በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በይሖዋ ላይ ያለህን እምነት አጠናክር

በይሖዋ ላይ ያለህን እምነት አጠናክር

በይሖዋ ላይ ያለህን እምነት አጠናክር

አንድ የግድያ ሴራ እየተቀነባበረ ነው። የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሙሉ በጋራ መክረው የአንድ አዲስ ሕግ ረቂቅ አዘጋጅተዋል። ማንኛውም ሰው መንግሥት ባልፈቀደው አምልኮ መካፈሉ በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ተደርጎ እንዲታይ ፈልገዋል።

ህን ጉዳይ ከዚህ በፊት የሰማኸው ይመስልሃል? በታሪክ ዘመናት በሙሉ ሕግን ተንተርሰው ተንኮል የሸረቡ በርካታ ሰዎችን መጥቀስ ይቻላል። ከላይ የተጠቀሰው በነቢዩ ዳንኤል ዘመን በፋርስ ግዛት ውስጥ የተከሰተ ሁኔታ ነው። ንጉሥ ዳርዮስ ተስማምቶበት ያወጣው ሕግ እንዲህ ሲል ይደነግጋል:- “ከአንተ በቀር ማንም እስከ ሠላሳ ቀን ድረስ ልመና ከአምላክ ወይም ከሰው ቢለምን፣ በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ይጣል።”​—⁠ዳንኤል 6:​7-9

ዳንኤል ይህ የግድያ ዛቻ እንዳለ ሲያውቅ ምን ያደርግ ይሆን? በአምላኩ በይሖዋ ላይ እንደታመነ ይቀጥል ይሆን? ወይስ አቋሙን አላልቶ ንጉሡ ያዘዘውን ይፈጽም ይሆን? ዘገባው እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “ዳንኤልም ጽሕፈቱ እንደ ተጻፈ ባወቀ ጊዜ ወደ ቤቱ ገባ፤ የእልፍኙም መስኮቶች ወደ ኢየሩሳሌም አንጻር ተከፍተው ነበር፤ ቀድሞም ያደርግ እንደ ነበረ በየዕለቱ ሦስት ጊዜ በጉልበቱ ተንበርክኮ በአምላኩ ፊት ጸለየ አመሰገነም።” (ዳንኤል 6:​10) የቀረው የዘገባው ክፍል በሰፊው የሚታወቅ ነው። ዳንኤል በእምነቱ የተነሳ በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ተጣለ። ሆኖም ይሖዋ ‘የአንበሶችን አፍ ዘግቶ’ ታማኝ አገልጋዩን አዳነው።​—⁠ዕብራውያን 11:​33፤ ዳንኤል 6:​16-22

ራሳችንን የምንመረምርበት ጊዜ

ዛሬ የይሖዋ አገልጋዮች የሚኖሩት ለአካላዊም ሆነ ለመንፈሳዊ ደኅንነታቸው ስጋት የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ባሉበት ጥላቻ በነገሠበት ዓለም ውስጥ ነው። ለምሳሌ ያህል ጭካኔ የተሞላበት የዘር ጥላቻ ድንገት በፈነዳባቸው በአንዳንድ አገሮች ብዙ የይሖዋ ምሥክሮች ተገድለዋል። በሌሎች አገሮች ደግሞ የይሖዋ አገልጋዮች የምግብ እጥረት፣ የኢኮኖሚ ችግር፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ ከባድ በሽታና ሌሎች ለሕይወት አስጊ የሆኑ ሁኔታዎችን ተጋፍጠዋል። ከዚህ በተጨማሪ የሚደርስባቸውን ስደት፣ በሥራ ቦታ የሚገጥማቸውን ጫና እንዲሁም ኃጢአት እንዲሠሩ የሚደቀኑባቸውን ልዩ ልዩ ፈተናዎች መቋቋም አለባቸው። ይህ ሁሉ በመንፈሳዊ ጤንነታቸው ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል። በእርግጥም ታላቁ ባላጋራ፣ ሰይጣን ስኬታማ ሆኖ ባገኘው በየትኛውም ዘዴ ተጠቅሞ የይሖዋን አገልጋዮች ለማጥፋት ቆርጦ ተነስቷል።​—⁠1 ጴጥሮስ 5:​8

እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲጋረጡብን ምን ማድረግ እንችላለን? ምንም እንኳ አንድ ሰው በሕይወቱ ላይ አደጋ ሲደቀን መፍራቱ ያለ ነገር ቢሆንም ሐዋርያው ጳውሎስ የተናገራቸውን አጽናኝ ቃላት ማስታወስ እንችላለን:- “[ይሖዋ] ራሱ:- አልለቅህም ከቶም አልተውህም ብሎአልና፤ ስለዚህ በድፍረት:- ጌታ ይረዳኛልና አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል? እንላለን።” (ዕብራውያን 13:​5, 6) በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ተመሳሳይ ስሜት እንዳለው እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ሆኖም ይሖዋ የሰጠውን ተስፋ ማወቅ አንድ ነገር ሲሆን ለእኛ ሲል እርምጃ እንደሚወስድ በእርግጠኝነት ማመን ደግሞ ሌላ ነገር ነው። በመሆኑም በይሖዋ ላይ እምነት ለመገንባት መሠረት የሚሆነንን ነገር መመርመራችንና እምነታችንን ለማጠናከርና ጠብቆ ለማቆየት የቻልነውን ሁሉ ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው። ይህን ካደረግን ‘አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችንንና አሳባችንን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።’ (ፊልጵስዩስ 4:​7) ከዚያም ፈተናዎች በሚያጋጥሙን ጊዜ በትክክል ማሰብና ፈተናዎቹን ጥበብ በተሞላበት መንገድ መወጣት እንችላለን።

በይሖዋ ላይ ለመታመን የሚያበቃ መሠረት

በእርግጥም በፈጣሪያችን በይሖዋ ላይ እንድንታመን የሚያደርጉን በርካታ ምክንያቶች አሉን። ከእነዚህ መካከል የመጀመሪያው ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ከልብ የሚያስብ አፍቃሪ አምላክ መሆኑ ነው። ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ፍቅራዊ አሳቢነት እንደሚያሳይ የሚገልጹ እጅግ በርካታ ማስረጃዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው ይገኛሉ። ይሖዋ ለተመረጡት ሕዝቦቹ ለእስራኤላውያን ያደረገላቸውን ነገር ሲገልጽ ሙሴ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በምድረ በዳ በጥማት፣ የነፋስ ጩኸትም በሞላበት ውድማ አገኘው፤ ከበበው ተጠነቀቀለትም፤ እንደ ዓይን ብሌን ጠበቀው።” (ዘዳግም 32:​10) በአሁኑ ጊዜም ይሖዋ በቡድንም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ለአገልጋዮቹ ጥሩ ጥበቃ ማድረጉን ቀጥሏል። ለምሳሌ ያህል በቦስኒያ በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች ከፍተኛ የምግብ እጥረት በገጠማቸው ጊዜ ይሖዋ በክሮኤሽያ እና በኦስትሪያ የሚገኙ ወንድሞቻቸው ባሳዩት ድፍረት የተሞላበት ጥረት አማካኝነት የሚያስፈልጓቸው ቁሳ ቁሶች እንዲደርሷቸው አድርጓል። እነዚህ የኦስትሪያ ወንድሞች ለወንድሞቻቸው አስቸኳይ እርዳታ ለማድረስ ሲሉ በጣም አደገኛ በሆነ ክልል ለመጓዝ በሕይወታቸው ቆርጠው ነበር የተነሱት። a

ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክ ስለሆነ በማንኛውም ሁኔታ ሥር ለሚገኙ አገልጋዮቹ ከለላ መሆን ይችላል። (ኢሳይያስ 33:​22፤ ራእይ 4:​8) ሌላው ቀርቶ ይሖዋ አንዳንድ አገልጋዮቹ እስከ ሞት ድረስ ታማኝነታቸውን እንዲያረጋግጡ በሚፈቅድበት ጊዜም እንኳ እስከ መጨረሻ ድረስ ጽኑ፣ ደስተኛና የተረጋጉ እንዲሆኑ በማስቻል ንጹሕ አቋማቸውን መጠበቅ እንዲችሉ ይደግፋቸዋል እንዲሁም ይረዳቸዋል። በመሆኑም መዝሙራዊው የነበረው ዓይነት ትምክህት ሊኖረን ይችላል:- “አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፣ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው። ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፣ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም።”​—⁠መዝሙር 46:​1, 2

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ የእውነት አምላክ መሆኑን ይገልጻል። ይህም ማለት ምንጊዜም የገባውን ቃል ይፈጽማል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ “የማይዋሽ” አምላክ በማለት ይገልጸዋል። (ቲቶ 1:​2) ይሖዋ አገልጋዮቹን ለመጠበቅና ለማዳን ያለውን ፈቃደኝነት በተደጋጋሚ ስለገለጸ ተስፋ የሰጣቸውን ነገሮች ለመፈጸም ችሎታ ብቻ ሳይሆን ፈቃደኝነትም እንዳለው ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።​—⁠ኢዮብ 42:​2

በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር የምንችልባቸው መንገዶች

ምንም እንኳ በይሖዋ እንድንታመን የሚያደርጉ አጥጋቢ ምክንያቶች ቢኖሩንም በአንድ ወቅት ያለን እምነት አብሮን ይኖራል ብለን መገመት አንችልም። ይህ የሆነበት ምክንያት በጥቅሉ ዓለም በአምላክ ላይ ያለው እምነት ደካማ በመሆኑና እንዲህ ዓይነቱ መንፈስ እኛ በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት በቀላሉ ሊያዳክምብን ስለሚችል ነው። ስለዚህ በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ለማጠናከርና ጠብቆ ለማቆየት ብርቱ ጥረት ማድረግ አለብን። ይሖዋ ይህን አሳምሮ ያውቃል፤ ደግሞም እምነታችንን ማጠናከር የምንችልባቸውን መንገዶች አዘጋጅቶልናል።

በመጀመሪያ ደረጃ ለአገልጋዮቹ ሲል ያደረጋቸውን በርካታ አስደናቂ ክንውኖች የያዘውን በጽሑፍ የሰፈረ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን ሰጥቶናል። እስቲ አስበው ከስሙ በቀር ስለእሱ ምንም ሌላ ነገር በማታውቀው ሰው ላይ ምን ያህል ትምክህት መጣል ትችላለህ? ትምክህት ልትጥልበት እንደማትችል የታወቀ ነው። በእሱ ላይ ትምክህት ለመጣል ባሕርይውንና ተግባሩን ማወቅ አለብህ። እንደዚያ አይሰማህም? እንደዚህ የመሰሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን ስናነብብና ስናሰላስልባቸው ስለ ይሖዋና አስደናቂ ስለሆኑት መንገዶቹ ያለን እውቀት ጥልቀት የሚያገኝ ከመሆኑም በላይ ምን ያህል እምነት ሊጣልበት እንደሚችል ያለን ግንዛቤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ይሄዳል። በዚህ መንገድ በእሱ ላይ ያለን ትምክህት ይጠናከራል። መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ለአምላክ ባቀረበው ልባዊ ጸሎት ግሩም ምሳሌ ትቶልናል:- “የእግዚአብሔርን ሥራ አስታወስሁ፤ የቀደመውን ተአምራትህን አስታውሳለሁና፤ በምግባርህም ሁሉ እናገራለሁ፣ በሥራህም እጫወታለሁ።”​—⁠መዝሙር 77:​11, 12

ከመጽሐፍ ቅዱስ በተጨማሪ የይሖዋ ድርጅት በሚያዘጋጅልን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች አማካኝነት የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ይቀርብልናል። ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ እነዚህ ጽሑፎች በዘመናችን ያሉ የአምላክ አገልጋዮች አስከፊ ሁኔታዎች ሲገጥሟቸው ይሖዋ ድጋፍና ሕይወት አድን እርዳታ ሊያደርግላቸው የቻለበትን መንገድ የሚገልጹ ስሜት ቀስቃሽ የሕይወት ታሪኮች ይዘው ይወጣሉ። ለምሳሌ ያህል ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ማርቲን ፖየትሲንገር ከትውልድ አገሩ ርቆ በአንዳንድ የአውሮፓ አገሮች በአቅኚነት እያገለገለ በነበረበት ወቅት በጠና ታመመ። መታከሚያ ገንዘብ አልነበረውም፤ ሊያክመው ፈቃደኛ የሆነ ዶክተርም አልነበረም። ይሖዋ ግን አልጣለውም። በመጨረሻም በከተማው የሚገኘው ሆስፒታል አንድ እውቅ ሐኪም ተጠየቁ። በመጽሐፍ ቅዱስ በጥብቅ የሚያምኑት እኚህ ሩኅሩኅ ሰው ያለ ምንም ክፍያ ልክ እንደ ልጃቸው አድርገው በመንከባከብ ረዱት። እንዲህ ዓይነት የሕይወት ታሪኮችን ማንበብ በእርግጥ በሰማያዊ አባታችን ላይ ያለንን እምነት ያጠናክርልናል።

