በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲኖር የፈቀደበት ጊዜ ማብቂያው ተቃርቧል

አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲኖር የፈቀደበት ጊዜ ማብቂያው ተቃርቧል

አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲኖር የፈቀደበት ጊዜ ማብቂያው ተቃርቧል

የትም ቦታ ብትሄድ ሥቃይና መከራ አለ። አንዳንድ ሰዎች በራሳቸው ላይ ሥቃይና መከራ ያመጣሉ። በፆታ ግንኙነት በሚተላለፍ በሽታ ይያዛሉ አሊያም አደገኛ ዕፅ መውሰድ ወይም የአልኮል መጠጦችን አላግባብ መጠጣት ወይም ማጨስ የሚያስከትሏቸው መጥፎ ውጤቶች ተጠቂ ይሆናሉ። ወይም ደግሞ ደካማ ከሆነ የአመጋገብ ልማድ የተነሳ የጤና ችግር ይገጥማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ከፍተኛ መከራ የሚደርሰው እንደ ጦርነት፣ የጎሳ ግጭት፣ ወንጀል፣ ድህነት፣ ረሀብ፣ በሽታ ባሉ ከአንድ ሰው አቅም በላይ በሆኑ ነገሮች ወይም ክስተቶች የተነሳ ነው። ሰዎች ፈጽሞ ሊቆጣጠሩት የማይችሉት ሌላው ነገር ደግሞ ከእርጅናና ከሞት ጋር ተያይዞ የሚመጣው ሥቃይና መከራ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ፍቅር ነው” በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል። (1 ዮሐንስ 4:​8) ታዲያ አፍቃሪ የሆነ አምላክ ይህን ለሚያህል ዘመን ሥቃይና መከራ እንዲቀጥል የፈቀደው ለምንድን ነው? ሁኔታውን የሚያስተካክለው መቼ ነው? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት አምላክ ከሰው ልጆች ጋር በተያያዘ የነበረውን ዓላማ መመርመር ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን አምላክ መከራ እንዲኖር የፈቀደበትን ምክንያትና በዚህ ረገድ ምን እንደሚያደርግ ለማወቅ ይረዳናል።

ነፃ ምርጫ የማድረግ ስጦታ

አምላክ የመጀመሪያውን ሰው ሲፈጥር አእምሮ ያለው አካል ከመሥራት የበለጠ ነገር አከናውኗል። በተጨማሪም አምላክ አዳምና ሔዋንን ማሰብ የማይችሉ ሮቦቶች አድርጎ አልፈጠራቸውም። በውስጣቸው ነፃ ምርጫ የማድረግ ችሎታ ሰጥቷቸው ነበር። ይህ ደግሞ መልካም ስጦታ ነበር፤ ምክንያቱም “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፣ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ።” (ዘፍጥረት 1:​31) አዎን፣ ‘ሥራው ፍጹም ነው።’ (ዘዳግም 32:​4) በማንኛውም ነገር ምንም ምርጫ ሳይኖረን መላው አስተሳሰባችንና ድርጊታችን በሌላ ሰው እንዲመራ ስለማንፈልግ ሁላችንም ይህን ነፃ ምርጫ የማድረግ ስጦታ ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን።

ይሁን እንጂ ይህን ነፃ ምርጫ የማድረግ ግሩም ስጦታ ያለ ገደብ ልንጠቀምበት እንችላለን? ለመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች በተሰጠው መመሪያ ላይ የአምላክ ቃል እንዲህ የሚል መልስ ይሰጣል:- “አርነት ወጥታችሁ እንደ እግዚአብሔር ባሪያዎች ሁኑ እንጂ ያ አርነት ለክፋት መሸፈኛ እንዲሆን አታድርጉ።” (1 ጴጥሮስ 2:​16) ለሁሉም ጥቅም ሲባል ገደብ ሊኖር ይገባል። በዚህ ምክንያት ነፃ ምርጫ በሕግ መመራት ይኖርበታል። ይህ ካልሆነ ግን ሥርዓት አልበኝነት ይንሰራፋል።

ማን ያወጣው ሕግ?

