በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልቤ በሃዘን ቢሰበርም ደስተኛና አመስጋኝ ነኝ

ልቤ በሃዘን ቢሰበርም ደስተኛና አመስጋኝ ነኝ

የሕይወት ታሪክ

ልቤ በሃዘን ቢሰበርም ደስተኛና አመስጋኝ ነኝ

ናንሲ ኢ ፖርተር እንደተናገረችው

ጊዜው ሰኔ 5, 1947 ሲሆን ከዩናይትድ ስቴትስ ደቡባዊ ምሥራቅ ጠረፍ ራቅ ብለው በሚገኙት የባሃማስ ደሴቶች ሞቅ ያለ ምሽት ነበር። አንድ የኢሚግሬሽን ባለሥልጣን እኔና ባለቤቴ ዘንድ በመምጣት የእኛ በደሴቲቱ ላይ መቆየት እንደማይፈለግ የሚገልጽና “በፍጥነት ደሴቲቱን ለቅቀን” እንድንሄድ የሚያዝዝ ደብዳቤ ሰጥቶን ሄደ።

እኔና ባለቤቴ ጆርጅ የባሃማስ ደሴቶች ትልቅ ከተማ ወደሆነችው ናሶ ለመምጣት የመጀመሪያዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች ሚስዮናውያን ነበርን። በሰሜናዊ ኒው ዮርክ ከሚገኘው ከጊልያድ የሚስዮናውያን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ስምንተኛ ክፍል ከተመረቅን በኋላ በባሃማስ ደሴቶች እንድናገለግል ተመደብን። ታዲያ ገና በሦስት ወራችን እንዲህ ያለ ጠንካራ እርምጃ ሊወሰድብን የቻለው ለምንድን ነው? ከ50 ዓመት በኋላስ እዚህ ልገኝ የቻልኩት እንዴት ነው?

የአገልግሎት ሥልጠና

አባቴ ሃሪ ኪልነር በሕይወቴ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል። የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ብዙ መሥዋዕትነቶችን በመክፈሉ ለእኔ በጣም ግሩም ምሳሌ ሆኖልኛል። ጥሩ ጤንነት ባይኖረውም እንኳ በቅንዓት የመንግሥቱን ፍላጎቶች በማስቀደም ሁልጊዜ ለማለት ይቻላል በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት ለመስበክ ይወጣ ነበር። (ማቴዎስ 6:​33) በገንዘብ ረገድ የነበረን በጣም አነስተኛ ቢሆንም በ1930ዎቹ ውስጥ ሌዝብሪጅ አልበርታ የሚገኘው የአባባ ጫማ ቤት የመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ማዕከል ሆኖ ነበር። አቅኚ በመባል የሚታወቁት የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ቤታችን ይመጡና ተሞክሮዎችን ይነግሩን ነበር። እነዚህ የልጅነት ትዝታዎቼ ናቸው።

በ1943 አልበርታ ውስጥ ፎርት ማክላውድና ክላርዝሆም ከሚባሉ ከተሞች አቅራቢያ አቅኚ ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ተቃዋሚዎች የተሳሳተ መረጃዎች በማሰራጨታቸው በካናዳ የስብከት ሥራችን ታግዶ ነበር። የአገልግሎት ክልላችን ከመኖሪያችን በሁለቱም አቅጣጫ እስከ 50 ኪሎ ሜትር ድረስ የሚያስኬድ የነበረ ቢሆንም ወጣቶችና ጠንካሮች ስለነበርን በአካባቢው ወደሚገኙት ትንንሽ መንደሮችና የእርሻ ቦታዎች ለመድረስ በብስክሌትም ሆነ በእግራችን መጓዙ ምንም አይመስለንም ነበር። በእነዚህ ጊዜያት ከአንዳንድ የጊልያድ ምሩቃን ጋር የመነጋገር አጋጣሚ አግኝቼ ስለነበር ተሞክሮዎቻቸው ሚስዮናዊ የመሆን ፍላጎት አሳደሩብኝ።

