘላለማዊ ዓላማ ጋር ከሚዛመዱት ከአምላክ ታላላቅ ሥራዎች ጋር በቅርብ የተሳሰረ ነው። በኤደን ዓመፅ ከተፈጸመ በኋላ ይሖዋ ተስፋ ያዘለውን የመጀመሪያውን ትንቢት ተናገረ። አምላክ በእባቡ ላይ የፍርድ ውሳኔ ሲበይን እንዲህ አለ:- “በአንተና በሴቲቱ መካከል፣ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ሰኮናውን ትቀጠቅጣለህ።” (ዘፍጥረት 3:​15) ይሖዋ ኖኅንና ቤተሰቡን ክፉውን ዓለም ጠራርጎ ካጠፋው የውኃ መጥለቅለቅ በማዳን ታላቅ ሥራ ካከናወነ በኋላ በነበሩት ጊዜያት ሁሉ የነበሩ የታመኑ ሰዎች የሴቲቱን ዘር በማስመልከት የተሰጠውን ተስፋ ሲጠባበቁ ኖረዋል። (2 ጴጥሮስ 2:​5) እንደ አብርሃምና ዳዊት ላሉ የእምነት ሰዎች የተነገሩት ትንቢታዊ ተስፋዎች ይሖዋ በዚህ ዘር አማካኝነት ስለሚያደርጋቸው ነገሮች ተጨማሪ ማስተዋል ሰጥተዋል።​—⁠ዘፍጥረት 22:​15-18፤ 2 ሳሙኤል 7:​12

14. ይሖዋ ለሰው ዘር ጥቅም ሲል ካደረጋቸው ታላላቅ ሥራዎች ሁሉ የላቀው የትኛው ነው?

14 ይሖዋ ለሰው ዘር ጥቅም ሲል ታላላቅ ሥራዎችን የሚያደርግ አምላክ መሆኑን ያስመሰከረው ከሁሉ የላቀ ድርጊት አንድያ ልጁን ማለትም ተስፋ የተሰጠበትን ዘር ኢየሱስ ክርስቶስን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ ማቅረቡ ነው። (ዮሐንስ 3:​16፤ ሥራ 2:​29-36) ቤዛው ከአምላክ ጋር እርቅ ለመፍጠር የሚያስችል መሠረት ጥሏል። (ማቴዎስ 20:​28፤ ሮሜ 5:​11) ይሖዋ በመጀመሪያ ከእርሱ ጋር የታረቁትን በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት በተቋቋመው ክርስቲያን ጉባኤ አሰባስቧቸዋል። የኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ታዛዥ የሰው ልጆች በአምላክ ሰማያዊ መንግሥት አገዛዝ ሥር ዘላለማዊ በረከቶች እንዲያገኙ በር የከፈተው እንዴት እንደሆነ በመግለጽ መንፈስ ቅዱስ በሚሰጣቸው ኃይል እየታገዙ ምሥራቹን በስፋት አውጀዋል።

15. ይሖዋ በዘመናችን ድንቅ ነገር እያከናወነ ያለው እንዴት ነው?

15 በዘመናችን ይሖዋ የቀሩትን ቅቡዓን ክርስቲያኖች አስደናቂ በሆነ መንገድ ሰብስቧል። ከክርስቶስ ጋር በሰማይ አብረው የሚገዙት ከ144, 000ዎቹ የቀሩት ታትመው እስኪያልቁ ድረስ የጥፋት ነፋሳት ታግደው እንዲቆዩ ተደርጓል። (ራእይ 7:​1-4፤ 20:​6) አምላክ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው “ከታላቂቱ ባቢሎን” መንፈሳዊ ባርነት ነፃ እንዲወጡ አድርጓል። (ራእይ 17:​1-5) በ1919 ያገኙት ይህ ነፃነትና ከዚያ በኋላ ባሉት ጊዜያት የተደረገላቸው መለኮታዊ ጥበቃ ቅቡዓን ቀሪዎች ምን እንዲያደርጉ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል? ይሖዋ የሰይጣንን ክፉ የነገሮች ሥርዓት ከፊታችን እየገሰገሰ በመምጣት ላይ ባለው ‘ታላቅ መከራ’ ከማጥፋቱ በፊት የመጨረሻ ምሥክርነት በመስጠት ብርሃናቸውን እንዲያበሩ አስችሏቸዋል።​—⁠ማቴዎስ 24:​21፤ ዳንኤል 12:​3፤ ራእይ 7:​14

16. በጊዜያችን እየተከናወነ ያለው ዓለም አቀፍ የስብከት ሥራ ምን ውጤት እያስገኘ ነው?