ይሖዋ በእሱ ላይ ያለንን እምነት እንድናጠናክር ያደረገልን ሌላው በዋጋ ሊተመን የማይችል ዝግጅት ውድ የሆነው የጸሎት መብት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ፍቅራዊ በሆነ መንገድ እንዲህ ሲል ይነግረናል:- “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ።” (ፊልጵስዩስ 4:​6) “በነገር ሁሉ” የሚለው ስሜታችንን፣ ፍላጎታችንን፣ የሚሰማንን ፍርሃትና ጭንቀት ሊያጠቃልል ይችላል። አዘውትረን ልባዊ ጸሎት ባቀረብን መጠን በይሖዋ ላይ ያለን እምነት ይበልጥ ይጠናከራል።

ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የሚረብሸው ነገር ሳይኖር መጸለይ እንዲችል አንዳንድ ጊዜ ጸጥ ወዳለ ሥፍራ ብቻውን ይሄድ ነበር። (ማቴዎስ 14:​23፤ ማርቆስ 1:​35) በጣም ከባድ የሆኑ ውሳኔዎች ከማድረጉ በፊት ሌላው ቀርቶ ሌሊቱን በሙሉ ወደ አባቱ ጸልዮአል። (ሉቃስ 6:​12, 13) ኢየሱስ በይሖዋ ላይ ከነበረው ጠንካራ እምነት አንጻር ሲታይ በሌላ ሰው ላይ ደርሶ የማያውቅ እጅግ አሰቃቂ ፈተና መቋቋም መቻሉ ምንም አያስደንቅም። በመከራ እንጨት ላይ እያለ የተናገራቸው የመጨረሻ ቃላት “አባት ሆይ፣ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” የሚሉ ነበሩ። ምንም እንኳ ይሖዋ እሱን ለማዳን ጣልቃ ባይገባም የኢየሱስን ትምክህት የሚገልጸው ይህ አባባል በአባቱ ላይ ያለው እምነት እስከመጨረሻ ድረስ እንዳልተዳከመ ያሳያል።​—⁠ሉቃስ 23:​46

በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ለመገንባት የሚረዳን ሌላው መንገድ ደግሞ በእሱ ላይ በሙሉ ልባቸው ከሚታመኑ ሰዎች ጋር አዘውትሮ መሰብሰብ ነው። ይሖዋ ስለ እሱ ይበልጥ ለመማርና እርስ በርስ ለመበረታታት እንዲችሉ ሕዝቦቹ አዘውትረው እንዲሰበሰቡ ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል። (ዘዳግም 31:​12፤ ዕብራውያን 10:​24, 25) እንዲህ ዓይነቱ ስብሰባ ከባድ የእምነት ፈተናዎችን እንዲቋቋሙ በማስቻል በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት አጠናክሮላቸዋል። የስብከቱ ሥራ ታግዶ በነበረባት አንዲት አፍሪካዊት አገር የይሖዋ ምሥክሮች የፖሊስ ጥበቃ፣ ከቦታ ወደ ቦታ መጓጓዝ የሚያስችሉ ሰነዶች፣ የጋብቻ ምሥክር ወረቀት፣ የሕክምና አገልግሎትና የሥራ ቅጥር ተነፍገው ነበር። በአንድ አካባቢ የእርስ በርስ ጦርነት ሲፈነዳ ልጆችን ጨምሮ 39 አባላት ያሉት በአቅራቢያው የሚገኝ አንድ ጉባኤ በከተማቸው ላይ ይደርስ ከነበረው የቦንብ ድብደባ ለማምለጥ ሲሉ በረሃ ውስጥ በአንድ አነስተኛ ድልድይ ሥር ለአራት ወራት ያህል ለመኖር ተገድደዋል። በእንዲህ ዓይነት አስከፊ ሁኔታ ሥር እያሉ በየዕለቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ላይ መወያየታቸውና ሌሎች ስብሰባዎችንም ማድረጋቸው ከፍተኛ ብርታት ሰጥቷቸዋል። በመሆኑም መንፈሳዊነታቸው እንደተጠበቀ ሆኖ መከራውን በጽናት መወጣት ችለዋል። ይህ ተሞክሮ ከይሖዋ ሕዝቦች ጋር አዘውትሮ መሰብሰብ ያለውን ጠቀሜታ በግልጽ ያሳያል።