በ1945 ከሳስካችዋን ካናዳ የመጣውን ጆርጅ ፖርተር አገባሁ። ወላጆቹ ከ1916 ጀምሮ ያገለገሉ ቀናተኛ ምሥክሮች ነበሩ። ጆርጅም የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ሥራዬ ብሎ ያዘው። የመጀመሪያዋ ምድባችን በሰሜናዊ ቫንኮቨር ካናዳ የምትገኘው ውቧ ሊን ሸለቆ ስትሆን ብዙም ሳይቆይ ወደ ጊልያድ እንድንሄድ ተጋበዝን።

ባለፉት ዓመታት ሁሉ ከተለያዩ ሃይማኖታዊ ተቋማት ከተመረቁ ግለሰቦች ጋር የመነጋገር አጋጣሚ ያገኘሁ ሲሆን የወሰዱት ሥልጠና ምን ያህል በአምላክና በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያላቸውን እምነት እንደሸረሸረው ለማየት ችያለሁ። ከዚህ በተቃራኒ ግን እኛ በጊልያድ የወሰድነው ሥልጠና የማሰብ ችሎታችን ስል እንዲሆን የረዳን ሲሆን ከሁሉም በላይ ደግሞ በይሖዋ አምላክና በቃሉ ላይ ያለንን እምነት አጠናክሮልናል። የክፍል ጓደኞቻችን ወደ ቻይና፣ ሲንጋፖር፣ ሕንድና ወደ አፍሪካ አገሮች እንዲሁም ወደ ደቡብ አሜሪካና ወደ ሌሎች ቦታዎች ተመድበው ነበር። የእኛ ምድብ ሞቃታማዎቹ የባሃማስ ደሴቶች መሆናቸውን ስንሰማ ምን ያህል እንደተደሰትን አልረሳውም።

እዚያው ልንቆይ የቻልንበት ምክንያት

እኛ ወደ ባሃማስ ያደረግነው ጉዞ ሌሎች የክፍል ጓደኞቻችን ካደረጉት ጋር ሲወዳደር በጣም አጭር ነበር። ብዙም ሳይቆይ ሞቃታማውን አየር፣ ጥርት ያለውን ሰማይ፣ ሰማያዊ መልክ ያለውን ውኃ፣ ደማቅ ቀለም ያላቸውን የተለያዩ ሕንጻዎች እና ተቆጥረው የማይዘለቁትን ብስክሌቶች እያየን መደሰት ጀመርን። ሆኖም ከዚህ ሁሉ ይበልጥ እስካሁን ከአእምሮዬ የማይጠፉት ከጀልባ ስንወርድ ሊቀበሉን የመጡት አምስት ምሥክሮች ናቸው። ብዙም ሳንቆይ የዚህ አገር ባሕል እኛ ከለመድነው የተለየ እንደሆነ ተገነዘብን። ለምሳሌ ባለቤቴ የኔ ፍቅር ብሎ በሕዝብ ፊት እንዳይጠራኝ ተነግሮታል። ምክንያቱም የአገሩ ሰዎች እንዲህ ያለውን መግለጫ የሚጠቀሙት ለውሽማቸው ነበር።

ብዙም ሳይቆይ ከሰዎቹ ጋር ቶሎ በመቀላቀላችን ስጋት ያደረባቸው የሚመስሉት ቀሳውስት ኮሚኒስቶች ናቸው በማለት የሃሰት ክስ በመሰንዘራቸው አገሩን ለቅቀን እንድንወጣ ታዘዝን። ይሁን እንጂ በወቅቱ ቁጥራቸው 20 እንኳ የማይሞሉት ምሥክሮች ሚስዮናውያኑ መቆየት ይችሉ ዘንድ እንዲፈቀድላቸው ለጻፉት ማመልከቻ ድጋፍ የሚሆኑ በሺህ የሚቆጠሩ ፊርማዎችን በማሰባሰባቸው ደሴቲቱን ለቅቀን እንድንወጣ የተሸረበው ሴራ ከሸፈ።

