በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?”

“እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?”

“እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?”

“እንግዲህ ስለዚህ ነገር ምን እንላለን? እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ይቃወመናል?”​—⁠ሮሜ 8:​31

1. ከእስራኤላውያን ጋር ግብፅን ለቅቀው የወጡት እነማን ናቸው? እንዲህ እንዲያደርጉ ያነሳሳቸውስ ምንድን ነው?

 እስራኤላውያን በግብጽ ከቆዩባቸው 215 ዓመታት ውስጥ አብዛኛውን በባርነት ካሳለፉ በኋላ ነፃ ሲወጡ ‘ብዙ ድብልቅ ሕዝብም ከእነርሱ ጋር ወጥቶ ነበር።’ (ዘጸአት 12:​38) እነዚህ እስራኤላውያን ያልሆኑ ሰዎች አሥር አስፈሪ መቅሰፍቶች የግብጽን ምድር ሲያወድሙና የሐሰት አማልክቶቻቸውን መሳለቂያ ሲያደርጓቸው ተመልክተዋል። በዚሁ ጊዜም በተለይ ከአራተኛው መቅሰፍት አንስቶ ይሖዋ ሕዝቡን ለመጠበቅ ያለውን ችሎታ ተመልክተዋል። (ዘጸአት 8:​23, 24) ስለ ይሖዋ ዓላማ የነበራቸው እውቀት ውስን ቢሆንም በአንድ ነገር ግን እርግጠኞች ነበሩ:- የግብፅ አማልክት ግብፃውያንን መጠበቅ ሲሳናቸው ይሖዋ ከእስራኤላውያን ጎን በመቆም ኃያል መሆኑን አስመስክሯል።

2. ረዓብ እስራኤላውያን ሰላዮቹን የደገፈቻቸው ለምንድን ነው? በእስራኤላውያኑ አምላክ ላይ ያሳደረችው ትምክህትስ ተገቢ የነበረው ለምንድን ነው?

2 ከአርባ ዓመት በኋላ ማለትም እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው ከጥቂት ጊዜ በፊት በሙሴ እግር የተተካው ኢያሱ ምድሪቱን እንዲሰልሉ ሁለት ሰዎች ላከ። እዚያም በኢያሪኮ የምትኖር ረዓብ የተባለች ሴት አገኙ። እስራኤላውያን ግብፅን ለቅቀው ከወጡበት ጊዜ አንስቶ በነበሩት 40 ዓመታት ይሖዋ እስራኤላውያንን ለመጠበቅ ስላከናወናቸው ኃያል ሥራዎች ከሰማቻቸው ነገሮች በመነሳት የአምላክን በረከት ለማግኘት ሕዝቡን መደገፍ እንዳለባት አውቃ ነበር። ጥበብ የተሞላበት ውሳኔ በማድረጓ ምክንያት ከጊዜ በኋላ እስራኤላውያን ከተማዋን በተቆጣጠሩበት ወቅት እርሷና ቤተሰቧ ከጥፋት ሊድኑ ችለዋል። እነርሱ ራሳቸው የዳኑበት ተአምራዊ መንገድ አምላክ ከእነርሱ ጋር እንደነበር የሚያረጋግጥ ግልጽ ማስረጃ ነበር። እንግዲያው ረዓብ በእስራኤል አምላክ ላይ ትምክህት ማሳደሯ ተገቢ ነበር።​—⁠ኢያሱ 2:​1, 9-13፤ 6:​15-17, 25

3. (ሀ) ኢየሱስ እንደገና በተገነባችው ኢያሪኮ ከተማ አቅራቢያ ምን ዓይነት ተአምር አከናወነ? የአይሁድ ካህናትስ ይህን በተመለከቱ ጊዜ ምን ተሰማቸው? (ለ) አንዳንድ አይሁዳውያንና ከጊዜ በኋላም አይሁድ ያልሆኑ ሌሎች በርካታ ሰዎች ምን ነገር ተገነዘቡ?