በመጨረሻም በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ለማጠናከር ምንጊዜም ምሥራቹን ለሌሎች ለማካፈል ዝግጁ በመሆን በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ንቁ መሆን ይኖርብናል። ለሞት በሚዳርግ የሉኪሚያ በሽታ ተይዛ የነበረች በካናዳ የምትኖር የአንዲት ቀናተኛ ወጣት አስፋፊ ስሜት ቀስቃሽ ተሞክሮ ይህን ያሳያል። ከባድ በሽታ ቢኖርባትም እንኳ የዘወትር አቅኚ ማለትም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ መሆን ፈለገች። ለአጭር ጊዜ ከበሽታዋ እፎይታ ባገኘችበት ወቅት ለአንድ ወር በረዳት አቅኚነት ለማገልገል ጥሩ ጤንነት አግኝታ ነበር። ከዚያም ጤንነትዋ እያሽቆለቆለ ሄደ፤ ከጥቂት ወራት በኋላም ሞተች። ሆኖም በይሖዋ ላይ ያላትን እምነት ለትንሽ ጊዜም እንኳ ሳታጣ እስከ መጨረሻው ድረስ በመንፈሳዊ ጠንካራ ሆና ቀጥላለች። እናቷ እንዲህ ስትል ታስታውሳለች:- “እስከሞተችበት ዕለት ድረስ ይበልጥ ታስብ የነበረው ስለ ራሷ ሳይሆን ስለ ሌሎች ነበር። ለሰዎች ‘በገነት ውስጥ እንገናኛለን’ ብላ በመንገር መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ ታበረታታቸው ነበር።”

በይሖዋ ላይ እምነት እንዳለን ማሳየት

“ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደ ሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው።” (ያዕቆብ 2:​26) ያዕቆብ በአምላክ ስለ ማመን የተናገረው ነገር በአምላክ ላይ ስላለን ትምክህትም ሊነገር ይችላል። በአምላክ ላይ እምነት እንዳለን ብዙ ብናወራ፣ እምነታችንን በተግባር እስካልገለጽን ድረስ ትርጉም የለሽ ይሆናል። አብርሃም ሙሉ በሙሉ በይሖዋ የታመነ ሲሆን ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ ለማቅረብ ዝግጁ እስከመሆን ድረስ ምንም ሳያቅማማ የይሖዋን ትእዛዛት በማክበር እምነቱን አሳይቷል። አብርሃም ይህን የመሰለ የላቀ እምነትና ታዛዥነት በማሳየቱ የይሖዋ ወዳጅ ሊባል ችሏል።​—⁠ዕብራውያን 11:​8-10, 17-19፤ ያዕቆብ 2:​23

በይሖዋ ላይ እምነት እንዳለን ለማሳየት አንድ ዓይነት ከባድ ፈተና እስኪደርስብን ድረስ መጠበቅ አይኖርብንም። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ሲል ነግሯቸዋል:- “ከሁሉ በሚያንስ የታመነ በብዙ ደግሞ የታመነ ነው፣ ከሁሉ በሚያንስም የሚያምፅ በብዙ ደግሞ ዓመፀኛ ነው።” (ሉቃስ 16:​10) ቀላል መስለው በሚታዩ ጉዳዮች እንኳ ሳይቀር ይሖዋን በመታዘዝ በዕለታዊ እንቅስቃሴዎቻችን ሁሉ በእሱ መታመንን መማር ይገባናል። እንዲህ ዓይነቱ ታዛዥነት የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ስንገነዘብ በሰማያዊ አባታችን ላይ ያለን እምነት ከባድና ይበልጥ አዳጋች የሆኑ ፈተናዎችን ለመጋፈጥ በሚያስችል ሁኔታ ይጠናከራል።

ዓለም አውዳሚ ወደሆነው ፍጻሜው ሲቃረብ የይሖዋ ሕዝቦች ተጨማሪ ፈተናዎችና አደጋዎች እንደሚደርስባቸው የተረጋገጠ ነው። (ሥራ 14:​22፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​12) በአሁኑ ጊዜ በይሖዋ ላይ ጠንካራና ጽኑ እምነት በመገንባት ታላቁን መከራ በሕይወት ለማለፍ አሊያም ትንሣኤ አግኝተን ተስፋ ወደተሰጠን አዲስ ዓለም ለመግባት በጉጉት መጠባበቅ እንችላለን። (2 ጴጥሮስ 3:​13) በእኛ በኩል ማንኛውም ዓይነት እምነት ማጣት ከይሖዋ ጋር ያለንን ውድ ዝምድና እንዲያበላሽብን ፈጽሞ አንፍቀድ። እንዲህ ካደረግን ዳንኤል ከአንበሶቹ ጉድጓድ ከወጣ በኋላ የተነገረለት ነገር ለእኛም ሊባልልን ይችላል:- “በአምላኩም ታምኖ ነበርና አንዳች ጉዳት አልተገኘበትም።”​—⁠ዳንኤል 6:​23

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት የኅዳር 1, 1994 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 23-7⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እንደ ማርቲን ፖየትሲንገር ያሉ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮችን የሕይወት ታሪክ ማንበብ እምነት ያጠነክራል