ወደ አዲስ የአገልግሎት ክልል መጓዝ

የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አምላክን በሚወዱ ሰዎች ልብ ውስጥ በፍጥነት ፍሬ በማፍራት ላይ ስለነበር ከጊልያድ የተመረቁ ተጨማሪ ሚስዮናውያን ወደ ባሃማስ ተላኩ። ከዚያም በ1950 ቅርንጫፍ ቢሮ ተቋቋመ። ከአሥር ዓመት በኋላ ደግሞ ብሩክሊን ኒው ዮርክ የሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት አባል የሆነው ሚልተን ሄንሼል ባሃማስን በጎበኘበት ወቅት ከመካከላችን ወደ ሌላኛው የባሃማስ ደሴት ሄዶ አዲስ የአገልግሎት ክልል ለመክፈት ፈቃደኛ የሆነ ሰው ይኖር እንደሆነ እዚያ የምንገኘውን ሚስዮናውያን ጠየቀን። እኔና ጆርጅ ፈቃደኝነታችንን ገለጽን። አሥራ አንድ ለሚያህሉ ዓመታት በሎንግ ደሴት ያደረግነው ቆይታ የጀመረው በዚህ መልኩ ነበር።

ከባሃማስ ብዙ ደሴቶች መካከል ሎንግ ደሴት አንዷ ስትሆን 140 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 6 ኪሎ ሜትር ስፋት አላት። በወቅቱ ደሴቲቱ ዓይነተኛ ከተሞች አልነበሯትም። ዋና ከተማዋ ክላረንስ ወደ 50 የሚጠጉ ቤቶች የነበሯት ስትሆን የሰዎቹ የአኗኗር ዘይቤ በጣም ኋላ ቀር ነው። ምንም ዓይነት ኤሌክትሪክ፣ የውኃ ቧንቧም ሆነ የቤት ውስጥ ማብሰያዎች አልነበሩም። በመሆኑም ከእንዲህ ዓይነቱ የደሴት ላይ ኑሮ ጋር ራሳችንን ማለማመድ ነበረብን። በዚህ ደሴት የሰዎችን ጤንነት የሚመለከቱ ጉዳዮች ተወዳጅ የመወያያ ርዕሶች ናቸው። በሰላምታችን ውስጥ “ዛሬ እንዴት ነህ?” የሚሉትን ቃላት መጠቀም እንደሌለብን ተገነዘብን። ምክንያቱም የሚሰጠው መልስ ብዙውን ጊዜ የሰውዬውን ጠቅላላ የሕክምና ታሪክ የሚያጠቃልል ስለነበር ነው።

ብዙውን ጊዜ ስብከታችንን የምናከናውነው ከወጥ ቤት ወደ ወጥ ቤት እየሄድን ነበር። ምክንያቱም ሰዎቹን የምናገኘው የሣር ክዳን ባላቸውና ከቤቶቻቸው ውጭ በተሠሩ ወጥ ቤቶቻቸው ውስጥ ምግባቸውን በእንጨት በማብሰል ላይ እንዳሉ ስለነበር ነው። ከነዋሪዎቹ መካከል አብዛኞቹ ኑሮአቸው ዝቅተኛ የሆኑ ገበሬዎች ወይም ዓሣ አጥማጆች ቢሆኑም ደግነት ያልተለያቸው ሰዎች ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ ሃይማኖታዊ ዝንባሌ ያላቸውና በአጉል እምነት የተጠላለፉ ነበሩ። እንግዳ የሆኑ ክስተቶች እንደ ገድ ምልክት ተደርገው ይወሰዳሉ።

ቀሳውስቱ ወደ ሰዎች ቤት ዘው ብለው ገብተው እኛ የሰጠናቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች መቀዳደዳቸው እንደ ነውር አይታያቸውም ነበር። ከዚያም ድንጉጥ የሆኑትን ያስፈራሯቸዋል። ሆኖም ፈርተው ያፈገፈጉት ሁሉም አልነበሩም። ለምሳሌ አንዲት ደፋር የ70 ዓመት አረጋዊት ለቀሳውስቱ ማስፈራሪያ እጃቸውን አልሰጡም። እኚህ ሴት መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት ፈልገው ነበር። በመጨረሻም ሌሎች ሰዎችን ጨምሮ አረጋዊቷ ሴት ምሥክር ሆነዋል። በመካከላቸው ፍላጎት ያላቸው ተጨማሪ ሰዎች በማግኘታችን እነርሱን በስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ለመርዳት ጆርጅ የተወሰኑ እሁዶች 300 ኪሎ ሜትር መንዳት ነበረበት።