ለነፃነት ተገቢውን ገደብ የሚወስነው ማን ያወጣው ሕግ ነው? ለዚህ ጥያቄ የሚሰጠው መልስ አምላክ መከራ እንዲኖር ከፈቀደበት መሠረታዊ ምክንያት ጋር ዝምድና አለው። ሰዎችን የፈጠረው አምላክ እንደመሆኑ መጠን ለራ​ሳቸውም ሆነ ለሌሎች ጥቅም የትኞቹን ሕጎች ማክበር እንዳለባቸው ከማንም በተሻለ ያውቃል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በተመለከተ እንዲህ ይላል:- “እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ።”​—⁠ኢሳይያስ 48:​17

በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ዋናው ነጥብ የሰው ልጅ ከአምላክ አገዛዝ ውጪ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ተደርጎ አልተፈጠረም። ስኬትም ሆነ ደስታ ማግኘታቸው የተመካው የጽድቅ ሕጎቹን በመታዘዛቸው ላይ ነው። የአምላክ ነቢይ ኤርምያስ እንዲህ ብሏል:- “አቤቱ፣ የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም።”​—⁠ኤርምያስ 10:​23

አምላክ የሰው ልጆችን የፈጠረው እንደ ስበት ሕግ ላሉ የተፈጥሮ ሕጎቹ እንዲገዙ አድርጎ ነው። በተመሳሳይም ሰዎችን የፈጠረው ስምምነት ያለው ሕብረተሰብ ለማስገኘት ተብሎ የወጡትን የሥነ ምግባር ሕጎቹን እንዲታዘዙ አድርጎ ነው። በመሆኑም የአምላክ ቃል እንዲህ ሲል የሚያሳስበን አለምክንያት አይደለም:- “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ።”​—⁠ምሳሌ 3:​5

በመሆኑም ሰብዓዊው ቤተሰብ ከአምላክ አገዛዝ ውጪ ራሱን በራሱ ለመምራት የሚያደርገው ጥረት ፈጽሞ ሊሳካለት አይችልም። ሰዎች ከአምላክ አገ​ዛዝ ነፃ ሆነው ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር ያደረጉት ጥረት ሁሉ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች እንዲፈጠሩ አድርገዋል፤ እንዲሁም ‘ሰው ሰውን ለመጉዳት ገዢ ሆኖበታል።’​—⁠መክብብ 8:​9

ስህተቱ ምን ላይ ነው?

አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ለአዳምና ለሔዋን ፍጹም ጅምር አድርጎላቸው ነበር። ፍጹም አካልና አእምሮ እንዲሁም የሚኖሩበት በአትክልት የተሞላ ገነት ነበራቸው። ራሳቸውን ለአምላክ አገዛዝ አስገዝተው ቢሆን ኖሮ ፍጹምና ደስተኛ ሆነው ይኖሩ ነበር። ከጊዜ በኋላ ገነት በሆነች ምድር ላይ የሚኖር ፍጹምና ደስተኛ የሆነ የመላው የሰው ዘር ቤተሰብ ወላጆች ይሆኑ ነበር። ይህ ደግሞ አምላክ ለሰው ዘር ያወጣው ዓላማ ነበር።​—⁠ዘፍጥረት 1:​27-29፤ 2:​15

ይሁን እንጂ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ነፃ ምርጫቸውን አላግባብ ተጠቀሙበት። ከአምላክ አገዛዝ ውጪ ራሳቸውን በራሳቸው ቢያስተዳድሩ ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ በተሳሳተ መንገድ አሰቡ። በራሳቸው ነፃ ምርጫ አምላክ ያወጣውን የሕግ ድንበር ጣሱ። (ዘፍጥረት ምዕራፍ 3) የእሱን አገዛዝ ስለ ናቁ እነሱን በፍጽምና የማኖር ግዴታ አልነበረበትም። “እነርሱ ረከሱ፤ ልጆቹም አይደሉም፤ ነውርም አለባቸው።”​—⁠ዘዳግም 32:​5

አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ካመፁበት ጊዜ አንስቶ በአካልም ሆነ በአእምሮ እየደከሙ መጡ። ይሖዋ የሕይወት ምንጭ ነው። (መዝሙር 36:​9) ራሳቸውን ከይሖዋ በመለየታቸው ምክንያት የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ፍጽምናቸውን አጡ፤ በመጨረሻም ሞቱ። (ዘፍጥረት 3:​19) ከባሕርይ ውርስ ሕግ ጋር በሚስማማ መንገድ ዝርያዎቻቸው መውረስ የሚችሉት ወላጆቻቸው ያላቸውን ነገር ብቻ ነው። ታዲያ የወረሱት ነገር ምንድን ነው? አለፍጽምናና ሞት ነበር። ከዚህ የተነሳ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ኃጢአት በአንድ ሰው [በአዳም] ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፣ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ።”​—⁠ሮሜ 5:​12