3 ከአሥራ አምስት መቶ ዘመን በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ እንደገና በተገነባችው የኢያሪኮ ከተማ አቅራቢያ አንድ ዓይነ ስውር ለማኝ ፈወሰ። (ማርቆስ 10:​46-52፤ ሉቃስ 18:​35-43) ይህ ሰው ምሕረት እንዲያሳየው ኢየሱስን በመለመን ኢየሱስ የአምላክ ድጋፍ እንዳለው መገንዘቡን አሳይቷል። በሌላ በኩል ግን የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎችና ተከታዮቻቸው ኢየሱስ ያከናወናቸው ተአምራት የአምላክን ሥራ እየሠራ እንዳለ የሚያረጋግጡ ማስረጃዎች መሆናቸውን አምነው ለመቀበል አሻፈረን ብለዋል። ከዚያ ይልቅ ይነቅፉት ነበር። (ማርቆስ 2:​15, 16፤ 3:​1-6፤ ሉቃስ 7:​31-35) ኢየሱስን ከገደሉት በኋላ ከሞት እንደተነሳ የሚያረጋግጥ ማስረጃ በቀረበላቸው ጊዜ እንኳን ይህ የአምላክ ሥራ እንደሆነ ለመቀበል ፈቃደኞች አልነበሩም። ከዚያ ይልቅ ‘የጌታን የኢየሱስን ወንጌል የመስበኩን’ ሥራ ለማስተጓጎል በማሰብ የኢየሱስን ተከታዮች በግንባር ቀደምትነት ማሳደዳቸውን ተያያዙት። ይሁን እንጂ አንዳንድ አይሁዳውያን ከጊዜ በኋላም አይሁድ ያልሆኑ ሌሎች በርካታ ሰዎች እነዚህን ነገሮች በመገንዘብ ትክክለኛ መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል። አምላክ እነዚህን ተመጻዳቂ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ትቶ ትሑት የሆኑትን የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች እየደገፈ እንዳለ ግልጽ ሆኖላቸው ነበር።​—⁠ሥራ 11:​19-21

በዛሬው ጊዜ የአምላክ ድጋፍ ያለው ማን ነው?

4, 5. (ሀ) ሃይማኖትን በመምረጥ ረገድ አንዳንድ ሰዎች ያላቸው አመለካከት ምንድን ነው? (ለ) እውነተኛውን ሃይማኖት ለይቶ በማወቅ ረገድ ወሳኝ የሆነው ጥያቄ የትኛው ነው?

4 እውነተኛ ሃይማኖትን አስመልክቶ በተነሳ ጥያቄ ላይ አንድ ቄስ በቅርቡ በቴሌቪዥን ተደርጎላቸው በነበረ ቃለ ምልልስ ላይ “እኔ አንድ ሃይማኖት ትክክለኛ ነው የምለው አባላቱን የተሻሉ ሰዎች እንዲሆኑ ከረዳቸው ነው” ሲሉ ተናግረዋል። እውነተኛ ሃይማኖት ሰዎችን ያሻሽላል ብሎ ማሰብ የሚጠበቅ ነገር ነው። ይሁን እንጂ አንድ ሃይማኖት ጥሩ ሰዎች ያሉት መሆኑ ብቻውን የአምላክ ድጋፍ እንዳለው ያረጋግጣል? አንድ ሃይማኖት እውነተኛ መሆኑን ለማወቅ የሚያስችለው መመዘኛ ይሄ ብቻ ነው?

5 ማንኛውም ሰው የሚከተለውን ሃይማኖት መምረጥን ጨምሮ የግል ምርጫ የማድረግ ችሎታውን ያደንቃል። ይሁን እንጂ አንድ ሰው የመምረጥ ነፃነት ያለው መሆኑ የሚያደርገው ምርጫ ሁሉ ትክክለኛ ይሆናል ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ሰዎች አንድን ሃይማኖት የሚመርጡት የተከታዮቹን ብዛት፣ ሃብቱን፣ ደማቅ ክብረ በዓላቱን ወይም የቤተሰብ ዝምድናቸውን በማሰብ ነው። ከእነዚህ ነገሮች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ አንድ ሃይማኖት እውነተኛ መሆን አለመሆኑን ለመወሰን አይረዱም። በዚህ ረገድ ወሳኝ የሆነው ጥያቄ:- ተከታዮቹ የአምላክን ፈቃድ እንዲያደርጉ በጥብቅ የሚያሳስበውና ተከታዮቹ “አምላክ ከእኛ ጋር ነው” ብለው በእርግጠኝነት መናገር ይችሉ ዘንድ መለኮታዊ ድጋፍ እንዳለው ጠንካራ ማስረጃ የሚያቀርበው ሃይማኖት የትኛው ነው? የሚለው ነው።

6. እውነተኛና ሐሰተኛ ሃይማኖትን በተመለከተ ብርሃን የሚፈነጥቁት ኢየሱስ የተናገራቸው የትኞቹ ቃላት ናቸው?