አንድም ሌላ ምሥክር ባልነበረባቸው በመጀመሪያዎቹ ወራት ጆርጅና እኔ አምስቱንም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በማድረግ መንፈሳዊነታችንን ጠብቀን ቆይተናል። ከዚህም በተጨማሪ ዘወትር ሰኞ ምሽት ለመጠበቂያ ግንብ በመዘጋጀት እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችንን በማድረግ ተግተናል። ሁሉንም የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶችም እንደደረሱን እናነባቸው ነበር።

ሎንግ ደሴት እያለን አባቴ ሞተ። ከዚያም በ1963 እናቴ ወደ እኛ መጥታ በአቅራቢያችን መኖር የምትችልበትን ዝግጅት አደረግን። በዕድሜ የገፋች ብትሆንም አንጻራዊ በሆነ መንገድ ራሷን ከአዳዲስ ሁኔታዎች ጋር በማላመዷ በ1971 እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ በሎንግ ደሴት መኖር ችላለች። ዛሬ ሎንግ ደሴት አንድ አዲስ የመንግሥት አዳራሽ ያለው ጉባኤ ሆኗል።

እጅግ አሳዛኝ ፈተና

በ1980 ጆርጅ ጤናው እያሽቆለቆለ መምጣቱን አስተዋለ። በሕይወቴ ካጋጠሙኝ አሳዛኝ ነገሮች ሁሉ በጣም ከባድ ሆኖ ያገኘሁት ፈተና የጀመረው በዚህ ጊዜ ነበር። ውዱ ባለቤቴ፣ የሥራ ባልደረባዬና ጓደኛዬ የነርቭን ሥርዓት በሚያጠቃው በኦልዛይመር በሽታ ሲሰቃይ ማየት ለእኔ በጣም ከባድ ነበር። ጠቅላላ ባሕርይው ተለወጠ። ጆርጅ በ1987 ከመሞቱ በፊት በነበሩት በመጨረሻዎቹ አራት ዓመታት በጣም ተሰቃይቶ ነበር። ወደ አገልግሎትና ወደ ስብሰባዎች ስሄድ አቅሙ የፈቀደውን ያህል ጥረት በማድረግ አብሮኝ ይሄድ የነበረ ቢሆንም የሚያደርገውን ጥረት ስመለከት ብዙ ጊዜ አለቅስ ነበር። ከዚያ በኋላ ክርስቲያን ወንድሞች ያሳዩኝ ፍቅር እጅግ አጽናንቶኛል። አሁንም ቢሆን ጆርጅ አጠገቤ አለመኖሩ ብዙ አጉድሎብኛል።

በትዳሬ ውስጥ ከፍ አድርጌ ከማያቸው ነገሮች መካከል አንዱ ከጆርጅ ጋር ዘወትር የምናደርገው አስደሳች የሐሳብ ልውውጥ ነበር። አሁን ጆርጅ አጠገቤ ስለሌለ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ “ሳታቋርጡ ጸልዩ፣” “በጸሎት ጽኑ፣” ‘በጸሎትና በልመናም ሁሉ ትጉ’ የሚል ግብዣ በማቅረቡ ለዚህ መብት ከመቼውም ጊዜ ይልቅ አመስጋኝ ነኝ። (1 ተሰሎንቄ 5:​17፤ ሮሜ 12:​12፤ ኤፌሶን 6:​18) ይሖዋ ስለ ደህንነታችን እንደሚያስብ ማወቁ ምንኛ ያጽናናል። እንደሚከተለው ሲል የዘመረው መዝሙራዊ ዓይነት ስሜት ይሰማኛል:- “በየቀኑ ሸክማችንን የሚሸከምልን ይሖዋ የተባረከ ይሁን።” (መዝሙር 68:​19 NW ) ልክ ኢየሱስ እንደመከረው ለነገ ሳይጨነቁ፣ የአቅም ገደብን ተገንዝቦና እያንዳንዱ ቀን ለሚያመጣቸው በረከቶች አመስጋኝ ሆኖ ሕይወትን መምራት በእርግጥም ከሁሉ የተሻለ የአኗኗር መንገድ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።​—⁠ማቴዎስ 6:​34