ዐቢይ ጉዳይ የሆነው የሉዓላዊነት ጥያቄ

አዳምና ሔዋን በአምላክ ላይ ባመፁ ጊዜ ሉዓላዊነቱን ማለትም የመግዛት መብቱን ተገዳደሩ። ይሖዋ እነሱን አጥፍቶ ሌላ ባልና ሚስት በመፍጠር ሁኔታውን እንደገና በአዲስ መልክ ማስጀመር ይችል ነበር። ሆኖም እንዲህ ማድረጉ ትክክል የሆነውና ለሰዎች የሚጠቅመው የማን አገዛዝ ነው ለሚለው ጥያቄ መልስ አያስገኝም። የሰው ልጆች በራሳቸው አስተሳሰብ የፈለጉትን ማኅበረሰብ ማቋቋም እንዲችሉ ጊዜ ቢፈቀድላቸው ከአምላክ የራቀ አገዛዝ ስኬታማ ስለመሆኑ ተጨባጭ በሆነ መንገድ ማረጋገጫ ሊያስገኝላቸው ይችላል።

በርካታ ሺህ ዓመታት ያስቆጠረው የሰው ልጅ ታሪክ ምን አስገንዝቦናል? በእነዚህ ሁሉ መቶ ዘመናት ሰዎች ብዙ ዓይነት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶችን ሞክረዋል። ይሁን እንጂ ክፋትና መከራ አልተወገደም። እንዲያውም በተለይ በእኛ ዘመን ‘ክፉዎች በክፋት እየባሱ ሄደዋል።’​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​13

በ20ኛው መቶ ዓመት በሳይንሳዊና በኢንዱስትሪ ግኝቶች ረገድ ከፍተኛ የእድገት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ሆኖም በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ መጠን እጅግ አስከፊ የሆነ መከራ የደረሰበት ዘመንም ነበር። በሕክምናው መስክ ምንም ዓይነት እድገት ቢደረግ የአምላክ ሕግ አሁንም ይሠራል:- የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከአምላክ የራቁት የሰው ልጆች ይታመማሉ፣ ያረጃሉ እንዲሁም ይሞታሉ። ሰዎች ‘አካሄዳቸውን ማቅናት’ እንደማይችሉ የሚያሳይ እንዴት ያለ ግልጽ ማስረጃ ነው!

የአምላክ ሉዓላዊነት ተረጋገጠ

ይህ ከአምላክ አገዛዝ ውጪ ራስን በራስ ለማስተዳደር የተደረገ አሳዛኝ ሙከራ የሰው ልጅ ከአምላክ ርቆ ያቋቋመው አገዛዝ ፈጽሞ ሊሳካ እንደማይችል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አረጋግጧል። ደስታ፣ አንድነት፣ ጤንነትና ሕይወት ማስገኘት የሚችለው የአምላክ አገዛዝ ብቻ ነው። በተጨማሪም መሬት ጠብ የማይለው የይሖዋ አምላክ ቃል ማለትም መጽሐፍ ቅዱስ ከአምላክ ርቆ ራሱን በራሱ በሚያስተዳድረው የሰው ልጅ አገዛዝ “በመጨረሻው ቀን” ውስጥ እንደምንኖር ያሳያል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1-5) ይሖዋ የሰው አገዛዝ እንዲሁም ክፋትና መከራ እንዲኖር የፈቀደበት ጊዜ ማብቂያው ተቃርቧል።

አምላክ በቅርቡ በሰው ልጆች ጉዳይ ጣልቃ ይገባል። ቅዱሳን ጽሑፎች እንዲህ ይላሉ:- “በእነዚያም ነገሥታት [አሁን ባለው ሰብዓዊ አገዛዝ] ዘመን የሰማይ አምላክ ለዘላለም የማይፈርስ መንግሥት [በሰማይ] ያስነሣል፤ ለሌላ ሕዝብም የማይሰጥ መንግሥት ይሆናል [ሰዎች ዳግመኛ ምድርን እንዲገዙ ፈጽሞ አይፈቀድላቸውም]፤ እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ [አሁን ያሉትን አገዛዞች] ትፈጫቸዋለች ታጠፋቸውማለች፣ ለዘላለምም ትቆማለች።”​—⁠ዳንኤል 2:​44

የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ በሰማያዊ መንግሥቱ አማካኝነት የይሖዋ አምላክ ሉዓላዊነት መረጋገጥ ነው። ኢየሱስ ይህን ጭብጥ የትምህርቱ ዐቢይ ክፍል አድርጎታል። እንዲህ ብሏል:- “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።”​—⁠ማቴዎስ 24:​14

የአምላክ አገዛዝ የሰውን አገዛዝ ሲተካ በሕይወት የሚተርፉትና የማይተርፉት እነማን ናቸው? በምሳሌ 2:​21, 22 ላይ እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ተሰጥቶናል:- “ቅኖች [የአምላክን አገዛዝ የሚደግፉ] በምድር ላይ ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና፤ ኀጥኣን [የአምላክን አገዛዝ የሚቃወሙ] ግን ከምድር ይጠፋሉ።” መዝሙራዊ በመለኮታዊ መንፈስ አነሳሽነት እንዲህ ሲል ዘምሯል:- “ገና ጥቂት፣ ኃጢአተኛም አይኖርም . . . ገሮች ግን ምድርን ይወርሳሉ፣ በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል። ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፣ በእርስዋም ለዘላለም ይኖራሉ።”​—⁠መዝሙር 37:​10, 11, 29

አስደናቂ የሆነ አዲስ ዓለም

የአሁኑ የነገሮች ሥርዓት ሲያከትም በሕይወት የሚተርፉ ሰዎች በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ከክፋትና ከመከራ በጸዳች ምድር ላይ ይኖራሉ። ከአምላክ የሚመጣ መመሪያ ለሰው ልጅ በሙሉ ይዳረሳል፤ ከጊዜ በኋላ “ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለች።” (ኢሳይያስ 11:​9) ይህ በሥነ ምግባር የሚያንጽና ገንቢ የሆነ ትምህርት እውነተኛ ሰላምና ስምምነት የሰፈነበት ሰብዓዊ ሕብረተሰብ ያስገኛል። በመሆኑም ጦርነት፣ ግድያ፣ ዓመፅ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ስርቆት ወይም ሌላ ማንኛውም ዓይነት ወንጀል አይኖርም።

በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ታዛዥ ሰዎች አስደናቂ የሆነ አካላዊ ጥቅሞችን ያገኛሉ። በአምላክ አገዛዝ ላይ የተፈጸመው ዓመፅ ያስከተላቸው አስከፊ መዘዞች በሙሉ ይወገዳሉ። አለፍጽምና፣ በሽታ፣ እርጅናና ሞት የተረሱ ነገሮች ይሆናሉ። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል:- “በዚያም የሚቀመጥ:- ታምሜአለሁ አይልም።” በተጨማሪም ቅዱሳን ጽሑፎች እንዲህ የሚል ተስፋ ይሰጣሉ:- “በዚያን ጊዜም የዕውሮች ዓይን ይገለጣል የደንቆሮችም ጆሮ ይከፈታል። በዚያን ጊዜ አንካሳ እንደ ሚዳቋ ይዘልላል፣ የድዳም ምላስ ይዘምራል።” (ኢሳይያስ 33:​24፤ 35:​5, 6) በየቀኑ፣ ለዘላለም የተሟላ ጤንነት አግኝቶ መኖር ምንኛ ያስደስታል!

በአምላክ ፍቅራዊ አመራር ሥር የዚህ አዲስ ዓለም ነዋሪዎች ምድር አቀፍ ገነት ለመገንባት ጉልበታቸውንና ችሎታቸውን ይጠቀማሉ። ድህነት፣ ረሃብና የቤት ዕጦት ለዘላለም ይወገዳሉ። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ተንብዮአል:- “ቤቶችንም ይሠራሉ ይቀመጡባቸውማል፤ ወይኑንም ይተክላሉ ፍሬውንም ይበላሉ። ሌላ እንዲቀመጥበት አይሠሩም፣ ሌላም እንዲበላው አይተክሉም።” (ኢሳይያስ 65:​21, 22) በእርግጥም “እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም።”​—⁠ሚክያስ 4:​4