6 ኢየሱስ “የበግ ለምድ ለብሰው ከሚመጡባችሁ በውሥጣቸው ግን ነጣቂዎች ተኵላዎች ከሆኑ ከሐሰተኞች ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ” ብሎ በመናገር እውነተኛውን አምልኮ ከሐሰተኛው ለይቶ ለማወቅ የሚያስችል ደንብ አውጥቷል። (ማቴዎስ 7:​15, 16፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን፤ ሚልክያስ 3:​18) በአሁኑ ጊዜ መለኮታዊ ድጋፍ ያላቸው እነማን እንደሆኑ በግልጽ ለይተን ማወቅ እንችል ዘንድ አንዳንዶቹን የእውነተኛ ሃይማኖት ‘ፍሬዎች’ ወይም መለያ ምልክቶች እንመልከት።

የአምላክ ድጋፍ ያላቸው ሰዎች የሚታወቁባቸው ምልክቶች

7. በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ትምህርቶችን ብቻ ማስተማር ማለት ምን ማለት ነው?

7 ትምህርቶቻቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። ኢየሱስ እንዲህ አለ:- “ትምህርቴስ ከላከኝ ነው እንጂ ከእኔ አይደለም፤ ፈቃዱን ሊያደርግ የሚወድ ቢኖር፣ እርሱ ይህ ትምህርት ከእግዚአብሔር ቢሆን ወይም እኔ ከራሴ የምናገር ብሆን ያውቃል።” ጨምሮም “ከእግዚአብሔር የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 7:​16, 17፤ 8:​47) የአምላክን ድጋፍ ማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ አምላክ በቃሉ ውስጥ የገለጠውን ብቻ ማስተማርና በሰብዓዊ ጥበብ ወይም ወግ ላይ የተመሠረቱ ትምህርቶችን ማስወገድ ይገባቸዋል።​—⁠ኢሳይያስ 29:​13፤ ማቴዎስ 15:​3-9፤ ቆላስይስ 2:​8

8. የአምላክን ስም በአምልኮ መጠቀም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

8 ይሖዋ በሚለው የአምላክ ስም ይጠቀማሉ እንዲሁም ለሌሎች ያሳውቃሉ። ኢሳይያስ እንዲህ በማለት ተንብዮአል:- “በዚያም ቀን እንዲህ ትላላችሁ:- እግዚአብሔርን አመስግኑ፣ ስሙንም ጥሩ፤ በአሕዛብ መካከል ሥራውን አስታውቁ፤ ስሙ ከፍ ያለ እንደ ሆነ ተናገሩ። ታላቅ ሥራ ሠርቶአልና ለእግዚአብሔር ተቀኙ፤ ይህንም በምድር ሁሉ ላይ አስታውቁ።” (ኢሳይያስ 12:​4, 5) ኢየሱስ ተከታዮቹ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:​9) ስለዚህ አይሁዳዊም ሆኑ አይሁዳዊ ያልሆኑ ክርስቲያኖች ‘ለአምላክ ስም የተለዩ ወገኖች’ ሆነው ማገልገል ነበረባቸው። (ሥራ 15:​14) አምላክ ‘ለስሙ የተለዩ ወገኖች’ በመሆናቸው የሚኮሩትን ሰዎች መደገፍ እንደሚያስደስተው የታወቀ ነው።

9. (ሀ) ደስታ የእውነተኛ ሃይማኖት ተከታዮች መለያ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) ኢሳይያስ እውነተኛ ሃይማኖትን ከሐሰተኛ ጋር በማወዳደር የተናገረው እንዴት ነው?