አገልግሎቱ ያስገኘው አስደሳች ውጤት

በክርስቲያናዊ አገልግሎት መጠመዴ ያለፈውን ነገር እያሰብኩ ከመጠን በላይ እንዳልተክዝ ረድቶኛል። በመሆኑም ወደ ጭንቀት ሊያመሩ የሚችሉትን አፍራሽ ስሜቶች መቋቋም ችያለሁ። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ማስተማር ልዩ ደስታ ይሰጠኛል። ሕይወቴ የተረጋጋ እንዲሆንና መልክ እንዲይዝ አስተዋጽኦ ያደረገልኝን ወጥ የሆነ መንፈሳዊ ልማድ እንዳዳብር ረድቶኛል።​—⁠ፊልጵስዩስ 3:​16

በአንድ ወቅት ከ47 ዓመታት በፊት የመንግሥቱን መልእክት ካካፈልኳት ሴት ስልክ ተደወለልኝ። በ1947 ባሃማስ ስንደርስ መጽሐፍ ቅዱስን ካስጠናናቸው የመጀመሪያ ሰዎች መካከል የእርሷ አባት ይገኝበታል። እናቷን፣ አባቷን፣ ወንድሞቿንና እህቶቿን እንዲሁም የእነርሱን ልጆችና የልጅ ልጆች ጨምሮ ከ60 የሚበልጡት የቤተሰቧ አባላት የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። እርሷ ግን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አልተቀበለችም ነበር። በዚህ ጊዜ ግን የይሖዋ አምላክ አገልጋይ ለመሆን ተዘጋጅታ ነበር። ጆርጅና እኔ ባሃማስ ስንደርስ እፍኝ የማይሞላ ቁጥር የነበራቸው ምሥክሮች አሁን ቁጥራቸው አድጎ ከ1, 400 ሲበልጥ ማየት ምንኛ ያስደስታል!

አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ልጅ ባለመውለዴ ቅር ይለኝ እንደሆነ ይጠይቁኛል። እርግጥ ነው ልጆች መውለድ በረከት ሊሆን ይችላል። ሆኖም መንፈሳዊ ልጆቼ፣ የልጅ ልጆቼ እንዲሁም የልጅ ልጅ ልጆቼ የሚያሳዩኝ የማያቋርጥ ፍቅር ምናልባት ሁሉም ወላጆች የማያገኙት ነገር ሊሆን ይችላል። በእርግጥም ‘መልካም የሚያደርጉ’ እና ‘በበጎም ሥራ ባለ ጠጎች የሆኑ’ ሰዎች ደስተኞች ናቸው። (1 ጢሞቴዎስ 6:​18) የጤንነቴ ሁኔታ እስከፈቀደልኝ ድረስ በአገልግሎት የምጠመደውም ለዚህ ነው።

አንድ ቀን በአንድ የጥርስ ሕክምና ማዕከል ውስጥ እንዳለሁ አንዲት ወጣት ሴት ወደ እኔ ቀረብ አለችና “አንቺ አታውቂኝም። እኔ ግን አውቅሻለሁ። እንደምወድሽ ደግሞ እንድታውቂ እፈልጋለሁ” አለችኝ። ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዴት ልታውቅ እንደቻለችና ሚስዮናውያን ወደ ባሃማስ በመምጣታቸው በጣም አመስጋኝ እንደሆነች ገለጸችልኝ።