16 ቅቡዓን የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥቱን ስብከት በመላው ዓለም በቅንዓት በማሰራጨቱ ሥራ በግንባር ቀደምትነት በመሥራት ላይ ናቸው። ከዚህም የተነሳ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄድ “ሌሎች በጎች” የይሖዋ አምላኪዎች በመሆን ላይ ናቸው። (ዮሐንስ 10:​16) ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ሁሉ ከእኛ ጋር ሆነው ይሖዋን ማወደስ የሚችሉበት አጋጣሚ አሁንም ክፍት መሆኑ ያስደስተናል። “ና” የሚለውን ግብዣ የተቀበሉ ሁሉ ከታላቁ መከራ ተርፈው ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሖዋን የማወደስ ተስፋ ለመውረስ ዝግጁ ይሆናሉ።​—⁠ራእይ 22:​17

በሺህዎች የሚቆጠሩ ወደ እውነተኛው አምልኮ እየጎረፉ ነው

17. (ሀ) ይሖዋ ከስብከት እንቅስቃሴያችን ጋር በተያያዘ ታላላቅ ሥራዎች እያከናወነ ያለው እንዴት ነው? (ለ) ዘካርያስ 8:​23 ፍጻሜውን እያገኘ ያለው እንዴት ነው?

17 ይሖዋ ከምናከናውነው የስብከት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ እርሱን እንድናወድስ የሚያደርጉ ታላላቅ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ነው። (ማርቆስ 13:​10) ከቅርብ ዓመታት ወዲህ “ሥራ የሞላበት ትልቅ በር” እንዲከፈት አድርጓል። (1 ቆሮንቶስ 16:​9) ይህም ምሥራቹ ከዚህ ቀደም በእውነት ጠላቶች ታግዶ በቆየባቸው ሰፋፊ የአገልግሎት ክልሎች እንዲሰበክ አስችሏል። በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ በርካታ ሰዎች አሁን ይሖዋን እንዲያመልኩ የቀረበላቸውን ግብዣ በመቀበል ላይ ናቸው። የሚከተሉትን ትንቢታዊ ቃላት በመፈጸም ላይ ናቸው:- “የሠራዊትም ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- በዚያ ዘመን ከአሕዛብ ቋንቋ ሁሉ አሥር ሰዎች የአንዱን አይሁዳዊ ሰው ልብስ ዘርፍ ይዘው:- እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና ከእናንተ ጋር እንሂድ ይላሉ።” (ዘካርያስ 8:​23) እዚህ ላይ ‘አምላክ ከእነርሱ ጋር እንዳለ’ የተነገረላቸው ሰዎች በአሁኑ ጊዜ ያሉት መንፈሳዊ አይሁዳውያን ማለትም ክርስቲያን ቅቡዓን ቀሪዎች ናቸው። አሥር ቁጥር ከምድር ጋር በተያያዘ ሙላትን የሚያመለክት በመሆኑ ‘አሥሩ ሰዎች’ “ከአምላክ እስራኤል” ጋር እንዲተባበሩ የተሰበሰቡትንና “አንድ መንጋ” የሆኑትን “እጅግ ብዙ ሰዎች” ያመለክታሉ። (ራእይ 7:​9, 10፤ ገላትያ 6:​16) በአሁኑ ጊዜ ይሖዋ አምላክን የሚያመልኩ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች አንድ ላይ ሆነው ቅዱስ አገልግሎት ሲያቀርቡ መመልከት ምንኛ የሚያስደስት ነው!

18, 19. ይሖዋ የስብከቱን ሥራ እየባረከው እንዳለ የሚያረጋግጥ ምን ማስረጃ አለ?

18 የሃሰት ሃይማኖት በተንሰራፋባቸው አገሮች የመንግሥቱን ምሥራች ፈጽሞ ሊቀበሉ የማይችሉ ይመስሉ የነበሩ በአሥር አዎን፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች እውነተኛውን አምልኮ ሲቀበሉ በማየታችን ደስ ይለናል። እስቲ በቅርብ የወጣ የዓመት መጽሐፍ ገለጥ አድርጉና ከ100, 000 እስከ 1, 000, 000 የሚጠጋ የመንግሥቱ አስፋፊዎች እንደነበሯቸው ሪፖርት ያደረጉ አገሮችን ተመልከቱ። ይህ ይሖዋ የመንግሥቱን የስብከት ሥራ እየባረከው እንዳለ የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ ነው!​—⁠ምሳሌ 10:​22

