በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሰው ልጆች መከራና ሥቃይ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?

የሰው ልጆች መከራና ሥቃይ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?

የሰው ልጆች መከራና ሥቃይ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው?

“አምላክ ሆይ፣ ለምን ዝም ብለህ ታያለህ?” በትንሿ እስያ አውዳሚ የመሬት መንቀጥቀጥ ከደረሰ በኋላ ይህ በትልቁ የተጻፈ ርዕሰ ዜና ሰፊ ስርጭት ባለው በአንድ ጋዜጣ ፊተኛ ገጽ ላይ ወጥቶ ነበር። ርዕሱ በጭንቀት የተዋጡ አንድ አባት ከፈራረሰው ቤታቸው ውስጥ ጉዳት የደረሰባት ልጃቸውን አቅፈው ሲያወጡ በሚያሳይ ፎቶግራፍ የተደገፈ ነው።

ጦርነት፣ ረሀብ፣ ወረርሽኝና የተፈጥሮ አደጋዎች ከፍተኛ ሥቃይ እንዲደርስ፣ እንባ እንደ ጎርፍ እንዲፈስና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎች እንዲሞቱ ምክንያት ሆነዋል። ከዚህም በላይ ምን ያህል ሰዎች ተገደው እንደሚደፈሩ፣ በልጅነታቸው እንደሚነወሩና ሌሎች ወንጀሎች እንደሚፈጸምባቸው፣ በዚህም ሳቢያ የሚደርስባቸውን መከራ አስብ። በአደጋዎች ሳቢያ የሚከሰተውን ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአካል ጉዳትና ሞትም አስብ። እንዲሁም በበሽታ፣ በእርጅናና የሚወዱትን ሰው በሞት በማጣት ምክንያት በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከባድ መከራ ይደርስባቸዋል።

በ20ኛው መቶ ዘመን ከሁሉ የከፋ መከራ ደርሷል። ከ1914 እስከ 1918 የተካሄደው አንደኛው የዓለም ጦርነት ወደ አሥር ሚልዮን የሚጠጉ ወታደሮችን ፈጅቷል። አንዳንድ የታሪክ ምሁራን ጦርነቱ ከዚያ የማይተናነሱ ሲቪሎችን ለሞት እንደዳረገ ይናገራሉ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት፣ ራሳቸውን መከላከል የማይችሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሴቶችን፣ ልጆችንና አረጋውያን ወንዶችን ጨምሮ 50 ሚልዮን የሚያክሉ ወታደሮችና ሲቪሎች ተገድለዋል። ባለፈው መቶ ዓመት በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የዘር ማጥፋት፣ የአብዮታዊ ንቅናቄ፣ የጎሳ ግጭት፣ የረሀብና የድህነት ሰለባ ሆነዋል። ሂስቶሪካል አትላስ ኦቭ ዘ ትዌንቲዝ ሴንቸሪ የተባለው መጽሐፍ እንደዚህ ያለው “ሕዝባዊ ብጥብጥ” ከ180 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎችን ሕይወት እንደቀጠፈ ይገምታል።

በ1918/19 የተከሰተው የኅዳር በሽታ 20 ሚልዮን ሰዎች ገድሏል። ባለፉት ሁለት አሥርተ ዓመታት 19 ሚልዮን የሚሆኑ ሰዎች በኤድስ የሞቱ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ወደ 35 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች የበሽታው መንስዔ በሆነው ቫይረስ ተይዘዋል። በኤድስ ሳቢያ ወላጆቻቸው የሞቱባቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ልጆች ያለ ወላጅ ቀርተዋል። እንዲሁም ገና በማኅፀን ሳሉ በሽታው የተጋባባቸው ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ሕፃናት በኤድስ ሳቢያ እያለቁ ነው።

ልጆች በሌሎች መንገዶችም ተጨማሪ መከራና ሥቃይ ይደርስባቸዋል። በ1995 ማብቂያ ላይ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) ያቀረበውን መረጃ በመጥቀስ በእንግሊዝ የሚታተመው ማንቸስተር ጋርዲያን ዊክሊ እንዲህ ብሏል:- “ባለፈው አሥርተ ዓመት በተካሄዱት ጦርነቶች 2 ሚልዮን ልጆች ተገድለዋል፣ ከ4-5 ሚልዮን በአካላቸው ላይ ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ 12 ሚልዮን የሚያክሉ ያለ መጠለያ ቀርተዋል፣ ከ1 ሚልዮን በላይ የሚሆኑ ወላጆቻቸውን በሞት አጥተዋል አሊያም ከወላጆቻቸው ተለያይተዋል፣ 10 ሚልዮን የሚያክሉ ደግሞ ሥነ ልቦናዊ ቀውስ ደርሶባቸዋል።” ከዚህ በተጨማሪ በየዓመቱ በዓለም ዙሪያ የሚፈጸመውን በግምት ከ40 እስከ 50 ሚልዮን የሚደርሰውን ፅንስ የማስወረድ ድርጊት አስብ!

የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዟል?

ብዙዎች የወደፊቱን ጊዜ በፍርሃት ይመለከቱታል። አንድ የሳይንቲስቶች ቡድን እንዲህ ብሏል:- “የሰው ልጅ የሚያደርጋቸው እንቅስቃሴዎች . . . ሕያው በሆነው ዓለም ላይ እጅግ ከፍተኛ ለውጥ ከማስከተሉ የተነሳ ዛሬ የምናውቀው ዓለም ሕይወትን ጠብቆ ማቆየት ይሳነዋል።” ቡድኑ በማከል እንዲህ ብሏል:- “በአሁኑ ጊዜ እንኳ ከአምስት ሰዎች አንዱ በቂ ምግብ ባለማግኘት በከፍተኛ ድህነት የሚማቅቅ ሲሆን ከአሥር ሰዎች አንዱ ደግሞ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ይሠቃያል።” ሳይቲስቶቹ አጋጣሚውን በመጠቀም “ከፊታችን ስለተደቀነብን ነገር የሰውን ዘር ባጠቃላይ ካስጠነቀቁ” በኋላ “በሰው ልጅ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ከፍተኛ መከራ ለማስቀረትና ዓለም አቀፍ መኖሪያችን የሆነችው ይህች ፕላኔት ልትጠገን በማትችል ሁኔታ ከመበላሸቷ በፊት ለምድርና በላይዋ ላይ ላለው ሕይወት በምናደርገው አያያዝ ረገድ ከፍተኛ ለውጥ ማድረግ ይጠበቅብናል” ብለዋል።

አምላክ ይህን የሚያህል መከራና ክፋት እንዲኖር የፈቀደው ለምንድን ነው? ሁኔታውን ለማስተካከል ምን ዓላማ አለው? የሚያስተካክለውስ መቼ ነው?

[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

ከላይ፣ ተሽከርካሪ ወንበር:- UN/DPI Photo 186410C by P.S. Sudhakaran; መሀከል፣ በረሀብ የተጠቁ ልጆች:- WHO/OXFAM; ከታች፣ የመነመነ ሰው:- FAO photo/B. Imevbore