በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

መተማመን የምትችለው ማን ባወጣቸው መሥፈርቶች ነው?

መተማመን የምትችለው ማን ባወጣቸው መሥፈርቶች ነው?

መተማመን የምትችለው ማን ባወጣቸው መሥፈርቶች ነው?

ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪካ የመጣ አንድ አገር ጎብኚ መንገድ ዳር ግትር ብሎ የቆመ አንድ ሰው ትኩረቱን ሳበው። ሰውዬው በየጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት ቀጥ ብሎ በቆመበት ቀስ በቀስ ወደ አንድ ጎን እየዞረ መሆኑን አስተዋለ። ሰውዬው በዚህ መንገድ የሚዞርበት ምክንያት ለጎብኚው ግልጽ የሆነለት ከጊዜ በኋላ ነበር። ለካስ ሰውዬው ከአንድ የስልክ እንጨት ጥላ ላለመውጣት እየጣረ ነበር። የከሰዓት በኋላዋ ፀሐይ አቅጣጫዋን ስትቀይር የስልክ እንጨቱ ጥላም ቀስ በቀስ አቅጣጫውን ይቀይር ነበር።

ፀሐይዋ እንደምትፈጥረው ጥላ ሁሉ የሰው ልጆች እንቅስቃሴዎችና መሥፈርቶችም በየጊዜው ይለዋወጣሉ። ከዚህ በተቃራኒ ግን ‘የብርሃናት አባት’ የሆነው ይሖዋ አምላክ አይለዋወጥም። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ‘በመዞርም የተደረገ ጥላ በእርሱ ዘንድ የለም’ ሲል ጽፏል። (ያዕቆብ 1:​17) ዕብራዊው ነቢይ ሚልክያስ አምላክ ራሱ የተናገረውን እንዲህ ሲል አስፍሯል:- “እኔ እግዚአብሔር አልለወጥም።” (ሚልክያስ 3:​6) በኢሳይያስ ዘመን ለነበረው የእስራኤል ብሔር አምላክ እንዲህ ብሎ ነበር:- “እስከ ሽምግልና ድረስ እኔ ነኝ፣ እስከ ሽበትም ድረስ እሸከማችኋለሁ፤ እኔ ሠርቻለሁ።” (ኢሳይያስ 46:​4) በመሆኑም የጊዜ ማለፍ ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ያለንን ትምክህት ሊለውጠው አይችልም።

ከሕጉ የምናገኘው ትምህርት

ይሖዋ የሰጣቸው ተስፋዎች አስተማማኝና የማይለዋወጡ እንደሆኑ ሁሉ ትክክልና ስህተት ለሆኑ ነገሮች ያወጣቸው መሥፈርቶችም አይለወጡም። ትክክለኛው አንዱ ብቻ ሆኖ ሳለ በሁለት ዓይነት ሚዛኖች የሚጠቀምን ነጋዴ ታምነዋለህ? እንደማታምነው የታወቀ ነው። በተመሳሳይ “አባይ ሚዛን በእግዚአብሔር ፊት አስጸያፊ ነው፤ እውነተኛ ሚዛን ግን ደስ ያሰኘዋል።” (ምሳሌ 11:​1፤ 20:​10) ይሖዋ ለእስራኤላውያን በሰጣቸው ሕግ ውስጥ የሚከተለውን ትእዛዝ አካትቶ ነበር:- “በፍርድ፣ በመለካትም፣ በመመዘንም፣ በመስፈርም ዓመፃ አታድርጉ። የእውነትም ሚዛን፣ የእውነትም መመዘኛ፣ የእውነትም የኢፍ መስፈሪያ፣ የእውነትም የኢን መስፈሪያ ይሁንላችሁ፤ ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እኔ ነኝ።”​—⁠ዘሌዋውያን 19:​35, 36

እስራኤላውያን ይህን ትእዛዝ ማክበራቸው የአምላክን ሞገስ እና በርካታ ቁሳዊ በረከቶችን አስገኝቶላቸዋል። በተመሳሳይ በሚዛንና በመለኪያ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ቋሚ የሆኑትን ይሖዋ ያወጣቸውን መሥፈርቶች በጥብቅ መከተሉ በይሖዋ ለሚታመን አምላኪ በረከት ያስገኝለታል። አምላክ እንዲህ ሲል ይገልጻል:- “እኔ የሚረባህን ነገር የማስተምርህ በምትሄድባትም መንገድ የምመራህ አምላክህ እግዚአብሔር ነኝ።”​—⁠ኢሳይያስ 48:​17