9 እንደ አምላክ እነርሱም የደስተኝነትን ባሕርይ ያንጸባርቃሉ። ‘የምሥራች’ ምንጭ እንደመሆኑ መጠን ይሖዋ “ደስተኛ አምላክ” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 1:​11 NW ) ታዲያ አምላኪዎቹ እንዴት ደስታ የራቃቸው ወይም ተስፋ ቢስ ሊሆኑ ይችላሉ? ዓለም የሚፈጥረው ጭንቀትም ሆነ በግል ችግሮች ቢኖሩባቸውም እውነተኛ ክርስቲያኖች ዘወትር የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ስለሚያገኙ ደስታቸውን ጠብቀው ይኖራሉ። ኢሳይያስ እነዚህን ሰዎች የሐሰት ሃይማኖት ከሚከተሉ ሰዎች ጋር በማወዳደር ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል:- እነሆ፣ ባሪያዎቼ ይበላሉ እናንተ ግን ትራባላችሁ፤ እነሆ፣ ባሪያዎቼ ይጠጣሉ እናንተ ግን ትጠማላችሁ፤ እነሆ፣ ባሪያዎቼ ደስ ይላቸዋል እናንተ ግን ታፍራላችሁ፤ እነሆ፣ ባሪያዎቼ ከልባቸው ደስታ የተነሣ ይዘምራሉ፣ እናንተ ግን ከልባችሁ ኀዘን የተነሣ ትጮኻላችሁ፣ መንፈሳችሁም ስለ ተሰበረ ወዮ ትላላችሁ።”​—⁠ኢሳይያስ 65:​13, 14

10. እውነተኛውን ሃይማኖት የሚከተሉ ሰዎች ነገሮችን በራሳቸው ጥረት ብቻ ለመማር ከመሞከር የሚድኑት እንዴት ነው?

10 አኗኗራቸውና የሚያደርጓቸው ውሳኔዎች የተመሠረቱት በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ነው። የምሳሌ ጸሐፊ እንዲህ በማለት ይመክረናል:- “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፣ በራስህም ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን እወቅ፣ እርሱም ጎዳናህን ያቀናልሃል።” (ምሳሌ 3:​5, 6) አምላክ የሚደግፈው መመሪያ ለማግኘት ወደ እርሱ ዘወር የሚሉትን እንጂ ለአምላካዊ ጥበብ ጀርባቸውን የሰጡ ሰዎች በሚሰብኩት እርስ በርሱ የማይጣጣም ሰብዓዊ ጥበብ ላይ የሚታመኑትን አይደለም። አንድ ሰው አኗኗሩን ከአምላክ ቃል ጋር ለማስማማት ፈቃደኛ በሆነ መጠን ነገሮችን በራሱ ጥረት ብቻ ለመማር ከመሞከር ይድናል።​—⁠መዝሙር 119:​33፤ 1 ቆሮንቶስ 1:​19-21

11. (ሀ) የእውነተኛ ሃይማኖት ተከታዮች ቀሳውስትና ምዕመናን በሚል የማይከፋፈሉት ለምንድን ነው? (ለ) በአምላክ ሕዝብ መካከል ግንባር ቀደም ሆነው የሚያገለግሉት ለመንጋው ምን ዓይነት ምሳሌ ይተዋሉ?

11 የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያን ጉባኤ በተደራጀበት መንገድ ተደራጅተዋል። ኢየሱስ የሚከተለውን መሠረታዊ ሥርዓት ተናግሯል:- “መምህር ተብላችሁ አትጠሩ፤ መምህራችሁ አንድ ስለ ሆነ እናንተም ሁላችሁ ወንድማማች ናችሁ። አባታችሁ አንዱ እርሱም የሰማዩ ነውና በምድር ላይ ማንንም:- አባት ብላችሁ አትጥሩ። ሊቃችሁ አንድ እርሱም ክርስቶስ ነውና:- ሊቃውንት ተብላችሁ አትጠሩ።” (ማቴዎስ 23:​8-11) ወንድማማች የሆኑ ሰዎች የተሰባሰቡበት ጉባኤ ራሱን በማዕረግ ስም የሚያቆላምጥና ከምዕመናኑ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ የቀሳውስት ቡድን እንዲኖር አይፈቅድም። (ኢዮብ 32:​21, 22) የአምላክን መንጋ በእረኝነት የሚጠብቁ ሁሉ “እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ ሳይሆን፣ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘት ሳይሆን ጐብኙት፤ ለመንጋው ምሳሌ ሁኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ” ተብለው ተመክረዋል። (1 ጴጥሮስ 5:​2, 3) እውነተኛ ክርስቲያን እረኞች በሌሎች እምነት ላይ ራሳቸውን አለቃ ከማድረግ ይቆጠባሉ። በአምላክ አገልግሎት አብረው የሚሠሩ እንደመሆናቸው ጥሩ ምሳሌ ሆነው ለመገኘት ይጥራሉ።​—⁠2 ቆሮንቶስ 1:​24

