መንፈሳዊ ፍላጎቱ ተሟላ
የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
መንፈሳዊ ፍላጎቱ ተሟላ
ቆጵሮስ በሜዲትራንያን ባሕር ሰሜናዊ ምሥራቅ ጫፍ የምትገኝ ደሴት ናት። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ቆጵሮስ ባላት ናስና ምርጥ እንጨት የታወቀች ነበረች። ጳውሎስና በርናባስ በመጀመሪያው የሚስዮናዊ ጉዞአቸው ወቅት የመንግሥቱን ምሥራች በቆጵሮስ አውጀዋል። (ሥራ 13:4-12) ዛሬም ቢሆን ምሥራቹ በብዙ ቆጵሮሳውያን ሕይወት ላይ በጎ ተጽእኖ እያሳደረ ነው። ይህንንም በ40ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ከሚገኘው የሉካስ ሁኔታ መረዳት ይቻላል። እንዲህ ሲል ሁኔታውን ይገልጻል:-
“ሰባት ልጆች ባሉበት በከብት እርባታ የሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ ተወለድኩ። ከልጅነቴ ጀምሮ ከፍተኛ የማንበብ ፍላጎት ነበረኝ። በጣም የምወዳት መጽሐፌ በኪስ የምትያዘው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች እትም ነበረች። አሥር ዓመት ሲሞላኝ እኔና አንዳንድ ጓደኞቼ አንድ ትንሽ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን አቋቋምን። ሆኖም አንዳንድ የመንደራችን ትላልቅ ሰዎች መናፍቃን እያሉ ይጠሩን ስለነበር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድናችን ብዙም አልዘለቀም።
“በኋላም ለትምህርት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በሄድኩበት ወቅት የተለያየ እምነት ካላቸው ሰዎች ጋር የመተዋወቅ አጋጣሚ አገኘሁ። ይህም ለመንፈሳዊ ነገሮች ያለኝን ፍላጎት እንደገና አቀጣጠለው። በዩኒቨርሲቲው ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ስለተለያዩ እምነቶች በማጥናት ብዙ ቀናት ያሳለፍኩ ሲሆን የተለያዩ ቤተ ክርስቲያኖችንም ጎብኝቻለሁ። ሆኖም የቱንም ያህል ጥረት ባደርግ መንፈሳዊ እርካታ አላገኘሁም ነበር።
“ትምህርቴን ከጨረስኩ በኋላ ወደ ቆጵሮስ ተመለስኩና የአንድ የሕክምና ላቦራቶሪ ዲሬክተር በመሆን መሥራት ጀመርኩ። አንቶኒስ የሚባል አንድ በእድሜ የገፋ የይሖዋ ምሥክር ሥራ ቦታዬ ድረስ እየመጣ ያነጋግረኝ ነበር። ሆኖም ከእርሱ ጋር የማደርገው ውይይት በግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሳይስተዋል አላለፈም።
“ብዙም ሳይቆይ አንድ የሃይማኖታዊ ትምህርት ምሩቅ መጣና ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መነጋገር እንደሌለብኝ ነገረኝ። ከልጅነቴ ጀምሮ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን እውነትን እንደያዘች ተምሬ ስለነበር ከአንቶኒስ ጋር የማደርገውን ውይይት አቋረጥኩ። ከዚያም ከዚህ ሰው ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መወያየት ጀመርኩ። በቆጵሮስ የሚገኙትን ብዙ ገዳማትም ጎብኝቻለሁ። በሰሜናዊ ግሪክ የሚገኘውንና የኦርቶዶክስ ክርስትናው ዓለም እጅግ ቅዱስ አድርጎ የሚመለከተውን የአቶስ ተራራ ሳይቀር ጎብኝቻለሁ። ያም ሆኖ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎቼ አሁንም መልስ አላገኙም ነበር።
“ከዚያም አምላክ እውነትን እንዳገኝ እንዲረዳኝ ጸለይኩ። ብዙም ሳይቆይ አንቶኒስ ሥራ ቦታዬ ድረስ ሊያነጋግረኝ መጣ። አምላክ ለጸሎቴ መልስ እንደሰጠኝ ተሰማኝ። በመሆኑም ከሃይማኖታዊ ትምህርት ምሩቁ ጋር የማደርገውን ውይይት አቋርጬ ከአንቶኒስ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ። እድገት ማድረጌን በመቀጠል ጥቅምት 1997 ራሴን ለይሖዋ ወስኜ ተጠመቅሁ።
“በመጀመሪያ ባለቤቴና በጊዜው የ14ና የ10 ዓመት እድሜ የነበራቸው ሁለቱ ሴቶች ልጆቼ ተቃውመውኝ ነበር። ይሁን እንጂ ባለቤቴ ባሳየሁት ጥሩ ጠባይ በመነካቷ በመንግሥት አዳራሽ በሚደረግ አንድ ስብሰባ ላይ ለመገኘት ወሰነች። በምሥክሮቹ ደግነትና ለእርሷ በግል ባሳዩዋት አሳቢነት በጥልቅ የተነካች ሲሆን በተለይ ከሁሉም በላይ ያስደነቃት የመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃቀማቸው ነበር። በመጨረሻም ባለቤቴና ሁለቱ ትልልቅ ሴቶች ልጆቼ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማሙ። በ1999 በተደረገው “የአምላክ ትንቢታዊ ቃል” በተሰኘው የአውራጃ ስብሰባ ላይ ሦስቱም ሲጠመቁ ሳይ ምንኛ እንደተደሰትኩ ገምቱ!
“አዎን፣ እውነትን ለማግኘት ያደረግሁት ፍለጋ ተሳክቷል። ዛሬ ባለቤቴንና አራቱን ልጆቼን ጨምሮ መላው ቤተሰባችን በይሖዋ ንጹህ አምልኮ አንድ ሆኗል።”