በዛሬው ጊዜ የአቋም ደረጃዎች እያዘቀጡ ያሉት ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ የአቋም ደረጃዎች እያዘቀጡ ያሉበትን ምክንያት ይገልጻል። የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ራእይ እስካሁን ድረስ በመላው የሰው ልጆች ላይ ተጽእኖ ስላለው በሰማይ ስለተካሄደ አንድ ጦርነት ይናገራል። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በሰማይም ሰልፍ ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ዘንዶውን ተዋጉ። ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ አልቻላቸውምም፣ ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም። ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው፣ ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፤ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ።”​—⁠ራእይ 12:​7-9

ወዲያው ጦርነቱን ተከትሎ የመጣው ነገር ምን ነበር? ዮሐንስ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ስለዚህ፣ ሰማይና በውስጡ የምታድሩ ሆይ፣ ደስ ይበላችሁ፤ ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቊጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና።”​—⁠ራእይ 12:​12

በ1914 አንደኛው የዓለም ጦርነት ፈንድቶ ዛሬ ካለው ፈጽሞ የተለየ የአቋም ደረጃ የነበረው ዘመን ወደ ፍጻሜው ሲመጣ ‘በምድር ላይ ወዮታ’ ደርሷል። የታሪክ ምሁር የሆኑት ባርባራ ተክማን “ከ1914-18 የተካሄደው ታላቁ ጦርነት የእኛን ዘመን ከዚያ ዘመን ጋር የሚለይ የወሰን መስመር ሆኖ ይታያል” ሲሉ ተናግረዋል። “ከዚያ በኋላ በነበሩት ዓመታት ብዙ ጠቃሚ ነገር ሊያከናውኑ የሚችሉ አምራች ዜጎችን በመፍጀት፣ የሰዎችን እምነት በማጥፋት፣ የአመለካከት ለውጥ በማስከተልና ሊድን የማይችል የግራመጋባት ጠባሳ በመተው በሁለቱ ምዕራፎች መካከል በተጨባጭ የሚታይም ሆነ ሥነ ልቦናዊ ክፍተት ፈጥሯል።” ሌላው የታሪክ ምሁር ኤሪክ ሀብስባም እንዲህ ሲሉ ተመሳሳይ አስተያየት ሰጥተዋል:- “ከ1914 ወዲህ ባደጉ አገሮች ውስጥ በወቅቱ አግባብ ተደርገው ይታዩ የነበሩ የአቋም ደረጃዎች በከፍተኛ ሁኔታ አዝቅጠዋል። . . . በአሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩት አባቶቻችን የበርበራውያን ኑሮ ብለው ሊጠሩት ይችሉ ወደነበረው ሁኔታ ምን ያህል በከፍተኛ ፍጥነት የኋልዮሽ እንደሄድን መረዳት ይከብዳል።”

ደራሲው ጆናታን ግሎቨር ሂውማኒቲ​—⁠ኤ ሞራል ሂስትሪ ኦቭ ዘ ትዌንቲዝ ሴንቸሪ በተባለው መጽ​ሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “የሥነ ምግባር ሕግ እየጠፋ መሄድ የጊዜያችን አንዱ ገጽታ ነው።” በምዕራቡ ዓለም ለሃይማኖት የሚሰጠው ግምት እየቀነሰ በመምጣቱ ከሌላ ወገን ለሚመነጭ የሥነ ምግባር ሕግ ያላቸው አመለካከት ጥርጣሬ የሞላበት ቢሆንም እንኳ እንዲህ ሲሉ አስጠንቅቀዋል:- “በሃይማኖታዊ የሥነ ምግባር ሕግ የማናምን ብንሆንም እንኳ ይህ ሕግ እየጠፋ መምጣቱ ሊያሳስበን ይገባል።”

በዛሬው ጊዜ በንግድ፣ በፖለቲካ ወይም በሃይማኖት አልፎ ተርፎም በግለሰብና በቤተሰብ ግንኙነቶች ረገድ የሚታየው ሰዎች እምነት የሚጣልባቸው ሆነው አለመገኘታቸውም ሆነ ይህ ባሕርይ የሚያስከትለው አስከፊ መዘዝ ዲያብሎስ በምድር ነዋሪዎች ላይ ወዮታ ለማምጣት የሚጠቀምባቸው ዘዴዎች አካል ነው። ሰይጣን እስከመጨረሻው ድረስ በውጊያው ለመቀጠልና የአምላክን የአቋም ደረጃዎች ጠብቀው ለመኖር የሚጥሩትን ሁሉ ከራሱ ጋር ለማጥፋት ቆርጦ ተነስቷል።​—⁠ራእይ 12:​17