12. አምላክ የእርሱን ድጋፍ ለማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች ሰብዓዊ መስተዳደርን በተመለከተ ምን ዓይነት ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖራቸው ይፈልጋል?

12 ለሰብዓዊ መስተዳድሮች የሚገዙ ቢሆንም ገለልተኞች ናቸው። ‘በበላይ ላሉት ባለ ሥልጣናት ለመገዛት’ አሻፈረኝ የሚል የአምላክን ድጋፍ አገኛለሁ ብሎ ሊጠብቅ አይችልም። ለምን? ምክንያቱም “ያሉትም ባለ ሥልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። ስለዚህ ባለ ሥልጣንን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል።” (ሮሜ 13:​1, 2) ይሁን እንጂ ኢየሱስ የሁለቱ ፍላጎቶች ሊጋጩ እንደሚችሉ ያውቅ ስለነበር “የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርንም ለእግዚአብሔር አስረክቡ” በማለት ተናግሯል። (ማርቆስ 12:​17) የአምላክን ድጋፍ ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ አምላክ ከሚጠብቅባቸው ከፍተኛ ኃላፊነቶች ጋር የማይጋጩትን የሚኖሩበትን አገር ሕግ እየታዘዙ ‘የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን በአንደኛ ደረጃ መፈለጋቸውን’ ሊቀጥሉ ይገባል። (ማቴዎስ 6:​33፤ ሥራ 5:​29) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም” ብሎ በመናገር የገለልተኝነትን አቋም ጠበቅ አድርጎ ገልጿል። በሌላ ጊዜም “መንግሥቴ ከዚህ አይደለችም” በማለት ጨምሮ ተናግሯል።​—⁠ዮሐንስ 17:​16፤ 18:​36

13. የአምላክን ሕዝቦች ለይቶ በማሳወቅ ረገድ ፍቅር ምን ሚና ይጫወታል?

13 ‘ለሰው ሁሉ መልካም በማድረግ’ ረገድ አያዳሉም። (ገላትያ 6:​10) ክርስቲያናዊ ፍቅር ከአድሎ ነፃ ነው። የሰዎች የቆዳ ቀለም፣ የኢኮኖሚ ሁኔታ ወይም የትምህርት ደረጃ፣ ዜግነት ወይም ቋንቋ ምንም ዓይነት ቢሆን ሁሉንም ሰው ይቀበላል። ለሰው ሁሉ በተለይ ደግሞ በእምነት ለሚዛመዷቸው ሰዎች የሚያደርጓቸው በጎ ነገሮች የአምላክ ድጋፍ ያላቸው ሰዎች መሆናቸውን ይጠቁማል። ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” በማለት ተናግሯል።​—⁠ዮሐንስ 13:​35፤ ሥራ 10:​34, 35