ምድር አምላክና ታዛዥ የሰው ልጆች ለሚያደርጉላት ፍቅራዊ እንክብካቤ ምላሽ ትሰጣለች። ቀጥሎ ያሉት ቅዱስ ጽሑፋዊ ማረጋገጫዎች አሉልን:- “ምድረ በዳውና ደረቁ ምድር ደስ ይላቸዋል፣ በረሀውም ሐሤት ያደርጋል እንደ ጽጌ ረዳም ያብባል። . . . በምድረ በዳ ውኃ፣ በበረሀም ፈሳሽ ይፈልቃልና።” (ኢሳይያስ 35:​1, 6) “በምድሩ ላይ በቂ እህል ይኑር፤ ተራራዎች በሰብል ይሸፈኑ።”​—⁠መዝሙር 72:​16 የ1980 ትርጉም

በቢልዮን የሚቆጠሩ የሞቱ ሰዎችስ ምን ተስፋ አላቸው? ‘ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን ስለሚነሡ’ በአምላክ ዝክር ውስጥ ያሉ ሁሉ እንደገና በሕይወት ይኖራሉ። (ሥራ 24:​15) አዎን፣ ሙታን ወደ ሕይወት ይመለሳሉ። የአምላክን አገዛዝ በተመለከተ አስደናቂ እውነቶችን የሚማሩ ሲሆን በገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚም ይሰጣቸዋል።​—⁠ዮሐንስ 5:​28, 29

በዚህ መንገድ ይሖዋ አምላክ የሰው ልጆችን ለበርካታ ሺህ ዓመታት አንቆ የያዘውን ሥቃይ፣ በሽታና ሞት ያለበትን አስከፊ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ይለውጠዋል። በሽታ፣ የአካል ጉዳተኝነትና ሞት አይኖርም! አምላክ “እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።”​—⁠ራእይ 21:​3, 4

በዚህ መንገድ አምላክ ስቃይንና መከራን ያስወግዳል። ይህን ብልሹ ዓለም አስወግዶ ‘ጽድቅ የሚኖርበትን’ ሙሉ በሙሉ አዲስ የነገሮች ሥርዓት ያመጣል። (2 ጴጥሮስ 3:​13) ይህ እንዴት ያለ ምሥራች ነው! ይህ አዲስ ዓለም በቶሎ እንዲመጣ ፍላጎታችን ነው። ደግሞም አዲሱን ዓለም ለማግኘት ረጅም ጊዜ መጠበቅ አያስፈልገንም። ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ አንጻር አዲሱ ዓለም ደፍ ላይ መሆኑን እናውቃለን፤ እንዲያውም አምላክ ሥቃይና መከራ እንዲኖር የፈቀደበት ጊዜ ማብቂያው ተቃርቧል።​—⁠ማቴዎስ 24:​3-14

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሰብዓዊ አገዛዝ የደረሰበት ውድቀት

የቀድሞው የጀርመን ቻንስለር ሔልሙት ሽሚት የሰውን አገዛዝ በተመለከተ እንዲህ ብለዋል:- “እኛ ሰዎች . . . ምድርን ሙሉ በሙሉ ያስተዳደርንበት ጊዜ የለም። እንደዚያም ሆኖ አብዛኛው አገዛዛችን መጥፎ ነው። . . . የተሟላ ሰላም በሰፈነበት ሁኔታ ዓለምን አስተዳድረን አናውቅም።” ሂውማን ዴቨሎፕመንት ሪፖርት 1999 እንዲህ ብሏል:- “ሁሉም አገሮች በሕዝባዊ ዓመፅ፣ እየጨመረ በሚሄድ ወንጀልና ቤት ውስጥ በሚፈጸም ግፍ ሳቢያ ማኅበራዊ መዋቅራቸው እየተሸረሸረ መሆኑን ሪፖርት አድርገዋል። . . . በዓለማችን ላይ ያሉት ስጋት የሚፈጥሩ ችግሮች አገራት ችግሮቹን ለመቅረፍ ካላቸው አቅምና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከሚሰጠው ምላሽ በላይ በፍጥነት በማደግ ላይ ናቸው።”

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።”​—⁠መዝሙር 37:​11

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከላይ ሦስተኛው፣ እናትና ልጅ:- FAO photo/B. Imevbore; ከታች፣ ፍንዳታ:- U.S. National Archives photo