የተለመደ ችግር የሆነው ሰዎች እምነት የሚጣልባቸው ያለመሆናቸው ጉዳይ መፍትሔ የሚያገኝበት መንገድ ይኖር ይሆንን? ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ የሚል መልስ ይሰጣል:- “ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።” (2 ጴጥሮስ 3:​13) አምላክ ዓላማውን ለማስፈጸም ኃይል ያለው ከመሆኑም በላይ ዓላማው ፍጻሜውን እንደሚያገኝ ዋስትና ስለሰጠ በዚህ ተስፋ ላይ እምነት መጣል እንችላለን። ይሖዋ ‘ከአፉ የሚወጣውን ቃል’ ሁሉ በተመለከተ እንዲህ ሲል ተናግሯል:- “የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም።” በእርግጥም እምነት የሚጣልበት ተስፋ ነው!​—⁠ኢሳይያስ 55:​11፤ ራእይ 21:​4, 5

አምላክ ባወጣቸው መሥፈርቶች መሠረት መኖር

ተለዋዋጭ የሆኑና እያዘቀጡ የሚሄዱ መሥፈርቶች ባሉት ዓለም ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው ለመኖር ይጥራሉ። ከዚህ የተነሳ ከብዙሃኑ ተለይተው የሚታዩ ሲሆን ይህ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ የሌሎች ትኩረት በእነሱ ላይ እንዲያርፍ ከማድረጉም በላይ ለጥላቻ ዳርጓቸዋል።

ለንደን ውስጥ በተካሄደ የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ አንድ የቴሌቪዥን ዘጋቢ የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛ ክርስቲያኖች ስለመሆናቸው ለአንድ ቃል አቀባይ ጥያቄ አቀረበለት። ቃል አቀባዩ እንዲህ ሲል መልስ ሰጠ:- “አዎን፣ የምንከተለው የኢየሱስን ፈለግ እስከሆነ ድረስ እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናችን ምንም ጥርጥር የለውም። በዓለም በከፍተኛ ሁኔታ ራስ ወዳድነት ይታያል። እኛ ግን ኢየሱስ ክርስቶስ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ስለሆነ በእሱ ላይ ትኩረት እናደርጋለን። ኢየሱስ የሥላሴ ክፍል ሳይሆን የአምላክ ልጅ መሆኑን ነው የምናምነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን የምንረዳበት መንገድ በሰፊው የሚታወቁ ሃይማኖቶች ካላቸው ግንዛቤ ይለያል።”

ቃለ ምልልሱ በቢ ቢ ሲ ቴሌቪዥን ከተላለፈ በኋላ ሪፖርተሩ ፕሮግራሙን ሲደመድም እንዲህ ብሏል:- “የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታችን የሚመጡት ለምን እንደሆነ በሰፊው ማወቅ ችያለሁ። ከዚህ በፊት ሥርዓታማ አለባበስና ጠባይ ያላቸው 25, 000 ሰዎች እንዲህ አንድ ላይ ተሰብስበው ያየሁ አይመስለኝም።” አምላክ ያወጣቸውን የማይለዋወጡ መሥፈርቶች መከተል ጥበብ መሆኑን የሚያሳይ አንድ የውጭ ታዛቢ የሰጠው ምንኛ ግሩም ምሥክርነት ነው!

አንዳንዶች ሌላ አካል ያወጣቸውን መሥፈርቶች ጠብቆ መኖር ላያስደስታቸው ቢችልም መጽሐፍ ቅዱስን እንድትመረምርና አምላክ ያወጣቸው መሥፈርቶች ምን ዓይነት እንደሆኑ እንድትማር እናበረታታሃለን። ሆኖም እንዲሁ ላይ ላዩን በመመርመር አትርካ። የሐዋርያው ጳውሎስን ምክር ተከተል:- “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ።” (ሮሜ 12:​2) በአካባቢህ ወደሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ ሄደህ እዚያ ከሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተዋወቅ። በመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች ላይ እምነት ያላቸውና አምላክ ያወጣቸውን መሥፈርቶች ተከትለው በመኖር በእሱ ላይ እምነት እንዳላቸው የሚያሳዩ ሰዎች መሆናቸውን ትገነዘባለህ።

የማይለዋወጡትንና አስተማማኝ የሆኑትን አምላክ ያወጣቸውን መሥፈርቶች በጥብቅ መከተልህ በረከት እንደሚያስገኝልህ የተረጋገጠ ነው። “ትእዛዜን ብትሰማ ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር” በማለት አምላክ ራሱ ያቀረበውን ግብዣ ተቀበል።​—⁠ኢሳይያስ 48:​18

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ በንግድ፣ በፖለቲካ፣ በሃይማኖትና በቤተሰብ ግንኙነቶች ረገድ ሰዎች እምነት የሚጣልባቸው ሆነው አልተገኙም