14. የአምላክን ድጋፍ ያገኙ ሰዎች በሁሉም ዘንድ ተቀባይነት ያገኛሉ ማለት ነውን? አብራራ።

14 የአምላክን ፈቃድ በማድረጋቸው ምክንያት የሚደርስባቸውን ስደት ለመቀበል ፈቃደኞች ናቸው። ኢየሱስ “እኔን አሳደውኝ እንደ ሆኑ እናንተን ደግሞ ያሳድዱአችኋል፤ ቃሌን ጠብቀው እንደ ሆኑ ቃላችሁን ደግሞ ይጠብቃሉ” በማለት ለተከታዮቹ አስቀድሞ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። (ዮሐንስ 15:​20፤ ማቴዎስ 5:​11, 12፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:​12) ዓለምን በእምነቱ በኮነነው በኖኅ ላይ እንደደረሰው የአምላክ ድጋፍ ያላቸው ሰዎች ሁሌም በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አግኝተው አልኖሩም። (ዕብራውያን 11:​7) በዛሬው ጊዜ የአምላክን ድጋፍ ለማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ ስደት እንዳይደርስባቸው ሲሉ የአምላክን ቃል ለማለዘብ ወይም አምላክ ያወጣቸውን መሠረታዊ ሥርዓቶች ለመጣስ አይዳዳቸውም። አምላክን በታማኝነት እስካገለገሉ ድረስ ሰዎች ‘እየተሳደቡ እንደሚደነቁባቸው’ ያውቃሉ።​—⁠1 ጴጥሮስ 2:​12፤ 3:​16፤ 4:​4

ሐቁን ለማገናዘብ ጊዜው አሁን ነው

15, 16. (ሀ) የአምላክ ድጋፍ ያለውን የሃይማኖት ቡድን ለይተን እንድናውቅ የትኞቹ ጥያቄዎች ይረዱናል? (ለ) በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ምን መደምደሚያ ላይ ደርሰዋል? ለምንስ?

15 ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ:- ‘የሚያስተምራቸው ትምህርቶች ብዙሃኑ ከሚያምንበት የተለየ ቢሆኑም እንኳ የአምላክን ቃል አጥብቆ በመከተል ረገድ ጥሩ ስም ያተረፈው ሃይማኖት የትኛው ነው? በአምላክ የግል ስም መጠቀም አስፈላጊ እንደሆነ አጥብቀው የሚናገሩ አልፎ ተርፎም ራሳቸውን በስሙ የሚጠሩት እነማን ናቸው? ለሰው ልጆች ችግሮች በሙሉ ብቸኛው መፍትሔ የአምላክ መንግሥት እንደሆነ በእርግጠኝነት የሚናገሩት እነማን ናቸው? ዘመን ያለፈባቸው እንደሆኑ ተደርገው ሊቆጠሩ ቢችሉም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የሥነ ምግባር የአቋም ደረጃ የሚጠብቁት እነማን ናቸው? የሚከፈለው የቀሳውስት ቡድን ሳይኖረው ሁሉም አባላቱ ሰባኪ የሆኑበት ቡድን የትኛው ነው? በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ እጃቸውን ባያስገቡም ሕግ አክባሪ ዜጎች በመሆናቸው ምክንያት የሚመሰገኑት እነማን ናቸው? ሰዎች ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ እንዲማሩ ለመርዳት ሲሉ ጊዜያቸውንና ገንዘባቸውን በፍቅር የሚለግሱት እነማን ናቸው? እንደዚህ ያሉ የሚያስመሰግኑ ሥራዎችን እየሠሩም ንቀት፣ ፌዝና ስደት የሚደርስባቸው እነማን ናቸው?’

16 በዓለም ዙሪያ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እውነታውን ካገናዘቡ በኋላ እውነተኛውን ሃይማኖት የሚያራምዱት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ እንደሆኑ አምነው ተቀብለዋል። እዚህ መደምደሚያ ላይ የደረሱት የይሖዋ ምሥክሮች የሚያስተምሯቸውን ትምህርቶችና አኗኗራቸውን እንዲሁም ሃይማኖታቸው ያስገኘላቸውን ጥቅሞች መሠረት በማድረግ ነው። (ኢሳይያስ 48:​17) በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በዘካርያስ 8:​23 ላይ እንደተተነበየው “እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር እንዳለ ሰምተናልና ከእናንተ ጋር እንሂድ” እያሉ ናቸው ማለት ይቻላል።

17. የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛው ሃይማኖት የእነርሱ ብቻ እንደሆነ መናገራቸው የሚያስወቅስ ያልሆነው ለምንድን ነው?