19 የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን እውነተኛ የሕይወት ዓላማ እንዲኖረን፣ በአገልግሎቱ አርኪ ሥራ እንድናከናውንና የወደፊቱ ጊዜ ብሩህ እንዲሆንልን ስላደረገ ሰማያዊ አባታችንን እናወድሰዋለን እንዲሁም እናመሰግነዋለን። መለኮታዊ ተስፋዎች በጠቅላላ ፍጻሜያቸውን የሚያገኙበትን ጊዜና ‘የዘላለምን ሕይወት’ በጉጉት እየተጠባበቅን ‘በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችንን ለመጠበቅ’ ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። (ይሁዳ 20, 21) አምላክን የሚያወድሰው የእጅግ ብዙ ሰዎች ቁጥር 6, 000, 000 መድረሱ ምንኛ የሚያስደስት ነው! ይሖዋ በሚሰጠው በረከት ቅቡዓን ቀሪዎች ጓደኞቻቸው ከሆኑት ከሌሎች በጎች ጋር ሆነው በ235 አገሮች በሚገኙ 91, 000 ጉባኤዎች ተደራጅተዋል። “ታማኝና ልባም ባሪያ” ያለመታከት በሚያደርገው ጥረት አማካኝነት ሁላችንም በመንፈሳዊ በደንብ እየተመገብን ነው። (ማቴዎስ 24:​45) እያደገ በመሄድ ላይ ያለው ቲኦክራሲያዊ ድርጅት 110 በሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮዎች አማካኝነት የመንግሥቱን እንቅስቃሴዎች ፍቅራዊ በሆነ መንገድ በመምራት ላይ ይገኛል። ይሖዋ ‘በሃብታቸው እንዲያከብሩት’ የሕዝቡን ልብ በማነሳሳቱ አመስጋኞች ነን። (ምሳሌ 3:​9, 10) ይህም ዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ መከናወኑን እንዲቀጥል በዓለም ዙሪያ የማተሚያ ሕንፃዎች፣ የቤቴልና የሚስዮናውያን ቤቶች፣ የመንግሥት አዳራሾችና የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾች አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ እንዲገነቡ አስችሏል።

20. ይሖዋ ባከናወናቸው ታላላቅና ድንቅ ሥራዎች ላይ ማሰላሰላችን እንዴት ሊነካን ይገባል?

20 ሰማያዊ አባታችንን እንድናወድስ ምክንያት የሚሆኑንን ድንቅ ነገሮች በሙሉ ዘርዝረን መጨረስ አንችልም። ይሁን እንጂ ከፍ ባለ ድምፅ ለይሖዋ ውዳሴ ከሚያሰሙት ቅን ልብ ካላቸው ሰዎች ጋር ከመተባበር ወደኋላ የሚል ይኖራልን? ፈጽሞ ሊኖር አይችልም! ስለዚህ አምላክን የሚወድዱ ሁሉ የሚከተለውን በማለት በደስታ ይዘምሩ:- “ሃሌ ሉያ። እግዚአብሔርን ከሰማያት አመስግኑት፤ በአርያም አመስግኑት። መላእክቱ ሁሉ፣ አመስግኑት፤ . . . ጕልማሶችና ቈነጃጅቶች፣ ሽማግሌዎችና ልጆች፤ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑ፤ ስሙ ብቻውን ከፍ ከፍ ብሎአልና፣ ምስጋናውም በሰማይና በምድር ላይ ነው።” (መዝሙር 148:​1, 2, 12, 13) አዎን፣ ላደረጋቸው ታላላቅ ሥራዎች ሁሉ ይሖዋን አሁንና ለዘላለም እናወድስ!

እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?

• አንዳንድ የይሖዋ ድንቅ ሥራዎች ምንድን ናቸው?

• ይሖዋን ለማወደስ የምትገፋፋው ለምንድን ነው?

• ተስፋችን ከአምላክ ታላላቅ ሥራዎች ጋር የተያያዘው እንዴት ነው?

• ይሖዋ ከመንግሥቱ የስብከት ሥራ ጋር በተያያዘ ድንቅ ሥራዎችን እያከናወነ ያለው እንዴት ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለይሖዋ በሚቀርቡ የውዳሴ መዝሙሮች በሙሉ ልብህ ትካፈላለህ?

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ልበ ቅን የሆኑ ሰዎች ከእኛ ጋር ሆነው ይሖዋን እንዲያወድሱ የሚቀርበው ግብዣ አሁንም በመቀጠሉ ደስተኞች ነን