በሌላ ጊዜ ደግሞ ከእረፍት ስመለስ አሁን በምኖርበት ናሶ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ክፍሌ በር ላይ “እንኳን በደህና ተመለስሽ” ከሚል ማስታወሻ ጋር አንዲት ጽጌረዳ አገኘሁ። ልቤ በአመስጋኝነት ስሜት ተሞላ። ቃሉ፣ ድርጅቱና መንፈሱ ያፈራቸውን ሰዎች መመልከቴ ይሖዋን ይበልጥ እንድወደው አድርጎኛል! እውነት ነው፣ የይሖዋ አጽናኝ እጅ ብዙውን ጊዜ የሚገለጠው በዙሪያችን ባሉት ሰዎች አማካኝነት ነው።

ልቤ በአመስጋኝነት ስሜት ተሞላ

ሕይወቴ ሙሉ በሙሉ ከችግር ነፃ ነበር ማለት አይደለም። አሁንም ቢሆን አንዳንድ ችግሮች አሉብኝ። ይሁን እንጂ አመስጋኝ የምሆንባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ። ለምሳሌ ያህል ከአገልግሎቱ የሚገኘው ደስታ፣ የብዙ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ፍቅር፣ የይሖዋ ድርጅት ፍቅራዊ እንክብካቤ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሰፈሩት አስደናቂ እውነቶች፣ በትንሣኤ አማካኝነት የምንወዳቸውን ሰዎች እንደገና የማየት ተስፋ እንዲሁም ከይሖዋ ታማኝ አገልጋይ ጋር ለ42 ዓመታት በትዳር ዓለም ያሳለፍኳቸው ትዝታዎች ናቸው። ከመጋባታችን በፊት ጆርጅ በጣም በሚወደው የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መቀጠል ይችል ዘንድ ድጋፍ እንድሆነው ጸልዬ ነበር። ይሖዋ ይህንን ጸሎቴን ግሩም በሆነ መንገድ መልሶልኛል። ስለዚህ ሁልጊዜ ለይሖዋ ታማኝ በመሆን አመስጋኝነቴን መግለጽ እፈልጋለሁ።

ባሃማስ በሺህ የሚቆጠር የአሜሪካን ዶላር በማውጣት በሞቃታማው አየር ለመዝናናት የሚመጡ ቱሪስቶች መናኻሪያ ናት። የይሖዋ ድርጅት በሚመድበኝ በየትኛውም ቦታ ለማገልገል በመምረጤ የአምላክን መንግሥት ምሥራች በማወጅ ደሴቶቹን በሙሉ አንድ በአንድ የማየት አስደሳች መብት አግኝቻለሁ። ከሁሉም በላይ ግን ወዳጃዊ የሆኑትን የባሃማሳውያንን ፍቅር ማየትና ማጣጣም በመቻሌ ተደስቻለሁ።

ለወላጆቼ እውነትን ላሳወቋቸው ሰዎች በጣም አመስጋኝ ነኝ። ወላጆቼም በተራቸው በልጅነት እእምሮዬና ልቤ ውስጥ የአምላክን መንግሥት የማስቀደም ልባዊ ፍላጎት ስለተከሉብኝ በጣም አመሰግናቸዋለሁ። ዛሬም ቢሆን ወጣት የይሖዋ አገልጋዮች አገልግሎታቸውን ለማስፋት የሚያስችሉ ግሩም አጋጣሚዎችን በሚከፍትላቸው “ትልቅ በር” ከገቡ ብዙ በረከቶችን ሊያገኙ ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 16:​9) እናንተም ሕይወታችሁን ‘የአማልክትን አምላክ’ ለማክበር ከተጠቀማችሁበት ልባችሁ በአመስጋኝነት ስሜት ይሞላል።​—⁠ዘዳግም 10:​17፤ ዳንኤል 2:​47

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1944 ቪክቶሪያ ቢ ሲ ውስጥ የመንገድ ላይ ምሥክርነት ስሰጥ

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እኔና ጆርጅ በ1946 በጊልያድ ትምህርት ቤት ተካፍለናል

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በ1955 ከጆርጅ ጋር ናሶ ባሃማስ በሚገኘው የሚስዮናዊ ቤታችን ፊት ለፊት

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከ1961 እስከ 1972 ድረስ ባገለገልንበት በዴድማንስ ኬይ የሚገኘው የሚስዮናዊ ቤታችን