17 የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ ድጋፍ ያላቸው እነርሱ ብቻ እንደሆኑ መናገራቸው ያስወቅሳቸዋልን? በመሠረቱ ይህ አቋማቸው ግብፃውያን የራሳቸው እምነት ቢኖራቸውም እንኳ የአምላክ ድጋፍ ያላቸው እነርሱ ብቻ እንደነበሩ ከተናገሩት በግብፅ ከነበሩት እስራኤላውያን ወይም አምላክ እነርሱን እንጂ የአይሁድ ሃይማኖትን እንደማይደግፍ ከተናገሩት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከነበሩት ክርስቲያኖች የተለየ አይደለም። ከዚህ ሌላ ማስረጃ አያሻም። ኢየሱስ “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፣ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል” በማለት በመጨረሻው ዘመን ተከታዮቹ እንደሚሠሩት አስቀድሞ በትንቢት የተናገረውን ሥራ የይሖዋ ምሥክሮች በ235 አገሮች በማከናወን ላይ ይገኛሉ።​—⁠ማቴዎስ 24:​14

18, 19. (ሀ) የይሖዋ ምሥክሮች ተቃውሞ የሚደርስባቸው ቢሆንም እንኳ የስብከት ሥራቸውን ከማከናወን ወደኋላ ማለት የማይኖርባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ምሥክሮቹ የይሖዋ ድጋፍ እንዳላቸው መዝሙር 41:​11 ማረጋገጫ የሚሰጠው እንዴት ነው?

18 የይሖዋ ምሥክሮች ስደት ወይም ተቃውሞ የሚያከናውኑትን እንቅስቃሴ እንዲያስቆምባቸው ፈጽሞ ባለመፍቀድ ይህን ተልዕኮ መወጣታቸውን ይቀጥላሉ። የይሖዋ ሥራ የግድ መሠራቱ አይቀርም፤ ደግሞም ይሠራል። ይሖዋ “በአንቺ ላይ የተሠራ መሣሪያ ሁሉ አይከናወንም፤ በፍርድም በሚነሣብሽ ምላስ ሁሉ ትፈርጂበታለሽ። የእግዚአብሔር ባሪያዎች ርስት ይህ ነው፣ ጽድቃቸውም ከእኔ ዘንድ ነው” በማለት ቃል የገባ በመሆኑ ባለፈው መቶ ዘመን ምሥክሮቹ የሚያከናውኑትን የአምላክ ሥራ ለማስተጓጎል የተደረጉት ጥረቶች ሁሉ ውለው አድረገው ከሽፈዋል።​—⁠ኢሳይያስ 54:​17

19 የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ ተቃውሞ እየደረሰባቸው ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ጥንካሬ እያገኙ መሄዳቸውና ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በስፋት መንቀሳቀሳቸው ሥራቸው በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው የሚያሳይ ማረጋገጫ ነው። ንጉሥ ዳዊት እንዲህ ብሏል:- “ጠላቴ እልል አይልብኝምና ስለዚህ እንደ ወደድኸኝ አወቅሁ።” (መዝሙር 41:​11፤ 56:​9, 11) መሪያቸው ኢየሱስ ክርስቶስ የመጨረሻውን ድል ለመቀዳጀት ወደፊት በመገስገስ ላይ በመሆኑ የአምላክ ጠላቶች የይሖዋን ሕዝቦች በማሸነፍ ፈጽሞ እልል ሊሉ አይችሉም።

መመለስ ትችላለህ?

• የአምላክ ድጋፍ የነበራቸው አንዳንድ ጥንታዊ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?

• እውነተኛውን ሃይማኖት ለይቶ ለማወቅ የሚያስችሉ አንዳንድ ምልክቶች ምንድን ናቸው?

• አንተ በግልህ የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክ ድጋፍ አላቸው ብለህ እንድታምን የሚያደርግህ ነገር ምንድን ነው?

[የአንቀጾቹ ጥያቄዎች]

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክን ድጋፍ ማግኘት የሚፈልጉ ሁሉ ትምህርቶቻቸው ሙሉ በሙሉ በቃሉ ላይ የተመሠረቱ እንዲሆኑ ማድረግ ይኖርባቸዋል

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ክርስቲያን ሽማግሌዎች ለመንጋው ምሳሌ ሆነው ያገለግላሉ